Monday, October 7, 2013

ዲሞክራሲ ቆቅ ናት !!

(አሌክስ አብረሃም) 
አዲስ ጉዳይ መፅሄት ላይ ወጥቶ የነበረ!

‹‹እኔ አለሙ ደገፋው በዚሁ መስሪያ ቤት ለድፍን ሃያ ዘጠኝ አመት ስሰራ የቆየሁ አሁን በግል ፍላጎቴ ጡረታ መውጣት ስለፈለኩ እንድታሰናብቱኝ እጠይቃለሁ !! ››


በቃ አባቴ ነገር አያበዛም !! ከተናገረም ተናገረ ነው !! ጡረታ ወጣ !! 

አባቴ ጡረታ የወጣው ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ ‹‹የዲሞክራሲን ትርጉም ›› ለማፈላለግ ነበር !! 

ከሃያ አመት በፊት ነበር ጎረቤታችን ፍስሃ ጋር በድንበር ተጋጭተው አፍ እላፊ ሲነጋገሩ አባቴ ተሰደብኩ ብሎ የከሰሰው ...
‹‹ምን ተብለው ተሰደቡ ›› አለው ክሱን የሚሰማው የፍርድ ሸንጎ ዳኛ ...

‹‹ ግቢው ውስጥ እየተንጎራደደ ድምፁን ከፍ አድርጎ አደባየሃለሁ ብሎኛል ››

‹‹ እና አደባዮዎት ወይስ ተናግሮ ብቻ ዝም አለ›› በማለት አባቴን ጠየቁት ...በጥያቂያቸው በጣም ተበሳጨ 

‹‹ምን ማለታችሁ ነው ...ዛቻስ ቀላል ነገር መሆኑ ነው እንዴ ...›› ቢላቸው 

‹‹ማንም ሰው በራሱ ግቢ መፎከር መሸለልአደባየሃለሁ› ...አፈር አስግጥሃለሁ ማለትዲሞክራሲያዊ መብቱነው እስካላደባየ አፈር እስካላስጋጠ ድረስ ›› ብለው በሰሞንኛ እንጩጩጭ የዲሞክራሲ አስተምሮ ክሱን ውድቅ አደረጉበት


ፀበኛው ፍስሃም ፊቱ በሳቅ ተፍለቅልቆ ‹‹ዴሞክራሲ ለዘላለም ትኑር ጓዶች ወደፊትም - ዲሞክራሲ ሃይሎች መንገድ የተገፋብኝን ድንበር በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንደማስመልስ እምነቴ ነው ›› ብሎ ተናገረ ለሁለት የታጠፈ እስኪመስል አጎንብሶ 

አባቴ ‹‹እች ዲሞክራሲ የሚሏት ነገር ዛሬ ክብሬን ካስነጠቀችኝ ነገ ድንበሬን ልታስወስድብኝ ነው ›› ብሎ በማሰብ ከዛን ቀን ጀምሮ ፍችዋን ለማግኘት ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም !! እንደውም የዲሞክራሲን ፍች ለመፈለግ እንዳባቴ የተንከራተተ ሰው ያለ አይመስለኝም ያገኘውን ሁሉ ይጠይቃል ሬዲዮ ይሰማል ቴሌፊዥንም ይመለከታል ዲሞክራሲ ግን የውሃ ሽታ ሆነች !

‹‹ኤልሳ ›› አለ አንድ ቀን እህቴን 

‹‹አቤት አባባ›› አለች ጥፍሯን የምትሞርድበትን መሞረጃ እንዳንከረፈፈች 

‹‹ዲሞክራሲ ምን ማለት ነው ...›› ቢላት 

‹‹ዲሞክራሲ ...ቆይ ጥፍሬን ሞርጀ ልጨርስና እነግርሃለሁ አባብየ›› አለችው 


‹‹እንዴዴዴዴ ጥፍር መሞረድ ድንበርን ከነገረኛ ጎረቤት አያስጥልም በሙንጭሪያ አይደለም እኮ የተረታሁት በቃል ነው ....መጀመሪያ ይሄን ጆሮ የሚሞነጭር ጥፍራም ቃል ሞርጅልኝ ከጥፍርሽ በፊት ›› አለ በቁጣ 

‹‹አባባ እኔ አላውቀውም ››

‹‹ተማሪ አይደለሽም ...ያውም አስረኛ ክፍል ›› እያለ ሲነታረኩ በመስኮት በኩል ንዝንዛቸውን ሲያዳምጥ የቆየው ወንድሜ ብቅ ብሎ ‹‹አባባ ዲሞክራሲ ትምርት ቤት አይገኝም እንደሰነፍ ተማሪክላስዘግቶ ጠፍቷል ›› አለ እየሳቀ 

‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው በለኛ ....›› አለና አባባ ተከዝ ብሎ አሰበ ከዚያም በመስኮት አፉ ብቻ ብቅ ያለ ወንድሜን እንዲህ ሲል ጠየቀው ‹‹ እና ዲሞክራሲ የሚባለው ጉድ የት ነው ያለው ›› 

‹‹ጦር ሜዳ ነዋ አባባ ›› በዛ ሰሞን ትምህርቱን አቋርጦ ወታደር ቤት ሊመዘገብ አሰፍስፎ አባባ አትሄድም ብሎት ስለነበረ ማሳመኛ አድርጎ አጋጣሚዋን ተጠቀመባት ....አባቴ ነገር አያረዝምም ወንድሜን መርቆ ወደወታደር ቤት ሸኘው!! 


በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ወንድሜ ከአመት በኋላ እያነከሰ ከጦር ሜዳ ተመለሰ ...አባባ ወንድሜ እስኪያገግም እንኳን አልታገሰም 
‹‹ እና ትርጉሟን አገኘሃት የኔ ሳተና ›› ሲል በጉጉት ጠየቀው 

‹‹ምኒቱን ?›› አለ ወንደሜ በተሰላቸ መንፈስ ከቆሰለ እግሩ ህመም ጋር እየታገለ 

‹‹ዲሞክራሲን ነዋ ...የሄድክበትን ዘነጋህ እንዴ››

‹‹እእእእ ! አባባ .... ..... እኛ በዚህ በኩል ጠላት ከዛ በኩል መሽጎ ተፋጠን ነበር ....ልክ ጦርነቱ ሲጀመር እኛ ‹‹ለዲሞክራሲ›› ብለን በታንክ ምሽጋቸውን ስናደባየው ጠላቶቻችንም ‹‹ለዲሞክራሲ›› ብለው በመድፍ ምሽጋችንን ያደበዩታል እኛ ለዲሞክራሲ ክላሽንኮቭ ስንተኩስ እነሱ ለዲሞክራሲ መትረየስ ይተኩሳሉ .......መጨረሻውን ሳላይ ለዲሞክራሲ በተወረወረ ቦምብ ቆስየ መጣሁ ›› አለ 


አንድ ቀን የአባባ ወንድም ከአሜሪካ ደውሎ ‹‹ምናለብን እዚህ የዲሞክራሲ አገር ነው›› አለው ለአባባ ...ሌላውን ወንድሜን ተበድሮም ያጠራቀማትንም ጨማምሮ አሜሪካ ላከው ....

‹‹ሃሎ በለጠ ደረስክ .......ዲሞክራሲን አገኘሃት ›› አለ አባባ በጉጉት 

‹‹እንዴዴ አባባ ገና መግባቴ እኮ ነው ››አለ ወንድም ጋሸ 


የወንድሜ ድምፅ ለረዥም ጊዜ ጠፋ ... ከስድስት ወራት በኋላ በቴሌፊዥን ‹‹አንዳንድ በውጭ አገር የሚኖሩ ለሆዳቸው ያደሩ የአገር ፍቅር ስሜት የሌላቸው ግለሰቦችለኢትዮጲያ ብድር እንዳይሰጥበማለት በአሜሪካ ጎዳናወች ሰልፍ ወጡ ...ይህም አገርና ህዝብን ያሳፈረ ድርጊት ....›› እያለ ቴሌቪዥኑ ሲያሳይ ወንድሜ በለጠ እጁ ላይ የኢትዮጲያ አናቱ ላይ የአሜሪካ ባንዲራ አስሮ ‹‹ዲሞክራሲ ወደአገራችን ይግባ ›› የሚል መፎክር ይዞ ታየ .....አባባ ‹‹ በቃ ልጀ የጠፋው የላከውን ዲሞክራሲ ጉሙሩክ አናስገባም ብለውት ነው›› በማለት አዘነ !!

...አባባ ሌላ ቀን ቴሌቪዥን ሲያይ አንድ የተማሩ ሰው ‹‹ዲሞክራሲ ዶሮ ናት ስንከባከባት እንቁላል ትጥላለች ...የሰላም ...የፍትህ ..የእኩልነት ...እንቁላል !! ›› እያሉ ሲናገሩ ስለሰማ እንደልጅ እየተምነሸነሸ ለእናቴ እንዲህ አላት ‹‹አስካለ አገኘኋት ...ዲሞክራሲ ለካስ ዶሮ ናት ያውም የፈረጅ እንቁላል የምትጥል ...›› 


ተናጋሪው የዲሞክራሲ መነሻዋ ህዝባዊ ፓርላማ መሆኑንም አክለው አስረዱ...አባባ ድሮም ፖለቲካ የሚወደውን የቤተሰቡን የበኸር ልጅ ፓርላማ እንዲገባ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ወንድሜ ‹‹የተከበሩ ወንድማለም ›› ሆነ !! የመጀመሪያ ፓርላማ መክፈቻ ቀን ቡና ተፈልቶና ጎረቤቱ ሁሉ እኛ ቤት ተሰበስቦየተከበሩ ወንድማለምንለማየት እንደጓጓን 
‹‹እኔ የምለው እች ዲሞክራሲ የሚሏት ዶሮ ለዚህ ሁሉ ባለወንበር እንዴት ልትበቃቸው ነው ›› አለች እናቴ የቀበሊያችን ሊቀመንበር 

‹‹ አየ አስካሉ ....ዶሮውን እኮ የህዝብ ተወካዮቹ ገነጣጥለውና አብስለውበሞቴ አፈር ስሆንእያሉ ለህዝቡ ነው የሚያጎርሱት ....አዎ ለህዝብ ነው ›› አለ ሁላችንም አመነው ......


በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የወንድሜ ምስል ድንገት የቴሌቪዥኑን እስክሪን ሲሞላው ጎረቤቱ ሁሉ ደነገጠ ‹‹ክቡር ወንድማለም›› ሱፉን ግጥም አድርጎ እንቅልፉን እየለጠጠ !! እንዲህ አፉን በመጠኑ ገርበብ አድርጉ የመነጋገሪያ ማይኩን ፊት ለፊቱ ደቅኖ ሲታይ መርጦ የላከውን ህዝብ ህልምና ቅዠት ሰብስቦ ወስዶ ለፓርላማው የሚያቀርብ ይመስል ነበር !!

ማታ አባባ ደውሎ ‹‹አንተ እንዴት በመጀመሪያው ቀን ትጋደማለህ ›› ቢለው 
‹‹አባባ ያደጉትም አገሮች ባንዴ ከእንቅልፋቸው አልነቁም እኮ ›› አለው ..... ፓርላማ ለእረፍት ተዘግቶ ወንድማለም አምሮበት ወዙ ግጥም ብሎ ሲመጣ የመረጠው ህዝብ ግን ዱቄት የነፉበት መስሎና የኑሮ ጫና ደቁሶት ነበር የጠበቀው ፡፡ እናቴ ታዲያ ‹‹ለክቡር ወንድማለም ›› ዶሮ ልትሰራ ጉድ ጉድ ስትል አባባ ‹‹ነግሪያለሁ እንዳትሰሪ›› አለ 

‹‹እንዴ እንዴት ነው የማልሰራው ... በስንት ጊዜው መጥቶ ›› አለች እንባ እየተናነቃት 

‹‹ የህዝቡን ዶሮ ሲበላ ለኖረ እንደገና በደሃ አቅማችን ዶሮ አንሰራም ›› አባባ ነገር አያንዛዛም ..... 

ከዛም ማስታወሻ ደብተሩ ላይ እንዲህ ብሎ ፃፈ ‹‹ዲሞክራሲ ዶሮ መሳይ ቆቅ ናት ብዙሃኑ ስለስጋዋ ጣፋጭነት ስለመረቋ ግሩም ቃና ሰምቶ የሚያሳድዳት ጥቂቶች... ሌሎችን ሳይሆን እራሳቸውን ያሸነፉ ብቻ ላባዋን የሚይዟት ...ዲሞክራሲ ቆቅ ናት ››

No comments:

Post a Comment