(በፍሬው አበበ)
የኢትዮጵያ ሕገመንግስት ከሚወደስባቸው በርካታ አንቀጾች መካከል የፕሬዚዳንቱን የሥራ ዘመን በሚታወቅ ገደብ መወሰኑ አንዱ ነው። በሕገመንግስቱ አንቀጽ 70 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ የፕሬዚዳንቱ የሥራ ዘመን ስድስት ዓመት እንደሚሆን፤ አንድ ሰው ከሁለት ጊዜያት በላይ ለፕሬዚዳንትነት መመረጥ እንደማይችል ይደነግጋል። ይህ ድንጋጌ ሹመኞች በፍጹማዊ ገደብ የለሽ ሥልጣን እንዳይባልጉ ትልቅ ዋስትናን ይሰጣል። ሕገመንግስቱ በሥራ ላይ ከዋለ በኋላ የመጀመሪያው የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሆነው ያገለገሉትና የህወሃት መሰንጠቅን ተከትሎ በተፈጠረ የፖለቲካ ልዩነት ምክንያት በተሃድሶ አራማጆቹ በእነአቶ መለስ ዜናዊ የመገለልና የመገፋት አደጋ የገጠማቸው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ስንብት አወዛጋቢ ሆኖ መክረሙን እናስታውሰዋለን።
መስከረም 28 ቀን 1994 ዓ.ም
የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ም/ቤቶች የዓመቱን ሥራቸውን በጋራ ጉባዔ በማካሄድ የሚከፍቱበት ዕለት ነበር። ይህ ዕለት ለስድስት ዓመታት በቅንነት፣በታማኝነት አገልግለዋል የተባሉትን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን በክብር በማሰናበት የ77 ዓመት ጡረተኛውን አዛውንት የመቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ወደስልጣን የተሳቡበት ዕለትም ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል። በወቅቱ ከነበሩ ፕሬሶች አንዳንዶቹ የመቶ አለቃ ግርማን ዕድሜ ብቻ በማየት “ኢትዮጽያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ መሪዋን ልትቀብር ነው” የሚሉ ስላቆችን ጭምር አስተናግደዋል። በርግጥም አቶ ግርማ ቃለመሃላ ከፈጸሙ ከሁለት ቀናት በኋላ ታመው ወደጦር ኃይሎች ሆስፒታል የመወሰዳቸው ነገር የጋዜጦቹን አስተያየት ያሟሟቀ ክስተት ነበር።
አቶ ግርማ በተሾሙበት ወቅት የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት መተዳደሪያ አዋጅ መውጣቱና የአዋጁ አንዳንድ አንቀጾች በወቅቱ ከህወሃት/ኢህአዴግ ጋር ክፉኛ ተላትመው ወደጎን በተገፉት የቀድሞ ፕሬዚደንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ልክ የተሰፋ መምሰሉ ሌላው የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ የሳበ ዓቢይ ነጥብ ነበር። ም/ቤቱ በሁለተኛው ዓመት የሥራ ዘመን የመጀመሪያ ልዩ ስብሰባ ላይ ተወያይቶ ያጸደቀው ይህ አዋጅ፤ ቁጥር 255/1994 በመባል ይታወቃል። አዋጁ በሕገመንግስቱ መሰረት ስለሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የተቀመጡትን ድንጋጌዎች አፈጻጸማቸውን በዝርዝር አስቀምጧአል ተብሏል።
በዚህ አዋጅ መሰረት ፕሬዚዳንቱ በአገሪቱ ከሚገኙት የፖለቲካ ኃይሎች ገለልተኛ ሆኖ እንደሚያገለግል በአዋጁ ላይ የተጠቆመ ሲሆን ፕሬዚዳንቱን የሚቀበል ዕጩ ከማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅታዊ ግንኙነት የሌለው መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል በሚል ይደነግጋል።
ተሰናባቹ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንታዊ ተቋም ሕግ አካል ይሆናል። በዚህ መሰረት የቀድሞ ፕሬዚዳንት በሕይወት ዘመኑ ፕሬዚዳንታዊ ተቋሙ ለቆመላቸው ዓላማዎች ተገዥ እንደሚሆን ተመልክቷል።
የቀድሞ ፕሬዚዳንት በሚሰናበትበት ወቅት በመንግስት ወጪ የሚተዳደር አንድ መደበኛ ቤት እንደሚኖረው በአዋጁ ላይ ተቀምጧል። በዚሁ መሰረት የቀድሞ ፕሬዚደንት ወርሃዊ ክፍያ አምስት ሺ ብር ሲሆን (በ1994 ዓ.ም አዋጁ በወጣበት ወቅት መሆኑን ልብ ይሏል) ምክርቤቱ የጊዜውን የኑሮ ውድነት እየተመለከተ እንደሚያሻሽለው ተገልጿል። ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት በመንግሰት ወጪ የግል ደህንነቱን የሚጠብቁ ሰራተኞችና አገልግሎቶችን ያገኛል። ለራሱና ለቤተሰቡ ነጻ የሕክምና አገልግሎቶችም እንደሚሰጡት ደንግጓል።
እንደአዋጁ ድንጋጌ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ከዚህ ዓለም በሞት በሚለይበት ወቅት ወርሃዊ ክፍያው ለባለቤቱና ለአቅመ አዳም ላልደረሱ ልጆቹ ማሳደጊያና መተዳደሪያ ሆኖ እንደሚቀጥል ተመልክቷል።
የቀድሞ ፕሬዚደንት ግዴታዎቹን ሳይወጣ ሲቀር መብቶቹ በሕዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ም/ቤቶች የጋራ ውሳኔ ወይንም በአፈጉባዔዎቹ በሚጠራ ልዩ ስብሰባ በጋራ በሚወሰድ ውሳኔ ሊቋረጥ እንደሚችል ተደንግጓል።(ዶ/ር ነጋሶ በፖለቲካ እሳተፋለሁ በማለታቸው ይህ ድንጋጌ በከፊል ተፈጻሚ እንደሆነባቸው ይታወሳል)
ይህ አዋጅ በድጋሚ ተመርጠው በቀጣይ ሳምንት የ12 ዓመታት የሚኒሊክ ቤተመንግስት የኃላፊነት ሥራቸውን ለሚያጠናቅቁት ለፕሬዚደንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስም የሚሠራ ሲሆን ዘግይቶ በ2001 ዓ.ም የወጣው የመንግስት ባለስልጣናት መብቶችና ጥቅሞች የሚመለከተው አዋጅ ተጨማሪና የተሻለ ጥቅማ ጥቅምን የሚያስገኝላቸው ይሆናል። ከኃላፊነት የተነሱ የሃገርና መንግስት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የምክርቤት አባላትና ዳኞች የሚያገኙዋቸውን መብቶችና ጥቅሞች ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 653/2001 የፕሬዚዳንቱን ጥቅምንም ይዘረዝራል።
የኢፌዲሪ ፕሬዚደንት መተዳደሪያ አዋጅ ቁጥር 255/1994 በጡረታ ላይ ላለ የቀድሞ ፕሬዚደንት የኑሮ ውድነት ደመወዝ ማስተካከያ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተመልክቶ ማሻሻያ ሊያደርግ እንደሚችል ሲደነግግ፤ የአገር መሪዎችና ባለስልጣናትን የሚመለከተው አዋጅ ቁጥር 653/2001 ግን በሥራ ላይ ያለ ፕሬዚደንት የደመወዝ ጭማሪ ባገኘ ቁጥር ጡረታ ላይ ያለውም ወዲያውኑ እንደሚያገኝ በመደንገግ የፓርላማውን ውሳኔ አስፈላጊ አለመሆኑን በተዘዋዋሪ ይጠቁማል።
አዋጅ ቁጥር 653/2001 ልብ ያላሉ በተለይ የማህበራዊ ድረገጽ ታዳሚዎች ፕሬዚደንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በወር 400ሺ ብር ኪራይ የሚከፈልበት መኖሪያ ቤት በመንግስት ወጪ እንደተከራየላቸው ሲሰሙ እሪ ብለዋል። ብዙዎቹ አስተያየት ሰጪዎች “በደሃ አገር ይህ ሁሉ ቅንጦት አልበዛም ወይ” በማለት ጥያቄ በመጫር የተጋነነ የቤት ኪራይ ክፍያውን የኬንያ ፓርላማ በአንድ ወቅት ለራሱ በገፍ ከጨመረው ወፍራም ደመወዝ ጋር አነጻጽረውታል። በተቃራኒው የቆሙ ወገኖች “ለአገር የሠራ መሪ ሲያንሰው ነው” በማለት ትችቶቹን ለመመከት ሲጥሩ ታይተዋል። ይህም ሆኖ ግን አዋጅ ቁጥር 653/2001 ከኃላፊነቱ ለተነሳ ፕሬዚደንት የሚሰጠውን ዳጎስ ያለ ጥቅማጥቅም ይዘረዝራል። አዋጁ እንደሚደነግገው ከኃላፊነቱ የተነሳ ፕሬዚደንት በሥራ ላይ እያለ የሚከፈለው ደመወዝና አበል ከኃላፊነቱ ሲነሳም አይቋረጥም።
በተጨማሪም በመንግስት ወጪ የሚተዳደር ለራሱና ለቤተሰቡ መኖሪያነት የሚያገለግል ከአራት እስከአምስት መኝታ ቤቶችን የያዘ ቤት የሠራተኞች ደመወዝን ጨምሮ ያገኛል። የህክምና አገልግሎት በመንግስት ሙሉ ወጪ በአገር ውስጥና በውጪ አገር የሚያገኝ ሲሆን ሕክምናው በአገር ውስጥ ከሆነ በአንደኛ ማዕረግ እንዲያገኝ ይደረጋል።
ተሰናባቹ ፕሬዚደንት በመንግስት ወጪ የግል ደህንነቱን የሚጠብቁ ሠራተኞች አገልግሎት ያገኛል። የዲፕሎማቲክ ፓስፖርትና የቪአይፒ አገልግሎትን ጨምሮ ቀድሞ የነበረውን ኃላፊነት የሚመጥን በአገር ውስጥና በውጪ አገር ሙሉ የፕሮቶኮል አገልግሎትን ያገኛል።
ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ደረጃቸውን የጠበቁ ሶስት ተሸከርካሪዎች ከእነሾፌሩ፣ከነዳጅና ጥገና አገልግሎት ጋር እንዲያገኝ ይደረጋል። ለራሱ ሁለት መደበኛ ስልኮችና አንድ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ለጥበቃ አገልግሎት የሚውሉ ስልኮች ይኖሩታል። በሕዝባዊ አገልግሎት ላይ ከተሰማራ መኖሪያ ቤቱ በሚገኝበት ከተማ የቢሮ አገልግሎት ይሰጠዋል። እንዲሁም ባለመብቱ የሚመርጣቸው አንድ ጸሐፊና አንድ ባለሙያ ወርሃዊ ክፍያ በመንግስት ይፈጸማል። ለቢሮው የሚያስፈልጉ ስልክ፣ኢንተርኔት፣የኮምፒውተርና የፖስታ አገልግሎቶችን መንግስት ያሟላል፤ ክፍያቸውንም ይፈጽማል። ባለመብቱ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ የጀመረው ሕዝባዊ አገልግሎት እስኪጠናቀቅ ለአምስት ዓመት ቤተሰቦቹ ቢሮውን ሊገለገሉበት እንደሚችሉ አዋጁ ጠቁሞ ባለመብቱ የተሰጠው ቢሮ ከሕዝባዊ አገልግሎት ውጪ ለሆኑ ሥራዎች ካዋለው አገልግሎቱ እንደሚቋረጥ ደንግጓል።
ተሰናባቹ ፕሬዚደንት ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ (የሰይጣን ጆሮ ይደፈን!) በመንግስታዊ ሥነሥርዓት የቀብሩ ሂደት ይፈጸማል፤ የአንድ ቀን የሐዘን ቀን ይታወጃል፤ የባለመብቱ የግል ወጪ (አበል) ለባለቤቱ ክፍያው ይቀጥላል፤ ባለቤቱ በሞት ከተለየች ክፍያው ሃያ አንድ ዓመት ላልሞላቸው ልጆቹ መከፈል ይቀጥላል። (ፕሬዚዳንት ግርማ ግን 21 ዓመት ያልሞላው ልጅ አላቸው እንዴ? ከሌላቸው ለማን እንደሚተላለፍ በአዋጁ አልተጠቀሰም) የባለመብቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ለቤተሰቡ የሚሰጡትን የመኖሪያ ቤት ፣የሕክምና እና የግል ደህንነት ጥበቃ አገልግሎቶችን አያስቀርም። ይህ አዋጅ በተመሳሳይ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ይመለከታል። (የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስም ቤተሰቦች የዚህ አዋጅ ተጠቃሚ መሆናቸውን ልብ ይሏል)
ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ሉጫ ማንናቸው
መስከረም 28 ቀን 1994 ዓ.ም የፕሬዚደንትነት ሥልጣናቸው በኢህአዴግ ታጭተው በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ም/ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ መንበሩን ከቀድሞ አቻቸው ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በይፋ የተረከቡት የመቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በተሾሙበት ወቅት በግል የፓርላማ ተመራጭ ነበሩ። በወቅቱ ስለአቶ ግርማ ግለታሪክ በንባብ ያሰሙት ኢህአዴግን በመወከል ዶ/ር ካሱ ኢላላ ነበሩ። ዶ/ሩ በዚሁ ንግግራቸው የመቶ አለቃ ግርማ በአገር ውስጥና በውጪ አገር ከፍተኛ ትምህርት መከታተላቸውን ከመጥቀስ ውጪ ስለትምህርታቸው በዝርዝር የገለጹት ነገር የለም። ፕሬዚዳንት ግርማ ኤርትራ በፌዴሬሽን ስትተዳደር በነበረበት ወቅት የሲቪል አቪየሺን ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል። በተጨማሪም በ1959 ዓ.ም የኢትዮጽያ ሲቪል አቪየሽን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከማገልገላቸውም በላይ በአየር መንገድ በቦርድ አባልነት አገልግለዋል።
የኢትዮጽያ የንግድ ኢንዱስትሪና ፕላን ሚኒስቴር ተብሎ በተቋቋመው መ/ቤት ዋና ዳይሬክተር በመሆን መስራታቸውን ዶ/ር ካሱ በወቅቱ ካቀረቡት ማብራሪያ ለመረዳት ይቻላል። አቶ ግርማ ከመንግስት ሥራ ከተሰናበቱ በኋላ በአዲስአበባ ከተማ ለፓርላማ አባልነት ተወዳድረው መመረጣቸውን፣ በም/ቤቱም ለሶስት ጊዜያት ያህል በፕሬዚዳንትነት እንዲሁም በወቅቱ 52ኛው የዓለም ፓርላማ ምክትል ፕሬዚደንትነት ተመርጠው አገልግለዋል።
ፕሬዚደንት ግርማ በቋንቋ ችሎታቸው የሚያውቋቸው ሁሉ ያደንቋቸዋል። ከአገር ውስጥ አማርኛን ጨምሮ ትግርኛ፣ አሮምኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ። ከውጪ አገር እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ጣሊያንኛ ስለሚናገሩ በተለይ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶችና ሰዎች ጋር ሲገናኙ እንደዋዛ ቋንቋውን እንደመኪና ማርሽ ቀየር ማድረጋቸው አድናቆትን አትርፎላቸዋል።
ፕሬዚደንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የፊታችን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2006 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ም/ቤቶች የዚህ ዓመት መክፈቻ የጋራ ስብሰባ በሚካሄድ ሥነሥርዓት ላይ የ12 ዓመታት በትረ ሥልጣናቸውን ለተተኪያቸው አስረክበው በ90 ዓመታቸው የጡረታ ሕይወታቸውን ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
No comments:
Post a Comment