Wednesday, October 16, 2013

እባብ ለእባብ፣ ይተያያል በካብ

ከወንድሙ መኰንን፣ ለንደን
ወዲያ ማዶ ሁኖ አንድ ሰው ተጣራ
ወዲህ ማዶ ሁኖ ሌላ ሰው ወይ አለው
ጎበዝ አንድ በሉ ይኽ ነገር ለኛ ነው።
የለንደኑ ጸረ-ሕዝብ አመጸኛ፣ አንድ እርምጃ ሲወስዱ፣ ሕዝቡ ሁለት እርምጃ ቀድሞአቸው ይጠብቃቸዋል። ሲበዛ ተንኰለኛ በመሆናቸው፣ አንድ ቀን ተሳስተውም ደግ ነገር ሠርተው ቢገኙ፣ የሚያምናቸው ሰው አይኖርም። በዓይነ ቁራኛ ነው እንቅስቃሴአቸውን የምንቆጣጠረው። በዕውነት ተጸጽተው እንኳን ቢያለቅሱ፣ የአዞ ዕምባ ብሎ ነው ሰው የሚሸሻቸው። አሁንም ተነቃቅተናል።London Ethiopian Orthodox church controversy
አባ ተባዩ አስመሳይ መነኵሴ፣ የሚጠቅማቸው መስሎአቸው፣ ለወየኔ የመሽሎኪያ ቀዳዳ አበጀተውለት አስጠቁን። “የአስተዳደር መዋቅሩ አይሻሻልም፣ እኔም ከሥልጣኔ አልወርድም” – እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ሁኖባቸው ለወያኔ ወደው ገብተው እኛን በሶልዲ ሸጡን።
ከአፈርኩ አይመልሰኝ ሁኖባቸው ነው መሰለኝ፣ የወያኔን ሴራና ሸር የምንቃወምዉን በሙሉ፣ የደርግ ባለሥልጣኖች ብለውን፣ በጠራራው ሜዳ ላይ በቪዲዮ እየተቀዱ “ንጉሳቸውን የገደሉ! ፓትርያርካቸውን የገደሉ![1]”  ብለው ተሳልቀውብን ለወያኔ ታማኝነታቸውን አረጋገጡ።  እነዚህናን የመሳሰሉትን የየጊዜውን ክስተቶች ብዙ ጸሐፊዎች፣ እኔም እንዳቅሚቲ ፣ ጭብጡን አያይዘናችኋል። ነገሩ አሁን አክርረው፣ በጣም አስቀያሚ አድርሰው አደገኛ የሆነ ፍልሚያ ቅዳሜና እሑድ 12th and 13th October 2013 ጠንሠው ተጋፍጠን ተርፈናል። እግዚአብሔር የመስገን!
aba gebreal londonየአዋሳ ገብርኤልን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጥሩ በኋላ፣ አቡነ ገብርኤል (በስተግራ) የለንደኗን ደብረጽዮን ቅደስት ማርያምን በቀሰሙት የትግል ልምድ በክርን ደቁሰው ቁጥጥራቸው ውስጥ ሊያስገቡን የደቡብ አፍርካውን አቻቸውን አቡነ ያዕቆብነ አስከትለው እየገሰገሱ ለሁለተኛ ጊዜ፣ ከተፍ አሉብን። ገና ከአዲስ አበባ ሳይነሱ፣ ሊማርኩን እና “እጅ ወደ ላይ ሊሉን”፣ ሲያስቡ፣ ከዚህ አባ ተባዩ አጭበርባሪ የቀበሮ ባህታዊ፣ ዝግጀታቸውን አጧጧፉ። ብዙ ሺ ብር አፍስሰው ዘማናዊ ቴክኖሎጂ፣ ወደፈለጉበት አቅጣጫ አዙሮ፣ ዙም አድርጎ ተንቀሳቃሽ ምስል መቅረጽ የሚችል ካሜራ ከሕግ ውጪ አስተከሉ። ትልቅ ኪሣራ!!! እንደ የጆርጅ ኦርዌሉ ናፖሊዩን ለዚህ ጉዳይ የሠለጠኑ (brainwashed) የተሸወዱ ወጣቶች እና በወያኔ የደኅንነት ነብሰ በላዎችን ለድብድብ አዘጋጁልን። ዝግጅቱ ተጠናቅቆ ቴክስት መለዋውጥ ጀምሩ። እነሱ ባላሰቡት መንገድ መልዕክቶቻቸው እጃችን ገባ! “ቤተክርስቲያናችሁ ከአዲስ አበባ በመጡ “ብጹአን” አባቶች ቅዳሜ ዕለት ሊከፈትና እሑድም አገልግሎት ሊሰጥ ነው፣ ዕልል በሉ” ተባለ። አሽቃባጮቻቸው “ለዚህ ያደረሰን እግዚአብሔር ይመሰገን” እየተባባሉ በቴክስትና በፊስ ቡክ እንኳን ደስ ያለህ/ሽ መልዕክት መለዋውጡ ጀመሩ። አይ እግዚአብሔርን አለማወቅ! ለእግዚአብሔር የሚሰጥው ትልቁ ስጦታ “ምስጋና” ነው ሲባል፣ ምስጋንውን አስቀድመው እንደ ጉቦ አቅርበው አረፉ! ከማንስ ይማሩ? “አይ አለማወቅሽ አገር መራቁ” አለ ሰዉዬው። የኛም ሰው ተደዋውሎ ምን መደረግ እንዳለበት ከተስማማ በኋላ መሪዎቻችንና የሚችሉ አባላት ማታ ተገናኝተው ዕቅድ አውጥተው ጨረሱ።
ከስብሰባ መልስ 8 የሚሆኑ አባሎቻችን እኩለ ሌሊት ገደማ ቤተክርስቲያን ተሳልመው፣ ወዲያው ሁኔታዎችን ቃኝተው ለማለፍ ሲሄዱ፣ እነ አባ ተንኵሉን ሽር ጉድ ሲሉ ደረሰቡቸው። እንኳን መመንኰስና ሽታውም ሽው ያለለባቸው የዓለም ሰው አባ ተባዩ፣ የግቢውን በር በሰንሰለት ግጥም አድርገው በታማኝ ደንገጡሮቻቸው ሲያሳስሩና ሲይስቆልፉ አገኟችው! አንዱ ወንድማችን አልፎ ወደ ቤተክርስቲያን ዘልቆ ሊሳለም ሲሞክር የአባ የቅሌት ዘበኞች ተረባርበው ሠፈሩበት። የሚሰነዘሩበትን ጡጫ ተቋቁሞ፣ የሚችለውን ያህል ተከላክሎ በዝተውበት ካሰበው ሳይድረስ አቆሙት። ስልክ ቢደወልልንም በዚያን ሰዓት ከሩቅ ቦታ ልንደርስላቸው አልቻልንም። ሌላውን ወንድማችንን አንዱ የአባ ደንገጡር እጁን መትቶ ተንቀሳቃሽ ስልኩ ወድቆ ተሠበሮበት ሊያመልጥ ሲሮጥ፣ ፖሊሶች ደርሰው ያዙት። አይ አባ ተባዩ! በተንኰል ባይሳካ፣ በጉልበት ገቡበት? አሁን ከእግዚአብሔር ቤት ማን ሊለየን ይችላል? እንኳን የሳቸው ሰንሰለትና፣ መትረየስም ቢደገንብን፣ በእመቤታችን ስም ከሚጠራው፣ ከአባታችን ቤት ሊነቀነቀን የሚችል አንዳችም ኃይል አይኖርም። እንዲሁ በከንቱ ነው የሚለፉት! ለማኛውም ነገሩ በዚያው በፖሊስ ጉልበት በርዶ ወደየቤታቸው ሁሉም ሂዱ።
አሁን ይኽ ሁሉ አተካሮ ለምን አስፈለገ? ነገሩ እንዲህ ነው! በOctober 21, Charity Commission ሁለቱንም አካል ሊያደራድር ጠርቷል። ወያኔና አባ ተባዩ፣ በዩኬ ሕግ ሳይሆን በአዲስ አበባው ሲኖዶስ ሕግ ብቻ ነው የምንተዳደረው ብለው ድርቅ ብለዋል። ቻሪቲ ኮሚሺን ይዘው የሚቅርቡት መደራደሪያ ሃሳብ የላቸውም። በሕግ ከተሄደ ቤተክርስቲያኑ ሊያመልጣቸው ሆነ። አስቀድሞ፣ አባ ተባዩ ተንደርድረው ቤተክርስቲያኗን ባይዘጉ እንዲህ ዓይነት ጣጣ ውስጥ ባልተገባ! “አንዴ ወድቄአለሁ፣ ጭቃው ላይ ልንከባለል” የሚሉ ይመስላሉ። ከዘጉም በኋላ፣ በወያኔ አይዞህ ባይነት ይኸን ሁሉ በደል ባላደረሱብን ነበር። አሁን ጉዳዩ በቻሪቲ ኮሚሺን ተይዞ ወደ ሕግ በሚገሰግሥበት ሰዓት ከአዲስ አበባ ሲኖዶስ ጳጳሳት አስመጥተው በራሳቸው ፍላጎት የዘጉትን ቤት ያንን ሁሉ ሕዝብ ውጪ አግደው ለመክፈት በከንቱ ለፉ! አቅማቸውን አለማወቃቸው፣ ይግርመኛል። “ለማይረባ አዕምሮ አሳልፎ ሰጣቸው” ነው የሚለው መጽሐፉ (ሮሜ.፩፡፳፰)?፡እግዚአብሔር ከላይ ሆኖ ስለሚመለከት ሀሳባቸው ከንቱ ሆነባቸው! ከንቱ! የከንቱ ከንቱ!
አባ ተባዩ የሚኖሩበትን አገር ጨርሶ የሚያውቁት አይመስሉም። ዛሬም ኢትዮጵያ የሚኖሩ ነው የሚመስላቸው። የእንግሊዝ ፓስፖርት ይዘው፣ በኢትዮጵያ ሕገ-አራዊት ሊያስተዳድሩን ነው የሚመኙት! ጊዜው በገፋ ቁጥር፣ ወደ አዕምሮአቸው የተመለሰላቸው አብረዋቸው የነበሩት ሰዎች ምንም የማያዋጣ አዘቅት ውስጥ ገብተው እንደሚዳክሩ ስለገባቸው፣ አንድ በአንድ ጥለዋቸው ሂደዋል። የቀሩት በሙሉ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ወያኔ የደኅንነት አባላት፣ ቀጥሎ፣ አሽቃባጮቻቸው፣ ከዚያም አሸሻ ገዳሜን እንጂ ምንም የማያውቁትን በጣት የሚቆጥሩ ወጣቶች ነው። አሁን ትግሉ፣ እነሱ በፊት ሊያስቀምጡት እንደሞከሩት፣ ቤተክርስቲያኗን ኮምፓኒ የማድረግና ያለማድረግ ሳይሆን፣ ቤተክርስቲያኗን ለወያኔ ከማስረከብና ካለማስረከብ ሁኗል። “ሕጋዊ ሲኖዶስ!” የሚሉት ነገር አላቸው። ደንቄም! ወያኔ እንደፈለገው የሚያሽከረክረው፣ የአዲስ አበባውን ማለታቸው ነው። እነዚህ አሁን “አለንልህ” የሚሏቸው ጳጳሳት፣ ከአባ ተባዩ ጀርባ የሚሏቸውን ቢሰሙ፣ በጠላቶቻቸው መከበባቸውን ማን በነገራቸው! አንዱ የተከበሩ አቡን፣ “አይ ግርማን ተወው! ለዚህ ያደረሰን እሱ መሆኑን መች አጣነው! ብቻ መጀመሪያ ቤቱን እንረከብና፣ እሱን የምናደረግውን እኛ እናውቃለን” ሲሉ ተደምጠዋል። በሬ ካራጁ ጋር ይውላል አይደል የሚባለው!
የአሁኑ የአባ ተባዩ እንቅስቃሴ የሞት የሽረት መሆኑን ሕዝቡ ተረድቷል። በሕግ ሳይሆን በጉልበት ለመውሰድ የተነሱ ቀማኛ መሆናቸውን አውቆ ሕዝቡ ቅዳሜ በማለዳ ቤተክርስቲያኑን ለመከላከል ሄደ።  ከዝግጅቱ መሀል አንዱ፣ እኛ ዘለን እንዳናልፍ ተከራይተው ያመጡት መክላከያ መሰናክል (barrier) የኛ ልጆች፣ ሄደው በሰንሰለት ግጥም አድረገው ቀስረው ቆልፈውላቸው ስለነበር፣ የአባ ተባዩ ደንገጡሮች ሊያንቀሳቅሱት አልቻሉም። ሌላ ልፋትና ኪሳራ!!! እነሱው የቆለፉትን የመግቢያ በር ሰንሰለት ፖሊስ “ከሕግ ውጭ ነው” በማለት ቆርጠው ቆራርጠው ጣሉላቸው! እዚያ ቤት ዕውር እውሩን እየመራ ገደል ተጎታትተው እየገቡ ነው። ኤድያ! ኪሳራ በኪሳራ! ገና ምን አይታችሁ! እግዚአብሔር የመጨረሻቸውን ያሳየናል። የግቢው በር በዚህ አኳኋን ሲከፈትለት፣ ሕዝቡ ግር ብሎ ገባ። ይኸኔ የአባ ተባዩ ዓይን ፍጥጥ ጥርስ ግጥጥ አለች! በሰው ብዛት አጠፍናቸው። ከገብሬኤል (ለትግሬዎች ተለይቶ የተደራጀ)፣ ከሥላሴ (ትግሬ ላልሆኑ ወዶ ገቦች በመፍቅረ ጳውሎሱ አባ ሙሴ ተመሥርቶ፣ በአባ እንጦስ የተደረጀ) ጸርሀ ጽዮን (ጃማይካ) ቤተክርስቲያኖች አባላት እስኪደርሱላቸው ድረስ ያን ሁሉ ሕዝብ ምንም ማድረግ ስለማይችሉ፣ እንደተተኰሰባት ድኵላ ደንግጠው፣ ጥግ ጥጋቸውን ይዘው ቆሙ። ሕዝብ ተመመ። መዝሙር ተዘመረ። አባ ተባዩ ፓሊሶችን አግባብተው ከጎናቸው ለማሰለፍ ሞከሩ። እኛን ወንጀለኞች ለማስመሰል፣ እንሱ ጨዋዎችን ለመምሰል ሞከሩ። ፓሊስ ያመናጭቀን ያስፈራራን ገባ! “እሱን ዲሲ” ነበር ያለችው ሴትዮዋ! በስደት ኖሮአችን እስከምን ፖሊሶቹን ልንጋፋ እንደምንችል ጠንቅቀን እናውቃለን። አባ ተባዩ ቪካሬጅ (ሕልፊኝ በሉት) ሲገቡ ሕዝቡ ተከትሎ ሊገባ ሞከረ። ፖሊስ ተሟሙቶ አገደን። ፖሊስ ከዚያ ውጡ እያለ ያዘናል።እኛ ደግሞ ያ ቤተክርስቲያናችን ነው የተም ንቅንቅ አንልም ብለን ተጋተርን። አባ ተባዩ ቀማኛ መነኵሴና እና ተከታዮቹ ከዚያ ሲወጡ እኛም ትዕዛዙን አክብረን እንደምንወጣ እቅጩን ነገርናቸው።
አባ ተባዩ እራሳቸው መጥተው በሩን መክፈት ፈርተው ይመስላል፤ ፖሊስ መግቢያ በሩን ሊቆጣጠርና ከፍቶ ጳጳሳቱን ሊያስገባ ተጠጋ። ነገሩ ገባን። ክርስቲያን እህቶቻችን ከዚህ በፊት አይቼው በማላውቅ ጀግንነት ግልገሏን ከነጣቂ ጅብ ልተከላከል እንደምትወረወር አራስ ነብር ተንደርድረው በሩ ላይ ተረባረቡ። ፖሊስ ቢጋፋ ቢያሽቀነጥር፣ ቢጮህ፣ ኃይል ቢጠቀም ምን ቢል እህቶቻችንን አልቻለም። የእህቶቻችንን ጀግንነት ያየን ወንዶች ዘለን ገባንላቸው። መሬት ላይ ቁጭ አልን። ፖሊስ እየተግተለተለ ቢመጣ፣ ወይ ፍንክች የአባ ብለዋ ልጅ! የእግዚአብሔር ኃይል ተጨምሮልን በምን ሊቋቋሙን! ኃይል የእግዚአብሔር ነው! የአባ ተባዩ ደንገጡሮች፣ ፖሊሶች እያነቁ ይወስዱናል ብሎ ከመመኘት በስተቀር፣ ምንም ማድረግ አልቻሉም! በእግዚአብሔር ኃይል ሁሉንም ቻልነው። ፓሊሶቹን በጥሞና አነጋገርናቸው። ያቺን ቤተክርስቲያን አባ ተባዩ በአቀዷት መሠረት ላትከፈት፣ ሕግ ሳንተላለፍ በሕይወታችን የቆረጥን መሆናችንን ሲገነዘቡ፣ “በቃ! በቃ! ቤተክርስቲያኗ በምንም ዓይነት በዚህ ሁኔታ ዛሬ አትከፈትም” ብለው ወሰኑ። “እናንተ ብቻ ሂዱልን” አሉን። እኛ የምንሄደው፣ አባ ተባዩ እራሳቸው፣ ከሥላሴ፣ ከገብርኤል፣ ከጸርአ ጽዮን (የጀመይካዎቹ) ቤተክርስቲያናት የወረሩን ወያኔና የወያኔ ወኪሎች፣ እና የአባ ተባዩ ደንገጡሮች እንዳሉ ካልወጡ አንሂድም አልን። አባ ተባዩ ወጥተው የሚሂዱት፣ “እናንተ ስትወጡ ነው” ተባልን።
በዚህ ክርክር ላይ አንዳለን አንድ ነገር ተከሰተ። ዞር ብለን ስናይ አባ ተባዩ ጠረንገሎ ጠረንገሎ የመሰሉ የደኅንነት ጥበቃ ዘበኞችን በሺህ የሚቆጠር ፓውንድ ከፍለው፣ ቀጥረው አምጥተው አገኘናቸው። ጉድ! ጉድ! “ጉድና ጅራት”  ከበስተኋል ነው የሚባለው? ዞር ብለን ስናያቸው፣ ሰዎች ሳይሆን ጉማሬ ጉማሬዎች ይመስል የሚንጎማለሉ መሰሉን። አንዳንዶቻችን “እነዚህ ወጠምሾች ቅዱስ ሚካሄል፣ ቅዱስ ገብሬል፣ ቅዱስ ሩፋኤል ወይስ ሌሎች ከአደጋ የሚከላከሉ መለዕክት ይሁኑ?” ስንል፣ በስላቅ ለጠየቅነው ጠያቄ፣ ሌሎች “አይ መላዕክት አይመስሉም፣ ክንፍ የላቸውም” ብለው ቀለዱባቸው! በአማርኛ ስለምናወራ፣ ፖሊስ ሳቃችን አልገባብውም። አባ ተባዩ፣ ዞሮባቸዋል ማለት ነው። ጡንቻው ያበጠ፣ ልቡ ያበጠበት የእግዚአብሔርን ልጆች አ-ያ-ሸ-ን-ፍ-ም! ኩርርርር!!!! አይሰሙም እንዴ! አሁን በሞቴ፣ እስከ አፍጢሙ የታጠቀ ፖሊስ ያልቻለንን እነዚህ ወጠምሾች ይችሉናል ብለው ነው፣ ገንዘባቸውን ያባከኑት? ከኛ ጋ የቆመው ከእነሱ ጋ ከቆመው የበለጠ ኃይለኛ አምላክ ነው (1ኛው የዮሐንስ መልዕክት፣ ም4 ቁ4)። ተጨማሪ ኪሳራ! ቀድሞውን መቸ በእግዚአብሔር መላዕክት ይመኩና። እሳቸው የሚመኩት፣ አይዘዎት በሚለው የወያኔ እምባሲ፣ እፍኝ በማይሞሉ ደንገጡሮቻቸውና ገና ተበልቶ ባላለቀው የጉርምስና ጉልበታቸው ነው። ውርደታቸውም እሱ ነው። አዙሮ አለማየት! ሰው መናቅ! ኢትዮጵያ ውስጥ ብንሆን እኚህ ሰውዬ በመትረየስ አስረሽነው ጨርሰውን ነበር። አሁንስ ቢሆን ጠብ ያለሽ በዳቦ በሚሉ፣ ምንም ዓይነት የክርስትና ጸባይ በማይታይባቸው ወጣቶች ካሰደቡን፣ ካስደበደቡን ምን ቀራቸው? እግዚአብሔር ብቻ እኚህን ከራስፑቲን የባሱ አመጸኛ ሰው ይገላግለን። የሰው ፍርድ ዋጋ የለውም!
ከፖሊስ ጋ ስንጋፈጥ ብዙ ብዙ ነገሮች ተፈጥረዋል። ወንድማችን አሥራት ይግለጡ በአንድ የወያኔ ቅጥረኛ ተመታ!። በኋላ ላይ እመጣበታለሁ። ፖሊሶች “ውጡ እያሉ” ሲገፈታትሩን፣  “ቢያንስ ቢያንስ እነዚያ ከሌላ ቦታ የወረሩን እና ደንገጦሩቹ ይውጡ ብለን” ለመብታችን ተሟገትን። አሁንም ፖሊስ በዘዴም ቢሆን አታሎ ከግቢው ሊያስወጣን ስላልቻለ፣ የአባ ተባዩን ጦር ከነወያኔ ወኪሎቻቸው ጋር ሲያስወጣ እኛም ሕግ አክብረን ከግቢው ወጣንላቸው። ወደ ቤት እንድንሄድ ፖሊስ ያላደረገው ጥረት አልነበርም። የማይቻል መሆኑን ነገርነው። አባ ተባዩ እንደኪራይ ቤት ውልቅ ብለው ጥርግ ሲሉ በዓይናችን ካላየን ላንነቃነቅ ዕቅጩን ነገርናቸው።
ቅዳሜ ዕለት፣ ያንን ሁሉ ተጋድሎ አድርገን፣ ከመውጣታችን በፊት፣ ለትውልድ የሚተላለፍ፣ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ናቸው፣ ኢትዮጵያዊነት ጨዋነት የማይታይባቸው ወንጀለኞች የሠሩትን እዚህ መመዝግብና ማስተላለፍ አስፈላጊ ነው። አዲስ አባባ ላይ፣ ወጣቶች ተደራጅተው፣ ወያኔን ይጋፈጣሉ። ይታሰራሉ፣ ይወድቃሉ ይነሳሉ። የአዲስ አበባ ወጣቶች፣ የሕዝብ ደጀን፣ የሕዝብ ተከላካዮች ናቸው። ወያኔ አግዓዚ የተባለውን ጦር፣ ወይ ፌዴራል ፖሊስ የተባልውን ኃይል ተጠቅሞ ሕዝባችንን ሲጨፈጭፍ፣ የመጀመሪያ ገፈቱን ቀማሾች፣ የአዲስ አበባ ልጆች ናቸው። ዛሬ ጎጃምና ጎንደርም ያሉ ወጣቶች፣ወያኔን ለመጋፈጥ፣ የአማራ ወጣቶች መከላከያ ኃይል ፈጥረው በረሀ ገብተው በመፋለም ላይ ናቸው። በኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶቻችን ወያኔን እየተጋፈጡ ታሪክ ሰርተው በማለፍ ላይ ናቸው! ለንደን ያሉ በጣት የሚቆጠሩ ወጣቶች ግን ኢትዮጵያን የሚወዱትን ሰዎች እየተተናኮሉ ይገኛሉ።
በአሁኑ ጊዜ ቱባ፣ ቱባ የወያኔ ባለሥልጣናት መቀሌ ሳይሆን ቨርጂኒያና ዋሽንግተን ለመመካከር ተሰብስበዋል። እዚያም ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እየተጋፈጧቸው ነው።  ጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድ ነፍሰ ገዳዩን ወያኔ ስብሐት ነጋን ስታርባክስ ቁጭ ብሎ በነጻነት ቡና ሲጠጣ አግኝቶት ተጋፍጦታል[2]። መስፍን የተባለ ሌላ ኢትዮጵያዊ፣ ቨርጂኒያ ውስጥ ስብሀትን አግኝቶ ሲጋፈጠው[3]፣ ከስብሀት ጋር የነበረ ሌላ ወያኔ፣ መስፍንን መትቶት ሲያመልጥ ሁለት መኪናዎች ገጭቶ በማምለጡ ይኽ ጽሑፍ ሲጻፍ ፖሊሶች ለመያዝ እያሳደዱት ነው። ሌላ ቦታ ያሉት የኢትዮጵያ ወጣቶች እንዲህ ታሪክ እየሰሩ ነው። በተለይ ኖርዌይ ያሉት ወንድሞቼ ሁሌ ያኮሩኛል! ለንደን ግን ታሪኩ በሌላ ተቀይሯል። እናንተ ከወያኔ ጎን የቆማችሁ ወጣቶች! ለንደንን አታሰድቡ። ብትሞቱ ይሻላችኋል!
አብዛኞቹ ወጣቶች፣ ልክ አዲስ አበባ እንደሚደረገው ከወያኔ ነጣቂዎች ጋር አንገት ለአንገት ተያይዘው፣ ከሕዝቡ ጎን ተሰልፈው መስዋዕትነት እየከፍሉ ነው። ከ20 እስከ ሰላሳ የሚደርሱ ወጣቶች ግን አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ወያኔ ጎን ተሰልፈው ይኸ ነው የማይባል ግፍ በወገኖቻቸው ላይ እያደረሱ ይገኛሉ። በእሑዱና በቅደሜው ትንቅንቅ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱብን የቻሉት እነዚህ ከ20 እስከ 30 የሚደርሱ የወያኔ ቅልብ ወጣቶች ናቸው። ከዚህ በፊት፣ ከሀዲውን አስመሳይ መነኩሴ በቃል ከማጋለጥ አልፈን በእንቁላል እስከመደብደብ ደርሰን ነበር። ግቢውንም እንዳይገቡ ያገትንበት ጊዜ ነበር። እነዚህን ወጣቶች በምን እንደመረዟቸው ሳናውቅ አምጥተው ሲያፈሱብን፣ ከነሱ ጋር ስንተናነቅ ፖሊስ ልቅም አድርጎ ዘብጥያ እንዳያወርዳቸው በመሳሳት፣ ወይ ወደ አገር ቤት አንቆ እንዳይመልሳቸው በመስጋት፣ ወገናዊነት አስገድዶን፣ ተመካክረን እነሱን የሚቀሰቅስ ምንም እርምጃ ላለመውሰድ፣ ብዙ ወንድሞችና እህቶች እየተቃወሙን አካሄዳችንን አለስልሰን ሕጉን ብቻ ተከትለን ነበር። “ፈሩን” ብለው ጨፈሩ! ይሁን አልን። የልብ ልብ ተሰማቸው። መስማት አይፈልጉም። ዘፈናቸው አንድ ናት። አባቶችን አዋረዳችሁ፣ ቤተክርስቲያን ደፈራችሁ እያሉ መንተክተክ ነው። እራሳቸውን እንጂ ሌላውን አይሰሙም። ታገስናቸው፣ ታገስናቸው፣ ታገስናቸው። በውስጣቸው ያሉ ወያኔዎች አየሉ።
እዚህ ፎቶግራም ላይ የተነሱት፣ “ለአስመሳዩ መነኩሴ አባታቸው” ለመሞት የማሉ ናቸው። ይኸን ፎቶ ለማስታወሻ ተነስተው በፌስ ቡክ የለጠፉት ለኔ መልዕክት ለማስተላለፍ ነበር። መለዕክቱ ደርሶኛል፣ አመሰግናቸዋለሁ። እሲቲ ይኸን ፎቶግራም ራስፑቲን ከተባለው የአባ ተባዩ ብጤ ሀሳዊ መነኵሴ ከአሻቃባጮቹ ጋር ከተነሳው ጋር እናወዳድር። ከጊዜው መራራቅ በስተቀር ምን ልዩነት አለው? እነዚህን ወጣቶች የሚሠሩት በደል የሚያስጠይቃቸው ነው፣ እያልን ለማስረዳትም ብንሞክር፣ “እናንተ ፖሊቲከኞች ናችሁ፣ ደርግ ናችሁ፣ ግንቦት 7 ናችሁ፣ አንድነት ናችሁ …” እያሉ ወያኒኛ እየተናገሩ፣ ሊያዳምጡን አልፈለጉም። ተውናቸው። ከዓርብ ማታ ቅዳሜና እሑድ ያደረሱት ጉዳት ግን በምንም ዓይነት ይቅር የማይባልላቸው፣ በየትኛው መድረክ ልንፋረዳቸው የሚገባን በደል ፈጽመውብናል።
በለንደን ውስጥ ላለፉት ብዙ ዓመታት በቆራጥነት ወያኔን መጋፈጣችን ይታወሳል። በነዚህ ጊዜያት በሙሉ አንድ በዓለም ድምጹን ያላስተጋባንለት ግንባር ቀደም ሁኖ ትግሉን ከማገዝ አልፎ እስከመምራት የደረሰ አሥራት የሚባል መመኪያ ወንድም አለን። አሥራት ጤንነቱ የተሟላለት አይደለም። ለመራመድ እንኳን በምርኩዝ ተደግፎ በግድ ነው የሚንቀሳቀው። ዳሩ ግን ማናችንም ጤንነታችን የተሟላልን የአሥራትን ያህል ለዚህ ትግል አስተዋጽኦ አላደረግንም። ደፍሮ “እኔ ከአሥራት በላይ አድርጌአለሁ” የሚልም ከኔ ጀምሮ አይኖርም። የትግላችን ሞተርና አንቀሳቃሽ እሱ በመሆኑ፣ አንዳንዴ ሕመሙን ጨርሶ እንረሳለን። እንዲያው አንባቢዎቼ ፍቀዱልኝና፣ ስለዚህ ጀግና በሕይወቱ እያለ ትንሽ ልበል። ይቅርታ አሥራቴ!
አሥራት ልዩ የኢትዮጵያ ልጅ ነው። ገና በወጣትነቱ ጀምሮ በረሀ ገብቶ ደርግን የተፋለመ ጀግና ነው። ከዕውቁ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ምሑር፣ ከነዶር ጌታቸው በጋሻ ጋር ሁኖ ለወገኑ መብት ደሙን አፍስሷል። የኢትዮጵያ ጉዳይ እስከዛሬ የሚያንሰፈስፈው ጀግና ነው። አሁን እንኳን ጤንነቱ እንደዚያ ተቃውሶበት፣ አንዲት ቀን ሳያርፍ፣ ባለችው መኪና የቤንዚን እንኳን ሳንከፍልለት የትግል መኪና አድርጓት፣ ሰላማዊ ሰልፍ ስናደርግ እንደልባችን የምናዘው ዕቃ አመላላሽ፣ እንግዳ ሲመጣብን አድራሽ፣ እኛ ስንዘናጋ፣ አስተዋሽ፣ ስንሰንፍ ቀስቃሽ፣ ወደ አውሮፓ ከተሞች ለሰልፍ ወይም ልስብሰባ ከተነሳን፣ በመኪናው የቻለውን ጭኖ አድርሶ መላሽ፣ ከጠዋት እስከማታ ለኢትዮጵያ ጉዳይ እንደባከነ ነው የኖረው። ዝግጅቶች ሁሉ ላይ አሥራት የሌለበት አልነበረም፣ የለም፣ አይኖርም። በዚህ አንቱ በሚባልበት ዕድሜው እንደ ልጅ ነው የሚታዘዘን። ኢትዮጵያዊ የተባለ ስብሰባ ላይ አንድም ቀን ሳይቀር፣ በጣም ጠቃሚ ሀሳቦችን እያፈለቀ እየመራንና እየመከረን የሎንደንን ትግል አንዲት ቀን እንዳትቋረጥ የረዳን፣ ሳይማረርብን እዚህ ያደረሰን ወንድም ነው። አንድም ቀን እንኳን እኛ ስንበላ ስንጠጣ አብሮን ቁጭ ብሎ ተዝናንቶ አያውቅም። ሁሌ ሥራ ነው። ድፍን ለንደን ኢትዮጵያው (ሲቀነስ ወያኔና ጀሌአቸው) የሚኮራበት ወንድም ነው። እነዚህ ወያኔዎች የዘረገፈብን ሰላዮቹና የጠለፏቸው የዋሆች አድብተው አድብተው ጠብቀው ቅዳሜ ዕለት ምርኵዙን ተደግፎ ከቆመበት ሳያስበው ዓይናችን እያየ እግሩን ከሥር በኃይል ሲመቱት ወደቀ እና እራሱን ተመታ። መቺው ጨካኝ አረመኔ ከደጊቱ ምድር ከትግራይ የተገኘ ወጣት ነው። እኛ ተደናግጠን ወንድማችንን ለማንሳት እየተሯሯጥን ስንጯጮኽ፣ ልክ አንበሳ ታግለው እንደጣሉ (ዕውነቱን እንናገር ከተባለ፣ አሥራት የአንበሳም አንበሳ ነው) ዙሪያውን ከበው በሳቅ ሲያሽካኩ ስናያቸው፣ ፖሊስ በቦታው ባይኖርና እየገፈታተረ ባያቆመን አንድ በአንድ ጎሮሮ ለጎሮሮ በተናነቅን ነበር። እነሱ እያፌዙ፣ እኛም አንጀታችንን እያረረ ዝም አልናቸው። አሥራት ሆስፒታል ተወስዶ ከሁለት ቀን ሕክምና በኋላ ተርፎልናል።
ይኸ ሁሉ ሆኖ ከግቢው ለመውጣት የተስማማነው፣ ፖሊስ አባ ተባዩን ጨካኝ ሰው  እንደሚያስወጣ ቃል ገብተውልን ነበር። ዳሩ ምን ይሆናል ፖሊሶች ቃላቸውን አጠፉ። ብንጠብቅ፣ ብንጠብቅ፣ ብንጠብቅ አልወጡም። የባሰውኑ፣ በጓሮ በር አቡነ ገብርኤልን፣ አቡነ እንጦስን፣ አቡነ ያዕቆብን፣ ተወልደ ወልደማርያም የተባለውን የወያኔ የአውሮፓ የሀይማኖት ሹም አስገብተው እርፍ አሉ! በወያኔ መከበባችን አወቅን። ልንሄድ የነበርን በሙሉ ተመልሰን ፍጥጫው ቀጠለ። ከግቢ ውጪ ሁለቱም ቡድን ቁመናል። ቀሚስ በማስረዘማቸው፣ ፖሊስ አከበራቸው መሰለኝ፣ ወጥተን ቡራኬ ሰጥተን እንሂድ አሉ ተባልን። አብዛኛው “አንፈልጋቸውም። ከነሱ የሚመጣ ቡራኬ በአፍንጫችን ይውጣ። በመጡበት አኳኋን ይመለሱ” ስንል፣ ከየወያኔ ቤተክርስቲያናት የመጡ በአንደኛው ወገን የቆሙ የወያኔ አገልጋዮች እና የተገዙ የአባ ተባዩ ደንገጦሮች፣ አባቶቻቸው፣ ፓብልኪ በሆነው ሥፍራ ቁመው ቡራኬ እንዲሰጧቸው፣ የመናገርና የመስማት መብታቸው እንዲከበር ጠይቁ። የፈረደበት ፖሊስ ሆዬ፣ እነሱን አስገብቶ እኛን ውጪ አስቀረን። በሚያስገርም ፍጥነት ያኔ በሙሉ እንዳለን ዋናው መንገድ ላይ ወጥተን ተነጥፈን። ትራፊክ ቆመ። የለንደኗ በተርሲ መንደር ቀውጢ ሆነች። ቢቢሲ ሬዲዮ፣ የአካባቢው ሬዲዮ በዚያ አትለፉ የሚል መልዕክት ከዳር እስከዳር አስተጋባ። ፖሊስ በገዛ እጁ ጭንቀት ውስጥ ገባ። ምድር ተናወጠች። ፖሊስ እኛን ለማንሳት ያ ሁሉ ኃይላቸው ባለመቻሉ በሩን ከፍተው ወደግቢ እንድንገባ ልመና ገቡ። መጨረሻ ላይ ተነስተን ገብተን ልንቀላቀላቸውና ጉዳቸውን ልናፈላ ስንሄድ ፖሊስ ግድግዳ ሠርቶ ጳጳሳት ተብዬዎቹ ጋ እንዳንደርስ ከዓይን ሰወር ባለ ቦታ ቁመው እርኩሶቻቸውን እንዲባርኩ ተደረጉ። ፓሊሶችን ገፍቶ ማለፍ ሕግ መተላለፍ ስለሆነ ቁመን ጮኸታችንን አቀለጥነው። “ሌባ ሌባ” በጩኸት ቦታውን ስናናውጠው፣ አንዲት እህት ከመካከላችን ድምጿን ከፍ አድርጋ ሕዝቡን “እንዴ ነውር ነው። ትክክል አይደላችሁም”። ምንም ቢሆን አባቶች ናቸውና ሌቦች አትበሏቸው” አለች። ታዲያ ምን እንበላቸው ብለን መልሰን ስንጮኽባት፣ አሁንም ድምጿን ከፍ አድርጋ “መነኮሳት አባቶች! ሂዱና ልጆቻችሁን አሳድጉ!” እየለች መጮኽ ጀመረች። ተቀብለን አስተጋባን። ግማሾቻችን ግን ሆዳችንን ይዘን ሳቃችንን አቀለጥነው። የነሱ ቡራኬ የኛን ድምጽ አልፎ አልተሰማም። ቡራኬ አትበሉት! የድፍረታቸው ድፍረት፣ የእግዛብሔርን የሕዝብ ጥያቄ የመናቃቸው ድርጊት፣ ለውርደት ዳረጋቸው። ወደመጡበት ተመለሱ! ቅዳሜ በዚህ ዓይነት ኢትዮጵያዊ ቆራጥነትና ጀግንነት አለፈ። ነገም እኛው ነን። በእግዚአብሔር ኃይል እንደግመዋለን!
ድንገት በነጋታው ተጨማሪ ውርድት ለመከናነብ ሽተው አሁንም “እንክፈት” ብለው ይሞክሩ እንደሆን በማሰብ እሑድ ዕለት ሕዝቡ ከቅዳሜው ሁለት እጥፍ ግልብጥ ብሎ ቤተክርስቲያን ከቸች አለ። የግቢውን በር ፖሊሶች ዘግተውት ጠበቁ። የአባ ተባዩ ልጆች (30 ገደማ ቢሞሉ ነው)፣ የዓይናውጣው መነኵሴ ነኝ ባይ የቅሌት ዘበኛ ሁነው ጠበቁን። ስላሴም፥ ገብርኤልም፣ ጸርአ ጽዮንም ተስፋ ቆርጠው ዝር አላሏትም። ሕዝቡም ጋጠወጦቹም ወደ ግቢው ገብተው እነሱም የድሮዋን ኮርነራቸውን ይዘው፣ ሕዝቡም ከፊለፊት ሰፈው ሚዳ ላይ ተንጣሎ፣ ዝናም ዶፉን እያወረደ ያለምንም ግርግር እንዲጸልይ ከፖሊሶቹ ጋር ተደራደሩ። ፖሊስም ነገሩን አውጥተው፣ አውርደው፣ በቂ ዝግጅት አድርገው፣ በኛም በኩል ያሉት ካህናት ገብተው፣ አባ ተባዩና አፍቅሪ ወያኔ ካኅናት ገብተው የየግል ጸሎት አለቀ። በተገባው ቃል መሠረት፣ ጸሎቱ አልቆ ሕዝቡ በሰላም ከግቢው መውጣት ጀመረ። ፖሊስ የኛ ወገን ብዛት እና ቆራጥ የትግል ዘዴአችን ስላሳሰበው፣ በኛ ላይ ብቻ ነበር ትኩረቱ። የአባ ተባዩን ውሪዎች ከምንም አልቆጠራቸውም።
እንሱ ግን እኩይ ዕቅድ ነበራቸው። እነዚያው አሳፋሪ በጣት የሚቆጠሩ ወጣቶች ተብዬዎች ሳይታሰብ ዘለው ከሕዝቡ መሃል አንዳንድ ሰው ላይ ሠፈሩ! በዚህ አጋጣሚ፣ ወንድማችንን፣ ገጣሚና ጸረ-ወያኔ አክቲቪስቱን፣ ጌታቸው ሙላቱን (የአያልነህ ሙላት ታናሽ ወንድም – አንዳንድ ግጥሞቹን በራሱ ፌስ ቡክ የግል ድረ-ገጽhttps://www.facebook.com/Getachewmulatu?hc_location=stream ማየት የቻላል) ሳያስበው፣ ማንኛውም ማጅራት መቺ  እንደሚያደርገው አሸምቀው ፊቱን ባልታወቀ ነገር መትተውት ደሙን አፈሰሱት። በፊቱኑ ዕቅደ አውጥተው ኑሮ፣ የተወሰኑት ሆን ብለው ግብግብ ሲፈጥሩ ፖሊሶቹ ወደአንድ አቅጣጫ ሲመለከቱ፣ ሊሎቹ የዚህን ትግል መሪዎች ናቸው የሚሏቸውን ለማጥቃት መንቀሳቀስ ጀመሩ። አንድ የትግሉን ዋና መሪ አዛውንትን ሰባት ሆነው ከበቧቸው። እቅዳቸው አዛውንቶችን እግር እግራቸውን መውጋት እንደሆነ አውቀነው ስለነበር ለአንዳንድ ሰዎች አስጠንቅቀን ነበር። አዛውንቱ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተከላከሉ። አንደኛው እንደምንም በዕቅዳቸው መሠረት እግራቸውን ለመምታት ሞከረ። እሳቸው ግን በሚያስደንቅ አኳኋን የተሰነዘረባቸውን ሲመክቱ፣ አንዱ እሳቸውን እመታለሁ ብሎ የሰነዘረው ኃይለኛ ምት፣ ጓደኛውን አጉኖት ሰማይ አድርሶት አፈረጠው። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሊደርስላቸው ቢሞክር ፓሊስ ገትሮ ያዘው። ግን እየጮኹ ወደ ተከበቡት አዛውንት ሲያመለክት፣ አንድ ጎበዝ ፖሊስ ዘሎ ገብቶ አዛውንቱን ከመሀል ጎትቶ አወጣቸውና እነዚያን ሲምቢሮ-ሲምቢሮ የመሳሰሉ ጨበሬውችን በታተናቸው። ፖሊስ ታክቲካቸው ገብቶት እኛን በዓይነ ቆራኛ እያየን እነሱ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ አተኮረ። ይኸኔ ነበር ዕቅዳቸው መክሸፉን ሲያቁ ውሪዎቹ ያበዱት። ሕዝቡና እነሱ መሀል ፖሊሶች አሉ፡፤ ድብድቡ አልተሳካላቸውም። እንዳበዱ ውሾች ጮኹ። ፖሊሶቹ ላይ ጉልበታቸውን ሊሞክሩ ወሰኑ። አንዱ ዱሩዬ ሙት ሲለው ዘሎ አንዱን ፖሊስ ረገጠው። ይኸኔ እልሁ ያለቀ ፖሊስ አንስቶት መሬት ላይ ፈጠፈጠው። ስድስት ገደማ ሁነው እንደቅሪላ ቀጠቀጡት! እራሱን በጉልበታቸው ከምድር አጣበቁትና በካቴና አሰሩት። ከትግራይ ሰልጥኖ የመጣው የወያኔ ቅጥረኛ የመጀመሪያ የፖሊስ ሰለባ ሆነ። መነሳትም አልቻለም። በካቴና ጠፍረው ወዲያ ሲወስዱት፣ ሌሎቹ አብሾ እንደጠጣ ወይም ዕጸ ፋርስ አጢሶ አንዳበደ ፌንጣ መዝለል ጀምሩ። ፖሊሶቹ ሊያስትግሷቸው ቢሞክሩ፣ እኛ ባፈለው ቀን ጥያቄአችንን ለማስከበር የተጠቀምነውን ታክቲክ ኮርጀው፣ ያለምንም ምክንያት መንገድ ላይ ተኙ። አንደኛ በቁጥር በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። ፖሊስ እያንዳንዷን ድመት ግልገሏን በአንገት ቆዳ አንጠልጥላ እንደምትሄድ አንጠልጥለው ሊወስዷቸው ይችላሉ። ሁለተኛ የሚያቀርቡት ጥያቄ አልነበረም። ሶስተኛ መንገዱን ፖሊስ ቀድሞውኑ ዘግቶት ስለነበረ፣ መንገድ አስዘግተው ቀውጢ መፍጠር የሚችሉበት ሁኔታ አልነበረም። እያንዳንዷን ፌንጣ ፖሊስ በአንገት እያንጠለጠለ አነሳ። ያ ሁሉ ሲሆን፣ አባ ተባዩና አንድ የቀሰሰ ሰይጣን ጉዳቸውን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ከሩቅ ይቀርጹ ነበር። እንግዲህ፣ እነዚህን ጅሎች፣ በሚመጣው እሁድ ሲሰበሰቡ፣ አባ ተባዩ “እናንተ ሰማዕታት ናችሁ” ብለው ለመስበክ አርዕስት አገኙ። ለሌላ ዙር አመጽ እንዲዘጋጁ ለመቀስቀስ ቪዲዮውን ይጠቀሙበት ይሆናል። ተመልከቱልንማ! ዕውነተኛ መንኵሴ በሱ ምክንያት አንዲት ነፍስ እንዳትወድቅ፣ ሱባኤ ይገባል። አንድ ሰው እንዳይጎዳ ጥንቃቄ ያደርጋል። ካልሆነ፣ እያለቀሰ፣ አምላኩን ይቅርታ እየለመነ ወደ ወደ ገዳሙ ይመለሳል። የኛ የለንደኑ የቀበሮ ባህታዊ ግን፣ “በሉ! ተሟሟሙት! በርቱ!” እያለ ምንም የማያውቁትን እምቦቅቅላ ወጣቶችን ለመስዋትነት ያዘጋጃል! ኧረ የትኛው ገዳም ነው እንዲህ ዓይነቱን አጭበርባሪ፣ ግብረ አልባ ሰው ሳይበቃ ያመነኰሰ? መነኵሴ እንዲህ ነው እንዴ! አሁንም ቢሆን፣ የወያኔ ምልምሎቹ ሰላዮች፣ ከአንዱ በስተቀር ሌሎቹን አጋፍጠው ሹልክ ብለው አምለጠዋል።
ፖሊስ በዚህ አኳኋን ሁኔታዎቹን በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ፣ ሕዝቡ ወደየመጣበት ተመለሰ። ዕለቱ የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ቡድን ከናይጄሪያ ጋር የሚጋጠምበት ዕለት ስለነበረ፣ አለባቸው ደሳለኝ የሚባል የወጣለት ፎቶ ጆርናሊስትና አንድ ቁጥር የወያኔ ተፋላሚ እና የኢትዮጵያ ቅርስ ሰብሳቢ ወንድማችን፣ ሁኔታውን በተርሲ ለታሪክ ሲቀርጽ ውሎ፣ ከጓደኞቹ ጋር ጨዋታውን ለመከታተል ማራቶን ሬስቶራንት ሄደ። እነዚያ መሠርይ የወያኔ ቅጥረኞች ተከታተሉት። እንግዶቹ ምሳ አዘው እንደተቀመጡ፣ ጋጠ ወጦቹ ተከታትለው ገብተው፣ አለባቸውን ተጋፈጡት። እየሰደቡት ለመማታት ሲጋበዙ፣ ምን እንደሚፈልጉ ጠየቃቸው። ቪዲዮ አንስቶአቸው የለጠፈውን ከድረ-ገጽ እንዲያነሳ ነገሩት። ከይትኛው ድረ-ገጽ ነው ብሎ ቢጠይቃቸው፣ መልስ አጡ እና ወደ ተራ ስድብ ወረዱ። ይኸኔ የሬስቶራንቱ በለቤት መጥቶ በጥሞና ደንበኞቹን እንዳይረብሹ ለመናቸው። ወደሱ ዙረው፣ እሱም ተባባሪ በመሆኑ እንደሚዞሩበት ሲጮኹበት ትቶአቸው ወደ ውስጥ ገብቶ ፖሊስ መጥራት ጀመረ። እነሱም ምግብ ቤቱን ለቀው እየወጡ ሳለ፣ የበሩን መስታወት በብረት ቦክስ ቡጢ ሰበሩት። ፖሊስ መጥቶ ብዙም ሳይርቁ ሶስቱን ሌጊዜው ማገት ቻለ። የዚህ ሁሉ ድራማ video፣ ዓርብ ኦክቶበር 18 ይለቀቃል። ልጆቹንም ዓለም ያያቸዋል። ልጆቻችሁ ብቻ እንዳይሆኑ ኢትዮጵያ የምትኖሩ አንባቢዎቼ፣ አጥብቃችሁ ጸልዩ!
የተቀሩት ጥቂት ዱሩዬዎች የሄዱት፣ በቀጥታ ወደአዲስ አበባ ሬስቶራንት እንደነበረና፣ ባለቤቱን ለመተናኰል እንደሞከሩ መረጃ ደርሶናል። ኧረ ምን ዓይነቶቹ ጉዶች ናቸው?
እስካሁን ፖሊስ 9 ከአባ ተባዮ ወጣቶች ከአንዱ ጥጋበኛ በስተቀር አስሮ ፈትቷል።የፈታቸውንም በሚፈለጉ ጊዜ ሊቀርቡ መዝግቦአቸው ለቆአቸዋል። ከኛ መሀል አንድም ሰው አልተያዘም። ሰላማዊ ነና! ያ የሚያሳየው፣ አባ ተባዩ የጠነሰሱት ሴራ አድጎ ተመንድጎ፣ ሕግ እንደማያዋጣቸው ሲረዱ፣ ወደ አመጽና ወንጀል አምጥቀውታል። ለደረሰው ጥፋት፣ ለልጆቹ ጉዳት፣ ተጠያቂው አባ ተባዩ ስግብግብ ሰው ናቸው። ፖሊሶቹ ትላንት ከገረማቸው ትልቁ ነገር አንዱ፣ ሕዝባችን በቁጥር እነሱን በብዙ እጥፍ ሲያጥፍ፣ አንዳችም ነገር ለማድረግ አለመንቀሳቀሱና፣ ፖሊሶቹን አለማስቸግሩ ነው። አንዲት ሴት ፖሊስ ለሌላው ፖሊስ ስትናገር፣ እነዚህ በጣም ዲሲፕሊን ያላቸው ሲሆኑ፣ እነዚያ በጣት የተቆጠሩ ወጣቶች ግን እንዲህ ማስቸገራቸው የሚግርም ነው ብላ ስትናገር ተሰምታለች። እንግዲህ፣ የአባ ተባዩ ጦር ሥነ-ሥርዓት የጎደለው መሆኑ በግልጽ በዩኬ ባለሥልጣኖች እየታወቀ መጥቷል። ይኸንን አመጽ ከኋል ሁኖ የሚሸርበው የወያኔ እምባሲ እንደሆነ ለአንዲት ደቂቃ እንኳን መዘንጋት የለብንም።
ከ30ዎቹ፣ አብዛኛው ወጣት ዝም ብሎ መናጆ ሲሆን አንቀሳቃሽ ሞተሮቹ ግን የወያኔ ቅጥረኞች ናቸው። ወያኔ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሥራ ፈት ወጣቶችን ለደኅነነት አሰልጥኖ እንዳስመረቃቸው እናውቃለን። በብዙ መቶ የሚቆጠሩትን፣ በተለያየ መልኩ ስደተኛ አስመስሎ ወደ ውጪ በማስወጣት በየዲያስፖራ እንደበተናቸው ብዙ መረጃ በእጃችን ላይ ይገኛል። ይኽ ድርጊቱ በኛ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም በግልጽ እየታወቀ መጥቷል። ወያኔ፣ ሰላዮቹን በግልጽም በስውርም እያሰውጣ ነው። በስውር ወደዚህ አገር የሚያስግባቸው፣ በትምህርት፣ በጉብኝት እያለ እያለ ነው። አንዴ እዚህ ካደረሳቸው በኋላ ፓስፖርታቸውን ደብቆ በመርከብ በሶማሌ ደላሎች ተመርተን መጣን እያሉ እጅ እንዲሰጡ፣ እራሱ ወያኔ ሲያሳድዳቸው እንደነበረ የሚገልጽ ሀሰት ሰነድ ሁሉ እየሰጣቸው፣ በሎንደን አማርኛ፣ “ያስረፍጃቸዋል”። ሌላውና ግልጹ ስደተኛ መስሎ የመውጣቱ መንገድ፣ ከዚያው ከኢትዮጵያ “የኤርትራ ስደተኞች ናቸው” እያስባለ ነው። ለኤርትራውያን ስደተኞች፣ ወደሶስተኛ አገር ”resettlement” የሚባል ፖርግራም አለ። ወያኔ ከእውነተኞቹ ትግራይ ውስጥ በቁጥጥሩ ሥር ከሚገኙት የኤርትራ ስደተኛ ካምፖች፣ የስደተኞች ዕድሉን እየነጠቀ ለሕወሀት የደኅንነት አባሎች እየሰጠ፣ ወደውጪ አስወጥቶ እመሀላችን ሰግስጎአቸዋል። መረጃውን ከኢሳት ሬዲዮ የOctober 9 ፕሮግራምhttp://ethsat.com/2013/10/09/esat-radio-oct-09-2/ ማግኘት ይችላል። ሲመጡ ለስሙ ኤርትራውያን ናቸው። ትግርኛ (ኤርትራዉያን ኤርትርኛ ይሉታል) የናታቸው ቋንቋ በመሆኑ፣ እንኳን ለውጪው ዜጋ እኛም ወንድሞች እና እህቶቻቸው ልዩነታቸውን አናውቅም። እዚህ ከደረሱ በኋላ፣ ኢትዮጵያዊነታቸውን ብቅ አድርገው ይቀላቀሉናል። ከዚያማ ወጣት ለወጣት መግባባት ቀላል ነው። የእግር ኳሱ አለ፣ ሙዚቃው አለ፣ የምሽት መዝናናቱ አለ፣ ጫት አለ፣ …። የወያኔ ዓላማ፣ እኛ ታላላቆቹ ስደተኞች ሙተን ስናልቅ፣ የሚተኩን አፍቅሪ ወያኔ እንዲሆኑ ልዩ የወደፊት የዲያስፖራ ደጋፊው ዚጎች ለማትረፍ ን እው። ለረጅም ጊዜ ያቀደው ስትራተጂ መሆኑ ነው። ታዲያ የሚያስፈልጋቸውን ጊዜያው ዕርካታ ሁሉ ወያኔ በቀላሉ እያቀረበላቸው፣ ዕወነተኞቹን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ልብ ይሰልባል። በቃ ተገናኝቶ ቸበርቻቻ መምታት ነው። ወያኔ ሲፈልጋቸው፣ ተቀጠሩት መሪነት፣ እዚሁ የተመለመሉት እና ሳያውቁ የተዶሉበትም አብረው ሆ ብለው መዝመት ነው። ለንደን ቤተክርስቲያን ላይ የዘመቱት፣ እኔ በግሌ የማውቃቸው ደህና ከመሀል አገር የመጡ ወጣቶች ሁሉ ተዱለውበታል። በጽሞና ሳነጋግራቸው፣ “እናንተ ፖሊቲከኞች ናችሁ። እኛ ፖሊቲካ አይገባንም። እናንተ የደርግ ባለሥልጣኖች ነበራችሁ፣ እያሉ ወያኔ የጋታቸውን መልሰው ያቀረሹብናል። ስንቶቻችን ከደርግ እንደተፋለምን ስንነግራቸው፣ “ፖሊቲከኞች ቤተክርስቲያናችንን ሊነጥቋት ነው፣ መነኵሴ ደበደቡ ስንባል፣ እንዴት ዝም ብለን እንቀመጣለን ብለን ነው የገባንበት” ይሉናል። እኔ በበኵሌ፣ ለማስረዳትም አልቻልኩም። መዝናናቱ ይቀርባቸዋላ! እድሜ ለአባ ተባዩ፣ አሁንማ በወንጀል የማንታወቅ ኢትዮጵያውያና ወንጌል ሳይሆን ወንጀል መታወቂያችን ሁኗል።
እሑድ ዕለት ከፖሊስ ጋር ሲከሳከሱ፣ አንድ የማውቀው ወጣት፣ “We are not Woyyane! We are not Woyyane!” እያለ ሲጮኽ ተሰምቷል። ልክ ነው። እሱ ወያኔ ላይሆን ይችላል። ዳሩ ግን አባ ተባዩ ምን ቢደግሙበት ይሆን እነተወለደን የመሳሰሉ ወያኔዎች በተሰበሰቡበት “ይቅርታ ያድርጉልኝ! በፊት ተሳስቼ ነበር”[4]ያሉትን በዓይኑ እያየ፣ ሙሉጌታ አሥራተ ካሳ በግልጽ ቤተክርስቲያን ድረስ መጥቶ፣ መመሪያ እየሰጠ እያየ፣ እነሰብሀት ነጋ ከመለመሉት ሲኖዶስ የመጡ ጳጳስት ሕንጻ ቤተክርስቲያናችንን ሊነጥቁ ሲያሰፈስፉ እያየ “እኔ ወያኔ አይደለሁም” ማለት! ጲላጦስ ክርስቶስ ላይ የሞት ፍርድ ፈርዶ፣ “እኔ ከደሙ ንጹህ ነኝ” ካለው በምንም አይለይም። በወያኔ መናጆ የሆናችሁ ወጣቶች ንቁ። አለበለዚያ ስማችሁ የወንጀል ሪኮርድ ውስጥ አንዴ ከተመዘገበ፣ እንጀራ ገመዳችሁ መበጠሱን ተረዱት! ትምህርት አይኖርም! ሥራ አይኖርም! በራሳችሁ አትፍረዱ! አባ ተባዩ ነገ ተሹመው ከሂዱ እኛ እና እናንተ እዚችው እንደተፋጠጥን ልንቀር ነው። አንዴ ሪኮርድ ከተያዘባችሁ በሆነው ባለሆነው እንደጥጃ ጎትተው ያስሯችኋል። በአጠፋችሁትም ባላጠፋችሁትም በዓይነ ቁራኛ ፖሊስ እየጠበቃችሁ ቁም-ስቅላችሁን ይሳዩአችኋል።
የመጨረሻው መልዕክቴ ለሸረኛው አባ ተባዩ እና ለወያኔ ነው። ለአባ ተባዩ ዓይናውጣ አጭበርባሪ አስመሳይ መነኵሴና ለወያኔ ደጋፊዎቻቸው የምናስተላልፈው መልዕክት አለ። ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ይኸን ሕንጻ ቤትክርስቲያን ለመንጠቅ የምትሞክሩትን በሙሉ አቁሙ። ወጣቶቻችንን መጠቀሚያ መሣሪያ አታድርጓቸው። ከሕግ ውጭ የምትሠሩት መጥፊያችሁ መሆኑን ዕወቁት። የሕግ የበላይነት የተከበረበት አገር ውስጥ መኖራችሁን አትዘንጉት። ንግስቲቱም ሳትቀር ለሕግ ተገዢ ናት። የአገሩ መንግሥት ሳይቀር ከሕግ በታች ነው። ሕጉ ከሰጣችሁ፣ ለሕግ እንገዛለን። ትተንላችሁ እንቀመጣለን። ውሰዱት። ሕግ ከሰጠን፣ የሕዝብ ንብረት ስለሚሆን አንዳችም ነገር ማድረግ አትችሉምና አትፈራገጡ። መፈራገጥ እንደእሁዱ ጉዳችሁ ለመላላጥ ብቻ ነው። ስለዚህ ያላችሁበት አገር ደንብ ጠንቅቃችሁ ዕወቁ። ወጣቶቻችንን መርዛችሁ መልሳችሁ እኛው ላይ አታዝምቱ! ወጣቶቻችን ሲጎዱ ማዘናችን ባይቀርም፣ ቢያሳዝነንም ታዲያ ተኝተን እንደማንታረድላችሁ ዕውቁ! ለንደን አዲስ አበባ አይደለችም! ለሕግ ተገዙ። የምትሠሩትን እናያለን! እንሰማለን! አንድ እርምጃ ስተውስድ ቀድመን እንጠብቃችኋለን። እባብ ለእባብ ይተያያል በካብ!

No comments:

Post a Comment