ከኢትዮጵያዊ ሙስሊም
እዚህ አሜሪካ ከዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የሚሰራጨው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ራዲዮ ጣቢያ በቅርቡ የሙስሊም ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ነፃነትና መብትን የማስከበር ሰላማዊ ትግልን ከ‹ፖለቲካዊ እስልምና› ጋር ለማያያዝ የሚቃጣ “የራዲዮ ዝግጅት” አቅርቧል፡፡ ዝግጅቱ ዊኪሊክስ በተሰኘው ድረ‑ገፅ አምና ይፋ የተደረጉ የስቴት ዲፓርትመንት ምሥጢራዊ ሰነዶችንና ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ከተከሰቱ ግጭቶች ጋር የተያያዙ የድምፅ ግብዓቶችን በመጠቀም ወቅታዊውን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሃይማኖት ነፃነትን የማስከበር ሰላማዊ ትግል ከ‹ፖለቲካዊ እስልምና› ጋር በማያያዝ ጭቃ ለመቀባት፣ ብሎም ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖችን ግንዛቤ ለማዛባት ይሞክራል፡፡
ይህ ጽሑፍ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን እየተነዛና እየተሰበከ ባለው ጥላቻና ግጭትን የመቀስቀስ ዓላማ ያዘለ ፕሮፖጋንዳ አኳያ፣ ወቅታዊውን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሃይማኖት ነፃነትን የማስከበር ሰላማዊ ትግል በአጭሩ በማስቃኘትና፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥትና አጫፋሪዎቹ እያካሄዱ ያሉትን ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ያለመ ዕኩይ ዘመቻ አደገኛነት በማመላከት ዓላማ የተዘጋጀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ራዲዮ ያቀረበውን ዝግጅት አሉታዊነት በድፍኑ ከመተቸት ይልቅ፣ በዝግጅቱ ይዘት ላይ ያተኮረ ሰፋ ያለ ሒስ ማቅረብ አስፈላጊ ይመስለናል፡፡ እናም በዚህ ጽሑፍ የራዲዮ ጣቢያው ባቀረበው ዝግጅት ይዘት ጥቂት አንኳር ጉዳዮች ላይ በማተኮር የጣብያውን አሳዛኝና አሳፋሪ ሥራ ለማስቃኘት እንሞክራለን፡፡
ምሥጢራዊ ሰነዶችና ይፋ የመውጣታቸው ፖለቲካዊ አንድምታ
የዳያስፖራው ራዲዮ “በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እስልምና እየተስፋፋ ነው” የሚል ክስ ያቀርባል፡፡ ለዚህ ክሱ ካቀረባቸው ማስረጃዎች መካከል ‹ዊኪሊክስ› የተሰኘው የዊሊያም አሳንጅ ድረ‑ገፅ ይፋ ያደረጋቸውን ከስቴት ዲፓርትመንት ያፈተለኩ ምሥጢራዊ ሰነዶች ይገኙበታል፡፡ እንደ ማስረጃ በተጠቀሱት ‹ዊኪሊክስ› ይፋ ያደረጋቸው ሰነዶች ይዘት ላይ ከማተታችን በፊት ግን፣ የእነዚህ ሰነዶች ከስቴት ዲፓርትመንት ዳታቤዝ ተሠርቆ በ‹ዊኪሊክስ› ድረ‑ገፅ ይፋ የመደረጉን ፖለቲካዊ አንድምታዎች መመልከት ተገቢ ይመስለናል፡፡
እንደሚታወቀው፣ ማንኛውም መንግሥት በ“ጥብቅ ምስጢር”ነት የሚይዛቸው ጉዳዮች ይኖሩታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰነዶች “ጥብቅ ምስጢር” (CLASSIFIED) በሚል ተፈርጀው በጥንቃቄ ይቀመጣሉ፡፡ በመንግሥት ሥራ ላይ አንድን ጉዳይ “ጥብቅ ምስጢር” የሚያደርጉ ተቀባይነት ያላቸው ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል አንዳንድ ጉዳዮች/ሰነዶች በ“ጥብቅ ምስጢር”ነት የሚይያዙት ይፋ ቢሆኑ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተቃውሞን ሊያስነሱ፣ ጠንካራ ትችትና ውግዘት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ስለሚታወቅ ነው፡፡ በ“ጥብቅ ምስጢር”ነት የሚያዙ ጉዳዮች/ሰነዶች ይፋ መውጣት ብሄራዊ እና/ወይም ዓለምአቀፍ ሕግን መሠረት ያደረገ ተጠያቂነትን ሊያስከትል፣ ወይም ደግሞ እንደ ይዘቱ በአገራት ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥ የሆኑ ኦፊሴላዊ የ“ጥብቅ ምስጢር” ሰነዶች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ከደረሱ፣ እንደሁኔታው በምሥጢር ሊካሄዱ የታቀዱ መርኃ‑ግብሮችን ሊያሰናክሉም ይችላሉ፡፡
በብዙ አጋጣሚዎች መንግሥታት፣ ይበልጡኑም በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ ያሉ ፖለቲከኞች ዕውን ሊያደርጉ የሚሹትና በአደባባይ ለህዝብ የሚናገሩት ፍፁም ለየቅል ሊሆን ይችላል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ የአንድን መንግሥት ተግባራት እውነተኛ መግፍዔ (Motive) ለማወቅ፣ አልያም የቅርብ ግምት ለመስጠት የሚቻለው በጥልቅ ፖለቲካዊ ትንተና ነው፡፡ … በዓለምአቀፍ የቴሌቪዥን ኔትወርኮች ዘወትር እንደምናየው፣ የአንድን መንግሥት እርምጃዎች፣ ውሳኔዎች ወይ የአቋም ለውጦች ከተለያዩ ማዕዘናት በመዳሰስ በይፋ ያልተነገሩ ብዙ መረጃዎችን የሚሰጡት የፖለቲካ ተንታኞች ናቸው፡፡ ግና ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በ“ጥብቅ ምስጢር”ነት የተያዘ የመንግሥት ሰነድ ድንገት ሾልኮ ቢወጣስ? ይህ ሲሆን፣ የፖለቲካ ተንታኙን የዙርያ‑ገብ ትንተና ድካም በመቀነስ፣ በቀላሉ ወደ እውነተኛው የጉዳዩ ምንነት ያደርሳል፡፡ በ“ጥብቅ ምስጢር”ነት የተያዘ የመንግሥት ሰነድ ይፋ መውጣት እንደ ጉዳዩ የክብደት ደረጃ አንድን መንግሥት በከፍተኛ ኃፍረት አልያም ቅሌት ውስጥ ሊከተውም ይችላል፡፡
በዚህ ማዕቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ራዲዮ ጣቢያ ባቀረበው ዝግጅት በስፋት ያጣቀሳቸውን በ‹ዊኪሊክስ› ይፋ የተደረጉ የስቴት ዲፓርትመንት “ምስጢራዊ ሰነዶች” በምን መልኩ ለዕኩይ ዓላማ እንደዋሉ ስናይ በጣም እንገረማለን፡፡ … እናዝናለንም፡፡
“ዊኪሊክስ” ማንን እና ምንን ነው ያጋለጠው?
በመሠረቱ፣ ዊኪሊክስ ይፋ ያደረጋቸው የስቴት ዲፓርትመንት “ምሥጢራዊ ሰነዶች” በአሁኑ ወቅት ሙስሊም ኢትዮጵያውያን እያካሄዱ ከሚገኙት ሕገ‑መንግሥታዊ የሃይማኖት ነፃነትን የማስከበር ትግል ጋር ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ግንኙነት የላቸውም፡፡ በአንጻሩ ግን “ምሥጢራዊ ሰነዶቹ” የኢሕአዴግ መንግሥት ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሃይማኖት ነፃነት ላይ የከፈተው ግብታዊነት የሚታይበት “የጥሰት ዘመቻ”፣ የአሜሪካ መንግሥት “አሳስቦኛል” ከሚለው አንድ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ሳይኖረው እንዳልቀረ ይጠቁማሉ፡፡ ሰነዶቹ ከምንም በላይ ዛሬ የኢሕአዴግ መንግሥት ከህዝበ‑ሙስሊሙ ጋር የተፋጠጠበት ጉዳይ፣ በኢትዮጵያዊ ዓይን የታየ ሳይሆን፣ በአሜሪካ መንግሥት ዓይን የታየ፣ በአሜሪካዊኛ የተተነተነ፣ በአሜሪካ ልዩ ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ የተቃኘ መሆኑን ነው በግልፅ የሚያሳዩት፡፡ … ይህ ሆኖ ሳለ፣ የዳያስፖራ ራዲዮ ጣቢያ፣ የአሜሪካ መንግሥት በራሱ ምክንያት ምሥጢር አድርጎ ሊይዝ ይፈልገው የነበረውን ይህን ሰነድ በማጣቀስ፣ ወቅታዊውን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሃይማኖት መብትን የማስከበር ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማጠልሸት ዓላማ አውሎታል፡፡ ይህ በአንድ በኩል በጣም የሚያስቅና የጣቢያውን ብስለት-የለሽነት የሚያሳይ ሲኾን፣ በሌላ በኩል ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የፍትኅና የነፃነት ተሟጋቾች (አክቲቪስቶች) ከአንድ ዓመት በፊት በፌስቡክ ላይ እንደነገሩ ነካክተው ያለፉትን ነገር ዛሬ ጠበቅ አድርገን እንድንመለስበት የጋበዘ በመሆኑ የሚመሰገን ነው፡፡
እስከምናውቀው ድረስ፣ ዊኪሊክስ ይፋ ያደረጋቸው አዲስ አበባ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ ስቴት ዲፓርትመንት የተላለፉ “ምሥጢራዊ ሰነዶች” በቁጥር ሦስት ሲኾኑ፣ ሦስቱም እ.አ.አ በኦገስት 2009 (በኢት. አቆጣጠር በነሐሤ 2001) የተዘጋጁ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰነዶች፣ የኢሕአዴግ መንግሥት በኢት. አቆጣጠር በሐምሌ 2003 በይፋ የጀመረው የአህባሽ አስተምህሮን በህዝበ‑ሙስሊሙ ላይ የመጫን መርኃ‑ግብር፣ ከዚያ ሁለት ዓመታት ቀደም ብሎ የአሜሪካ መንግሥት በዊኪሊክስ ላይ ባንፀባረቀው በጥልቀት ያልተተነተነ ስጋት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ነው ያጋለጡት፡፡ … እነዚህ “ምሥጢራዊ” የነበሩ ሰነዶች በይዘታቸው በአሁኑ ወቅት የኢህአዴግ መንግሥት በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ እያካሄደ የሚገኘው የአገሪቱን ሕገ‑መንግሥት የሚጻረር (የሃይማኖት ነፃነትን የመገደብ) መርኃ‑ግብር በእውነትና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ከመሆን ይልቅ፣ የአሜሪካ መንግሥት ከራሱ ዕይታ ያንፀባረቀው፣ ኢሕአዴግ በጥልቀት ሳያጠናውና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሙስሊም ዜጎቹ (ቢያንስ ከሚያምናቸው ሙስሊም ምሁራን) ጋር ሳይማከርበት ዓይኑን ጨፍኖ በግብታዊነት ሊያስፈጽም የተቀበለው የቤት ሥራ መሆኑን ነው በግልፅ የሚያሳዩት፡፡ ዊኪሊክስ ምሥጢራዊ ሰነዱን ይፋ ባያደርግ ኖሮ፣ የአሜሪካ መንግሥት እ.አ.አ እስከ 2019 (በኢት. አቆጣጠር እስከ ነሐሤ 2011) ድረስ ይህንን ሐቅ በምሥጢር ሊይዘው ነበር የፈለገው፡፡ ምናልባት ሰነዱን ምሥጢር ማድረግ የተፈለገው ተግባሩ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደመግባት ሊቆጠር ይችላል ከሚል ስጋት በመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራው ራዲዮ “እኛ” በተሰኘ ፕሮግራሙ፣ በዊኪሊክስ ይፋ በመደረጋቸው የአሜሪካ መንግሥትና ኢሕአዴግ የተጋለጡባቸውን እኒህኑ በምሥጢር ተይዘው የነበሩ ሰነዶች ዋቢ በማድረግ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በሃይማኖታዊ ነፃነታቸው ላይ የተቃጣውን ጥሰት በመቃወም የሚያካሂዱትን ሰላማዊ ትግል ሊያጠለሽ ይሟሟታል፡፡ የራዲዮ ጣቢያው ዝግጅት ከአገረ‑አሜሪካ ለሚገኝ ዳረጎት ሲሉ የ“አክራሪነት”ን ነጋሪት እየጎሰሙ ሙስሊሙን ዜጋ ቁም ስቅል የሚያሳዩት ገዢዎቻችን የተጋለጡበትን “የአደባባይ ምሥጢር” እየተረከ፣ በአገሪቱ ሕገ‑መንግሥት ስለተደነገገው የሃይማኖት ነፃነታቸው መከበር የሚጮሁ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን በ‘ፖለቲካዊ እስልምና’ አስፋፊነት በመወንጀል ሊያሸማቅቅ ይሞክራል፡፡ በሌላም በኩል፣ የሙስሊም ኢትዮጵያውያንን ሕጋዊ፣ ፍትኃዊና ሰላማዊ ጥያቄ ደግፈው የቆሙ ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖቻችንን ግንዛቤ ለማዛባትና የሙስሊም ወገኖቻቸውን ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል በጥርጣሬ እንዲመለከቱት ለማድረግ ይተጋል፡፡ በዚህ ብቻ ግን አያበቃም፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት በአገራችን አንድ ክፍል በተከሰተ የማንም አዕምሮ የማይቀበለው ግጭት ላይ የደረሱ ጥፋቶችን፣ ስሜት በሚኮረኩሩ የድምፅ ግብዓቶች አጅቦ በማቅረብ፣ ሙስሊም ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን በሙስሊም ወገኖቻቸው ላይ ጥላቻና ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው የሚገፋፋ መሠሪ ፕሮፖጋንዳ ይነዛል፡፡ እግረ መንገዱንም፣ ወቅታዊውን የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ሰላማዊ የመብት ትግል ስውር ዓላማ ያለው ለማስመሰል ዳር ዳር ይላል፡፡
በቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ያማሞቶ አማካይነት የተዘጋጀውና ዊኪሊክስ ይፋ ያደረገው የመጀመርያው ሰነድ ‹‹GROWING WAHABI INFLUENCE IN ETHIOPIA: AMHARA›› የሚል ርዕስ አለው፡፡ ሰነዱ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የህዝብ ጉዳዮች ክፍል (Public Affairs Section) ኃላፊዎች በአማራ ክልል፣ ደሴ አቅራቢያ በሚገኙ የገጠር ወረዳዎች (እ.አ.አ. ከጁን 3‑5፣ 2010) ባካሄዱት የሦስት ቀናት ቅኝት ላይ ተመሥርቶ የተዘጋጀ ነው፡፡ የኤምባሲው ባልደረቦች ይህን ቅኝት ያካሄዱት ከአንድ የዞን መሥተዳድር ኃላፊ ጋር መሆኑም በሰነዱ ላይ ተጠቁሟል፡፡ …
ሰነዱ በአማራ ክልል ‹ወሃቢያ› የተባለው የእስልምና አስተምህሮት እየተስፋፋ መሆኑን፣ በገጠር ከተሞች በርካታ መስጊዶች ከኩዌት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በተገኘ ፈንድ መታነፃቸውን፣ የኤምባሲው ኃላፊዎች በጎበኟቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሙስሊም ሴቶች ሃይማኖታዊ አለባበስ በመከተል ፊታቸውን እንደሚሸፍኑ፣ ወንዶች ደግሞ ሱሬያቸውን እንደሚያሳጥሩ፣ ፂማቸውን ግን እንደማያሳድጉ ወዘተ. ይጠቃቅሳል፡፡ በተጨማሪም፣ የወሃቢያ አስተምህሮ የነቢዩ ሙሐመድን ልደት (መውሊድ) ማክበርን ስለሚቃወም፣ በዚህ ረገድ በወሃቢ አስተምህሮና በሱፊ አስተምሀሮ ተከታዮች መካከል፣ በተለይ የሱፊ እስልምና ተከታዮች መውሊድን በሚያከብሩበት የጀማ ንጉስ መስጂድ አካባቢ ከዚያ ቀደም ባለ ጊዜ ሁኔታው ወደ ግጭት አምርቶ እንደነበረ ይገልፃል፡፡ አክሎም የሱፊ እስልምና ተከታዮች የመውሊድ በአልን ለሚያከብሩበት የጀማ ንጉስ መስጂድ እድሳት በማድረግ ባህላዊ ቅርሱን ስለመጠበቅ አስፈላጊነት ያወሳል፡፡ ለዚህም አሜሪካ ከአምባሳደሩ የባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ፈንድ ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳላት ይጠቁማል፡፡ [http://wikileaks.org/cable/2009/07/09ADDISABABA1672.html#]
ሰነዱ የኤምባሲው የስራ ኃላፊዎች ለሦስት ቀናት ባካሄዱት ቅኝት፣ ከአካባቢው መስተዳድር የሥራ ኃላፊ እንዲሁም ከወቅቱ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) በተገኘ መረጃ ላይ ተመሥርቶ፣ በኢትዮጵያ የወሃቢ አስተምህሮ መስፋፋት ለዘመናት የቆየው የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች የመቻቻል ዕሴት አደጋ እንደተደቀነበት ይጠቅሳል፡፡ ሰነዱ በገፅ 3 [8.(C)] በዚህ ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ምክር ቤቱን ሲጠቅስ እንዲህ ይላል፡‑
the IASC continues to be very concerned about growing Wahabi influence in Ethiopia. The newly appointed Council is decidedly anti-Wahabi and speaks openly of their concern about Wahabi missionaries and their destabilizing influence in Ethiopia.
ሰነዱ በገፅ 4 (13.(C)) ላይ ደግሞ የመጅሊሱን ኃላፊዎች ዋቢ በማድረግ በወቅቱ (እ.አ.አ. በ2010) መጅሊሱ ከወሃቢ አስተምህሮ ተከታዮች እንደፀዳ ይጠቅሳል፡፡
13. (C) In a shift from past practice, the IASC is now completely purged of Wahabi members. […] the Council members acknowledged that the Council is now all Sufi and in their public statements they repeatedly make reference to Ethiopia’s tradition of religious tolerance and co-existence with the Christian communities.
በተጨማሪም በዚሁ ገፅ ላይ፣ የእስልምና ምክር ቤቱ [የአመራር] አባላት በመንግሥት እንደሚሾሙ በግልፅ ይናገራል፡‑
As the Ethiopian government appoints the members of the Islamic Council, it is clear that the GoE shares this concern about growing Wahabi influence and is supporting moderate Muslim leaders in trying to counter that influence.
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ቁም ነገር የመላው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የጋራ ተቋም እንደሆነ በሚታሰበውና ለረዥም ጊዜያት የሱፊና የሰለፊ አስተምህሮ ተከታዮች በጋራ ሲያስተዳድሩት በኖረው መጅሊስ ላይ፣ በዚህ ወቅት (እ.አ.አ. በ2010) መንግሥት ሙሉ በሙሉ የአህባሽ አስተምህሮ ተከታዮችን የሾመ መሆኑ ነው፡፡ የአህባሽ አስተምህሮ፣ ከሰለፊ አስተምህሮ ጋር የከረረ ተቃርኖ እንዳለው የሚታወቅ ሲኾን፣ በሰለፊ አስተምህሮ ተከታዮች ላይም እጅግ የመረረ ጥላቻ ያንፀባርቃል፡፡ ከዚህ በላይ በጠቀስነው የዊኪሊክስ ሰነድ ላይ እንደተመለከተው፣ መንግሥት በጠቅላይ ምክር ቤቱ ላይ የአህባሽ አስምህሮ ተከታዮችን የሾመው ለዘብተኛ ሙስሊሞችን በመደገፍና የወሃቢን ተፅዕኖ ለመቋቋም ነው ተብሏል፡፡ ይህም ‹‹እርምጃው የወሃቢ አስተምህሮ በሃይማኖቶች የመቻቻል እሴት ላይ ደቅኖታል የሚባለውን ስጋት የማስወገድ ዓላማ ያለው ነው›› የሚል አንድምታ አለው፡፡ ነገር ግን እውን ሐቁ ያ ነዉን? የወሃቢ አስተምህሮ ደቅኖታል የተባለውን ስጋት የማስወገጃው መንገድስ ይህ ነውን? ብለን ስንጠይቅና … መሬት ላይ ያለውን ሐቅ ስንፈትሽ የምናገኘው ምላሽ ይህንን አያረጋግጥልንም፡፡ [ለዚህ አባባላችን ዋቢ የሚሆኑ ተግባራዊ ምሳሌዎችን ወደኋላ ላይ እናቀርባለን፡፡]
ዊኪሊክስ ይፋ ባደረጋቸው ሰነዶች ላይ፣ የአሜሪካ መንግሥት የሱፊ ስርዓተ‑አምልኮ የሚከናወንባቸውን ጥንታዊ መስጂዶችና የቅዱሳን የመቃብር ሥፍራዎችን ጠብቆ በማቆየት ዓላማ መሠራት አለባቸው ብሎ የሚያምናቸው ተግባራት ተጠቅሰዋል፡፡ … የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል ፀንቶ የኖረው የመቻቻል ባህል በዘላቂነት ይቀጥል ዘንድ የራሱን ጥረት ለማድረግ በመሻቱ ሊመሰገን እንጂ ሊወቀስ አይገባውም፡፡ ነገር ግን፣ እንዲህ ዓይነቱ ጥረት፣ የቱንም ያህል ቀና ቢሆን እንኳ፣ ጉዳዩን እጅግ በቅርበትና በጥልቀት መመርመር የሚጠይቅ መሆኑ አይካድም፡፡ ከዚያም በላይ ግን፣ የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ማኅበረሰብ፣ ከማኅበረሰቡም ተደማጭነት ያላቸውን የእምነቱ መሪዎች ወይም የሃይማኖቱን ሊቃውንት ባላካተተ መልኩ ሲካሄድ የሚፈለገውን አዎንታዊ ውጤት ያመጣል የሚል እምነት የለንም፡፡ በየትኛውም የሃይማኖት ማኅበረሰብ ውስጥ ከእምነት‑ተኮር አስተሳሰብ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ልዩነቶች ሊፈጥሩ የሚችሉትን አላስፈላጊ ፍጥጫና ይህም ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ውጤት በማስቀረት ጥረት ውስጥ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የሃይማኖት ማኅበረሰብ እና ተደማጭ መሪዎቹ ያላቸው ሚና በምንም የሚተካ አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የወሃቢያ መስፋፋትም ሆነ ከሱፊያ አስተሳሰብ ተከታዮች ጋር ያሉ ልዩነቶችንና ከልዩነቶቹ ሊመነጩ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ውጥረቶችን በዘላቂነት ለመፍታትም የጉዳዩ ባለቤቶችን የመፍትኄ አካል በማድረግ ፈንታ የችግር ምንጭ አድርጎ ማሰብ ትክክለኛ ነው ብለን አናምንም፡፡
ወሃቢያ እንደ ስጋት …
ለመሆኑ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ነው የሚለውን የ‹ወሃቢ› አስተምህሮ ከምን አኳያ ነው እንደ ስጋት የተመለከተው? … ይህ ስጋት በመሬት ላይ ያለ ነውን? ካለስ ስጋቱን የማስወገጃው መንገድ ምንድን ነው? … ሙስሊም ኢትዮጵያውያንስ ይህን ስጋት በማስወገድ ረገድ ያላቸው አቋምና አስተሳሰብ ምን ይመስላል? … በተግባርስ ይህን ስጋት ለማስወገድ ምን አድርገዋል? … ‘ዊኪሊክስ’ ይፋ ያደረጋቸውን “ምስጢራዊ ሰነዶች” መነሻ አድርጎ ስለ ‘ፖለቲካዊ እስልምና በኢትዮጵያ’ ሀተታ ያቀረበው የዳያስፖራ ራዲዮ እነዚህን ቁልፍ ጥያቄዎች አልጠየቀም፡፡ ባለመጠየቁም በኢትዮጵያ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ አላየም፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ ሰነዱን ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን እያካሄዱ ያሉትን ሃይማኖታዊ ነፃነትን የማስከበር ሰላማዊ ትግል ጥላሸት ለመቀባት ዓላማ አውሎታል፡፡
በእኛ እምነት በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ የሚንፀባረቁ የጽንፈኝነት ዝንባሌዎችን ማረቅ የሚቻለው ትምህርትና እውቀትን በማስፋፋት ብቻ ነው፡፡ በዚህም መንፈስ በኢትዮጵያ ሙስሊም ማኅበረሰብ ውስጥ የአገሪቱ ሙስሊሞች የጋራ ተቋም ከሚሰኘው መጅሊስ ይልቅ የሃይማኖቱ ምሁራን በርካታ አዎንታዊ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ ከአስተምህሮ ልዩነቶች የሚመነጩ ውጥረቶችን ከማስወገድ አኳያም አንዱን ወገን በጽንፈኝነት ፈርጆ የማሳደድን አማራጭ ከሚያራምደው የመንግሥትና የመንግሥታዊው መጅሊስ መንገድ ይልቅ፣ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ አንጋፋ የሃይማኖት ሊቃውንት በጥልቅና በሳል ውይይቶች አማካይነት ኅብረተሰቡን ወደጋራ መግባባት ለማምጣት በርካታ አዎንታዊ ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ2000/2001 የተለያዩ አስተምህሮ የሚከተሉ አንጋፋ የሙስሊም ሊቃውንት፣ በሱፊው በኩል በሸኽ ዑመር ኢድሪስ መሪነት፣ በሰለፊ በኩል ደግሞ በዶ/ር ጀይላን መሪነት፣ ይህን በመሰሉ ጉዳዮች ላይ ተከታታይ የሆኑ በሳል ውይይቶችን በማድረግ ከመግባባት ላይ ደርሰው፣ የአንድነት ጉባዔ ለማካሄድ የመጨረሻ ዝግጅት እያካሄዱ ነበር፡፡ ይህን መሰል ታላቅ አዎንታዊ እርምጃ ከኢትዮጵያ በቀር በሌሎች ሙስሊሞች በሚበዙባቸው አገራት እንኳ መካሄዱ ያጠራጥራል፡፡ ግና ይህ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የተለየ አዎንታዊ ተግባር በህዝብ ባልተመረጠው የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮችም ሆነ በመንግሥት ዘንድ በበጎ ዓይን አልታየም፡፡ እናም መንግሥት እና ምክር ቤቱ ይህንን ሰላምና አንድነትን የማምጣት ዓላማ የነበረውን ሂደት ሆን ብለው አስተጓጉለውታል፡፡ ከቶ ይህ ለአገር እና ለህዝቦች ሰላም የማሰብ ተግባር ነውን? መልሱን ቅን ልቦና ላላቸው ወገኖች ኅሊና ትተነዋል፡፡
በሙስሊሙ ኅብረተሰብ መካከል የሚፈጠሩ የሃይማኖት አስተምህሮን መሠረት ያደረጉ ማናቸውም ችግሮች ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በራሱ ሊፈታቸው የሚገባ፣ የውስጥ ጉዳዮቹ ናቸው፡፡ የጋራ ተቋማችን በምንለው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ላይ በመንግሥት የተሾሙ አመራሮች ይህንን የማድረግ ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸው ሳያንስ፤ ጭራሽ በዚህ መንፈስ ይካሄዱ የነበሩ የሙስሊም ሊቃውንት ውይይቶችን ማሰናከላቸው እየታወቀ፣ የኢሕአዴግ መንግሥትን እና በእርሱ ሹማምንት የሚመራውን መጅሊስ ፀረ‑አክራሪ፣ ህዝበ ሙስሊሙን ግን የፖለቲካዊ እስልምና አስፋፊ አድርጎ ለመሳል የሚደረገው ሙከራ በጣም የሚያሳዝን እና የሚያስተዛዝብ ነው፡፡
ስለ እኛ ማን ይናገር …
ዊኪሊክስ ይፋ ያደረጋቸው የስቴት ዲፓርትመንት የ2010 ሰነዶችን ዋቢ በማድረግ በዳያስፖራ ራዲዮ በ‘ፖለቲካዊ እስልምና’ ዙርያ በቀረበው ዝግጅት ላይ የምናቀርበው ሌላው ዐብይ ሒስ፣ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ስለ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ማንነትና ምንነት ማን ነው የሚነግራቸው በሚል ጥያቄ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በእኛ እምነት ሙስሊም ላልሆኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ስለ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ማንነትና ምንነት በሦስተኛ ወገን ሊነገራቸው አይገባም፡፡ መንግሥታችን የገዛ ዜጎቹን፣ ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖቻችንም ለዘመናት አብረናቸው የኖርን ሙስሊም ወገኖቻቸውን በውጭ መንግሥት ዕይታ፣ ግንዛቤ፣ አረዳድና አስተሳሰብ ላይ ተመሥርተው ሊያዩን ይገባል ብለንም በፍፁም አናምንም፡፡ በእኛ እምነት ይህ ለዘመናት አብሮ በመኖር ያጎለበትነውን ተዋድዶ፣ ተፋቅሮና ተከባብሮ የመኖር ታላቅ እሴት ትርጉም‑አልባ የሚያደርግ የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡ …
**********
በኢትዮጵያ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በህዝብ ሀብት የሚንቀሳቀሱትና ሙሉ በሙሉ በኢሕአዴግ ቁጥጥር ሥር ያሉት መገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት አንስቶ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ያሉ የኢሕአዴግ ካድሬዎች፣ “ወሃቢ!” የሚለውን ስያሜ ህዝብን፣ በተለይም ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖቻችንን የሚያስፈራሩበት ጭራቅ አድርገውታል፡፡ … ከኩዌት መንግሥት በተገኘ የገንዘብ እርዳታ መስጊዶች መገንባታቸው አልያም አሮጌ መስጊዶች መታደሳቸው የወሃቢ እምነት መስፋፋቱን ይገልጻል ብሎ መደምደም የሚቻል አይመስለንም፡፡ በአዲስ አበባ ፒያሳ አቅራቢያ የሚገኘው ኑር (በተለምዶ በኒ) መስጂድ ከኩዌት በጎ አድራጊዎች በተገኘ የገንዘብ እርዳታ ነው ፈርሶ በአዲስ መልክ የተገነባው፡፡ ነገር ግን መስጂዱ የአንድ የተለየ አስተምህሮ ማስፋፊያ አይደለም፡፡
በምሥጢራዊ ሰነዱ ላይ ባህላዊ ወረራ በማስፋፋት የተጠቀሰችው ሳዑዲ አረቢያ፣ ከኢትዮጵያም በላቀ መልኩ ለዩናይትድ ስቴትስ ወዳጅ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ምናልባትም ሰነዱን ምስጢራዊ (Classified) ተብሎ እንዲፈረጅ ካደረጉት ነጥቦች አንዱ፣ “የሳዑዲ ባህላዊ ኢምፔሪያሊዝም” ‘ያሳስበኛል’ የሚለው የአሜሪካ መንግሥት በባህላዊ ኢምፔሪያሊዝም አስፋፊነቷ ከሚያማት አገር ጋር ባለው ወዳጅነት አኳያ ሰነዱ በሚያንፀባርቀው ተቃርኖ ላይ የተመሠረተ ይመስለናል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምና ፀጥታ ለምን ያሳስባታል አንልም፡፡ ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለቀጣናውም ሆነ በይበልጥም ለአገራችንና ለመላው ህዝቧ ሰላም፣ ዕድገትና ብልፅግና ያለን መቆርቆር ከዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የበለጠ እንጂ ያነሰ እንዳልሆነ ማንም ሊዘነጋው አይገባም፡፡ የአገራችን ሰላም፣ ፀጥታና ደኅንነት ቢረጋገጥ፣ ከሌሎች ወገኖቻችን ጋር የእነዚህ ዕሴቶች ትሩፋት በሆነው ዕድገትና ብልፅግና ተጠቃሚዎቹ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችም ነን፡፡ በአንፃሩ፣ የእነዚህ ዕሴቶች መጓደል ከሌሎች ወገኖቻችን ጋር ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችንም ጭምር ነው የሚጎዳው፡፡
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሃይማኖታችን ኢስላም የአገራችንን ሰላም የሚያውክ የየትኛውም የውጭ ኃይል መሣርያ እንዲሆን የምንፈቅድ ዜጎች አይደለንም፡፡ ነገር ግን በተለምዷዊ አሉታዊ ዕይታ፣ ሃይማኖታችን ኢስላምም ሆነ ተከታዮቹ ሙስሊሞች በድፍኑና በጭፍኑ የችግር ምንጮች ተደርገን መታሰብንም አንቀበልም፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከሃይማኖታችን ጋር ተያይዞ ለሚነሳ፣ ወይም ይነሳል ተብሎ ለሚታሰብ ማንኛውም ችግር የመፍትኄ አካል እንጂ የችግር ምንጭ አይደለንም፡፡ እዚህ ላይ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ እ.አ.አ ጁን 4 ቀን 2009 በካይሮ ዩኒቨርሲቲ፣ ግብፅ፣ ተገኝተው ለሙስሊሙ ዓለም ከደረጉት ታሪካዊ ንግግር ላይ መጥቀስ እንወዳለን፡‑ “ኢስላም ነውጠኛ ጽንፈኝነትን ለመዋጋት በሚደረገው ትግል ሰላምን እውን ለማድረግ የሚያግዝ አጋር እንጂ፣ ከቶም የችግሩ አካል አይደለም፡፡”
ፕሬዚደንት ኦባማ በዚሁ የካይሮ ታሪካዊ ንግግራቸው፣ “አንድን ንፁህ ነፍስ የገደለ፣ መላውን የሰው ልጅ እንደገደለ ነው፡፡ አንድን ንፁህ ነፍስ በግፍ ከመገደል ያዳነ መላውን የሰው ልጅ ያዳነ ያህል ነው” የሚለውን ቁርአናዊ ቃል ጠቅሰውታል፡፡ ይህ ቁርአናዊ ቃል ምንጊዜም ህያው ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በዚሁ መድረክ ላይ እንደተናገሩትም፣ “ከአንድ ቢሊዮን የሚበልጡ ተከታዮች ያሉትን ዘመናትን ያስቆጠረ እምነት ከጥቂቶች ጠባብ እና በጥላቻ ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ እጅግ የገዘፈ” የመሆኑ እውነታ ከቶውንም ሊዘነጋ አይገባም፡፡
የዊኪሊክስ ሰነዶች ይፋ ያደረጋቸው አዎንታዊ ነጥቦች
በዊኪሊክስ ላይ ይፋ ከተደረገውና የአሜሪካ መንግሥት፣ በአዲስ አበባው ኤምባሲው አማካይነት ካስተላለፈው መልዕክት ውስጥ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሃይማኖታዊ ትውፊቶችና ቁሳዊ ቅርሶችን ከጥፋት ለመታደግ አስቦ ያከናወናቸው ተግባራት ተጠቅሰዋል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በዚህ የአሜሪካ መንግሥት ተግባር በጣም ደስተኞች ከመሆናችንም በላይ ምስጋናችንም ከፍተኛ ነው፡፡ በእርግጥም፣ ጠንካራ የሃይማኖት ተቋም ቢኖረን ኖሮ፣ ይህ በእኛው ተቋም ሊፈፀም ይገባው የነበረ እጅግ ትልቅ ተግባር ነበር፡፡ እኛ ልንሠራው ይገባን የነበረውን ሥራ የአሜሪካ መንግሥት በራሱ ተነሳሽነት ስላከናወነልን እጅግ ትልቅ ውለታ እንደዋለልን ሳናወሳ አናልፍም፡፡
**************
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በላይኛው የሥልጣን እርከን ላይ ካሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት እስከ ወረዳ ያሉ የኢህአዴግ ካድሬዎች አለአንዳች እፍረት እኛን ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ስለ ሱፊያ እና ሰለፊያ ሊያስተምሩን ይገዳደራሉ፡፡ ካድሬ ጋዜጠኞችና የፌደራል ፖሊስም በመግለጫዎቻቸው፣ “ታላቁ መሪ” የተጠነቀቁትን ያህል እንኳ ሳይጠነቀቁ፣ “የወሃቢያ/ሰለፊያ ምንደኞች” እያሉ በአደባባይ አፋቸውን ይከፍቱብናል፡፡ ከቶውኑ እነዚህ ስያሜዎች ዊኪሊክስ ይፋ ካደረጋቸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምሥጢራዊ ሰነዶች የተለቃቀሙ አይደሉምን?! ለመጀመርያ ጊዜ ከሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አንደበት የተሰሙት “ነባሩ” እና “አዲሱ እስልምና” የሚሉ ስያሜዎችስ ከወዴት ተቃረሙና ነው እኛን ለመወንጀል ዊኪሊክስ የሚጠቀሰው?! … እኛማ ዊኪሊክስን እናመሰግነዋለን! ምክንያቱም፣ የተመሰገነው ዊሊያም አሳንጅ የኢሕአዴግ መንግሥትን በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት፣ በህዝብ‑ሙስሊሙ ተቋም ላይ ሹማምንቱን እንደሚያስቀምጥ ነውና ያጋለጠልን! …
የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት “የሳዑዲ ባህላዊ ወረራ” ሲል የጠራውን ይህን መሰሉን ተግባር ለመቀናቀን የወሰደው ለኢስላማዊ ቅርሶችና ታሪካዊ እሴቶች ጥበቃ እገዛ የማድረግ ባህላዊ መርኃ‑ግብር የሚደገፍ ቢሆንም፣ የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ህዝበ‑ሙስሊም ባሳተፈ መልኩ የተካሄደ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ኤምባሲው በህዝብ ካልተመረጠው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራር ጋር በመተባበር ያከናወናቸው የቅርስ ጥበቃና ተሃድሶ ተግባራት ብዙዎችን ከጀርባው ሌላ ዕኩይ ዓላማ ያዘለ ሳይሆን አይቀርም ወደሚል ጥርጣሬ ገፍቷቸዋል፡፡
የኢሕአዴግ መንግሥት፣ የቴልአቪቭ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሐጋይ ኤርሊች፣ ከሌላ አንድ ምሁር ጋር በጣምራ የሠሩትን ጥናት፣ እንዲሁም ምናልባት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ዶ/ር ዴቪድ ሺን በተለያዩ አጋጣሚዎች የሰጧቸውን የግል አስተያየቶች ዋቢ በማድረግ ይመስላል፣ አለ ብሎ የሚያስበውን የወሃቢያ አክራሪነት ለመቋቋም የአህባሽ አስተምህሮን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣትን እንደመፍትኄ አድርጎ ወስዶታል፡፡ መንግሥት ከወሃቢያ አስተምህሮ ሊመነጭ ይችላል ብሎ የሚያስበውን የ“አክራሪነት” ስጋት ለመቋቋም፣ ከላይ በተጠቀሱት ምሁራን “ለዘብተኛ” ተብሎ የተሞካሸውን ሊባኖስ‑ወለድ አስተምህሮ በህዝበ‑ሙስሊሙ ላይ ለመጫን የህዝበ‑ሙስሊሙን የጋራ ሃይማኖታዊ ተቋም (መጅሊስን) መሣሪያ ለማድረግ በመሻት በተቋሙ ላይ የአህባሽ አስተምህሮ ተከታዮችን ሾሟል፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ፣ በ2003 መገባደጃ ላይ የኢሕአዴግ መንግሥት “አክራሪነትን መዋጋት” በሚል ምክንያት፣ በዋነኛነትም የወሃቢያ አስተምህሮን ዒላማ በማድረግ የወሰዳቸው እርምጃዎችና፣ ይበልጡንም በህዝበ‑ሙስሊሙ ላይ የአህባሽን አስተምህሮ ለመጫን የተደረገው ሙከራ ከላይ የተጠቀሰውን ጥርጣሬ በማጠናከር እነሆ ሁለት ዓመታት ሊደፍን ለተቃረበው የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ መነሻ ሆኗል፡፡ መንግሥት ይህን ድርጊት በመፈፀም ከጣሰው ሕገ‑መንግሥት ባሻገር የህዝበ‑ሙስሊሙን የጋራ ተቋም ለአንድ እንግዳ አስተምህሮ ተከታዮች አሳልፎ በመስጠት የወሰደው እርምጃ በአገራችን በአስተምህሮ ላይ የተመሠረተ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ውጥረት ከመፍጠር በቀር ምንም ያመጣው አዎንታዊ ውጤት የለም፡፡ …
ላለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አጥብቀው እየተቃወሙ ያሉት እነዚህን የተሳሳቱ የችግር አፈታት መንገዶች ነው፡፡ የእኛ ሁኖ ሳለ የእኛ ያልሆነው የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ይህን የተሳሳተ የችግር አፈታት ከማረም ይልቅ፣ የተሳሳተው አካሄድ ዋነኛ ተዋናይ በመሆኑ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ በዋነኝነት ይህን ተቋም እውነተኛ የህዝበ ሙስሊሙ ተቋም በማድረግ ላይ ለማተኮር ተገዷል፡፡ በኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ዓመታት እየተካሄደ በሚገኘው የህዝበ‑ሙስሊሙ ሰላማዊ ትግል የተነሱት ቁልፍ ጥያቄዎች በግልፅ የሚያመለክቱትም ይህንኑ ሐቅ ነው፡፡ ሰላማዊ ትግሉ በጠራ ግንዛቤና ግብ ላይ የተመሠረተ፣ በመላው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚካሄድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ በአገራችን ሕገ‑መንግሥት በሠፈሩት የሃይማኖት ነፃነት ድንጋጌዎች ላይ እየተቃጡ ያሉ የመንግሥት ጥሰቶች እንዲቆሙ በግልፅ የሚጠይቅ እንጂ፣ ከቶውንም በሌላ እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ ዕኩይ ነገር ያለመና የተለመ አይደለም፡፡ ነገር ግን፣ ይህንን ህዝባዊ፣ ሕጋዊ እና ፍትኃዊ ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ብልህነት መሆኑን ያልተረዳው የኢሕአዴግ መንግሥት፣ የህዝበ‑ሙስሊሙን ጥያቄዎች ላለመመለስ በወሰደው፣ በእኛ እምነት ፍፁም የተሳሳተ ፖለቲካዊ ውሳኔ ምክንያት፣ የፕሮፖጋንዳ አውታሮችን በመጠቀም ጉዳዩን ወዳልተፈለገ እና አደገኛ ወደሆነ አቅጣጫ እየለጠጠው ይገኛል፡፡ ከእነዚህ አደገኛ አካሄዶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው በአገራችን ለረዥም ዘመናት በሰላምና በፍቅር አብሮ የመኖር እሴትን ባጎለበቱት የእስልምና እና የክርስትና ተከታይ ህዝቦች መካከል የእርስ በርስ ጥርጣሬና ግጭትን የመፍጠር ዕኩይ ስትራቴጂው ተጠቃሽ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ዲያስፖራ የራዲዮ ጣቢያዎች ዊኪሊክስን ዋቢ በማድረግ የቀረቡት ዝግጅቶች ይህንን ዕኩይ ዓላማ ከመመገብ ውጪ ለኢትዮጵያ ህዝቦች በሰላም እና በፍቅር መኖር የሚያበረክቱት አንዳችም አዎንታዊ አስተዋጽዖ ይኖራል ብለን አናምንም፡፡ በሰነዶቹ ላይ የተጠቀሱትን የአሜሪካ መንግሥት ፖለቲካዊ ምሥጢራት ልክ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ከክርስትያን ወገኖቻቸው የደበቁት ምሥጢር አስመስሎ ለማቅረብ መሞከር እጅግ በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ ከዚህ በላቀ የሚያሳዝነው ግን በዚሁ የራዲዮ ዝግጅት ጥቅም ላይ የዋሉት ምንጫቸው የማይታወቅ የድምፅ ግብዓቶች ናቸው፡፡ ከዓመታት በፊት በውሱን አካባቢዎች ከተከሰቱ ግጭቶች ውስጥ ስሜት ኮርኳሪ ድምፆችን እንደ በግብዓትነት ተጠቅሞ የሰዎችን ስሜት መኮርኮርም፣ ለአገር ሰላም ተቆርቋሪነትን ያሳያል ብለን አናምንም፡፡
ውድ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ራዲዮ “ጋዜጠኞች” እና የኢሕአዴግ የፕሮፖጋንዳ ድረ‑ገፆች ሆይ! ስለምን ተወናብዳችሁ የኢትዮጵያ ህዝብን ለማወናበድ ትሟሟታላችሁ?! እውን ተወናብዶ ህዝብን በማወናበድ አገር ይቀናል ብላችሁ ታስባላችሁን?! … እውነት እንላችኋለን፣ የምትጓዙበት መንገድ ደግ አይደለም፡፡ ግዴላችሁም አድምጡን፣ … እንደምናየው ደግ ነገርን አላለማችሁም፡፡ … ከመጎራበትም በላይ አንድ ግርግዳ ተጋርተው ለአያሌ ዓመታት በሰላምና በፍቅር በኖሩ ህዝቦች መካከል የጥላቻና የቁርሾ እሳትን ለመጫር የምትተጉት ከቶ ለዚህች አገር ምን ብትመኙላት እንደሆነ ሊገባን አልቻለም፡፡… እመኑን፣ ፍፁም በተሳሳተ መንገድ ላይ እየሄዳችሁ ነው፡፡ ግዴላችሁም ይህንን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ግሣፄ ከልቦናችሁ ሁናችሁ አድምጡት፡፡ … ወደ አቅላችሁ ብትመለሱ መልካም ነው፡፡ … ወደ አቅላችሁ ተመለሱና እንደማመጥ፡፡ … በሰላም መብታችንን በጠየቅን እየደረሰብን ያለው መገፋት ፈጽሞ ለርካሽ ፕሮፖጋንዳ ተንበርክከን የያዝነውን ሐቅ እንድንለቅ አያደርገንም፡፡ ይህንን ብታውቁት መልካም ነው፡፡ … ከእኛ ይልቅ እናንተ ፅንፍ ሄዳችኋል፡፡ … ግዴለም ዓይኖቻችሁን ክፈቱ፡፡
መልዕክታችንን ከፕሬዚደንት ኦባማ የካይሮ ንግግር በመጥቀስ እንደምድመው፡‑
“የግንኙነታችን ውል በልዩነቶቻችን ላይ እስከተመሠረተ ድረስ፣ ከሰላም ይልቅ ጥላቻን ለሚዘሩት፣ እንዲሁም መላ ሕዝቦቻችን ፍትኅና ብልጽግናን ያገኙ ዘንድ አስፈላጊ የሆነውን የትብብር መንፈስ ከማጎልበት ይልቅ የግጭትን ጎዳና መጥረግ ለሚሹት (ጽንፈኞች) ሁነኛ አቅም እንፈጥርላቸዋለን (የልብ ልብ እንሰጣቸዋለን)፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የጥርጣሬና የቅራኔ ዑደት ማብቃት አለበት፡፡”
No comments:
Post a Comment