Friday, October 18, 2013

የሃበሻው ፈርጥ! – ቨርጂኒያ ድምፃዊ ፀሓይ ዮሃንስ – ቨርጂኒያ (እየሩሳሌም አርአያ)

የሃበሻው ፈርጥ! – ቨርጂኒያ
ታዋቂና ተወዳጅ፣ ለእናት አገሩ ኢትዮጲያና ለሕዝቧ ጥልቅ ፍቅር ያለው፣ ክብርና ፍቅሩን ሁሌም በተሰለፈበት ሙያ በተግባር የሚያሳይ፣ የአላማ ፅናት ያለው፣ ውድ የሃበሻ ልጅ፣ ድንቅ አርቲስት…ነው። አዎ፤ ድምፃዊ ፀሓይ ዮሃንስ። ዛሬ በእጅ ስልኬ ደውሎልኝ በቨርጂኒያ ተገናኘን። ተቃቀፍን። ለፀሓዬ ስራዎች እጅግ በጣም የተለየ ስሜትና ጥልቅ ፍቅር እንዳለኝ ሁሉም ወዳጆቼ ያውቃሉ። ፀሓዬም ያውቃል። የእርሱን ዘፈን ሳልሰማ የዋልኩበትና ያደርኩበት ቀን የለም። ..ከሰላምታ በኋላ፥ « ፀሓዬ የዛሬ ስድስት አመት አገር ቤት እያለሁ በስልክ አግኝቼህ ምን እንዳልኩህ ታስታውሳለህ?» ስል ጠየኩት። ደስ በሚል ፈገግታ፥ « አዎ አስታውሳለሁ!» አለኝ። እንዲህ ነበር ያለኩት፤ « ፀሓዬ በዝች ምድር ዳግመኛ የመፈጠር እድል ብታገኝ..እንደኔ ጨርሶ ሊወድህ የሚችል አይኖርም!! ዘፈኖችህ ለኔ የተዜሙ ያክል ይሰማኛል። በአጥንቴ ውስጥ ሰርፀው ገብታዋል። ረጅም እድሜ እመኝልሃለሁ!! » ..እሱም የተናገርኩትን ቃል በቃል አስታውሶ ደገመልኝ። ..« እንዴት ነሽ ገላዋ..እንዴት ነሽ ገላዋ ..ሃያል ህመሜዋ » እያለ ሲያንጎራጉርልኝ በደስታ ስሜት ተሳከርኩ። የምናገረው ሁሉ ጠፋኝ። …ለግማሽ ሰአት ያክል ከማደንቀውና ከማከብረው እንዲሁም ስራዎቹን ሰምቼ ከማልጠግበው ድምፃዊ ፀሓይ ዮሃንስ ጋር አወራን። ፀሓዬ – ከ12 አመት በፊት በቨርጂኒያ የገዛው መኖሪያ ቤት አለ። ሜዳ ቴኒስ በየቀኑ ለሁለት ሰአት ያክል ይጫወታል። ስፖርት በማዘውተሩ ሸንቃጣና ጤናማ ሰውነት እንዲኖረው አስችሎታል። ሰይፉ ፋንታሁን በአንድ ወቅት የድምፃዊያን የመድረክ ስራዎችን በተመለከተ ሲናገር፥ « ፀሓይ ዮሃንስ ከሌላው ለየት የሚያደርገው መድረኩን (ኦዲየንሱን) የመቆጣጠር ትልቅ ተሰጥኦ አለው። » በማለት አድናቆቱን ገልፆለት ነበር።…ፀሓዬ ዛሬ ምሽት ወደ ለንደን ተጉዞ በዛ ኮንሰርት እንደሚያቀርብና ከዛም ወደ ኢትዮጲያ እንደሚሄድ ነገረኝ። በፋሲካ የሚወጣ አዲስ አልበም ለመስራት ነው፥ አገር ቤት የሚጓዘው።.. አንድ ስለሰማሁት የእርሱ በጎ ተግባርና ሌላም ጉዳይ ጠየኩት። ፀሓዬም ፥ « ልክ ነህ! ገንዘብ ይመጣል፣ ይሄዳል። ዋናው ጥሩ ነገር መስራት ለወገንህ መልካም ማድረግ ነው ትልቁ ቁም ነገር። ከምንም በላይ ጥሩ ማድረግ ለህሊናህ እርካታን ይሰጣል!!…» ካለኝ በኋላ አያያዘና፥ « የኢትዮጲያ ህዝብ ትልቅና ጨዋ ነው!! ሕዝብ በጭራሽ አይሳሳትም!! ይህን አስተዋይና ለትልቅ ደረጃ ያደረሰህን ህዝብ እንዴት ታስቀይማለህ!? ለምን?…» አለኝ። ..ከተወዳጁ ድምፃዊ ጋር የነበረን ቆይታ አጭር ቢሆንም፣ ነገር ግን ጥሩ ቁም ነገሮችን አወጋን። በተለይ ለእኔ ብዙ ገጠመኞች ባላት ረቡዕ ቀን ፀሓዬን ማግኘቴ አስደናቂ ነበር። ..የመለያያችን ሰአት ሲደርስ ዳግም ትከሻውን በአድናቆትና ፍቅር አቅፌ « የሃበሻ ፈርጥ ነህ!!» ስል ከልብ በመነጨ ስሜት ነገርኩት። ..ከፀሓይ ዮሃንስ ጋር የነበረኝን ውሎ ስከትብ የእርሱን ዜማ « ማን እንደእናት ማን እንዳገር..» የሚለውን እያደመጥኩ ነበር። ፀሓዬ – ረጅም እድሜ ለአንተ ይሁን!!
( ከማደንቀው አርቲስት ፀሓይ ዮሃንስ ጋር በቨርጂኒያ ..)
 አርአያ ተስፋማሪያም

No comments:

Post a Comment