ሰብአዊ መብት ድርጅቱ ” በማዕከላዊ የሚገኙት መርማሪ ፖሊሶች ታሳሪዎች ጥፋታቸውን እንዲያምኑ፣ እንዲናገሩ ወይም ሌላ መረጃ እንዲያወጡ የሚያደርጉት በሃይል የማስፈራራት መንገድን በመጠቀም ሲሆን ይህም እስከ ማሰቃየት እና ሌላ ጎጂ አያያዝ እስከ መፈጸም ይደርሳል፡፡ ” ብሎአል።ከ2002 ዓም እስከ 2005 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ በማእከላዊ እስር ቤት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በሚዘረዝረው መግለጫ ፣ በእስር ቤቱ ውስጥ ያለፉ ከ35 በላይ ሰዎች ቃለመጠይቆች ተካተውበታል።
“አብዛኛውን ጊዜ እስረኞች ከጠበቃ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናገኙ አይፈቀድላቸውም፡፡ እስረኞቹ የመርማሪዎቹን ፍላጎት ለማሟላት በሚያደርጉት ትብብር መጠን በቅጣት ወይም በማበረታቻ መልክ የውሃ፣የምግብ፣ የመብራት እና የሌሎች አስፈላጊ ነገሮች አቅርቦት ሊከለከሉ ወይንም ሊፈቀድላቸው” እንደሚችል ሪፖርቱ ይጠቅሳል።
በኢትዮጵያ በፖሊስ እና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ስለሚፈጸሙ በዘፈቀደ የማሰር፣ የማሰቃየት እና ጎጂ አያያዝን የተመለከቱ ወቀሳዎችን መስማት አዲስ አለመሆኑን መግለጫው ጠቅሶ፣ ከአወዛጋቢው የ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት፣ የመደራጀት እና የመሰብሰብ መብቶች ላይ የሚያደርገውን ገደብ በማጠናከር ተቃውሞን ለማዳፈን የሚያስችሉ በርካታ እርምጃዎችን መውሰዱን አስታውሷል፡፡ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎችን፣ ጋዜጠኞችን እና ሌሎች ለመንግስት
ያልወገነ ድምፅ የሚያሰሙ ወገኖችን ይዞ ማሰር፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ሥራ እና የመገናኛ ብዙሃን ነፃነትን በእጅጉ የሚገድቡ ህጎችን በሥራ ላይ ማዋል ከማፈኛ ዘዴዎች መካከል ተጠቅሰዋል፡፡
ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው እስረኞች “ በጥፊ፣ በእርግጫ፣ በቦክስ እንዲሁም በብትር እና በሰደፍ መመታታቸውን ፣ የተወሰኑት እጆቻቸውን ከኮርኒስ ጋር ታስረው እንዲንጠለጠሉ አሊያም ደግሞ እጆቻቸው ከጭንቅላታቸው በላይ ታስረው እየተደበደቡ ለረጅም ሰዓታት እንዲቆሙ እንደተደረጉ ” ተናግረዋል።
እጃቸው በሰንሰለት ታስሮ በክፍላቸው ውስጥ ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ እንደሚደረጉና አንድ ሰው ለአምስት ተከታታይ ወራት በዚህ ሁኔታ እንዲቆይ የተደረገበት አጋጣሚ መኖሩ በሪፖርቱ ተመልክቷል።
የማዕከላዊ ሃላፊዎች አስገዳጅ የምርመራ ዘዴዎችን አስከፊ ከሆነው የእስር ሁኔታ ጋር በማዳመር የሚጠቀሙት በታሳሪዎቹ ላይ ያለውን ጫና ለመጨመር እና ታሳሪዎቹ እንዲናገሩ፣ እንዲያምኑ አሊያም ትክክለኛ ሆነም አልሆነ መረጃ እንዲያወጡ
ለማድረግና ከዚያም ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን በወንጀል እንቅስቃሴ ተሳትፈዋል ለማሰኘት ነው።
ሪፖርቱ አንዳንድ ጊዜ በማስፈራራት የተገኘን የእምነት ቃል ታሳሪዎች ከተለቀቁ በኋላ የመንግስት ደጋፊዎች እንዲሆኑ ለማስፈራሪያነት ወይም ደግሞ ፍርድቤት በታሳሪዎቹ ላይ በማስረጃነት እንደሚቀርብ አመልክቷል።
አንዳንዶቹ በእስር በቆዩባቸው ወራት ሙሉ በምንም መልኩከሰው ጋር እንዲገናኙ እንዲሁም በምርመራ ወቅት የህግ ጠበቃ እንዲገኝ አለመደረጉ ፣ በታሳሪዎቹ ላይ የሚፈፀመውን ማንገላታት እንዲጨምር ፣ በመርማሪዎቹ የሚፈጸሙ ጎጂ አያያዞችንና ማሰቃየትን የሚመለከቱ መረጃዎች እንዳይመዘገቡ ፣ እንዲሁም ፍርድ ቤት ይህ ያልተገባ አያያዝ እንዲሻሻል መፍትሔ ሊሰጥ የሚችልበትን እድል እንደሚገድብ አመልክቷል፡፡
በማዕከላዊ የሚገኙ መርማሪ ፖሊሶች በብሔራዊና ዓለማቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጣቸውንና ለታሳሪዎች ሊደረጉ የሚገባቸውን በማስገደድ የተገኘን ቃል በፍርድ ቤት በማስጃነት ከማቅረብ መቆጠብን የመሳሰሉ መሠረታዊ የህግ ጥበቃዎች ተፈጻሚነት እንዳይኖራቸው በዚህ መልክ መሰናክል ይፈጥራሉ ሲል አክሏል።
በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ገለልተኛነት አይንጸባረቅባቸውም የሚለው ሂውማን ራይትስ ወች፣ እስረኞቹ ማዕከላዊ ስለተፈጸሙባቸው የማሰቃየት ድርጊቶች
እና ጎጂ አያያዞች ፍርድ ቤት አቤቱታቸውን ሲያሰሙ አቤቱታ የቀረበላቸው ፍርድ ቤቶች ሁኔታው እንዲስተካከል አጥጋቢ እርምጃ እንደማይወስዱ ገልጿል።
አብዛኞቹ የቀድሞ ታሳሪዎች ወደ ማዕከላዊ ሲመለሱ መርማሪዎቹ ሊያደርሱባቸው የሚችለውን የበቀል እርምጃ በመፍራት ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ስለደረሰባቸው ያልተገባ አያያዝ እንደማይናገሩ ለሂዩማን ራይትስ ዎች ገልፀዋል፡፡ ሌሎቹ ጭራሽ ፍርድ ቤት ቀርበው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ እንዲሻሻል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጅ እንዲሁም የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጆች መሻሻል አለባቸው፡፡
በኢትዮጵያ እውነተኛ ለውጥ የሚመጣው “በደሎቹን የሚፈጽሙት ሰዎች ላይ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እርምጃ ሲወስዱ እና ጥፋተኞች ተጠያቂ እንዳይሆኑ የሚያደርገው የአሰራር ባሕል እንዲወገድ ሲያደርጉ ነው።” በማለት የድርጅቱ አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሌይ ሌፍኮው ገልጸዋል።
ጥቅምት ፰(ስምንት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና
No comments:
Post a Comment