Saturday, October 5, 2013

“ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነዉ”

 መልስ ለአቶ መስፍን አብርሃ “
መርዓዊ አና መንታ መንገዳቸዉ” በሚል ለተጻፈዉ እንደሚከተለዉ አቁዋሜን በተቃዉሞ መልክ አቀርባለሁ። በመጀመሪያ ስለራሴ ባጭሩ ልግለጽ፣ እኔ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመን እና ባለፉት 30 ዓመታት ዉስጥ በኮሎኝ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተሳላሚ ስሆን በዚሁ ቤተ ክርስቲያን 3 ልጆቼን እና የልጅ ልጅ ክርስትና አስነስቼያለሁ። በዚህ ጊዜ ውስጥም በሰበካ ጉባኤ አስተዳደር አባልነት ለተወሰኑ ጊዜያት አገልግያለሁ።
ዛሬም የቤተ ክርስቲያኒቱ ተገልጋይ ነኝ። ይህን የምገልጸዉም ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያለኝን ቅርበት ለማመልከት እና ሊቀ ካህናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀን ለ 30 ዓመታት አብሮ በመጓዝ የሥራቸውን ሂደት እንዲሁም ጥረታቸዉን ስላየሁ በተለይም ለመንፈሳዊ አባትነታቸዉ በቂ ምስክርነት እንደምሰጥ በማመን ነው። እርማቶች 1. አቶ መስፍን፣ አባታችን ሊቀ ካህናት እርሶ እንደሚያስቡት የኮሎኝ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል አስተዳዳሪ ብቻ ሳይሆኑ በጀርመን ላሉ አብያተ ክርስቲያናት በመሥራችነትና በመሪነት (በ ኤፋዉ ሕግ መሰረት) ከዛም በላይ በአባትነት የሚያስተዳድሩ ሊቀካህናት ናቸዉ። ይሄ በጥሞና እንዲታወቅልኝ!!! 2. የሰላማ መጽሔትን በተመለከተ በማንኛውም ጊዜ አባታችን ሊቀካህናት እኛን ምመናንንና አብረዋቸው በተለያዩ ከተሞች የሚያገለግሎትን ቀሳውስት የጽሑፍ ተሳትፎ እንዲኖረን እና አስያየታችንን እንድንጽፍ ሳያሳስቡና ሳይለምኑን የቀሩበት ጊዜ የለም። በዚህ ዓመትም የተደረገዉ ይኸዉ ነዉ። የተሳትፎ ጥሪዉ አልደረሰኝም የሚል አባት ካለ እኛም ብንሰማዉ መልካም ነበር። ሆኖም ግን ይህ የ30ኛ ዓመት ልዩ እትም የተሳትፎ ጉድለት ኖሮትም በአብዛኛዉ ግሩምና ቤተ ክርስቲያኒቱን አቋቁሞ ከዚህ ለማድረስ የተደረገዉን በታሪክነት ለማቆየት በተጨማሪም የተከናወነዉን ለማሳየት፣ የተሞከረ እና ለምእመናን ብዙ የ መንፈሳዊ ትምህርትን በተመለከተ ፍሬነገር ያዘለ ቀጥሎም ስለህብረተሰባዊ ኑሮ ትምህርት የሚያንፀባርቅ ከዚህም በላይ ለአዲሱ ትውልድ ጥሩ የግብረገብነትን መመሬያ የሚሰጥ መጽሔት መልሶ በነቀፌታ መቅረብ የለበትም እላለሁ። «ነገርን ከስሩ ዉሃን ከጥሩ» እንደሚባለዉ አንድን ነገር ጥሩ አድርጎ ሳያውቁ አስተያየት መሰጠት አይገባም። የመጽሔቱ ሽያጭ ገቢም ቢሆን የቤተ ክርስቲያን እንጂ የግለሰብ መጠቀሚያ እንዳልሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱን በቅንነት ከሚያገልግሉ ወገኖች ጠጋ ብለዉ ቢረዱ መልካም ነበር። ቢሆንም እንኳን ከዚህ የበለጠ ሐዋርያዊ አገልግሎት የለምና እንደቤተ ክርስቲያን ልጅ የምንደግፈዉ ነዉ። መጽሐፍ ጽፎ ለሽያጭ ማቅረብ አዲስ ነገር እኮ አይደለም። 3. የኮሎኝ ደብረ ስላም ቅዱስ ሚካኤልን የእኛ ንብረት ለማድረግ የተደረገዉን ጥረት እርስዎ ከሩቅ ባይረዱት አይገርመኝም። እንዲገዛ ሳንቲምም ቢሆን ለማዋጣት አልደፈሩ ይሆናል። ነገር ግን ግዢዉ እንዳልተፈጸመ በድፍረት ጽፈዋል። ለመሆኑ ክስዎ ወይም የስም ማጥፋትዎ ካህኑን ብቻ የሚመለከት ይመስልዎታል? ቤተ ክርስቲያኑ ባለቤት ነበረዉ ባለቤቶቹ እንዴት በሕጋዊ መንገድ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታቸዉን ሰጡ ብለዉ ለማስብ ሞክረዉ ይሆን? ይህን በሚመለከት ግዢዉ ሲከናወን በአገልግሎት ላይ የነበረዉ የሰበካ ጉባኤ አስተዳድርና ሻጩም ወገን በሕግ ሊጠይቅዎ እንደሚገባ አሳስባለሁ። «ዉሸት ሲደጋገም እዉነት ይመስላል» እንደሚባለዉ ይህን መሰል የሃሰት ወሬ ለሚያናፍሱ ሁሉመማሪያ ይሆናልና። 4. ሙስና አና ያስተዳደር ችግር እያሉ ያልተጨበጡ ነግሮችን ጠቃቅሰዋል። በመሠረቱ ያለማሰረጃ ያንድን ሕጋዊ የሆነ ተቋም አስተዳዳሪ ስም ማጥፋት በሕግ ያስጠይቃል። የሂሳብ መርማሪ (ኦዉዲተር) ቢመጣ ያሉትም ቢሆን ምንም በማያዉቁት ነገር አንባቢን ግራ የሚያጋባ እና እኛን የቤተ ክርስቲያኒቱን ተግልጋዮች ጥርጣሬ ዉስጥ የሚከት ስለሆነ እንዲያርሙ አሳስባለሁ። 5. ሊቀ ካህናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ እኔ እንደማዉቀዉ ከሀገራቸዉ አልፈዉ በራሺያ እና በጀርመን ሀገር ባጠናቀቁት የትምህርት ደረጃ ዶክትሬታቸዉን ተቀብለዋል። እርስዎ ቢቀበሉትም ባይቀበሉትም ይሄ በሕጉ መሠረት ከስማቸዉ ጋር አብሮ የሚጠሩበት መብታቸዉ ነው። የተማረ ሰውም ይሄን ያዉቀዋል በዘፈቀደ ዘርጥጠዉ መጥራት ስህተት ብቻ ሳይሆን አላዋቂነትን በግልጽ የሚያሳይ ነዉ። እንዲሁም ሊቀ ካህናት የተባሉትም የቤተክርስቲያን ማዕረግ እንደመሆኑ አብሮ መጠቀስ አለበት። ይህ ክብረነክ መሆኑን እንዴት አላስተዋሉም? በሕግም ያስጠይቃል። 6. ሊቀ ካህናት ዶክተር መርዓዊ መንታ መንገድ ላይ እንደቆሙ ለመግለጽ ሞክረዋል። እኝህ አባት ከመጀመሪያዊዉም በቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚያምኑ ለመሆናቸዉ በተደጋጋሚ የጻፏቸዉና በይፋም የተናገሯቸዉን ቁምነገር አዘል ጽሑፎችና ንግግሮችን መመልከት በተገባዎት ነበር። ከየትኛዉም ወገን ለመሆንም መብታቸዉ በሕግ የተጠበቀ ሆኖ ሳለ
አንድነትን መምረጣቸዉ ግልጽ ነዉ። በዚህ አቋማቸዉም ይከበራሉ እንጂ አይነቀፉም። እኝህ አባት የዋልድባ መነኮሳት የገጠማቸዉን ችግር ገልጸዉ ድረሱልን ሲሉ በድፍረት መንግሥት ከገዳማችን እጁን እንዲያነሳ ከጸሎት በቀር አንዳች የሌላቸዉ መነኮሳት አባቶቻችንን ድምጽ በምድረ ጀርመን ያስተጋቡ ብቸኛ ካህን መሆናቸዉንስ ልብ አላሉት ይሆን? እኛ ደግሞ ይህንን ጨምሮ ለሚያሳዩን አባታዊን ግዴታ የመወጣት ጥረት እናደንቃቸዋለን። ለእርስዎ ግን ይህ ዋጋ የሚሰጠዉ ተጋድሎ አለመሆኑን ዘለፋን ብቻ ያጨቀዉ ጽሑፈዎ ያመለክታል።
7. „ለምን በጥምቀት አንድነን ተባለ ብለዉላቀረቡት ወቀሳ“ የምመልስሎት አለቦታዉ ገብተዉ አይዘባርቁ ይሆናል። ይህ በመንፈሳዊ ትምህርት የላቁ የሊቃውንቶች መድረክ የሚመለከት ነዉ። መደምደሚያ በእኔ አስተያየት አቶ መስፍን ከጽሁፍዎ ውስጥ የተወሰኑ ነጠቦችን ጠቅሼ ግድፈቱን ለማሳየት ሞክሬያለሁ። ሆኖም ግን አንድ ያልገባኝ ነገር አለ። ይኸዉም ጥያቄ ኖሮዎት የበለጠ ለመረዳት የጻፉት ከሆነ ጽሁፍዎ የጥያቄ ዘይቤ ይጎለዋል። የሰዉን ጥረት አንኳሶ የደከሙ አባትን ልፋት አሳንሶ ለማሳየት የሚጥሩ ከሆነም ይህ ምግባር ከቤተ ክርስቲያናችን አባል የሆነ ሰው የማይጠበቅ ከሃይማኖታችንም አንጻር ሲታይ፣ ከኢትዮጵያዊ ባህላችን እና ከስርዓታችንም ጋር የማይግባባ ነው። በ አስርቱ ትዛዛት፣ በእምነታችንም ሆነ በባህላችን ወላጅ አባት ይከበራል በተለይ ካህን በ እጃቸው መስቀልን ያህል የሚያሳልሙ አባት ይከበራሉ። በተለይም እንደ ሊቀካህናት ዓይነት አባት ሕይወታቸውን በሙሉ የተለያየ መስዋዕትነት በመክፈል ለኛ ለኢትዮጵያኖች እና ኤርትራዉያን እገሌ ከእገሌ ሳይሉና ሳይለዩ ለነፍሳችን መድረሻ እንዳናጣ በባእድ ሀገር በቋንቋችንና በባህላችን ክርስቲያናዊ ስርዓት ሳይጓደልብን እንድንኖር ያበቁን ናቸውና። እንደዛሬዉ አብያተክርስቲያናት ሳይኖሩና ካህናት አባቶችም ሳይዘገጁ የነበረዉን ሕይወት በምናዉቅ ወገኖች ምንግዜም አይዘነጋም። ሊዘነጋም አይገባም እላለሁ። እኔም በእርስዎ በኩል አላግባብ የተጻፈዉ ዘለፋና ባዶ ድፍረት የተሞላበት ጽሁፍ ይህን ሁሉ እንደተመለከተና እንዳሳለፈ ምዕመን በጣም አሳዝኖኛል። እኔ አላውቅዎትም ለመሆኑ በጀርመን ሀገር ኑሮዎና ሥራዎ ምን ዓይነት ይሆን? የትምሁርቶስ ደረጃ ምን ይሁን? ከአንድ አልፎ 10 ቤተ ክርስቲያናትን የሚያስተዳድሩ አባት አጉድፎ ለማቅረብ ሕሊናዎስ እንዴት እሺ አሎት? በሀገራችን እንደሚባለው «ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው» ዛሬ አነሰም አደገ በተደላደለ ሁኔታ የሚገኙትን አብያተክርስቲያናት ከዚህ ለማድረስ የተለፋዉን ልፋት በእርግጥም ድካሙን ያለፈበት ብቻ ነዉ ሊረዳ የሚችለዉ። ለማይሠራዉ ግን መተቸቱ እጅግ ቀላል ነዉ ከበሮ በሰዉ እጅ ያምራልና። እኔ የእርስዎ የዘለፋ ጽሁፍ ገፋፍቶኝ ይሄንን ብፅፍም የተለያየዩ ምእመናንም ሃሳብ መሆኑን አምናለሁ። የቤተ ክርስቲያናችን ስም እንዲጠፋ ያስተዳደሩም ስም እንዲነቀፍ የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር አባላትም ልፋት ከንቱ ሆኖ እንዲቀር፣ በጠቅላላዉ እኛ ምእመናን ጥፋተኛ እና ትክክለኛ ያልሆነ አባት ይዘን እንደምንጓዝ አድርጎ የሚያቀርበውን ፅሁፎን ዝም ብለን አንቀበልም ማስተካከያና ማረሚያ ፅፈዉ እንዲያቀርቡ እጠየቃለሁ። እርማቱን ይህ መልዕክት ለርሶ ከደረስና ለንባብም እርስዎ እንዳደረጉት ይፋ ከሆነ በሁዋላ ከአንድ ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ እንዲያቀርቡ አሳስባለሁ። ካልሆነ ግን በውጭ በኩል ያለዉ የቤተ ክርስቲያናችን ገጽታ እና አቁዋም (Außenbild) (Image) በእርሰዎ ፅሁፍ ምክንያት አላግባብ እንዲበላሽ በመደረጉ ሕጋዊ በሆነ መልኩ እንዲያነሱት የጀርመን ህግ ያስገድዶታል። ከአክብሮት ጋር ወ/ሮ መሰረት፡ አለ፡ ፈለገ፡ ሠላም-ቫየር ኢርፍት ሸታት

ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com

No comments:

Post a Comment