Sunday, September 9, 2012

ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ.....

እያወቅን በትርጉም !
      የእድገትና ልማት አብሳሪው ብቻ የሆነውን የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሁልጊዜ አንድም ፕሮግራም ሳያስቀር በንቃት እና በትግስት ከሚከታተሉት ውስጥ ነኝ ምክንያቱም ምንም አማራጭ ከሌለው ሰው ስለነበርኩ ። የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ፕሮግራሙን ሲጀምር << እንደምን አመሻቹ ዲሽ የሌላችሁ >>  ብሎ የሚጀምር ሳተላይት ቴሌቪዥን ይመስለኛል። ውሸት የመሰራቤቱ ባህሪው ስለሆነ ማለቴ ነው ። የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ስመለከት ምን ውሸት ተገኘ ብዬ ሰለምመለከት በትግስቴ ሁሉም ጓደኞቼ የቤተሰብ አባላት እንዲሁም የስራ ባልደረቦቼ እንደተደነቁብኝ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም ።

   << A GOOD NEWS IS NOT A NEWS AT ALL >>( ጥሩ ዜና - ዜና አይባልም ) የሚለውን የነጮቹን ሚዲያ ወግ በኢቴቪ ቦታ የለውም:: ዜናውም ፕሮግራሙም ዶክመንተሪውም መዝናኛውም የልጆች ክፍለ ግዜውም ኧረ ምኑን ብዬ ምኑን ላስቀረው በአጠቃላይ ሁሉንም ማለት ይሻላል :: በአንጻሩ 
    << A TRUE NEWS IS NOT A NEWS AT ALL >> ( እውነተኛ ዜና ዜና አይባልም ) የጣቢያው ተግባር፣ ተልኮና ራዕይ መሪ ቃል ይመስላል ። የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ለህዝቡ ሁልግዜ የሚናገሩት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አደገ፣ ተለወጠ፣ ተመረቀ ፣ተስፋፋ እየጨመረ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው በሚል ቃል በውሸት የተሞላ ነው ።
   በዚህ ዓመት ውስጥ ልማታዊው ኢቴቪ << በኢትዮጵያ ያለው የሀብት ክፍፍል ፍትሀዊ ነው  ብሎ ዘገበ >> መቼም እንዳባባሉ ነብሳቸውን ይማረውና ጠቅላይ ሚኒስተሩም በፓርላማ ሪፖርተራቸው የሚያስተዋውቁት የኢኮኖሚውን ቃል በማብራራት ልማታዊዎች  ተወጥረውና ተጠምደው ሰነበቱ እያሉ የተለመደውን ወሬአቸውን ያጠግቡን ነበር :: ወይ ጉድ ብዬ ሳልጨርሰ የወሬ ዱብዳ ጫኑብን የስራ አጡ ቁጥር ቀነሰ ብለው በፐርሰንት ያስቀመጡ እንደነበር :: የተረጂውም ቁጥር ቀንሷል ብለው ይደመድሙት ነበር :: ይህን ሁሉ ስሰማ ይሁን ከማለት ውጪ ምን ይደረግ ታዲያ ።
    አሁን ደግሞ የተቀበረና የተዳፈነ ብሶቴን የሚኮረኩር ዘገባ ኢቴቪ ሲያስተላልፍ ምን ለማለት ፈልጎ ነው እንዲ ያለው በማለት ይህንን ፕሮግራም ለመመልከት የመንፈስ ጥንካሬ አልነበረኝም :: ከዚህ በፊት ኢቲቪ እድለኛ ትውልድ በማለት የወሬ ፕሮፓጋዳውን ሲለቅ እድለኛ የተባለው ትውልድ ምንስ አግኝቶ ነው እድለኛ ለመባል ያበቃው? አባይ እስኪገነባ ድረስ እድለኛ ትውልድ አልነበረም ማለት ነው ? ወጣትነት ወርቃማ እድሜ ነው:: ወርቃማው እድሜ ላይ ሲደረስም ምንም አስደሳች ነገር የለም። የህወሐት ሎሌ የወነው ኢቲቪ << እድለኛ >> እያለ እያሞገሰ ያሞኘዋል ። በጫት ሱስ አእምሮ የሚያደነዝዘውን ትውልድ፣ ስደት ብቸኛ አማራጭ ያደረገውን ትውልድ፣ ሀሳቡን በነጻነት ያለ ፍርሀት መግለፅ የሚያስፈራው ትውልድ፣ የሚያነበው ነጻ እትመት ያጣ ትውልድ፣ ተምሮ ተመርቆ ስራ ያጣውን ትውልድ፣ የራሱን ስራ ለመጀመር ተደራጅቶ እንኳን መንገድም ህይወትም ኢህአዴግ ነው ካላለ ህይወት ተራራ የሚሆንበት ትውልድ ኧረ ምኑ ተባለና ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ አይደለ የሚባለው ይህን ትውልድ ነው << እድለኛው ትውልድ >> እያሉ መሳለቅያ ሲያደርጉት የነበረው ። እውነተኛው እድለኛው ግን የኢህአዴግ መንግስት ነው በእድለቢስ ትውልድ መሀከል በራበው ህዝብ መሀከል መልካም አስተዳደር እና ፍትህ ባጣው ህዝብ መሀከል ትክክለኛ ዲሞክራሲ ባጣው ህዝብ መሀከል ለ21 አመታት የነገሱት እንዴት እድለኛ አይባሉም ? ኢትዮጵያዊ ጀግንነትና ወኔያችን ተሰልቦ፣ አንድ መሆን አቅቶን ለየብቻችን በየቤታችን ብሶታችንን ስንጮህ ፣ ከሁሉም በላይ የሰማዩ አምላክ ፍርዱን ሲያቆየው እድለኛው ትውልድ ማነው ብለን አሰብን? ፍርዱን ለአንባቢ
     ደግሞ የተቀበረና የተዳፈነ ብሶቴን የሚኮረኩር ዘገባ ኢቲቪ ሲያስተላልፍ ያልኩት ውሸት የባህሪው ተብሎ የሚነገርለት ኢቲቪ የጠቅላይ ሚኒሰትሩን የጤና ሁናቴ ፣ መታመም ሳይናገር በስተመጨረሻ በኢንፌክሽን ምክንያት ታመው በህክምና ሲረዱ ቆይተው እንደሞቱ አደባብሰው ለኢትዮጵያ ህዝብ አሳወቁ ።
     ጠ/ ሚኒስትሩ  ከ 2 አመት ወዲ በካንሰር ህመም እንደሚሰቃዩ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገሩ ነበር :: በተለይ በቡድን 8 የመሪዎች ስብሰባ ላይ ዓርብ  ግንቦት 10 / 2004 ከፍተኛ ተቋውሞ ደርሶባቸው ነበር ። በአሜሪካ አገር ውስጥ በሬገን ህንጻ በምግብ ዋስትና ስብሰባ ላይ አራት የአፍሪካ መሪዎች እንደነበሩና ሶስቱ በአግባቡ ንግግራቸውን እንደጨረሱ ጠ/ ሚኒስትሩ ግን ንግግራቸው ሲጀምሩ ነበር ተቋውሞ በጋዜጠኛ በአበበ ገላው ከፍተኛ ድምፅ አዳራሹ የተናወጠው  << WE NEED FREEDOM >> በሚል እና በተለያዩ የነጻነት ቃላት ጥያቄ አዳራሹ በነበልባል ድምፅ አስተጋባው በአዳራሹ ውስጥ ያሉ ታዳሚ እነ ባራክ ኦባማን እንዲሁም ትልልቅ የአለም መሪዎች ትኩረት እንዲሰጡበት ያደረገ ታላቅ ጋዜጠኛ ነበር ።ከዚያን በኋላ ነበር ጠ/ሚኒስትሩ ሳይኮሎጂካሊ የጤናና ፖለቲካዊ ክስረት የደረሰባቸው ። ከዚሁሉ ኪሳራ በኃላ ከቴሌቪዥን እይታ ውጪ ሆኑ ። ብዙም ሳይቆይ መታመማቸው በአንዳንድ ሚዲያ ይገለፅ ጀመረ ። ከትንሽ ቀናትም በኃላ መሞታቸው ሰማን በግል ሚዲያ ። ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ደግሞ ከወር አስራምስት ቀን በኃላ መሞታቸውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳወቀ ። ብዙም አልተደነቁም ውሸት የመስሪያቤቱ መርህ ሰለሆነ ብቻ ሳይሆን ለፕሮፓጋዳም የሚጠቀምበት ግዜም ያስፈልገውም ስለነበረ ነው።
    ነሐሴ 15 / 2004  የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ኢትዮጵያ ታላቅ መሪዋን አጣች ብሎ ዘገበ። ከዚህ በኋላ ነበር ፕሮፓጋዳውን መንፋት የጀመረው ኢቲቪ ። እኔም ከኢቲቪ ለየት የሚያደርገኝ  ኢትዮጵያ ትንሿን መሪ አጣች ብዬ ጽሁፌን ልጀምር !!
       ሕዝብን ሲሰድቡ፣ ሕዝብን ሲንቁ፣ ሲያዋርዱ፣ ፓርላማ ውስጥ ተጠየኩ ብለው በአሽሙር ሲመልሱ ነው የምናየው የነበረው፣ ስለ አገራቸው ሕዝብ ፍቅር የሌላቸው መሆናቸውን ነው  የምናውቀው፣ስለ ኢትዮጵያ ሲጠየቁ ስለ ጋና፣ ስለ ቻይና ሲናገሩ ነበር የምናዳምጠው የነበረው ላለፉት 21 ዓመታት እንዲ ሆኖ ሳለ ከሞቱ በኋላ በዚያን 15 ቀናት ውስጥ ያየነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀግና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለራዕይ ኢትዮጵያ ራሷን ምድሯን ከፍ አድርገው ወደ ሰማይ ያስባረኩ እስኪመስል ድረስ ኢቲቪ ፕሮፓጋንዳውን ሲሰጥ እንደነበር ይታወቃል ይህም የሆነበት ምክንያት ሙሾ ለማሰባሰብ የተጠቀመበት ዘዴ መሆኑን አያጠያይቅም ። ከጥቂት ወራት ብንመለከት በኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ገዳማት ሲነካ ፣ ሲፈራርስ ፣አባቶች ሲሰደዱ ፣በሙስሊሞች እምነት ላይ የመንግስት ጣልቃገብነት ጥያቄ ሳይመለስ ባለበት ወቅት፣ጋዜጠኞች በሚታሰሩበት ወቅት ፣ለፖለቲከኞች ዕድል ተሰቶ የማይታወቅበት አገር፣ፖለቲከኞች ተስማምተው እንኳን አውርተው የማያውቁባት አገር፣ ነፃነትና ፍትህ በሌለበት አገር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በግዳጅ አልቅሱ ማለት ተገቢ አይመስለኝም ።
      ለኢትዮጵያ ሕዝብ 21 ዓመታት ግፍና በደሉን ተሸክሞ ያሳለፋቸው መሪር አዘን እራሱ ሕዝቡ ውስጥ ነው ያለው እንጂ ሰው እንዲሰብክለት ስለበደሉ አይፈልግም ። ሕዝቡ አንድ ቀን እንኳን ሳያያቸው በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ የተመለከታቸው ህዝብ ፣ እሳቸው ሲያልፉ እንኳን መንገድ ተዘግቶ ይታጠራል ሕዝቡ ማለፍ ፣መንቀሳቀስ በማይችልበትና በመሳሪያ አፈሙዝ እያስፈራሩትና ፊትን አዙር እንዳትመለከት ተብሎ እሳቸውን እንዳያይ ይሁን ከቡዳ ለመከላከል አይገባኝም ነበር ። ምን አልባት በ 97 ምርጫ ሚያዚያ 29 ቀን ነበር በመስቀል አደባባይ ላይ ነበረ መአበል ባሉት ሰልፍ ያየናቸው ምን ዋጋ አለው ሚያዚያ 30 ቀን በንጋታው ደግሞ ሱናሜ የሆነባቸው ። በጣም የሚታዩት ካልን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ነበር ያን ጥሩ የሆነውን የስድብ ችሎታቸውን ሲያወርዱብን፣ ከሳቸው በላይ አዋቂ እንደሌለ የሚቆጥሩበት የግል ፓርላማ ፣አንድ ቀን እንኳን ሀገሬ ብለው ባልጠሯት ፓርላማ፣ሚኒስትሩ አሳሪና ፈቺ መሆናቸው በምናይበት ፓርላማ ነበር ኧረ ምኑ ተብሎ………………….
  ይህን ሁሉ ሕዝብ ሳያቅ ቀርቶ አልነበረም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፕሮፓጋንዳውን ሲነፋ የነበረው ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ይባል የለ ።
   ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ጀምሮ ጥቁር በጥቁር በመሆን ሽር ጉዱን ለማሳመር ተፍተፍ እያለ የለቅሶ ሴርሞኒ በአስለቃሽ ተዋናኝነት ለማሳመር ሲጠበብ ያሳለፈበት ግዜም ነበር። ይህም ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜም ይመስለኛል ።ህገ-መንግስቱም እንደሚያዘው ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ፐሬዝዳንቱ ሲሞቱ የአንድ ቀን ብሔራዊ አዘን እንዲሆን ነው የሚደነግገው ነገር ግን ህገ መንግስቱን በጣሰ ሁኔታ አስራ አምስት ቀን ብሔራዊ አዘን እንዲሆን ተደርጓል። ይህ ድርጊት በአገር ላይ ያለው ጉዳት ስናይ ከባድ ነው። አስራ አንድ ፐርሰንት በእድገት ጎዳና ላይ ነች ብለው የሚናገሩላት አገር ምን ያህል ኪሳራ እንደደረሰ ማንም የሚገነዘበው ጉዳይ ነው ።ሕጉስ ቢሆን የራሳቸው አይደል ምንስ ይደረጋል ።
     የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሕዝብ ትኩረት እዲሰጥበት ብሎ የተለያዩ ሰዎችን ለለቅሶ ድምቀት በቲቪ መስኮት አውጥቶም ነበር ።ለምሳሌ የኢትዮጵያ አርቲስቶችና ዘማሪንም ጭምር ስለ መለስ ዜናዊ እልፈት በተመለከተ እንዲያወድሱ የተደረገው,,,,,በተለይ ጥበብና ጠቢባኞች፣ ከያንያን፣ ገጣሚዎች፣ሙዚቀኞች፣ሙዚቃ አቀናባሪዎች፣ቴአትረኞች፣ የማስታወቂያ ባለሙያዎች ወዘተ የጠቅላይ ሚኒስተሩን እልፈት አስመልክቶ ወደውም ይሁን ተገደው ወይም ለማስመሰል አልያም በትክክለኛው ስሜት የተለያየ አስተያየት ሰተው ደመቅ ለማድረግም ተደርጎ ነበር።
    የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሃያ አንድ ዓመት የአመራር ውጤት የሚያደንቁ ገድል ሲነገር ቆራጥ አመራራቸውን ፣የስራ ታታሪነታቸውን፣ጀግና መሆናቸውን እረፍትለምኔ መሆናቸውን፣ለኢትዮጵያ እንደሚቆረቆሩ፣ አገር ወዳድ መሆናቸውን በዘፈን፣ በዝማሬና በግጥም ተወድሰውም ነበር።
     ሐዘኑን ወዶ ያዘነው ወዶ አዝኖ ነው ይባላል ወዶ ያላዘነውን ግን ለምንስ ይጎዳ በስንቱ ነገርስ ተጎድቶስ ይችላል።ይኽው እንደምናየው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቲቪ እንኳን አይቶአቸው የማያቁትን ሰው አልቅሱላቸው ብሎ ማስገደድ ምንስ ይባላል ። ለ21 ዓመታት አልቅሶ የተጎዳን ሕዝብ ድጋሚ እንዲያለቅስ ማስደረግ አምባገነናዊ ስርዓትን ማስፋፋት ይመስለኛል ። የሕዝብ ፍቅር የሌላቸውን መሪ የሕዝብ ፍቅር እንዳላቸው ተደርጎ በኢቲቪ ሰዎችን እየጠየቁ ጥሩነታቸውን እንዲናገሩ ፣ እንዲመሰክሩ ፣ እንዲያወድሱ ፣ ማድረጉ ለምን አስፈለገ ? ገድል ያለው ሰው ራሱ ስራው ይመሰክራል ። በተለይ ለተመልካች የሐዘን ገቢ ማሰባሰቢያ ያደረጉት የጎዳና ተዳዳሪዎችን ሰብስበው << እሳቸውን ስላሉ ነበረ ጎዳና የወጣነው እሳቸውን ተማምነን ነው አሁን አባት የሌለው ሰው ሆነናል >> አሉ ብለው ጎዳና ተዳዳሪዎችን በኢቲቪ አሳይተውን ነበረ። አንድ ቀንስ ቢሆን  ስለ ጎዳና ተዳዳሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስበውና አውርተው አይተንም ሰምተንም አናውቅም ። እኔ እንግዲ የማውቀው ለእለት ምግባቸው እንኳን ሲለምኑ ፖሊሶች ሲያባርሯቸውና ሲያሳድዷቸው ነበር የምናውቀው። ለካስ ኢቲቪ ደብቆን ነበር ይህን ሚስጢር ?
   ይባስ ብሎ ኢቲቪ ለተተኪው ትውልድ ያወረሰው ነገር በጣም ነው የገረመኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ መላዕክት እንዲወደሱና ፎታቸውን አስቀምጠው እንዲሳለሟቸው ማድረግ ምን ገድል ሰርተው ነው ? ወይንስ አገሬን አላውቅም እስከምል ድረስ ነበር ግራ ያጋባኝ እናንተስ ምን ትሉ ይሆን ?
    በመጨረሻ ለማንሳት የምፈልገው ነገር ቢኖር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲ የሚወደዱና የሕዝብ ፍቅር ከነበራቸው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መታመማቸው ለሕዝብ አሳውቆ  የኢትዮጵያ ሕዝብ በየሐይማኖቱ እንዲፀልይላቸው ለምን አላደረገም ? ሕዝቡ እንኳን መታመማቸውንና መሞታቸውን ቀድሞ እንኳን የሰማው ከግል ሚዲያ ነበር።  ለማንኛውም ሙት ወቃሽ አያድርገኝ.... ብዙ ብንል ብዙ እንላለን ። እያወቅን በትርጉም እንዳይሆንብን እንጂ !!!
 እውነቱ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተደርጎለት ቀርቶ ሳይደረግለትም የዋህ ፣ አዛኝ ሕዝብ መሆኑን ማወቅ ብቻ ሳይሆን መረዳትና መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል ።
  << ሕዝብን በፍቅር መግዛት ቀብርን ያሳምራል >>
            ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!  
                                                     ከዘካሪያስ


 

No comments:

Post a Comment