Thursday, October 10, 2013

ይድረስ ለፕሬዚደንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ

ይሄይስ አእምሮ
ክቡር ፕሬዚደንት ግርማ ሆይ፣
ኢትዮጵያንና “ሕዝቦቿ”ን የሚወዱ ከሆነ ቀጥዬ የምነግርዎትን ከልብ እንዲሰሙኝ በሚያምኑት እለምነዎታለሁ፡፡
ሰሞኑን በጡረታ ሊሰናበቱ እንደሆነ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ዜና ዘገባ ሰማሁ፡፡ በመጀመሪያ ሥራዎን ጨርሰው ለዚህ በመብቃትዎ እንኳን ደስ ያለዎ፡፡ ቀጥዬም በሥራ ዘመንዎ ምን እንደሠሩና እኛ በምናውቅልዎም ሆነ እርስዎ በሚያውቋቸው ምክንያቶች የተነሣ ምን ምን መሥራት ፈልገው ሊሠሩ እንዳልቻሉ “ፕሬዚደንታዊ የሥልጣን ዘመን”ዎን የኋሊዮሽ በማሰብ  ከራስዎ ጋር በምልሰት ለመነጋገር የሚያስችል የማሰላሰያ ጊዜ በማግኘትዎ አሁንም በድጋሚ እንኳን ደስ ያለዎ – መልካም ዕረፍት፡፡ ነገር ግን ከስንብትዎ ጋር በተያያዘ የሰማሁት፣ ክፉኛ ያስደነገጠኝና ማመንም ያቃተኝ አንድ ጉዳይ ስላለ ይህን ማስታወሻ ልጽፍልዎ ተገደድኩ፡፡
 President Girma Wolde-Giorgis
ጡረታ ሲወጡ እንዲኖሩበት መንግሥት የተከራየልዎት ቤት በነዚሁ ሚዲያዎች እንደሰማሁት በርግጥም በወር ብር አራት መቶ ሺ ነው እንዴ???…(የመጀመሪያውና ባለ530 ሺው ቤት ምናልባትም “ስለተወደደ” ሊሆን ይችላል እንደተሰረዘ ሰምቻለሁ፡፡)
የሰማሁት ጉድ እውነት ከሆነ አሁኑኑ ተግባራዊ ሊያደርጉት የሚገባዎ አንድ ምክር ልለግሰዎ፡፡ ይህን የምለው በብዙ ምክንያቶች ነው፡፡ ዋናው ግን የራሴው ምክንያት ነው፡፡ ቤቴን ቢጎበኙ – እርግጠኛ ነኝ – “ይቅርብኝ በራሴው ቤት እኖራለሁ” ይላሉ፡፡
ውድ ፕሬዚደንት ግርማ፣
የኔ ደመወዝ ብር 4200 ነው፡፡ ተቆራርጦ በሚደርሰኝ ብር 3200 አካባቢ አራት ቤተሰቤን ከወር ወር ማድረስ እየተቸገርኩ ውጪ ሀገር ከሚኖሩ የቤተሰባችን አባላት የምደጎምበት ጊዜ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ልጆቼን ከፍዬ ማስተማር ስላቃተኝ ውለው እንዲመጡልኝ ብቻ በመንግሥት ትምህርት ቤት አስገብቻቸዋለሁ፡፡ ወሮችን እንዴት እንደማጋጥማቸው እኔና አንድዬ ብቻ ነን የምናውቅ፡፡ በመላዋ ሀገራችን የተንሠራፋው የኑሮ ውድነት እንኳንስ ከእጅ ወደ አፍ ልንኖር ከፍለን በማንጨርሰው ዕዳ ውስጥ ተነክረንም እንኳን ከአነስተኛ የምግብ አቅርቦትና ከትራንስፖርት ያለፈ ለሌላ ነገር የምናውለው ገንዘብ ሊኖረን አልቻለም፡፡
እንግዲህ ልብ ያድርጉ፡፡ እኔ ሀገሬን ከ30 ዓመታት በላይ በቅንነት አገልግያለሁ፡፡ በትምህርት ረገድም እስከዚህ ባያኮራም ሁለተኛ ዲግሪ አለኝ፡፡ እኔ መኖር አቅቶኝ እንግዲህ ከኔ ደመወዝ በግብር መልክ ለመንግሥት ገቢ ከሚደረግ አነስተኛ የሀገር ሀብት ለእርስዎ የቤት ኪራይ ብቻ ብር አራት መቶ ሺህ ወጪ ሲደረግ ይታይዎት፤ ይህ ድርጊት የግፎች ሁሉ የበላይ ሊሆን የሚገባውና ማሰብ የሚችል ኢትዮጵያዊን ጭንቅላት ሊያፈነዳ የሚችል አስነዋሪ ተግባር ነው፡፡ መንግሥትዎ ይህን ሲያደርግ የራሱ ዓላማ ሊኖረው ይችላል፡፡ ዐብዶም ሆነ ሰክሮ ሊሆን ቢችልም እርስዎ ግን ኃላፊነት ስላለብዎ ይህን ነገር በጭራሽ መቀበል የለብዎትም፡፡ ቢቀበሉት – እግዚአብሔር ምሥክሬ ነው – ከሚጠቀሙበት ይልቅ ይጎዱበታል፤ በጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ የድንቃድንቅ መጽሐፍም በግፈኝነት ይመዘገቡበታል፡፡ ገንዘቡ ትልቅ ሆኖ እንዳይመስልዎ – እኛ ሕዝቡና ሀገሪቱ ሙልጭ የወጣን ድሆች ስለሆን እንጂ፡፡
ልብ እንዲያደርጉልኝ የምፈልገው ሌላ ጉዳይ አለ፡፡ ይሄውም እኔ በወርኃዊ ገቢ ከሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን በእጅጉ የተሻልኩ መሆኔን እንዲረዱልኝና እኔ ‹ሀብታሙ› ዜጋ እንዲህ በመኖርና ባለመኖር መካከል ተሰንቅሬና የኗሪ አኗኗሪ ሆኜ እየተቸገርኩ ሳለሁ ሌላውና ወርኃዊ ገቢው አምስት መቶም የማይደርስና ምንም ገቢ የሌለውም ዜጋ እንዴት አፈር እየጋጠ እንደሚኖር ያስቡት – መቼም አንጎል አለዎ ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህች የመጨረሻ ድሃ ሀገር በግል ጥረታቸው ሀብታም ለሆኑና ጡረታ ለሚወጡ ፕሬዚደንት ይህን ያህል ወጪ ከሀገር ባዶ ካዝና እንዲወጣ ፈቃደኛ መሆን በምድር ባይሆን በሰማይ ያስጠይቃልና አፋጣኝ እርምጃ ወስደው ከሕዝብና ከታሪክ ፍርድ በቶሎ ያምልጡ – ጊዜ አለዎት፡፡ ለሀገር የምንቆረቆር ዜጎች ዛሬ ድምጻችን ባይሰማና ብንታፈን ነገ በምናስመዘግብብዎ ክስ በሥጋም ይሁን በነፍስ እንደሚጎዱ ከአሁኑ ይረዱትና ጤናማ ውሳኔ ይወስኑ፤ በኋላ ለከፍተኛ ፀፀት እንዳይዳረጉ በቅጡ እንዲያስቡበት እማጸንዎታለሁ፡፡ የወያኔው መንግሥት የሚያደርገውን አያውቅምና የሀገርን አነስተኛ ሀብት እያሟጠጠና እያነቀረ ለእንደዚህ ዓይነቱ አስገራሚ ወጪና ለጦር መሣሪያ ግዢ እንዲሁም ለወንበር ጥበቃ ለሚያሰማራቸው የደኅንነትና የፀጥታ ተቋማትና ባልደረቦች ቢከሰክስ የሀገሪቱ ችግር ለሱ ጉዳዩ ባለመሆኑ የመንግሥትን “ችሮታ” ከቀጣይ የአብሮነት ሕይወታችን ለይተው እንዲመለከቱ አሳስብዎታለሁ፡፡ በምንም ይሁን በምን ያገለግሉት የነበረው መንግሥት ሀገሪቱን እንደሀገሩ የማያይ ባዕድ አገዛዝ በመሆኑ ለሀገሪቱና ለዜጎቿ ማሰብ አይችልም – ቢያስብ ኖሮ የሦስት መቶ ብር ደመወዝተኛ ከጉሮሮው እየተነጠቀና በኑሮ ውድነትና በደመወዝ ማነስ ምክንያት በርሀብ አለንጋ እየተገረፈ የወር ደሞዙን ለአባይ ግድብ እንዲሰጥ በሚገደድበት በዚህ አስቸጋሪ የድህነት ዘመን ግፋ ቢል ከአሥርና አሥራ አምስት ሺህ ብር ባለፈ ይህን ያህል ገንዘብ ለኪራይ ብቻ ባልመደበ ነበር – ስለዚህ ዋናው ኃላፊነት የእርስዎ እንጂ የዕብዱ መንግሥት እንዳልሆነ ልጠቁም እፈልጋለሁ፡፡ ገበሬው በርሀብና በርዛት እየተሰቃዬና ባገኘው አቅጣጫ እየተሰደደ፣ የሠራተኛው ደመወዝ ለወር ቀርቶ ለሦስትና አራት ቀናትም እንኳ መሆን አቅቶት ብዙው ሰው ከመደበኛ ሥራው በተደራቢ በልመና ኑሮውን ሊደጉም እየተገደደና ሀገሪቱ በድህነት ሰንጠረዥ በመጨረሻው ተርታ ተቀምጣ እያለ እርስዎ በወር ይህን ያህል ገንዘብ በሚከፈልበት ቤት ውስጥ ለመኖር ቢስማሙ የኢትዮጵያ አምላክ አይለመንዎት፤ ይህን ተማፅኖየን እምቢ ቢሉ ፈጣሪ የሲዖል ወራሽ እንዲያደርግዎ የዘወትር ጸሎቴ ይሆናል፡፡ የዚህ ቤት ባለቤት ቢፈተሸ ምናልባት ከወያኔዎቹ አንዱ እንደሚሆን አልጠራጠርም – በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ለመምታት፡፡ ቤቱ የማንም ይሁን የማን -  ነገር ግን እርስዎን በጭራሽ አይመጥንምና – የሕዝብ አፍም በሥጋም በመንፈስም እያሳደደ ዕረፍት ይነሳዎታልና – ወደፊትም እርስዎ ወይም ልጆችዎና የልጅ ልጆችዎ ዕዳዎትን ለመክፈል ለፍርድ ይቀርቡበታልና ይቅርብዎ፡፡ ከኔ አወረድኩ፤ቀሪው የእርስዎ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment