Friday, August 23, 2013

አምስተኛው ባርነት – ከፋሲል የኔዓለም(ጋዜጠኛ)

በጥንቱ ስርዓት፣ አንድ ሰው ከአራቱ በአንዱ መንገድ
ባሪያ ይሆናል። የመጀመሪያው በጦርነት ተሸንፎ
ከተማረከ ፣ ሌላው እዳውን መክፈል አልችል ብሎ በእዳ ከተያዘ ፣ ሶስተኛው ከባሪያ ቤተሰብ የተወለደ ከሆነ በውርስ፣ አራተኛው ደግሞ ባሪያ ፈንጋዮች ይዘው ከሸጡት ነው። በዚህ ዘመን የባሪያ ንግድ ቢጠፋም፣ ባርነት ግን አልጠፋም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዲያውም አምስተኛውን የባርነት መንገድ እያየን ነው፤ ይሄ ባርነት በባህሪው እስከዛሬ ከታዩት ሁሉ የተለየና አስገራሚም ነው እመለስበታለሁ።

ባሪያ ማለት፣ የጌታውን እጅ አይቶ የሚያድር፣ በራሱ
ነጻነት የሌለው፣ ሰምቶ የመቀበል እንጅ ሰምቶ
የመመለስ መብት የሌለው፣ በግዑዝና በነጻ-ሰው መካከል ያለ ፍጥረት ነው። ባርያ ሰውን ሰው የሚያደርገውን ነጻነት ሙሉ በሙሉ የተገፈፈ በመሆኑ፣ ከሰው ተርታ የሚመደበው ስለሚመገብ፣ ስለሚለብስ፣ መጠለያ ስላለው፣ ቋንቋ ስለሚጠቀም እና አውራጣት ስላለው ብቻ ነው፤ ከዚያ በተረፈ ግን የጭነት እንስሳ ማለት ነው።ባሪያ በእግዚአብሄር አምሳል በመፈጠሩ ክፉና ደጉን የመለየት ስልጣን ቢሰጠውም ፣ ስልጣኑን በጌታው በመነጠቁ፣ሁልጊዜ የጌታውን ደግ ነገር ብቻ እያየ እና እያመሰገነ የሚኖር ፍጥረት ነው።

በአሁኑ ጊዜ የሚታየው አምስተኛው የባርነት መንገድ
40 በ60 ከሚባለው የቤት ግንባታ ጋር የተያያዘ ነው፤ በዚህ የባርነት መንገድ ለመጓዝ የወሰነው ደግሞ
ዲያስፖራው ( በውጭ የሚኖረው) ኢትዮጵያዊ ነው። መንግስት ለዲያስፖራው 40/በ60ን ሲያዘጋጅ ሁለት አላማዎችን ታሳቢ አድርጎ ነው- ዲያስፖራው ጥሮ ግሮ ያገኘውን ሀብት ሰብስቦ ደቋናውን ለመሙላት እና ዲያስፖራው ስለነጻነቱ እንዳይጠይቅ ወይም መንግስትን እንዳይቃወም አፍ ለማዘጋት።
40 /በ60 የተመዘገበ ዲያስፖራ እናት እና አባቱ፣
እህትና ወንድሙ፣ በአጠቃላይ የአገሩ ሰዎች ቢገደሉ፣
ቢታሰሩ ፣ ቢሰደዱ፣ ቢራቡ ፣ ቢጠሙ፣ ” ለምን?” ብሎ አደባባይ ወጥቶ የመጠየቅ እና የመቃወም ነጻነት
አይኖረውም፤ ነጻነቱን በ40/በ60 ተገፎአል።ለሌላው
መብት ሊሟገት ቀርቶ፣ በጥፊ ቢመታም እንኳን፣ “ጥፊው እንዴት ይጣፍጣል፣ እባክህ ግራ ጉንጨንም ድገምልኝ” ከማለት ውጭ፣ “ለምን ትመታኛለህ?’ ብሎ የአባትና እናቱን ወኔ ቀስቅሶ ብድሩን የመመለሻ ልብ አይኖረውም።

እስክንድር ነጋ፣ አበበ በለው፣ ብርሀኑ ነጋ፣ እና ሌሎችም፣ ከስጋቸው ድሎት ነጻነታቸውን ያስቀደሙ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ባርነት በቃን በማለታቸው፣ ጥረው ግረው ያፈሩትን ሀብት ተነጥቀዋል።40/በ60 የተመዘገበ ዲያስፖራ ስለወገኑ ለመጮህ ከእንግዲህ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ከተሞች እጅግም አይታይም፣ ለይሉንታ ቢታይ እንኳ ፊቱን በወረቀት ሸፍኖ ከሁዋላ ከመሰለፍ የዘለለ ሚና አይኖረውም።

በነጻነት አገር እየኖሩ ገንዘብ ከፍሎ፣ በፍላጎት
ባርነትን መምርጥ ማለት ይህ አይደለምን? የሚገዛ
የለም እንጅ እነዚህ ሰዎች እኮ መንግስት ቢሸጣቸው
እንኳ ምንም የሚናገሩ አይደሉም። ገንዘብ ተከፍሎ
ባሪያ አድርጉን ብሎ የሚጠየቅበት አሰራር በታሪክ
ታይቶ ይታወቃልን?
በአገር ቤት ያለው ህዝብ ለ 20/በ80 ቢመዘገብ
አይገርመኝም፤ በባርነት ውስጥ የሚኖር ህዝብ
በመሆኑ፣ አንድ ቀን ራሱን ነጻ እስኪያወጣ፣ ለጊዜው
ተመችቶት ይኑር። ባሪያም እኮ ልብሱን ይቀይራል፣
የምኝታውን ሳር ተባይ ሲወርበት በሌላ ሳር ይተካዋል፤ባበርነት ስር ያለው የአገር ቤት ሰው በነፍሱም በስጋውም ሊበደል አይገባውም፤ ቢያንስ እስከ ጊዜው በስጋው ይደሰት። ዲያስፖራው ግን የኢትዮጵያን ምድር ከለቀቀባት ጊዜ ጀምሮ ከባርነት ነጻ ወጥቷልና በነጻነት መኖር የሚችለበት እድል አለው፤ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ነጻነት ለመታገል ሁኔታው ተመቻችቶለታል፤ ይህን ነጻነቱን ግን እራሱ ገንዘብ ከፍሎ ሊሸጠው ይደራደራል። ፍርፋሪ እየተጣለለት ወደ ቄራ የሚወሰድ እሪያ መጨረሻው ሞት እንደሆነው ሁሉ፣ 40/በ60 የተመዘገበ ዲያስፖራም መጨረሻው ባርነት
ነው።
አምስተኛው ባርነት!

No comments:

Post a Comment