Monday, August 26, 2013

በሚኒሶታ ለአባይ ቦንድ ሽያጭ የተጠራው ስብሰባ ሳይጀመር ተበጠበጠ

21
(ዘ-ሐበሻ) በሴንት ፖል ሚኒሶታ የአባይን ቦንድ ለመሸጥ የኢትዮጵያ መንግስት አዳራሽ ተከራይቶ ለዛሬ ኦገስት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ከ ቀኑ 2 ሰዓት እስከ ምሽቱ 8 ሰዓት ስብሰባ የጠራ ሲሆን ስብሰባው ከመጀመሩ አንድ ሰዓት በፊት ብጥብጥ ተነሳ።
በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን “ወያኔን አናምንም፤ 2 ሰዓት ብሎ ጠርቶ ስብሰውን ቀድሞ ሊጀምርና ሊነሳበት የታቀደውን ተቃውሞ ሊያከሽፍ ይችላል” በሚል ገና ከጠዋቱ ስብሰባው ይደረግበታል የተባለበት አዳራሽ በር ላይ ሲጠባበቁ ቆይተዋል። ልክ ስብሰባው ሊጀመር 1 ሰዓት ሲቀረው አንድ የስርዓቱ ደጋፊ የሆነ ሰው ካሜራ ይዞ “ከአባይ በፊት ሰብአዊ መብት ይከበር፤ የታሰሩት ይፈቱ” በሚል ለተቃውሞ የተሰባሰበውን ሕዝብ ሊቀርጽ ሲጠጋ ሕዝቡ “ሃገር ቤት ቪድዮ የቀረጻችሁት ሳያንስ እዚህ ልትቀርጹ ነው ወይ?” በሚል ልጁን ክፉኛ ከደበደቡት በኋላ ካሜራውን ሰባብረውበታል ያሉት የአይን እማኞች ወዲያውም ከ20 የሚበልጡ የሴንት ፖል ከተማ ፖሊስ መኪናዎች አካባቢውን በመክበብ ብጥብጡን አርግበውታል።

የሴንት ፖል ፖሊሶች መቃወም ትችላላችሁ፤ ሆኖም ግን ሰውን መደብደብ አግባብ አይደለም በሚል ለተቃውሞ የተዘጋጁትን ሲበትኑ ሕዝቡም “በአባይ ስም የሚደረገው ሕገወጥ ስብሰባ ነው” በሚል ለፖሊስ በማመልከታቸው ፖሊስም የቦንድ ሽያጩ አይደረግም ሲል ቃል ገብቷል።
ሕዝቡ ፖሊስ የቦንድ ሽያጩ ተሰርዟል ቢላቸውም ማረጋገጫ የለንም በሚል በአካባቢው የሚገኝ ሲሆን ብጥብጡን ተከትሎ በሴንት ፖል ፖሊስ ታስረው የነበሩት ኢትዮጵያውያን ወዲያው ተለቀዋል።
የኢሕአዴግ መንግስት በሚኒሶታ የአባይ ቀን በሚል ቦንድ ለመሸጥ የተከራየው የላኦ ኮምዩኒቲ አዳራሽ አድራሻ 320 University Ave W St Paul, MN 55103 ነው።
ዘ-ሐበሻ ተጨማሪ መረጃዎችን ከፎቶ ግራፍ እና ቪድዮዎች ጭምር ይዛ ትመለሳለች።
ይጠብቁን፤ ይመለሱና ይመልከቱን።

No comments:

Post a Comment