በዘሪሁን ሙሉጌታ
በትግራይ ክልል እየተንቀሳቀሰ ያለውና በቅርቡም ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ ነባር አመራሮቹን በአዳዲስ የተካው የአረና ትግራይ በዲሞክራሲና በሉአላዊነት (አረና) ፓርቲ ለአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የውህደት ጥያቄ ማቅረቡ ታወቀ።
ፓርቲው በቅርቡ መቀሌ ላይ ባካሄደው ጉባኤ ዋነኛ አጀንዳ የነበረው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መዋሃድን እንደ ቀዳሚ አጀንዳ በማንሳት በጉዳዩም ላይ በመወያየት ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም። በዚሁ መነሻ ቀደም ሲል መድረክ ከግንባር አደረጃጀት በላቀ መንገድ እንዲዋሃድ ከሚያደርገው ግፊት በተጨማሪ ከአንድነት ፓርቲ ጋር ለማዋሃድ በግልፅ ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል።
ፓርቲው የውህደት ጥያቄውን ለአንድነት ማቅረቡን ያረጋገጡት የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ በረኸ ናቸው። እንደሳቸውም አጭር ገለፃ ፓርቲው በቅርቡ ባካሄደው ጉባኤ መነሻ በማድረግ የውህደት ጥቄው ቀርቧል፤ መልሱንም እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአንድነት ፓርቲ የጽ/ቤት ጉዳይ ኃላፊ አቶ አስራት ጣሴ በበኩላቸው አረና ለአንድነት ፓርቲ የውህደት ጥያቄ ማቅረቡን አረጋግጠዋል። ም/ቤቱ በጉዳዩ ላይ እንደሚወያይበት ታውቋል። በቅርቡ የአንድነት ፓርቲ በሚያካሂደው “ስትራቴጂካዊ ጠቅላላ ጉባኤ” ጉዳዩ ቀርቦ ውሳኔ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አንድነትና መኢአድም በተመሳሳይ ለመዋሃድ አስር አባላት ያሉበት ኮሚቴ አቋቁመው እየመከሩ መሆኑም አይዘነጋም።
No comments:
Post a Comment