Thursday, August 22, 2013

የሆስኒ ሙባረክ መፈታት ግብጽን እንደገና ሊከፍላት ይችላል ተባለ

ነሃሴ ፲፭(አስራ አምስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሲኤን ኤን፣ ቢቢሲ እና ሌሎችም ታዋቂ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀን የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞችን በማነጋገር እንደዘገቡት የቀድሞው የግብጽ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ከእስር መፈታት ግብጽን በድጋሜ ከሁለት ሊከፍላት ይችላል።
አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት ሙባረክን ለማውረድ የታገሉ ወጣቶች ምናልባትም ራሳቸውን ከሙስሊም ብራዘርሁድ ጋር በማቀናጀት በስልጣን ላይ ባለው መንግስት ላይ ሊዘምቱ ይችላል። ይሁን እንጅ የሙርሲን መንግስት ከስልጣን በማውረድ ከፍተኛ ሚና የተጫወተው ታምሩድ የሚባለው የወጣቶች ስብስብ፣ ለሆስኒ ሙባረክ መፈታት ተጠያቂው የሙርሲ መንግስት ነው ብሎአል። የሙርሲ መንግስት በሙባረክ ላይ በቂ ማስረጃዎችን ቢያቀርብ ኖሮ ሙባረክ ሊለቀቁ አይችሉም ነበር በማለት የሙባረክን መፈታት ብልጠት በተሞላበት መንገድ ተቀብሎታል።

ሌሎች ተንታኞች በበኩላቸው የግብጽ ወጣቶች አብዮቱ መቀልበሱን በማስታወስ ምናልባትም ለተቃውሞ ወደ አደባባይ ሊወጡ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የሙባረክ ደጋፊዎች ምናልባትም ለቀድሞው መሪ ያላቸውን ድጋፍ በማሳየት ወደ አደባባይ ሊወጡ ይችላሉ።
ሙባረክ ከእስር የሚፈቱት አገሪቱ ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳይነሳ ነው።
ሆስኒ ሙባረክ ከእስር ቢለቀቁም፣ ከአገር መውጣት አይችሉም፡፡   ከሁለት አመት በፊት በተገደሉ ወጣቶች ዙሪያ የቀረበባቸውን ክስ በውጭ ሆነው እንደሚከራከሩ ይጠበቃል።

No comments:

Post a Comment