Monday, March 9, 2015

አድዋ እና ደደቢት የተቀመጡበት ሰባራ ሚዛን

ወርሃ የካቲት በሃገራችን በርከት ያሉ ወሳኝ ታሪካዊ ሁነቶች የተካሄዱባት ወር ነች፡፡ከሃገራችን አልፎ አፍሪካን፣ ከዛም ገፍቶ የላቲን አሜሪካን ጥቁሮችን ያኮራው፣ በአጠቃላይ በነጭ ቅኝ አገዛዝ ስር ለነበሩ ሁሉ የነፃነት ተስፋ ለመሆን የበቃው የአድዋ ድል የተከወነው በዚች ታሪካዊ ወር በየካቲት ነው፡፡አብረሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ፋሽስቱን ግራዚያኒን ለመግደል ባደረጉት ሙከራ በበቀል የነደደው የፋሽስት ኢጣሊያ አስተዳደር ኢትዮጵያዊ ምሁራንን እያሰሰ፣ ድሆችን በእህል ውሃ እየደለለ ሰብስቦ የከበደች የበቀል ክንዱን ያሳረፈባቸውም በዚሁ በየካቲት ወር ነበር፡፡ በሃገራችን ታሪክ ጉልህ ስፍራ ያለው የመሬት ላራሹ ጥያቄ የቀረበበትም በየካቲት 18 ነበር፡፡
‘ብሶት ወልዶን፣ ምሬት አብርሮን አስራ አንድ ሆነን፤ አራት ጠብመንጃ፣አንድ አሮጌ ሽጉጥ እና አንድ ቢለዋ ተማምነን፤ ተጉዘን ተጉዘን ደደቢት በረሃ የደረስነው የካቲት 11 ቀን ነበር’ የሚሉት ህወሃቶችም ‘ደማቅ ታሪክ ፃፍንባት’ ሲሉ ይህችን ቀን ይዘክሯታል፡፡
ታጋዮቹ የካቲት 11 በታላቅ ጨለማ ውስጥ የነበረው መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ ሚደነቅ ብርሃን የተሸጋገረበት የቀን ቅዱስ አድርገው ያወሩ ይፅፉለታል፡፡ አለቅነት በጫንቃቸው ላይ ነውና ብዙ ንዋይ አፍስሰው ደግሰው ያስቡታል፡፡ለዚህ ድንቅ የጀግንነት ተግባር ደግሞ የትግራይህዝብ ላቅ ያለ ጀብዱ ሰርቶ ከእርሱ በብዙ እጥፍ በሚልቀው መሬት ላይ የሰፈረውን ሰፊ የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃ እንዳወጣ ሰርክ ደግመው ደጋግመው ሲናገሩት፣ በተግባርም ከትግራይ የወጡ “መኳንንትን” በወሳኝ የስልጣን እና የሃብት ማማ ላይ በመሰየም ሲያሳዩት የኖሩት ነው፡፡ትግራይን እንገነጥላለን ብለው ስለትግራይ ብቻ የሚታገሉ የጠባብ ብሄርተኞችን ትግል፣ በዛ ላይ ስለኤትራ ፍቅር ሃገራቸውን ቀኝ ገዥ አድርገው የሚያወሩ ታጋዮችን የትኛው ኢትዮጵያዊ ‘ልክናችሁ ሃገራችን ኢትዮጵያ ኤርትራንም ትግራይንም ቀጥቅጣ የምትገዛ ቅኝ ገዥ ናት’ ብሎ ሊያግዛቸው እንደፈለጉ ግራ ነው፡፡ የኋላ ኋላ ሻዕብያ ‘የምን ትግራይን ነፃ ማውጣት ነው አርፋችሁ ደርግን ለመጣል ተዋጉ’ ሲላቸው ‘ህብረብሄራዊ ነን’ ሲሉ ኢህአዴግን በመሰረቱ ሰዓት ግን ደርግን የሚጠላው የኢትዮጵያ ህዝብ የቀደመ ንግግራቸውን ሳይቆጥር አብሯቸው ታገለ፡፡ኢህአዴግ ነን ከማለታቸው በፊትም ቢሆን የሰሜን ወሎ እና የደቡብ ጎንደር ህዝብ ዘሩን ሳይቆጥር የነሱ ስምም ‘የትግራይ ብቻ ሃርነት’ እንደሆነ እያወቀም ደርግን በመጥላት ብቻ ሳይሆን እነሱም ወንድሞቼ ናቸው ብሎ አሯቸው ታግሏል፡፡ ይህን ግን እንደ አቶ አሰገደ ገ/ስላሴ ያሉ የእውነት ምስክሮች ካልሆኑ ጀግንነቱን ሁሉ እነሱ ለወጡበት ብሄር ለማድረግ ይፈልጋሉና ሌሎች ህወሃቶች ሲናገሩት አይደመጥም፡፡ ዘንድሮ በተደረገው የድርጅታቸው የአርባኛ አመት በአል አከባበር ላይ ደግሞ ይህንኑ የቆየ ዝንባሌ ጫን፣ ጠብሰቅ አድርገው ሲያስተጋቡ ሰንብተዋል፡፡ ከሌላው ኢትዮጵያዊ “ለየት ያለ ጀግንነት” ባለው የትግራይ ህዝብ ክንድ ተራዳኢነት አሁን ለሚኖርበት “ድንቅ የነፃነት ኑሮ” እንደበቃ በተለያየ ዘዴ ደጋግመው ነግረውታል፤ አስነግረውታል፡፡ ይህ መልዕክት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልቦና ውስጥ ይሰርፅ ዘንድ ከሁለት ወር በፊት አንዱን አስራ አንድ አድርገው የሚያቀርቡ “የልብ አድርስ” አርቲስቶች ደደቢት ድረስ ተጉዘው የተለመደ ግራቀኝ ያላየ የፕሮፖጋንዳ ነጋሪትነት ሚናቸውን እንዲወጡ ተደርጓል፡፡
መገናኛ ብዙሃኑም ከጥር ጀምረው ስራ አልፈቱም፤ ተጋዳላዮቹ ስለህዝብ ነፃነት የቧጠጡትን ተራራ፣የተንደረደሩበትን ቁልቁለት፣የተሸከሙትን ዝናር እና መውዜር፣ የታጠኑትን ባሩድ፣ የረጋገጡትን እሾህ ቆንጥር የሚያሳይ ፊልም ሳያሰልሱ ለተመልካች አድርሰዋል፡፡ የህወሃት ትግል የወንዶች ብቻ የነበረ ይመስል ወንድ ተጋዳላዮችን ብቻ ያስተወነው የብርሃኔ ንጉሴ “ድንቅ አስመድራኪነት” የታየበት “ሙሴ” ፊልም በብዙ ስፖንሰሮች ታጅቦ (ሲኒማ ቤት ሄደን ለማየት ለማይዳዳን) ቤታችን ድረስ መጥቶ እንድናይ የተደረገውም የትግራዊያኑን ጀግንነት በአይነ ልሳን አይተን፤ በልባችን ማህተም እንድናትም ነው፡፡ ይህን ፊልም ካነሳሁ አይቀር ከአቶ መለስ ጋር ስለተጣሉ ብቻ በትግሉ የመጀመሪያ አመታት፣ መለስ ራሱ እዚህ ግባ የሚባል ሚና በሌለው ወቅት ትልቅ አስተዋፅኦ የነበራቸውን እንደ ግደይ ዘርኣፅዮን ያሉ ቀደምት ታጋችን እንዳልነበሩ የማድረጉ ወይም ሚናቸውን አሳንሶ የማቅረቡ ነገር አስተዛዛቢ ነው፡፡ ሌላውን ብሄር ብሄረሰብ እንወክላለን የሚሉ የኢህአዴግ አባል እና አጋር ድርጅት ባለስልጣናት ይህንኑ የትግራይ ህዝብ እነሱ ለመጡበት ብሄር ነፃነት መረጋገጥ ያደረገውን ጀግንነት፣ ተራዳኢነት እና ውለታ ከአንድ ወር ቀደም ብለው በሃገሪቱ ቴሌቭዥን መግለጫ እየላኩ፣ በአካል እየቀረቡ ሲያስተጋቡ የሰነበቱት አንሰሶ ሲቃ እየተናነቃቸው “ለጀግና ህዝብ” እንደሚገባ ምስጋና እንዲሰው ቅጠልያ የሚሊሽያ ጃኬት፣ ቀለም የበዛበት የተጋዳላይ ሽርጥ አንገታቸው ላይ ጠምጥመው እዛው መቀሌ እንዲከትሙ ሆኗል፡፡
ድህነት ባጎበጣት ሃገራችን አቅም ቀርቶ ለባለፀጎቹ ሃገራትም ቢሆን ቀላል ያልሆነ ወጭ ወጥቶበት በተከበረው የህወሃት ልደት በአል ላይ የተገኙ ‘ታግለን ነፃ አወጣናችሁ’ ባይ የህወሃት ባለስልጣናት እና ‘ታግለው ነፃ አወጡን’ ባይ የአጋር ወይም የአባል ፓርቲ ሹመኞች እንደሚያወሩት ትግሉ ኢትዮጵያን ምድረ ገነት አድርጓታል ወይ የሚለውን ለማተት መነሳት አንባቢ የእጁን መዳፍ ያህል የሚያውቀውን ሃቅ በመደጋጋም ማሰልቸት ይሆንብኛልና ወደዛ አልገባም፡፡ ከዛይልቅ ህወሃቶች ከፈልን የሚሉት መረራ መስዕዋትነት ፣ሰርክ በቴሌቭዥን የሚያሳዩን መሳሪያ ዘቅዝቆ መሮጡ፣መራብ መጠማቱ፣መቁሰል መድማቱ በፖለቲካችን በጎ ለውጥ እንዲመጣ ካላስቸለ በራሱ ትርጉም ሰጭ ተደርጎ በየአመቱ ከበሮ የሚያስደልቅ ነው ወይ? የሚለውን ማንሳቱ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ የተከፈለው መስዕዋትነት መራራነት ባያጠያይቅም የተጨበጠ ለውጥን ያላመጣ ትግል ከኢህአዴግ ባለስልጣናት እና የስርዓቱ ባለሟሎች በቀር ሌላውን ህዝብ ሊያስፈነጥዝ እንደማይችል መታወቅ አለበት፡፡ብዙ ገንዘብ ፈሶበት እንዲታይ የተደረገው ትርኢትም ሆነ ‘የዛሬዋ ኢትዮጵያ የገነት ቅርንጫፍ ነች’ የሚለው አሰልች ፕሮፖጋንዳ ሰፊውን የኢትዮጵያ ህዝብ እንደማያሳምን፣ይልቅስ ተናጋሪዎቹ ይህን በተናገሩ ቁጥር ብቻውን እንደሚያወራ ሰው እንደሆኑ ሊያውቁት ይገባል፡፡ ደሃው የኢትዮጵያ ህዝብ ለበአሉ ድምቀት የፈሰሰውን ንዋይ ሲመለከት ገንዘቡ የእርሱን ድህነት የማቃለል አንዳች ፋይዳ ባለው ጉዳይ ላይ ቢውል ሳይመርጥ አይቀርም፡፡
የህወሃት አርባኛ አመት ሲከበር በደርግም ሆነ በህወሃት በኩል ያለቁት ኢትዮጵያዊያን ናቸውና ነገሩ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እናቶች የእግር እሳት እንጅ የከንፈር እልልታ ይዞ የሚመጣ ነገር እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል! እናም ወንድም እና ወንድም የተላለቁበትን ጦርነት ልክ የሩቅ ጠላትን ድምጥማጥ ያጠፉበት ጀግንነት አድርጎ እንዲህ ጫፍ በወጣ ሃሴት ማክበር አንድም በፕሮፖጋንዳ የመታወር ሁለትም አርቆ ያለማስተዋል ምልክት ነው፡፡እንደ ቃየል የወንድምን ደም ማፍሰስ የወንድማማቾቸች ደም ውሃ ሆኖ የስልጣን እድሜያቸውን ካለመለመላቸው፣ ደርሶ የሃብት ማማ ላይ ቂብ ካደረጋቸው ትቂቶች በስተቀር ለሌላው ኢትዮጵያዊ ይህን ያህል የሚያስፈነጥዝ ጀብዱ አይደለም፡፡ መተላለቁ ሌላው ቀርቶ በአብዛኞቹ የአፍሪካ ሃገራት ደረጃ እንኳን ዲሞክራሲን፣ፍትህን፣ እኩልነትን፣ነፃነትን ያመጣ ቢሆም እንኳን ልጆቻቸውን የአሞራ እራት ያደረገ ነውና ለኢትዮጵያዊያን እናቶች ግንጥል ጌጥ መሆኑ አይቀርም ነበር፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ደግሞ ወላጆችን ከሁለት ያጣ ጎመን ያደረገ፣ አንገት ሊያስደፋ የሚገባ ነገር እንጅ እንዲህ ክንፍ አስጥሎ የሚያስጨፍር ውጤት ያመጣ አይደለም፡፡ ሃቁ ይህ ነው!
ሰባራው ሚዛን
የአርባኛ አመቱ አከባበር ይባስ እንጅ ከዚህ ቀደም ለህወሃት ምስረታ በአል የሚፈሰው ገንዘብ፣ ጊዜ እና ፕሮፖጋንዳ ለሌሎች የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ተደርጎ የሚያውቅ አይደለም፡፡የህወሃት ምስረታ በአል ነገራ ነገሩን ላስተዋለው የአንድ ክልል ፓርቲ ቀርቶ ለሃገር አቀፍ ብሄራዊ ክብረ-በአል እንኳን የሚበዛ ሽርጉድ እና የገንዘብ ብክነት የሚታይበት ነው፡፡ከላይ እንደተጠቀሰው የህወሃት ምስረታ በዓል በሚከበርበት የካቲት ወር ለሃገራችን ትልቅ ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ ፋይዳ ያመጡ እና በደማቅ ሁኔታ መከበር የሚገባቸው ሁነቶች የተከናወኑበት ቢሆኑም አስተዋፅኦቸውን የሚመጥን ትኩረት ተነፍገዋል፡፡ በአንፃሩ ለህወሃት ምስረታ በአል ካመጣው ፋይዳ የትየለሌ የሚልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እናያለን፡፡
እንደሚታወቀው የህወሃት ትግል ለሃገሪቱ ያመጣው ፋይዳ ምንም ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ ትግሉን ለማስጀመር አነሳሳ የተባለው የደርግ ዲሞክራሲ የራቀው ተጠያቂነት አልባ አገዛዝ በነፃአውጭነን ባዮቹ ህወሃቶች አገዛዝ ዘመን ሙስናን አክሎ መጣ እንጅ የቀነሰ የአምባገነንነት ፈለግ የለም፡፡ዛሬም በኢትዮጵያ ሰዎች በአስተሳሰባቸው ከመንግስት ስለተለዩ ብቻ ይገደላሉ፣ አድራሻው በማይታወቅ እስር ቤት የመከራ ገፈት ይጎነጫሉ፣በቤተ ዘመዶቻቸው እንዳይጎበኙ ይከለከላሉ፣ፍርድቤት ሳይቀርቡ በኢህአዴግ ባለስልጣናት ቀጭን ትዕዛዝ ብቻ ለወራት ጨለማ ቤት ይዘጋባቸዋል ፣በጥበቃ ስር ያሉ እስረኞች በጥይት ተደብድበው ይሙቱ ይኑሩ እንኳን ለዘመዶቻቸው አይነገርም(ደርግ እንኳን በእስር ቤት የገደለውን ሰው ልብስ ለቤተሰቦቹ በመመለስ እንደሞተ በቅኔ ይናገር ነበር)፡፡ እድላቸው ቀንቶ የነገስታት መልካም ፈቃድ ሆኖ የታሰሩበት አድራሻ እንዲታወቅ የሆኑት ደግሞ ከዘመዶቻቸው ርቀው ዝዋይ እስርቤት እንዲታጎሩ ይደረጋል፣ዛሬም የኢትዮጵያ እናቶች እስርቤት ያሉ ልጆቻቸውን እያሰቡ እድሜ ባደከመው አይናቸው ያለቅሳሉ፡፡ ህወሃቶች ከገነት በሚያወዳድሯት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ቀርቶ መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች ያለጠያቂ ይረጋገጣሉ፡፡ይህን ሁሉ የሚያደርግ ስርዓት ወደ ትግል የገባበትን ቀን ከበሮ እየደለቁ፣ የሆነ ያልሆነውን እየቀላመዱ ማክበር እና እንደ አድዋ ድል መታሰቢያ ያሉ የሃገር ኩራት በአላትን ደግሞ እንዲሁ በለሆሳስ ማለፉ የሃገራችንን ወቅታዊ ፖለቲካ ሚዛን ሰባራነት ያሳያል፡፡
በህወሃት ምስረታ ክብረ-በዓል ላይ የራሳቸውን ወታደራዊ ጀብድ ትንፋሽ እስኪያጥራቸው የሚያወሩት የህወሃት/ኢህአዴግ ባለስልጣናት የአድዋ ድል በአል ላይ ተገኝተው ከተናገሩ እንኳን የሚናገሩት በዚህ ዘመን መወራት ያለበት ስለ ጦርሜዳ ጀግንነት ሳይሆን ከድህነት ጋር ስለሚደረገው ተጋድሎ ጀግንነት እንደሆነ ነው፡፡በዚህ ዘመን ስለ ጦርሜዳ ጀግንነት መወራት የሌለበት ለአድዋ እና ማይጨው ሲሆን ብቻ ነው? ምነው የህወሃቶችን የተኩስ ጀግንነት፣ ውጅግራ ይዞ ሩጫ፣ ታንክ ወድሮ ጥድፊያ እስኪያቅለሸልሸን ያሳዩናል? ስለ ጦርሜዳ ጀግንነት በዚህ ዘመን መወራት የለበትም ከተባለ የአይጥ ምስክር ድምቢጥ ሆነው እርስበርስ እየተሸላለሙ ጭምር ስለራሳቸው ጀግንነት የሚያላዝኑትንም ማቆም አለባቸው፡፡ ካልሆነ ለአድዋ፣ ማይጨው፣ የአርበኞች ቀን አይነት ብሄራዊ አርማ ለሆኑ በአላት ሲሆን ብቻ ‘ስለጦርሜዳ ጀግንነት አታውሩ’ ማለት በእነዚህ ጦርነቶች እንደ ህወሃቶች የአረብ ምንዳ ሳይቀርብላቸው ከራሳቸው ቤት ከልጆቻቸው አፍ ነጥቀው በሰነቁት ስንቅ ፣ በኋላ ቀር መሳሪያ ከሃገር ዳርቻ ተጠራርተው ወራሪ ባዕድ ጠላትን ያደባዩትን ጀግኖች አባቶቻችን ድንቅ ጀብዱ ሆን ብሎ ለማለባበስ መሞከር ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በእነዚሀ ጦርነቶች ጀገኖች አባቶቻችን የከፈሉት መስዕዋትነት ያመጣው ፋይዳ ሃገርን ከነነፃነቷ ለመጭው ትውልድ የማስረከብን ታላቅ አላማ ያነገበ እንጅ እንደ ህወሃት ትግል እናት ሃገርን ቀኝ ገዥ አድርጎ፣ ከአንድ አይሉ ሁለት ወደብ አሳጥቶ፣ ቋንቋን መሰረት አድርጎ የአንድ ሃገርን ህዝብ በጎጥ ለመሸንሸን ያለመ አይደለምና በልዕልና ከህወሃት ድል የትየለሌ ከፍ ብሎ የተቀመጠ፣ ጠያቂ ጠፋ እንጅ በአህጉር ደረጃ የአፍሪካ በአል ሆኖ ቢከበር የማያንስበት ነው፡፡ ስለሆነም ህወሃት መራሹ መንግስት የፈለገውን ያህል ሊያደበዝዘው ቢሞክር የነፃነት ፈርጥ የሆነው የአድዋ ድል በዓል ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው ጥቁር ህዝብ ልቦና የታተም አንፀባራቂ ድል ነው፡፡
ስብሃት ለጀግኖች አርበኞች አባቶቻችን !!!!!!
(ፍቱን መፅሄት ላይ የተስተናገደ)

No comments:

Post a Comment