Monday, October 7, 2013

ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ይሏታል ጅግራ

ባለፈዉ ዐርብ መስከረም 25 ቀን 2006 ዓ.ም. የወያኔዉ ሎሌ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ አዲስ አበባ ዉስጥ ለአገር ዉስጥና ለዉጭ አገር ጋዜጠኞች በሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በየእሁዱ ለሚጠሩት ሰልፍ ጥበቃ ማድረግና በየእሁዱ ተመሳሳይ ጥያቄ ማድመጥ መንግስትን ከሚገባዉ በላይ ያሰለቸዉ ስለሆነ እነዚህ አንድ አይነት ጥያቄ ያነገቡ ሰልፎች የሚቀጥሉ ከሆነ የተቃዉሞ ሰልፍ ማድረግ ይከለከላል በማለት ጌቶቹና ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች የመብትና የነጻነት ጥያቄ የሚያነሳ ማንንም ሰዉ ለማሰር፤ ለመደብደብና ለመግደል ያላቸዉን እቅድ በግልጽ ተናግሯል። የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ባቀረቡ ቁጥር መሪዎቻቸዉ የሚታሰሩባቸዉ፤ አባላቶቻቸዉ የሚደበደቡባቸዉና ቢሯቸዉ ተሰብሮ ንብረታቸዉ የሚዘረፍባቸዉ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ድርጅቶች አንድም ቀን ሰለቸን ሳይሉ ደብዳቢዉ፤ አሳሪዉና የተቃዋሚ ድርጅቶችን ቢሮ እየሰበረ ንብረታቸዉን የሚዘርፈዉ ወያኔ ሰላማዊ ሰልፍ “ሰለቸኝ” ማለቱ ወያኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚደረግ ምንም አይነት ትግል የሱን የስልጣን “ዘለአለማዊነት” የሚጻረር መስሎ ከታየዉ ምንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ የማይመለስ ፀረ ህዝብ ኃይል መሆኑን እንደገና አረጋግጧል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም ቤት ውስጥ ሆነው ይጠይቁት የነበረውን ጥያቄ አሁን አደባባይ ወጥተዉ መጠየቅ መቻላቸዉ ዲሞክራሲያዊ ስኬት ነው ያለዉ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በሌላ በኩል ደግሞ ሰላማዊ ሰልፍ በችርቻሮ የሚሰጥ የወያኔ ችሮታ ይመስል ሰልፉ በየእሁዱ የሚቀጥል ከሆነ ሰልችቶናልና እንከለክላለን ማለቱ እንደ ግንቦት 7 እምነት ቀድሞዉንም ቢሆን ወያኔ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ ይቻላል ብሎ ፈቃድ የሰጠዉ ለዲሞክራሲ ካለዉ እይታና እራሱ የጻፈዉን ህገ መንግስት ተከትሎ ሳይሆን እርዳታ ሰጪ ምዕራባዉያን አገሮችን ለማስደሰት ብቻ ነዉ።
አገር ዉስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከቅርብ ግዜ ወዲህ የተቀናጀ ትግል ማድረግ በመጀመራቸዉ ክፉኛ የተደናገጠዉ ወያኔ “ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ይሏታል ጅግራ” አንደሚባለዉ እነዚህን ኢትዮጵያ ዉስጥ ፍትህ፤ እኩልነትና፤ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን የሚታገሉትን ፍጹም ህዝባዊና ፍጹም ሰላማዊ የሆኑ ድርጅቶች ለማጥፋት ሰበብ ሲፈልግ የተለመደዉን ግንቦት 7 የሚል ዘፈኑን መዝፈን ጀምሯል። የወያኔ አገዛዝ በአፉ አንደሚናገረዉ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስብና የሚጨነቅ ከሆነ ማድረግ ያለበት ከኢትዮጵያ ህዝብ ለሚቀርብለት ጥያቄ ተገቢዉን ምላሽ መስጠት ብቻ ነዉ። አለዚያ ህዝብ ጥያቄ ባነሳና ለመብቱና ለነጻነቱ በታገለ ቁጥር የሐይማኖት አክራሪዎች፤ የቀድሞ ስርዐት ናፋቂዎች ወይም የግንቦት ሰባት ተከታዮች ናችሁ እያለ ቢያቅራራ እንዲህ አይነቱ የተለመደ የአምባገነኖች ቀረርቱ ያ የማይቀረዉ ክፉ ቀን ሲመጣ ስንቅ እንደማይሆነዉና ከህዝባዊ ቁጣ እንደማያድነዉ ከወዲሁ ሊገነዘብ ይገባል። ደግሞም ግንቦት 7 አላማዉ፤ ለህዝብ ያለዉ ክብርና ለኢትዮጵያ አንድነት ያለዉ ቀናኢነትና የማያወላዉል አቋም በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ በአጭር ግዜ ዉስጥ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አስገኝቶለታልና የወያኔን የዕለት በዕለት አስተዋዋቂነት በፍጹም አይሻም።
ግንቦት 7 አላማዉና ፍላጎቱ እንደ ስሙ ፍትህ፤ ነጻነትና ዲሞክራሲ ነዉና የህዝባዊ ትግላችን አላማ ወያኔንና ዘረኛ ስርዐቱን መደምሰስ ብቻ ሳይሆን አገራችን ዉስጥ የህግ የበላይነት ሰፍኖ ኢትዮጵያ ዛሬም ነገም ከሽብርተኝነት የነጻች አገር አንድትሆን ነዉና ወያኔ ያሰኘሰዉን ቢናገር ወይም እንዳሰኘዉ ቢፎክር ንቅናቄያችን ከዚህ ህዝባዊ አላማዉ ንቅንቅ እንደማይል ለወገንም ለጠላትም ማረጋገጥ ይፈልጋል። ግንቦት 7 የኢትዮጵያና የህዝቦቿ ዋነኛ ጠላት ወያኔ ነዉ ብሎ ያምናል፤ ስለሆነም የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ክንድ ያነጣጠረዉ በዚሁ በዋነኛዉ የህዝብና የአገር ጠላት ላይ ብቻ እንደሆነ ኢትዮጵያዉያንና ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና ብልጽግና የሚመኙ ሁሉ እንዲገነዘቡለት ይፈልጋል።
ግንቦት 7 ህዝባዊ አላማ አንግቦ፤ ግብ አስቀምጦና ወዳስቀመጠዉ ህዝባዊ ግብ የሚያደርሰዉን የትግል ስልት በጥንቃቄ ነድፎ የሚንቀሳቀስ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ነዉ። ግንቦት 7 ወያኔና ዘረኛ ስርዐቱ ተደምስሰዉ ኢትዮጵያ በዜጎቿ ሙሉ ፍላጎትና ፈቃድ ብቻ የምትመራ አገር የመሆኗ ሀቅ የማይቀርና ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል ገድቦ ሊያቆመዉ የማይችል ህዝባዊ ማዕበል ነዉ ብሎ ያምናል። ግንቦት 7 በዚህ አጋጣሚ በየዋህነት ተሳስተዉና ግዜያዊ ጥቅም አታሏቸዉ ከሚንቋቸዉና እንደ ቤት ዉስጥ ዕቃ ከሚጠቀሙባቸዉ ዘረኞች ጋር እጅና ጓንት የሆኑ እንደ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ አይነቶቹ የዋሆች የበደሉትን ህዝብ ይቅርታ ጠይቀዉ ህዝባዊ ትግሉን እንዲቀላቀሉ ወገናዊ ጥሪ ያቀርብላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ግንቦት 7 ባለፉት ሁለት አመታት በተለይም ከወያኔዉ ቁንጮ ሞት በኋላ ከወያኔ ጋር ከፍተኛ ቅራኔ ዉስጥ የገባችሁ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና በድርጅቶቹ ዉስጥ የምትገኙ የኢትዮጵያ ህዝብ ወገኖች ወያኔን ለማስወድ ከዛሬ የተሻለ ግዜ አይመጣምና ኑና በጋራ ጠላታችን ላይ እንዝመት የሚል ህዝባዊ ጥሪዉን ያስተላልፋል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

No comments:

Post a Comment