በፀጋው መላኩ
በልደታ አካባቢ የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚኒየም) የደረሳቸው የቤት ባለቤቶች ከመሰረተ ልማት አለመሟላት ጋር በተያያዘ በቤቶቹ መጠቀም አልቻሉም። የቤቶቹ ግንባታ መጠናቀቁ ተገልፆ ባለፈው ግንቦት ወር 2005 በሰፊ የሚዲያ ሽፋን ለባለእድለኞቹ ቁልፍ ቢሰጥም እስከዛሬም ድረስ አካባቢው ውሃና መብራት መሰል መሠረተ ልማቶች ያልተሟሉለት መሆኑን ከቤቶቹ ባለቤቶች መካከል አንዳንዶቹ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልጸዋል። በዚሁ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት ከአካባቢው የቤቶች ባለቤቶች ተወካይ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ መስፍን መንግስቱ የቤቶቹን ቁልፍ ከተረከቡ በኋላ ነዋሪዎቹ በቤቶቹ ለመጠቀም ጥረት ቢያደርጉም ውሃና መብራት አለመለቀቁ እንቅፋት የሆነባቸው መሆኑን አመልክተዋል። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንዶቹ ቤቶች የውስጥ መብራት፣ የባኞና የሽንት ቤት ቁሶችም ያልተሟላላቸው መሆኑ ታውቋል። የቤቶቹ ባለቤቶች የውሃ ቆጣሪ እንዲተከልላቸውና ውሃም እንዲለቀቅላቸው ከውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ጋር ውል ቢፈራረሙም እስከ ዛሬ ድረስ ተግባራዊ አለመሆኑን ገልጸውልናል።
መብራትንም በተመለከተ መስመሩ ቢዘረጋም ነዋሪዎቹ ቆጣሪ ለመረከብ ገና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ጋር ገና ውል በመፈፀም ላይ ናቸው። ቆጣሪ መተከሉ ግን ኤሌክትሪክ ለመለቀቁ ዋስትና አለመሆኑን የገለፁት የቤቶቹ ባለቤቶች ኤሌክትሪክም ሆነ ውሃ አለመለቀቁ የቤቶቹ የማጠናቀቂያ (Finishing) ሥራ በማከናወን ለመግባት ወይም ለማከራየት እንዳይችሉ ያደረጋቸው መሆኑን አመልክተዋል። አንዳንዶቹ ነዋሪዎች ውሃ በጀሪካን በማመላለስና በጀኔሬተር በመጠቀም የብየዳ ሥራ በማከናወን የማጠናቀቂያ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን ተመልክተናል።
አንድ የቀበሌ ቤት ነዋሪ የኮንዶሚኒየም ቤት ከደረሰው ቤቱን በኋላ ማስረከብ የሚጠበቅበት ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘም አንዳንድ የቀበሌ ቤት ነዋሪዎች በሚኖሩበት ቀበሌ የተከራዩትን ቤት እንዲለቁ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ባለፈ እንዲወጡ በመደረጋቸው መሰረተ ልማት ባልተሟላበት ሁኔታ ወደ ኮንዶሚኒየም ቤቶቹ ለመግባት ተገደዋል። ይሁንና በተለይ የውሃ አለመኖር በሽንት ቤት አጠቃቀም ላይ ችግር የፈጠረባቸው መሆኑን ነዋሪዎቹ ጨምረው ገልጸዋል።
ከቤቶች ኤጀንሲ በመወከል የልደታ ኮንዶሚኒየምን ቀሪ ስራዎች ተከታትለው እንዲያስፈፅሙ ኃላፊነት የተሰጣቸውና ስሜ አይጠቀስ ያሉ ኃላፊ፤ ለኤሌክትሪክ ኃይል አለመለቀቅ ዋነኛው ምክንያት ቀደም ሲል የተዘረጋው የኤሌክትሪክ መስመር የዲዛይን ለውጥ ስለተደረገበት እሱን ለማስተካከል በተደረገ ጥረት ጊዜ በመውሰዱ መሆኑን ገልጸውልናል። ከዚህ ውጪም ነዋሪዎቹን በፍጥነት ለማስተናገድ እያንዳንዱ የቤት ባለቤት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ጋር የደንበኝነት ውል በመፈራረም ቆጣሪ እንዲረከብ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። የልደታ ሳይት 51 ብሎኮች ያሉት መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው፤ ከአንድ እስከ አስራዘጠኝ ያሉት ብሎኮች ነዋሪዎች ውል የፈፀሙ ሲሆን በቀጣይም ሌሎቹ ውል እንዲፈፅሙ ከተደረገ በኋላ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል። ውሃን በተመለከተም አንዳንድ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ጨረታ የወጣ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፤ በአንዳንድ ብሎኮች ላይም ሮቶ የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖችንም የመስቀል ስራም እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ከመሰረተ ልማቶቹ አለመሟላት ጋር በተያያዘ ማብራሪያ እንዲሰጡን በስልክ ያገኘናቸው የቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ካሳ ወልደሰንበት ኤጀንሲው የኢትዮጵያ ኤሌክሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለቤቶቹ ኤሌክትሪክ ኃይል እንዲለቅ ክፍያ የፈፀመ መሆኑን በመግለፅ ተጨማሪ መረጃዎችን ለመስጠት አንድ ቀን በኋላ እንድንደውል በነገሩን መሰረት ብንደውልላቸውም ልናገኛቸው አልቻልንም። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኩል ስለሁኔታው አጠር ያለ ማብራሪያ የሰጡን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ምስክር ነጋሽ መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት በማንኛውም ሁኔታ ለሚገነቡ የጤና፣ የትምህርት፣ የጋራ መኖሪያቤቶች እንዲሁም ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ኤሌክትሪክ ለመስጠት ኮርፖሬሽኑ ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የዛሬ ዓመት 50ሺ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ የተደረገ መሆኑን ያመለከቱት የህዝብ ግንኑነት ኃላፊው፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የተሰጠውን ኃላፊነት ከመወጣት ባለፈ ለቤቶቹ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የቴክኒክ ድጋፍ ሳይቀር እየሰጠ መሆኑን አመልክተዋል። በዚህ በኩል ለኮርፖሬሽን መስሪያቤቱ ክፍያ ተፈፅሞ ዘገየ የሚባል ሥራ ካለም ኮርፖሬሽኑ ፊት ለፊት ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኮንዶሚኒየም ቤት እድለኞች ቁልፍ ካስረከበ በኋላ ከመሰረተ ልማት አለመሟላት ጋር በተያያዘ መሰል ችግር ሲፈጠር ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ነዋሪዎች እጣ ከወጣላቸው በኋላ ቁልፉን ከተረከቡበት ጀምሮ ከክፍያ ነፃ የሚሆኑበት ወደ አንድ ዓመት የሚጠጋ ጊዜ ቢኖራቸውም ብዙው ጊዜ የሚባክነው ከዚሁ መሰረተ ልማት ግንባታ መዘግየት ጋር በተያያዘ ነው።
No comments:
Post a Comment