ህወሓትን ለመጥቀስ ‘ወያኔ’ የሚለው ቃል ተጠቅሜ አላውቅም። ከወራት በፊት ታድያ ለምን ‘ወያነ’ የሚል ቃል እንደማልጠቀም አንድ የፌስቡክ ጓደኛዬ በውስጥ መልእክት ልኮልኝ ነበር። በሆነ ምክንያት መልስ አልሰጠሁም ነበር።
አሁን ግን ትንሽ ልበል። ምክንያቱም ከሁለት ቀናት በፊት ከዞን ዘጠኝ አባላት (ጓደኞቼ) በአካል ተገናኝተን ‘ወያነ’ ስለሚለው ቃል ተጫውተን ነበር። ርእሰ ጉዳዩ ‘የህወሓት /ኢህአዴግ መንግስት ወያነ እንዲባል አይፈልግም፤ ወያነ ብለው ለሚፅፉ ወይ ለሚናገሩ ሰዎች በተለየ ሁኔታ ይጠምዳል’ የሚል ነበር።
እኔ ግን በዚህ ሓሳብ በከፊል አልስማማም። ምክንያቱም ህወሓቶች ‘ወያነ’ የሚል ስም አይጠሉትም። የሚኮሩበት ስማቸው ነው። ‘በህወሓት ምትክ ‘ወያነ’ የሚል ቃል የሚጠቀሙ ዜጎች በጥቁር መዝገብ ውስጥ ይገባሉ’ በሚል ግን እስማማለሁ። ምክንያቱም አንድ ሰው ህወሓትን በመጥፎ ለማንሳት ፈልጎ ‘ወያኔ’ የሚል ቃል ሲጠቀም የህወሓት መሪዎች ሁለት ነገሮች ይገነዘባሉ።
(አንድ) ያ ‘ወያኔ’ የሚል ቃል የሚጠቀም ሰው ከትግራይ አለመሆኑ ይገነዘባሉ። ምክንያቱም ከትግራይ ከሆነ ትግርኛ ቋንቋ ይችላል። ትግርኛ ከቻለ ‘ወያነ’ የሚለው ቃል ትርጉሙ ያውቃል። የወያነ ትርጉም ካወቀ ህወሓትን ለመስደብ ‘ወያነ’ የሚል ቃል መጠቀም አይችልም። ምክንያቱም ‘ወያነ’ የትግርኛ ቃል ሲሆን ትርጉሙ ‘አብዮተኛ፣ ለጭቆና የማይምበረከክ፣ መንግስትን ለመቃወም ድፍረት ያለው፣ የማይፈራ፣ ጨቋኝ ስርዓት ለመጣል የሚታገል’ ማለት ነው።
ስለዚህ ‘ወያነ’ የሚለው ቃል ስድብ ወይ አፀያፊ ቃል አይደለም። ለዚህ ነው ትግርኛ ተናጋሪዎች ለህወሓት ወያነ ብለው መሳደብ የማይችሉት። ምክንያቱም ‘ወያነ’ ካሉ እያሞካሹ እንጂ እየተሳደቡ አይደሉም።
(ሁለት) ህወሓትን ለመንቀፍ ወይ ለመቃወም ‘ወያነ’ የሚል ቃል የሚጠቀሙ ዜጎች በህወሓትኛ አተረጓጎም ‘ፅንፈኛ ተቃዋሚዎች’ ተደርገው ይወሰዳሉ። ህወሓትም ለስልጣኑ ሲል እነኚህ ሰዎች በልዩ ሁኔታ ይጠምዳቸዋል። ምክንያቱም ‘ወያነ’ ካሉ ለህወሓት ልዩ ጥላቻ እንዳላቸው ይረዳል። ህወሓት ወያነ እንዲባል ስለማይፈልግ ግን አይደለም።
‘ወያነ’ የሚል ቃል የትግርኛ ቋንቋ አንድ አካል እንጂ ለህወሓት ብቻ የተሰጠ ስም አይደለም። በቋንቋው መሰረት ጭቆናን ለማስወገድ የሚታገል ሁሉ ወያነ ተብሎ ይጠራል። ህወሓቶች በትግሉ ወቅት የትግራይን ህዝብ ለማነሳሳት የተጠቀሙት ዋነኛ ቃል ‘ወያነ’ ነው። ወያነ ስትባል የተለየ የጀግንነት ስሜት ይሰማሃል። በዚህ መሰረት ‘ወይን’ እያሉ ብዙ ሰው ከጎናቸው ማሰለፍ ችለው ነበር።
ለዚህ ነው ህወሓትን ለመሳደብ ወያነ የማልለው። (1) መሳደብ አያስፈልግም (2) ‘ወያነ’ የሚል ቃል ለማወደስ እንጂ ለመውቀስ እንደማይሆን ጠንቅቄ አውቃለሁ። ለህወሓት ‘ወያነ’ ብዬ ከጠራሁት እያወደስኩት ነው። ይህ ደግሞ ፍፁም አላደርገውም። ምክንያቱም (አንድ) ህወሓት የሚወደስ ተግባር አላየሁበትም፤ (ሁለት) ህወሓት ወያነ እንዳልሆነ ስለተገነዘብኩ ነው።
ህወሓት ወያነ አይደለም። እንዴት? በትጥቅ ትግሉ ወቅት የትግራይ አርሶ አደሮች ፀረ ጨቋኝ ስርዓት ተነስተው ያለ ምንም ፍርሓት አብዮታዊ እርምጃ ሲወስዱ ‘ወያነ’ የሚል ማዓርግ አግኝተው ነበር። ይገባቸዋል። አዎ! እነሱ ትክክለኛ ወያነ ነበሩ። ለነሱ ወያነ ብዬ ማወደስ እችላለሁ። ምክንያቱም መስፈርቱ ያሟላሉ። ለውጥ ፈልገው ፀረ ገዢዎች የሚታገሉ አርበኞች ነበሩና።
የአሁኑ ህወሓት ግን ወያነ አይደለም። ምክንያቱም ገዢውን መደብ ለመጣል በትግል ላይ ያለ የአርበኞች ስብስብ አይደለም። የደርግን ስርዓት ከተገረሰሰ ወዲህ ህወሓት ነፃ አውጪ ግንባር ሳይሆን ራሱ ገዢ መደብ (ገዛኢ ደርቢ) ነው። ወያነ የሚባል ግን ገዢውን መደብ ለመጣል የሚታገል ነው። ስለዚህ ህወሓት ወያነ አይደለም፤ ገዢ መደብ ነው። ለገዢ መደብ ወያነ አይባልም።
ህወሓት (ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ) የአንድ ነፃ አውጪ ቡድን ስም ነው። የድሮ ስም ነው። ስሙ ስልጣን ለመያዝ የትጥቅ ትግል የሚያካሂድ ቡድን ይወክላል። የአሁኑ ህወሓት ግን ስልጣን ለመያዝ የሚታገል ቡድን ሳይሆን ገዢ መደብ ሆነዋል። ስለዚህ ስሙ ተግባሩና ደረጃው አይወክልም። ስልጣን ከያዘ ወዲህ ስሙ መቀየር ነበረብት። ግን ለምን የድሮ ስሙ ይዞ መቆየት መረጠ? ይቺ ‘ወያነ’ የምትለዋን ህዝብ ለመቀስቀስ የምታስችል ወኔ የምታላብስ ስም ላለማጣት ፈልጎ ነው። ስለዚህ ህወሓቶች ወያነ የሚል ስም አይጠሉትም፤ እንደውም ይወዱታል።
ግን ህወሓት ምንድነው? አማርኛ የለውም እንዴ? አማርኛ ተናጋሪዎችም ህወሓት ይላሉ። በእንግሊዝኛስ ምንድነው? ህወሓት አወቃቀሩም ቃሉም ትግርኛ ነው። ‘ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ’ ይወክላል። ወደ አማርኛ ሲመለስ ‘ የትግራይ ህዝብ አብዮታዊ ነፃ አውጪ’ እንድ ማለት ነው። ይሄው እስካሁን ነፃ አውጪ! እስካሁን ተፋላሚ፣ ተዋጊ ቡድን። በተግባር ግን ገዢ መደብ።
ሌላው የሚገርም ነገር የፓርቲው የትግርኛና የእንግሊዝኛ ስም የተለያየ መሆኑ ነው። በትግርኛ ህወሓት (ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ) ወይ በአማርኛ (የትግራይ ህዝብ አብዮታዊ ነፃ አውጪ) ሲሆን በእንግሊዝኛ ግን TPLF (Tigray People’s Liberation Front)። TPLF (Tigray People’s Liberation Front) ወደ ትግርኛ ሲመለስ ‘ግንባር ሓርነት ህዝቢ ትግራይ’ (ግሓህት) ወይ በአማርኛ ‘የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር’ (ትህነግ) ይሆናል። ህወሓት ወደ እንግሊዝኛ ሲመለስ ደግሞ ‘Tigray People’s Revolution for Liberation’ ይሆናል። ስለዚህ ምስቅልቅሉ የወጣ ስም ነው።
ባጠቃላይ የገዢው ድርጅት ስም ‘ህወሓት’ መሆን የለበትም። ምክንያቱም ግንባር አይደለም። ግንባር ስልጣን ለመያዝ የሚታገል ድርጅት ያመለክታል። ህወሓት ደግሞ ስልጣን ይዟል። ህወሓት ወያኔ መባል የለበትም። ምክንያቱም ወያነ አይደለም፤ ገዢ መደብ ነው።
‘ወያነ’ ብዬ የምለው ነፃነታቸውን ለመጎናፀፍ የፖለቲካ ለውጥ በመሻት ሰለማዊ የስልጣን ሽግ ግር እውን እንዲሆን ሙሉ ወኔ ተላብሰው በጀግንነት ለሚታገሉ ጓደች ነው።
ህወሓት ወያነ አይደለም።
(ግን ስም’ኮ የፈለገው ቢሆን መጥርያ እንጂ ምንም አይደለም።)
No comments:
Post a Comment