*ሕዝብ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ተማፅኖ ቀርቧል
*የጋዜጣው ዋና አዘጋጅና ስራ አስኪያጅ በእስር ላይ ናቸው
በዘሪሁን ሙሉጌታ
ባለፈው ዕረቡ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮምህዳር ጋዜጣ ላይ ያቀረበውን የ300ሺህ ብር የስም ማጥፋት ክስ ለመከታተል ወደ ሐዋሳ አቅንተው ጉዳያቸው ከተከታተሉ በኋላ ለስራ በከተማዋ በባጃጅ ሲንቀሳቀሱ በሞተር ሳይክል አደጋ ከደረሰባቸው የኢትዮ ምህዳር ጋዜጠኞች አንዱ ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ የሕክምና እርዳታ ቢደረግለትም ጤናው መሻሻል ባለማሳየቱ ሕይወቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ ነው።
ጋዜጠኛ ኤፍሬም አደጋው በደረሰበት ወቅት አንገቱ አካባቢ አከርካሪው ላይ በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት አጥንቱ በመሰበሩና ነርቩን በመነካቱ ሁለቱን እግሮቹን ማንቀሳቀስ ተስኖት ነበር። ነገር ግን በኮሪያ ሆስፒታል በተደረገለት ሰዓታትን የፈጀ ቀዶ ጥገና ጤናው መጠነኛ መሻሻል ቢያሳይም በገጠመው የአተነፋፈስ ችግር ባለፈው ቅዳሜ አመሻሽ ላይ በድጋሚ ቀዶ ጥገና ተደርጎለታል። ከዚህ ቀዶ ጥገና በኋላም በራሱ መተንፈስ ባለመቻሉ በመሳሪያ ኃይል በመተንፈስ ላይ ነው። ከቅዳሜ ዕለት ጀምሮም ከፍተኛ ክትትል በሚደረግበት ሪከቨሪ ክፍል ውስጥ ይገኛል። የአተነፋፈስ ሁኔታው እስከሚሻሻል ድረስም በሪከቨሪው ውስጥ እንደሚቆይም ለማወቅ ተችሏል።
ጋዜጠኛ ኤፍሬም ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ከተመረቀ በኋላ በነጋድራስ ጋዜጣ ላይ በሪፖርተርነት በሌሎች ተቋም በሕዝብ ግንኙነት መስራት ከጀመረ ጥቂት አመታትን ያስቆጠረ ወጣት ጋዜጠኛ ነው። ቤተሰቦቹም ሆኑ የሚሰራበት ተቋም ገና አዲስ በመሆናቸው ለህክምና የሚሆን የገንዘብ እጥረት ገጥሞታል።
በጋዜጠኛ ኤፍሬም ላይ ጉዳቱ እንደደረሰ የሰሙት በተለያዩ ጋዜጦች የሚሰሩ ጋዜጠኞች ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አድማስ ቢሮ በመሰባሰብ ምን እናድርግ ሲሉ ከተወያዩ በኋላ አምስት አባላት ያሉበት ኮሚቴ አቋቁመው ልጁ በሕክምና ተረድቶ የሚድንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የእርዳታ ማሰባሰቢያ የሚሆን የባንክ ሂሳብ ከፍተዋል።
ሆኖም ከልጁ የሕክምና ውስብስብነትና ከደረሰው አደጋ ከፍተኛነት የተነሳ ለህክምና እየተጠየቀ ያለው ገንዘብ አሁን ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 130ሺ ብር መድረሱን የኮሚቴው አባል የሆነው ጋዜጠኛ ብዙአየው ወንድሙ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልጿል።
ጋዜጠኛ ኤፍሬም ያለበት አሳሳቢ ሁኔታና የሕክምና ገንዘብ እጥረት እንደገና ለመፍታት የተቋቋመው ኮሚቴ ነገ በስምንት ሰዓት በጉዳዩ ላይ መግለጫ እንደሚሰጥም ታውቋል። እስካሁን ለህክምና እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተስፋ አስቆራጭ ባይሆንም ከህክምናው ወጪ መናር ምናልባትም ውጪ ሄዶ የሚታከምበትን አማራጭ በመፈለግ በህትመት ዘርፍ ካሉት ጋዜጠኞች በተጨማሪ በኤሌክትሮኒክስ ዘርፍ ያሉ ጋዜጠኞችንም በማሰባሰብ ጥረቱ እንዲሳካ ለማድረግ ኮሚቴው ጥረት እያደረገ መሆኑን ጋዜጠኛ ብዙአየሁ ጨምሮ ገልጿል።
ወጣቱን ጋዜጠኛ ለመታደግ ባለሀብቶች ማህበራት እና በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እገዛ እንዲያደርጉም በዚሁ አጋጣሚ ኮሚቴው ተማጽኗል። በቀጣይ ጋዜጠኞች ላይ የሚደርስን ድንገተኛ አደጋ ለመከላከልና ከደረሰም በኋላ በገንዘብ እጥረት በጋዜጠኞች ላይ የሚደርስን ችግር ለመፍታት ኮሚቴው እንደሚሰራ ለጊዜው ግን የጋዜጠኛ ኤፍሬምን ሕይወት ለመታደግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ኮሚቴው አስታውቋል። በዚህ ሂደትም በቅርቡ የተቋቋመው የአሳታሚዎች ማህበርም የልጁን ህይወት ለመታደግ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑም ታውቋል።
በተያያዘ ከሐዋሳ በመኪና አደጋ የተረፉት የጋዜጣው ስራአስኪያጅና ጋዜጠኛ ሚሊዮን ደግነው እና የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ በለገጣፎ ከተማ በእስር ላይ ናቸው።
ከለገጣፎ ከተማ ጋር በተያያዘ በሰሩት ዜና ባለፈው ቅዳሜ የለገጣፎ ፖሊሶች በጋዜጣው ጽ/ቤት በመገኘት በመጀመሪያ የጋዜጣውን ስራአስኪያጅና ፀሐፊዎች ይዘው የሄዱ ሲሆን ፀሐፊዎቹን ከተለቀቁ በኋላ ስራአስኪያጁ ከቅዳሜ ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል። በተመሳሳይ በአጋጣሚ በወቅቱ በጋዜጣው ቢሮ ያልነበረው ጋዜጠኛ ጌታቸው ለዚህ ሳምንት ጋዜጣ እንዲታተም ካደረገ በኋላ ከሰኞ ዕለት ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል። ጋዜጠኞቹ በህጋዊ መጥሪያ አለመያዛቸውና በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸው እያነጋገረ ይገኛል።
No comments:
Post a Comment