· ኢቲቪ ክርክሩን መቼ እንደሚያስተላልፍ አልገለፀም
በዘሪሁን ሙሉጌታ
ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2005 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ውስጥ ኢህአዴግና አራቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በፀረ-ሽብር ሕጉ ላይ ለሦስት ሰዓታት ያደረጉት ክርክር በጉጉት እየተጠበቀ ሲሆን፤ ኢቴቪ ክርክሩን መቼ እንደሚያስተላልፍ ግልፅ አለማድረጉ በተከራካሪ ፓርቲዎች በኩል ቅሬታ አስነስቷል።
በክርክሩ ላይ የተሳተፉት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች መድረክ፣ አንድነት፣ ሰማያዊ እና ኢዴፓ ፓርቲዎች ሲሆኑ ኢህአዴግ በሁለት ተወካዮቹ በኩል ቀርቦ በክርክሩ ተሳትፏል።
በክርክሩ ወቅት ኢህአዴግን በመወከል የቀረቡት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማልና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የፕሬስና የፐብሊሲቲ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ጌታቸው ረዳ ሲሆኑ፤ ከአንድነት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ ከሰማያዊ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል፣ ከመድረክ አቶ በቀለ ነጋ እና ከኢዴፓ አቶ ሙሼ ሰሙ ናቸው።
በክርክሩ ወቅት አራቱ ፓርቲዎች ተመሳሳይ አቋም በማራመዳቸው ሚዛን መድፋታቸውን በክርክሩ ላይ የተሳተፉት አቶ ሐብታሙ አያሌውና አቶ ሙሼ ሰሙ ተናግረዋል።
በሕጉ ላይ አንቀፅ በአንቀፅ ለማወያየት ፍላጎት ቢኖርም በቅዳሜው ዕለት ክርክር ላይ ከሕጉ መሠረታዊ ጭብጦች ባለፈ ፖለቲካዊ ጎኑ ማመዘኑን ተከራካሪዎቹ ተናግረዋል። በቀጣይ በአወዛጋቢው የፀረ-ሽብር ሕግ ላይ አንቀፅ በአንቀፅ ለመወያየት ቀጠሮ መያዙንም አመልክተዋል።
ሕጉ ከወጣ ከአራት አመት በኋላ በተካሄደው በዚህ ክርክር ላይ በገዢው ፓርቲ ተከራካሪዎች በኩል ተቃዋሚዎች ኢትዮጵያ የፀረ-ሽብር ሕግ እንደማያስፈልጋት አድርገው ለማቅረብ የሞከሩ ሲሆን፤ በተቃዋሚዎች በኩል ሕጉ ከወጣ በኋላ የሀገሪቱ ሕዝቦች የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ጥሷል። ዜጎችም ሕጉ ከወጣ በኋላ በፍርሃት ድባብ ውስጥ እንዲሆኑና ጋዜጠኞችና የፖለቲካ አመራሮች መታሰራቸውን በመጥቀስ ተከራክረዋል።
የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ክርክሩን ቢቀርፅም በፕሮግራም መደራረብ እስካሁን አለማስተላለፉ ለድርጅቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልፀዋል። የፕሮግራም መደራረቡ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሙት ዓመት ጋር የተያያዘ እንደሆነም ተጠቅሷል።
No comments:
Post a Comment