Wednesday, April 1, 2015

አሳዛኙ የተገን ጠያቂዎች ይዞታ በፈረንሳይ

በአሁኑ ጊዜ ህገ ወጥ በሚባል መንገድ በአደገኛ ጉዞ አውሮፓ የሚደርሱ ስደተኞች በሙሉ አውሮፓን እንደጠበቋት ሆና አያገኟትም ።ከሞት ተርፈው ምድሪቱን ለመርገጥ ከበቁት መካከል ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠው አስከፊ ህይወት የሚገፉ ጥቂት የሚባሉ አይደሉም ።
ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው በህገ ወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚሞክሩ በርካታ አፍሪቃውያን ስደተኞች ካስቡበት ሳይደርሱ የበረሃና የውሐ ሲሳይ መሆናቸው ተደጋግሞ የሚነገር ጉዳይ ነው ። ከመካከላቸው እድል የቀናቸው ደግሞ በህይወት አውሮፓ መድረስ ቢችሉም እዚህም የሚጠብቃቸው አበሳ ቀላል የሚባል አይደለም ። የጥገኝነት ጥያቄ ማመልከቻቸው ተቀባይነት ሳያገኝ ለዓመታት የሚንገላቱ ከዚያም አልፎ በደረሱበት ሃገር ማረፊያም ይሁን ምግብ ለማግኘት የሚቸገሩ የጎዳና ተዳዳሪ ሆነው ህይወታቸውን የሚገፋም ጥቂት አይባሉም ። በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ መውጫ ላይ በሚገኝ ባቡር ጣቢያ ስር ተጠልለው የሚኖሩ አፍሪቃውያን ስደተኞች ለዚህ አብነት ናቸው ።

አገር ጎብኚዎች ከሚያጨናንቋቸው ብርቅዮ የአውሮፓ ከተማዎች አንዷ ፓሪስ ናት ።ከፓሪስዋ ሞንማርትር ብዙም ሳይርቅ በሚገኝ አንድ አካባቢ ግን ብዙም አገር ጎብኚ አይታይም ።ብዙ ህዝብ በሚንቀሳቀስበት በዚህ አካባቢ በሚገኝ ባቡር ጣቢያ ስር ሰዎች የተጠለሉባቸው አነስተኛ የቆሸሹ ድንኳኖች ይገኛሉ ። ከላይ የከተማ ባቡር ከስ
ር ደግሞ አገር አቋራጭ ባቡሮች በሚያልፉበት በዚህ ስፍራ ባሉት ትናንሽ ድንኳኖች ውስጥ ከተጠለሉት አብዛኛዎቹ ከምሥራቅ አፍሪቃ የመጡ ተገን ጠያቂዎች ናቸው ። በዚያ የሚኖሩት ስደተኞች ታሪክ የተለያየ ነው ትላለች ያነጋገረቻቸው የዶቼቬለዋ ሊዛ ብራያንት ።
ብራያንት እንደዘገበችው ከስደተኞቹ አንዳቸውም መጨረሻቸው መፀዳጃም ሆነ ማረፊያ ቤትም የሌለው የዚህ ዓይነት ስፍራ እንዲሆን ፍላጎት አልነበራቸውም ።በዚያ ከተጠለሉት አንዱ ከአዲስ አበባ ኢትዮጵያ መምጣቱን የሚናገረው የ24 ዓመቱ ሚክያስ ነው ። ሚክያስ የዛሬ ሁለት ዓመት ከሃገሩ ከመውጣቱ በፊት ተማሪ ነበር ። ለምንህ ከሃገሩ እንደወጣ ብራያንት ላቀረበችለት ጥያቄ ይህን መልስ ነበር የሰጠው ።
«ምክንያቱም እኛ ጋ የፖለቲካ ጦርነት ስላለ ነው ። ኦሮሞ የሚባለውን ዘር ታውቂያለሽ ? አዎ እኔ ኦሮሞ ነኝ »
ሚክያስ እንደሚለው በፈረንሳይ ጥገኝነት እንዲሰጠው አመልክቶ ጊዜያዊ ወረቀት አግኝቷል ። ከ6 ወር በኋላ የሚደረግለትን የመጨረሻ ቃለ መጠይቅ እየጠበቀ ነው ።እስከዚያው ግን ሌላ መኖሪያ ስላላገኘ በዚህ ድንኳን ውስጥ ለመቆየት ተገዷል ። ፕራሲ የተባለው በዚሁ ስፍራ የሚኖር ሌላው የ25 ዓመት ወጣትም ተማሪ ነበርኩ ይላል ።በመንግሥት ጫና ምክንያት ሃገሩን ለቆ የሊቢያ በረሃን አቋርጦ መምጣቱን ይናገራል ።
«ከሊቢያ ጀልባ ይዘን የሜዲቴራንያንን ባህር አቋርጠን ነው የመጣነው ። ጀልባዋ አነስተኛ ብትሆንም እጅግ በርካታ ሰዎችን ነበር የጫነችው ። ባህሩ መሃል ስንደርስ ጀልባዋ ተሰበረች ።የባህር ድንበር ጠባቂዎች እስኪመጡልን ድረስ መጠበቅ ነበረብን ። መጥተው ወደ መሬት ወሰዱን ።»
ፓራሲ መጀመሪያ የገባው ኢጣልያ ነበር ። ከዚያም ወደ ፓሪስ ተሻገረ ።
«ፓሪስ እንደመጣሁ ወዲያውኑ ተገን እንዲሰጠኝ አመለከትኩ ።መኖሪያ እንዲሰጠኝም እየሞከርኩ ነው ። ከቀጠሮ ቀጠሮ ሲሰጠኝ ቆይቷል ። ግን ምን የተገኘ ነገር የለም ። ወደ ሚመለከተው ክፍል ስትሄድ ብዙ ተራ የሚጠብቁ ሰዎች እንዳሉ ነው የሚናገሩት ።እናም ደጋግሞ መሄድ ያስፈልጋል ።እዚያ ስመላለስ አንድ ዓመት ከግማሽ ሆነኝ ።»
በፓሪስ ይህን መሰሉን ህይወት የሚገፉ ተገን ጠያዊዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም ። የፓሪስዋ ዘጋቢያችን ሃይማኖት ጥሩነህ እንደገለፀችው ወደ ፈረንሳይ የሚገቡ ተገን ጠያቂዎች ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው ።ይሁንና ሁሉም ማመልከቻቸው ተቀባይነት እስኪያገኝ ድረስ የመጠለያ የምግብ አቅርቦትና የህክምና አገልግሎት ላያገኙ ይችላሉ ። ማመልከቻቸው መልስ ሳያገኝ እየዘገየ የሚጉላሉም ብዙዎች ናቸው ።
በፈረንሳይ የተገን ጠያቂዎች አያያዝ ግን ይህ መሆን አልነበረበትም ። በፈረንሳይ ህግ የአንድ ተገን ጠያቂ ጉዳይ መልስ እስኪያገኝ ድረስ መንግሥት መሠረታዊ ፍላጎቶቹን ማሟላት ነበረበት ። በአውሮፓ ህብረት ደረጃም ሁሉም ሃገራት ይህን ይህ መሰረታዊ ጉዳይ ማሟላት ይጠበቅባቸዋል ።ፕየር ሄነሪ ተገን ጠያቂዎችን የሚረዳ መንግስታዊ ያልሆነew ቴር ደ አዚል የተባለው ድርጅት ሃላፊ ናቸው ። በርሳቸው አስተያየት ተገን ጠያቂዎች ድልድይ ስር ድንኳን ውስጥ መጠለላቸው ተቀባይነት የለውም ።
«የዓለም ህዝብ የጉዞ መናሃሪያና የሃገራችን ርዕሰ ከተማ በሆነችው ፓሪስ በሚገኘው በዚህ ድልድይ ስር ያለውን ሁኔታ ተመልከች ፤ተገን ጠያቂዎች እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ።የተገን አሰጣጥ ስርዓታችንን እንደገና ማደራጀት አለብን ።ቢያንስ መጠለያ መስጠትና ማመልከቻቸው መልስ እስኪያገኝ ድረስ ልንረዳቸው ይገባል ።»
ፈረንሳይ በርካታ ተገን ጠያቂዎች ከሚገኙባቸው የአውሮፓ ሃገራት አንዷ ናት ። በአሁኑ ጊዜ በፈረንሳይ ወደ 60 ሺህ የሚጠጉ ተገን ጠያቂዎች ይገኛሉ አብዛኛዎቹ የሚመጡትም ወደ ዋና ከተማይቱ ፖሪስ በመሆኑ መኖሪያ ችግር እንደሚገጥማቸው የስደተኞች መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ ።ይህንና ሌሎችም ተገን ጠያቂዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ያቃልላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት አዲስ ህግ ለፈረንሳይ ፓርላማ ቀርቧል ።ይኽው የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ውሳኔን የሚጠብቀው ህግ የተገን ጠያቂዎች ማመልከቻ መልስ እስኪያገኝ ድረስ የሚወስደውን ጊዜ በግማሽ የሚያሳጥር ነው ። አዲሱ የፈረንሳይ የተገን አሰጣጥ ደንብ ማሻሻያ ምን እንደሆነና በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ሃያማኖት ትገልፅልናለች ።
ማሻሻያው የመብት ተሟጋች ድርጅቶችን ቢያስደስትም በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ አጠራጣሪ መሆኑ አልቀረም ።የፈረንሳይ ፓርላማ በዚህ ዓመት በታህሳስ ወር የተነጋገረበትን ይህን ማሻሻያ የስደተኞች መበት ተሟጋቾች በበጎነቱ ቢቀበሉትም የስደተኞችን ችግር ሙሉ በሙሉ ማቃለሉን ግን ይጠራጠራሉ ።
በድንኳን ለተጠለለው ፕራሲ አዲስ ህግ መዘጋጀቱ ያን ያህል አላጓጓውም ። በፖለቲካ ስርዓቱ ላይም እምነት አጥቷል ።
«ፖለቲከኞቹ በቴሌቪዥን ና በራድዮ ይናገራሉ ።እኛም ያንን አምነን አሁን ጥሩ እድል ይኖረናል እንላለን ግን ምንም እድል የለም ። ሁሉጊዜም አድስ ህግ ፣አዲስ አዲስ አዲስ ይባላል ።ሆኖም ለኛ አዲስ አይደለም ለነርሱ እንጂ »
ያም ሆኖ ተገን ጠያቂዎች ፍፁም ተስፋ ቆርጠዋል ማለት አይደለም ። አማራጭ እስኪያገኙ ድረስ እድላቸው የሚያመጣላቸውን እየጠበቁ ነው ። ፈረንሳይና ሌሎችም የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ህገ ወጥ በሚሏቸው ስደተኞች ላይ የያዙት አቋም በትክክል ከለላ የሚያስፈልጋቸውን ተገን ጠያቂዎች በጣም እየጎዳ ነው ሲሉ የመብት ተሟጋቾች ጩኽታቸውን ማሰማታቸውን ቀጥለዋል ።

No comments:

Post a Comment