Wednesday, April 1, 2015

ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ያስፈልጋል

ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ያስፈልጋል፤ ለውጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይኾን የትም ያስፈልጋል። የለውጥ ፍላጎት ተፈጥሯዊ ስለኾነ አልፈልግም ብለው ቢሸሹት እንኳ አደኑን አያቆምም። የትኛውም ሰው (ገብቶትም ይኹን ሳይገባው) ከእንቅልፉ በባነነ ቁጥር ለውጥ መሻቱ የማይቀር ጉዳይ ነው። ይኹን እንጂ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያኖች ከዚህ ከተለመደው ለየት ያለ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል። ምን ዐይነት ለውጥ? መልሱ ቀላል ነው። የሥርዐት ለውጥ።
በፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርገው አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል “የሥርዐት ለውጥ ያስፈልጋል ወይስ አያስፈለግም?” በሚለው ጉዳይ ላይ ብዙም ብዥታ ሳይኖርበት በአንድ ድምጽ የሚስማማ ዐይነት ነው። ልዩነቱ ይህ የሥርዐት ለውጥ መምጣት ያለበት የትኛውን መንገድ (አማራጭ) እንከተል በሚለው ላይ ነው። ገዝፈው የወጡ ሁለት አማራጮች አሉ፤ ሥርዐቱን በሠላማዊ መንገድ ለመቀየር መታገል እና በትጥቅ ትግል (በሚያውቀው ቋንቋ ማናገር) መፋለም ናቸው።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በብዙ ከንፈር መጣጭ “አዛኞች” የተሞላ ቢኾንም፤ ጥቂቶች ግን ጎራ ለይተው ሐሳብ ይፈትላሉ፤ ይቀምራሉ፣ ያሻሉ፣ ያፋጫሉ። የሰላማዊ ትግል አማራጭ በር ጨርሶ አልተዘጋም የሚል መከራከርያ የሚያቀርቡት ወገኖች የትጥቅ ትግል አማራጭን እንደ መፍትሄ ለመውሰድ ይቸገራሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከ2005 ምርጫ በሁዋላ ሥርዐቱ በሰላማዊ ትግል ሊመጣ የሚችለውን ለውጥ ለማዳፈን ቆርጦ ስለተነሳ ምህዳሩን አጥቦ ፍጹማዊ አምባገነንነትን እያንሰራፋ ነው የሚል መከራከርያ ያቀርባሉ። ያለፉትን ዐሥር ዓመታት ብዙ ኪስ የሚቀዱ ዝርዝሮችና ልብ የሚያፈሱ ጭቆናዎች ዋቢ አድረገው ያስቀምጣሉ። በዋነኝነትም “ሥልጣን የምትፈልጉ ከኾነ ጫካ ግቡ” የሚል አመለካከት ከሚያራምድ መንግሥት ጋራ የሰላማዊ ትግል ቁማር መጫዎት ሩቅ አያስኬድም ይላሉ።
የትጥቅ ትግል አማራጭን በጥርጣሬ የሚያዩትም ኾኑ ጨርሶ መስማት የማይሹት ሐሳቡ የሚጎፈንናቸው በጉዳዩ ላይ ኤርትራ (የኤርትራ መንግሥት) ስላለችበት/ስላለበት ነው። አንዳንዶች ከኤርትራ መንግሥት ጋራ የሚደረገውን ትብብር/ግንኙነት በጥርጣሬ ከማየትም አልፈው “አላስፈላጊ ጋብቻ” ነው የሚል መከራከርያ ይዘው ይነሳሉ፤ ሌሎች በተግባር ካላየነው አናምንም ብለው የማርያም መንገድ እየሰጡ ልጓም ያዝ ለቀቅ ያደርጋሉ።
ደረሰ ጌታቸው የራሱን መከራከርያ ነጥቦች ይዞ መጥቷል። የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ የትኛውን አማራጭ እንጠቀም?

No comments:

Post a Comment