Wednesday, August 28, 2013

አንድነት ፓርቲ በአሜሪካ ኤምባሲ ቅር መሰኘቱን ገለፀ

በዘሪሁን ሙሉጌታ

አንድነት ለዲሞክራሲ ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ቅር መሰኘቱን ገለፀ። ፓርቲው በኤምባሲው ላይ ቅሬታውን የገለፀው የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የስራ አስፈፃሚ አባል የሆነው ወጣት ዳንኤል ተፈራ ለፓርቲው የስራ ጉዳይ ለአንድ ወር ወደ አሜሪካ እንዳይሄድ በመደረጉ ነው።
የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሦ ጊዳዳና ወጣት ዳንኤል ተፈራ በጋራ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደተናገሩት ኤምባሲው ቪዛ በመከልከሉ የፓርቲውን ስራ መስተጓጎሉን ተናግረዋል።
ወጣት ዳንኤል ወደ ዋሽንግተን ለማቅናት ግብዣ የቀረበው አሜሪካን ሀገር በሚገኙ የፓርቲው ድጋፍ ሰጪ ቻፕተሮች አማካኝነት ሲሆን በቅርቡ ፓርቲው የጀመረው ‘‘የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት’’ የተባለውን ሕዝባዊ ንቅናቄ በአሜሪካን ተገኝቶ ገለፃ እንዲያደርግና ድጋፍ የማሰባሰቡን ተግባር ለማጠናከር ነበር።
ይሁን እንጂ ኤምባሲው የዳንኤል ተፈራን ወጣት መሆን በማየት ብቻ ቪዛ መከልከሉ የኤምባሲው የስራ ኃላፊዎችን የአመለካከት ችግር ማሳያ መሆኑን ወጣት ዳንኤል የገለፀ ሲሆን በቀጣይም ፓርቲው በዚሁ ጉዳይ ላይ ኤምባሲውን ማብራሪያ እንደሚጠይቅም አመልክቷል። ወጣት ዳንኤል ቪዛ ከማግኘቱ በፊት ደመወዙን፣ የቤት መኪና እና የቤት ካርታ በቅድመ ሁኔታ እንዲያቀርብ መጠየቁ አሳዛኝ መሆኑን ገልጿል።
‘‘እኔ ቤተሰብ ያለኝ ሀገሬን የምወድና ከፓርቲው ተልእኮ ውጪ አንድም ቀን በአሜሪካን ሀገር የመቆየት ፍላጎት የለኝም’’ ያለው ወጣት ዳንኤል በኤምባሲው ድርጊት ማዘኑን ገልጿል።
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ በአሁኑ ወቅት በሽብርተኝነት ክስ ጥፋተኛ ተብሎ ዕድሜ ልክ የተፈረደበት አቶ አንዱአለም አራጌ ቪዛ መከልከሉ አይዘነጋም።
ጉዳዩን በማስመልከት የኤምባሲውን የህዝብ ግንኙነት ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት ሮበርት ፖስትን ለማነጋገር ብንሞክርም ተንቀሳቃሽ ስልካቸው ባለመስራቱ ልናገኛቸው አልቻልንም።

No comments:

Post a Comment