***አንዱ የኣንድነታችን መገለጫ የጋራ ታሪካችን ነዉ***
#ሰብኣዊ
በተለምዶ ያ ትውልድ እያልን የምንጠራው ቀዳሚው ትውልድ ኣንድ የሆነ ሼል ሰብሮ የወጣ ነበር። ያ ትውልድ ለዘመናት የነበረውን ዘውዳዊ ኣገዛዝ ደፍሮ የጠየቀ፣ የፍትህና የእኩልነትን ጥያቄዎች ኣንግቦ ግንባሩን ለጥይት የሰጠ በመሆኑ ታሪክ ሁልጊዜም ያ ትውልድ……….እያለ ሲያስታውሰው እንዲሁ ይኖራል።
ያ ትውልድ የሆነ ሼል ሰብሮ ሲወጣ ፍትህና እኩልነት እንደ እንጀራና ውሃ ለሰው ልጅ ያስፈልጋሉ ብሎ ያመነ እንደነበር መረዳት እንችላለን። ያ ትውልድ ለበሩለት ለነዚህ ቁልፍ ጉዳዩች ታላቅ ንቅናቄን ኣድርጓል። ይሁን እንጂ ፍትህና እኩልነት የሚበየኑበት ወይም መሬት ላይ ወርደው የሚከፋፈሉበት ሜካኒዝም በሚገባ ማጤን ተገቢ ነበረና ያ ትውልድ ይህን ሃላፊነትም ተሸክሞ ነበር። የዘውዳዊው ኣገዛዝ ማክተሙ ብቻ ሳይሆን ፍትህ እንዴት በኢትዮጵያ ሁኔታ ይበየናል? የሚለው ጉዳይ ታላቅ የቤት ስራ ነበር።
የታሪክ ኣጋጣሚ ሆነና በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የግራው ዘመም ኣስተሳሰብ ኢትዮጵያን ተጭኖ ስለነበር ፍትህና እኩልነት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩበትን ወይም የሚተረጎሙበትን መነጽር በወጣቶች ላይ ኣደረገ። ንጹህ ኣይምሮ ይዘው ፍትህና እኩልነትን ያነሱ ወጣቶች የፍትህና የእኩልነትን ትርጓሜ ሶሻሊዝም ባጠለቀላቸው መነጽር ማየት ጀመሩ። ሳይንሳዊ መሆኑ ብዙ ልባቸውን የማረካቸው ወጣቶች ፍትህን እና አኩልነትን በወል የማየትና የመተርጎም ኣስተሳሰብ ሰረጻቸው። ከፍ ሲል እንዳልነው ኣማራጭ የኣስተሳሰብ ዘየ ባለማየሉ እነዚህን ጥያቄዎቻቸውን በነሲብ እንዲያዩ ስላደረጋቸው ይህ ዝንባሌ በተፈጥሮ በቋንቋና ባህል ተቦድኖ ባለው ቡድን ላይ የፖለቲካ ኣይናቸው እንዲያርፍ ኣቀብሎ ሰጣቸው። ችግሩን የስርዓት ኣድርጎ ከማየት በላይ የብሄር ጥያቄ በማንሳት ፍትህ በኢትዮጵያ የሚበየንልን ብሄሮች እኩል ሲሆኑ ነው የሚል ኣስተሳሰብ በሃይል ሰረጸ።
እንግዲህ አንድ ነን ስንል አንዱ የኣንድነታችን መገለጫ የጋራ ታሪካችን ነዉ፡፡ አጼ ምኒልክ በአድዋ ጦርነት ጊዜ ድል ካደረጉ በኃላ የዘመተዉን ወታደር በብሄር ስታትስቲክስ ሰርተዉ ይህን ያህል ኦሮሞ፣ ይህን ያህል አማራ፣ ይህን ያህል ትግሬ ወዘተ ብለዉ መዝገብ አላስቀመጡልንም፡፡ ድሉ የሁላችን የኢትዮጵያዊያን ነዉ፡፡ ለዚህ ድል ወታደሩ ብቻ ሳይሆን ቀረጥ ሲከፍል የነበረዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ፣ በኢትዮጵያ ግዛት ዉስጥ (Jurisdiction) የነበረዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ድሉ ነዉ፡፡ ሌሎች ቁሳዊና መንፈሳዊ ታሪኮቻችን ሁሉ የጋራ ታሪካችን መሆናቸዉን ስንቀበል ስንስማማ ነዉ አንዱ የአንድነት መገለጫ፡፡ ሌላዉ ሁለተኛዉ ደግሞ መሬት ሲሆን ሁላችን ቡድኖች የተፈጠርንበትን መሬት ሁሉ አገጣጥመን የሰራናት ይህቺ አንዲት ዉብ ኢትዮጵያ አንድ ስትሆን በዚህም ነዉ አንድነታችን የሚገለጸዉ፡፡ ሌላዉ ሶስተኛዉ ፍትህና እኩልነት ሲሆን ሁላችን እኩል ስንሆን፣ በብሄሮች መካከል ትልቅና ትንሽ ሲጠፋ አንድነታችን በዚህም ይገለጻል፡፡ በእዉነተኛ ዴሞክራሲ ፊት ትልቅና ትንሽ ብሄር አይኖርም፡፡ ሌላዉ አራተኛዉና ከዚህ ርዕስ ጋር በቀጥታ የሚያያዘዉ የጋራ እሴት ግንባታዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ አንግዲህ እነዚህ ብዙ ብሄሮች ያሏቸዉን ጥበቦች እያዋጡ በጋራ የሚሰሩበት ባህል ሄዶ ሄዶ የጋራ ባህላቸዉን እያበዛ ተግባቦታቸዉን እየጨመረ ሲሄድ አንድነታቸዉም እንደዚያዉ እየጠነከረ ይመጣል፡፡ በስምምነት ላይ የተመሰረተ የባህል ዉህደት ለማድረግ ብሄሮች ሲስማሙና ኪዳን ሲገቡ አንዱ የሚሆነዉ ነገር ብሄሮች ሁሉ ቋንቋቸዉንና ባህላቸዉን ለጋራዋ አገራቸዉ ለኢትዮጵያ መስዋዕት ያደርጋሉ፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
ከሰብኣዊ
No comments:
Post a Comment