Friday, March 20, 2015

ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው! በፍቅር

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው!›› በሚለው በዚህ የሰውን ክብርና ልእልና ከፍ ባደረገው ፍቅር፣ ሰብአዊነትና ርኅራኄ ልባቸው የተሸነፈ የመቄዶንያ መስራች ከሆነው ከአቶ ብንያም ጀምሮ በበጎ ፈቃደኝነት በማዕከሉ ውስጥ እያገለገሉ ያሉ ወገኖቻችን በየጎዳናው ላይ የወደቁ፣ እርጅና ተጫጭኖአቸው፣ ጉልበትና ጊዜ ከድቶአቸው፣ በመጦሪያቸው ዘመን የቀኑ ሐሩር የሌሊቱ ቁር እየተፈራረቀባቸው፣ አምስትና አስር ሳንቲም ፍለጋ የእኛን እጅ የሚጠባበቁ፣ መውደቂያና መጠጊያ የሌላቸውን ወገኖችን ሰብስበው ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ እፎይ እንዲሉ እያደረጉ ነው፡፡

መላ አካላቸው በቁስል ተመቶ፣ ሰውነታቸው በትል ተውርሶ፣ አካላቸው ተጎድቶ እጅግ በሚሰቀጥጥ ሁኔታ ያሉ ወገኖቻችንን ሰብስቦ አስፈላጊው እንክብካቤና የሕክምና ዕርዳታ እንዲያገኙ እያደረገ ያለው መቄዶንያ የብዙዎችን ልብ ለፍቅርና ለበጎ ሥራ እያነሳሳና እያበዛ እንዳለ ይሰማኛል፡፡ የአእምሮ ሕመም ተጠቂ የሆኑ እንደ እነ ያሬድ ያሉ በሚውሉበትና በሚያድሩበት ጫካ በአውሬ ተነክስው፣ ሰውነታቸው በስብሶና በትል ተወርሶ የተገኙ ወገኖች ዛሬ ከሥቃያቸውና ከሕመማቸው አገግመው፣ አካላቸው ድኖ ሌላውን ለመርዳት ደፋ ቀና ሲሉ ማየት ልዩ የሆነ የደስታ ስሜትን ያጭራል፡፡
እነዚህን ወገኖቻችንን እየተንከባከቡ ያሉ ሥራቸውና ስማቸው በአደባባይ ያልወጣ፣ ምስጋናም በይፋ ያልተነገረላቸው በጎ ፈቃደኛ ወገኖቻችን በብዙ ሊከበሩና ሊወደዱ ይገባል፡፡ ቁስላቸውን ሳይጠየፉ፣ ሕመማቸውና ሥቃያቸው እየተሰማቸው በብዙ ፍቅርና ርኅራኄ እነዚህን ወገኖችን በመንከባከብ እየተጉ ያሉ ወጣቶች ይህ በጎ ሥራቸው ሊደነቅና በእጅጉ ሊመሰገን የሚገባው ነው፡፡ ከዚህ ጋርም መቄዶንያ ‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው!›› በሚለው መርሕ ቃሉን በተመለከተ ባለፈው እሑድ በሚሊኒየም አዳራሽ ባደረገው የምስጋና እና የገቢ ማሰባበሲያ ዝግጅት ጋር በማያያዝ ሰው በመሆን ዙሪያ ጥቂት አሳቦችን ለማንሳት ወደድኹ፡፡
መቄዶንያ የአረጋውያንና አእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል መንግሥት በስጦታ ላበረከተለት 30 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ምስጋና ለማቅረብና በስጦታ በተገኘውም በዚህ ቦታ ላይም የሁልጊዜም አጋሩና ደጋፊው ከሆነው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመተባበር ለአረጋውያንና ለአእምሮ ሕሙማን ደረጃውን የጠበቀና ሁሉን አቀፍ አገልግሎት የተሟላለት አዲስ የመኖሪያ ሕንፃ ለመገንባት ታላቅ የሆነ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ባለፈው እሑድ በደመቀና በሞቀ ሥነ ሥርዓት አካሂዶ ነበር፡፡
በዚህ የምስጋና እና የገቢ ማሰባሰቢያ እለትም ‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው!›› የሚለው የመቄዶንያ ማዕከል መርሕ/መሪ ቃልም በሚሊኒየም አዳራሽ ነግሦና ገኖ ነበር ያመሸው፡፡ ይህ የማዕከሉ መርሕም የብዙዎችን ስሜትና ልብ የገዛና በርካታዎችም በፍቅር ተሸንፈው ለወገናቸው እጃቸውን እንዲዘረጉ ያነሳሳ ታላቅ የሆነ ሰብአዊነትን፣ ርኀራኄን ያዘለ መርሕ እንደነበር በዝግጅቱ ወቅት በነበረኝ ቆይታዬ ታዝቤያለሁ፡፡
‹‹ሰው ማለት ሰው የሚሆነው ሰው የጠፋ እለት›› ያለው አንድ አንጋፋና እውቅ የአገራችን አርቲሰት ማን ነበር?! ለጊዜው ስሙ ጠፍቶኛል፤ ግና ከዚህ አርቲስት አባባል ጀርባ አንድ ትልቅ እውነት አለ፡፡ ሰው የመሆን ታላቅ ክብርንና ልዩ ጸጋን እንድንመረምር፣ እንድንፈትሽ የሚያተጋን፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት የኖረው ግሪካዊው ፈላስፋ ዲዮጋን በአንድ ወቅት በአቴንስ ከተማ በጠራራ ፀሐይ ፋኖስ ይዞ ይዞር ነበር፡፡ ይህን እንግዳ ሥራውን ያዩ አቴንሳውያን ዲዮጋን በጠራራ ፀሐይ ፋኖስ ይዘህ የምትዞረው ለምንድን ነው ባሉት ጊዜ የሰጣቸው መልስ እንዲህ የሚል ነበር፡- ‹‹ሰው እየፈለኩ ነው!›› በእርግጥ በአቴንስ ከተማ ዲዮጋንን የከበቡት በርካታ ሰዎች ነበሩ፡፡ ግን በዲዮጋን እሳቤ እነዚህ ሰዎች ሰው ከመሆን ክብር የወረዱና የተዋረዱ፣ ፍቅርንና ራኅራኄን የተራቆቱ፣ በጎነትና ቅንነት አርቀው የገፉ፣ ሰው ሰው የማይሸቱ ሆኖ ስላገኛቸው ነበር ዲዮጋን በሰዎች መካከል ሆኖ ‹‹ሰው እየፈልኩ ነው!›› ሲል ለወገኖቹ በአደባባይ የተናገረው፣ የጮኸው፡፡
አዎን ዲዮጋን በወቅቱ የነበረበት ማኅበረሰብ ፍቅርን የተራቆተ፣ ስግብግብና አልጠግብ ባይ፣ ለእኔ ለእኔ ብቻ የሚል አውሬነት የነገሠበት፣ ጨካኝና ክፉ ቢሆኑበት ነው እረ ባካችሁ እናንተ ሰዎች ሰው ሁኑ ሲል የተጣራው፡፡ በመሠረቱ ሰው በመንፈሳዊው ዓለምም ሆነ በሳይንሱ ዓለም አስተምህሮና ትንታኔ አንፃር የፍጥረታት ሁሉ የበላይ እንደሆነ ነው ብዙዎች የሚስማሙት፡፡ አሁን በደረስንበት የእውቀትና የዕድገት ደረጃም የሰው ልጅ የፍጥረት ሁሉ ማእከልና መዳረሻ እንደሆነ ይታሰባል፡፡
በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖቶች አስተምህሮ መሠረትም በምድር ያሉ ፍጥረታት ሁሉም ለሰው ልጆች ጥቅምና ክብር ሲባሉ እንደተፈጠሩ ያስተምራሉ፡፡ እንዲሁም በሥነ ፍጥረት ታሪክ የፍጥረታት ቁንጮና ፍጻሜ የሆነው ሰው፣ ፍጥረትን ሁሉ እንዲገዛና እንዲነዳ የተሾመ ክቡር ፍጥረት እንደሆነ ይናገራሉ፣ ይተርካሉ፡፡
ስለሆነም በመንፈሳዊም ሆነ በሳይንሱ ዓለም ሰውን ከፍጥረታት ሁሉ በማላቅና በማክበር ረገድ ተመሳሳይ አስተምህሮ ወይም ግንዛቤ እንዳለ ልብ እንላለን፡፡ መቄዶንያ ‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው!›› የሚለው መርሕ ቃሉም/አባባሉ ከዚህ በሃይማኖቱም ሆነ በሳይንሱ ዓለም ስለ ሰው ተፈጥሮአዊ ማንነት፣ ጸጋና ታላቅ ክብር ካለው እውነታና ትንታኔ በመነሳት እንደሆነ አስባለሁ፡፡
ይኸውም ሰው የመሆን ምስጢር ውስጥ ሰውን ወደላቀ የሰውነት ደረጃና ከፍ ወዳለ መንፈሳዊ ክብርና ልእልና ከፍ የሚያደርግ፣ የሚያደርስ ፍቅር የተባለ ረቂቅና ታላቅ ኃይል አለ፡፡ ስለሆነም ፊት ለፊት በዓይናችን ከምናየው ከአካላዊ መገለጫው ባለፈ ሰውን ሰው ሊያሰኘው፣ ሰው ሰው እንዲሸት ሊያደርገው የሚችል ሰው በፍቅር፣ ስለፍቅር የተሰጠው ክቡር የሆነ የሰብአዊነት ሕያው ማንነትና ልዩ መገለጫ አለው ማለት ነው፡፡
ይህ ሰው የማንነት መገለጫው መለኮታዊ የሆነ የፍቅር መነሻና አሻራ ያለውና በሃይማኖቱ አስተምህሮ፣ ለዘመናት በተጓዘበት በባህሉ፣ በታሪኩና ሥልጣኔው ረጅም ጉዞው እያዳበረው የመጣ በልቡ ውስጥ የተተከለ ሕያው ማንነቱና ክቡር መገለጫው ነው፡፡ ስለዚህም ሰው ስንል ከሥጋው፣ ከመንፈሱና ከነፍሱ ጋር በጥልቅ የተሳሰረ የተለየ ማንነት ያለው ክቡር ፍጥረት እንደሆነ እየተናገርን ነው ማለት ነው፡፡
እንግዲህ ይህ ሰው የመሆን ታላቅ ክብርና ጸጋ የተጎናጸፈ የሰው ልጅ በተለያዩ አጋጣሚዎች በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ አደጋዎች ለራሱ መሆን ሲያቅተው፣ ሀብት ንብረቱ ሲጠፋ፣ ጉልበት ሲካደው፣ ወዳጆቹና ዘመዶቹ ሲጸየፉት፣ እርጅና ሲጫጫነው፣ ጧሪ ቀባሪ ሲያጣ፣ ተስፋው ተመናምኖ ቅስሙ ሲሰበር ‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው!›› አሊያም ‹‹ሰው ማለት ሰው የሚሆን ነው ሰው የጠፋ እለት!›› የሚለውን ታላቅ አባባል በፍቅር፣ በሥራ እንገልጸው ዘንድ ግድ የሚለን፡፡
እማሆይ ማዘር ተሬዛ አብዝተው በሚነሡበት በብዙዎቻችን ዘንድ በሚታወቀው አንድ ምርጥ አባባላቸው ጽሑፌን ላጠናቅ፡- ‹‹What matters a lot it is not what you are doing but the amount of love you put in doing that.››
ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው!

No comments:

Post a Comment