Thursday, August 29, 2013

ህዝብ እኮ ነው!

ከበላይ
ህዝብ ሲባል ልዕልናው፣ ህዝብ ሲባል ቻይነቱ፣ ህዝብ ሲባል ቁጣው፣ ህዝብ ሲባል ሃያልነቱ ወ.ዘ.ተ. በእሳቢያችን ሊመጣብን ይችል ይሆናል፡፡ ይህ ግን በሀገሬ ኢትዮጵያ እንደ መስከረም ሰማይ ብልጭ ድርግም የሚል ክስተት እንጂ ሁሌም ህዝብ ቻይነቱ፣ ልዕልናውና ሃያልነቱ አይስተዋልም፡፡ ህዝብ በሀገሬ... የፖለቲከኞች ንግግር ማሳመሪያና ቁማር መጫዎቻ ሲሆን እንጂ ሃያልነቱን ተጠቅሞ ፖለቲከኞችንና አምባገነን መሪዎቹን ሲገራ፣ አደብ ሲያሲይዝና በልዕልናው ተመክቶ አንገቱን ቀና አድርጎ ሲንጎማለል ማየት ብርቅ ነው፡፡

በየመድረኩ የሚናገረው፣ በየጋዜጣውና መጽሔቱ የሚጽፈው ወገኔም እንደመሪዎችና ፖለቲከኞች ባይሆንም የህዝብን ሃያልነትና ልዕልና ሲደሰኩር ይሰማል፤ ክፍተቱን አድበስብሶ በማለፍም ጊዜያዊ ሙገሳ ያተርፍበታል፤ ግልብ «ጨዋነቱንም» ያሳይበታል፡፡ እናም ህዝብን ማሞካሸት እንጂ መተቸት እንደ ነውር የተቆጠረ ይመስል እምብዛም ደፍሮ ህዝብ ሲሳሳት በህዝቡ ላይ ትችት አቅራቢ አይደመጥም፡፡ ይህም የሆነው ህዝብ አይሳሳትም ከሚል የተሳሳተ አመለካከት የመነጨ ሳይሆን አይቀርም፤ ምክንያቱም ህዝብ ስለሆነ ብቻ የሚሰራው ሁሉ ልክ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ፡፡ 
ለመሆኑ ህዝብ አይሳሳትም እንዴ? አንተ ህዝብ ሆይ ልዕልናህና ሃያልነትህ ለፍትህ ወይስ ለግፍ? እውነትህስ የቱ ነው....ዝምታህ ወይስ ጩኸትህ....ምሬትህ ወይስ ሳቅህ....መለያየትህ ወይስ አንድነትህ? በደምሳሳው «ህዝብ እኮ ነው!» እያለ የሚያሞካሽህ እውነትነት አለው ወይስ....? እስኪ እኛም ዛሬ ስምህን ተውሰን ስለአንተ ለማውራት «ህዝብ እኮ ነው» እንበል፡፡

ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ንጉሰ ነገስት ኅይለ ስላሴ የጦርነቱን አዝማሚያ ካጤኑ በሗላ ሀገር ጥለው ሲሄዱ «ንጉሰ ነገስቱ ከዳተኛ ናቸው... ንጉሰ ነገስቱ ፈሪ ናቸው፤ እንደ አፄ ቴወድሮስ በጀግንነት ጦር ሜዳ መሞት ይሻላቸው ነበር...ሀገርን ለጠላት አስረክበው ሄዱ» ያለው ህዝብ እኮ ነው፡፡ ያ የእብሪተኞች ጦርነት በጀግኖች አርበኞችና በእንግሊዝ ጦር ድጋፍ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ንጉሰ ነገስቱን «ድል አድራጊው ንጉሳችን» እያለ ከስደት መልስ እያሞካሸ የተቀበላቸው... ንጉሱ እንደ በላይ ዘለቀ አይነት ስመጥር አርበኞችን እንደ ወንበዴ በስቅላት ሲገድሏቸው «ግርማዊነትዎ ልክ ነዎት....ሺህ ዓመት ይንገሱ» እያለ እግራቸው ጫማ ስር ይደፋ የነበረው ህዝብ እኮ ነው፡፡

ይህ ነው ታዲያ የአንተ ፍትህ? ኦ! ለነገሩማ ህዝብ እኮ ነው!

መንግስቱ ንዋይና ግርማሜ ንዋይ በንጉሰ ነገስቱ ላይ መፈንቅለ መንግስት ሲያደርጉ «እሰይ አበጃችሁ... ከጎናችሁ ነን» ብሎ አደባባይ የወጣው ህዝብ እኮ ነው፡፡ ታዲያስ፣ መፈንቅለ መንግስቱ ከሽፎ ሁለቱ ወንድማማቾች እርምጃ ሲወሰድባቸው «እኒህ ወንበዴዎች ይሰቀሉ፣ ይሙቱ፣ ዙፋንዎን ደፍረዋልና ቅጣት ይገባቸዋል....ንጉስ ሆይ እንዴት ቢደፍርዎት ነው! አይቀጡ ቅጣት ይቅጧቸው...» ያለውም ህዝብ እኮ ነው፡፡

ታዲያ ህዝብ አይሳሳትም እንዴ?

ፕሬዚደንት መንግስቱ ኅይለማርያም ከ«ኢትዮጵያ ትቅደም!» መፈክራቸው ጋር ወደ ስልጣን ወጥተው እኒያን «ሽማግሌ ንጉስ» በቁጥጥር ስር አውለው ከትንሽ ቆይታ በሗላ ሲገድሏቸው «ጎበዝ የህዝብ ልጅ መንጌ....እኒህን አድሃሪ ልክ አስገባልን!» እያለ ያወደሰው ህዝብ እኮ ነው፡፡ ስልሳዎቹን የንጉሰ ነገስቱ ባለስልጣን የነበሩትን መንግስቱ ኅይለማርያም ሲፈጃቸው ወይም ሲያስፈጃቸው ዝም ጭጭ ያለውም ህዝብ እኮ ነው፡፡ አክሊሉ ሀብተወልድን የመሳሰሉ ለሀገር ከፍ ያለ ዋጋ የከፈሉ ሰዎች በወታደራዊ እርምጃ «የአብዮቱ ጠንቅ ናቸው» ተብለው ሲገደሉ ህዝብ ምን አለ? ጭጭ!

ምን ይሄ ብቻ.... በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ጦር አንስተው ጠብመንጃ አንግበው ደርግን መዋጋት የጀመሩትን ታጋዮች ደርግ ወንበዴ ሲላቸው ተከትሎ «ወንበዴ፣ ገንጣይ፣ አስገንጣይ...» እያለ መፈክር ያሰማው ማን ነበር፤ ህዝብ አይደለምን? ወንበዴ የተባሉት ታጋዮች ድል እየቀናቸው ወደ መሐል ሀገር ሲመጡ «ታጋይ የህዝብ ልጅ...»ን የዘመረ ህዝብ እኮ ነው፡፡ ወንበዴዎች እያለ ለተቃውሞ ሰልፍ የወጣው ህዝብ አይደለም እንዴ ድል አድራጊነታቸው እውን እየሆነ ሲመጣ «ጅግኖች! እንኳን ደህና መጣችሁልን» ብሎ የድጋፍ ሰልፍ ያደረገው! የታጋዮችን ጠብመንጃ በእጁ እየጠቆመ...መኪኖቻቸው ላይ ዘሎ ጉብ እያለ አሸወይናዬ፣ አሸንዳየ፣ ሻደይ፣ አያ ሆሆ፣ ሰለሜ....የጨፈረው ህዝብ እኮ ነው፡፡
ታዲያ ህዝብ ወረተኛ አይደለምን?

ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ብቅ ብሎ «ነፍጠኛ፣ ጠባብ፣ አድሃሪ፣ የድሮ ስርዓት ናፋቂ ወዘተ» እያለ በቡድን ከፋፍሎ ተለጣፊ ስም ሲሰጥ የመሪውን አፍ ተከትሎ ስድቦችን ዜማ የሰጣቸው ህዝብ እኮ ነው፡፡ ሰንደቅ አላማህ «እራፊ ጨርቅ ነው!» ሲባል አሜን ብሎ የተቀበለው ህዝብ አይደለምን የሰንደቅ አላማን ቀን አክብር ሲባል ግልብጥ ብሎ የሚወጣው? መለስ ዜናዊን ትናንት «ሐገርን የሸጠና ያስገነጠለ...ኤርትራን አሳልፎ የሰጠ....ወደብ አልባ ያደረገን» ሲል የነበረውና አሁን «ባለራዕዩ መሪ....የክፍለ ዘመኑ ምርጥ መሪ....አባይን የደፈረ መሪ... የአፍሪካ ድምጽ የነበረ...» እያለ የሚያሽሞነሙነው ህዝብ እኮ ነው፡፡ ነገስ ምን ይላቸው ይሆን?

ትናንት «ማንዴላችን ነህ.... የህዝብ አለኝታ ነህ....የቁርጥ ቀን ልጅ ነህ» እያለ ያወደሰውን ዛሬ «ከዳተኛ ነህ...እንዲያውም ክህደቱ ብለንሃል» ያለውም ህዝብ እኮ ነው፡፡ ዛሬ ቅንጅትን ደግፎ መስቀል አደባባይን ያጥለቀለቀው ህዝብ አይደለምን በሚቀጥለው ቀን ኢህአዴግን ብሎ ቦታ ያጣበበው፤ ትናንት «እውነተኞቹ የኢትዮጵያ መሪዎች እናንተ ናችሁ... በአቶና በወይዘሮ መመራት ሰለቸን» ያለው ህዝብ እኮ ነው ዛሬ «አተራማሾች፣ የህዝብን ድምፅ የሻሩ፣ የአሜሪካ ጉዳይ አስፈጻሚዎች፣ የስልጣን ጥመኞች...» እያለ ወደ እስር ቤት የሸኛቸው፡፡

የቅንጅት መሪዎች በ«ይቅርታ» ከእስር ቤት ሲለቀቁ «አወይ የመንግስት ሆደሰፊነት....አወይ የኢህአዴግ ይቅር ባይነት....አወይ የዚህ ስርዓት ለዴሞክራሲ መጎልበት ያለው ቁርጠኝነት...» እያለ በተቃራኒው ታስረው በተለቀቁ የፖለቲካ መሪወችና የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች ላይ የተሳለቀው ህዝብ እኮ ነው፡፡ በሗላስ «ይቅርታ አልጠየኩም» ብላ ድጋሜ በመንግስት ወደ ወህኒ ቤት የተወረወረችውን ፖለቲከኛ ጉዳይ በዝምታ ያለፈው ህዝብ አይደለምን?

ታዲያ ህዝብ ልጁን አሳልፎ የሚሰጥ ግዴለሽ አይደለምን!

ትናንት በሚሰጣቸው ጥልቅ ትንታኔዎች የተመሰጠ፣ በድፍረቱ የተደመመ፣ ህዝባዊ ወገንተኝነቱን የመሰከረለት፣ ሙያውን ያፈቀረለት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በመንግስት «አሸባሪ» ተብሎ ሲታሰር አፉን የከደነው ጆሮውን የደፈነው ህዝብ እኮ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ ልጁን እየሳሳና እየናፈቀ በእስር ሲለየው ህዝብ ምን አለ? ምንም፡፡ ትናንት «ቆፍጣናውና ወጣቱ ትንታግ ፖለቲከኛ ይህ ነው» እያለ ያሞካሸው የነበረው ህዝብ ዛሬ ለአንዱዓለም አራጌ ፍቅሩን በምን ገለፀለት? ኢህአዴግን ተከትሎ «አሸባሪ» በማለት?!

አሁንም ህዝብ እኮ ነው እንበል አይደል!

ትናንት የሐይማኖት ነጻነት ይከበር ዘንድ ይታገል የነበረው ህዝብ ዛሬ «መንግስት በሐይማኖታችን ጣልቃ መግባቱን ያቁም» ብለው በሰላማዊ መንገድ ጥያቄያቸውን ላሰሙ ሙስሊሞች ቀሪው ህዝብ ምን አይነት ወገንተኝነቱን አሳያቸው? በተቃራኒ ወገን ተሰልፎ «መንግስት አክራሪዎችን ይሰርልን» ከማለት ውጭ ምንም ያልፈየደው ህዝብ እኮ ነው፡፡ በሐይማኖት ልዩነት እከል አይገጥመውም የተባለውን ወሎን የሚንጠው ሰልፍ ጥያቄው ምንኛ ነው? እውነት ወሎ ላይ አሸባሪ አሸበረ?!

በየጊዜው ህዝቡ የመረጃ ጥሙን ይቆርጥበት ዘንድ ዘወትር የሚታትሩ ጋዜጦችና መጽሔቶች በሰበብ አስባቡ በኢህአዴግ መንግስት ሲዘጉ፣ ሲከረቸሙ ዝም ጭጭ የሚለውና ዝም እንዳለ ያለው ህዝብ እኮ ነው፡፡ መንግስት እንደፈለገ ለማንሸዋረር የሚመቹትንና «ከህገ መንግስቱ ጋር የሚጋጩ አዋጆች»ን እያወጣ የዓይናቸው ቀለም የደበረውን ሁሉ ሲያስርና ሲፈታ፣ ከአገር ሲያባርርና ሲሰውር «እሰይ ኢህአዴግ ደግ አደረገ» የሚለውም እኮ ህዝብ ነው፡፡

እውነትም ደራሲ ከበደ ሚካኤል ወዶ አልነበረም ህዝብን በአንድ ወቅት አምርሮ የወቀሰው፤ እንዲህ ሲል፣ «...ምን ጊዜም ቢሆን ሕዝብ ማለት እውር፣ የማያመዛዝን፣ ወረተኛ፣ ጊዜ የሰጠውን ብቻ ደስ ለማሰኘት የተዘጋጀ ነው፡፡» 

ታዲያስ፣ ህዝብ እኮ ነው! «አንቺ ወረተኛ ወረት የለመድሽው...» ነው ያለው ዘፋኙ?

No comments:

Post a Comment