Thursday, August 29, 2013

የኢህአዴግን አክራሪነት ተቃውመን እንጂ ደግፈን ሰልፍ አንወጣም!!!

ሰማያዊ ፓርቲ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱበት ሰላማዊ ሰልፍ አድርጎ ነበር፡፡ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ስለሙስሊሙ የሐይማኖት ጥያቄ፣የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችና የፖለቲካ እስረኞች ባፋጣኝ እንዲፈቱ፣ስለኑሮ ውድነት ወዘተ ነበር በሰልፉ ላይ የተስተጋባው፡፡ በሰልፉ ማብቂያ ላይ እንደተነገረው እነነዚህ ጉዳዮች በ3 ወር ጊዜ ውስጥ የማይመለሱ ከሆነ እንደገና የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚጠሩ በእለቱ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ተናገረው ነበር፡፡ እንደቀልድ ሶስት ወሯም አልቃ የተጠየቁትም ጥያቄዎችም ሳይመለሱ ነሃሴ 26, 2005 ቀን ደረሰች፡፡

ከፋፋዩ ኢህአዴግ የተጠየቁትን ጥያቄዎች በመመለስ ፋንታ በማን አለብኝነት ዜጎችን ማሰሩን፣ማንገላታቱን አልተወም፡፡ አንድነት ፓርቲ ‹‹የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ›› በሚለው ዘመቻው በርካታ ሰልፎች ከ አዲስ አበባ ውጪ ማደረጉ ተጨማሪ እንቅልፍ የነሳው ይመስላል፡፡ ለዚህ ነው ከአንድ ገዢ ፓርቲ የማይጠበቅ በየእንቅስቃሴያቸው ላይ እየተከተለ ጎማ ሲያተነፍስ የነበረው፡፡ የነፃነትን በዚህ ሁኔታ ማስቆም የሚቻል መስሏቸው እንዲሁ ይደክማሉ፡፡ አንባገነኖች እንዲህ ናቸው፡፡ ከስህተታቸው መማርን አያውቁም ጦሩ አጠገባችን ነው ብለው በጦር ይመካሉ፡፡ ይህ ደግሞ ያየነው ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ታሪካችን ብንጀምር እንኳን ደርጉ ምን እንደነበር ምን እንደሆነ እናስታውሳለን፡፡ ከዚህ ከቅርቧ እንኳ መማር አልቻሉም፡፡ የጉልበት መንገድ( ፕሮፍ መስፍን ህገ አራዊትነት ይላታል፡፡) የት እንደሚያደርሳቸው የምናየው ይሆናል፡፡ ሆነም ቀረም አምባገነኖች አምባገነኖች ናቸው፡፡
በየእንቅስቃሴዎች መርበትበት የያዘው አምባገነኑ ስርአት በተለይም አክራሪነት ለመዋጋት ብሎ የጀመራት ዘመቻ እንዲሁም ከሼህ ኑር ይማም ሞት ጋር ተያይዞ በፓርቲዎች ላይ ጨምሮ በሙስሊም የሃይማኖት ጥያቄ ጠያቂዎች ላይ ዘመቻ ከፍቶ ነበር፡፡ ሃገር በውሸት ትመራ ይመስል ነጋ ጠባ ውሸትን ማዝነብ ይዘዋል ሚዲያዎቹ፡፡ ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል የሚለው ለዚህ ግዜ የሚሰራ አይደለም ፡፡ በእጅ ስልካችን እንኳ የሚደርሰን መረጃ ቀላል አይደለም፡፡ ይህም ቴክኖሎጂው እየተስፋፋ ሲሄድ ከዚህ በላቀ ሁኔታ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ አሁንም የነፃነት ጉዞው አቅም በፈቀደው ሁሉ ይቀጥላል፡፡
እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት ሰማያዊ ፓርቲ ነሃሴ 26 ሰልፍ እንደሚያደርግ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ እንደሰማነው ገዢው ፓርቲ ‹‹ፀረ አክራሪነት ትግል›› በሚል ከተለያዩ የሓይማኖት ተወካዮች ጋር በመተባበር በሚመስል መንገድ ለስምም ‹‹የሐይማኖቶች ጉባኤ›› ተሰባስበው ሰልፍ ለመውጣት እንደወሰኑ ተናግረዋል፡፡ መቼም ለወጉ ብዬ እንጂ የሓማኖት ተወካይ ያልኩት፤ ተወካይ ነን ያሉት ሁሉም ሓይማኖታቸውን የሚወክሉ ሳይሆኑ ለስርዐቱ ያደሩ ናቸው፡፡ የሐይማኖት አክራሪነት ምናምን የሚሉትት ፍረጃ ሰላማዊ የሆነውን እና ለ 18 ወራት ያህል ሲጠይቁት የነበሩትን የሙስሊም ወገኖቻችንን ጥያቄ አፈር ለማስበላት ያቀደ ነው፡፡ ይህም የሚሳካ አይደለም፡፡የሙስሊም ወገኖቻችን ጥያቄ መልስ ሊያገኝ ይገባል፡፡
አምባገነኑ ኢህአዴግ በጣም በሚያስቅ እና በሚያሳዝን መልኩ ሰዎች በሰልፉ ላይ እንዲወጡ እያስገደደ ይገኛሉ፡፡ በየቤቱ እተዞረ ቅስቀሳው ተጧጡፏል፡፡ በየክፍለ ከተማው ባሉ መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት ትእዛዝ ተላልፏል፡፡ በየክፍለ ከተማው ያሉ ወረዳዎችም በወረዳዎቻቸው ውስጥ ለሚገኙ ተቋማት ባለ ሁለት ገፅ መልእክት በትነዋል፡፡ በጣም የሚያስቀው እጄ ከገባው ባለ ሁለት ገፅ ፅሁፍ ውስጥ ሰልፉ ነሃሴ 26 እንደሚደረግ ወዘተ ይገልፅና ቀጥሎ እንዲህ ይለናል ‹‹ስለሆነም በወረዳችን የምትገኙ የመንግስትና የግል ተቋማት በስራችሁ ያሉ አጠቃላይ ሠራተኖችን በማነቃነቅ ነሃሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም በሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ እንዲሳተፉ እንድታደርጉልን እያሳሰብን ለዚህም ስራ ይረዳችሁ ዘንድ ለባነርና ለመፈክር የሚሆኑ መልዕክቶችን አያይዘን የላክን መሆኑን አሳውቃሉ፡፡›› ይልና በሁለተኛው ገፅ ‹‹በሰላማዊ ሰልፍ መተላለፍ ያለባቸው ዋና መልዕክቶች›› በሚል ይዘረዝራል፡፡ የአንድነትና የመከባበር፣የሰላም እሴቶቻችን በአክራሪዎችና ፀረ ሰላም ሃይሎች እንደማይናጋ›› እያለ ቅዠት የተሞላበትን ዲስኩር ያወራል፡፡ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ሰልፍ የሚወጡ ዜጎችን እንኳን በሰልፉ ላይ የሚያስተጋቡትን የሚመርጥላቸው ኢህአዴግ ነው፡፡ ከዚህ በላይ መውረድ ምን አለ? እንደዚህ አይነት ፓርቲስ በየትኛው አገር ነው የሚገኘው? ኢህአዴግ በፍፁም አይመጥነንም አራት ነጥብ
ስለሆነም ይህን ሰልፉ ማለትም ስርዐቱና የስርዐቱ ሎሌዎች በሚያዘጋጁት ሰልፉ ላይ መገኘት ሙስሊም ወገኖቻችን ለ18 ወራት ያህል ሲጠይቁት የነበረውን ፍፁም ሰላማዊ የሆነ የሐማኖት ጥያቄ ስርአቱ አለባብሶ ለማለፍ በሚያደርገው ሴራ ላይ ተባበሪ መሆን ይሆናል፡፡ እንዲሁም ለከፋፍለህ ግዛ፣ለኢ-ዴሞክራሲያዊነት፣ ለብልጣብልጥነት፣ለአምባገነንነት በአደባበይ እውቅና መስጠት ነው፡፡ ስለሆነም ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፉን አካሄደም አላካሄደም ስርአቱ እራሱ በጠራው ሰልፍ ውርደትን ልናከናንበው እንችላለን፡፡ ለዚህም ከስርዐቱ ሴራዎች ለማምለጥና የተሳካ ስራ እንድንሰራ በእለቱ ለምናካሂዳቸው እንቅስቃሴዎች ልንመክር ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment