Tuesday, March 17, 2015

በመልካም አስተዳደር ከአፍሪካ 52 አገራት ኢትዮጵያ 32ኛ! ለመልካም አስተዳደር መፍትሔው "በልማታዊነት ላይ በተመሠረተ የተራዘመ ትግል ነው" ኢህአዴግ

* የናሚቢያው ፕሬዚዳንት የሞ ኢብራሂም ሽልማትን አሸነፉ
የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን በየዓመቱ በሚያወጣው የአፍሪካ መልካም አስተዳደር ጠቋሚ ኢትዮጵያ ከ52 አገሮች 32ኛ ወጣች፡፡
እ.ኤ.አ. የ2014 የሞ ኢብራሂም የመልካም አስተዳደር ጠቋሚ ከ30 ገለልተኛ የአፍሪካና ዓለም አቀፍ ታማኝ ምንጮች የተገኙ ከመቶ በላይ መለኪያዎችን በመገምገም ነው የአገሮች የመልካም አስተዳደር ደረጃን ማውጣቱን የገለጸው፡፡ ዋነኛ መለኪያዎቹ አራት ምሰሶዎች መሆናቸውን የሚገልጸው ሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን፣ እነዚህም ሕዝቦች ከመንግሥታቸው የሚጠብቋቸውና መንግሥትም ማቅረብ የሚጠበቅበት ግዴታዎችን የሚዳስስ ነው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ምሰሶዎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ የመናገር ነፃነት፣ የንፅህናና የንብረት ባለቤትነት መብቶች ጥበቃን የሚዳስሱ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት ሞሪሺየስ፣ ኬፕ ቨርዴና ቦትስዋና ከአንድ እስከ ሦስተኛ ወጥተዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ፣ ሲሸልስ፣ ናሚቢያ፣ ጋና፣ ቱኒዚያ፣ ሴኔጋልና ሌሴቶ እስከ አሥረኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል ሩዋንዳ በ11ኛ ደረጃ፣ ኬንያ 17ኛ ደረጃ፣ ኡጋንዳ 19ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ ኢትዮጵያ 32ኛ ላይ ትገኛለች፡፡ ሶማሊያ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ስትገኝ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክና ኤርትራ ይከተሏታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን በየዓመቱ ለአፍሪካ መሪዎች የሚሰጠውን ሽልማት የሥልጣን ዘመናቸውን በማጠናቀቅ ላይ ለሚገኙት የናሚቢያው ፕሬዚዳንት አድርጓል፡፡ ይህ ሽልማት ላለፉት አራት ዓመታት ብቁ የሆነ መሪ ባለመገኘቱ ሳይካሄድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ሽልማቱ በሥልጣን ላይ እያለ ለአገሩ መልካም አስተዳደር ላሰፈነ፣ የሕዝቦቹን የኑሮ ደረጃ ከፍ ላደረገና በሰላማዊ ሽግግር ከሥልጣን ለወረደ መሪ የሚሰጥ ነው፡፡ ሽልማቱም በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ አምስት ሚሊዮን ዶላርና እስከ ዕድሜ ልክ ደግሞ በየዓመቱ 200 ሺሕ ዶላር ያስገኛል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2004 ጀምሮ ሁለት የሥልጣን ጊዜያትን ያሳለፉት የናሚቢያው ፕሬዚዳንት ሂፈክፑንዬ ፓሃምባ፣ በቅርቡ በተደረገ ምርጫ ላሸነፉትና ገና ሥልጣን ላልተረከቡት ሄግ ጌንጐበ ይለቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የዛሬ ዓመት አካባቢ የኢሕአዴግ ምክር ቤት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው “በልማታዊነት ላይ በተመሠረተ የተራዘመ ትግል ነው” በማለት በዚህ ረገድ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን አስታውቋል፡፡ በዚህም የሕዝብን እርካታ ለማረጋገጥ የተጀመረው ልማታዊ መንገድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በመላ አገሪቱ የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ ሁላችንንም ያግባባናል፡፡ የዚህ ችግር መሠረታዊ ምክንያት ምንድነው ብለን ስንጠይቅ መልሱን በቀላሉ እናገኘዋለን፡፡ በመላ አገሪቱ በመንሰራፋት ላይ ያለው ሙስና የመጀመሪያው ተጠያቂ ሲሆን የተሿሚዎች ብቃት ማነስ፣ የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ መኮስመን፣ ደንታ ቢስነትና በራስ ያለመተማመን ይጠቀሳሉ፡፡
የመልካም አስተዳደር ችግር ዋነኛ ጠንቅ የሆነው ሙስና ከአነስተኛው የአስተዳደር እርከን ከወረዳ ጀምሮ የፌዴራል መንግሥት መዋቅር ውስጥ ሰርጎ ገብቷል፡፡ አንድን አዋጅ ለማስፈጸም የሚወጡ መመርያዎችና ደንቦች የሚፈጥሯቸውን ክፍተቶች በመጠቀም ባለጉዳዮችን በማጉላላት በሕገወጥ መንገድ የሚጠቀሙ በዝተዋል፡፡ በመሬት አስተዳደር፣ በግንባታ ፈቃድ፣ በብቃት ማረጋገጫ፣ በንግድ ፈቃድ አሰጣጥና ዕድሳት፣ በገቢዎችና ጉምሩክ አሠራሮች፣ ማስረጃ በማረጋገጥ፣ በኮንዶሚኒየም ቤቶች አሰጣጥ፣ ወዘተ ተገልጋዩ ሕዝብ በሕግ የተከበረለት መብት ተጥሶ የሙሰኞች ሲሳይ እየሆነ ነው፡፡ አንገታቸውን ደፍተው የሚሠሩ ትጉሃን  ሠራተኞችን የሚያሳቅቁ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፡፡
በብዙዎቹ የአስተዳደር እርከኖች ላይ ተሿሚ የሆኑ ግለሰቦች ማንነት ሲታይ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በሚቻል ሁኔታ የገዥው ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ አባል በመሆናቸው ብቻ የማይመጥኑት ኃላፊነት ላይ ተቀምጠው ከሚያግበሰብሱት ሕገወጥ ጥቅም በተጨማሪ፣ በአቅም ማነስ ምክንያት ሥራ መሥራት ያቃታቸው አሉ፡፡ ድሮ ጠንካራ ግምገማና ቁጥጥር ስለነበር ራሱን ያላዘጋጀ ሰው ሥልጣን አያገኝም ነበር፡፡ ዛሬ የመልካም አስተዳደር ችግር የዜጎችን አዕምሮ እያወከ የለብ ለብ ግምገማ ሲደረግ እንኳን አይታይም፡፡ በዚህ ላይ ደንታ ቢስነትና በራስ ያለመተማመን ጣሪያ በመንካታቸው የሕዝቡ ምሬተ በየዕለቱ እየጨመረ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ችግር ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር እንዴት የተራዘመ ትግል ያስፈልጋል ይባላል? ደፋርና በራሱ የሚተማመን የነበረ ዜጋ ተሸማቆ አድርባይነት ሲነግሥ እንዴት ዝም ይባላል?
በየወረዳው፣ በየክፍለ ከተማውና የተለያዩ የአስተዳደር መዋቅሮች ለጉዳይ ሲኬድ ስብሰባ፣ ሥልጠና፣ ትምህርታዊ ጉብኝት፣ የአቅም ግንባታ፣ ልምድ ልውውጥ፣ ወዘተ እየተባለ ለስንት ጉዳዮች የሚውለው የአገሪቱ ሀብት ይባክናል፡፡ ከዚህ ሁሉ ግርግር በኋላ የአሠራር ወይም የአመለካከት ለውጥ አይታይም፡፡ ሥልጠናውና አቅም ግንባታው አስፈላጊ መሆኑ ባያጠራጥርም፣ ሥራ እየቆመ ለውሳኔ የሚፈለጉ ሹማምንት በየሰበቡ ሥራ ላይ አለመገኘታቸው ሌላው የመልካም አስተዳደር ጠንቅ ነው፡፡ ለአበልና ለተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች አንድ ወይም የተወሰኑ ሹማምንት ከአንድ መሥርያ ቤት በተደጋጋሚ ሲጠፉ ለስንቶች መከራ እንደሆነ አይታሰብም፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ችግር ፈጣን ዕርምጃ ወይስ የተራዘመ ትግል? (ምንጭ: ሪፖርተር)

No comments:

Post a Comment