Thursday, October 17, 2013

እስኪጣራስ

በልጅግ ዓሊ
ሃገር ውስጥ የተገኙ ዝሆኖች ሁሉ ይታሰሩ የሚል አዋጅ ይወጣል። አንድ አይጥ ከላይ ወደ ታች ትራወጣለች።  ምን ሆነሽ ነው ብለው ይጠይቋታል። በሃገር ውስጥ ያሉ ዝሆኖች ሁሉ ይታሰሩ ተብሎ የወጣውን አዋጅ አልሰማችሁም እንዴ? ብላ ትነግራቸዋለች። ታዲያ አንቺ አይጥ እንጂ ዝሆን አይደለሽ ብለው ሲጠይቋት ። እሲኪጣራስ ብላ መለስች አሉ።
እሲኪጣራ በዝሆንና በአይጥ መካከል ያለውን ልዩነት ጊዜ ይወስዳል። የተስፋዬ ገብረአብ ጉዳይም እንዲሁ ነበረ።

ልጅ ይታየዋል።
የአማርኛ ተረቶች አንዳንዶቹ እንዴት እንደተፈጠሩ ማጥናትና በጽሁፍ ማስፈር አስፈላጊ ነው። ተረቶቹ እውነትነታቸው በተግባር የተፈተነ ነው።  ብዙ ጊዜ ተረቶች ከልምድ ጋር የተያያዙ ናቸው።
በነፃ የተለቀቀልንን የተስፋዬ ገብረ አብን መጽሐፍ ሳነብ አንድ የሚገርም ጉዳይ አገኘሁ። ሰለ አንድ ማሊክ ሰለሚባል ሶማሌያዊ ሕጻን ፦
ገጽ 25 ፡ -
ማሊክ በእናቱ እንደታቀፈ አንገቱን ወዲያ ወዲህ ሲያሽከረክር እኔ ከሁዋላ ነበርኩና አይን ለአይን ተጋጨን። ልክ እኔን ሲያይ እንደገና ማልቀስ ጀመረ። እናቱ ልጇ ያለቀሰበትን ምክንያት ለማወቅ ነው መሰል ዘወር ስትል እኔን አየችኝ። ሰይጣዊ ክፉ መንፈስ እንዳየች ሁሉ እሷም ፊቷን ጭምድድ አድርጋ ዘወር አለች። እኔም ምንም እንዳልተፈጠረ መንገዴን በመቀጠሌ እናትና ልጅ ከሁዋላዬ ሆኑ።
ማሊክ ማልቀሱን አቆመ።
ልጁ ያለቀሰበትን ምክንያት ተስፋዬ የተለያየ መላምቶች አስቀምጧል።ከሰይጣናዊ ክፉ መንፈስ እስከ ሞቃድሾ እስከዘመቱት አበሾች ድረስና የሶማሊዎች በአበሾች ላይ ጥላቻ።
ተስፋዬ ስለ ማሊክ ማልቀስ ራሱ የመሰለውን ከእውነት የራቀ መላ ምት ይስጠው እንጂ በዓለም የተሰራጩ የሶማሌ ሕጻናት እኛን ባዩ ጊዜ አያለቅሱም። ስለዚህ ስለ ሃበሻ  የተሰጠው ትንታኔና ምክንያት ኩታ ገጠም አይደለም። ስለዚህም  ክፉ መንፈስ የሚለውን አጠንክረን ከሌላ መላ ምት ተቆጥበን እዚሁ ላይ እንተወው። ከላይ የጠቀስኩት ተረት ልክ ነው። ለልጅ ይታየዋል . . . ። 
ንቆሮ የሰማ ዕለት ያብዳል። 
እንደ ዝሆኑና እንደ አይጧ ያለው ልዩነት  ተመልሶ አጀንዳ ሆኖ ሲያምሰን ከረመ። የተስፋዬ ገብረአብ ጉዳይ። መቼም ዛሬ እንዲህ የገነነበት ጉዳይ ምክንያት ይኖረዋል። እያደር መጋለጡ አይቀርም። ለትንሽ ጊዜ ኢንተርኔት በቀላል የማይገኝበት ቦታ ነበርኩ። ወደ ቦታው ከመሄዴ በፊት ስለ ተስፋዬ ገብረአብ የተገኘው መረጃ ለሕዝብ የተበተነበት ወቅት ነበር። ከሄድኩበት ተመልሼ ስመጣም ተሰፋዬ አጀንዳ ነው። ተስፋዬ እንደፈራው መድፍ አልተተኮሰበትም። ከውስጥ አዋቂ ከሆነ አገር ወዳድ የተጫረች ትንሽ ክብሪት ነች አቃጥላ የጨረሰችው። እኛም ብዙ ሲነገረን ያልገባን መረጃውን ስናይ አበድን።  ደንቆሮ የሰማ ለት ያብዳል እንዲሉ።ተስፋዬም የአጻፋውን መልስ ተኮሰ።
አንዳንዶቻችን  ሰላቢ ጸሐፊዎች ብሎ አማን። ደፍሮ ግን ሰለኔ የጻፉት ትክክል አይደለም ብሎ መጻፍ ተሳነው። ምን ብዬ እንደጻፍኩ ወደ ኋላ ተመልሼ አነበብኩት። “የማታውቅበትን . . .’’ በሚለው ጽሁፌ ላይ ትንቢት የመሰለ ጉዳይ ይገኛል።
“ተስፋዬ በአሁኑ ወቅት አንገብጋቢውን ጥያቄ መመለስ ሲያቅተው በሕይወት የማይገኙ ግለሰቦች እየጠቀሰ የተሳሳተ መረጃ ከሰጠ እኔም ባልሆን ሌሎች የሚታዘቡ ይቀጥሉታል።’’
ልክ ነው የተሳሳተ ግምት አልነበረም። ሌሎች ቀጠሉበት። በመረጃም አጋለጡት። ተስፋዬ ሁሉንም የመከፋፋያ ዘዴ ተጠቅሟል። ግን አልተሳካም። አባት ሃገሬ ብሎ የሚኮራባት ኤርትራም በቅርብ በልጆቿ ትግል ከኢሳያስ ጭቋና ነጻ ትወጣለች። እሱም ለአርባ አራቱ ታቦት የሚሳልበት የሃገራችን የእርስ በእርስ ጦርነት በጀግኖች ልጆቿ ይከሽፋል። የሃገራችን ትንታግ ጸሐፊዎች ዜጎቻችንን የሚከፋፍለውን ሳይሆን የሚያፋቅረውን የአንድነት ገድል ይጽፉታል። ሆ ብሎ የተስፋዬን ሥራ ያጋለጠው ሁሉ ሰደድ እሳቱን በቅርብ ቀን በወያኔም ይሁን በሻብዕያ ጓዳ ውስጥ ይለቀዋል። ያ ጊዜ ወዮላችሁ! ዘርን ከዘር ለማናከስ እንቅልፍ ያጡ እንኳን የሆላንድ ዜግነት መታወቂያ የሚያምኑበትም “የቆሪጥ’’ ግብር አያድናቸውም። እውነት እውነት እላችኋለሁ ጊዜው ሳይመሽ ንሰሃ ግቡ። ከሃያ ዓመት በላይ የጠበቃችሁት የርስበርሱ ጦርነት በራሳችሁ ምናብ ውስጥ ብቻ ተጽፎ ቀርቷል። ቢቻላችሁ የያዛችሁ የዘር ጋኔል ይለቃችሁ ዘንድ ከሃገራችን አዛውንቶች ጋር ቁጭ ብላችሁ ታሪክን ተማሩ። ስለአንድነት የተጻፉትንም ቢያንገፈግፋችሁም አንብቡት።
በድሉ ዋቅጅራ ለልጁ በጻፈው ደብዳቤ እንዲህ ብሎ ነበር።
የኔ ልጅ፣
አማራው አፋሩ ኦሮሞው ሲዳማው ፣ጉራጌኛሽ ባይሰማ፣
ያልገባው እንዳይመስልሽ  ሀዘን ደስታሽን ያልተጋራ።
የየልቦናችንን ሀቅ ፍንትው አድርጎ እያሳየ 
ህዝቦችን ከሰንደቃቸው አስተሳስሮ  ያቆየ፣
ሀገር ቋንቋ ነው ልጄ የሁለንተናሽ መስታወት፣
ሲከፋሽ ትሽሽጊበት  ሲደላሽ ትኳኳይበት  
የኔ ልጅ 
አያት ቅም አያትሽ ፣ሰላም ሲሆን ከወልቂጤ አድማስ ማዶ ሸቅጦ፣
ሲያቀና ወረቱን 
ለእኔና ለአንቺ መኖሪያ ሲያቀና ቀዬና ቤቱን 
ሀገር ጠላት ሲደፍራት ጦሩን ሰብቆ እየፎከረ፣
ከኦሮሞው ከትግሬው ከአፋሩ ከወላይታው ከሁሉም የጦቢያ ልጆች 
አጥንቱን እየማገረ 
ሀገር ይሉት መግባቢያ ፣ሰንደቅ ይሉት መለያ ፣ሲያቆይልሽ 
በጉራግኛ የማትገልጭው በጎጥ የማትገድቢው፣ ስንት አለ ታሪክ መስለሽ።
እነ በድሉ ዋቅጅራ ፣ እነ ዓለማየሁ ገላጋይ ፣ እነ ተሰመስገን ደሳለኝ ፣ እነ በእውቀቱ ስዩም . . .  ወዘተ እየገነቡ ያሉትን አንድነት ፣ እነ ተስፋዬ ንደው ይጨርሱታል የሚል እምነት የለኝም። ግና የሃገራችን ጠላቶች የሚያፈሱላቸውን ነዋይ በመጠቀም መድረኩን ሞልተው፣ በአሉባልታ ጽሁፋቸው ይታዩበታል። እውነተኛዎቹ የአንድነት ጸሐፊዎች ግን በውስጥ ወያኔ ፣ በውጭ ወያኔና ሻብዕያ በመተባበር መቆሚያ መቀመጫ እያሳጧቸው ነው። በቅርብ ቀን መስፍን ማሞ ተሰማ የገመገመውን  “ኢህአዴግን እከሳለሁ”  የሚለውን የዓለማየሁ ገላጋይን  መጽሐፍ የምናውቅ ስንት ነን? የአንድነት ተሟጋች ጸሐፊዎችን የምንረዳበት ምክንያት ስላለን ሁላችንም በያለንበት መጽሐፎቻችው በመግዛት መተባበር በትግሉ ውስጥ እርዳታ እንደማድረግ ይቆጠራል።
ወደ ተነሳሁበት ስመለስ ታዲያ ተስፋዬ ሰላቢ ጻሐፊዎች የሚለን እሱን የተጠናወተው እርኩስ መንፈስ፣ እኛን ስላልተጠናወተን አንታየው ይሆናል። ለእውነት ቅርበታችን ደግሞ ከማንኛው በላይ እንዳስፈራው ግልጽ ነው። ለወዳጆቻቸንና ዓላማ ለምንጋራው ግዙፍ ሆነን እንታያለን። እኛንና እሱን የቅርብ ሩቅ የሚያደርገን የዓላማው ከአጥናፍ አጥናፍ መሆኑ ነው። እውነት እውነቱን ስንናገር፣ ዓላማ ስንጋራ፣ የሚከፋፍለውን ትተን የሚያቀራርበውን ስንሰብክ  ቅርብ ነንና እንታየው ይሆናል። በተለያየ ዓላማ ግን አጠገባችንም ሆኖ ለመታየት አንችልም። ከከፋፋይና ሕዝብን እርስ በእርስ ለማዋጋት ከሚጥር እቁብ አንጠጣም፣ እድርም የለንም። ራሳችንንም ለማሳወቅ ብዙ ጥረት አናደርግም። ለሃገራችን ስንል ስንሰደብ ደግሞ ደስ ይለናልና የከፋን እንዳይመስልብን። ስለሆነም ለሻብዕያና ለወያኔ ሰላቢ ሆነን መቆየትን መርጠናል።
ሰለተስፋዬ “የማታውቅበትን የሰው . . . ’’  በሚለው ኀዳር / 2004  በተጻፈው ፅሁፌ ውስጥ የጠቀስኩት አሁንም እደግመዋለሁ።
ታሪክም ቋንቋም ቢሆን ባለቤት አለው። ማንም ሲመቸው እየተነሳ የሚደለቅበት የዛር ዘፈን አይደለም። ቋንቋደግሞ በረዥም የማህበረ-ሰብ ሁለገብ ግንኙነት፣ እድገትና ውድቀት፣ እምነትና ፍልስፍና (እውቀት) አመራረትናአኗኗር .. የዳበረና በማኅበረ-ሰብ ሕግ ሠፊ ተቀባይነት አግኝቶ በሁሉም ዘንድ በአወንታ ለዘመናት ሲሰራበትየኖረና የሚኖር ዓብይ የጋራ እሴት ነው።
የጨረባ ተዝካር ዓይነት፣ የቃላት የአሉባልታ ጋጋታ ላንድ ሰሞን ተባለ እንዴ……. ! ባዮች ቡና ማጣጫ ሊጠቅምይበጅ እንደሁ እንጂ ሃገራዊ ጥቅም የለውም። ሃገር በአሉባልታ አትገነባም። ” ጦር ከፈታው፣ ወሬ የፈታው ”እንዲሉ። ተስፋዬ በለመደበትና ባደገበት ብእሩም በሚመጥነው ደረጃ ቢናገርም፣ ቢጽፍም ባልከፋ ነበር። ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ጠቃሚ ሀሳብ ማፍለቅ ከሰከነ አይምሮና ከተባ ብእር አንጀት ይወለዳል።የተማረ ሁሉ አያነበንብም፣ ያነበነበ ሁሉ አያዜምም፣ ያዜመ ሁሉ ደግሞ ቅኔ አይዘርፍም።  አንዳንዶች መንታልብና መንታ እግር ስለአላቸው የሁለት ዓለም ሠራዊት በአንዴ ማዝመት ያምራቸዋል።
በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ ታሪክና ሕዝብ ላይ አረም የበዛበት ዘር ለማብቀል የሚፍጨረጨሩ በርካታ ጸሃፊዎችእንደአሸን እየፈሉ በአሉበት በአሁኑ ወቅት እንኳ፣ እንዲህ በገሀድ ፍጥጥ ያለ፣ ፈሩን የሳተና የተዛባ የሐሳብናየቃላት ትርጉም ደራሲ አላጋጠመኝም። የሁለት ዓለም ወግ ባንድ ምላስ ማስተናገድ ይቻል ይሆንበተዛባእውቀትና ትርጉም፣ አለያም በስውር ተልእኮ፣ እንዲያም ሲል ከመሰሪነት በሚመነጭ  ሀሳብ የሌሎችን ቀልብለማደፍረስ ከንቱ ቅኝት መቃኘት ነው የሚሆነው። እሱ ደግሞ መጨረሻው ቅሌት ነው የሚያተርፈው። የአሉሽአሉሽ ወግ እንኳን ሀገር የግል ቤት አይገነባም። ወግ መጠረቅ ወይም መጻፍ፣ ታሪክን ከመቃኘትና ከመክተብ ጋርእጅግ የተራራቁ ግብሮች ናቸው።
ከተስፋዬ ጽሁፍች ብዙ ታዝበናል፣ አዝነናል ስቀናልም።  አንዳንዶቻችን ገና ከጅምሩ መዳረሻቸው ለመቃኘትችለናል።የሱንም ማንነት ለማወቅም ቢሆን ብዙ ማጣቀሻ አላስፈለገንም።  ራሱን በዛው በጀመረው የወግ ጥረቃ (በተልእኮም ይሁን በግል አቋምዙሪያ ገድቦ ቢጫወት የሚያዋጣው ይመስለኛል።
ምክንያቱም አቶ ተስፋዬ ከምድር በላይ ሊያሳየን የሚሞክረው የጥላቻ ዛፍ ከምድር ውስጥ ከብዙ ከምንወዳቸውዛፎች ጋር በሥሮቹ አማካኝነት ተጋምዶና ተጠላልፎ እየኖረ ስለመሆኑ አስቦ የሚያውቅ አይመስለኝም። የቡርቃ ዝምታ ሊቀጥል የማይገባው ለሕዝብና ለሃገር የማይጠቅም የባዕድ ተልእኮ ነውና ።
ዛሬም ዜጎቻችንን የሚስተሳስርልን ታሪክ አጉልተን፣ በሩዋንዳ የተደረገው ዓይነት አሳዛኝ ታሪክ እንዳይፈጸም የታሪክ አደራ አለብንና ሁላችንም ዘብ መቆም ይጠበቅብናል። ልንተርከው የሚገባ ሕዝባችን አንድ አድርጎ የቆየ ስንት ታሪክ በጎሣ ፖለቲከኞች ቢደበቅም አደባባይ አውጥተን ማሳየት ያሻል። አለበለዚያ ግን ለነተስፋዬ ቦታ መልቀቅ አደገኛነቱን የጎላ ነው።
ስለ ሕዝብ አንድነት የሚሰብኩ በሰላም ይክረሙ።
በልጅግ ዓሊ
14.10.2013
ለንደን

No comments:

Post a Comment