ባለፈው ሰኞ አዲስ ፕሬዚደንት በመምረጥ የዚህን ዓመት ሥራውን የጀመረው የኢትዮጵያ ፓርላማ በፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመ በንባብ የቀረበውን የመንግስት የዚህ ዓመት የትኩረት አቅጣጫና ዕቅድ ጋር በተያያዘ በቀጣይ ሳምንት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት በሚቀርቡ የድጋፍና የተቃውሞ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ይወያያል፡፡ፓርላማው በትላንት ውሎው መስከረም 27 ቀን 2006 ዓም አዲሱ ፕሬዚደንት ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግርን አስመልክቶ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የድጋፍ ሞሽን ማቅረቡ ታውቋል፡፡ ኢህአዴግ በዚሁ ሞሽኑ በፕሬዚደንቱ ንግግር ሙሉ በሙሉ መርካቱን በመግለጽ እደግፈዋለሁ ብሎአል፡፡
በንግግሩ ላይ መካተት ያለባቸው ጉዳዮች ወይም መሰረዝ ያለባቸው ጉዳዮች ካሉ በሞሽን መልክ መቅረብ የሚችሉ ሲሆን በዚህ ረገድ ብቸኛው ተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ የተቃዋሞ ሞሽን ጠ/ሚኒስትሩ በሚገኙበት መድረክ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡በፕሬዚደንቱ ሰፋ ያለ ንግግር ውስጥ በተለይ ምርጫን በተመለከተ ያስቀመጡት እውነታውን የማያሳይ መሆኑን አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ጠቁመው ፕሬዚደንቱ ገና በተሾሙበት ዕለት የውሸት ሪፖርት እንዲያቀርቡ መደረጉ ኢህአዴግ ለሕዝብ ያለውን ንቀት ያሳየበት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ፕሬዚደንቱ በንግግራቸው “ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የማካሄድ አቅማችን ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቶአል፤ በዚህ ረገድ ባለፈው ዓመት የተካሄደው የአካባቢ ምርጫ ሕዝቡ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ በስፋት ሕዝብ የተሳተፈበት፣ ዴሞክራሲያዊ ነበር” ማለታቸው መቶ በመቶ ሐሰት መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረው ወደ 33 የሚጠጉ ፓርቲዎች ከምርጫው ራሳቸውን ባገለለሉበት ሁኔታ፣ ገዥው ፓርቲ ብቻውን ተወዳድሮ አሸነፍኩ ያለበትን ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ካለፉት የተሻለ ነበር መባሉ የሚያሳዝን መሆኑን ተናግረዋ፡፡
ገዥው ፓርቲ የተቃዋሚዎችን እንቅስቃሴ ለማዳከም እያካሄደ ያለው ጸረ ሕገመንግስታዊ አካሄድና አፈና ጉዳይ ላይ ፕሬዚደንቱ በንግግራቸው ምንም አለማለታቸው ገዥው ፓርቲ አሁንም የአፈና መንገዱን ለማጠናከር ማሰቡን አንድ ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ ይህንን ጉዳይ አቶ ግርማ በሚያቀርቡት ሞሽን ይሞግቱታል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ገልጿል።
No comments:
Post a Comment