በኢትዮጵያው ጠ/ሚኒስትር ፊታውራሪነት የአለማቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤትን አሰራር ለመቃወም አፍሪካ መንግስታት በአዲስ አበባ ለአስቸኳይ ስብሰባ መጠራታቸው ታውቋል።ጠ/ሚ ሀይለማርያም ሰሞኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ቀርበው የወንጀል ፍርድ ቤቱን ተችተው ነበር።ይህን ተከትሎ በሚመስል ሁኔታ የወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር መሪዎችን ከጥቅምት 1 እስከ 2 በሚካሄደው ስብሰባ ላይ እንዲገኙ አስቸኳይ ጥሪ አቅርበዋል።
የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ እንዲሁም የሱዳኑ መሪ ፕሬዚዳንት አልበሽር በስልጣን ላይ ያሉ በአለማቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የሚፈለጉ መሪዎች ናቸው።የኬንያው መሪ ቀሪውን የፍርድ ቤት ሂደት በቪዲዮ ለመከታተል ጥያቄ አቅርበው ውሳኔ እየተጠባባቁ ነው።
ኢትዮጵያ የአለማቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ፈራሚ አገር ባትሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን ፍርድ ቤት በማውገዝ ላይ መጠመዷ የኢህአዴግ መንግስትን ያሳሰበው ጉዳይ ሊኖር እንደሚችል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።
በ1997 ምርጫ የኢህአዴግ መንግስት ከ200 በላይ ዜጎችን መግደሉ ፣ ከሺ በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ማቁሰሉ ይታወቃል። በኦጋዴን፣ በጋምቤላና በኦሮምያና በደቡብም እንዲሁ በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ግድያዎች ተፈጽመዋል። በወንጀሉ እስካሁን ተጠያቂ የሆነ የመንግስት ባለስልጣን የለም።የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት በፍርድ ቤቱ ላይ የሚያሳልፉት ውሳኔ ፣ በፍርድ ቤቱ ላይ ተጽኖ ይኖረዋል ተብሎ አይታመንም።
መስከረም ፳፱(ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-
No comments:
Post a Comment