(ዘ-ሐበሻ) የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ዛሬ እንደዘገበው “አክራሪዎች በእምነት ስም የህዝብን ሰላም ለማደፍረስ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በመቃወም እሁድ ነሃሴ 27/2005 ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለፀ” ብሏል። በሌላ በኩል ድምጻችን ይሰማ “አክራሪነትን ለመዋጋት ተብለው በተዘጋጁ ስብሰባዎች ጸረ እስልምና የሆኑ ዘለፋዎች እተበራከቱ ነው!” ሲል ተቃውሞውን አሰማ።

“ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በእምነት ስም የሀገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ ጥረት የሚያደርጉ አካላትን በመቃወም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰልፍ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡” ሲል የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሲዘግብ ድምጻችን ይሰማ በበኩሉ “መንግስት አክራሪነትን ለመዋጋት በሚል እያዘጋጃቸው ባሉ ስብሰባዎች የእስልምና ሃይማኖት ላይ ዘለፋዎች እየተሰነዘሩ ነው፡፡ በየክፍለ ከተማውና ወረዳዎች ለካድሬዎች እና የሀይማኖት አባቶች ተብለው በሚካሄዱ ስብሰባዎች ‹‹የእስልምና ሃይማኖት የአክራሪዎች መፈልፈያ ነው››፣ ‹‹እስልምና የሚባል ነገር ነው ሰላም የነሳን›› ከሚሉ ተነስቶ ሌሎችም በርካታ ስድቦች እና ዘለፋዎች እየተንጸባረቁ ነው፡፡ በተለይ ባለፈው ረቡእና ሐሙስ የአዲስ አበባ ፍትህና ጸጥታ ቢሮ ባዘጋጀውና በስድስት ኪሎ ስብሰባ ማእከል በተደረገው ስብሰባ ሲንጸባርቅ የነበረው ስሜት ሕዝቡ ያወረዳቸው የመጅሊስ ሹመኞችን ጨምሮ ኢማሞችን ሁሉ አንገት ያስደፋ እንደነበር ታውቋል፡፡ ብዙዎችንም የመንግስትን አካሄድ በድጋሚ እንዲያጤኑት የጋበዘ ሆኗል፡፡” ብሏል።

ድምጻችን ይሰማ በበኩሉ “በዚህ በቢሮ ሀላፊው አቶ ጸጋዬ ሀይለማርያምና በደህነነት መስሪያ ቤት ሀላፊዎች በተመራው ስብሰባ የተገኙና ቀድመው ንግግር የሚያደርጉበት አጀንዳ የተሰጣቸው የፓርቲ ካድሬዎች በከፍተኛ ሁኔታ የእስልምናን ሃይማኖት የሚያራክሱ ንግግሮች ሲያደርጉ ከመታየታቸውም በላይ አንዳንዶች ለእስልምና ያላቸውን ጥላቻ ከመግለጽ ጭምር አንኳ አልተቆጠቡም፡፡ የሱና ምልክት የሚንጸባረቅባቸው አካላትን መንግስት ሊታገላቸው እንደሚገባ ያሳሰቡት እነዚህ ካድሬዎች የእስልምና ሃይማኖት መንፈሳዊ ተግባራትን ሁሉ የአክራሪነትና አሸባሪነት መገለጫዎች አድርገው ሲፈርጇቸው ተደምጧል፡፡ አቶ ጸጋዬ ኃይለማርያም ከመንግስታዊው ሃይማኖት የማጥመቅ ዘመቻ ጀምሮ ሙስሊሙን ህብረተሰብ ሲዘልፉና በሙስሊሞች መካከል የልዩነት እሾህ ለመትከል ሲሯሯጡ የቆዩ ግለሰብ እንደሆኑ በድምጽ ማስረጃ ጭምር መጋለፁ ይታወሳል፡፡” ብሏል።
Short URL: http://www.zehabesha.com/amharic/?p=6736
No comments:
Post a Comment