Thursday, August 29, 2013

የጋዜጠኝነት ሙያና ፤ በውጪ ያሉ ሚዲያዎች አገልግሎት ሲገመገም

ከደምስ በለጠ
ስለጋዜጠኝነት ስናስብ የመጀመሪያው ጥያቄ የሚሆነው ጋዜጠኝነት “journalism”
፤ ምንድነው ? ጋዜጠኝነት መቼ ተጀመረ ? እንዴትስ አደገ ? የጥሩ ጋዜጠኛ መገለጫ
ባህሪዎችስ ምንድን ናቸው? የሚለው ይሆናል :: ጋዜጠኝነት የተፈፀሙ ፤ የተደረጉ
ሁኔታዎችን ፤ በጋዜጣ ስርጭት ፤ በመፅሄት ፤ በመፅሃፍ ፤ በራዲዮ ፤ በቴሌቪዥን ፤ አሁን ደግሞ በኢንተርኔት “Internet” ፤ በብሎግ ፤እና በሞባይል ሜዲያ ፤ ለብዙሃኑ አድማጭ ውይም አንባቢ ፤ ማዳረስ ነው። በመጀመርያ ጋዜጣ የሚለው የአማርኛ ቃል እንዴት ተገኘ? ጋዜጣ “gazzetta” የሚለው ቃል ከፈረንሳይኛ የተወረሰ ቢሆንም ፤ ፈረንሳዮች ያገኙት ፤ ቨኒሲያ ከምትባለው የጣሊያን ደሴት ከተማ ነው ። በቨኒሲያ የመጨረሻዋ ቅንስናሽ ሳንቲም ወይም አንድ ሳንቲም ጋዜታ “ ” “gazzetta” ትባል ነበር ። ከተማዋ በንግድ ፤በኪነ-ጥበብና በእውቀት ፤ እጅግ በልፅጋ በነበረበት ከ15ኛው እስከ 17ኛው መዕተ-አመታት ፤ በከተማዋ በዚች ቅንስናሽ ሳንቲም የምትሸጥ የዕለቱን ወሬ ይዛ የምትወጣ ሌጣ ወረቀት ነበረች ።“gazeta de la novita” ትባል ነበር፤ የአንድ ሳንቲም ዜና እንደማለት ነው።
ስለዚህ ጋዜጣ “ ” የሚለው ቃል አንድ ሳንቲም እንደ ማለ ት ነው ። የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አዕምሮ ጋዜጣ ይወጣ የነበረው በአማርኛና በፈረንሳይኛ ስለነበር ፤ ጋዜጣ የሚለው ቃል ከዚሁ ጋዜጣ ጋር ከፈረንሳይኛ ወደ አማርኛ ገብቶ ፤ ዛሬ የአማርኛ ቃል ለመሆን በቅቷል ።
የጋዜጠኝነት መሰረቱ ጋዜጣ ሲሆን በ 17ኛው ክፍለ-ዘመን ይጀምራል ፤ በ 18ኛውና በ 19 ምዕተ- ዓመት መፅሄትን ይጨምርና ፤ በ 20ኛው ክፍለ-ዘመn ደግሞ ራዲዮና ቴሌቪዥንን አካትቶ ፤ be 21ኛው መዕተ-ዓመት ወደ “Internet” ሜዲያ ተሸጋግሯል ።
ዛሬ በውጪው አለም በጋዜጠኝነት ለመጠራት የሚያስፈልገው ገንዘብ ይዞ ወደ ራዲዮ
ጣቢያዎች በመሄድ የአየር ሰአት መግዛትና አንዱን ከአንዱ እያጋጩ የፈለጉትን መደቅደቅ አለያም የኢንተርኔት ዶሜይን ገዝቶ ከተገኘው የዜና አውታር ስለ ኢትዮጵያ የተፃፈውን ሁሉ እየቆረጡ መቀጠል በቂ ሆኗል ። ወይም በፓልቶክ 500 ሰው ሰብስቦ ጭራና ጆሮየሌለው መጨበጫው የጠፋ ባዶ የወሬ ጋጋታ መነስነስም ጋዜጠኝነት ነው እየተባለም ነው ።
ውድ አንባብያን ሆይ! ስለጋዜጠኝነት መሰረታዊ ሃቦች ለመረዳትና እየተሰራ ያለውንም
ለመገንዘብ ይረዳችሁ ዘንድ የሚከተለውን ፍሬ ሃሳብ በትንሹም ቢሆን ማገናዘብ ይጥቅማል።
ጥሩ ጋዜጠኛ ሁልጊዜ ጥንቁቅ ነው ። ጥሩ ጋዜጠኛ ማንበብ ይወዳል ፤ ስለአካባቢውና
ስለአለማችን ለማወቅ ይጥራል ፤ ወሬ የት እንደሚገኝ ያነፈንፋል ። ይህ የጋዜጠኛነት ሙያዊ ጥረቱ ለአንባቢዎች ፤ ለተመልካቾችና አድማጮች ትክክለኛ ፤ ሃቅ ላይ የተመሰረተ መረጃ ለማቅረብ ይረዳዋል ። ጥሩ ጋዜጠኛ ተጠራጣሪም ነው ፤ ሰዎች መግለጫዎችና ማብራሪያዎች ሲሰጡ ከጀርባ ሊሰሩ የታሰቡ ያልተገለፁ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ መጠርጠር ይኖርበታል ፤ በዚሁ ዙሪያም አሳማኝ ማስረጃም እስኪያገኝ ድረስም መቆፈር ያስፈልገዋል ። ጥሩ ጋዜጠኛ ተስፋ አይቆርጥም ። አንዳንድ ጊዜ የተወሰኑ ሰዎች ቃለ መጠይቅ ለመደረግ ላይስማሙ ይችላሉ ። ጋዜጠኛ በእንዲህ አይነቶቹ ተስፋ ሳይቆርጥ ፤ሙያው በሚጠይቀው መሰረት የደበቁትን ሃሳብ ፀሃይ እንዲሞቀው ማድረግ ይኖርበታል ።
አንዳንዴ በጣም ቀላል የሆነ ዜና ብዙ ድካም ሊጠይቅ ይችላል ። ጥሩ ጋዜጠኛ ጠቅላላ
እውቀት የሚባሉ ሁኔታዎች ላይ በተለይ ህግን ፤ ፖለቲካንና ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በየቀኑ መረጃዎች ሊኖረው ይገባል ፤ የማይረቡ ዜናዎች ናቸው የተባሉትን እንኳ የማወቅ ግዴታ አለበት ። ጥሩ ጋዜጠኛ በህብረተሰቡ ታማኝነትን ማትረፍ ይኖርበታል ። ቃለመጠይቅ ሲያደርግ ምን ፤ መቼና በምን ስነ-ስርአት መጠየቅ እንዳለበት ማወቅ የጥሩ ጋዜጠኛ ግዴታው ነው ። ሰዎች እምነት ሲጥሉበት ድብቅና የግል የሆነ ሚስጥራቸውን ሁሉ ያካፍሉታል ።ስለዚህም የሰዎችን ሚስጥር እንደመረጃ አውጥቶ አለመስጠት የጋዜጠኛው ግዴታ ይሆናል ።
ምርጥ ጋዜጠኛ ጠንካራ ስነምግባርና ጨዋነት ስለሚኖረው የትኛውን መረጃ ማውጣትና
የትኛውን መተው እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል ። ጥሩ ጋዜጠኛ የጉዳዮችን ወይም የሁነቶችን እርግጠኝነት ልምድ ማሳደግ ይኖርበታል ። ጥቃቅን ለተባሉ ነገሮች ሁሉ አይኖቹ ክፍት መሆን ይገባቸዋል ። የአንድን ጉዳይ እርግጠኝነት እስኪያገኝ ድረስ ደግሞና ደጋግሞ የመጠየቅ ፍራቻ ሊያድርበት አይገባም ። በህትመትም ሆነ በራዲዮ ወይ በቴሌቪዥን ላይ የሚሰራ ጥሩ ጋዜጠኛ የመጻፍ ልምድ ሊኖረው ይገባል ። አድማጮችን ወይም አንባቢዎችን በሚስብ ጣፋጭ ቋንቋና በፍጥነት የመጻፍ ልምድ ሊያዳብር ይገባዋል ።እንግዲህ ከብዙ በጥቂቱ ፤ የጋዜጥኝነት መሰረታዊ ሃሳብም የሚነሳው ከዚህ በላይ በጠቀስናቸው መርሆዎች ላይ ነው። ይህን ተግባር የሚያከናውኑ ሰዎችም ጋዜጠኞች ይባላሉ።ይህ ሙያ ታዲያ ፤ ኤዲቶርነትን ዲዛይንንና ፎቶግራፍን ያካትታል ። ለህብረተሰቡ መረጃ መስጠት የሚለውን አቢይ መርህ ተከትሎ ጋዜጠኛ በሚሰራው ስራ ግለ-ሰቦችን ፤ድርጅቶችን ፤ ተቋማትን ፤ የመንንግስት መስሪያ ቤቶችን ፤ ንግድን ብሎም የህብረተሰቡን ባህላዊ እሴቶችን እንደ ኪነ- ጥበብና መዝናኛ እንዲሁም ቤተ-እምነቶችን የመሳሰሉት ሁሉ ላይ በማተኮር ይሰራል። ስለዚህም ህዝባዊ ጉዳዮችንና መርጃዎችን በማሰራጨት ረገድ ጋዜጠኝነት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ጋዜጠኝነትም እንደሌሎች ሙያውች ሁሉ የተለያዩ የአቀራረብ ዘዴዎችን ይከተላል ። አንዳንድ ጋዜጠኞች ከጋዜጠኝነት መሰረታዊ ህሳብ እና ስነ-ምግባር የወጡ ሲሆኑ ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ስነ ምግባሩን ተከትለው የሚሰሩ ናቸው ።
ስለዚህም ጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የተሰማሩ ሁሉ በህብረተሰቡ ውስጥ ስፍራ
ይኖራቸው ዘንድ ፤ ለአንባቢዎቻቸውም ሆነ ለአድማጮቻቸው የጋዜጠኝነትን ስነምግባር ተከትለው ፤ ትክክለኛ መረጃ ማቅረብ ይጠብቅባቸዋል።
ጋዜጠኝነት በራሱ የተለያያዬ የአቀራረብ ባህርይ አለው ብለናል ። አለም አቀፍ እውቅና
ካገኙት ወስጥ እሰኪ አንዳንዶቹን በዝርዝር እንመልከታቸው ።
 “ወገንተኛ ጋዜጠኝነት” “ ፤ በእንግሊዝኛው Advocacy journalism” የሚባለው
ጋዜጠኛው አከራካሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ወገንተኛ ሆኖ ጋዜጠኛው ራሱ በራሱ ውስጥ
የሚያሳድገውን ሃሳብ የሚያቀርብ ሲሆን ፤ አቢይ ከሚባለው ሚዛናዊነትና የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር ያፈነገጠና የወጣ ነው። አገልግሎቱም ከህረተሰቡ ውስጥ ለተወሰነ ቡድን ወይም ስብስብ ብቻ ይሆናል ። ስለሆነም በአብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተቀባይነቱ የላላ ነው።
 “አድፋጭ ጋዜጥኝነት” “ ወይም Ambush journalism” የሚባለው ደግሞ ሰዎች
ለጋዜጠኛው መንገር የማይፈልጉትን ባልጠበቁት ሰአት ጥብቆ በማፋጠጥ ወይም በማስጨነቅ ማውጣጣት ማለ ት ነው ። ምን ጊዜም ጋዜጠኛ ለ ተጠያቂውችም ሆነ ለ ህብረተሰቡ ግልፅ ሆኖ መቅረብ ያስፈልገዋል ። ተጠያቂው ጥያቄውን መመለስ ባይፈልግ እንኳ ፤ ለህብረተሰቡ በጥያቄው የተጋለጠ ስለሆነ ፡ ህብረተሰቡ በራሱ ግምት ሚዛናዊ ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ ያግዛል ። ይህ አይነቱ አቀራረብ ጠንካራና ልምድ ያለው ተጠያቂ ላይ ተግባራዊ ማድረግ ስለሚከብድ ፤ ስልቱን ደካማ ያደርገዋል።
 “የግዢ ጋዜጥኝነት” “ ወይም Checkbook Journalism” የሚባለው ደግሞ ጋዜጠኛው መረጃ ወይም ዜና ሳይኖረው ገንዘብ ተከፍሎት ሌሎች የሚሰጡትን እንዳየና እንደነበር አድርጎሲያቀርብና ለዚህም አስፈላጊው ክፍያ ሲደረግለት ነው። በትገላቢጦሹም ፤ ጋዜጠኛው ራሱ ለአንድ ድርጊት ሁነት ፤ ወይም ክስተት ምንም ምንጭና ግልፅ ያለ መረጃም ሆነ ሰእል ሳይኖረው ዜና ወይም መረጃ ለመግዛት ገንዘብ ሲከፍል ነው ።
ዜጋዊ ጋዜጠኝነት ” ወይም Citizen journalist” የሚባለው ደግሞ በአለማችን በፍጥነት እያደገ ያለሲሆን ሰዎች የጋዜጠኝነት ትምህርትና ልምድ ሳይኖራቸው ፤ ዜጎች ልክ እንደ ጋዜጠኞች ለብዙሃን መገናኛዎች መረጃ አቅራቢዎች ሲሆኑ ነው። ሰዎች ድርጊቱ በተከናወነበት ስፍራ ላይ መቶ በመቶ ማለት ይቻላል ባጋጣሚ በመገኘት ፤ አንድን ድርጊትወይም ክንውን ፤ ጊዜው በወለደው ቴክኖሎጂ አማካይነት ከቀረፁ በሁዋላ ፤ ለዋና ዋናዎቹ ሚዲያዎች የሚያደርጉት አቅርቦት ነው። ይህን አይነቶቹ አቀራረቦች ብዙውን ጊዜ በፊልም የተደገፉ ናቸው፤ ዘመኑ የወለደው የቪዲዎና የስልክ ካሜራዎችም ትልቁን ሚና ይጫወታሉ
ለዜጋዊ ጋዜጠኝነት።
 “መጣጥፈኛ” “ ወይም Columnist” የሚባለው ደግሞ በአንድ ርዕስ ላይ ተመርኩዞ
ትንታኔና አስተያየት የሚሰጥ የጋዜጠኛነት ባህርይ ነው።
 “ፀያፍ ጋዜጠኝነት” “ በእንግሊዘኛው Gonzo journalism” በ 1970ዎቹ በአሜሪካን ሃገር እየታወቀ የመጣ ስልት ሲሆን ከመደበኛው ጋዜጥኝነት ስነ-ምግባር በወጣ መልኩ ፀያፍና ብልግና ቃላትን በመጠቀም ከተለመደው ጋዜጥኝነት ስልት ደግሞ የተጨባጭ ሁኔታዎችን መረጃ ሰንቀር በማድረግ ወዝ ለመስጠት የሚደርግ የጋዜጥኝነት ስልት ነው። በአሜሪካን ሃገር ለምትኖሩ Rush Limbaugh “ረሽ ሊምባኽ ጥሩ ምሳሌ ሊሆናችሁ ይችላል። ” 
መርማሪ ጋዜጥኝነት “Investigative journalism” የተወሰኑ ሰዎች ወይም ቡድኖች ፤ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ሆን ብለው ህዝብ እንዳያውቃቸው ያደረጓቸውን ጉዳዮች ፤
ከተቀበሩበት ቆፍሮ ፈልፍሎ ፤እውነትን ፍለጋ ረጅም ጊዜ ወስዶ መርምሮና ፈትሾ ፤ኢ-
ሞራላዊ ኢስነ-ምግባራዊና ህገ-ወጥ የሆኑ ፤ መንግስታዊም ሆነ ግለሰባዊ ወይም የቢዝነስ
ድርጅቶች ድርጊቶች የሚያጋልጥ የጋዜጠኝነት ስልት ነው።
 “የውጥንቅጥ ጋዜጠኝነት ” “Jazz journalism” የሚባለው ደግሞ እውነቱን ከሃሜት ጋር እየቀላቀለ በሌሎች ላይ የሚነዛ የአሉባልታ ጋዜጠኝነት ስልት ነው። ብዙወን ጊዜ የታዳጊ አገር ጋዜጥኞች ላይ የሚታይ ባህርይ ነው። ይህን ስልት የሚጠቀሙ ጋዜጠኞች ምንጊዚም ቢሆን የማይፈልጉትን ወገን ድምፅ መስማት አይፈልጉም። ይህን እንደጠላት የቆጠሩትን ወገንያሸነፉ እየመሰላቸው ሃሰቱንና ሃሜትን ከእውነት ጋር ይቀላቅላሉ። ጠላቴን ያጋልጥልኛል ያሉትን ሃስብ ከሌላ ድርጊትም ቢሆን ወስደው በመቀባት ህብረተሰቡን ይጎዳሉ። መረጃዎቹ የሚቀርብለትንም ህብረተሰብ ህሳቤ ያንሸዋርሩታልም ። የታዳጊ አገራት ጋዜጠኝነት ባህርይ ስለሆነም ወደኋላ ላይ ይህን አስመልክቶ የምመለስበት ሁኔታም ይኖራል።
መንጋ ጋዜጠኝነት “Pack journalism” ደግሞ ጋዜጠኞቹ መረጃ የሚኮራረጁት ከእርስ በርሳቸውና ሁሉም መረጃቸውን የሚያገኙት ከአንድ ምንጭ ብቻ ስለሚሆን መንጋ ጋዜጠኛ ያሰኛቸዋል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት ውስጥ መንግስት ነፃ ጋዜጥኞችን ስለሚያገልል ፤ጋዜጠኞች የመረጃ ቋቶቻቸው ከአንድ ቦታ ሊቀዳ የሚችልባቸው ሁኔታዎች ሰፊ ናቸው።
ይሁንና በአንዳንድ ሚዲያዎቻችን ላይ የምንመለከተው አሳሳቢ ክስተት ሆኗል ። የዜና
ምንጮቹ ማለትም CNN, Reuters, Associated Press, ወይም ሌሎች እንዳቀረቡት ፤ እንዳለ ተቆርጦ ፤ ምንም አይነት ኢትዮጵያዊ ማስተካከያ ሳይታከልበት ለፈረንጅ ፍጆታ እንደተዘጋጀ እንዳለ፤ በሁሉም ድረ-ገፆች ላይ ማለት ይቻላል የቃላት ልዩነት እንኳ ሳይኖረው ይቀርባል።
የመንጋው ጋዜጠኛ ሚና እዚህ ላይ ቆርጦ መቀጠል ብቻ ይሆናል።
ቢጫው ጋዜጠኝነት “Yellow journalism” የሚባለው አሜሪካ ኒው ዮርክ ውስጥ
ከ1880ዎቹ እስከ1890 ዎቹ ገደማ የተፈጠረ የጋዜጠኝነት ስልት ነው ። ይህ ስልት በደንብ ያልተጠናና መሰረተ-ቢስ የሆነ መረጃን አይን በሚስብ ርዕስ በማስዋብ በብዛት ጋዜጣን ለመሸጥ የሚደረግ ጥረት ነው ። መጠቀሚያ ዘዴውም ዜናዎችን ማጋነን ፤ ጠብ ማጫጫርና ማራገብ ብሎም ስሜታዊነት ላይ ማተኮር ናቸው ።
የአፍሪካን ጋዜጠኝነት አስመልክቶ ደግሞ ፍራሲስ ካሶማ እንደሚከተለው ያቀርቡታል ፤
አንዱንና አደገኛውን ልግለፅ ።
 A foundation of African ethics (Afriethics) and the professional practice of Journalism: 
“the case for society -centered media morality” “የአፍሪካ ጋዜጠኝነት ሙያዊ ተግባራት ስነ-ምግባራዊ መሰረት ሕብረተ “ -ሰብን ያማከለየሚዲያ ሞራላዊነት ፤ በሚለው ጥናታዊ ” ፅሁፋቸው ላይ እንዲህ ያስቀምጡታል ።
 “በቀልተኛ ጋዜጠኝነት ” “Vendetta Journalism” ከስነ-ምግባር አኳያ ስህተት ነው ይላሉ ። ጋዜጠኛው የራሱን ስሜትና ፍላጎት ስለሚያስቀድም የህብረተሰቡን ጥቅም ወይም የጋዜጠኝነት ሙያዊ ግዴታ አይከተልም ። በቀልተኛ ጋዜጥኝነት ፤ በጋዜጠኛው የግል ጥላቻምክንያት ፤ የበቀል ፍላጎቱ ስለሚነሳሳ ፤ የዜናው ተዋንያን ላይ የሚያሳድረው የግል ቂም ላይ ይመሰረታል ። የአፍሪካ ጋዜጠኞች ከላይ የጠቀስኩትን ሁኔታ የሚያራምዱባቸው ዘዴዎች አራት ናቸው ፤ ይላል የፍራንሲስ ካሶማ ጥናት ።
 1ኛ- በዜናው ምንጮች ወይም በዜናው ተዋንያን ላይ ፅዩፍ ቋቋዎችን መጠቀም
 2ኛ- ጋዜጠኛው የግል ፍላጎቱን ሊያጋልጥበት የሚችለውን ምንጭ ላለማነጋገር
የራሱን የግል ምርጫ ያደርጋል ። ምክንያቱም ስህተት ፈፅማችኋል ተብለው በሚዲያ
የሚጋለጡ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ሃሳባቸው ሊደመጥ ሲገባ ጋዜጠኛው ይህን
አያደርግም ። ሌሎች ላይ ጣትን ቅሰራ በጋዜጠኝነት ደረጃ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው ።
አለበለዚያ ይህ ተግባር ህብረተሰቡን እርስ-በርስ ወደ መወነጃጀል ይገፋፋል ።
 3ኛ- ጋዜጠኛው እውነተኛውን ስእል መጥፎ ቀለም መቀባት ይመቸው ዘንድ
የሚፈልገውን መረጃ ብቻ ሆን ብሎ መሰብሰብ ። ለበቀል ሲል የዜናውን ተዋንያን ደደቦችና አልባሌዎች አድርጎ ለመሳል ይመቸው ዘንድ ድርጊቱን ከመሰረታዊ ሃሳቡ በማዘናበል ማቅረብ።
 4ኛ- ጋዜጠኛው የማይወዳቸው ወይም የሚጠላቸው ግለ-ሰቦች ወይም ቡድኖች
ላይ በማፌዝና በመቀለድ ፤ በዜና ተዋናዮቹ ላይ ፌዘኛ የሆነ አቀራረብን በመጠቀም እነዚህን የሚጠላቸውን ሰዎች ወይም ቡድኖች ሞኞች ፤ መሃይሞች ፤ ኢምንቶችና ዋጋ ቢሶችበማድረግ አሳንሶ ራሱን ደግሞ የሁሉን አዋቂነት ሞኖፖሊ ያጎናፅፋል ። ሲሉ ይተነትኑታል ፍራንሲስ ካሶማ ፤ የአፍሪካን የበቀል ጋዜጠኝነት ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ ስላደገው ተለማማጭና ደብተራዊ ጋዜጠኝነት በጥቂቱ ላውሳ
ሓስብ ለማጫር ያህል ።
 “ተለማማጭና ደብተራዊ ጋዜጠኝነት ” ደግሞ በኛ ሃገር ተወልደው ያደጉ የጋዜጠኝነት
ስልቶች ናቸው ። እንደሚከተለው ላብራራ፤- በነገረ መለኮት ትምህርት እንደሚታወቀው ሁሉ ፤ ሁልጊዜ አምላክን ፤ መላእክቱንና ቅዱሳኑን ማወደስና ከፍ ከፍ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል ፤ በተቃራኒው ደግሞ ዲያቢሎስንና ርኩስ መንፈስን ማውገዝና መኮነንም ተገቢ ይሆናል ። በዚህ አስተምህሮ መሰረት የደብተራ ጋዜጠኝነት ስልት ፤ ገዢዎችንና ባለስልጣናትን ከፍ ከፍ በማድረግ እስከ መለኮታዊ ባህርይ
ድረስ ማጎናፀፍ ፤ የገዢዎቹና የባለስልጣናቱ ተቃዋሚዎች ወይም ተቃራኒዎች ናቸው
የሚባሉ ወገኖች ካሉ በማራከስና በማንኳሰስ እስከ ጭዳነት ማቅረብን ያካትታል ። ይህን ተግባር ለመፈፀም ጋዜጠኛው የሚተጋው ብራሱ አነሳሽነት ምን ይዤ ልቅረብ ከሚለው ባህርይው እንጂ በገዢዎቹ አስገዳጅነት አይደለም ። በተጨማሪም የእነዚህን ገዢዎችና ባለስልጣናት አነጋገርና አባባል ፤ እያጎሉ ፤ እያካበዱና እያጣፈጡ በማቅረብ ከንቱ ውዳሴና የሌላቸውን ሰብዕና የማላበስ ስልት ነው ። ለምሳሌ በአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ ፀኅዩ ንጉስ እየተባለይነገር የነበረው ሙገሳ ፤ በደርግ ዘመን ደግሞ ስለኮለኔል መንግስቱ ቆራጥነትና አብዮታዊ መሪነት ፤ አሁን ደግሞ ባለራእዩና አባይን ደፋሪው የሚባለውን ከንቱ ውዳሴ ማንሳት ለደብተራዊ ጋዜጠኝነት በቂ ምሳሌ ሊሆን ይችላል።
ጠለማማጭ ጋዜጠኝነት በጥቂቱም ቢሆን ከደብተራ ጋዜጠኝነት ጋር የሚመሳሰል ባህርይ አለው ። ጋዜጠኛው ብዙ ሊጠይቃቸው የሚችላቸውና የሚያቃቸው ሁኔታዎች እያሉት ባለታሪኮቹን ወይም ደጋፊዎቻቸውን ላለማስቀየም ሆን ብሎ የሚተዋቸውና የሚያልፋቸው ጥያቀዎች ይኖሩታል ። ተጠያቂዎቹ እንዲባልላቸው የሚፈልጉትን ቀድሞ በማፈላለግና በማጥናት ጎላ አድርጎ በማድመቅ ላይ ያተኩራል ። በጋዜጠኝነት አቀራረቡም ጥያቄውቹን ለባለታሪኮቹ የሚመቻቸውንና የሚፈልጉትን ቀደሞ በማጥናት የሚደረግየተጠና ድራማ የሚመስል የጋዜጠኝነት ስልት ነው ። ተለማማጭ ጋዜጠኞችን በህትመት ሚዲያ መለየት ባይቻልም በተለይ በቴሌቪዥን መስኮትና ባራዲዮ አቅርቦት ላይ በቀላሉ መለየት ይቻላል ። በራስ የመተማመናቸው ጉድለትና የድምጻቸው አወጣጥ ከዚህ በፊት ከሚያቀርቡበት ድምፅ በተለወጠና በተለይ ከተጠያቂው ድምፅ ሰው በታች የራሳቸውን ድምፅ ለማሳነስ በሚያደርጉት ጥረት በቀላሉ ተለማማጭነታቸውን መለየት ይቻላል ። ተለማማጭጋዜጠኞች በተቃራኒው ሊለማመጡት የማይፈልጉት እንግዳ ሲኖራቸው ደግሞ በራስ መተማመናቸው ይጨምራል ፤ድምፃቸውም ከተጠያቂው በላይ በማድረግ ድንፋታ ቢጤ ስለሚጨምሩበት በቀላሉ ይለያሉ ።
“ሙያዊ ጋዜጠኛነት ” “Professional journalism” በ 20ኛው ክፍለዘመን መባቻ ላይ በአሜሪካን ሐገር የተጀመረና ሙያዊ ዜናና መረጃ አቅራቢነት ፤ ከመደበኛው የጋዜጠኝነት ትምህርት ጋር በአሜርካ ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎችም ደረጃ ያደገና ሌሎች ሐገሮችም የወረሱት ሙያ ነው። ይህ ሙያ ምንጊዜም ቢሆን ከጋዜጠኛው የግል ፍልጎትና አቋም የወጣና የሚመለከታቸው ወገኖችን መረጃዎች ያለምንም ቅመም በግልፅና በእውነተኝነት ማቅረብ ነው። ሚዛኑንም ለአድምጩ ወይም ለአንባቢው መተው የሙያዊ ጋዜጠኛ ተግባር ነው።
የሙያዊ ጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር ከፍርድ ስርአት ጋር ይመሳሰላል ። አንድ ጉዳይ ለፍርድ
ሲቀርብ የሁለቱም ወገን ምክንያቶች ተደምጠውና በቂ ክርክር ተደርጎባቸው ነው ፍርድ
የሚሰጠው። የሙያዊ ጋዜጠኛው ሚና እዚህ ላይ ሁለቱም ወገኖች ድምጻቸውእንዲሰማ
ማገዝ ብቻ ይሆናል ። የብዙ ኢ-ሙያዊ ጋዜጠኞች ችግር በዚህ ሁኔታ ላይ ዳኛ ሆኖ
የመቅረብ ፍላጎት ነው። ዳኛ መሆን ያለበት አድማጭ አንባቢና ተመልካቹ ህብረት-ሰብ ነው።
ለሎችም አይነቶች የጋዜጥኝነት ስልቶች አሉ ። ሆኖም ለዛሬው በኛ በኢትዮጵያውያኑ
ወቅታዊ የዲያስፖራ ጋዜጠኝነት ላይ ለትንታኔ ይጠቅማሉ ያልኳቸውን ነው ከላይ ለመዘርዘር የፈለኩት።
ዛሬ በዴያስፖራው ሚዲያ ላይ የሚታየው ሙያዊ የስነምግባር ጉድለት ፡ ትግሉን
ጎድቶታል ብየ ከሚያስቡት ወገን ነኝ ።
ከድረ-ገፆች ልጀምር። ከላይ ጨረፍ አድርጌ ያለፍኩትን ሃሳብ እንደገና ላንሳ ። ድረ-
ገፆቻችንን የሞሏቸው ዜናዎች በሙሉ ከታላልቅ የዜና አውታሮች የተወሰዱ ናቸው ።መወሰዳቸው ባልከፋ ፤ ዜናዎቹ ፈርንጃዊ እይታ የታከሉባቸው ስለሆኑ ለኢትዮጵያዊ አንባቢ ከራሱ እይታ ጋር አይቀራረቡለትም ። ምንም እንኳ ዜናዎቹ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ቢሆኑም ፤ አንባቢው ሳይፈልግ ራሱን በፈረንጅ እይታ መቃኘት ይገደዳል ። የቃኘ ይቃኛል ፤ መቃኘት ያልቻለም ይቀርበታል ። በድረ-ገፆቹ ላይ የሚወጡ መጣጥፎች የየራሳቸው ባህርያት ቢኖራቸውም ፤ አስተያየቶች ፡ ትምህርት አዘል ትንታኔውች ፤ ጥናታዊ ጽሁፎች ፤ ገጠመኞችና የፈጠራ ስራዎች ስለሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል። የህዝባችን አገልጋዮች ነን ስለሚሉንም የኛ ናቸው ብለን ስናስብ ፤ የድረ-ገፆቹ ባለቤቶች እነሱ ብቻ የሚፈልጓቸውን ፅሁፎች የሚያቀርቡበት ሁኔታም ይስተዋላል ። በገዢው መንግስት ሳንሱር ተደረግን ፤ በየግልም በፃፍናቸው ፅሁፎች ምክንያት በደል ደረሰብን ፤ ታሰርን ተገረፍን ሲሉ የነበሩ የድረ- ገፅ ባለቤቶች ዛሬ እነሱ ባለቤት በሆኑባቸው ድረገፆች ላይ የማይፈልጉትን አናቀርብም ሲሉ ከአሳሪዎቻቸው በምን ተሻሉ ? የአሳሪዎቻቸውም ጥያቄ እኮ የማንፈልገውን ለምን አቀረባችሁ የሚል ነበር ። ይህን ስል በተቃዋሚ ጎራ ካሉት ወገኖች የሚቀርብላቸውን ፅሁፎች ማለቴ ነው። ብዙ ጊዜ በዲያስፖራው እንደተስተዋለው ፤ ዘመን አንድ ሰሞን ሰማይ አድረሶ ኋላ ላይ መሬት የፈጠፈጣቸው ድርጅቶችን ላለፉት 22 አመታት አስተውለናል።
ከእነሱም ጋር ተነስተው አብረው የወደቁ ድረ-ገፆችንም አይተናል ። ለ ረጅም ጊዜም የዘለቁ አስካሁንም ያሉ አሉ። በአብዛኛው ባለቤቶቻቸው እንደግል ንብረቶቻቸው የሚቆጣጠሯቸውና ዜናዎቹን ለማቅረብ እንኳ የጊዜ ገደብ የሌላቸው ሲፈልጉ በአራትን በአምስት ቀን ልዩነት ዜናዎችን post የሚያደርጉ ናቸው ። አንባቢዎቻቸው አዲስ ዜና ፍለጋ በቀን አስር ጊዜ ሲመላለሱ ቢውሉ የዜና ቋንጣ ከማግኘት በስተቀር የሚተርፋቸው የለም ። ስለዚህም በዚህ የመረጃ ዘመን አንባቢዎች የሚፈልጉትን ከለመዱበት ቦታ ሲያጡ ፤ እንደየሁኒታው ብቅ ብቅ ማለት በጀመሩት የወያኔ መረጃ መረቦች ላለመጠመዳቸው ምን ዋስትና አለ? ውድ አንባቢዎችን እዚህ ላይ የምጠይቀው እስኪ በየራሳችሁ ጥናት አድርጉ ፤ ውጤቱን ታገኙታላችሁ። እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት በአንድ ቋንቋ ፤ ኢትዮጵያዊ ለዛውን ሳይለቅ ፤ ሁሉም ሰው በሚገባው መንገድ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ድረ-ገፆች እንዳሉም ሊታወቅ ይገባል። ይህ ትንታኔ ታዲያ የፖለቲካ ድርጅቶች ድረ-ገፆችን ወይም የሚዲያ መስመሮችን አይመለከትም። በተወሰነ የፖለቲካ አቅጣጫና ፕሮግራም ላይ ያነጣጠሩ ስለሆኑ።
ዛሬ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚኖሩባቸው የአሜሪካም ሆኑ የአውሮፓ ከተሞች
የራዲዎ ፕሮግራሞች የሌላቸው ከተሞች ጥቂቶች ናቸው ። ለራዲዎ ጋዜጠኝነት በድምፅከመተላለፉ በስተቀር በፅሁፍ መቅረብ ያለባቸው ሁኔታዎች መዘጋጀት ይኖርባቸዋል ። ስለዚህ አቅራቢው የፅሁፍ ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል። በፅሁፍ ዝግጅት ማድረግ ካልቻለ ከጋዜጠኝነት መስፈርት ውጥቶ ተራ ወሬኛ ይሆናል ። የራዲዎ አቅራቢውም ቢያንስ በጣቢያዎቹ የሰአት ቀመር ምክንያት በሳምንት በተከራየው ጊዜ በአግባቡ ሰአቱን ጠብቆ የገባል ይወጣል ። በብዛት የዲያስፖራውራዲዎ ከሚተላለፍባት ዋሽንግተን ከተማ ጀምሮ አንድና ሁለት ራዲዎኖች ባሉባቸው ከተሞችም ውስጥ ያሉ ችግሮች ተመሳሳይ ናቸው። አዘጋጆቹ ላይ የሙያ ክህሎት ማነስ ፤ የራስ የሆነ
የአቀራረብ ስልት አለመኖርና በተለይ ደግሞ አቀራረብንም ሆነ የቃላት አጠቃቀምን ጭምር የመኮራረጅ ባህርያት ስለሚስተዋል ፤ በአደማጩ በኩል መሰላቸትን የሚፈጥር ይሆናል።
ከዚህ በተጨማሪ የራዲዎው ዝግጅት ከሌሎች ፕሮግራሞችና ሰዎች የቀደመ ስራ ላይ
በተደጋጋሚ እየተቀረፀ ፤ለሰአት ማሟያ ስለሚቀርብ የፕሮግራም ድሪቶ ይሆናል። ለራዲዮ የአየር ሰአቱን ለመክፈል የሚያስፈልገው ገንዘብ ለድረ-ገጾች ከሚከፈለው ጋር ሲነፃፀር እጅግ ብዙ ስለሆነ ማስታወቂያ ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ውሰጥ የእርስ በርሱ ስም መጠፋፋትና የነገር አተካሮ ምልልስ የአየር ሰአቱንና የአድማጩን ጊዜ በእጅጉ ያባክነዋል ። ብዙዎቹ የራዲዎ አቅራቢዎችም የፅሁፍም ሆነ ሁኔታዎችን የመረዳት አቅማቸው ውሱን ስለሆነ ፤ሳያውቁት ትኩረቶቻቸው ከላይ በቀረቡት አሉታዊ የጋዜጠኝነት ስልት ላይ ያተኮሩ ናቸው።
አንዳንዶቹ እንዲያውም በግል ባህሪያቸው ምክንያት ማይክሮፎን ሲጨብጡ ፤ የየአካባቢያቸው ሰው ላይ የነገሡ የሚመስላቸውና በከተማዋ ውስጥ የሚካሄደው ማህበራዊ ጉዳይ ሁሉ እነሱ እንዲያውቁት ካልተደረገ ፤ በራዲዎ ወጥተው የማህበረሰቡን ጉዳይ ሁሉ ኩስ የነካ እንጨት ለማድረግ ይምይሄዱበት መንገድና ርቀት የለም። እንደነዚህ አይነቶቹ ሰዎች የህብረተሰቡ የመረጃ ምንጮች ሳይሆኑ የግጭትና የጠብ ምንጮች ይሆናሉ ። በጋዜጠኝነት መለኪያም በዝቅተኛው ደረጃ እንኳን ለማስቀመጥ ያስቸግራሉ ።
ሌላው የአንዳንድ ግለሰቦችን ሰብእና ከተገቢው በላይ ማግዘፍና ማደንቆር ፤ ይህ
የሚሆንበት ምክንያት ለራዲዎው የአየር ሰአት ገንዘብ ለማሰባሰብ በሚያስፈልግበት ሰአት ሰብእናው የገዘፈለትን አርቲስት ጋብዞ ገንዘብ ለመሰብሰብ የተቀየሰ ዘዴ መሆኑ ነው። እባብን “ ያየ በልጥ ይደነብራል እንደሚባለው የቆራጡን መሪ ስብእና ግዝፈት ያስተውል የነበረ ፤ ” እንዲህ በሰዎች ስበእና ግዝፈት ላይ ሲተኮር ሲያይ ወይ ግሩም! ከማለት ወደኋላ አይልም ።
እንዲህ አይነቱ ተግባርም ከደብተራ ጋዜጠኝነት ሌላ ሊሰጠው የሚችል ስም አይኖረውም ።ይህ ታዲያ የራዲዎኖች ችግር ብቻ ሳይሆን የድረ-ገፆችም ችግር ነው። በህብረተሰቡ ላይ ለሚፈጠርው ስነልቡናዊ ጫናም ፈፅሞ አይታሰብም።
ቴሌቪዥንን በተመለከት ፤ የአንድ ድርጅት አባላትና ደጋፊዎች የአመራሩንም ሆነ የተግባር ስራዎችን በሙሉ በሞኖፖል በያዙበት ሁኒታ ፤ ነፃ ሚዲያ ነኝ እየተባለ ስለተለፈፈ ብቻ ነፃ መሆን አይቻልም ። የአንድ ድርጅት አመራሮች ባስፈላጊውም ሆነ ባላስፈላጊው ሰአት እየወጡ የሚዲያ ሽፋን ሲሰጣቸውና የሌሎች ድርጅቶች አመራሮች ደግሞ ጠይቀው እንኳ በሰበብ ባስባቡና ሲነፈጉና እንዲሰላቹም ከአንዱ ሰው ወደሌላው በቢሮክራሲ መሰል ዘዴ ሲታፈኑ የሚዲያ ነፃነት አለሊባል አይችልም ። የነፃ የቴሌቪዥን ተብየውን ሹማምንት ለምን እንዲህ ይደረጋል የሚል ጥያቄ ሲነሳባቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ ስንል እያደረግነው ያለነው ነው ። ይህን የሚያስወሩብን ወያኔውች ናቸው ። ለኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ የመረጃ ፍላጎቱን ፤ በተለይ ደግሞ አገር ወስጥ ላሉት ድርጅቶች አለኝታዎቻቸው እኛ ነንና ስለ ነጻ ሚዲያ አትንገሩን ፤ የሚሉ ምክንያቶችን ይደረድራሉ።
ከዛሬ 30 እና 35 አመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ሰብአዊ መብት ሲጣስ ፤ መብቶች
ሲረገጡ በነፃ የመሰብሰብና የመፃፍ ነፃነት ሲታፈን ፤ የጊዜው ሹማምንት አብዮታችን ግቡን እንዳይመታ የሚታገሉን ፀረ-አብዮት ሃይሎችና አለ ም አቀፍ ኢምፔሪያልዝም ፤ እየሰሩብን ያለደባ ነውና ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ድሉን እስክናጎናፅፍህ ድረስ በትእግስት ተጨቆንልን የሚል መልእክታቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው ። ዛሬ ላይ ደግሞ የመብት ረገጣውንና አፈናውን በሰፊው የተያያዘው የወያኔ ስርአት ፤ በኛ ላይ ወቀሳና ትችት የሚያቀርቡብን ፤ የልማታችንና የእድገታችን ፀሮችና ተባባሪዎቻቸው ናቸው እያሉን ነው ። በአብዮታዊም ይሁን ፤ በልማታዊ አለያም በትግል ስም የሚደረግ ፤ የመበት ረገጣ ወይም አፈና ያው አፈና ነው ፤የመብት ረገጣ ነው ። የፈለገውን አይነት ኩል ቢኳል ፤ ሌላ መጠሪያ የለውም ። የተደረደሩ ምክንያቶችም ፈውስ አይሆኑትም ። ፈውሡ አንድና አንድ ብቻ ነው ፤ ይኽውም ቢያንስ በተቃዋሚው መሃል ልዩነት ሳይፈጥሩ ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶች በእኩልነት ማስተናገድ ።
ሌላው መረዳት የሚገባን ጉዳይ ቢኖር እነዚህ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉት ሌሎች ድርጅቶች የአባላት ቁጥሮቻቸው ምንም ቢሆን እንኳ ፤ ሲደመሩ ግን ብዙህን ናቸውና ቅሬታቸውሊደመጥ ይገባል ።
ለዛሬው በዚሁ ላብቃ ፤ የከርሞሰው ይበለን ።ለአስተያየቶቻችሁ mgmbelete@gmail.com ታገኙኛላችሁ ።

No comments:

Post a Comment