Monday, October 14, 2013

አላባራ ያለው የአማራ ህዝብን ማንነቱንና ታሪኩን የማጥፋት ዘመቻ

ከገረመው አራጋው ክፍሌ – ከኖርዌ
ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ላለፉት 40 ዓመታት  አንግቦት የተነሳው አንድን ብሔር ለይቶ የማጥራት (Ethnic cleansing) ዘመቻ  ዛሬም ቀጥሎበታል፡፡ይህ ቡድን በስልጣን እስካለ ድረስም ወደፊት ይቀጥላል፡፡ ዜጎች በገንዛ ሀገራቸው ከእንስሳት ያነሰ ክብር ተነፍገው ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወሩ፣ ንብረት እንዳያፈሩ፣ ያፈሩትንም ንብረት በተደራጁ ዘራፊዎች እንዲነጠቁ እየተደረገ  ነው፡፡በተለያዩ ሀገራት የእንስሳት መብት ተከራካሪ ወገኖች ስለእንስሳት አያያዝ እና እንክብካቤ ተደራጅተው በጋራ እየተንቀሳቀሱ  በሚገኙበት ባሁኑ ወቅት ከጊዜው ጋር አብሮ መራመድ የተሳናቸው ዘረኛ ቡድኖች በተለያዩ ጊዜያት በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ወገኞቻችን ላይ የሚፈጽሙት ጭካኔ የተሞላበት ግፍ  የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ልብ የሚያደማ ነው፡፡
 ወያኔ ኢትዮጵያዊነትንና የአማራን ህዝብ ማንነትና ታሪኩን ለማጥፋት የላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቶአል አሁንም አጠናክሮ ቀጥሎበታል ለምሳሌ ወያኔ ወደስልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ በአማራው ህዝብ ከፈፀሟቸው አያሌ ከሆኑት ናዚያዊ ተግባሮቻቸው መካከል ዋና ዋናዎቹን ለማስታወስም ያህል፦  
- ገና ሲሽፍቱ በትግራይ ውስጥ ብቻ በሚነቀሣቀሱበት የመጀመሪያዎቹ ሦሥት ዓመታት እነርሱ ቀዳሚ የዘር ማፅዳት ሠለባ ያደረጓቸው እዚያው ትግራይ ውስጥ በሥራም ሆነ በሌላ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ምክንያት ይኖሩ የነበሩትን ዐማሮች ነበር። እንዲያውም ከእነዚያ  ዐማሮች መካከል አንዳንዶቹ ከትግሬዎች የተጋቡ እና የተዋለዱ ነበሩ። ወያኔዎች ግን እኒያ ሰዎች ዐማሮች ሰለሆኑ መወገድ ነበረባቸው። ስለዚህ አንድ በአንድ በወረንጦ እየለቀሙ ጨፈጨፏቸው።
- ከ1971 ዓ.ም. ጀምሮ ወያኔ ከትግራይ ወደ ጎንደር የመስፋፋት ጦርነት አድማሱን ሲያሠፋ የመጀመሪያ እርምጃው በወልቃይት እና ጠገዴ  የሚኖሩ የጎንደር ዐማሮችን በጅምላ መፍጀት ነበር። እስከዛሬ ምን ያህል የወልቃይት እና የጠገዴ ዐማሮችን እንደጨፈጨፉ በአሃዝ ለይቶ  ለማስቀመጥ ቢከብድም በ20 ሺህዎች የሚቆጠሩትን ከምድረ ገፅ እንዳጠፉ፣ ከ70 ሺህ የማያንሱትን ደግሞ ከጥንት አባቶቻቸው ርስት  አፈናቅለው ስደተኛ እንዳደረጓቸው ይታወቃል። ወያኔዎች የጎንደር ግዛት የሆነውን የወልቃይት ፣ የጠገዴ እና የፀለምት አካባቢዎችን  «የትግራይ ክልል» ብለው ነጥቀዋል። በአካባቢውም ከተለያዩ የትግራይ አውራጃዎች ያመጧቸውን የራሣቸውን ዘር አሥፍረውበታል።
- ሥልጣን ከያዙበት ከግንቦት 1983 ዓም ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያ ዐማሮችን፦ «ነፍጠኞች፣ ትምክህተኞች፣ አድሃሪዎች፣ ጨቋኞች፣ የትግራይ ሕዝብ ደም መጣጮች፣ ወዘተርፈ» እያሉ ከአገራቸው አፈናቅለዋል፣ ጨፍጭፈዋል። በተለይም ከግብር አጋሮቻቸው ከሻቢያ ፣ ከኦነግ እና ከኦብነግ ጋር በመሆን በሐረርጌ (በበደኖ፣ በሐብሩ፣ እና ሌሎች ሥፍራዎች)፣ በአርሲ (በአርባ ጉጉ እና ጢቾ)፣ በወለጋ፣በጅማ፣ በኢሉባቦር፣ በባሌ፣ በሲዳማ፣ በጌድኦ፣ በወላይታ፣ በከፋ፣ በጉራፈርዳ፣ በመተከል፣ በአሶሳ እና በሌሎችም አካባቢዎች በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዐማሮችን በአሠቃቂ ሁኔታ ፈጅተዋል።
- ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ «ብረት ማስፈታት» በሚሉት ዘመቻ ዐማራው ሙሉ በሙሉ ትጥቁን እንዲፈታ ተደርጓል። በተለይም «የዐማራ ክልል» ብለው በሠየሙትና አብዛኞቹ የዐማራ ተወላጆች በሚኖሩበት አካባቢ ይህንን ዘመቻ በበላይነት የመራው ኤርትራዊው በረከት  ስምዖን ነው። ዛሬ ዛሬ የዐማራ ተወላጅ እንኳን የጦር መሣሪያ ይቅርና የብረት ጅንፎ ያለው ዱላ መያዝ ጦር መሣሪያ እንደመታጠቅ ተቆጥሮበት ራሱን ከትንሽ አውሬ የሚከላከልበት ዱላ እንኳን መያዝ አይችልም።
- ከ1985 እስከ 1987 ዓ.ም. ባካሄዱት «ሽፍታ ምንጠራ» ብለው በሠየሙት ዘመቻ ከዐማራው መካከል ንቃተ-ኅሊናቸው ከፍ ያሉትን እና  «ለወያኔ አገዛዝ አይንበረከኩም» ብለው የሚያስቧቸውን ዐማራዎች እየለቀሙ አሥረዋል፣ ደብዛቸውን አጥፍተዋል፣ ገድለዋል።
- ከ1986 እስከ 1987 ዓ.ም. ዐማራውን በሦሥት መደቦች ከፋፍለው፦ የወያኔ ኮር አባል፣ ተራ ዜጋ እንዲሁም ቢሮክራት እና ፊውዳል  ብለው መድበው መሬት አከፋፍለዋል። የመሬት ድልድል ሲያደርጉ በገጠሩ የዐማራ ማኅበረሰብ መካከል የመደብ ልዩነት በመፍጠር  ዐማራው እርስ በእርሱ እንዲፋጅ ሲያደርጉ፣ በተለይም ደግሞ አብዛኛውን ዐማራ የኢኮኖሚ ዐቅሙ የተዳከመ እና ፍፁም በድነህት የሚማቅቅ ምስኪን አድርገውታል።
- ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ በምሥራቅ ወለጋ ለዘመናት ይኖሩ የነበሩትን ዐማሮች «የጦር መሣሪያ ታጥቃችኋል፣ የኦሮሚያን መሬት ለግላችሁ  አድርጋችኋል፣ የኦሮሚያ የቦታ ሥሞችን የዐማራ ስም አውጥታችሁላቸዋል፣ የከብት ዝርፊያ ትፈፅማላችሁ፣ ደን ትመነጥራላችሁ» እና  የመሣሠሉትን ሠበቦች በመደርደር ከ12 ሺህ የማያንሱትን አፈናቅለዋቸዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩትን ዐማሮች ደግሞ የአካባቢው የወያኔ  ሎሌ የሆኑት የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ታጣቂዎች ፆታ እና ዕድሜ ሣይለዩ በአሠቃቂ ሁኔታ ጨፍጭፈዋቸዋል።  የተፈናቀሉት ዐማሮች ከነበሩበት ሥፍራ ተባርረው ጎጃም ክፍለሀገር አገው ምድር አውራጃ ውስጥ ጃዊ የሚባል እጅግ ሞቃታማ እና  በወባ ወረርሽኝ በሚጠቃ ወረዳ እንዲሠፍሩ ተደርገው አብዛኞቹ በወባ ወረርሽኝ እንዲያልቁ ተደርገዋል።
- ከሚያዝያ 16 ቀን 2001 ዓ.ም. ወዲህ ከአዲስ አበባ እና ከሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች “የግንቦት 7 ንቅናቄ አባሎች ናችሁ” ተብለው  ከታሠሩት ከ37 በላይ የሲቪል ፣ የደህንነት ፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የወታደር እስረኞች መካከል አብዛኞቹ ዐማሮች ናቸው። በእኒህ  እሥረኞች  ላይ የወያኔ መርማሪ ፖሊሶች ካደረሱባቸው ዘግናኝ ግርፋት ዓይነቶች መካከል፦ የወንድ የዘር ብልት ማኮላሸት፣ በኤሌክትሪክ መጥበስ፣ ጥፍር መንቀል፣ ከባድ ድብደባ፣ በአስጨናቂ ሁኔታ በካቴና ጠፍሮ ማሠር እና ከጣሪያ ላይ ማንጠልጠል፤ እንቅልፍ መከልከል፣  በርሃብ እና በውኃ ጥም ማሠቃዬት፣ ጫካ ውስጥ ወስዶ ግድያ እንደሚፈፀምበትና ሬሣው ለአውሬ እንደሚጣል ማስፈራራት  ይገኙባቸዋል። እኒህ እሥረኞች በአካል የተሠቃዩት ሣያንስ እጅግ ቅስም-ሠባሪ ዘለፋ ለመስማትም ተገድደዋል፦ ከወያኔዎቹ አረመኔ ገራፊዎች ከሚወጡት ቃላት ውስጥ፦ “ትምክህተኛ ዐማራ፣ ግም ዐማራ ፣ ብስብስ ዐማራ፣ ሽንታም ዐማራ፣ ፈሪ ዐማራ፣ በኤድስ ቫይረስ  የተበከለ ደም እንወጋሃለን፣ ከሃምሣ ጋይንት አንድ አጋንንት ይሻላል አንተ ሆዳም ጋይንቴ፣ ዘር-ማንዘርህን ቀሚስ አልብሰን የወጥ-ቤት  ሠራተኛ አድርገን እንገዛዋለን፣ አንተ ደም መጣጭ ጎጃሜ እናቃጥልሃለን፣ ዘረ-ቆሻሻ ዐማራ፣ ወዘተርፈ” የሚሉ ይገኝባቸዋል። እኒህ  እሥረኞች በወያኔው የጨረባ ፍርድ ቤት እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት ተጥሎባቸዋል።
- ሰሞኑን በሕዝብ መገናኛ ተቋሞች አማካይነት ይፋ የሆነውና የሕዝብ መነጋገሪያ የሆነው አሣዛኝ ዜና እንዳተተው  የጃን አሞራ፣ የማይጸብሪ አዋሳኝ፣ ራስዳሸንን ጨምሮ የአዲአርቃይን አካባቢዎች ወደ ትግራይ፣ በመተማ በኩል ደግሞ የተወሰነውን ክፍል ለቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለመስጠት ድርድር በመካሄድሌይ ነው።መንግስት ከአሁን በፊት በአማራ ክልል ስር የነበረውን የመተከል ዞን ለቢኒሻንጉል ጉምዝ ፤ራያና ቆቦ ፤ዳንሻ እና ሁመራ ፤በመተማ በኩል ለሱዳን ፤የመተማ ቀሪው ክፍል ለቤንሻንጉል ፣ በሰሜን ሺዋ በኩል  ለኦሮምያ የልማት እገዛ በሚል መሰጠቱን በማውሳት ፣ አሁንም ተጨማሪ መሬት እየተቆረሰ ክልሎችን ለማስደሰት እየዋለ ነው ።
የአንቀጽ 39 ቱርፈቶች የሰጡን ገፀ በረከቶች ናቸው ሲሉ የአማረሩት የድንበር ከተማ ነዋሪዎች፣  ”ጨለምተኛ አባት መሬት እየሸጠ ልጆቹን ከእርስት ይነቅላል፡፡ ጨለምተኛ መንግስት አገርን በመሸጥ ዜጎችን ያስደፍራል፡፤ ምንነታቸውን ያሳጣል መንግስትም ማንነታችን እየነጠቀን ነው ሲሉ” ገልጸዋል።
- በወልቃይት በሚገኘው ጎሮ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይማሩ የነበሩ የአማራ ልጆች ዘንድሮ እንዳይመዘገቡና እንዳይማሩ መከልከቸው ልቻቸው እንዳይማሩ የተከለክሉባቸው ወላጆች ጉዳዩን በአካባቢው ወደሚገኝ የ የወያኔ አስተዳደር አቤት ማለታቸውንና በስፍራው ካሉ የወያኔ  አካላትም “ይህ የትግራይ እንጅ የአማራ አገር ባለመሆኑ ትምህርት ቤቱ የአማራን ልጆች አለመቀበሉ ተገቢ ነው” የሚል ምላሽ  አግኝተዋል ። ወልቃይት ከጥንት ከጠዋት ጀምሮ የጎንደር ክ/ሃገር ግዛት የነበረ ቢሆንም አሁን ግን የትግራይ ነጻ አውጭ ቡድን የትግራይን ግዛት ለማስፋፋት ካለው ገደብ የለለው ህልሙ በመነሳት ባለእርስት የሆነውን አማራ በሃይል በማፈናቀልና በማጥፋት ከ500,000 በላይ የትግራይን ተወላጆች ተከዜን አሻግሮ አስፍሮበታል።
በአማራ ህዝብ ላይ ጥላቻን መሰረት አድርገው በመካሄድ ላይ ያሉ ማንነቱንና ታሪኩን የማጥፋት ዘመቻ  ተባብሰው ቀጥለዋል አማራው እንደ ህዝብ እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ ጭቆናና መከራ ሁሉ ተጠያቂ ተብሎ ሲወገዝ ቆይታል ገዝው ሁሉ አማራ ተባለ እንጂ ፓለቲካቸው ለሰፊው የአማራ ህዝብ የፈየደው ብዙ አልነበረም የአማራ ህዝብ ሰፊ ነው በኢትዮጵያነቱ አምኖ ከሌሎች ብሄሮች ጋር በመሆን ታሪክ የሰራም ህዝብ ነው ወያኔ  ይህንን እውነታ ወደጎን  በመተው የአማራን ህዝብ ማስጨፍጨፍና ማፈናቀልን ለጥቃት  ማጋለጡን ቀጥሎበታል ብዙሃኑ የአማራ ህዝብ  በማያወላዳ መልኩ ለአገር አንድነት የቆመ ነው ይህ የኢትዮጵያዊነት ስሜቱ እንደ ሀጥያትና ወንጀል ተቆጥሮበት ከተወገዘ ደግሞ እራሱን ለማዳንና መከላከል የግድ ይሆንበታል አማራን ያህል ሰፊ ህዝብ አግልሎና አውግዞ ልማት አካሂዳለው ማለት ዘበት መሆኑን ወያኔ  ጠንቅቆ  ሊያውቀው ይገባል:: ሀገራችን የጋራ ናትና ሁላችንም ልንጠብቃት ይገባል:: ሁሉም የሚሆነው በሀገር ነው:: አቦይ ስብሀት: ወያኔ: መኢአድ: ጣሊያንና ሌሎች ጠባብ ድርጅቶች ከፋፋይና ዘረኞች ናቸውና እንርሳቸው:: ለነጻነትና ለዴሞክራሲ የሚደረገው ትግል ግን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል::  አማራነት የሀገርን ፍቅር ነው:: ቀደም ብለው የተሰሩ ስህተቶች ካሉ አርመን ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን አንድነቷ የተጠበቀ: ሰላምና እኩልነት የሰፈነባትና ዴሞክራሲያዊት የሆነች ኢትዮጵያን እንመስርት:: ዘረኞችና ከፋፋዮች የሚጠፉት ሀገር ወዳድ የሆንን ሁሉ በጋራ ስንቆም ነውና አንድነታችንን እናጠንክር::
ኢትዮጲያና ኢትዬጲያዊነት ለዘላለም ይኖራል። ወያኔ ግን በተባበረ የ ኢትዮጲያዊያን ጠንካራ ክንድ ይወገዳል!!

No comments:

Post a Comment