Wednesday, August 28, 2013

ግልጽ ደብዳቤ ለሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት – አማኑኤል ዘሰላም

ለተከበሩ ኢንጂነር ይልቃል፣ ለክቡራን ከፍተኛ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት፣ በቅድሚያ ሰላምታዬ ባላችሁበት ቦታ ይድረሳችሁ! ጤና ይስጥልኝ።
ለሰማያዊ ፓርቲ አድናቆት አለኝ። የግራዚያኒ ሃዉልትን በመቃወም ያደረጋችሁት ሰልፍን ተከታትያለሁ። በብዛት ግን ሰው ያወቃችሁ፣ በአዲስ አበባ በጠራችሁት ሰላማዊ ሰልፍ ነዉ። ያኔ ትልቅ ሥራ ነው የሰራችሁት። አኩርታችሁኛል። ብዙ ደጋፊዎችም በአጭር ጊዜ ዉስጥ አግኝታቹሃል።
ያኔ የጠራችሁትን ሰልፍ አብዛኞቻችን ብንደግፈውም፣ ሌሎች ድርጅቶችን ሳታማክሩ ፣ ሰልፉን በችኮላ መጥራታችሁ ግን ብዙዎችን ደስ አላሰኝም ነበር። ነገር ግን «ማንም ይጥራዉ፣ ማንም ፣ ትግሉን እስከጠቀመ ድረስ መተባበር ያስፈልጋል» የሚል አቋም በርካታ የአንድነት ፓርቲና መኢአድ አመራር አባላት በመያዝ ድጋፍ ሰጧችሁ።
መኢአድ በመግለጫ ድጋፉን ገልጸ። በፓርቲ ደረጃ፣ የሥራ አስፈጸማዊ፣ ምክር ቤቱ ተነጋግሮበት ዉሳኔ ለመወሰን 15 ቀናት በቂ ስላልነበረ፣ በኦፈሴል የአንድነት ፓርቲ ድጋፍ ባይሰጥም፣ የፓርቲዉ አመራር አባላት ግን እንደ ኢሳት በመሳሰሉ ሜዲያዎች በመቅረብ፣ የአንድነት አባላትን ደጋፊዎች በሰልፉ እንዲገኙ፣ ሰማያዊ ፓርቲ ለጠራዉ ሰልፍ ድጋፍ እንዲሰጡ ጥሪ አቀረቡ። በአዲስ አበባ 23ቱም ወረዳዎች የሚገኙ የአንድነት አስተባባሪዎች፣ «የሰማያዊ ፓርቲ የጠራዉ ሰልፍ፣ የኛም ሰልፍ ነው» በሚል በየወረዳዎቻቸዉ ቅስቀሳ ሲያደርጉ፣ መፈክሮችን ሲያዘጋጁ እንደነበረም ታውቃላችሁ። የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባላትም በሰልፉ ተገኝተዋል። አንድነት ፓርቲ፣ እንዲሁም መኢአድ ለሰማያዊ ፓርቲ ሙሉ ድጋፉቸውን በዚህ መልኩ መስጠታቸው ተገቢና አስፈላጊ ነበር።
የአዲስ አበባዉን ሰልፍ ተከትሎ፣ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ፣ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት በሚል መርህ እንቅስቃሴ ጀመረ። በጎንደርና በደሴ ቅስቀሳ ይደረግ በነበረበት ጊዜ፣ የሰማያዊ ፓርቲ፣ ድጋፉን እንዲሰጥና ከጎንደርና ከደሴ ሕዝብ ጎን እንዲሰልፍ አንዳንዶቻችን ጠይቀን። ከአዲስ አበባ ዉጭ ድርጅታዊ አቅም እንደሌላችሁ እናውቃለን። ነገር ግን ቢያንስ ቢያንስ፣ በመግለጫ ደረጃ ሰላማዊና ህዝባዊን ንቅናቄ በመደገፍ ከጎንደርና ከደሴ ሕዝብ ጎን መቆም ይገባችሁ ነበር። ያንን ግን፣ ተጠይቃችሁም እንኳን፣ አላደረጋችሁም። አንድነት ፓርቲ ከእናንተ ጋር አጋር እንደነበረዉ፣ እናንተ ግን ወገናዊ ምላሽ መስጠት ተሳናችሁ። ከጎንደሩና ከደሴዉ ሰል በኋላ በጂንካ፣ በአርባ ምንጭ፣ በባህር ዳር፣ በፍቼ ሰላምዊ ሰልፎች የተደረጉ ሲሆን፣ በመጨረሻዉ ሰዓት ላይ የአንድነት አመራር አባላትን በማሰርና በማንገላታት ከፍተኛ ጫና ሕወሃትና ኦሕድድ በማድረጋቸው ሰልፎቹ ተላለፉ እንጂ፣ በመቀሌና በባሌ/ሮቢ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። በነዚህ ሁሉ ከተሞች የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጹን ለሰላም፣ ለዲሞክራሲን አለነጻነት ሲያሰማ ድርጅታችሁ ድምጹን አጥፍቶ ነበር። በዚህ እዝኜባቹሃለሁ።
የጎንደሩን እና የደሴዉን ሰልፍ ተከትሎ የአንድነት ፓርቲ አዲስ አበባ ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ሊያደርጋቸው ያቀዳቸውን ሰልፎችና ህዝባዊ ስብሰባዎች ለሕዝብ አሳወቀ። በፕሮግራሙ መሰረት፣ ከበርካታ ሰልፎች መካከል ፣ በአዲስ አበባ መስከረም 5 ቀን፣ በአሶሳና ጋምቤላ ነሐሴ 26 ቀን ሊደረጉ የታሰቡ ሰልፎች ይገኙበታል።
ብዙዎቻችንን የገረመን የአንድነት ፓርቲ ሰልፍ እንደሚጠራ ባሳወቀ በሁለት ቀኑ ፣ በችኮላ ነሐሴ 26 ቀን በአዲስ አበባ ሰልፍ እንደምትጠሩ መግለጻችሁ ነበር። እየተደረገ ያለው፣ ትግል እንጂ ጨዋታ እንዳልሆነ በማስመር፣ ሰልፉን ከአንድነት ፓርቲ ጋር እንድታደረጉ ጥያቄ አቀረብንላችሁ። ያ ብቻ አይደለም፣ የፖለቲካ ፕሮግራም ልዩነቶችን ባለመኖራቸው፣ ከአንድነትና ከመኢአድ ጋር መዋሃድ የሚቻልበትን ሁኔታ እንድታመቻቹ አበረታታን።
አንድ የአንድነት ፓርቲ አመራር አባልን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ሳነጋገር «እንኳን ሰልፍ ከነርሱ ጋር ለማድረግ፣ እንደዉም የፖለቲካ ፕሮግራሞቻችን አንድ ናቸው። እንዋሃድ ብለን ጠይቀናቸው ፍቃደኛ አልሆኑም» የሚል መልስ ነው የሰጡኝ። በአጭሩ፣ በአንድነት ፓርቲ ዘንድ፣ ከማንም ድርጅት ጋር፣ በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ አብሮ ለመስራት፣ ሰላማዊ ሰልፎችን ለማስተባበር ፣ ፍቃደኝነት እንዳለ ነዉ የተረጋገጠልኝ።
ነገር ግን ከእናንተ አዎንታዊ ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም። «የሚጠየቁት ጥያቄዎች አንድ አይነት ሆነው፣ ለሰልፍ የሚጠራዉ ህዝብ አንድ ሆኖ፣ በሁለት ሳምንት ጊዜ ዉስጥ፣ ሁለት ሰላማዊ ሰልፎች መጥራት ምን ይባላል ? ። ገንዘብና ጊዜ ማባከን ነዉ» በሚል ብትችሉ አብራችሁ ከአንድነት ጋር መስክረም 5 ቀን ሰልፍ እንድታደርጉ፣ ካልተቻለ ደግሞ የሰልፉን ቀን ትንሽ ራቅ እንዲል ተማጸንን።
በነሐሴ 26 ቀን በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራት፣ በጋምቤላና በአሶሶ፣ ነሐሴ 26 ቀን የአንድነት ፓርቲ ሊያደርጋቸው ያቀዳቸውን ሰላማዊ ሰልፎችና በዚያም የሚኖረው ሕዝብ ጥያቄ በስፋት እንዳይዘገብና ትኩረት እንዳያገኝ የሚያደርግ መሆኑን በማስገንዘብ፣ ለጋምቤላና ለአሶስ ሕዝብ ክብር እንድትሰጡም ጠየቅናችሁ።
ነገር ግን «አልሰማም፣ እምቢ አሻፈረን» አላችሁ። ግትር ሆናችሁ። በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ የድርጅታችሁ ሊቀመንበር አቶ ይልቃል «ለምን ከሌሎች ድርጅቶች ጋር አብራችሁ አትሰሩም ? » ተብለው ሲጠየቁ «ምን የሚረባ ድርጅት አለህ ብለህ ነዉ ? » የሚል አሳዛኝና አሳፋሪ ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪ የማይጠበቅ ምላሽ ነበር የሰጡት። በአሜሪካን ድምጽ ራዲዮ፣ ከማንም ድርጅት ጋር ግንባር፣ ቅንጅት፣ ዉህደት ለመፍጠር ሰማያዊ ፓርቲ ፍላጎት እንደሌለውም አቶ ይልቃል በድጋሚ አስምረዉበታል። በአጭሩ ሰማያዊ ፓርቲ ለብቻው መጓዝ የመረጠ ይመስላል። በዚህም ምክንያት ሰማያዊ ፓርቲ ከሰላሳ ስምንቶቹ ዉጭ ሊሆን ችሏል።
የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት፣ «ሰማያዊም ሆነ ማንም ድርጅት፣ ድርጅታዊ ነጻነትና፣ ባመነበትና ባቀደው መንገድ የመንቀሳቀስ መብት አለዉ» በሚል የሰማያዊም ሆነ የሌሎችን ሥራ ላይ አስተያየት መስጠት አልፈልጉም። ሌሎች የሚያደርጉትን ለነርሱ ትተው፣ በኦሮሚያ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በመቀጠል በሮቤና በአዳማ፣ እንዲሁም በመቀሌ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላእንዲሁም አዲስ አበባ ሰላማዊ ስለፎችን ለማድረግ እየተዘጋጁ ነዉ። የኢትዮጵያን ሕዝብ፣ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በደቡብ፣ በትግራይ፣ በአማራዉ ክልል፣ በኦሮሚያ ፣ በጋምቤላ፣ በቤኔሻንጉል …እያንቀሳቀሱት ነዉ። ጸጥ ብለው ስራቸውን እየሰሩ ነዉ። በዚህ በርቱ፣ ቀጥሉበት እንላቸዋለን።
ድርጅታችሁ በሕዝብ ካልተደገፈ የትም ሊደርስ አይችልም። እንደከዚህ በፊትም ሕዝቡ በቀላሉ ለፖለቲካ ድርጅቶች ድጋፍ ለመስጠት ፍቃደኛ አይደለም። ሕዝቡ ከፖለቲካ ድርጅቶች የሚጠብቀዉ ነገር አለ። «አንድ የተቃዋሚ ድርጅት ኢሕአዴግን ተክቶ፣ በኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉ ልዩነቶችን አጣቦ፣ ያገሪቷን አንድነት ጠብቆ፣ በአገሪቷ ሁሉ ሰላምና መረጋጋትን አስፍኖ አገር ማስተዳደር ይችላል ወይ ?» የሚል ጥያቄ ይጠይቃል። ሕዝቡ «ምን ያህል ኢሕአዴግን ይቃወማል ?» የሚል ጥያቄ አይደለም የሚጠይቀው። «ከኢሕአዴግ ይሻላል ወይ ? » የሚል ጥያቄ ነዉ የሚጠይቀዉ። ሕዝብን ለማሰባሰብ የሚችል ድርጅት ደግሞ ሌሎችን የሚያከብር፣ ትሁት መሪዎች ያሉት ድርጅት መሆን ይኖርበታል።
እንግዲህ ትህትና ይኑራችሁ እላለሁ። ከአሁን ለአሁን አንድ ሰልፍ ጠራችሁና እራሳችሁን እንደ ግዙፍ ማየታችሁን አቁማችሁ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ እራሳችሁን አስገዙ እላለሁ። በነሐሴ 26 የጠራችሁት ሰላማዊ ሰልፍን ሰርዙ። የአዲስ አበባ ሕዝብ በአስራ አምስት ቀናት ዉስጥ ሁለት ጊዜ ሰልፍ ሊወጣ አይገባም። ሰልፍ ለማዘጋጀት ትልቅ የገንዘብ አቅም ይጠይቃል። በመሆኑም ሰልፉን መስክረም 5 ቀን ከአንድነት ፓርቲ ጋር አብራችሁ አድርጉ። በአንድነት ፓርቲና በሰማያዊ ፓርቲ ፣ ካስፈለገም ሌሎች ድርጅቶችን ያቀፈ ግብረ ኃይል ተቋቋሞ የመስከረም 5ቱን ሰልፍ ያስተባብር። ይሄን ለማድረግ ትንሽ ጊዜ ካስፈለገም የመስከረም 5 ቱን ሰልፍ በአንድ ወይንም 2 ሳምንታት እልፍ እንዲል ማድረግም ይቻላል።
እግርጥ ነዉ ለኢሕአዴግ የሶስት ወራት ጊዜ ሰጥታችሁታል። «ጥያቄያችንን ስላልመለሰ በገባነው ቃል መሰረት በሶስት ወሩ ሰልፍ መዉጣት አለብን» የሚል አስተያየት ሊኖራችሁ ይችላል። እስቲ ልጠይቃችሁ …ከመጀመሪያዉ ሰልፍ በኋላ ያልሰማችሁ ኢሕአዴግ፣ አሁን ለምን ይሰማቹሃል ? እንዳለፈው ጊዜ የአንድነት/መኢአድ አባላትና ደጋፊዎች አይተባበሯችሁም ። ለምን ለመስክረም 5 ዝግጅት ስለሚያደርጉ። ለሰልፍ የሚመጣዉ ሕዝብም ቁጥሩ ሊያንስ ይችላል። ያ ደግሞ የበለጠ ተቀባይነታችሁን ይሸረሽርዋል እንጂ የሚፈይደው አንዳች ፋይዳ የለም።
ይልቅስ በኢሕአዴግ ላይ የበለጠ ጫና ማሳደር ከፈለጋችሁ፣ በሚቀጥለው ሰልፍ ኢሕአዴግ እንዲሰማ ከፈለጋችሁ፣ ከአንድነት ፓርቲ፣ ከመኢአድ ከመሳሰሉ ጋር እጅና ጓንት ሆናችሁ መስራት ይኖርባቹሃል። የአንድነት ፓርቲ ያለ አንዳች ቅደመ ሁኔታ ከናንተ ጋር ለመነጋገር፣ ሕብረት ለመፍጠር ዝግጁ ነዉ። ከእናንተ ጋር ብቻ አይደለም ከማንም ድርጅቶች ጋር አብሮ መስራት ይፈልጋል። ለዚህም ነዉ ከአምስት አመት በላይ በመድርክ ዉስጥ ሲንቀሳቀስ የነበረዉ። (ይሄን ያህል ዉጤት ባይገኝም) ለዚህም ነዉ ከመድረክ አልፎ፣ መድረክን ተክቶ፣ ድርጅቶችን በሚስማሙበት ጉዳይ አሰባስቦ ጥሩ ሥራ ሊሰራ ይችላል ብዬ በማስበው፣ በሰላሳ ሰምንቶቹ ዉስጥ ፣ ድርጅቶች በአንድ ላይ ሆነው በአገዛዙ ላይ ጫና እንዲያሳድሩ እየሰራ ያለዉ። ለዚህ ነዉ ዘሃበሻ እንደዘገበዉ ከመኢአድ ጋር ለመዋሃድ እንቅስቃሴ የሚያደርገዉ።
እዚህ ላይ አብቃ። ተስፋ አደርጋለሁ ምክሬን እንደምትሰሙ። ሕዝቡ ይከታተላል። ሕዝቡ ሁሉንም ይመዝናል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቅ ሚና ልትጫወቱ ከፈለጋችሁ ጉዟችሁን በጥንቃቄና በማስተዋል አድርጉ። ትላንት ግዙፍና ተወዳጅ የነበሩ፣ አሁን ግን የተተፉ የተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎችና ድርጅቶች እንደነበሩና እንዳሉም አትርሱ።
(ዘግይቶ የደረሰኝ መረጃ የአንድነት ፓርቲ፣ ነሐሴ 26 ቀን ፣ ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ ከመጥራቱ በፊት፣ አስቀድሞ በጋምቤልና በአሶሳ ያቀዳቸዉን ሰልፎችን እንዲሁም በድረደዋ በመሳሰሉ ከተሞች ሊደረጉ የታቀዱ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ሰርዟል። ይመስለኛል ሰማያዊ ፓርቲ ተገቢዉን የሜዲያ ትኩረት እንዲያገኝ ታስቦ ሳይሆን አይቀርም። ለሌሎች ድርጅቶች ከበሬታ ማሳየት ማለት ይሄ ነው)
amanuelzeselam@gmail.com

No comments:

Post a Comment