Saturday, October 12, 2013

ኢህአዴግን እከስሳለሁ

ደራሲ፤ ዓለማየሁ ገላጋይ
ቅኝት፤ መስፍን ማሞ ተሰማ
1መንደርደሪያ
ሰቀቀን ጭንቀታቸውን እንደ ተጋቦ የሚያጋቡ፤ ግፍና በደሉን ጠኔና
ጣዕሩን እንደ ሾተል አሹለው፤ ከልብ የሚቸክሉ ከአእምሮ ጓዳ
የሚቀብሩ፤ አዝነው የሚያሳዝኑ፤ ተቃጥለው የሚያሳርሩ…ፍትህ
ተሟጋች፤ ነፃነት ተፋራጅ፤ ጧፍ ነዳጅ...ደራሲያን፤ ቀመረ ቃላት
ጠቢባን…ቢኖሩም…የብዕር ትሩፋታቸው ጨለማን ተጋፍቶ ጨለማን
ተዋግቶ የወጣው - ‘ኢምንቱ’ ነው። እነርሱም ቢሆኑ ታዲያ፤ በጨለማ
እንደሚተኮስ ርችት ወጋጋናቸው አድማስ ካድመስ የሚያሳይ ብርሃን
ሆኗልና፤ እሰየው!!

ከዳፍንት ጨለማው እየቀለጡ ከበሩ፤ እየበሩ ከቀለጡ…ደራሲያኑ
አንዱ፤ ኢህአዴግን ከሳሹ ኢህአዴግን ተሟጋቹ ዓለማየሁ ገላጋይ ነው፤
የሠላማዊ ትግሉ ብዕረተኛ አርበኛ። (የሠላማዊ ትግል ብዕረተኛ፤ ከተነሳ
አርበኛ፤ ይጠቅሷል አብነት - እስክንድር ነጋን፤ ፕሮፌሰር መስፍን
ወልደማርያምን፤ ርዕዮት አለሙን፤ ተመስገን ደሳለኝን እና…በርካቶችን)
ኢህአዴግን እከስሳለሁ - በህወሃት ኢህአዴግ ቀንበር ለአመታት
ተቀንብሮ በወላፈኑ ውስጥ እየኖረ የተለበለበ፤ እንደ ህዝብ መራራውን
የስቃይ ገፈት የተጋተ፤ እየተገረፈ፤ እየተንገላታ…የኑሮን አበሳ ያረሰ፤ በብዕር ልሳን ማሳውን የማሰ፤ የደም ብዕር
እንጥፍጣፊ - የፍትህ ያለህ! የባንዲራ ያለህ! የሀገር ያለህ! የህዝብ ያለህ!...የሚል ከማዶ ማዶ የሚያስተጋባ፤
የትውልድና የሀገር እሪታ…የሠላማዊ ትግሉ እንቢልታ!!
በ2004 ዓ/ም በወርሃ ነሀሴ የታተመው ‘ኢህአዴግን እከስሳለሁ’ በ231 ገፆች በአራት አብይ ክፍሎች ሰላሳ
ስድስት መጣጥፎችን ያካተት መድብል ነው። ‘ኢህአዴግን እከስሳለሁ’ በአንድ ጀንበር እንደውም በተከታታይ
ጀንበሮችም ቢሆን እንደዋዛ የሚጨርሱት መፅሀፍ አይደለም። ሰላሳ ስድስቱ መጣጥፎች አቀበትን የመውጣት
ያህል የሚያደክሙ ወይም የውስጣዊ ደዌን ጥዝጣዜ ለማስታገስ የሚጨነቁትን ያህል የሚያስጨንቁ ናቸውና
ነው እያረፉ አልያም እያዘገሙ ራስንም እያስታመሙ ይነበቡ ዘንዳ ግድ እሚሉት።
ይህቺ መፅሀፍ አሻራን ይዞ ያለመቀበር ፍጭርጭሮሽ ናት። በዚህች መፅሀፍ የምበትናቸው የልቤን ዘገርና
ዘር፤ ከዘመንና ከፖለቲካ ሁኔታ የተቀበልኩት ነው...ይለናል ደራሲው የልቡን ዘገር የዘር ቋጠሮ በበተነበት
መድብሉ መግቢያ።
ከህይወት የተቀዳውን የልቡን ዘገር የዘር ቋጠሮ ዘመንና ፖለቲካ እንደምን ፀንሰው እንደምን እንደወለዱት
ሲያረዳን፤ ተወልጄ ያደግሁት ባሻ ወልዴ ችሎት አካባቢ ነው። ባሻ ወልዴ ችሎት ጉብታ ላይ የተንሰራፋው
የምኒልክ ቤተ መንግሥት ግርጌ ከተኮለኮሉት ጎስቋላ ሰፈሮች አንዷ ነበረች። ይህቺ ሰፈር ነዋሪዎቿን እንደ
ታቀፈች ፖለቲካ ሰራሽ በሆነ በሽታ ወድቃ፤ ቃትታና አጣጥራ ስትሞት አብሬያት ነበርኩ…
የዚህ ዘመን ፖለቲካ ሰለባ መሆኔን የተረዳሁት እጅግ ዘግይቼ ነበር። እንደውም እንደአድፋጭ በሽታ
ሲለክፈኝ ሳይሆን ሲጥለኝ ነበር መጠቃቴን የደረስኩበት... ይላል ዓለማየሁ።
ዓለማየሁ የሚነግረን የልቡ ዘገር ዘር አሻርን ይዞ ያለመቀበር ፍጭርጭሮሹ እንደ ድንገተኛ መርፌ ሥጋችንን
ዘልቆ የሚጠቀጥቀን ገና ከመግቢያው ስለ ባሻ ወልዴ ችሎት ሰፈር የውሻ ሞት አሟሟት ሲያረዳን ነው። ከባሻ
ወልዴ ችሎት ሰፈር ነዋሪዎች ጋር የተንከራታች ውሻ ሞት ሞቻለሁ - ይላልና። ባሻ ወልዴ ችሎት ሰፈርን
አናውቀው ይሆናል። ባናውቀውም ግዴለም። የተወለደበት መንደር ሰፈርና ነዋሪዎች አካል ያልሆነ የለምና ባሻ
ወልዴን ሰፈር ራሳችን በተወለድንበትና ባደግንበት ሰፈር ስም ለውጠን የቤተሰባችንን፤ የጎረቤቶቻችንን፤
2
የጓደኞቻችንን፤ የመንደሩንና የአካባቢውን ነዋሪዎችና ህይወት በእዝነ ልቦናችን ይዘን…በፖለቲካ በሽታ ታመው
የውሻ ሞት ሲሞቱ፤ ሰፈሩ አሻራው ሲጠፋ፤ ነዋሪው ሲበተን እንይ።…ምን ተሰማን?
ለመሆኑ የውሻ ሞት መሞት እንዴት ነው? የሚያክመው ወይ የሚያስጠጋው አጥቶ ዙሪያ ገባውን
እንደተዋከበ፤ እንደተንከራተተ…ክልትው ማለት ነው፤ የውሻ ሞት። ስንትና ስንት ባሻ ወልዴ ችሎት ሰፈሮች
የውሻ ሞት ሞተዋል? ስንትና ስንት ነዋሪዎች ተወልደው ካደጉበት፤ አድገው ከተዋለዱበት…ሰፈር (በከተማም
ይሁን በገጠር) በፖለቲካው በሽታ ታመው እንደ ውሻ ተዋክበው ከቀያቸው ተባረዋል? የት ናቸው? እንዴት
ናቸው?...
ዓለማየሁ እንዲህ ይላል በመግቢያው፤
ከአራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት ጋር ወድቄ ስቃትትና ሳጣጥር...ለእብደት የሚዳርግ የውስጥ መብሰልሰሌን
ለእናንተ የማጋራበት ዕድሉ ተፈጠረልኝ። ለአንድ ዓመትም በየሳምንቱ ፈሰሱ...ይለናል ‘እግዚኦታውን’
ካቀረበበትና እሱን መሰሉ የነፃነትና የፍትህ የሠላማዊ ትግሉ ብዕረተኛ አርበኛ ከሆነው የፍትህ ጋዜጣ አዘጋጅ
ተመስገን ደሳለኝ ጋር ስለተገናኘበት አጋጣሚ ሲያወሳ።
በምድረ ኢትዮጵያ እየወረደ ባለው ሠይፍ የህዝብን ዋይታና ሰቆቃ ‘አቤት!’ ብሎ ባስተጋባው የፍትህ
ጋዜጣም ላይ ሰይፉ ሲሰነዘርና ፍትህ ሲሰየፍ ዓለማየሁም የልቡን ዘገር ዘር የበተነባቸውን መጣጥፎቹን
አሰባስቦ ‘ኢህአዴግን እከስሳለሁ’ አለ...
እነሆ በብዕር ልሳን ስርቅርቅታ፤ ከዐይን ሳይሆን ከልብ ደም ጠብታ፤ አጣቅሶ - ለውሶ፤ ያደለበውን የክስ
መድብል በየፈርጁ በርዕስ እየፈረጅንና እያንሰናሰልን እንደሚከተለው እንቃኛለን...
ወይ ሀገር! ወይ ህዝብ! ወይ ገዢ!
1. የቄሳሩ ‘ልማታዊ’ መንግሥትና የህወሃት/ኢህአዴግ ‘ልማታዊ’ መንግሥት
የኢትዮጵያውያን ታሪክ ከገዢዎቻቸው ህልም በስተጀርባ አገራቸውን የመፈለግ መማሰን ነው። የጦርነት
ህልም፤ የመንፈሳዊነት ህልም፤ የልማት ህልም። ስለሀገር ፤ በሀገር፤ ለሀገር ከሆነ ኢትዮጵያውያን የትኛውንም
መከራ ታጋሾች ናቸው። ታዲያ ምነው ዛሬ? ታዲያ ምንነው አሁን? ታዲያ ምነው በዚህ ትውልድ?...ሰፈር
ልቀቁ ስንባል ያጥወለውለናል፤ አዋጡ ስንባል ያመናል፤ ቦንድ ግዙ ስንባል ደም ያስተፋናል። ለምን?...
ይራበን፤ ይጥማን፤ እንታረዝ። ይሄ ችግራችን ሀገር ቅልቅል፤ ባንዲራ ቅይጥና ሉዐላዊ ድብልቅ ከሆነ
እንታገስ አልነበር? ታዲያ አሁን ‘ተገነባ’ ሲባል የማይሞቀን፤ ‘ተደነባ’ ሲባል የማይበርደን ስለምን ነው? እንኳን
ተገንብቶ እስኪገነባ አላስችል ብሎን ገዢዎቻችን ፊት ቀርበን አቤት እንል አልነበር?...
ታዲያ አሁን ሳይጠየቅ አገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ጋር ለመደባለቅ የተነሳ መንግሥት እንዴት
ሙሉ ድጋፍ ያጣል? እንደምንስ እምነት ይነፈጋል?...በማለት ይጠይቃል ዓለማየሁ።
ዓለማየሁ በስታትስቲክስ ድርድር ወይም በኢኮኖሚስት ቀመር ትንተና ወይም በፖለቲካ ልሂቅ አሰልቺ
ዲስኩር አይደለም የክስ መዝገቡን የሚዘረዝረው፤ የሚያበራየው። በህዝብ ህይወት፤ በህዝብ ተስፋ፤ በህዝብ
ሰቆቃ፤ በህዝብ ሚዛን፤ በህዝብ ልሳን ለህዝብ ብይን እንጂ።
እንቀጥል፤
በኢትዮጵያ ውስጥ ድጋፍ የተነፈገው፤ ዕምነት ያልተጣለበት ‘ልማታዊ’ መንግሥት አንድ ብቻ ነበር።
አንጡራ ኢትዮጵያዊ ችላ ያለው ልማት፤ ችላ ያለው ድህነት ማጥፋት፤ ችላ ያለው የመልካም አስተዳደር ሥራ
ነበር። ያ ‘ልማታዊ መንግሥት’ የፋሽስት ኢጣሊያ አገዛዝ ነበር…በማለት ዓለማየሁ አንጥቦ የንፅፅሮሹ
መንደርደሪያ የሆነውን የታሪክ ውርዴ ከታሪክ ሲያወራርድ እንዲህ ይላል።
“የቄሳር መንግሥት መልዕክተኛ” የተባለው የፋሽስት ጋዜጣ ጥር 25 ቀን 1933 ዓ/ም ባወጣው ዕትሙ
የሚከተለውን ለኢትዮጵያ ህዝብ አስተላልፎ ነበር፤
3
ስሙ፤ ስሙ፤ ስሙ፤ በእግዚአብሄር ፈቃድና ቸርነት ሃያሉ የኢጣሊያ መንግሥት ኢትዮጵያን ከያዘ ዛሬ
አምስተኛ ዓመት ነው። በዚህ አምስት ዓመት ውስጥ የተሰራው ቤት፤ መንገድ፤ ድልድይ፤ የተማሪ ቤት፤
ኤሌክትሪክና የመታከሚያ ቤቶች ሌላውም የተሰራው ሥራ ብዙህ ነው። የኢጣሊያ...መንግሥት ለገንዘቡ
አይሰስትም። ህዝብ እንዲበለጥግና ሀገር እንዲለማ ነው የሚፈልግ። በኢትዮጵያ መንግሥት ጊዜያት ግን ድሃን
እያስለቀሱ ገንዘብ መቀማት፤ ማሰር፤ መፍታት ነበር ሥራቸው። ለድሃው ትንሽ አያዝኑለትም ነበር። የኢጣሊያ
መንግሥት ለቸርነቱ ወሰን የለውምና ለወደፊቱም ለሥራና ለተቸገረው ሰው መርጃ እንዲሆን ብሎ ከባንክ
ያስቀመጠው ገንዘብ ብዙህ ሚሊአርድ ነው። እናንተም የኢትዮጵያ ልጆች በቅንነት መንግሥትን ካገለገላችሁ
ጥቅሙን ወደፊት ታገኙታላችሁ።…ለጊዜውም ባላገሩ ሰርቶ እንዳይበላ፤ ነጋዴውም እንደልቡ እንዳይነግድ ዋና
ጠላት የሆኑት ሽፍቶቹ (አርበኞቹ ማለቱ ነው) ናቸው። እነሱ ሲጠፉ ወይም ወደ መንግሥት በገቡ ጊዜያት
የኢትዮጵያን ማማር፤ የህዝቡን መበልጠግ በዚያን ጊዜያት ታዩታላችሁ።
‘ድንቅነሽ የአንኮበር ቅጠል፤ ከማቃጠልሽ የመለብለብሽ’ አሉ! ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የያዝኩት
በእግዚአብሄር ፈቃድና ቸርነት ነው አለችና አረፈችው። ይባስ ብላም የነፃነት፤ የባንዲራና የሉዐላዊነት
ተፋላሚዎቹን ፤አርበኞቹን ጠላቶቻችሁ ናቸው ስትል መርዛማ ፕሮፓጋንዳዋን በቄሳር መልዕክተኛ ጋዜጣዋ
አርበኞቹን በጉያው ላቀፈው የኢትዮጵያ ህዝብ ለፈፈች። ልብና ጆሮ ግን ተነፈገች።
ፋሽስት ኢጣሊያ መርዝ ጋዝ እንደ ዝናም አዝንማ፤ አያሌ ኢትዮጵያውያንን በመትረየስ ረሽና፤ በቁጥጥር
ስር ባዋለቻት ኢትዮጵያ የድል በአሏን ስታከብር…’ልማታዊ መንግሥት’ ነኝና ከድንቁርና ከጨለማ፤ ከሁዋላ
ቀርነት ከድህነት ነፃ እየወጣችሁ ነውና፤ ‘አሜን!’ ብላችሁ ፀጥ ብላችሁ ብትገዙ፤ ጥቅሙ ለእናንተ እንጂ እኛማ
ምን አጣንና?...ታዲያ እንዳትበለጥጉ፤ እንዳታድጉ እንዳትመነደጉ፤ እንቅፋት ሆነው ያስቸገሩ፤ ነፃነት፤ ባንዲራ፤
ሉዐላዊነት፤ ኢትዮጵያዊነት፤ ‘ገለመሌ’ የሚሉ አርበኞቹ…የልማት ጠንቆች ሽብርተኞች ናቸውና፤ የእነሱ
መጥፋት የእናንተ መልማት መሆኑን እወቁ - ነበር መልዕክቱ፤ የቄሳሩ።
ዓለማየሁ የቄሳሩን መልዕክት እንዲህ ሲል ያበራያል፤
ኢትዮጵያውያን ከፋሽስት ኢጣሊያ የሚሹት ምን ነበር? የቤት ግንባታ? የመንገድ ሥራ? የድልድይ ማቆም?
የተማሪ ቤት? የኤሌክትሪክና የመታከሚያ ቤቶች ማቋቋም?...አልነበረም! የተጣሰው ድንበር ወደነበረበት
እንዲመለስ፤ የወደቀው ባንዲራ እንዲነሳ፤ የፈረሰው መንግሥት እንዲቋቋም ነው። እነዚህ ነገሮች ከግምት
ባይገቡ ከኢጣሊያ የተሻለ “ልማታዊ መንግሥት” ከየት ሊገኝ? አምስት ዓመት የገነባው ሃምሳ ዓመት
አላንደረደረንም? ይለናል ብዕረተኛው አርበኛ።
አዎ ሀቅ ነው! የየትኛውም ሀገር ዜጋ፤ በየትኛውም ዐይነት የዕድገት እርከን ላይ ይሁን፤ በማንኛውም ዐይነት
ቅኝ ገዢ ወይም ሀገር በቀል መንግሥት ይገዛ - በገዛ ሀገሩ ዜግነቱ ተዋርዶ በሀገሩ ባይተዋር ከሆነ፤ ታሪኩ
ተንቋሾ በታሪኩ እንዲያፍር ከተደረገ፤ የማንነቱ መለያ፤ ሀገራዊ መታወቂያ ዓርማው፤ ባንዲራው
ከተዋረደ…በዳር ድንበሩ መዘዋወሩ፤ ባይተዋርነት መጤነት፤ ከሆነበት - የእድገት ትርጉሙ የልማት ውጤቱ፤
ለእርሱ ሁሉ ከንቱ! ለዚህም ነው አብናቶች በተምሳሌ ሲያስረዱ፤
ሰው ባገሩ ቢበላ ሳር፤ ቢበላ መቅመቆ
ይከበር የለም ወይ ሰውነቱ ታውቆ፤ ማለታቸው።
እነሆ ደግሞ ቀጣዩን የዓለማየሁ ነቁጥ በአፅንዖት ያነቧል፤
በሀገር ስም ሀገር ላይ ስለተሰራ ሀገርን ይወክላል ማለት እንዳልሆነ አንጡራው ኢትዮጵያዊ ያኔም
ተረድቶታል። ይራበን፤ ይጥማን፤ እንታረዝ። ይሄ ችግራችን ሀገር ቅልቅል፤ ባንዲራ ቅይጥና ሉዐላዊነት
ድብልቅ ከሆነ እንታገሳለን። ሀገር የጠገቡት ዜጎቿ ብቻ ነች የሚል ድምዳሜ የለንም። የተራቡትም ነች።
መጥገቢያ ብቻ ሳትሆን መራቢያና መጠሚያ መሆኗ አይጠፋንም። የድሎት ገነት ትሁን አይወጣንም። በሀገር
መኩራት ጠግቦ ከመብላት፤ አማርጦ ከመልበስና መጠለያ ካለማጣት ይመነጫል የሚል ድምዳሜ ቢኖረን ገና
ድሮ፤ በአያቶቻችን በቅድመ አያቶቻችን ጊዜ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ባለቀላቸው ነበር። ወይ ሀገሬ!
እውነትም ወይ ሀገሬ! ወይ ኢትዮጵያዬ!
አዎ ረሀብ ጥንትም ነበር። ጥማትም ጥንትም ነበር። እርዛትም ጥንትም ነበር። ድህነትም ጥንትም ነበር።
መጠለያ እጦትም ጥንትም ነበር። የጥንቱ ረሀብና ጥማት፤ እርዛትና ታዛ ማጣት፤ ድህነትና ሁዋላ ቀርነት -
ሀገር ቅልቅል፤ ባንዲራ ቅይጥ፤ ሉዐላዊነት ድብልቅ ነበር ብሎናል ዓለማየሁ። ምን ማለቱ ነው?
4
ድህነቱም ሆነ ችግሩ፤ ረሀቡም ሆነ ድቀቱ፤ ግብሩም ሆነ ግዞቱ፤ ጭቆናውም ሆነ ልማቱ፤ እንደ ህዝብ እንደ
ሀገር እንደ ዜጋ - እንደ ኢትዮጵያዊነት - ክልላዊ አጥር ያልገደበው፤ የዘር የቋንቋ አጥር የሌለው፤ የጎጥ ሰንደቅ
ያልሰደቀ፤ የጎጥ ማገር ያልማገረ...በሁሉም ዜጋ ላይ ያረፈ፤ የሰፈፈ ነበር። ይህ ባይሆን ኖሮ፤ ገና ድሮ ያኔ
ጥንቱን በኖሩ ቅምቅም አያት ምንጅላቶች ሀገር ብሎ ኢትዮጵያ ዜጋ ብሎ ኢትዮጵያዊ ባልተፈጠሩ! በደማቸው
ፍሳሽ፤ በአጥንታቸው ክስካሽ ኢትዮጵያን ባልገነቡ ኢትዮጵያዊነትንም ባላነፁ፤ ትውልድም ባልፀነሱ
ትውልድም ባልወለዱ፤ ታሪክም ባልሰሩ ታሪክም ባልመተሩ ነበር! እናም ይሄ ትውልድ ኢትዮጵያ የሚላት
ሀገር ኢትዮጵያዊ የሚልም የማንነት የምንነት መገለጫ ክቡር መለያ ባልኖረውም ነበር!
በጥንቱ ሥርዐት (እንደውም እስከ ደርግ መውደቅ) ገዢውና ተገዢው፤ የራበውና የጠገበው፤ ገባሪውና
አስገባሪው - ሁሉም የተማከሉባት የሁሉም ታዛና መኩሪያ ሀገራቸው፤ የደም የታሪክ ትስስራቸው -
ኢትዮጵያዊነታቸው - ነበር። ሀገር ቅልቅል፤ ባንዲራ ቅይጥ ሉዐላዊነት ድብልቅ በነበረው መከራ ችግራቸው
ሁሉ ድምር ኢትዮጵያውያኑ የሀገር ፍቅር፤ የባንዲራ ክብር የዜግነት ኩራት - ኢትዮጵያዊነታቸው - ከቶም
ሳይሸረሸር ከትውልድ ትውልድ የኖረው…በሀገር ለሀገር ስለሀገር ብለው ነው።
ይህንን ሀቅ ሲያስረግጥ ዓለማየሁ እንዲህ ይላል፤
‘ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል’ በሀገር ጉዳይ አይሰራም። ብቻውን የበላ ብቻውን ለሀገር ሲሞት
በታሪካችን አልታየም። የጨቆነው ዘምቶ የተጨቆነው አልቀረም። የገዛው ከልቡ ተዋግቶ የተገዛው ሲለግም
አልተሰማም። የበደለውና የተበደለው፤ የተራበውና ያስራበው፤ የገደለውና የሞተው የዕርቅ ማዕዳቸው ሀገርን
ያማከለ ነው።
እነሆ ብዕረተኛው አርበኛ የታሪክን ዕውነታ አንዳች ግነት አልያም አንዳች ምፀት በሌለው ግና አንጀት
የሚያርስ የልብ የሚያደርስ በሆነ ቃለ ቀመር ‘ቀደምት ኢትዮጵያውያን ገዢና ተገዢው የዕርቅ ማዕዳቸው
ሀገርን ያማከለ ነበር’ ሲል ጥልቀትና ምጥቀትን ያዋሃደ ሳይንሳዊ የታሪክ ንድፍ አስቀምጦልናል።
እነሆም በትውልድ ሠንሠለት ከዘመን ዘመን እየተወራረደ የመጣው ሀገርን ያማከለው የዕርቅ ማዕድ
በዘመኑ ትውልድ ገዢ - ህወሃት/ኢህአዴግ- እና ተገዢ - የኢትዮጵያ ህዝብ - መካከል ምነዋ አልተስተዋለም?
ምነዋ የተገላቢጦሽ ሆነ? ለምላሹ እነሆ ደራሲውን እናቀርባለን፤
ደረታችን ላይ የሚንቀዋለሉ ግንባታዎች፤ ከልባችን ያልደረሱ አዳዲስ ተቋሞች፤ ቀልባችንን ያልሳቡ የልማት
ዕቅዶች አሉ። መንገዶች፤ ፋብሪካዎች፤ ጤና ጣቢያዎች፤ ዩኒቨርሲቲ ማስፋፊያዎች፤ የኤሌክትሪክ
ማመንጫዎች…ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ውስጥ ድጋፍ የተነፈገው እምነት ያልተጣለበት ሁለተኛው ልማታዊ
መንግሥት መሆኑ ነው። ለምን? እንደ ፋሽስት ኢጣሊያ የድንበር፤ የባንዲራ፤ የነፃነት ጥያቄ ስላለበት? በከፊል
አዎ!
አንጡራው ኢትዮጵያዊ (ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ) ዘንግቶ የማይዘነጋቸው፤ ድኖም የማይሽር ቁስለት
ያተረፈባቸው የዚህ መንግሥት ድርጊቶች አሉ። በተለይ ኤርትራን በተመለከተ። ኢትዮጵያን ይዞ የማስደብደብ
ተግባር ተፈፅሟል። ይሄ ተግባር ከባዕዱ ኢጣሊያ እኩል የሚያስቆጥር የጠላት ድርጊት ቢሆን አያንስም።
ከሀገር ባሻገር የመንፈስ፤ የክብር፤ የህሊና፤ የሰው መሆን ድንበር ተጥሷል። ያንን ቁጭት ይዞ መገንባት፤ ያንን
ጥቃት አርግዞ ማልማት፤ ያንን መደፈር እያብሰለሰሉ ድህነት ማጥፋት የከንቱ ከንቱ ነው! ወይ ሀገሬ!
እውነትም ወይ ሀገሬ! ወይ ኢትዮጵያዬ!
የዓለማየሁ ገላጋይ ዘገር ብዕር ከተኛንበት አባንኖ፤ ከድነን ያስቀመጥነውን ከፍቶ፤ የሸሸግነውን ፊት ለፊት
አጋፍጦ ከመራራው ዕውነታ ከነባራዊው ሀቅ ጋር ያፋጥጠናል።
ከቄሳሩ ልማታዊ መንግሥት ቀጥሎ በኢትዮጵያውያን ድጋፍ የተነፈገው፤ አመኔታ ያልተጣለበት
የህወሃት/ኢህአዴግ መንግሥት ለዚህ የበቃው - ሉዐላዊነትን በመግሰሱ፤ ባንዲራ በማዋረዱ፤ ታሪክ
በማንቋሸሹ፤ ዳር ድንበር በማጣረሱ፤ ሀገር በመመዝበሩ…ብቻ አይደለም። በፀረ ኢትዮጵያነት ተፀንሶና
ተወልዶ በኢትዮጵያውያን ደምና አንጡራ ሀብት ማጅራት ላወጣው ለፋሽስቱና አምባገነኑ የሻዕቢያ መሪ
ኢሳያስ አፈወርቂና በርሱ ለሚመራው የሻዕቢያ መንግሥት ኢትዮጵያን መያዣ ማድረጉና ማስደብደቡም
ጭምር እንጂ!! አንጡራው ኢትዮጵያዊ ዘንግቶም የማይዘነጋው፤ ድኖም የማይሽር ቁስል በህወሃትና በሻዕቢያ
ተፈፅሞበታል። ይህንን መራራ ዕውነት በጥቂቱ ብናበራየውስ?
5
አዎ! ህወሃትና ሻዕቢያ የአንድ ሳንቲም ሁለት መልክ ናቸው። ህወሃትና ሻዕቢያ በተፈጥሮ ውሁድ
ዓላማቸው ምክንያት ፈፅሞም እርስ በርስ በጠላትነት ተፈራርጀውና ቆመው አያውቁም አይቆሙም።
በሁለቱም ተፈጥሯዊ ዕምነት የሁለቱም ጠላት ኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነቱ አምኖ ዜግነቱን የሚያስቀድመው
የኢትዮጵያ ህዝብ ናቸውና።
ሆኖም በህወሃት/ሻዕቢያ ተፈጥሯዊ ዕምነትና ግብ ውስጥ ይጨፈለቅ ዘንዳ የማይገባውና አፅንዖት ይሰጠው
ዘንዳም ግድ እሚል ታላቅ ጉዳይ አለ። የኤርትራ ህዝብ እንደ ህዝብነቱ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ጠላት
አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፋረደው ሻዕቢያ ዕኩይና ወንጀለኛ የፖለቲካ ድርጅት እንጂ ራሱ የኤርትራ
ህዝብ ማለት አይደለም። ግልባጩ ህወሃትም እንዲሁ። የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብነቱ ከቀረው ኢትዮጵያዊ
ወገኖቹ ጋር ከቶም በፍፁም ጠላትነት ኖሮት አያውቅም፤ የለውም፤ አይኖረውም። ‘የትግራይ ህዝብ ነፃ
አውጪ’ የሚል ቅፅል ስላንጠለጠለ ህወሃት የትግራይን ህዝብ ይወክላል ወይም ህወሃት ማለት የትግራይ
ህዝብ ነው ማለት ከቶም በፍፁም እጅግ የከበደ ስህተት ይሆናል። ህወሃት እንደ ሻዕቢያ ሁሉ ዕኩይና መሰሪ
ደግሞም በወንጀል የተበከለ የፖለቲካ ድርጅት እንጂ የትግራይ ህዝብ ማለት አይደለም። ይህ ዕውነት ጠርቶና
ጎልቶ ይሰመርበት፤ ይታመንበትና በማያሻማ ቋንቋም ይቀመጥ ዘንዳ ይኖርበታል።
ከኮሚኒስቷ የሶቪየት ህብርት መፍረስ ከሳተላይቶቿም መበታተንና ከቀዝቃዛው ጦርነትም ማከተም
በሁዋላ በዓለም ላይ ከተፈጠሩት ዘመን አፈራሽ አዳዲስ መንግሥታት መካከል እጅግ አምባገነን፤ አፋኝና
ኢሰብዓዊ ከሆኑት መንግሥታት አንዱ በአመባገነኑ ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የኤርትራው የሻዕቢያ
መንግሥት ነው።
ሻዕቢያ ፀረ ዲሞክራሲ መንግሥት ነው። ሻዕቢያ ለሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶች የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል
ደንታ የሌለው እርኩስ መንግሥት ነው። ሻዕቢያ ፀረ ሠላምና ፀረ መልካም ጉርብትና ፖሊሲ አራማጅ የታበየ
መንግሥት ነው። ሻዕቢያ እስከ ወዲያኛው ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ያለው ዘረኛ መንግሥት ነው።
ሻዕቢያ ኤርትራን በተቆጣጠረና መንግሥት በሆነ ማግሥት መሳሪያቸውን አስቀምጠው የተማረኩ በብዙ
አስር ሺዎች ወይም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላትን ያለ ርህራሄ ጨፍጭፏል፤
ሬሳቸውን ለአውሬ ሰጥቷል። በግፍ አሰቃይቶ ገድሏል፤ በችጋር ጠብሶ በጠኔ እንዲያልቁ አድርጓል፤
በቁማቸው ቀብሯል። ርቃነ ስጋቸውን በበረሃ እንዲጓዙ አድርጎ በሀሩር ተቃጥለው ወድቀው ቀርተዋል።
ሻዕቢያ ሥልጣን ይዞ መንግሥት ሲሆን በኤርትራ ምድር ከኖሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት
ወይም በተለያዩ ምክንያቶችና ሥራ ከኤርትራ ተወላጆች ጋር ተሳስረው የመሰረቱት ቤተሰብ እንዲበተን
አድርጓል። ንፁህ ኤርትራዊ ደም የላችሁም ተብለው ስንትና ስንት ቤተሰቦች እንዳልነበር ሆነዋል? ስንትና
ስንት አባቶች፤ ስንትና ስንት እናቶች፤ ስንትና ስንት ህፃናት በግፍና በአረመኔያዊ ዘረኝነት ደመ ከልብ ሆነው
በኤርትራ ምድር ወድቀው ቀርተዋል? ሻዕቢያ ኢትዮጵያውያን ከሚላቸው ኤርትራዊ ካልሆኑ ዜጎች ጋር ትዳር
የመሰረቱ ኤርትራውያን ሴትችን ሳይቀር ያረደ አረመኔ መንግሥት ነው። በኤርትራ ምድር በአስተማሪነት፤
በሀኪምነት፤ በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ሲሰሩ የኖሩትን ‘ኢትዮጵያዊ’ የሚላቸውን
ሁሉ ንብረታቸውን ዘርፎና የቻለውን ገድሎ ሌሎችን በእስር አማቆ የጨረሰ ወንጀለኛ መንግሥት ነው።
ግፈኛውና ፋሽስት የሻዕቢያ መንግሥት ሌላው ቀርቶ ጥርሳቸው ላይ ወርቅ ያላቸውን ኢትዮጵያውያን
የሚላቸውን ያለ ማደንዘዣ የወርቅ ጥርሳቸውን እየነቀለ ኢሰብዓዊና ዘግናኝ ግፍ ያለ አንዳች ርህራሄ ፈፅሟል።
እኒህን ሁሉ ማን ተፋረደላቸው? ማን አቤት አለላቸው? እነዚህ በግፍ ያለቁ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ
እስከ ምዕራብ የኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ዜጎች በምድረ ኢትዮጵያ ስንት ሚሊዮን ቤተሰብ፤ ዘመድ አዝማድ፤
ጓደኛና አብሮ አደጎች አሉዋቸው?...እኒህ ሁሉ ቀን ጠባቂ ናቸው - ሻዕቢያን ሊፋረዱ!!
ፋሽስቱና አምባገነኑ ኢሳያስ አፈወርቂና የሚመራው የሻዕቢያ መንግሥት የጦር ወንጀለኞች ናቸው። ሻዕቢያ
መንግሥት ሲሆን ስለፈጃቸው ኢትዮጵያውያን በጦር ወንጀለኝነት ተጠያቂ ነው። ሻዕቢያ መንግሥት ሲሆን
ኢትዮጵያውያን በሚላቸው ላይ የፈፀመው የጦር ወንጀል የጀርመን ናዚዎች የአርያን ዘር ባልሆኑትና በተለይም
በአይሁዳውያን /ጅውስ/ ላይ ከፈፀሙት ወንጀል የማይተናነስ ነው።
ሻዕቢያ መንግሥት ሆኖ በግፍ ስለጨፈጨፋቸው ኢትዮጵውያን አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ መንግሥት
የሆነው ህወሃት/ኢህአዴግ አልጠየቀም። ሊጠይቅም አይችልም። ምክንያቱም የዐላማ ውሁድነት ያላቸው
በመሆኑ በህወሃት/ኢህአዴግ አይን ሻዕቢያ ወንጀል አልፈፀመምና! ይልቁንም ህወሃት/ኢህአዴግ ለሻዕቢያ
‘የደም ካሳ” ከኢትዮጵያ ካዝና ዘርፎ ወደ አስመራ አጉርፏል። አሰብን በገፀ በረከትነት ሰጥቷል…ፋሽስት
የሻዕቢያ መንግሥት በኢትዮጵያ የቡና ምርት እንዲበለጥግ አድርጓል…
6
ሠማይና መሬት ያልፋሉ እንጂ ፋሽስት የሻዕቢያ መንግሥት ኢትዮጵያ ሠላም ሰፍኖባት በዲሞክራሲያዊ
ሥርዐትና በህዝብ ድምፅ በህገ መንግሥት የሚገዛ፤ የህግ የበላይነትን የሚቀበል መንግሥት እንዲቆም፤ ሰብዓዊ
መብቶች የተረጋገጡባትና ህዝቦቿ በፍቅር በአንድነትና በእኩልነት እየኖሩ ማዕዷን የሚጋሩባት ሆና
እንድትኖርና እንድታድግ የሚመኝና የሚደግፍ ጎረቤት መንግሥት አይደለም!! ሻዕቢያ በመንግሥትነት እስካለ
ድረስ በኢትዮጵያ ምድር እሾህና አሜኬላ ከመዝራት ከቶም እረፍት አይኖረውም!…ይህንን መካድ ወይም
ለቅፅበት መጠራጠር ወይም ሻዕቢያ ይቀየራል ማለት…ከእባብ እንቁላል እርግብ ይፈጠራል…ብሎ እንደ ማመን
ነው!!
በመስከረም ወር 2006 ዓ/ም ቀንደኛው ፀረ ኢትዮጵያ የሻዕቢያ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ አስመራ ላይ
ለጋዜጠኞች በሰጠው ቃለ ምልልስ የኢትዮጵያ ዘላቂ ደመኝነቱን አድሷል፤ እንዲህ ሲል፤
ለመሆኑ ኢትዮጵያ መቼ ነው የተፈጠረችው? ኢትዮጵያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ በሁዋላ
የተፈጠረች ሀገር ናት። ኢትዮጵያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊዎች ለራሳቸው ጥቅም መሳሪያ ሆን
ተብሎ የተፈጠረች አገር ነች። ስለዚህ ኤርትራን የእነሱ ወኪል ሆና ገዝታ ይሆናል እንጂ ራሷ በቀጥታ
ኤርትራን የገዛችበት አጋጣሚ አለ ማለት አይቻልም።
የጦር ወንጀለኛው ፋሽስቱ የሻዕቢያ መሪ ለኢትዮጵያ ያለውን ንቀትና ጥላቻ ከዚህ በላይ እንደምን አድርጎ
ሊገልፅ ይችላል? እንደ ዕውነቱ ከሆነ የሻዕቢያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ያለውን የጥላቻ ደርዝ ከዚህ የኢሳያስ
ንቀት በላይ ሊገልፀው የሚችል ቋንቋም ሆነ ማስረጃ አይገኝም። በዚህ ፅሁፍ ይህንን የእንቧይ ካብ ታሪክ
ለመናድ ጊዜ አናጠፋም…
የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሳያስ የሳንቲም ግልባጭ አቶ መለስ ዜናዊ፤ ‘ኢትዮጵያ
የምትባል አገር የአንድ መቶ ዓመት ታሪክ ያላት ናት፤ ለዛውም ሌሎች ብሄረሰቦችን ቅኝ በማድረግ’ ብለው
በአደባባይ በመናገር በሥልጣን በቆዩባቸው ሃያ አንድ ዓመት የኢትዮጵያን ታሪክ በኢቲቪና በሬዲዮ እየቀረቡ
በማንጓጠጥ፤ በመሳለቅና በማዋረድ እንዲያ ሲዘባበቱበት ኖረው በ2004 ዓ/ም አረፉ፤ ዝም አሉ።
እሳቸው ባረፉ፤ ዝም ባሉ በዓመቱ፤ ሻዕቢያው ኢሳያስ የአቶ መለስን ሀርሞኒካ አንስቶ ያው ህወሃታዊ
መለሳዊ ዜማና ቅኝቱን ሳይቀይር፤ ነገር ግን ሻዕቢያዊ ኢሳያሳዊ እንጉርጉሮ ቀምሮ ‘ኢትዮጵያ ከ1945
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በሁዋላ አውሮፓውያን የፈጠሯት አገር ነች ሲል አንጎራጎረ። እነሆ በዚህ
ስሌት - በትክክል በየትኛው ዓመተ ምህረት እንደተፈጠረች ባይናገርም ከጦርነቱ ማብቃት በሁዋላ ምናልባት
በ1945/46/47 አካባቢ ተፈጠረች ቢባል - ይህ ፅሁፍ ለንባብ ሲቀርብ ኢሳያስ 67 ዓመቱ ሲሆን ኢትዮጵያ
ስትፈጠር፤ ኢትዮጵያውያን የሚባሉ ዜጎችም ሲፈጠሩና እሱ ሲፈጠር ‘መንትዮች’ ይሆናሉ ማለት ነው።
አምባገነኑና የጦር ወንጀለኛው ኢሳያስ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ፌብሩዋሪ 2፤ 1946 ነበርና
የተፈጠረው። የዚህን የኢሳያስ ዘለፋ አንደምታና ተልዕኮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ትኩረት ሰጥቶት በያለበት
ሊያብላላውና ሊያበራየው የሚገባ አገራዊ ጉዳይ ነው። ነገር ግን በሻዕቢያው ኢሳያስና በቀድሞው ጠቅላይ
ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መካከል በኢትዮጵያ መፈጠርና ታሪክ የጊዜ ቅደም ተከተል ካልሆነ በቀር የይዘት
ተቃርኖ የሌላቸው መሆኑን ያጤኗል። የኢሳያስ ወንጭፍ ዓላማ ኤርትራ ከኢትዮጵያ የትና የት በፊት ተፈጥራ
የኖረች ሀገር በመሆንዋ የኢትዮጵያ አካል ሆና ወይም በኢትዮጵያ ግዛትነት ተጠርታ በቀደምት ነገሥታትና
መሪዎች ተስተዳድራ የማትታወቅ ከመሆንዋም በላይ ምናልባት ወደፊት አሰብን የማስመለስ ሀሳብ ቢኖራችሁ
የታሪክ መሰረት የላችሁምና አትድከሙ ማለቱ…ከወዲሁ ማስጠንቀቁ መሆኑ ነው...
በአንፃሩ አስደማሚውና ከንካኙ ጉዳይ ኢሳያስ ይህንን ዘለፋ የናኘው እንደ ኤርትራ መንግሥት መሪነቱ
በሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ሲሆን በህወሃት/ኢህአዴግ መንግሥት በኩል ከኤርትራው መሪ ለተሰነዘረ አገራዊ
ዘለፋ ምላሽ የሰጠ መግለጫም ያወጣ አለመኖሩ ነው። ግን አይጠበቅባቸውም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ
ቀደምት ታሪክ ያላት ጥንታዊት ሀገር ናት ካሉ ከመለስም ከኢሳያስም ከራሳቸውም ጋር መጋጨታቸው
ይሆናልና!
የእነሱ፤ የህወሃት/ኢህአዴጋውያኑስ እሺ ይሁን። እንደው ግን ለመሆኑ ፋሽስቱ ኢሳያስ አፉን ሞልቶ ደረቱን
ነፍቶ ኢትዮጵያን ለሰደበ በታሪኳ ሲዘባበት ላለፈረ፤ ምነዋ የእኛ ዝምታ፤ ‘የአልሰማንም’ ፍርሃት መሰል ጥላ
ባለንበት ሁሉ አጠላ?! የፈራነው ማንን ነው? የጦር ወንጀለኛውን ፋሽስቱን ኢሳያስንና መንግሥቱን ሻዕቢያን
ወይስ ራሳችንን?
አየሽ አንቺ ኢትዮጵያ፤ አየሽ አንቺ እናት ሀገር አየሽ አንቺ እናት ዓለም፤ ቃል የዕምነት ዕዳ እንጂ የናት
ያባትኮ አይደለም! እናም - በስምሽ ሲምሉ ሲገዘቱ፤ ከህወሃት ውጋት ነፃ እናወጣሻለን ሲሉ የኖሩ፤ ዛሬ
በሻዕቢያ ስትዘለፊ ስትንጓጠጪ ስትዋረጂ፤ በትልቁ በትንሹ ሲያንጋጉት የኖሩት መግለጫ፤ እስቲ እሱን እንኳ
7
ግማሽ ገፅም ቢሆን ማውጣት ማንን ገደለ ወይስ ይገድላል? ግዴለም እናት ሀገር፤ በስምሽ ሲምሉ የኖሩ ዝም
ጭጭ ቢሉ አንደበታቸውን ቢዘጉ፤ ብዕራቸውን ቢያዶለድሙ፤ ቃላቸውን ከፍ! አድርገው ባያሰሙ - አይክፋሽ
አትዘኚ! ወቅቱ የመኸር ዘመን ነውና ለአንቺም ለእኛም ህልውና፤ ዝምታቸው ሽሽታቸው መልካም ነው!
አንቺም እኛም ምርቱን ከግርዱ እናበራያለንና!!
ያም ሆነ ይህ ግን የወቅቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ፤ ዝንጀሮዋ ሰውነቷን ሙሉ እሾህ ጠቅጥቋት የቱ ይነቀልልሽ
ቢሏት መጀመሪያ የመቀመጫዬን አለች እንዳሉት አይነት ታሪክ ነው። የመቀመጫዋ እሾህ ከተነቀለ የቀረውን
ራሷው እየመዘዘች ታወጣዋለችና! እነሆም በአሁኑ ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ ዋና ተግባር መጀመሪያ በጫንቃው
ላይ የተንሰራፋውን አፓርታይዳዊ አምባገነናዊ የህወሃት/ኢህአዴግ መንግሥትን ማውረድ ነው። የኢትዮጵያ
ህዝብ የመቀመጫውን እሾህ ለማውጣት ከጦር ወንጀለኛው ኢሳያስና በእርሱ ከሚመራው የሻዕቢያ
መንግሥት በኢትዮጵያውያን ደም የተበከለ ምፅዋት (የገንዘብም ይሁን የመሳሪያ) አይፈልግም፤ አይጠይቅም።
የሻዕቢያን የአዞ እንባም አይሻም፤ አይፈልግም።
እያደር እየጋመና እየሰፋ በመጣው ህዝባዊ ሠላማዊ አመፅ በራሱ ትንታግ ወጣት ልጆች እየተመራ
በአናጋፋዎቹም እየታገዘ ይዋል ይደር እነጂ የመቀመጫውን እሾህ ራሱ ነቅሎ ያወጣዋል። ነፃ ይወጣል።
በየካቲት ወር 1966 ዓ/ም ባቀጣጠለው ህዝባዊ አመፅና ባካሄደው ሠላማዊ ትግል ለውጥ እንደሚመጣ
በተግባር ያረጋገጠውና ነገር ግን አብዮቱ በመስከረም 1967 ዓ/ም የሥርዐት ለውጥ ማግሥት የተጠለፈበትና
መነሻ ግቡን ያልመታለት የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ የህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን የጀመረው ህዝባዊ ሠላመዊ
የትግል እንቅስቃሴ ወደ ዳግም አብዮት እየተምዘገዘገ እንደሆንና ድል እንደሚያደርግ፤ ድሉም በአስተማማኝ
መሰረት ላይ የሚቆም እንደሚሆንም አንዳች ጥርጣሪ ከቶም ሊኖረን አይገባም!! እንደውም በዘመናዊቷ አፍሪካ
ታሪክ በሠላማዊ ህዝባዊ አመፅ ለዘመናት ፀንቶ የቆየን ሥርዐት በመጣል ቀዳሚ ታሪክ ያስመዘገበው
የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑንም መርሳት አይኖርብንም። ዛሬ ግብፅ፤ ሊቢያና ቱኒዚያን እንደ ምሳሌ ብናነሳም ቅሉ
ከእኒህ ሁሉ በፊት ግን ከየካቲት 1966 ዓ/ም እስከ ህዳር 1967 (ደርግ ርሸና እስካደረገበት ወቅት) የኢትዮጵያ
ህዝብ ተምሳሌታዊ የሆነ ሠላማዊ አብዮት ማካሄድ የቻለ ታላቅ ህዝብ እንደሆን (ምናልባት የዘነጉት ቢኖሩ)
በአፅንዖት ማስታወስ እንወዳለን።…የኢትዮጵያ ህዝብ የከሸፈውን የሠላማዊ ትግል ለውጥ ከፍፃሜ
የሚያደርስበት ወቅትም እነሆ በዘመናችን ተቃርቧል…እናም በሙሉ ሃይላችንና መንፈሳችን ከጎኑ እንቁም!!
ዓለማየሁ ገላጋይ፤ ህወሃት/ኢህአዴግ ኤርትራን ይዞ ኢትዮጵያን ማስደብደቡ ከባዕድ ኢጣሊያ እኩል
የሚያስቆጥር የጠላት ድርጊት ቢሆን አያንስም።…አንጡራው ኢትዮጵያዊ ዘንግቶ የማይዘነጋቸው፤ ድኖም
የማይሽር ቁስለት ያተረፈባቸው የዚህ መንግሥት ድርጊቶች አሉ፤ በማለት ያሰፈረውን የታሪክ ቋጥኝ ዕውነት
አንተርሰን የጦር ወንጀለኛው ኢሳያስ አፈወርቂና የሚመራው የሻዕቢያ መንግሥት የፈፀሙትንና ለመፈፀምም
በሚዘጋጁት ፀረ ኢትዮጵያ ወንጀሎች ላይ የነቀነቅነውን ዘገር (ጦር) እዚሁ ላይ ቸክለን ወደ ቅኝታችን ተከታይ
ክፍል እናቀናለን።
ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ህዝብ አመኔታ ለማጣቱና ድጋፋ ለመነፈጉ ከፊል ምክንያቱ፤ እንደ ፋሽስት ኢጣሊያ
የድንበር፤ የባንዲራ፤ የነፃነት ጥያቄ ስላለበት ነው ብሎን ነበር - ብዕረተኛ አርበኛ ዓለማየሁ። ለመሆኑ ከፊሉ
ምክንያትስ ምንድን ይሆን? እነሆ ዓለማየሁ በስፋት ከዘረዘራቸው የኢህአዴግ ወንጀሎች ከፊሉን
እንደሚከተለው ይመለከቷል።
2. ‘ለልማት’ የውሻ ሞት የሞቱና በመሞት ላይ ያሉ ስንቶች ናቸው?
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በ2004 ዓ/ም ከማለፋቸው አስቀድሞ ለ21 ዓመት በመሩት
የህወሃት/ኢህአዴግ መንግሥት ኢትዮጵያ በታሪኳም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ መንግሥታት ታሪክ ያልታየ
የዕድገት፤ የልማትና የኢኮኖሚ ምጥቀት አሳይታለች እየተባለ ሲነገርና ሲደለቅ ተኖረ። ብዙዎች በውጪ ሀገር
የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ከእለት እንቅልፍ እየተቆጠቡ ጥረው ግረው በመሥራት ያጠራቀሙትን ዶላር
ይዘው ሀገር ቤት ደርሰው በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች መዝናኛዎች፤ ሆቴሎች፤ ዳንስ ቤቶች፤ የቱሪስት
መናኸሪያዎች…ተዝናንተው፤ በአስፋልቱም መኪና ተከራይተው ተንሸራሽረው፤ ከአዳዲሶቹ ሰፈሮች ወይ ቪላ
ወይ ፎቅ አሰርተው…ቦንድም ተቧድነው ወደ ፈረንጅ ሀገር ሲመለሱ - ከኢህአዴግ የኢኮኖሚ እድገት ዲስኩር
በላይ ስለ ህንፃዎቹ ማማር፤ ስለ አስፋልቱ መንዠርገድ፤ ስለ ሆቴሎቹ አውሮፓዊነት…ብዙ፤ ብዙ አስተዛዛቢ
ነገር ሲናገሩ - ሰምተናቸዋል በጆሯችን አይተናቸዋልም በዐይናችን።
ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ - ነውና፤ የዕውነት መስተዋት ገመና፤ ኑሮን ሳይሸሹ የኖሩ፤ በልማትና
ዕድገት ግሬደሩ የታረሱ…እነርሱ ግን እንዲህ ይላሉ።
8
አሮጌ ከተማ ስር የምትሰደው በደሳሳ ጎጆዎቿ አይደለም። በነዋሪዎቿ ህይወት ነው። አቧራ የቃሙ የእግር
መንገዶቿ ለነዋሪዎቿ የደም ስሮች ናቸው። የጉልት ካቦቿ መተንፈሻ ሳንባ፤ መሸታ ቤቶቿ የልብ ምቶቿ
ናቸው። እነዚህን ድንገት ተነስቶ በዶሮ ስልት መጫር ሃላፊነትን ከግምት የከተተ ተግባር አይደለም።
የግዴለሽነትና የምን ታመጣላችሁ መታበይ እንጂ…
አዲስ አበባ ከ3 (ሶስት) ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንዳላት እአአ በ2009 በወጣው መረጃ
መሰረት ተጠቁሟል። ከእነዚህ ነዋሪዎች ውስጥ 35% ያህሉ በህይወት መቆየታቸው እንደ ተዓምር
የሚያስቆጥረው የድህነት ሥር ነዋሪዎች /ናቸው/። /በዚህ ስሌት/ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪ የአዲስ አበባን
አቧራማ መንገድ የኑሮው ደም ስር አድርጎ፤ የጉልት ካቦቿን ሳንባው፤ መሸታ ቤቶቿን የልቡ ምት አድርጎ
ተዓምራዊ ህይወት የሚያከናውን ነው። ይህንን ነዋሪ ከአካባቢው ላይ ማንሳት ዛፍን ነቅሎ እንደ መጣል ያለ
ተግባር ነው። ነቅሎ መጣል፤ ነቅሎ መጣል…
የመኻል ባተሌ ነዋሪው ከመኻል ተነቅሎ ዳር ዳሩን ተደፍቷል። ምን ያህሉ በረሀብ፤ ምን ያህሉ በበሽታ ስር
ይሆን? የፀጥታ እልቂት! የዝምታ ሞት! ይህቺን ከተማዬን የሚማለዳት የሚታደጋት የለም። ብዙ የአዲስ አበባ
ጎሰድቋላ መንደሮችና ነዋሪዎች ለዚሁ የፀጥታ ሞት ተዘጋጅተው የሚጠባበቁ ይመስላል…ወይ ከተማዬ!
እውነትም ወይ ከተማዬ! ወይ አዲሳባዬ!
እነሆ ዓለማየሁ ገላጋይ ‘ሲለክፈኝ ሳይሆን ሲጥለኝ አወቅሁት’ ያለው የኢህአዴግ የልማት አውሎ ነፋስ
ሊያለማው የሚገባውን የህብረተሰብ ክፍል ከስሩ ከመሰረቱ እየመነገለ፤ አዲስ አበባን በዶሮ ስልት
እየመነቀረ…የስንትና ስንት ነዋሪን ህይወት በቁም እንደቀበረ…የብሶት ዘገሩን በሰበቀበት ብዕሩ ተናዟል።
እኛም እንላለን፤
አቧራማ መንገድ፤ ደሳሳ ጎጆ፤ መሸታ ቤት፤ የእንጀራ፤ የጎመን፤ የቂጣ፤ የቆሎ…መሸጫ ጉልት…ሙዚየሞቻችን
ናቸውና አይነኩ አይለወጡ አልወጣንም። ዕድገት፤ ልማት፤ ለውጥ ‘እንዴት ተደርጎ አካኪ ዘራፍ’ - አላልንም።
ታዲያ ምንድን ነው ችግሩ? እነሆ ስለ ችግሩ ዓለማየሁን እናቀርባለን፤
አሮጌ ቤት ላይ የምንወጣው ሰው ለማፍረስ ነው። የምንመዘው የህይወት ጉድ እንጂ የአሮጌ ቤት ግድግዳ
አይደለም። የምንንደው ስጋ እንጂ ጭቃ አይደለም።
እዚህ ነባር መንደር ላይ ሳያገናዝቡ ድጅኖ ማንሳት ጥፋት እንጂ ልማት አይሆንም። ከዚያስ? ተብሎ
የማይጠየቅበት ፍጥነት ያለው የድሃ ቀብር ላይ እንጂ ህይወት ላይ አይደለም።
አዲስ አበባ የዶሮው ፖሊስ የጫረው ገላዋ ተገጣጥቦ ብዙ ግጥብጥብ ደሴቶች በብረት አጥር ተከትረው
እየተዘጉ ነው። ተዘጋጅተው የሚጠብቁት ልማት ሳይመጣ የሙሽርነት ጊዜያቸውን የጨረሱ ብዙ ክትር
ፍርስራሾች። አንዳንዶቹ ከአስር ዓመት በላይ በሌጣነት የዘለቁ ቦታዎች ናቸው። ለምሳሌ ግቢ
ገብርኤል…ነዋሪዎቹና ነጋዴዎቹ ተካልበው ከተባረሩ ዓስር ዓመት ሆኖታል። ቱሪስት ሆቴል መውጫ ላይ
እንዲሁ ስምንት ዓመት ሙሉ በጋለሞታነት የቆየ ቦታ አለ። ብሄራዊ ቲያትር ጀርባ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ፊት
ለፊት ጭሮ አዳሪዎቿን ዝናብ እንደመታው ውሻ ከላዩዋ ላይ ካራገፈች ሰባት ዓመት /አልፏል/...
ይህም ሆኖ ማፈናቀሉ አሁንም አልቆመም። የታጩት መሬቶች ሳይዳሩ ቆመው ቀርተው መንግሥት
ጠለፋውን ጋብ ለማድረግ እንኳን ፈቃደኝነት አላሳየም። ከተፈናቀሉት የታነቁት፤ ከታነቁት ደግሞ
የተዛተባቸው ይበልጣሉ። መንግሥት በእጁም በእግሩም የከተማ አጨዳ ላይ ተሰማርቷል። መሬትን እንደ
መክሊት ቆፍሮ መቅበር ስራዬ ብሎ ተያይዞታል። ወይ ከተማዬ!
አዎ ዕውነትም ወይ ከተማዬ! ወይ አዲሳባዬ!
እንደው ለመሆኑ የልማት ሚዛኑ ምንድን ነው? የሰቆቃ፤ የዋይታና የፍዳ ህይወት ድንበሩስ የት ድረስ ነው?
የኢህአዴግ ልማት - ነባር ሰፈሮችን መናድ - እኮ ግቡ ለማንና ምንድን ነው? ስለምን ‘አዱ ገነት’ ህይወት
የሰጧትን - ሸገር፤ አዲስ አበባ - ያሰኟትን ነዋሪዎቿን እንደ ክፉ ድመት እናት ትቀረጭጫቸዋለች?...ለምን? እኮ
ለምን?! አዲስ አበባን ማን ይታደጋት? ማን ይማለዳት? ነዋሪዎቿንስ ማን ይታደጋቸው?
9
የህወሃት/ኢህአዴግ መንግሥት ፈጣሪና መሀንዲስ /አርኪቴክት/ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ የአዲስ አበባን
ነባር ሰፈሮች በግሬደር ማፈራረስና ነዋሪዎቹን እያካለቡ ዝናብ እንደ መታው ውሻ ማባረር የጀመሩት ገና
በጠዋቱ፤ ሥልጣን ጨብጠው አስር ዓመት’ኳ ሳይሰነብቱ ነበር።
ደሳሳ ጎጆዎች ተመንግለው፤ ነዋሪዎቻቸው ተባርረው ባዶው መንደር - መሬቱ - በብረት አጥር ተከትሮ፤
የተረሳ መቃብር መስሎ - ባለሀብቶቹ እስቲገነቡ ዓመታት መክረሙ፤ ምኑ ነው ልማቱ? ለመሆኑ ከርታታዎቹ
ነዋሪዎቹ የት ገቡ? ኑሯቸውስ እንደምን ተሻሽሏል? ካልሆነስ እንደምን ዘቅጧል?
ብዕረተኛው አርበኛ ዓለማየሁ ‘ለልማት-ጥፋት’ መሀንዲስ ለነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ
መለስ ዜናዊ ‘አቤት!’ ባለባት አንደኛው የብዕር ዘገር የሚከተለውን አንጥቧል፤
…ምንም በደልዎ ቢከብድ ወርዶ ማናገር እንጂ ወጥቶ ይቅርታ ማድረግ አይከብድም። እንኳን የቆምነው
በአፀደ ሥጋ የሌለነውም ለይቅርታ ወደ ሁዋላ አንልም። በደሌ ምንድን ነው? ይሉ ይሆናል።…በደልዎን አሁን
ካሉበት ከላይኛው ቤተ መንግሥት እምብዛም ሳይርቁ ቁልቁል ይመልከቱ። ባድማ አይታይዎትም?
ካልታይዎት ወደ ሸራተን አዲስ ሄደው መስኮቶቻቸው ወደ ሰሜን ከዞሩ ክፍሎች በአንዱ ብቅ ይበሉ። ያ
ባድማ አይንዎ ላይ ይጋረጣል።
የዛሬው ባድማ ከሁለት ዓመት በፊት ሞቅ ያለ የድሃ ቤት የሚመስል ሰፈር ነበር። ሰፈሩ በሶስት የተከፈለ
ነው። ፊት በር፤ ሥላሴ ገበያና አሮጌ ቄራ። እርስዎ የሚያውቁት በአራዳ ክፍለ ከተማ ስር ካሉ አንዱ ቀበሌ
አድርገው ነው። የዚህ ቀበሌ ሰፋሪዎች ካካባቢያቸው ሳይወጡ መተዳደሪያቸውን እንደ ዶሮ እዚያው
እየለቀሙ የሚኖሩ ነበሩ። ሰፈሩ ከስድስት ያላነሱ ኢኮኖሚያዊ ክልሎች ነበሩት። ጨርቅ ተራ፤ ቁልፍ ተራ፤
ቅጠል ተራ፤ ሞጋ (ጫማ) ተራ፤ ደቦቃ፤ ብረታብረት ተራ።…እነዚህ ‘ተራዎች’ ድሃውን በኑሮ ሸክፈው የያዙ
ናቸው።…
እንግዲህ “አረንጓዴና ፅዱ” የተሰኘው የልማት ምናባዊ ፖሊሲዎ መጥቶ ይህንን ተመጋጋቢ የኑሮ ይትባህል
ከስሩ መነቃቀረው። ያለ ምንም ጥናት ሰው በመጠለያ ብቻ ይኖር ይመስል የብሎኬት ድርድር ውስጥ
ወሸቁት። አይ መለስ! መቃብርም’ኮ በድንጋይ ይሰራል። የኑሮ መፍትሄ ከሌለው ኮንዶሚኒየምም ያው
የድንጋይ መቃብር ነው። የኑሮ መፍትሄ ያጡት ወጣት የአሮጌ ቄራ ልጆች…እናት አሮጌ ቄራን ሞታ
የታጋደመችበት አጥንቷን እየጋጡ በላስቲክ ከለላ ይኖራሉ። ድንጋይ እየፈለጡ፤ ሚስማር እየለቀሙ፤ ማገዶ
እየሰበሰቡ…ይሸጣሉ። እስከመቼ?...
እኛም እንላለን። አዎ እስከመቼ? ለዚህ ጥያቄ የአቶ መለስና መንግሥታቸው ኢህአዴግ ምላሽ ‘አረንጓዴና
ፅዱ’ ልማታዊ ዘመቻ ማካሄድ ነው። ዘመቻው በማን ላይ ነው? ዘመቻው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ግፉዐን
ነዋሪዎቿን ያካተቱትን የአዲስ አበባን ነባር ሰፈሮች ድራሽ በማጥፋት ማፅዳት!
ለመሆኑ አዲስ አበባ ፅዱና አረንጓዴ ብትሆን የሚጠላ የትኛው አዲሳቤ የትኛው ኢትዮጵያዊ ነው?
ፅዱነቷና አረንጓዴነቷ ግን ራሷን እያቃጠለች ጭስና አመድ ሆና በመክሰም መሆን አለበት እንዴ? ህዝብን
በመጠየፍ አርቆ መወርወር ‘ልማታዊነት፤ ፅዱነትና አረንጓዴነት’ ይሆናልን?
የህወሃት/ኢህአዴግ መንግሥት ከዓለም ባንክ፤ ከአውሮፓ ዩኒየንና ከምዕራባውያን መንግሥታት
የሚመፀወተው ነገር ግን እንደ ሽክሽክ ጆንያ የማይሞላውና አየሁ የማይለው በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር
በሥራ መዋሉን ማሳያ፤ ማስመሰያ - የድሃው ሰፈር እየተመነቀረ ህብረተሰቡ ያለ አንዳች የዕለት ተዕለት የኑሮ
ዋስትና በብሎኬት ውስጥ እንዲታጎር ማድረጉ ምኑ ይሆን ልማቱ? ምኑስ ይሆን ፅዳት አረንጓዴነቱ? ሰው
በብሎኬት ብቻ ይኖር ዘንድ ይቻለዋልን?
ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሞገተበት ፅሁፍ እንዲህ ይላል፤
…እነዚያ በልብሱም፤ በቁልፉም፤ በሞጋውም፤ በበሰበሰ ብርቱካኑም…ነፍሳቸውን ቋጥረው የቆዩት
ጎረቤትዎችዎ እዛው የኮንዶሚኒየም ግዞታቸው ውስጥ በሞት እየረገፉ ይገኛሉ። በአንድ ዓመት ብቻ አንድ
መቶ ባተሌዎች በግፍ አልቀዋል። እስኪ አንድ ጥያቄ ላቅርብልዎ፤ የአረንጓዴና ፅዱነት ተልዕኮ የሚለካው
ቆሻሻውን ድሃ እና ቡላማ ኑሮውን በማውደም ነው? እንደ ደረቅ ቆሻሻ አርቆ በመቅበር? ከምሮ በማቃጠል?
እንደ ሙጃ በመደዳ በመዘለስ?...በደልዎ ይሄ ነው!
አዎ እውነት ብለሃል ዓለማየሁ! የጣዕር ድምፅ አውጥተህ አሰምተኻል። የፀጥታ ሞት ሟቾቹን ኑዛዜ ‘ኤሎሄ’
ብለሃል። የህወሃት/ኢህአዴግ መንግሥት ‘አረንጓዴና ፅዱ ልማት’ የኢትዮጵያውያን መለያ የሆነውን ሥነ
10
ልቦናና የአኗኗር ይትባህል ማጥፋት ነው። ለመሆኑ የዚህ ዲያቢሎሳዊ ዓላማ ቤተ ሙከራ የሆኑት አዳዲስ
ቀበሌዎች ህይወት ምን ይመስላል? ዓለማየሁ እንዲህ ይላል፤
አዳዲሶቹ ከተሞች ላይ ህይወት አይታይም። የህንፃዎቹ አኗኗር ስር የሰደደና እርስ በርስ የተደጋገፈ
አይደለም። ዕድሩ በኢንሹራንስ፤ ዕቁቡ በባንክ፤ የአገር ሽማግሌው በችሎት፤ መተሳሰቡ በሥነ ልቡና አማካሪ
ተተክቷል። ጉርብትናው ባለመደራረስ ህግ ሞቷል። የከተማ ዘላንነት ተስፋፍቷል…
እነሆ ‘ማን ይመስክር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ’ ማለታችን ለዚህ ነበር። እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ‘ሸቀጥ
አምልኮው’ የሆነው ዘመነ ካፒታሊዝም እንደ ዘንዶ ወገቧን ጠምዝዞ፤ ትንፋሿን ሰቅዞ፤ ጉራማይሌ ዘመን
ውስጥ ገብታ ትቃትታለች።
እንደ ‘ኦክቶፑስ’ እጀ ብዙው ዓለም ዐቀፍ ካፒታሊዝም በህወሃት/ኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ
አዝማችነት ዘንዶ ምላሶቹን በየዘርፉ ሰዶ - ዕቁቡን በባንክ ዕድሩን በኢንሹራንስ ቢያንቅ፤ መተሳሰቡን - ‘አንቺ
ትብሽ አንተ ትብስ፤ አንተም ተው አንቺም ተይ’ በአገር ሽማግሌ መወቃቀሱን፤ መደኛኘቱን - በአማካሪ
‘ጠቢባን’ ቢያፍን፤ መኖሪያን በሊዝ ቢያሲዝ…ሌላ ሌላውንም የኢትዮጵያውያንን አኗኗር ይትባህል ሊያጠፋ
ቢገዘግዝ…የገበሬው አኗኗር ‘በቻይናው፤ በህንዱ፤ በሳውዲው..’ ዲታ፤ አናት አናቱን ቢመታ…ኢህአዴግን
በሥልጣን እስካኖረ ለህወሃት እስከተመቸ፤ ኢህአዴጋውያን ቱጃሮችን እስከፈጠረ…እንግዲህ ልማት ማለት
ይኸው ነው፤ ለነበረከት ለነስብሃት፤ ለነአዜብ ለነሳሞራ፤ ለነአባዱላ ለነሃይለማርያም…
እንመለስ ወዳለማየሁ፤ …የተቀጠፈው ሳይበላ ሌላ መዘንጠፍ እውነት እንደሚባለው የልማት ነው ወይስ
የጥፋት? የማልማት ነው የማበላሸት?...የነባር መንደሮችን አኗኗር መንግሥት ፈርቶታል። መተሳሰቡ፤
መተዋወቁ፤ መደጋገፉና አለመፈራራቱ ከዚህ ቀደም ለነበሩ አመፆች በር ከፋች እንደሆነ ተገንዝቧል።
በተመሳሳይ ችግር ላይ የተጣደ ተደጋጋፊ ማህበረሰብ ቱግ ብሎ የተነሳ ዕለት ከአጠገቡ የሚጠራጠረው የለምና
ወደፊት ብቻ መቀጠሉ ዕሙን ነው።
ስለዚህ መንግሥት ልማት ሳይሆን ‘ብወዛ’ ላይ ነው። አንዷን መንደር ሃያ ቦታ በትኖ አንድ የማይተዋወቅ
ማህበረሰብ የመፍጠር ፍላጎት። የሚፈራራ፤ የማይደጋገፍ፤ የማይተሳሰብ ተጠራጣሪ ማህበረሰብ
ለአምባገነንነት ምቹ እንደሆነ ግልፅ ነው። እናም መንግሥት ልምድ ባለው ቁማርተኛ ቅልጣፌ መንደሮችን
እንደ ካርታ ይበውዛል። በዚህ መካከል ነባሩ ነዋሪ ይታመሳል፤ ይመሰቃቀላል፤ ፀጥተኛ ሞት ይሞታል። ወይ
ከተማዬ!
ብዙ ሃላፊነት የሚሰማቸው መንግሥታት አሮጌ ከተሞችን ከመመነቃቀር ታቅበዋል። ጥፋቱ ብዙ፤
ስብራቱም የማይጠገን እንደሆነ ያውቁታልና ነው። ለምሳሌ ግብፅ “አሮጌዋን ካይሮ’ እንዳለ ትታ ‘አዲሷን
ካይሮ’ ጥቂት ፎቀቅ ብላ ገንብታለች። ምክንያቱ ደግሞ የአሮጌዋን ከተማ አቧራማ መንገድ ደም ሥራቸው፤
ጉልቶቿን ሳንባቸው፤ ሺሻ ቤቶቿን ልባቸው…ያደረጉ ነዋሪዎች መኖራቸው በመታወቁ ነው። ናይጄሪያም
በቅርቡ ተመሳሳይ ርምጃ ወስዳለች። የአሮጌዋን ሌጎስ ዋና ከተማነት ለነዋሪዎቿ ትታ አቡጃን አዲስ
አቋቁማለች። ይሄ ሃላፊነትን በቅጡ መወጣት ነው። አዲስ አበባ፤ አዲስ አበባ ግን ‘ባልበላውም ልጫረው’
የሚል የዶሮ እልህ በተጠናወተው መንግሥት ሥር ወድቃለች። ወይ ከተማዬ!
ዕውነትም ወይ ከተማዬ1 ወይ አዲስ አበባዬ! ወይ ኢትዮጵያዬ!
3. ነጋዴው መንግሥትና ኢኮኖሚው
ጥንታዊዎቹ ፋርሶች ከእኛ ጋር የሚመሳሰሉ ሶስት ንጉሦች ነበሩዋቸው። ይህንን የሚነግረን የመጀመሪያው
ግሪካዊ የታሪክ ሰው ሔሮዱትስ ነው - ሲል ይጀምራል ብዕረተኛው አርበኛ ዓለማየሁ። አያይዞም ‘ፋርሶች
‘ቂሮስ’ የተባለው ንጉሥ እጅግ አዛኛቸው ስለነበር ‘አባት’ ነው ይሉታል። ልክ እኛ አጤ ምኒልክን ‘እምዬ’
እንደምንለው። አሁንም ፋርሶች ‘ካምቤሲስ’ የተሰኘ ንጉሣቸው ብዙ የግፍ ሥራ ስለዋለባቸው ‘ጨካኝ ነው’
ይሉታል። እኛ መንግሥቱ ሃይለማርያምን እንደምንወቅሰው መሆኑ ነው። ‘ዳርዮስ’ የተባለ ንጉሥ ደግሞ
ሊያገኝ በቻለበት ሁሉ ለማትረፍ የተነሳ በመሆኑና ህዝቡን በግብር አስጨንቆት ስለነበር ፋርሶች ‘ነጋዴ ነው’
ይሉታል። አሁን እኛ ይሄን መንግሥታችንን /ኢህአዴግን/ እንደምንወቅሰው ማለት ነው።
ዓለማየሁ ገላጋይ ‘ኢህአዴግን እከስሳለሁ’ በሚለው መድብሉ የክስ ዝርዝር አወቃቀሩ፤ የጥፋት መጠን
አደራደሩ፤ የታሪክ እማኝ የዕውነት ዳኛ አመራረጡ፤ ለኢህአዴግ ‘ይግባኝ’ አይመቹም። የዕውነት ዘር ይዘራሉ
እንጂ፤ ሀቅ አርግዘው ሀቅ አምጠው ለሀቅ ይፋረዳሉ እንጂ፤ የኢህአዴግን ወንጀሉን ውድቅ ክሱን ዝቅ
ለማድረገግ አልተፈጠሩም። ለኢህአዴግ ‘ይግባኝ’ አይመቹም!
11
ዓለማየሁ ክሱን ሲያጠናክር ዘረ-ቃሉ እንዲህ ይወርዳል፤
ወታደራዊውን መንግሥት የተካው የኢህአዴግ መንግሥት ከ”ነፃ አውጪነት” ወደ “ባርነት ከታችነት”
የተሸጋገረው በንግድ ነው። እንኳን ዜግነትን ሰው መሆንን እንኳን ከግምት ያልከተተ የንግድ አባዜ
ተጠናውቶታል። መሸጥ የለመደ ነውና የለበስነውን፤ የጎረስነውን፤ የቆምንበትን፤ የተቀበርንበትን ያስማማል።
ለዚህ መንግሥት ኢትዮጵያዊ ሁሉ ነጋዴ ነው። ቤተሰብ የንግድ ሽርካ ይመስለዋል። አባት ለልጁ
የሚናዘዘው በንግድ ኮንትራት አግባብ ነው ብሎ ደምድሟል። አባት ሲያወርስ፤ ልጅ ሲወርስ ከነፍስ አባት
ቀድሞ የሚገኘው መንግሥት ነው። በዚህ የአባትና የልጅ “የንግድ ልውውጥ” (ውርስ) ግብር መቀበል
የጀመረው ለዚህ ነው።
በዚህ መንግሥት የምንበላው ለማትረፍ ነው። የምንጠጣው ለማትረፍ ነው። ማኘክ ንግድ ሲሆን መዋጥ
ትርፍ ነው። አኝኮ የሚውጥ ሁሉ የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) የተጣለበት ለዚህ ነው፤ ይላል ብዕረተኛው።
አጀብ ነሽ አገር!
በደርግ ኮሚኒስት መንግሥት ዘመን ኢኮኖሚው ‘ባለህበት እርገጥ’ ነበር፤ እዛው ሞላ እዛው ፈላ።
በህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን “ነፃ ንግድ” መጣና ነጋዴው መንግሥት ተነጋጁ ህዝብ ሆነና አረፈው። ነጋዴው
መንግሥት እየገፈፈ ማትረፉ ሳያንስ፤ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማነቆው ይባስ!
ኢኮኖሚያቸው የዳበረ፤ የበለፀጉ ባለ ኢንዱስትሪ አገሮች ከሚባሉት አንዷ የዚህ ቅኝት አቅራቢ የሚኖርባት
አውስትራሊያ ናት። አንድ የአውስትራሊያ ሰራተኛ በሰአት አነስተኛ መነሻ ክፍያው ከ15 (አስራ አራት)
የአውስትራሊያ ዶላር ይጀምራል። በአውስትራሊያ ማህበረሰብ ውስጥ እንደ “ተጨማሪ እሴት ታክስ” /ቫት/
አይነት “የሸቀጥና የአገልግሎት ታክስ” /ጂኤስቲ/ የሚባል አለ። ይህ የታክስ ዐይነት በሥራ ላይ የዋለው
በቅርቡ ሲሆን ለዛውም በዘመኑ በነበረው የመንግሥት ምርጫ ወቅት ተፎካካሪው ፓርቲ ሀሳቡን ለህዝብ
አቅርቦ ህዝብም ይህንን ሀሳቡን ተገንዝቦ ይጠቅማልም ብሎ ስለመረጠው ነበር። እንግዲህ ልብ በሉ። ይህ
የአውስትራሊያ መንግሥት በስራ ላይ ያዋለው የታክስ አይነት ሀገሪቷ በድህነት እየማቀቀች፤ ህዝቡ ከእጅ ወደ
አፍ የሆነ ህይወት እንኳን በማይመራበትና በድህነት ወለል ላይ በሚገኝበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ አይደለም።
በዚህ ታክስ ህዝቡ በሚገዛው ሸቀጥ ወይም ውል ላይ 10% ተጨማሪ ይከፍላል፤ የነፍስ ወከፍ ዓመታዊ
ገቢውም ይህንን ያደርግ ዘንዳ ያስችለዋልና!
በአንፃሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በድህነት ወርዶ የተፈረጀ፤ ሥራ አጥነት የተንሰራፋ፤ ድምሩ ማህበረሰብ
ጭሮ አዳሪ፤ ከእጅ ወደ አፍ ብቻ የሆነ ህይወት የሚመራ። አንድ ኢትዮጵያዊ የቀን ሰራተኛ ከጠዋት እስከ
ማታ (ዘጠኝ፤ አስር) ሰአት ላቡን አንጠፍጥፎ ጥሮ ግሮ የሚያገኘው ገቢ በሰአት ተሰልቶ ሳይሆን በቀን
ውሎው ከአንድ ወይም ከሁለት ዶላር አይዘልም። እነሆ ነጋዴው መንግሥት የህዝቡንና የአገሪቱን ሁለንተና
ሶሺዮ ኢኮኖሚ ህልውና ገፍቶ ከዚችው ገቢ ላይ ነው “የተጨማሪ እሴት ታክስ” /ቫት/ ከሱቅ በደረቴው
አንስቶ የሚገፈው። “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ ይሏል እንዲህ ነው።
ኢህአዴግ “ከነፃ አውጪነት’ ህዝቡን ወደ “ባርነት ከትቷል” ሲል ዓለማየሁ መክሰሱ፤ መያዣ መጨበጫ
በሌለው ህይወት የሚዳክረውን ባተሌ ህዝብ ያለ ርህራሄ በመግፈፍ ላይ ያለ ለትርፍ ብቻ የቆመ ነጋዴ
መንግሥት መሆኑን ለማንጠር ነው።
እንንቀስ፤ ከዓለማየሁ ክስ፤ …እዚች አገር ላይ ንግድ መንግሥትና ህዝብ የሚገናኙበት ብቸኛው ማዕከል
ሆኗል። መንግሥትን የምንፈልገው አበድሮን እንድናተርፍ ብቻ ይመስለዋል። እሱም የሚፈልገን አራጣ
ሊበላብን። ህዝብ ለመንግሥት እንደ ተቀናቃኝ ባላንጣ ይታያል። መንግሥት ህዝብ እንዳያጭበረብረው
የሚጠነቀቅ ነጋዴ ነው። ስኳር በጨረታ የሚሸጥልን ከጥንቃቄዎቹ በአንዱ ሲጠቀም ነው።
መንግሥት የገዛ ህዝቡ የሚበላውን ውጪ ካለ ገበያ ጋር ያወዳድራል። ኬንያዊውን በዋጋ ካልበለጥን የገዛ
በቆሎአችንን አንበላም። አሜሪካዊውን በዋጋ ካልበለጥን የገዛ ቡናችንን አንጠጣም። ሳውዲ አረቢያውን በዋጋ
ካልበለጥን የገዛ ከብታችንን አንበላም። ከህንዱ ነጋዴ የተሻለ ዋጋ ካላቀረብን የገዛ መሬታችንን አናርስም።
…ገቢ ሸቀጥን ከውጪ ጥሬ እቃ ጋር ለማመጣጠን ስንቶቻችን ጦማችንን አደርን? ሠሊጥ ካየን ስንት
አመታችን ነው? ቡና ስንት ገባ? ስጋ ስንት ሆነ? ጥራጥሬስ?...ያገኘነውን ተፈላጊ ነገር እያጋፈፍን በመላክ
ቤታችንን አልዘጋንም? ቤተሰባችንን አልበተንንም? ጎዳና አልወደቅንም?...
12
አዎ ሀቅ ነው ዓለማየሁ! አበው ተናግረው ነበር በብሂል፤ ‘ሰው እንደ ቤቱ’ጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም’ ሲሉ።
ህወሃት/ኢህአዴግ ግን ጆሮ የለውም። ለአቶ መለስና ጀሌዎቻቸው የአበው ብሂል ‘ነፍጠኛ’ ነው። እና
አንጡራው ኢትዮጵያዊ ሥጋ በላ አልበላ፤ ሠሊጥ ኖረው አልኖረው፤ ቡና ጠጣ አልጠጣ፤ ጥራጥሬ አገኘ
አላገኘ…የኢህአዴግ ራስ ምታት አይደለም።
እነሆ ብዕረተኛውን ያቀርቧል፤ …መንግሥት ከጥላው ጋር በመወዳደር ከህልሙ ጋር በመፎካከር …ጩኸት
የሚሰማ ጭንቅ የሚረዳ አልሆነም። “በቡሃ ላይ ፎረፎር” እንዲሉ መንግሥትም የአገር ውስጥ ቻይና ሆኗል።
እንደ ማሰሮ አገንፋይ፤ እንደ ድስት አብሳይ…ቅኝቱ “አምጡ፤ አምጡ” የሆነ ሸቀጥ…
ለትምህርት የወጡ ልጆች ጠኔ እየጣላቸው ነው። በስራ የደደሩ እጆች ለምፅዋት እየተዘረጉ ነው። አፋራም
እናቶች የሰው ፊት እንደ እሳት እየገላመጣቸው ነው። ህፃናት ለሴተኛ አዳሪነት እየተዳረጉ ነው…በዚህ ሁሉ
መኻል፤ የመንግሥት ነጋሪት ይጎሰማል። “ገብር፤ ገብር” ይላል። እንግዲህ ከጎናችን ማን አለ?
መንግሥታችን ለችርቻሮ ተቀምጧል። ፖሊስ፤ ህግ፤ አዋጅ፤ መመሪያ…”ሸቀጦቹ” ናቸው። ስለ
አቅርቦታቸው ይቤዠናል። ተምኖ ይቀበለናል። ወስኖ ይወርሰናል…ከመንግሥታችን ጠባይ ውጪ ነጋዴነቱ
አይሎብናል።
ሊያገኝ በቻለበት ሁሉ ለማትረፍ የተነሳ የሚመስለው መንግሥታችን ስርቻ ለስርቻ እያሳደደ ገቢውን
በማሳደግ ላይ ይገኛል። ከጥላው ለመፎካከር፤ ከህልሙ ለመወዳደር…የማይደራደርበት ዘርፍ የለም። ችለን
የማናንቀሳቅሰውን ሸክም ለመጫን ማገናዘቢያ ሰአት አልመደበም፡፤ ከ”ገብርና አምጣ” ውጪ ከበሮና
ጭብጨባ የለውም። እንግዲህ ከጎናችን ማን አለ?
እኛም እንላለን። እርግጥ ነው ግብር ጥንትም ነበር። መንግሥትም ጥንትም ነበር። ግብርና መንግሥት
መንትዮች ናቸው። አንዱ በሌላው ውስጥ ይኖራል። ይፋፋልም። ሁለቱም ተዋህደው እየኖሩ እዚህ ደርሰዋል።
መንግሥት የሚያስገብረው፤ ህዝብም የሚገብረው መንግሥታዊ ሥራን ለማካሄጃ እንዲረዳው ነው።
መንግሥት መንግሥትነቱን ትቶ እንደ መንግሥትና እንደ ህዝብ አስተዳዳሪነት ማሰቡንና መተግበሩን አቁሞ
ነጋዴ ከሆነ ግን ያኔ - አገር ተጋጠ፤ ዜጋ ቀለጠ። እነሆ ይህንን ሀቅ ሲያስረግጥ የዓለማየሁ ዘገር ብዕር እንዲህ
ይላል፤
ስለ ሰዎች ዋይታ የግሬደሮች ጩኸት ምላሽ ይቀርባል። ስለ ቤተሰብ መፍረስ የመንገዶች መገንባት እንደ
ምክንያት ይሰጣል። ስለ ሰው ልጅ ሆድ ባዶ መሆን የምድር በህንፃ መጥገብ እንደ ማካካሻ ይሆናል።…የሰው
ልጅ በሸቀጦች ብቀላ እንደሚሳደደው ሁሉ ማዕከላዊነቱን በግንባታዎች ተነጥቋል። መንግሥት ከህዝብ ይልቅ
ግንባታዎችን ወደማስተዳደር ተሸጋግሯል። ከአገር ይልቅ የግንባታዎችን ሉዐላዊነት ይጠብቃል። ከድንበር
ይልቅ ለግንባታዎች ዘብ ይቆማል።…
እዚህ መካከል እኛ አለን። በቻይና ሸቀጥና በመንግሥት ግንባታ መካከል ተደፍጥጠናል። በግራ ለቻይና
በቀኝ ለመንግሥት እንሰራለን። በምትኩም ህልምና ቁጥር እንወርሳለን። ጥላሎት እናከማቻለን…
ዕውነት አንጥበኻል ዓለማየሁ፤ እኛም እንመሰክራለን፤ የሚያንቅ ሀቅ ነው እንላለን። አዎ፤ ኢህአዴግ
የአገሪቷ ኢኮኖሚ ዕድገት ተወንጭፏል ይላል፤ ተመንጥቋል። በሁለት አሃዝ /ዲጂት/ ገቢያችን ተመንድጓል
ሲል ይፎክራል። ታዲያ ገቢው የት ገባ? ስለምን ከዓመት ዓመት ተሻግረን ሁለት አስርታትም እንኳ ዘ ልቀን
ምነዋ የአንጡራው ኢትዮጵያዊ የህይወት ለውጥ እንደ ግመል ሽንት የሁዋሊት ሆነ? ምነዋ እያደር ከድጡ ወደ
ማጡ ወረደ?
የአንጡራው ኢትዮጵያዊ ፀጥተኛ ሞት፤ ከሞቱት በላይ ከቆሙት በታች ፍጭርጭሮሽ ህይወት፤ እንደው
ከቶ…ሁሉ ተከፍቶ ሳይህን እንደው ተገርብቦ፤ ሲመለከቱት ምን ይመስላል? እንደምንስ ያሳምማል?
ሠፈር ክልሉን እየዞረ፤ አገር ቀዬውን እያካለለ፤ የአንጡራውን ዜጋ ህይወት የተጋራ - ብዕረተኛው አርበኛ፤
እነሆ ሲያብራራ…
…ብዙ ምግብ ቤቶችን ለመጎብኘት ሞክሬያለሁ። ሁሉም ከተመጋቢ ፊት የሚያነሱትን ትርፍራፊ ለተቸገረው
መመፅወት ካቆሙ አመታት ተቆጥረዋል። ተረካቢዎች አሉዋቸው። ከሶስት መቶ እስከ አራት መቶ ብር
ይሸጡታል። ከቀን ወደ ቀን የትርፍራፊ ዋጋ እያሻቀበ ነው። በችርቻሮ፤ በስኒ ማስቀመጫ እየተሰፈረ እስከ
አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ይሸጣል። አንድ ሰው ለመጥገብ ቢያንስ ስምንት ብር ያስፈልገዋል። ክብሩን፤
ቅርሱን፤ ልብሱን…ያገኘውን ሸጦ ይምጣ…ወዴት እያመራን ነው?
13
መቼም የእኛ ቄሳር (ገዢ)…ልግስና ያድርጉልን፤ እህል ይስፈሩልን፤ ዘይት ይመዝኑልን አይወጣንም። ነገር
ግን እንደ ዶሮ ጭረን ያገኘነውን እንደ ጫጩት ካፍ ካፋችን መልቀማቸውን ቢተዉን መልካም ነበር። ደሳሳ
ምግብ ቤቶች ድረስ ወርደው ‘ቫት’ ይሉት መልቀሚያ መንቆራቸውን በፍጥነት ከመጠቅጠቅ ቢገቱልን
በቂያችን ነበር። እንግዲህ ይሄ የቄሳሩ ሸክም እስከ ትርፍራፊው ድረስ ወርዶ ኢትዮጵያዊ መተዛዘናችንን ነሳን።
ነባር ጨዋነታችንን አሳጣን…
እዚህ ዘመን ላይ ከግብር ጋር ተያይዞ እንደ ቀይ ሽብር ዘመቻ ቤት ለቤት በተካሄደው የግብር አሰሳ ብዙ
ጭሮ አዳሪዎች እጃቸውን አጣጥፈው እንዲቀመጡ ተፈርዶባቸዋል። ሻይ በፔርሙዝ እያዞረች የምትሸጥ
የልጆች እናት ሱቅ ሳይሆን ጥጋት ቢጤ ቡና ማፍያዋ በመታሸጉ ወደ ደቡብ ሱዳን ለመሄድ መገደዷን በአይን
እማኝነት ያየሁት ነው። እንጀራ እየጋገሩ ለትናንሽ ሆቴሎች የሚያቀርቡ አንዲት እናት በአዲስ ንግድ ፈቃድና
በዳግም ምዝገባ ሰበብ እጅ እግራቸው ታስሮ ተቀምጠዋል። በደንበኞቻቸው የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር
ካላወጡና ህጋዊ ደረሰኝ ካልሰጡን እንጀራ አንረከብም የተባሉት ወይዘሮ የቤተሰብ ሃላፊና የልጆች እናት
ናቸው።
ከእንዲህ ያለ ሮሮ በስተጀርባ ያለ ልማት እንዴት ያለ ነው? ከገዛ ሥጋ መዋጮ እንዲደረግለት የታሰበው
የሰማየ ሰማያት ጉዞ የት ያደርሰናል?...ለመሆኑ ወዴት እያመራን ነው?
አዎ እኛም እናስተጋባለን፤ ወዴት እያመራን ነው? ለመሆኑ በህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን በኢኮኖሚ መነጠቀች
የተባለችው ኢትዮጵያ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዜጎቿ በኢትዮጵያ ቀዳሚ ታሪክም ሆነ ወይም ድሃ በተባሉት
የአፍሪካ መንግሥታት ታሪክ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ የማያውቅ በስኒ ማስቀመጫ እየተሰፈረ የሚሸጥ ትርፍራፊ
ምግብ ተመጋቢ እንዴት ሊሆኑ ቻሉ? ይህ ውስጥን ካላመሰ፤ ሲቃው ካላጥወለወለ፤ የኑሮው ዝቅጠት የቁም
ነፈዝ ካላደረገ ሌላ ምን? መንግሥት ለትረፉ ድልበት፤ ለህልሙ ስምረት…ከዚህ በላይ እንደምን አድርጎ
የዚህን ህዝብ ሰብዕና ማድቀቅ ይችላል?
እነሆ አስቀድሞ የጨለፍነው የኑሮ ገመና የአዲስ አበባውን ነውና፤ ዓለማየሁን ተከትለን እስቲ ደግሞ ወደ
ሐዋሳ እናቅና…
ሐዋሳ ነቃች። እንደ አራስ ህፃን ከፈገግታ ጋር እንቅልፍ የጠገቡ አይኖቿን ስታሻሽ ታየች። የፍቅር ሀይቅ
እንደ ዝናር የታጠቀችው ከቀለህ የማይበልጡ ሱቆችም ተከፈቱ። የሚከፈቱት በብስራት እንጂ በተዘጋ
በራቸው አይደለም። ምክንያቱም አብዛኞቹ ሱቆች በር የላቸውም። ዓሳ መጥበሻ የብረት ቁናቸውን አንስተው፤
ቡና ማፍያ ስኒያቸውን አዝለው፤ በር የሌለው ሱቃቸውን ትተው ይሄዳሉ። ጠዋት በማለዳ ተመልሰው
ሲያሰነዳዱና ውሃ አርከፍክፈው ሲጠራርጉ የሱቁ መከፈት ብስራት ተነገረ ማለት ነው…
ከሐዋሳ ጠዋት ጋር ወደሚዳበለው የጀበና ቡና አመራሁ። የህፃን ልጅ አልጋ የሚያክል ረከቦት ብዙ ሳቂታ
ስኒዎችን ታቅፎ ጠበቀኝ። አንዲት ትልቅ ጀበና የጣደች ጠይም ልጅ እንደ ስኒዎቹ እየሳቀች ተቀበለችኝ።
ከስኒዎቹ እጅግም ከፍ የማይሉ ብዙ ጀበናዎች ልጅቷን ከበዋታል። አይቼ የማላውቀው አይነት ጀበናም
አለ።…ልጅቷ የጀበናዎቹን መምጫ አካባቢ ጠቆመችኝ።
“ይሄ ከአዲስ አበባ ነው”
“እሺ”
“ይሄኛው ከትግራይ ነው” ቡናው በአፉ ነው የሚቀዳው።
“እሺ”
“ይሄ ደግሞ ከደቡብ ነው።…ከሐረር…ከመቱ አካባቢ…”
ለካ አንድነት ነው በጀበና የተወከለው። ሐዋሳ አሰባሳቢ መሆኗ ነው። አንዱ ጀበና ከሌላው ጋር ተሰባጥሮ
ተቀምጧል። ጀበናን ከጀበና የሚለየው ቅርፅ ብቻ ነው። ቻርተሩ፤ ፖሊሲው፤ የክልል
መንግሥቱ…አይደለም።…
ሐዋሳ መስተንግዶዋ ፅንፍ-አልባ ነው። ከፍ ብሎ መዝናናት ለሚፈልግ እስከ “ሃይሌ ሪዞርት” አለለት። ዝቅ
ማለት ለሚሻ ”አሞራ ገደል” አለለት…አሞራ ገደል እንደ እናት ፍጡር ከፍጡር ሳይለይ ሁሉንም የሚያቅፍ፤
የመጣ የማይመለስበት መዝናኛ ነው።…
“አሞራ ገደል” ኩታንኩቱ ይበዛል። የሚታየው ሁሉ አስደሳች አይደለም። የዓሳ ሾርባ የሚቀቀልበት ጎስቋላ
በርሜል አካባቢው ላይ ከሚታዩት ሰዎች እንደ አንዱ ይመስላል። ሐዋሳ የገፋቻቸው የሚያፈገፍጉት ወደዚህ
14
ነው። ህፃናቱ ሎሚ፤ ቂጣ…ይዘው በየተስተናጋጁ ስር ይሹለከለካሉ። ሁሉም የመሬት ቁራሽ እንጂ የሰው
ፍጡር አይመስሉም። አፈር ጎርሰው አፈር ለብሰው “ሎሚ፤ ቂጣ” ይላሉ…
የሚሰቅቅ ትዕይንት የሞላበት አካባቢ ነው። ከሎሚና ከቂጣው ጋር አይናቸውም በላተኛው አጎራረስ ላይ
ይንከራተታል። ዓሳ ጠባሹ ከበላተኛው ፊት ያነሳውን የዓሳ አጥንት የቆሻሻ በርሜል ላይ ሲደፋ ከጭልፊት
የፈጠኑ ልጆች እንደ ዝንብ ግር ብለው ይሰፍሩበታል። ስጋ ይኑረው አይኑረው ሳያረጋግጡ በእጃቸው አፍሰው
ራቅ ይላሉ። ከዚህ በሁዋላ ነው የሚበላው ከማይበላው የሚመረጠው። አቧራ የለበሰ ፊታቸው በዓሳው ቅባት
አፋቸውጋ ብቻ ወዝቶ ይመለሳሉ።
“ሎሚ…ቂጣ” አዙሪታም ህይወት።
ደግሞ ሌሎች ህፃናት አሉ። ሎሚና ቂጣ አይዙም። “አገልግሎት ሰጪዎች” ናቸው። ፀጉረ ልውጥ ሲያዩ
“ዳንስ ትፈልጋላችሁ?” ይላሉ የሲዳምኛ ቃና ማለው አማርኛ። “አንድ ዳንስ አንድ ብር ነው”
ያግባባሉ።…አራትና አምስት አፈር ለበስ ህፃናት የመኖር ፍጭርጭሮሻቸውን በዳንስ
ያሳዩዎታል።…ለኢንተርቴይመንቱ የሚከፍሉት ዋጋ ካለባቸው ችግር አንፃር ምንም ሆኖ መታየቱ ግድ ነው።
አንድ ብር ላንድ ዳንስ፤ ለኑሮስ?
አሞራ ገደል የሐዋሳ ሀፍረተ ገላ ነው። መዝናናትም በነውር ነገሮች መካከል የመሹለክለክ ጀብዱ
ይሆንብዎታል። እጅግ የሚያሰቅቀው የህፃናቱ ነው። ቀኑን ሙሉ ለመኖር በመፍገምገም ያሳልፋሉ። ሆድን
ለመሙላት፤ ህይወትን ለማቆየት ብቻ። በተረፈ እነዚህ ልጆች ጭንቅላት ውስጥ “ነገ” የለም። ዛሬ ዋስትና
አጥታ የምን ነገ?
እነሆ ደራሲው ከአሞራ ገደል፤ ሐዋሳ ከቀዳቸው አንገት አስደፊ፤ አንጀት አጣፊ፤ ልብ አንሰፍሳፊ፤ ሰፊ
የመኖር ፍጭርጭሮሽ ታሪኮች ለቅኝታችን ናሙና የነቀስነው ይህን ይመስላል፤ ኑሮ ካሉት መቃብርም ይሞቃል
- እንዲሉ። ህወሃት/ኢህአዴግ እንደ መንግሥት ዘመነ መንግሥቱ እየተቆጠረ ዓመታት በገፉ ቁጥር…የድምሩ
ኢትዮጵያዊ ህይወት ለውጡ - አዛውንቶች አፋራማ ለሆነ ልመና፤ ወጣቶች መያዣ መጨበጫ በሌለው የኖሮ
አዘቅት ውስጥ በስራ አጥነት…ተስፋ በጨለመበት ህይወት ዛሬን ተንጠራውዞ ማለፍ፤ ህፃናት ለሰቆቃ የኑሮ
ፍጭርጭሮሽ…ተዳርገው መታየቱ የዘመኑ መንግሥት አገዛዝ አይነተኛ ውጤት ሆነዋል። መንግሥት
በዘረኝነቱና በአምባገነንነቱ ላይ ነጋዴነቱ አይሎ ህዝብንና ሀገርን የሚመዝንበትና የሚመራበት ስሌቱ፤ ቅኝቱ
ሁሉ ከቶም ተለውጧል። የሚከተለውን የዓለማየሁ ድምዳሜ ልብ ይሏል፤
ለዚህ መንግሥት ኢትዮጵያ የንግድ “ዩኒየን” ናት። ክልሎች የንግድ ኮንፌዴሬሽኑን ያቋቋሙ የንግድ
ቀጠናዎች ናቸው። የክልሎች መገንጠል ከንግድ ኮንፌዴሬሽኑ እራስን ማግለል ነው። ንግድን ማዕከል
ላደረገው መንግሥት ሀገር፤ ዜጋ፤ ባንዲራ…ዋጋ የላቸውም። ጠላት የሚመጣው የንግድ መደብርህን ለመዝረፍ
ነው፤ አንተም የምትዋጋው መደብርህ እንዳይዘረፍ ብቻ ነው። ሀገርና ዜግነት እንዲህ ዝቅ ያሉበት ክፉ “ጊዜ”!!
ታዲያስ! ዓለማየሁ ገላጋይ ኢህአዴግን መክሰስ ይነሰው?!
አዎ! በዚህ ቅኝት በቀረቡትና ደግሞም ባልቀረቡት በርካታ የህወሃት/ኢህአዴግ ወንጀሎች እኔም ኢህአዴግን
እከስሳለሁ!!
መቋጫ
‘ኢህአዴግን እከስሳለሁ” የሰላሳ ስድስት መጣጥፎች መድብል ውጤት ነው - ብለን ነበር በመነሻችን።
ታዲያ አስካሁን እያሰባጠርንና እያሰናሰልን ራሳችን በፈጠርናቸው ርዕሶች ስር የቃኘነው አምስቱን (5ቱን)
መጣጥፎች ብቻ ነው። ይህ ማለትም ከሳላሳ በላይ በሥነ ፅህፍ ክህሎት የመጠቁ፤ በበርካታ ፈላስፎች፤ የሥነ
ህብረተሰብ ተመራማሪዎችና ዓለም አቀፍ ዕውቅና በተቸራቸው ደራሲያን አባባሎችና አስተምህሮዎች የታጀቡ
የተለያዩ የታሪክክና የፍጭርጭሮሽ ህይወት ደርዝ ያላቸው መጣጥፎች የመፅሀፉን አንባቢ ይጠብቃሉ። ይህን
ታላቅ መፅሀፍ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ - የህወሃት/ኢህአዴግ ደጋፊም ይሁን ተቃዋሚ ወይም መኻል ሰፋሪ
አፈላልጎ ሊያነበው የሚገባ ነው። የብዕረተኛውን አርበኛ መፅሀፍ ማንበብ ከሀገርና ከህዝብ ጋር በደምና
በልብ፤ በአካልና በመንፈስ - ያገናኛልና!!
ምጥቀትና ጥልቀት ያለውን የብዕረተኛውን አርበኛ፤ የዓለማየሁ ገላጋይን መፅሀፍ እንዳነበው በፖስታ
አሽገው ለላኩልኝ የደቡብ አውስትራሊያ ወዳጆቼ በዚህ አጋጣሚ የከበረ ምሥጋናዬ ይድረሳቸው!
15
ብዕረተናው አርበኛ ዓለማየሁ ገላጋይ ሆይ! “ኢህአዴግን እከስሳለሁ” ብለህ ከዘመንና ከፖለቲካው ሁኔታ
የተቀበልከውን አሻራን ይዞ ያለመቀበር ፍጭርጭሮሽ ውጤት የሆነውን፤ የልብህን ዘገር የዘር ቋጠሮ
የበተንክበት መፅሀፍ ከቅድስቲቱ አገር ኢትዮጵያ አድማሷን ዘልቆ ባህር አቋርጦ ካለንበት ደርሶን
ተመልክተነዋል። ውስጣችንን ዘልቆም ለህመም ዳርጎናል፤ ከተኛንበትነም አባንኖናል። ራሳችንንም ጠይቆናል፤
ሞግቶንማል። ከዚህ ሌላማ…ምንስ መናገር፤ ምንስ ማቅረብ እንችላለን? ስለ ሀገርህና ስለ ህዝብህ ላደረግኸው
ሁሉ የኢትዮጵያ አምላክ ‘ሠላምና’ ጤናውን ሰጥቶ ይጠብቅህ። የኢትዮጵያ ባንዲራ ባለህበት በሄድክበት ጥላ
ከለላ ይሁንህ!!
በመጨረሻም፤
ኢትዮጵያ በማህፀኗ ውስጥ ባሉት ትንታግ ልጆቿና መሪዎቿ በሰከነና ህዝብን ባሳተፈ ሠላማዊ ትግል
በየካቲት 1966 ዓ/ም የጀመረችውን አብዮት ከግብ ማድረሻዋ ጊዜ በቅርብ እርቀት ላይ ይገኛል። አዎ!
ኢትዮጵያ በማህፀኗ ውስጥ ባሉት ልጆቿና መሪዎቿ የግፍ አገዛዝን ቀንበር ታወርዳለች! ከዚህ “ክፉ ዘመንም”
ትገላገላለች!! የሠላም፤ የፍቅር፤ የአንድነት፤ የእኩልነትና የመልካም አስተዳደር ዘመን ብሥራት ችቦም
ታበራለች!!
በያለንበት ቸር ይግጠመን!
ጥቅምት 2006 ዓ/ም
ኦክቶበር 2013
ሲድኒ አውስትራሊያ
ለአስተያየትዎ፤ የመልዕክት አድራሻዬ ይኸውልዎ፤ mmtessema@gmail.com

No comments:

Post a Comment