Wednesday, August 21, 2013

ሰማያዊ ፓርቲ ሕዝባዊ ስብሰባ እንዳላደርግ አዳራሽ ተከለከልኩ አለ

“ግጭት አፈታት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ የውይይት ሃሳብ ያቀርባሉ
በዘሪሁን ሙሉጌታ

ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የመብራት ኃይል አዳራሽና በምኒልክ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አዳራሾች ውስጥ ሕዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ ቢያቅድም ማድረግ አለመቻሉን ፓርቲው አስታወቀ።
የፓርቲው የህግ ጉዳይ ኃላፊ ወጣት ይድነቃቸው ከበደ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፀው ፓርቲው በመጪው እሁድ በመብራት ኃይል አዳራሽና በምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አዳራሽ ጥያቄ አቅርቦ የአዳራሾቹ ባለቤቶች ፓርቲው ስብሰባ ለማካሄድ ከአዲስ አበባ አስተዳደር የፈቃድ ደብዳቤ እንዲያመጣ ሲጠይቁ የአዲስ አበባ አስተዳደር በበኩሉ ለአዳራሽ የከፈላችሁበትን ደረሰኝ አምጡ በማለቱ ቢሮክራሲያዊ በሆነ መንገድ አዳራሾቹን መከልከሉን ተናግረዋል።
“ወደ አዳራሾቹ ባለቤት ሄደን ክፍያ ልንፈፅም ስንል ፈቃድ አምጡ ይሉናል። ከአዲስ አበባ አስተዳደር ደግሞ ፈቃድ ስንጠይቅ የተዋዋላችሁበትን ደረሰኝ አምጡ በማለት አጉላልተውናል” ያለው ወጣት ይድነቃቸው በግል የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የሆኑትን አቶ አባተ ስጦታውን ቢያናግሩም ፈቃዱ ሊሳካ አልቻለም ብሏል።
በተያያዘ ፓርቲው ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ የእውቅና ደብዳቤ ማስገባቱንና ሰልፉን ሊያደምቁ የሚችሉ ልዩ ልዩ ቅድመ ዝግጅቶች እያካሄዱ መሆኑን ከወጣት ይድነቃቸው ገለፃ መረዳት ተችሏል።
በሌላ በኩል ፓርቲው ቀበና በሚገኘው ጽ/ቤቱ በየሳምንቱ እሁድ ምሁራንን እየጋበዘ የሚያደርገውን ውይይት በመቀጠል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መምህር የሆኑትን ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬን በመጋበዝ “የግጭት አፈታት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በቀጣይ እሁድ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ ፓርቲው ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መረጃ አመልክተዋል።
ዶ/ር በቃሉ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ሲሆኑ በሳይኮሎጂና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሁለት ማስተርስ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በትምህርት (Education) የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በቋንቋና ስነልቦና የፒኤች ዲግሪ አላቸው። ከአስር ዓመት በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማስተማር ላይ ይገኛሉ።

No comments:

Post a Comment