Monday, October 14, 2013

መልከጥፉን በስም ይደግፉ

ከይሄይስ አእምሮ
በሀገራችን የስም አወጣጥ ወግና ልማድ እልም ያለችዋ ጥሩራ ባሪያ “አልማዝ” ወይም “ፀሐይ”፣ በነጭናጫነቷና በምግባረ ብልሹነቷ መንደርተኛው ሁሉ የሚያውቃት ሴት ወይዘሮ “ዐመለወርቅ” ወይም “አበቅየለሽ”፣ እልም ያለው ቦቅቧቃ “ደም መላሽ” ወይም “ሺመክት”፣ ቤሣቤስቲን የሌለው የኔቢጤው መናጢ ድሃ “ሀብታሙ” ወይም “አዱኛ”፣ እንዴት ያለው ንፉግና ክፉ ሰው “ቸሩ” ወይም “ደጉ”፣ … ተብሎ ሲጠራ እናውቃለን፡፡ መቼም ‹ስም አይገዛም› ይባላልና በዚህ ረገድ ማኅበረሰባችን ቢፈተሽ ብዙ አስገራሚ ነገር አይታጣም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ “ስም ይቀድሞ ለነገር” እንዲሉ ይሆንና አልፎ አልፎ ጠሪና ተጠሪ የሚገናኙበት ሁኔታ መኖሩ አይካድም፡፡
ይህም ማለት ስሙ ‹ታመነ› ሆኖ በምግባሩ ለሀገሩም ሆነ ለትዳሩና ለጓደኞቹ የሚታመን፣ ስሟ ‹ሠናይት› ሆኖ በምግባሯም እንዲሁ እንከን የማይወጣላት፣ ስሙ ‹ፍቅሩ› ሆኖ እውነትም የፍቅር አብነት የሚሆን … ሰው የሚያጋጥመን ጊዜ ይኖራል፡፡ ምንም እንኳን የስያሜና የተሰያሚ ሥነ ልሣናዊ ግንኙነት ባሕርያዊ አለመሆኑና ይልቁናም ዘፈቀዳዊ መሆኑ በባለሙያዎቹ ቢነገርም በዘልማዳዊ አነጋገር ብዙውን ጊዜ ስምና ምግባር የሚስማሙበት ወይም የሚጣረሱበት አጋጣሚ መኖሩን መታዘባቸን አልቀረም፡፡ እንግዲህ የራሳችሁንም ስም ከመልካችሁና ከምግባራችሁ ጋር እያነጻጸራችሁ ራሳችሁን ገምግሙና ታዘቡ፡፡ እርግጥ ነው - ምናልባት ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ እንደሚባለው ነውና የራሳችን ጥፋት ላይታየን የሚችል እንዲያውም ጥፋትን ከልማት የምንቆጥር ሰዎች አንጠፋም ብቻ ሳይሆን ከጥንፍ እስካጥናፍ ሞልተናል፡፡ በዚህም ምክንያት ራሳችንን በመፈተሸ ጠንካራና ደካማ ጎናችንን አብጠርጥረን ለማየት የምንቸገር ሰዎች አለን፡፡ ለራስ ፍርድን እንደመስጠት ያለ አስቸጋሪና ከባድ ነገር ደግሞ ያለ አይመስለኝም፤ በተለይ ባገራችን፡፡
ይህችን ጽሑፍ ልጫጭር ያነሳሳኝ ብርሃኑ ነጋ አዲሱ መጽሐፉ ሲመረቅ ይመስለኛል “ስምህን መጽሐፉ ላይ ስትጽፍ ለምን ‹ዶከተር› የሚለውን ማዕረግህን ሳትጽፍ ቀረህ?” ተብሎ ሲጠየቅ የሰጠው ለኔ እጅግ ማራኪ የሆነ መልስ ነው፡፡ በምዕራቡ ዓለም ይህ ዓይነቱ በማዕረግ የመጠራራት ባህል ፋሽኑ ያለፈበት መሆኑንና ማንም ሰው ማንንም ሲጠራ በስሙ ብቻ እንደሚጠቀም፣ በሀገራችን ግን ለመኮፈስና ከሌሎች የተለዩ መሆንን ለማመልከት ይበልጡን ለጉራ መቸርቸሪያነት እንደሚውል በመጥቀስ በዚያም የተነሳ ያን በሀገራችን ብዙዎች ሰዎች በህልማቸው ሳይቀር እየመጣ አርቲፊሻል ደስታ የሚሰጣቸውን ‹ዶክተር/ፕሮፌሰር› የሚል የማዕረግ ስም ሆን ብሎ ነቅሶ እንዳወጣው ገልጾአል፡፡ የሀገራችን ደናቁርት ምሁራን ተብዬዎች ከዚህ ብዙ ይማራሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ እውነቱን ለመናገር - ሀገራችን በብዙ ነገር እንዳልታደለች ለመገንዘብ የምሁራንን መንደር በመፈተሸም መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህን ስል ከዚህ የመጠሪያ ማዕረግ ተነስቼ ብቻ ሣይሆን ብዙዎች የኮሌጅና የዩኒቨርስቲ ምሁራን ተብዬዎች ከፈረሱ ጋሪው ቀድሞባቸው ዕውቀቱ ሣይኖራቸው ማዕረጉን ይሸከሙና በሥራቸው መወላከፋቸውና ከደረጃ በታች መሆናቸው ሳያንስ ማዕረጋቸው በጫነባቸው የጉረኝነት አባዜ ካላቅማቸው ሲወጣጠሩ ሳይ ስለሚያሳዝኑኝ ነው፡፡ በሀገራችን ‹ዶክተር› መባልን እንደብርቅ የሚያዩ ምሁራን ብቻ ሳይሆኑ ‹ዶክተር!› ብሎ ሰውን መጥራትን የሚወዱ ማይማንም አሉ - ምን ማለቴ መሰላችሁ - ‹ዶክተር› መባልን በፍቅር የሚቀበል ሰው የመኖሩን ያህል ‹ዶክተር፣ ዶክተርዬ› ብሎ መጥራትንም እንዲሁ ለጉራ የሚፈልገው ዜጋ ብዙ መሆኑን ለማስታወስ ነው - ለምን መሰላችሁ - ‹አሃ! የዚህ ሰው ጓደኛ/ ወዳጅ ለካንስ ዶክተር ነው/ናቸው!› እንዲባልና የራስን ሥነ ልቦናዊ ችግር በሌሎች ሥነ ልቦናዊ ችግር የማከም ነገር ነው፡፡ ምን ያህል ግልጽ እንደሆንኩላችሁ አላውቅም፡፡ ደግሞም አደራ - ይህንና እንዲህ የምለው በየዕለቱና በያጋጣሚው ከምታዘበው እውነት ተነስቼ እንጂ አንዳች ችግር ኖሮብኝ አይደለም - ይሄ ምናምን ኮምፕሌክስ የምትሉት ነገር የተጣባኝ እንዳይመስላችሁ፡፡ የምሁሮቻችንን ጉረኝነትም ሆነ የትምህርት ጥራት ወደ ኢትዮጵያ ኑና እዩ - ብዙ የሚገርም ሁኔታ ትታዘባላችሁ፡፡
በነገራችን ላይ ዶክተር ፕሮፌሰር ነኝ እያለ መሬትን ለመርገጥ የሚጠየፍ አንዳንድ ባለስንኩል አእምሮ ‹ምሁር› ዘርህን ወይም ሃይማኖትህን ወይም የአካባቢ ልጅነትህን ወይም ክፍል ውስጥ በጥያቄ መሞገትህን ወይም ፆታሽን ወይም የፖለቲካ አስተሳሰብህን ወይም መልክና ቁመትህን መሠረት አድርጎ የማለፍ አለማለፍህን ውጤት ሲተምንልህ ቅንጣት አያፍርም፡፡ በበኩሌ አንድ ተማሪ ከቀሪዎቹ የክፍል ጓደኞቹ ጋር በትክክል እኩል ተፈትኖና በእኩል ዐይን ታርሞለት ከሚያመጣው ነጥብና በእስኬሉ መሠረት ነጥቡ ከሚያስገኘው ሆሄያዊ የውጤት መግለጫ ውጪ በሰውኛ (subjective) የአድልዖ አሠራር ተማሪን በመመዘን የሚጥል ወይ የሚያሳልፍ ከሆነ ይህ ሰው እንኳንስ ምሁር ሊባል ከነአካቴው ሰው ስለመሆኑም ያጠራጥረኛል፡፡ ይህ ዓይነቱ ‹ምሁር›፣ ከሠላሣ ዓመታት በፊት ዶክትሬቷን ስትሰራ ፈጸመችው በተባለችው ፕላጃሪዝም (ጽሑፋዊ ስርቆት) ሰበብ የዶክትሬት ማዕረጓ እንደተገፈፈባት እንደዚያች የጀርመኗ የጤና ጥበቃ ይሁን የትምህርት ሚኒስትር ማዕረጉ ተገፍፎ ኮብልስቶን እንዲሠራ ቢመደብ ከቅጣቶቹ ሁሉ እጅግ አነስተኛውና ‹እልል በቅምጤ› ብሎ እጅ ስሞ ሊቀበለው የሚገባው የመጨረሻ ዕጣው ቢሆን እመርጥለታለሁ፡፡ ስንቶች መሰሏችሁ በዚህ መልክ የሰውን ዕድል እያበላሹ ያሉና የነበሩ ፡፡ እነዚህ ናቸው እንግዲህ የሀገር አለኝታዎች - ወጣቱን የሚቀርጹ፣ አምራች ኃይል የሚያፈሩ፣ ሀገርን የሚያንጹ፣ ተረካቢ ትውልድን በየአቅጣጫው በትምህርትና በመልካም ሥነ ምግባር ኮትኩተው ለቁም ነገር እሚያበቁ፤ ድንቄም መኮትኮት፡፡ ሀገር ጠፍታልሃለች ይልቁንስ፡፡ አለመታደል ሆኖ እንጂ “ወደድሽም ጠላሽም ካልተኛሁሽ በፈተናው ዜሮሽን አስታቅፍሽና መጨረሻ ላይ ታይኛለሽ ኤፍሽን አስቀምጥልሻሁ” የሚል ዶክተርና ፕሮፌስር ወይም ባለማስተርስ ምሁር ሊኖር ይገባ ነበር? አቤት- በዩኒቨርስቲ ካምፓሶች አካባቢ የሚወራውን ቅሌት ብትሰሙ፡፡ አቤት የሚታይና የሚሰማ ጉድ! ይህ እንግዲህ በማስተማር ሙያው ሙትቻ የሆነውን፣ ጎበዝ ነው እንኳን ቢባል ሳይዘጋጅ ወደ ክፍል የሚገባውን ዘምቦለል፣ አይደለም የትምህርቱን ይዘት የሚያስተምረውን ኮርስ ሳይቀር የማያውቀውን ደደብ፣ ሌላ ቢዝነስ እያሯሯጠ በሴሚስተር ሁለቴና ሦስቴ ብቅ ብሎ ፈተና ላይ ግን ቦምብ ጥያቄ የሚያወጣውን ወይም ከፈተና ባንክ መዝርጦ የሚፈትነውን ዘረጦ … ሳይጨምር ነው፡፡ ያ ያ ከታዬ ከመቶ አስተማሪ - የየትኛውም የትምህርት ደረጃ ወይም ተቋም ማለት ነው- ስንቱ የመምህርነት መመዘኛውን እንደሚያልፍ እግዜር ይወቅ፡፡ ልብ አድርግ፡- “EPRDF has winned(ዊንድ) the election!” የሚል ፕሮፌሰር በተፈጠረባት ኢትዮጵያ፣ “He have three childs.” እና/ወይም “Do not afraid me.” የሚል ባለማስትሬት ዲግሪ የእንግሊዝኛ መምህር በፈለቀባት ኢትዮጵያ በዕፁብ ድንቅ አግራሞት እየኖርን ስለትምህርት ጥራት መነጋገር አስቸጋሪ እንደሆነ ይገባኛል - ምሳሌዎቼ እውነተኛ ናቸው ‘by the way’ - ጉራማይሌው ለምን በጽሑፍስ ይቅር? ትምህርት አሁን ያልጠፋች፣ ትምህርት ዛሬ ያልሞተች መቼ ትሙት? ይህ ዓይነቱ ምሁር ነው እንግዲህ ካለማንጠልጠያየ ከጠራችሁኝ ሞቼ እገኛለሁ እያለ በሥነ ልቦናዊ ደዌ ተቀስፎ የሚገኝ - ተሳስተህ በስሙ ብቻ ብትጠራው የሚያኮርፍህም እኮ ሞልቷል፡፡ ይህን ስል ከንፍሮ ጥሬ እንደሚወጣ ሁሉ አንዳንድ ደረጃቸውን የጠበቁና ከጉረኝነት ባርነትም ነጻ የወጡ ጎበዞች መኖራቸውን አልክድም፤ ስለልባሞች መነጋገር ጊዜ ማባከን
ነው - እሱ ችግር አይደለምና፡፡ አዎ፣ ወገኖቼ ሙያ በልብ ነው፡፡ በከንቱ ምድራዊ ማዕረጋት አንታበይ፤ ትህትናን የባሕርይ ልብሳችን እናድርግ፡፡ መጽሐፉም እንዲህ ይላል፡- ‹እላይ መቀመጥ የሚፈልግ እታች ይቀመጥ› - ይህም ሲባል ትህትናችን ከልብ እንጂ ከአንገት በላይ ለታይታና ለውዳሤ ከንቱ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል፤ በእውነት መቀለድ አይቻልም፡፡ ዋጋችንን ራሳችን ከተመንን ልንሳሳትና ትዝብት ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡ በቅጡ ከተረዳነው በዚህች ምድር ልብን ሊያሳብጥ የሚቻለው አንዳችም ነገር የለም፡፡ ራቁታችንን መጣን ራቁታችንንም እንሄዳለን፡፡ ሌላው ሁሉ ተደራቢና ትርፍ ነገር ነው፡፡ በሰው መፍረድ ቀላል ቢሆንም ለኔ እንግዲህ ገሃዱ እውነታ እንዲህ ይመስለኛል፡፡
ብሂላችን አሣምሮ አስቀምጦታል - “ከመጠምጠም ማወቅ ይቅደም” ብሎ፡፡ መቼስ ወደኢትዮጵያ ሲገባ ውሉን የማይስት አንድም ነገር የለም፡፡ ፖለቲካው ምዕራቡም ምሥራቁም ከሚያውቁት በእጅጉ በተለዬ መልክ በፍትጊያና በእርስ በርስ መተላለቅ ላይ የተመሠረተ ለሰሚም ግራ ነው፡፡ ኢኮኖሚው ዓለም ከምታውቃቸው የዕድገት ቀመሮችና የአሠራር ይትበሃሎች ፈጽሞውን የወጣ ነው፡፡ ንግዱም እንደዚሁ ዓለም ከምትከተላቸው የንግድ ሥርዓቶች ባፈነገጠ መልኩ የዓሣማ ይሁን የጅብ አይታወቅም፡፡ አንድ ሰው ቢዝነስ በገባ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከኪራይ ቤትና ከከተማ አውቶቡስ መጓጓዣ ወጥቶ የራሱ አውቶሞቢልና በተንጣለለ ግቢ የራሱ ቪላ ቤት ባለቤት የሚሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በገሃነምም የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ በትምህርቱ ዘርፍም ይሄው ኢትዮጵያዊው የማፈንገጥ ዘመን አመጣሽ በሽታ ተስፋፍቶ ከሌላው ዓለም በተለዬ በማዕረግ መጀነንና ቆዳን ለማዋደድ በማስታወቂያነት መጠቀም ከተጀመረ ሰነበተ፡፡ ከማቴሪያላዊው የአስፋልት መንገድና የፎቆችና ሕንጻዎች ግንባታ በተጓዳኝ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የሚታየውን አጠቃላይ ዝቅጠት (decadence) የሚታዘብ አስተዋይ ዜጋ ስለሀገሩ ተንሰቅስቆ ቢያለቅስ ማን ሊያጽናናው ይችላል?
ይህ የማዕረግ ነገር በተነሳ ቁጥር ከፍ ሲልም ለማየት እንደተሞከረው ብዙ የሚስተዋሉ ችግሮች አሉ፡፡ በመሠረቱ በምናገኘው ማናቸውም ዓይነት ማዕረግ ካላንዳች መሳቀቅ የመጠራት መብት አለን፡፡ እኔን ጨምሮ አንዳንዶች እያልን ያለነው አለቅጥ አንለጥጠው፣ እንደብርቅ እያየንም ያልተገባ የጉራ ችርቻሮ ውስጥ አንግባ ነው፡፡ (ከ‹አድማስ በሻገር› መጽሐፍ ውስጥ ያነበብኩት አንድ ነገር አሁን ትዝ አለኝ፤ ገድሉ የሚባለው የመጽሐፉ ባለታሪክ ይመስለኛል - ከተሳሳትኩ አርሙኝ፡፡ ብቻ ይህ ሰው እንደዘመናችን ብዙዎች ‹ምሁራን› በጣም ጉረኛ ነው - (ይቺን ጽሑፍ የሚያነቡ/ያነበቡ ምሁሮቻችን ቡናና ሻይ ላይ ሲቀረጣጥፉኝ ታየኝ)፡፡ ይሄ ገድሉ የተባለ ገጸ ባሕርይ ገነት ሆቴል ሲዝናናም ይሁን በሚሄድበት ሌላ ቦታ መኪናውን መግቢያ መውጫ አሳጥቶ አላግባብ ይገትራታል - ሆን ብሎ፡፡ ከዚያ - ለምሳሌ በመጽሐፉ እንደተጠቀሰው በገነት ሆቴል - አስተናጋጆች በሙዚቀኞቹ ማይክራፎን “ ባለ እንዲህ ያለ ታርጋ መኪና እባክህን ወደመድረክ ትፈለጋለህ!” ሲባል ደናሾችን አቋርጦ ወደሚፈለግበት ሥፍራ እየተንጎማለለ ይሄዳል፤ በዚህ መሃል የቆመውም የተቀመጠውም ‹አሃ! ኦኦ! ለካንስ ይሄ ሰውዬ ሀብታም ነውና ጃል! ባለሊሞዝንም ኖሯል!” እያለ በልጆች ቋንቋ ‹ይላጥለታል›፤ ይህ ብቻም አይደለም - በዘመኑ ‹ቆርቆሮ›ና ቆዳ ኮት ወይም ጃኬት እንደብርቅ ይታዩ ስለነበረና የሀብት መገለጫም ስለነበሩ በተለይ እንስቶችን ለመሳብ እነዚህን ቁሦች የሚገለገሉ አሰለጦች የጉብሎችን ዐይን ያንከራትቱ እንደነበር የዕድሜ ባለጠጎች አሁን ድረስ በትዝታ ያስታውሳሉ፡፡ ያኔ ታዲያ - በኩራት እየተጀነነ ወደመድረኩ የሚያቀናው ያ መጥረቢያ ፊት በሚል ተቀጥላ ስም የሚታወቀው ገድሉ ሰውነቱ ይነፋፋል፤ ያቺ ቀትረ ቀሊል ሥነ ልቦናዊ ኮረጆው በትዕቢትና በትምክህት ተወጥራ አየር ላይ ትንሳፈፋለች፡፡ የዚህ ሁሉ በሽታ መነሻም “እኔ የራሴ መኪና ሲኖረኝ አዳሜ በእግሯ ወይም በታክሲና በአውቶቡስ ተጋፍታ ነው ‹ሕዝብ ሕዝብ እየሸተተች› እዚህ የመጣችው” የሚለው በሀበሻ ምድር የተሠራ ቫይረስ ይሁን ባክቴሪያ ወይም ጀርም ነው፡፡ በውነቱ ሊለቀን ያልቻለ ምናልባትም እየባሰብን ያለ ትልቅ ነቀርሣ ነው፡፡ እንደሚመስለኝ ሀገራችንን ከሁሉም ይበልጥ እየጎዳት የሚገኘው ሌላ ሳይሆን ይህ ዓይነቱ ጉረኝነትና ራስን ከሌሎች በላይ ሰቅሎ ወይም ክቦ የማየት ሥነ ልቦናዊ ችግር ይመስለኛል፡፡ ይህ ነገር ባልተማረው አካባቢ ቢሆን ብዙም ላያስደንቅ ይችላል - ያልተማረ መቼም ያው ስላልተማረና ስላላወቀ ነው ይባላል፡፡ ነገር ግን የተማረ በሚባልና ሀገርን ሊለውጥ በሚጠበቅበት የማኅበረሰብ ክፍል ዘንድ እንዲህ ያለ ከሚዛን የሚያወርድ ጠባይና ምግባር ሲታይ ያስጨንቃል፤ በቀቢፀ ተስፋ ወጀብም እያላጋ ነገን አጨልመን እንድናይ ያስገድደናል፡፡ ሀገርን የሚረከቡ ዜጎች የዚሁ ነባራዊ ሁኔታ ውርሶች ስለሚሆኑ የሀገር መጥፋት መባቀያም ይሄው ነው፡፡ ማስተዋል የሌለበት፣ ትዕቢትና ትምክህት ያጠላበት፣ ጉረኝነትና የበላይነት ስሜት የተቆራኘው ዜጋ ሀገርን በትክክል መርቶ ወደ ላቀ የዕድገትና ብልጽግና ደረጃ ያደርሳል ብሎ መጠበቅ ደግሞ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ዕድገት ሲባልም ቁሣዊ ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ መንፈሳዊና ኅሊናዊም ነው፡፡
በመሆኑም ጉረኝነትን ማሸነፍ ራሱ ዋና የዕድገት ምልክት ነው፡፡ ስግብግብነትንና ንፉግነትን ማሸነፍ የዕድገት መሠረት ነው፡፡ የዘረኝነትን አስተሳሰብ ከነሰንኮፉ መንግሎ ማውጣት ወደርየለሽ የዕድገት ተምሳሌት ነው፡፡ ግለኝነትንና ራስ ወዳድነትን ማሸነፍ ትልቅ ዕድገት ነው፡፡ አድልዖንና አግላይነትን ማስወገድ ብፅዓት ነው፡፡ ፍትሃዊነትን የተላበሰ ስብዕና ባለቤት ለመሆን በግድ የመደበኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ወይም በማንኛውም ፍርድ ቤት ቆሞ መከራከር የሚችል ጠበቃ መሆንን አይጠይቅም - እናም የፍትህ ርትዕ ሰው መሆንም ዕድገት ነው፡፡ እንደዛሬው አይሁን እንጂ ሀበሾች ደግሞ የሕግ ትምህርት ኖረንም አልኖረንም እንዲሁ በተፈጥሯችን ሃቀኛ ፍርድ መስጠትን እናውቅበታለን - ከፈለግን:: (I am trying to remind you of the sagacious nature of Ethiopians in the good old days.) ስለዚህ ምሁርነትን ከነ“ሙሉ ክብሩ፣ ግዴታውና ጥቅሙ” መያዝ ይበጃል እንጂ እንደደሮ ብልት እየገነጣጠሉ በ”ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ” ዓይነት ለታሪክና ለሕዝብ ትዝብት መዳረግ እንደማይገባ ለአስተዋይ ምሁራን መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ እያልኩ ያለሁት አስተዋይነታችንን የነጠቀንን ሞራ እንግፈፍና ሰው እንሁን ነው፡፡ እነሌኒን ያላሉት መቼም የለም -“ጠባይን ለመግራት ማንበብ፣ ማንበብ፣ አሁንም ማንበብ” አላሉ ይሆን?
አንድ ጊዜ በመሥሪያ ቤቴ እንዲህ ታዘብኩላችሁ፡፡ መኪና ማቆሚያው ገላጣ ቦታ አካባቢ አንድ ወዳጄ ሥልክ እየደወለ ነው -ጧት እንደገባን፡፡ በዚያኛው ጫፍ የተደወለለት ሰው ሥልኩን አነሣ፡፡ ይህኛው ሰው ማንነቱን ሲገልጥ “እኔ ዶክተር አጎናፍር ነኝ” ሲለው እኔ አፈር አልኩና ወደ አንድ ሌላ ጓደኛየ ቢሮ ሄጄ እርጥብ ሥጋውን አወራረድነው፡፡ ይህም ሌላው ነቀርሣችን ነው - ሰውን ማማት፡፡ ቢያንስ የሥራ ጊዜን ያባክናል - የኅሊናን ንጽሕና ያጎድፋል - ኃጢአትም ይመስለኛል፡፡ የዚህን ሰው ‹ህፀፅ› በመጠኑ ልግለጽ፡፡
ምን ሊል ይችል ነበር መሰላችሁ፡- የሚደውልለት ሰው ጓደኛው ነው እንበል፡፡ እንደዚያ ከሆነ በሥልክ ቁጥሩ ወይም በድምጹ ሊያውቀው ይችላልና ‹ዶክተር እገሌ ነኝ› ማለቱ ትርፍ ይመስላል - የታወቀን ማንነት ባላስፈላጊ ሁኔታ መግለጥ ያን ያህል አስገዳጅ አይደለምና፡፡ ጓደኛው አይደለም እንበልና እንነሣ ደግሞ፡፡ የሚጠራው ሥልክ ሲነሣ “ ጤና ይስጥልኝ፣ እንደምን አደርክ እንትናዬ - አጎናፍር ነኝ” ይበል፡፡ ያኛው ሰው “አጎናፍር፣ አጎናፍር…” ይበለውና የደወለለትን ሰው ለማወቅ መቸገሩን ይግለጥ፡፡ “ባለፈው እዚህ ቦታ አድራሻህን የወሰድኩት…” ወይም “ባለፈው እንትና አድራሻህን የሠጠኝና ለዚህ ዓይነት ጉዳይ እንደምደውልልህ የተነጋገርነው አጎናፍር ነኝ፡፡…” ቢለው በቀላሉ ያስታውሰዋል፡፡ እርግጥ ነው - የዶክተርነቱ መጠቀስ አስፈላጊ ከሆነ ግዴለም ይናገረው፤ ማዕረግን እንዳስፈላጊነቱ መጥቀስ ገና ለገና በግብዝነት እንደሚያሳማ ተፈርቶ በመሃላ የሚከረችሙት ወይም በግዝት የሚጠፈንጉት አለመሆኑንም መገንዘብ አለብን፡፡ “ፕሮፌሰር እገሌ ነኝ - እንደምን አደርክ፤ ፊልድ ማርሻል ሞንትጎመሪ ነኝ - እንደምን አመሸህ” ማለት ግን ከጤናማነቱ ይልቅ ወደሥነ ልቦናዊ በሽተኛነት የተጠጋ ነው፡፡ የተማረ ሰው ትሁት መሆን አለበት - በወታደራዊ ሣይንስ የተካነም እንዲሁ፡፡ በጣም ባወቅን መጠን እንዲያውም ምንም እንዳላወቅን እንዲሰማንና ዓለምን እንድንንቃት ይጠበቅብናል፡፡
በእውቀቱ ሥዩም ግጥም ውስጥ “አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ ስትገቡ ደግሞ ሌላ በር ይጠብቃቿል” የሚሉ ሥንኞች ትዝ ይሉኛል - በፍቅር፡፡ እናም አንዱን የዕውቀት በር ባለፍህ ቁጥር ተከፍተው የማያልቁ የዕውቀትና የጥበብ በሮች እጅግ ብዙ አሉና በማዕረጋት ጭምብል በከንቱ የምንኮፈስ ማለቴ የምትኮፈሱ ሰዎች አረማመዳችሁን ብትመረምሩ መልካም ነው፡፡ ማዕረጋት ሲቪ ላይ ይበልጥ ያምራሉ፤ የቡዴና (እንጀራ) ጉዳይ ነውና፡፡ ደግሞም አይምስለን - ዕውቀት በዶክትሬትና በፕሮፌሰርነት መክሊቶች አይሠፈርም ወይም አይለካም፡፡ ህልም እንደፈቺው እንደሆነው ሁሉ ዕውቀትም ባለቤቱ እንዳደረገው ነው፡፡ አንድ ማይም ገበሬ ከዶክተር የሚበልጥባቸው አንድ ሺህ አንድ አጋጣሚዎች አሉ - ለነገሩ ከዶክተሩ በፊት የተፈጠረው ገበሬው መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፤ የገበሬው ሕይወት ነው የዶክተሩ መሠረት፡፡ ባፈሱ ሳይሆን በጎረሱ ነው ወንድሜ፤ በጠመጠሙ ሣይሆን ባወቁ ነው እህቴ፡፡ ጊዜና ቦታ ይጠበናል እንጂ ስንትና ስንት ምሳሌ አምጥቼ ማስረዳት በቻልኩ፡፡ ስለዚህ ቆም ብለን እናስብ፡፡ “በሕይወት ገጠመኝና በትምህርት ምን ዐውቄያለሁ - ምንስ ይጎድለኛል?” በማለት ራሳችንን በዕውቀትና በጥበብ እንገንባ እንጂ “ከዚህ ቦታ እንዲህ ያለ ዲግሪ ያለኝ ዕውቅ ምሁር እኮ ነኝ!” እያልን በከንቱ አንኩራራ፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ የመኮፈስ ጠባይ በትምህርት ማዕረጋት ብቻ የተወሰነ አይደለም - ነገር አንዛዛሁ መሰለኝ፡፡ የአሁኑን አያድርገውና በባህላዊ የሹመት ማዕረጎችም፣ በወታደራዊ ማዕረጎችም፣ በሀብትም፣ በሥልጣንም፣ በዘርም፣ በሃይማኖትም - ምን አለፋችሁ በሁሉም ነገር የተለዬነት የሚለጠጡ ማለትም የሚኮሩና የሚታበዩ ሞልተዋል፡፡ ግብዝነት በየፈርጁ እንደማለት ነው፡፡
በማንኛውም ዓይነት ነገር መኩራትና መታበይ የበሽታ ምልክት ነው፡፡ በሀብት አትኮራም፡፡ ልትደኸይ እንደምትችል ማወቅ አለብህና፡፡ በጤንነት አትኮራም፡፡ በማንኛውም ጊዜ፣ በየትኛውም ሥፍራና ሁኔታ ልትታመምና ልትሞትም ትችላለህና፡፡ በሥልጣንም አትኮራም፡፡ አንድ ያልተጠበቀ ወጀብ ወይ ማዕበል ይመጣና ከሥልጣን ማማህ ሊገፈትርህ፣ ወደዘብጥያ ሊያወርድህና እስከሞትም ሊያደርስህ ይችላልና፡፡
በመልክህ ማማርም አትኮራም - ነገ ያንተ አለመሆኑን መረዳት አለብህና፡፡ ማዲያትን፣ ዕርጅናንና ያልታሰበ አደጋን የማታውቂ ካልሆነ በስተቀር በውበትሽና በአማላይነትሽ አትኮፈሽም፡፡ ራስነትም ይሁን አፄነት፣ ማርሻልነትም ይሁን ጄኔራልነት ሞትንና ህመምን አያስቀሩምና አያኮሩም - በእስካሁኑ ሁኔታ ሞትን ያሸነፈ መልካም ሥራ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የሚያኮራህ ነገር መሆን ያለበት በዋናነት ሰውነት ነው፤ ሰውነት ደግሞ ከሌሎች እንስሳት በተለዬ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ልዩ ፀጋ ነው፡፡ ሰው መሆንህን ማንም የማይገፍህ ወይም የማይሰጥህ የተፈጥሮ መብትህ ስለሆነ መኩራት ካለብህና ካማረህ በርሱ ኩራ - “እኔ እኮ ዶክተር ነኝ! እኔ እኮ የጠራሁ ጎጃሜ ነኝ፣ አኒ ኦሮሞዳ! አነ ወዲ ትግራይ!” ብለህ ሣይሆን “እኔ እኮ በአርአያ ሥላሴ የተፈጠርኩ ሰው ነኝ” ብለህ ተጀነን፡፡ ሰዎችንም ሁሉ እንደራስህ ውደድና በነሱ ላይ በምንም ነገር ልትንጠባረርባቸው አትሞክር - ሁሉ ነገር ከሰውነት በኋላ በሰው ለሰው ስለሰው የመጣ መሆኑን መዘንጋት የለብህም፡፡
ይህን እውነት ታዲያ ምንጊዜም አትርሳ - ሰው ከሰው አይለይም፤ የሰው ግርድና ምርትም የለውም፡፡ አንተ ያገኘኸውን ዕድል ማንም ቢያገኘው ከአንተም ሊበልጥ እንደሚችል አስብ - የአቶ አዝብጤ ዘበኛ ልትሆንም ትችል ነበር እኮ! እንደምሥኪኗ ስደተኛ ልጄ ወይ እህቴ በየመን በረሃ መቅኒሽና ኩላሊቶችሽ በሌቦች ተቦጥቡጦ አውሬ በልቶሽ መና ልትቀሪ ትችይ ነበር እኮ! ትልቁንም ትንሹንም እናስብ፡፡ ማንም ማንንም የመሆን ዕድሉ ፈጽሞ የተዘጋ እንዳልሆነ ደግሞ እንመን፡፡ ትንሽ አጋጣሚና ነቁጥ ዕድል በመሆን አለመሆናችን ሂደት ላይ ትልቅ አስተዋፅዖ ስላለው ተለያየን እንጂ ሁላችን አንድና እኩል ነን - መማር አለመማርና መክበር መደኽየትም በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው::
ስለዚህ እንዲህ ‹እየተዋወቅን› ማን በማን ላይ በዕብሪት ደረቱን ሊነፋ ይቻለዋል? ይህ ነባራዊ እውነት አንዳንዶቻችንን ሊያስኮርፍ ይችል ይሆናል - ቢሆንም እውነቱ እውነት ነው፡፡
ለመሆኑ ልትሆን የቻልከውን ልትሆን ባልቻልከው ወይም በዕድል ለጥቂት ሳትሆነው ባመለጥከው ራስህን ተክተህ አስበኸው ታውቃለህ? እስኪ አሁን አስብ፡፡ ራስህን ልክ እንደመንገድ ጠራጊ፣ እንደከንቲባ፣ እንደተራ ወታደር፣ እንደአዛዥ መኮንን፣ እንደሀኪም፣ እንደበሽተኛ፣ እንደንጉሥ፣ እንደጠቅላይ ሚኒስትር፣ እንደዳኛ፣ እንደጽዳት፣ እንደአካል ጉዳተኛ፣ እንደሾፌር፣ እንደተላላኪ፣ እንደፓይለት፣ እሥር ቤት እንዳለ፣ ከእሥር እንደተፈታ፣ እንደዕብድ፣ እንደጤነኛ፣ እንዳገባ፣ እንደፈታ፣ እንደወንደላጤ፣ እንደጨዋ፣ እንደባለጌ፣ እንደአመንዝራ፣ እንደጭምት፣ እንደባላገር፣ እንደከተሜ፣ እንደጎበዝ ሠራተኛ፣ እንደሰነፍ ልግመኛ፣ እንደተጣላ፣ እንደታረቀ፣ እንደመምህር፣ እንደተማሪ፣ እንደሴት፣ እንደወንድ፣ እንደአላሙዲን፣ እንደአጣሙዲን … አድርገህ ዐይንህን ጨፍንና አስብ፤ እንዲህ ብሆን ወይም ባልሆን ኖሮስ? በልናም ራስህን በሁሉም ኑባሬዎች እየገጠምህ በምናብህ አሰላስል፤ ልንገርህ - ወደህና ፈቅደህ ሀብታም ልትሆን ትችል ይሆናል፤ ነገር ግን ወደህና ፈቅደህ እግርና እጅ የሌለው ወይም ሁለት ዐይኖቹ የጠፉ የኔ ቢጤ ቧጋች ልትሆን አትችልም - እንደጤናማ አካሄድ፡፡
አየህ? ሁሉም ለበጎ ነው የሚባለው ገባህ አይደል? ሰው ሁሉ ፓይለት ቢሆን፣ ሰው ሁሉ ለማኝ ቢሆን፣ ሰው ሁሉ ፕሬዚደንት ቢሆን፣ ሰው ሁሉ ሀብታም አበዳሪ ቢሆን፣ ሰው ሁሉ ድሃ ተበዳሪ ቢሆን፣ ሰው ሁሉ እሥረኛ ቢሆን፣ ሰው ሁሉ ዳኛ ቢሆን፣ሰው ሁሉ አንጠረኛ ቢሆን፣ ሰው ሁሉ ሸማኔ ቢሆን፣ ሰው ሁሉ ጨቋኝ ቢሆን፣ ሰው ሁሉ ተጨቋኝ ቢሆን፣ ሰው ሁሉ ከዳተኛ ቢሆን፣… ብለህ ደግሞ አስብ፡፡ ስለዚህ በሆንከው ከምታዝን ወይ በኩራት ከምትመፃደቅ የሆንከው ነገር ‹መጥፎ›ም ይሁን ‹በጎ› ወደዚህች ዓለም የመምጣትህ ትርጉም እሱ ነውና በማንኛውም የምትሆነው ነገር ብዙ አትደነቅበት፤አትጨነቅም፡፡ በመሠረቱ መለያየት ጤናማ ነው - የዓለማችን ዓይነተኛ ሀብትም ነው፡፡ ችግሩ ባልተገባ ጣልቃ ገብነት ልዩነቶችን እያሰፉና ላልተገባ ግላዊ ጥቅም እያዋሉ ያልተጠበቀ ጉዳት ማድረስ ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ ባለህ ከምትዘባነን ወይም በሌለህ ነገር የምኞትህ ባሪያ ከምትሆን ይልቁንስ ከተቻለህና ዕድሉን ካገኘህ መልካም ነገር ሥራና ከመቃብር በላይ ስምህን ተክለህ ለማለፍ ሞክር፡፡ ያም ይቻላል፡፡
ሰበር ወሬ፡- ለአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይህን ያህል አማካሪ መመደቡ ለጤና ነው ትላላችሁ? አራት ደረሱ እኮ፡፡ ለአንድ የውሸት ጠቅላይ ሚኒስትር አራት አማካሪ መሾም አስፈላጊነቱ ጨርሶ ሊታየኝ አልቻለም፡፡ የዓባይ ፀሐዬ ወደዚያ ቦታ መጠጋት ከበፊትም የሚጠበቅ መሆኑን አንዳንድ የሚዲያ አካላት ፍንጭ በመስጠታቸው እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ምናልባት ሀገር ሲረጋጋና አቧራው - ምን ሲል ነው እሚባል? - ጠፋኝ - አቧራው … when the dust settles አሻንጉሊቱን ሰው ለመተካት ዓባይ ወደቦታው ተጠግቶ ሰውነቱን እንዲያሟሙቅ ታስቦ ይሆናል፡፡ በአንዲት ድሃ አገር በሚኒስትር ማዕረግ አራት ‹የፖሊሲና ምርምር› ጽ/ቤት የጠ/ሚኒስትር አማካሪዎችን መመደቡ የወያኔው መንግሥት የሚሠራውን አለማወቁን ከመጠቆም ውጪ ትርጉም የለውም፡፡ ድንቄም የፖሊሲና የምርምር ቢሮ፡፡ በደናቁርት ባለሥልጣናት ምን ምርምር አለ? በደናቁርት የወንበዴ ቡድን አባላት የሚመራ መንግሥት ከጉልበትና ከጡንቻ ውጪ ምን ፖሊሲ አለው? … ብቻ መጨረሻቸውንና መጨረሻችንን ማየት ነው፡፡
ሌላ ሰበር ወሬ፡- የሊቢያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬ ጧት በታጣቂዎች ታግቶ ተለቀቀ - አስቂኝና አስገራሚ ድራማ፡፡ ባለፈው ሣምንት አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የአሜሪካን ሀገር የመንግሥት ሠራተኞች “ሸትዳውን” በሚሉት የማይገባኝ የቅንጡዎች ፈሊጥ ከሥራ ገበታቸው ላልተወሰነ ጊዜ ታገዱ - ያለደመወዝ፡፡ ዝኆኖች ሲራገጡ ሣር ይጎዳል፤ የፉክክር ደጃፍም ሳይዘጋ ያድራል፡፡ በፓርቲዎች አለመስማማት ዜጎች ለስቃይ እየተጋለጡ ነው፡፡ ሦርያን ተመልከት፤ ግብጽንና ኢራቅንም አትርሳ፤ እስራኤልንና ኢራንን በፍጹም ከ‹ቅን›ጭላትህ አታውጣ፤ ቦኮሃራምንና አልቃኢዳን እንዲሁም አልሻባብንና ቱዋሬግን ሌሎችንም የዐመፃና የነጻነት ትግል እንቅስቃሴዎች ከረሳህ ልክ አይደለህም፤ የባህር ላይ ዝርፊያንና የባሕርዳሯን ሶማሊያን እንደነገሩ አስታውስ፤ በቀየህ የአራት ኪሎውን የሚንተከተክ ድፍድፍ ከዘነጋህ ደግሞ አጉል ነው - ትሳነፋለህ ወዳጄ፤ በየዓለም ሀገሮች የገባውን የምግብ እህል አቅርቦትና የነዳጅ ዋጋ ንረት አስብ፤ በብዙ ሀገሮች ውስጥ ያለዐዋጅ እየተጧጧፈ የሚገኘውን ‹ሰላማዊ ጦርነት› ልብ በል - የኑሮውን መጦዝ፣ እንደሮኬትም መተኮስ ‹ግንዛቤ አድርግልኝ›፤ ሲያልቅ አያምር ይባላል፡፡ ሁሉም ነገር እያለቀ ነው እህታለም፡፡ ይሄ ነገር ማለትም እነዚህ ነገሮች ወዴት እያመሩን ይሆን? ጠርጥር ገንፎም አለው ስንጥር! ግን አትጨነቅ ወንድማለም፤ ተጨንቀህ ምን ልታመጣ? ብዙ ተጨነቅን፤ ነገር ግን አንድ ትልቅ የተለዬ ሀገር የሚሞላ ሕዝብ ከኢትዮጵያ በየጊዜው እየተሰደደ ሲወጣ ያ ሁሉ ጭንቀታችንና ይሄ ሁሉ ጥበታችን ይህን ፍልሰትና ግዞት፣ ይህን የሲዖልና የዋዕይ ዘመን ጋብ ሊያደርገው አልቻለም፡፡ ስለዚህ የጌታ ጊዜ እስኪመጣ መታገስ ነው - በጸሎት፡፡ ከሰው ስህተት ከብረትም ዝገት አይጠፋምና (ካ/ባ)ጠፋሁ ይቅርታ፡፡
ለአስተያየት አድራሻዬ yiheyisaemro@gmail.com መሆኑን በታላቅ አክብሮት እገልጣለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment