Wednesday, August 21, 2013

አምልኮተ መለስና ሌጋሲው…

ግሬስ አባተ
የቀድሞ / በሞት ከተለዩ ወዲህ ቦታውን የተኩት / ኃይለማርያም ደሳለኝ በፓርላማ ቀርበው ‹‹ ከኔ አንዳችም የምጨምረው የምቀንሰው ነገር የለም፡፡ የቀድሞውን / ራዕይ ነው የማስቀጥለው›› ብለው ተናግረዋል፡፡ በርግጥ ግለሰቦች ስለተቀየሩ ብቻ ችግሮች ይፈታሉ የሚል ቅዠት ባይኖረኝም ፤አንድ ግለብ ሲሄድ በዉሃ አጠጣጥ እንኳን እሱን ለመምሰል የሚጥር ግለሰብ ይመጣል የሚል ነገር አልነበረኝም፡፡ እናም የኃይለማርያምን ሁኔታ ሳስበው ግርም ይለኛል፡፡ ራሱን መሆን ሲገባው ባፀደ ስጋ የሌለውን ሰው ለመምሰል መጣሩን ሳይ አሳዝኖኛል፡፡ ነገሮች በደቂቃና በሴኮንድ በሚለዋወጡበት አለም ‹‹ምንም የምጨምረው የምቀንሰው ነገር የለም›› ማለት ምን ማለት ነው? ኃይለማርያም ደሳለኝም ሆነ ሌሎች የሰርዐቱ ሎሌዎች ይህንን መመለስ አይችሉም፡፡ እንግዲህ እንደነዚህ አይነት ግራ የገባቸው ሰዎች ናቸው እየመሩን ያሉት፡፡ለዚህ ይመስላይ / ያቆብ ይህ ስርዐት ለዚህ ትውልድ በምንም መንገድ አይመጥንም ያሉት፡፡

የውሸት ፋብሪካ በሆነው ኢቲቪ የሚስተጋባው ራዕዩን ከዳር ማድረስ ምናምን የሚሉ ፕሮፓጋንዳዎች በዝተዋል፡፡ የአገሪቱ የሁሉም ነገር አድራጊ ፈጣሪ አድርጎ ማቅረብ፤ እንዲሁም ምንም ድጋፍ ያላደረገባቸውን ዘርፎች መለስ ለጥበብ፣ መለስ ለስፖርት ምናም የሚሉ መዘባረቆች እስኪሰለቸን ሰምተናል፡፡ በተግባር ግን ለሚባሉት ዘርፎች ሰውዬው ያበረከከተውን አስተዋፅኦ ስናስብ ከማልማት ማጥፋት የሆነባቸው መስኮች ብዙ ናቸው፡፡ ማን ይህን ይናገር? ማን ይህን ይመስክር?‹‹ መረጃ ሃይል ነው›› የሚባል አባባል አለ፡፡ ውሸት ሲበዛ እውነት ሳይሆን የሚፈጥረው ውዥንብርን ነው፡፡ ገዢዎቻችን ግን ውሸት ሲበዛ እውነት ይሆናል በሚል ብሂል ነጋ ጠባ ውሸትን መንዛት ስራዬ ብሎው ይዘውታል፡፡ ይህም ውዥንብርን ፈጥሯል፡፡


እንድ ግለሰብን እንደዚህ ሰማይ ድረስ አውጥቶ የሁሉ ነገር ፈጣሪ አድራጊ ማድረግ ከአምልኮ ሌላ ምን ይባላል፡፡ ስልጣን ላይ ያሉትስ ሰዎች ፖሊሲ አውጪው መለስ፣ አድራጊ ፈጣሪው መለስ፣ ተሟጋቹ መለስ ማለታቸው ለወደፊት ገዢው ፓርቲው የሚያገኘውን ፖለቲካዊ ጥቅም አስልተው አሁንም አጠናክረው ቀጥለውታል፡፡ እሺ እንደ ወረደ መለስ እነዛን ሁላ ነገሮች ሰርተዋል ብለን ብናስብ ሌሎቹ ምን ሲሰሩ ነበር ? / ኃይለማርያም ደሳለኝም ስለዚህ ቢጠየቁ አይመልሱም ምክንያቱም ባደባባይ መለስን ስለሚያመልኩ፡፡


አንደኛ የሙት አመቱን አስመልክቶ የተለያየ ነገሮች እየተባሉ ነው፡፡ ከዚህም የአረንጓዴ ልማት የምትለው አንዷናት፡፡ ሰውየው ስለ ካርቦን ልቀት መጠንና ስለአየር ንብረት አፍሪካን ወክሎ ከመከራከሩ ውጪ እስኪ በኢትዮጵያ በደርግ ጊዜ ከነበረው የደን ሽፋን ምን ያህሉ ነው አሁን ያለው? የለም በሚባልበት ሁኔታ አይደለም ያለው? ታድያ ከየት መቶ ነው የሰማይና የመሬት ያህል የሚወራው? የችግኝ ተከላውን አስመልክቶ ሰሞኑን እንድ ያነበብኳት መፈክር እንዲህ ትላለች ‹‹የመለስ ተራሮች በጎርፍ አይሸረሸሩም›› ይላል፡፡ መጀመሪያውኑ ተራሮቹ የመለስ ነበሩ እንዴ? ከዚህ በላይስ አምልኮስ ከየት አለ? ግራ መጋባቱ ቀላል አይደለም፡፡ መለስ አገሬ ብሎ እንኳን የተናገረበትን ጊዜ አላስታውስም፡፡ ታድያ ከየት መቶ ነው ተራራው ወንዙ ሁሉ የመለስ የተደረጉት? ጨርቅ ነው ያለውን ሰንደቅስ ስለምን አብሮት አፈር እንዲገባ ተደረገ? ሰንደቃላማ ሲቀበር ሳይ ይህ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ይህስ ተገቢ ነው? ይህን ያህል ሰዎቹ ግራ ተጋብተዋል፡፡

የምናስቀጥለውስ ራዕይ ምንድን ነው? ኢትየጵያን በዘር ከፋፍሎ አንዱ አንዱን የጎሪጥ እየተያየ እንዲኖር ነው?፣አንባገነንነት በቋሚነት እንዲቀጥል ነው? ሙሰኝነት ህጋዊ እውቅና አግኝቶ እንዲቀጥል ነው? ሃገርን ያለወደብ ማስቀረትን ነው? የሃገርን መሬቶች ለባዕድ አገር መሸጥን ነው? ለውጭ ሃገር ሰዎች ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን እየሰጡ የገዛ አገርን ዜጎች ግን ከሚኖሩበት ማፈናቀልን ነው? ቆይ ታድያ ታድያ የሰውዬው ራዕይ ምንድን ነው? ራዕዩን እናስቀጥላለን ሲሉስ ጎጠኝነትን፣ ከፋፍለህ ግዛን፣ሙሰኝነትን .. ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አይደልም? ወጣቱ ግን ይህን ያደርጋል ማለት ፌዝ ነው፡፡ በተቃራኒው ይህንን አቅማችን በቻለው መጠን ሁሉ እንታገላለን፡፡መሞት ካለብንም እንሞታለን፡፡ይህ እንዲቀጥል በፍፁም አንፈቅድም፡፡

No comments:

Post a Comment