Monday, October 14, 2013

ህገ ወጡ የማስፈራራት ዘመቻ እንደቀጠለ ነው

በአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት ህዝባዊ ንቅናቄ ንቁ ተሳትፎ ያደርጉ ከነበሩ ወጣቶች መካከል ሁለት ደህንነቶች ዘላለም ደበበን ወደ ሚሰራበት የአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ ግቢ በመዝለቅ በህገ ወጥ መንገድ ከወሰዱት በኋላ በማስፈራራትና ተራ የስድብ ቃላትን በማዝነብ በመጨረሻ ያለ ምንም ክስ መልቀቃቸው ታውቋል፡፡
እንደሁልግዜው ማልዶ በስራ ገበታው የተገኘው ዘላለም በሚሰራበት የአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ ቤተ መጻህፍት ለአዳዲስ ተማሪዎች እገዛ በማድረግ ስራ ተጠምዷል፡፡ሁለት ሰዎች መደበኛ ልብስ ለብሰው ሊያናግሩት እንደሚፈልጉ በመግለጽ ደህንነቶች መሆናቸውን ይነግሩታል፡፡

በስራው የተጠመደው ዘላልም ሊያናግሩት ለፈለጉት ደህንነቶች ‹‹እንደምታዮት በስራ ላይ ነኝ፣የተፈለግኩበትን ምክንያት የሚገልጽ ወረቀት አምጡና ከስራ በኋላ እኔው እራሴ እመጣለሁ››ይላቸዋል፡፡ይዘውት ለመሄድ መምጣታቸውን በመግለጽ በጉልበት ሊወስዱት ሲሞክሩ ግርግር ይፈጠርና ተማሪ መጮህ ይጀምራል፡፡ሁኔታው ያላማረው ዘላለም ይሁንታውን በመግለጽ ከደህንነቶቹ ጋር ይሄዳል፡፡

ሶስተኛ አካባቢ በሚገኝ አንድ መናፈሻ ውስጥ ዘላለምን ያስገቡት ደህንነቶች ሌሎች አጋሮቻቸውን በመጨመር በመናፈሻው ውስጥ ‹‹በአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ ወረቀት ተበትኗል፡፡ወረቀቱ የሙስሊሞች ትግል ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የሚገልጽ ነው፡፡ይህንን ወረቀት የበተነው አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ መሆኑን ደርሰንበታል፣ወረቀቱን የበተነው አንድነት በመሆኑ ደግሞ እዚህ ግቢ ውስጥ ለአንድነት የምትቀርበው አንተ ነህ ስለዚህ ወረቀቱን የበተንከው አንተ ነህ››ይሉታል፡፡
ፓርቲው የትኛውንም አይነት ስራ በህቡዕ እንደማይሰራ በመግለጽ ውንጀላቸውን ያጣጣለው ዘላለም ‹‹በዚህ እኔንና ፓርቲዬን መክሰስ የምትፈልጉ ከሆነ ቦታው እዚህ ቦታ አይደለም፡፡ፖሊስ ጣብያ እንሂድ ቃሌን ልስጣችሁ በፍርድ ቤት ደግሞ ማስረጃችሁን በማቅረብ መከራከር ትችላላችሁ፡፡ከዚህ ውጪ ተበተነ የምትሉትን ወረቀት በግቢው ውስጥ አልተመለከትኩትም፡፡የፓርቲዬም እምነት አይደለም፡፡››ይላቸዋል፡፡
ደህንነቶቹ ‹‹ቀዩን መስመር እያለፋችሁ ነው፣አንድነት ምን እያደረገ እንደሆነ እናውቃለን፣እኛ ትእግስተኞች በመሆን አንድ ቀን ከስህተታቸው ይመለሱ ይሆናል በማለት ስንጠብቃችሁ ነበር››በማለት እዚህ ቦታ ለመጥቀስ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የማይፈቅዳቸውን ዋልጌ ቃላቶች በመናገር ለሰዓታት በመናፈሻው ካቆዮት በኋላ ወደ ቤትህ ሂድ ብለውታል፡፡
ዘላለም ‹‹በዚህ ማስፈራራትና ህገ ወጥ አፈና የሚታጠፍ የሰላማዊ የትግል ስልት እንደሌለ አምናለሁ፡፡የአንድነት አላማ ግልጽና በህግ የሚመራ መሆኑንም እገነዘባለሁ እናም በማስፈራራታቸው ሳንደነግጥ ትግሉን መግፋት ይኖርብናል፡፡››ብሏል፡፡
በሰላማዊ ሰልፉ ወቅት የሙስሊም ኢትዮጵያዊያኑን እስራት ለማስታወስ ራሱን በሰንሰለት ያሰረውን ወጣት ስንታየሁ ቸኮልን ሰላማዊ ሰልፉ እንደተጠናቀቀ ሁለት ደህንነቶች በሃይል አስገድደው መኪና ላይ ሊጭኑት ሲሞክሩ አብረውት በነበሩ የፓርቲው አባላት ርብርብ አፈናው ሳይሳካ መቅረቱ ይታወሳል፡፡
ከሶስት ቀናት በፊት በተመሳሳይ መልኩ የአንድነት አባልና የህዝባዊ ንቅናቄው ንቁ ተሳታፊ የነበረችውን ወጣት ወይንሸት ስለሺን ስታዲየም አካባቢ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት አንድ ሲቪል የለበሰና የደንብ ልብስ የለበሰ አንድ ፖሊስ አስገድደው ወደ ፖሊስ ጣብያ በመውሰድ ‹‹በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ሴት እስረኞችን በመወከል ቱታ በመልበስ እጆችሽን በሰንሰለት ያሰርሽው አንቺ እንሆንሽ ደርሰንበታል፡፡ይህንን የምታደርጉት አመጽ ለመቀስቀስ በማሰብ ነው፣በቅርቡም ዋጋችሁን እንድታገኙ እናደርጋችኋለን››በማለት በማስፈራራት ከምሽቱ ሶስት ሰዓት መልቀቃቸው አይዘነጋም፡፡1376625_527515184000087_849090941_n

No comments:

Post a Comment