Sunday, October 6, 2013

የተቃዋሚዎች የሰላማዊ ሠልፍ ጥያቄ ከቀጠለ እንደሚቆም ገለጹ! የወያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

‹‹በኢሕአዴግ ውስጥ መከፋፈል አለ የተባለው ምኞት ነው››  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ
የሃይማኖት አክራሪነት ትግል ፖለቲካዊ ነው አሉ
-የተቃዋሚዎች የሰላማዊ ሠልፍ ጥያቄ ከቀጠለ እንደሚቆም ገለጹ
-በኬንያ የደረሰው ጥቃት በኢትዮጵያ ላይ እንደደረሰ ይሰማናል ብለዋል
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሕልፈት ተከትሎ በ2005 ዓ.ም. መስከረም ወር ላይ በይፋ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሥልጣን ቆይታ አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ የአንድ ዓመት የሥልጣን ቆይታቸው ከተቆጠረ ሁለት ሳምንታት በኋላ ባለፈው ዓርብ ለአገር ውስጥና ለውጭ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ይህ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ወደ ሥልጣን የመጡበትን አንደኛ ዓመት ለማስታወስ ባይሆንም፣ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ እንዲሁም በአኅጉራዊና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ በመስጠት ከጋዜጠኞች ለቀረቡ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በዋናነት ካነሷቸው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዋነኞቹ በኢትዮጵያ የሃይማኖት አክራሪነትና ሽብርተኝነት፣ በኢሕአዴግ ውስጥ አለ ስለሚባለው አለመግባባትና የተቃዋሚ ፓርቲዎች በሰላማዊ ሠልፍ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ይገኙበታል፡፡ በኢኮኖሚ ረገድ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በተጠናቀቀው ዓመትም ፈጣን ዕድገት ማስመዝገቡን፣ የግል ባለሀብቶች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው ዘርፎች ለመሳተፍ አለመፈለግ፣ መሠረታዊ በሚባሉት የመጠጥ ውኃ፣ የሞባይል ስልክና የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎቶች የሚስተዋሉ የአገልግሎት መቆራረጦች ሊቀረፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋዜጠኞች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ዕድል ከመስጠታቸው በፊት ባለፈው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አገሪቱ ስላስመዘገበቻቸው ውጤቶች አጠር ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በእሳቸው ማብራሪያ መሠረት የአገሪቱ ኢኮኖሚ በተጠናቀቀው ዓመትም በፈጣን ዕድገት ውስጥ አየተጓዘ ነው፡፡ ወደ መግለጫው ከመግባታቸው ቀደም ብሎ ደርሶኛል ባሉት መረጃ መሠረትም የአገሪቱ የግብርና ዘርፍ ቀደም ሲል ከነበረው ዓመት የተሻለ ዕድገት ማስመዝገቡን፣ በተመሳሳይም የኢንዱስትሪ ዘርፉ ካለፈው ዓመት የተሻለ ዕድገት በተጠናቀቀው ዓመት ማሳየቱን አስረድተዋል፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውና ላለፉት ዓመታት ከሌሎቹ ዘርፎች የተሻለ ዕድገት ሲያስመዘግብ የነበረው የአገልግሎት ዘርፍ፣ በተጠናቀቀው ዓመት ያስመዘገበው ዕድገት ቀደም ሲል ከነበረው ቅናሽ ማሳየቱን፣ ነገር ግን የተመዘገበው ዕድገት በራሱ ፈጣን የሚባል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የምትገኝበት አካባቢ ለሽብር የተጋለጠ መሆኑን ከግምት በማስገባት መንግሥታቸው በአገሪቱ ደኅንነት ላይ ሲሠራ መቆየቱን፣ እንዲሁም ኢትዮጵያን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአፍሪካ ኅብረት በሚገባ የወከለ ተግባር መከናወኑን አስረድተዋል፡፡
ለመግቢያ እንዲረዳ ካቀረቡት አጠር ያለ ማብራሪያ በመቀጠል ጥሪ ለተደረገላቸው 30 የሚሆኑ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች መድረኩን ለጥያቄ የለቀቁ ቢሆንም፣ ከእርሳቸው ጥያቄ የመቀበልና ምላሽ የመስጠት ፍላጎት ጋር ያልተገናዘበ ፕሮግራም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ የተቀመጠ በመሆኑ፣ ጥያቄ መቀበል የቻሉት ከአምስት ጋዜጠኞች ብቻ ነው፡፡
ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል በኢሕአዴግ ውስጥ መከፋፈል መኖሩ እየተሰማ እንደሆነ በመጠቆም፣ በሊቀመንበርነት ‹‹የሚመሩት ፓርቲ ጤንነት እንዴት ነው?›› የሚል ጥያቄ ይገኝበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ለዚህ ጥያቄ የመረጡት ምላሽ በጣም አጭር ነው፡፡ ‹‹በኢሕአዴግ ውስጥ መከፋፈል አለ የተባለው ምኞት ነው›› በሚል ብቻ የተወሰነ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ይበሉ እንጂ በገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውስጥ መለስተኛ አለመግባባት መኖሩን፣ በተለይ ደግሞ ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የተሻለ ተሰሚነትና የበላይነት እንዳለው በሚነገርለት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ውስጥ አለመግባባት መኖሩ ይነገራል፡፡
በሕወሓት ውስጥ ያለው አለመግባባት የፓርቲው ደጋፊዎችን ጥያቄ ውስጥ የከተተ መሆኑንና በድርጅታቸው አካሄድ ላይ ጥያቄ እንዲያነሱ ማድረጉን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ ሕወሓት በተመሠረተበትና ሰፊ መሠረቱን በጣለበት ትግራይ ክልል ውስጥ ጥያቄ እየተነሳ እንደሆነ ይናፈሳል፡፡
ግንቦት 7 የተባለው መቀመጫውን በውጭ ያደረገው ተቃዋሚ ድርጅት የገዢውን ፓርቲ አገዛዝ ለማብቃት የኃይል ትግልን እንደ ብቸኛ አማራጭ በመውሰድ በተለየ የትጥቅ ትግል ጥቃቱን ለመሰንዘር መሰናዳቱን በቅርቡ ስለማስነገሩና በአገር ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ ባካሄዱት ሰላማዊ ሠልፍ ለሚያነሱት ጥያቄ የመንግሥት ምላሽ ምንድን ነው የሚሉት ሌሎች የቀረቡ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽም ‹‹ግንቦት 7 ተናገረ ስለተባለው ወሬ ሰምቻለሁ፡፡ ሕልም አይከለከልም፡፡ ሲነሱ ሕልም መሆኑን ያውቁታል፤›› ብለዋል፡፡
በአገር ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ መብታቸው እንደሆነ በመግለጽ ምላሽ መስጠት የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ፓርቲዎቹ የሚያቀርቡት ጥያቄ ቀድሞውንም የታወቀና ከዚህ ቀደም መንግሥት ምላሽ የሰጠበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹ፓርቲዎቹ በሚያቀርቡት ጥያቄ ላይ መንግሥት ያስተዋለው አዲስ ነገር ከዚህ ቀደም ቤት ውስጥ ሆነው ይጠይቁት የነበረውን አሁን በአደባባይ ነው እየጠየቁ ያሉት፡፡ ይህ መሆኑ ዲሞክራሲያዊ ስኬት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ፓርቲዎቹ እያነሱ የሚገኙት ከዚህ ቀደም የተነሳና መንግሥትም መልስ የሰጠበት በመሆኑ የምንሰጠው መልስ ምን እንደሆነ ነው ያልገባን፤›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርቲዎቹ ጥያቄ ምን እንደሆነና መንግሥት ከዚህ ቀደም ምን ብሎ ምላሽ እንደሰጠ ግን በዝርዝር የተናገሩት የለም፡፡ ቢሆንም ፓርቲዎቹ በዋናነት ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል የፀረ ሽብር አዋጁ መሰረዝ እንደሚገባው፣ የታሰሩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች እንዲፈቱና መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይግባ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች በፓርቲዎቹ እየተነሱ ቢሆንም፣ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የውጭ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም ካነሷቸው፣ መንግሥትን ከተቹባቸው፣ አሁንም የኢትዮጵያ መንግሥትን ከሚወቅሱባቸው ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማቱ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ላይ ለሚያቀርቡት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሪፖርት መንግሥት የተወሰኑ ምላሾችን መስጠቱን ከግምት በማስገባት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ለሚነሱት ጥያቄዎች ‹‹መንግሥት ቀደም ሲል ምላሽ የሰጠበት ነው›› ማለታቸው ከዚህ የመነጨ ይመስላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በዚህ ላይ ማብራሪያ ባይሰጡም፣ የፓርቲዎቹን ጥያቄዎች አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ መስጠት ቀጥለዋል፡፡ የቀጠለው ምላሻቸው ስላቅና ወደፊት ሊኖር ስለሚችለው የመንግሥታቸው ዕርምጃ የተካተተበት ነው፡፡
በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ወደ ዘጠና የሚጠጉ ፓርቲዎች እንዳሉ የተናገሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ዘጠና ፓርቲዎች አሉ፣ ዘጠና እሑዶችን መጠበቅ ነው፤›› በማለት ፓርቲዎቹ እሑድ እሑድ ባደረጓቸው ሰላማዊ ሠልፎች በሚያቀርቡት ጥያቄ ተመሳሳይነት ላይ በስላቅ ተናግረዋል፡፡
‹‹መንግሥት ምን ምላሽ መስጠት እንዳለበት ሊገባው አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄውን በተመለከተ መንግሥት አቋሙን ከዚህ ቀደም በግልጽ አሳውቋል፤›› የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ፓርቲዎቹ ለሚያደርጉት ሰላማዊ ሠልፍ ‹‹በየእሑዱ ጥበቃ ማቆምና ተመሳሳይ ጥያቄ ማድመጥ ያሰለቻል፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ተመሳሳይነት ያለው ጥያቄ ያነገበ ሰላማዊ ሠልፍ የሚቀጥል ከሆነ ‹‹ሠልፉ እንዲቆም ይደረጋል›› በማለት የመንግሥታቸውን የወደፊት ዕርምጃ አሳውቀዋል፡፡
ከተጠየቁዋቸው ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጥያቄዎች መካከል በኢትዮጵያ የሃይማኖት አክራሪነትን የሚመለከት ይገኝበታል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን በመውሰድና ጠንከር ያለ ድምፅ በመጠቀም የጉዳዩን አሳሳቢነት አንፀባርቀዋል፡፡
አክራሪነት በውጭ ኃይሎች የሚደገፍ አመለካከት መሆኑን በመግለጽ የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንቅስቃሴው ሃይማኖትን ተገን ያደረገ በመሆኑ ከዋነኞቹ ጉዳዩ የገባቸው አራማጆች ይልቅ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሃይማኖት ተከታይ ‹‹ፅድቅ የሠራ እየመሰለው ተሳስቶ የሚገባ ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹የአክራሪነት ትግል ለእኔ የፖለቲካ ትግል ነው፤›› በማለት በአገሪቱ የሚስተዋለውን ከሃይማኖት ተቋማት ተከታዮች ለሚነሳ ፖለቲካዊ ጥያቄ የመንግሥት ምላሽም ፖለቲካዊ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
በዚህ የአክራሪነት እንቅስቃሴ ዙሪያ መንግሥታቸው ቀይ መስመር እንዳስቀመጠ፣ ይህም የሌላውን እምነት መጋፋት እንደሆነ በመጠቆም ከዚህ መለስ ማንኛውንም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
‹‹ከቀይ መስመር በላይ መሄድ የሚፈልግ ይቆነጠጣል፤›› በማለት ጠንከር ያለ ዕርምጃ መንግሥታቸው እንደሚወስድ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ባለማወቅ ከአክራሪዎች ጋር ተለጥፈው የሚሄዱ ራሳቸውን እንዲነጥሉ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፤›› በማለት መድረኩን ተጠቅመዋል፡፡
በኬንያ ናይሮቢ ከተማ የደረሰው የሽብር ጥቃት በኢትዮጵያ ላይ እንደደረሰ ይሰማናል በማለት ሐዘናቸውን በመግለጽ በሽብርተኝነት ላይ ለቀረበ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ከሽብርተኝነት ነፃ ነኝ ብሎ በአሁኑ ወቅት ማሰብ አይቻልም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
ሽብርተኝነት አሁን በማንኛውም አገር ውስጥ ያለ ፈተና መሆኑንና አደጋውንም በራስ ብቻ መታገል እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ ሽብርተኝነት ሕዝብ ውስጥ የሚደበቅ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝብን ያሳተፈ ፀረ ሽብር ትግል ዋነኛ መሣሪያው እንደሆነ፣ የፀጥታና የደኅንነት ኃይል ደግሞ በተጨማሪነት እንደሚሳተፍ ተናግረዋል፡፡

No comments:

Post a Comment