
ሀገራችን የአለማችን አካል እንደመሆኗ አንባገነኖች ተፈራርቀውባታል። አንባገነኖችም በህዝባዊ ሀይል ተጠራርገውባታል። ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ ትልቅ ወታደራዊ ሀይል የነበረው የትናንቱ ደርግ እንደ እንቧይ ካብ ሲናድ ተመልክተናል። አንባገነኖች መናገር እንጂ መስማት የማችሉ፤ ማየት እንጂ ማስተዋል የተሳናቸው በመሆናቸው እነሆ ዛሬም የወያኔ ዘረኛው ቡድን ህዝባ ላነሳው የነፃነትና የፍትህ ጥያቄ ያለ የሌለውን ወታደራዊ ሀይል በጠራራ ጸሀይ በማሰለፍ መቼውንም ያልተቻለውን ህዝብን በሀይል አሸማቆ ለመግዛት መከራውን ሲያይ ይስተዋላል። ለዚህም ነው ….. ከሌላው የሀገራችን ክልሎች ከፍ ባለ ሁኔታ የህዝባዊ እንቢተኝነት እየታየ ባለበት ጎንደርና አካባቢው በሰራዊት ማጥለቅለቅ የተያያዘው።
ለሚነሱ ህዝባዊ ተቃውሞዎችና ህዝባዊ የመብት ጥያቄዎች የሚሰጡት ምላሾች እስር፤ አፈናና ግድያ ከሆነ ህዝባዊ እንቢተኝነትን ማስከተሉ አይቀሬ ነው። በእስር ፤በአፈናና በግድያ እንዲሁም በሰራዊት ሀይል ህዝብን በማሸማቀቅ በስልጣን መቆየት የሚቻል ቢሆን ደርግም ከቤተ-መንግስት ባልወጣ፤ ወያኔም ዛሬ ከቤተ-መንግስቱ ባልተንፈላሰሰ ነበር። ይህ ደግሞ ሊያስተምር በተገባ ነበር።
እስከ ዛሬ የትኛውም አንባገነን ስርአት በሚተማመንበት የወታደራዊ ሀይል አማካይነት የመንኮታኮቻቸውን ሰዓት በአንድ ሰኮንድ ማዘግየት የቻለ እንደሌለ ሁሉ ወያኔም ያለ የሌለውን ወታደራዊ ሀይል ሲያርመሰምስ ውሎ ቢያድር ውድቀቱን በአንድ ሰኮንድ ማዘግየት እንደማይችል በተለይ እንቢ ለነፃነቴ፤ እንቢ ለሀገሬ… ብለን ለትግል የተነሳን ሀይሎች በመረዳት፤ ይበልጡኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተቀጣጠለ ያለውን ህዝባዊ እንቢተኝነት ይበልጥ እያሰፋን የጀመርነውን የነፃነት ጉዞ ከነፃነታችን አደባባይ ለማድረስ ሌት ተቀን የመስራት ሀላፊነታችንን መወጣት ይገባናል።
በጎንደር የሚታየውን የአልገዛም ባይነት ትንቅንቅ በሌሎች ክልሎችም በማቀጣጠል፤ በደብረወርቅ የታየውን የመምህራን የስራ ማቆም አድማ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በማስፋት፤ እንደ ድምፃችን ይሰማ ሁሉ ተቃውሞን ወደ እንቢተኝነት በማሸጋገር …… ወዘተ የነፃነታችንን ቀን ለማቅረብ መከፈል የሚገባውን መክፈል ይገባናል።
በደርግ የተነሳው እንቢተኝነት እያየለ ሲመጣ ያሰለፈው ሰራዊት ወያኔን አጅቦ የደርግን ቀብር እንደቆፈረለት ሁሉ ዛሬም በወያኔ ላይ እየተቀጣጠለ የሚገኘው ህዝባዊ እንቢተኝነት እየጠነከረ በመጣ ቁጥር የደረደረው ሰራዊት የወያኔን ቀብር ቆፋሪ ከመሆን እንደማይመለስ ከቅርብ ጊዜ ታሪካችን በመማር ነፃነታችንን ለማስከበር የጀመርነውን የእንቢተኝነት ትግል በመላው የሀገራችን ክፍሎች በማስፋፋትና በማቀጣጠል አይቀሬውን የወኔ ቀብር ለማቅረብ በአንድነት የነፃነት ጉዞውን እንቀላቀል። የጀመርነው የነፃነት ጉዞ መቆሚያው የነፃነታችን አደባባይ መሆኑን በተግባር ከምናሳይበት ወቅት ላይ እንገኛለንና በአንድነት እንነሳ!!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
No comments:
Post a Comment