Tuesday, March 24, 2015

‹‹ተወይኖብኛል›› … በዶ/ር አድማሱ ጸጋዬ ተልእኮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተባርሬአለኹ (ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ)

ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ከሦስት እሥርት ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ በሚሌኒየሙ መባቻ ወደ አገራቸው ተመልሰው ላለፉት ሰባት ዓመታት በማስተማር ሥራ ላይ ቆይተዋል፡፡ ምሁሩ በዋናነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር ቢሆኑም በሕግ ፋክልቲ፣ በሴንተር ፎር ሂዩማን ራይትስ፣ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ በአምስት ኪሎ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋክልቲ፣ በቴአትሪካል አርትስና በያሬድ የሙዚቃ ት/ቤትም አስተምረዋል፡፡ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት በተጠቀሱት የትምህርት መስኮች በተለያየ ጊዜ ሲያስተምሩ ቢቆዩም ከጠየቁት የዓመት ዕረፍት(sabbatical leave) ጋር ተያይዞ ከዩኒቨርስቲው መሰናበታቸው ተሰምቷል፡፡ በዚህ ዙሪያ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ከዶ/ር ዳኛቸው ጋራ ተከታዩን አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡
Dr Dagachew Assefa
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና በእርስዎ መካከል ምንድን የተፈጠረው?
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አስተዳደር ጋራ በሁለት ጥያቄዎች ዙሪያ የማይታረቅ ልዩነት ተፈጥሯል፡፡ በመጀመሪያ የዩኒቨርስቲው የሴኔት ሕግና የቅጥር ውሌ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው÷ አንድ መምህር ለስድስት ዓመት በተከታታይ ከአስተማረ፣ ለአገለገለበት ዘመን የአንድ ዓመት የጥናትና ምርምር ዕረፍት (sabbatical leave) እንደሚሰጠው ተደንግጓል፡፡ ሆኖም ግን ዩኒቨርስቲው ‹‹የጡረታ ሥርዓተ – ሒደቱን አላሟላኽም›› በሚል በሕጉ ፊት የማይጸና ሰበብ ፈጥረው ይገባኻል ብለው ከፈቀዱልኝ በኋላ መልሰው ነጥቀውኛል፡፡ ለማንኛውም መምህር ሥርዓተ ሒደቱን የማስፈጸም ሓላፊነት የሰው ሀብት አስተዳደሩ ድርሻ ሆኖ ሳለ እኔን ተጠያቂ ማድረጋቸው ብዙዎችን አስገርሟል::
በነገራችን ላይ የጥናት ዕረፍት ፈቃዴን የጠየኩት ከሦስት ዓመት በፊት፣ ስልሳ ዓመት ሳይሞላኝ ነበር፡፡ በየሰበቡ ሲጓተት ስለቆየ ወደ ስዲስ ዓመቱ ገደብ ደረስኩ፡፡ ጉዳዩ ወደ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት ከመሔዱ አስቀድሞ ውስጣዊ ተቋማዊ መፍትሔ ለማበጀት ወደ ዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ ቀርቦ ምላሽ ስጠባበቅ ከሦስት ወራት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ የሥራ ውሌን በተመለከተ፣ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል የእኔን የአገልግሎት ቆይታ እንደሚፈልግና በተለይም በቅርቡ ለሚጀምረው የሦስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ተሳትፎዬ እንደሚጠቅም በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ በመወሰኑ ውሌ እንዲራዘም ለማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ አካዳሚክ ኮሚሽን ጽፎልኝ ነበር፡፡ የማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ሓላፊዎች በተሰበሰቡበት፣ ኮሚሽኑ ጉዳዩን በአጀንዳ ይዞ ከተወያየበት በኋላ የፍልስፍና ትምህርት ክፍሉን ጥያቄ ዳግመኛ በሙሉ ድምፅ ተስማምቶበት፣ ውሳኔው በማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲኑ በፕ/ር ወልደ አምላክ በዕውቀት በኩል የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ይሁንታቸውን እንዲሰጡበት (እንዲያጸድቁት) ተጠይቆ ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቱ ግን ከአራት ወራት ያህል ቸልተኝነት በኋላ ‹‹ወረቀቱ ይመጣለታል›› በሚል ለተከታዩ ሴሚስተር እንዳልደለደል በአዲሱ ዲን በኩል ለትምህርት ክፍሉ ሊቀ መንበር መመሪያ አስተላለፉ፡፡ መመሪያው የእኔን መሰል ጥያቄ ባቀረቡ ሌሎች መምህራን ላይም የተላለፈ ነበር፡፡ ከሦስት ወራት በላይ ደመወዜን ይዘው መክፈል ከአቆሙ በኋላ ‹‹ለሚመጣው ሴሚስተር አትመድቡት›› ማለት በአካዳሚያ ቋንቋ ግለሰቡ ተሰናብቷል ማለት ነው፡፡
በመሠረቱ፣ የትምህርት ክፍሌና አካዳሚክ ኮሚሽኑ የሥራ ውሌን መራዘም ተስማምተው ላቀረቡት ጥያቄ ሲኾን እንደወጉ ማጽደቅ አልያም በአስቸኳይ ውሳኔን ማሳወቅ ሲገባ ፕሬዝዳንቱ ከሦስት ወራት በላይ ማቆየታቸው ኢ-ሕጋዊ ነው፤ ሕጉን ጠብቆ በወጉ ለቀረበ ጥያቄ ከሦስት ወራት በላይ ምላሽ አለመስጠት እብሪት፣ ትዕቢትና ማናለብኝነት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፤ በተመሳሳይ ወቅት አንድ ዐይነት ጥያቄ በደብዳቤ ከአቀረብነው መምህራን መካከል፣ ለምሳሌ ከኛው ትምህርት ክፍል ዶ/ር በቀለ ጉተማ በሥራው እንዲቀጥል በቃል ትእዛዝ ፈቅደው፣ ለእኔ በአግባቡ ውሳኔ ሳይሰጡ ‹በሚቀጥለው ሴሚስተር እንዳትመድቡት ማለት የአድልዎ አቀራረብ ብቻ ሳይሆን በዘፈቀደና በግፊት የሚካሔድ አመራር መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ በሌላ በኩል፣ ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር አድማሱ ዩኒቨርስቲውን ለመምራት ያላቸውን ብቃት ከዝህ ቀደም በአደባባይ ስለጠየቅሁ በቂም በቀልና ሁን ብለው እኔን ለመጉዳት የደረሱበት ውሳኔ ነው፡፡
የጥናትና ምርምር ዕረፍት(sabbatical leave) በተመለከተ በጊዜው የካሌጁ ዲን የነበሩት ዶ/ር ገብሬ ይንቴሶ የፕሬዝዳንቱን ፍላጎት ተከትለው ከላይ እንደጠቀስኹት የሰጡኝን ፈቃድ መልሰው ነጥቀውኛል፡፡ ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት ከማምራቴ በፊት፣ የፕሬዝዳንቱን ምላሽ ከወዲሁ ባውቀውም አቤቱታዬን የግድ ለእርሳቸው ማቅረብ ነበረብኝ፡፡
በኮሌጁ የቀድሞ ዲን ውሳኔ ላይ ከዐሥር ገጽ ያላነሰ አባሪ ሰነዶች አያይዤ ጠዋት ላቀረብኹት አቤቱታ፣ ከቀትር በኋላ ‹‹በጥልቅ መርምረን›› በሚል በአንድ መሥመር የኮሌጁ ውሳኔ እንደማይሻር የሚገልጽ ፌዝና የቀልድ ምላሽ ነው የተሰጠኝ፡፡ ይህ የሚያሳየው ፕሬዝዳንቱ ለዩኒቨርስቲው መምህራን ከበሬታ የሌላቸውና አመራራቸውም ከሞራላዊነት የተራቆተ መሆኑን ነው፡፡ እኔ ግን ታዋቂው አርበኛ አበበ አረጋይ በአንድ ወቅት በፋሽስት ጣልያንና በባንዳ ለተከቡበት የተራቡ ጭፍሮቻቸው ‹‹ሞተን አንጠብቃቸውም፤ ተረጋግታችኹ ብሉ›› እንዳሉት፣ ከማባረር ያልተናነሰ የዘገየ አንድ ብጣሽ ወረቀት ገና ለገና ይመጣል ብዬ ሞቼ አልጠብቃቸውም፡፡ የጡረታ ጊዜያቸው ደርሶ ለማራዘም የተፈቀደላቸው መምህራን አሉ ወይ? ማለትም በዩኒቨርስቲው አሠራር የጡረታ ጊዜያቸው የደረሰ መምህራን ውላቸውን ማራዘም ይችላሉ ወይ?
በተለምዶ ስድሳ ዓመት የሞላቸው መምህራን የውል ማራዘሚያ ጊዜ ይጠይቃሉ፡፡ እኔ የማውቃቸውና በተደጋጋሚ የተጨመረላቸው መምህራንም አሉ፡፡ በጣም አስገራሚና በግቢው አነጋጋሪ የኾነው የእኔና የዶ/ር መረራ ጉዲና የውል ማራዘሚያ ጊዜ መከልከሉ ነው፡፡
የዚኽ ኹሉ መነሻ ምንድን ነው ብለው ይገምታሉ?
ከሁሉ በፊት የእኔ መከልከልና መሰናበት ከፖሊቲካ እይታ አኳያ የመነጨ መሆኑ ማንም አይስተውም፡፡ ማለት… በዩኒቨርስቲው በማስተማር ሥራ በቆየኹባቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት፣ በጽሑፍና በተለያዩ መድረኮች የማደርጋቸው የዐደባባይ አእምሯዊ እንቅስቃሴዎች አልተወደደዱም፡፡ እንዲያውም ለሹመኞች ቅርበት ያላቸው አንዳንድ ወዳጆቼ እንዳጫወቱኝ፣ ‹‹ዳኛቸው፣ ዩኒቨርስቲውን እንደ ደጀንና ገዥ መሬት ተጠቅሞ መድፍ ሲተኩስብን ቆይቷል›› ተብዬአለሁ ፡፡ በርግጥ ይህ ዓይነቱ አቋም ከተወሰደ በኋላ በሥራ ገበታዬ እንድቀጥል አለመደረጉ አይገርመኝም፡፡
ለሰባት ዓመት ካስተማሩበት ዩኒቨርስቲ በዚህ መልኩ ሲሰናበቱ ምን ተሰማዎ?
እንደ እውነቱ ከሆነ የተደበላለቀ ስሜት ነው በውስጤ የተፈጠረው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይህ ነገር ከሰባት ዓመት በኋላ መሆኑ አስደስቶኛል፡፡ ይኸውም የመጣሁበትን የማስተማር ዓላማ ከሌሎች ባልደረቦቼ ጋር በመሆን ለመስኩ ተተኪና ምሉዕ የሆኑ ተማሪዎች ለማፍራት በመብቃታችን አስደስቶኛል፡፡ ይህ ክልከላና ስንብት በቂ ምሩቃን ባላፈራንበት ከሦስትና ከአራት ዓመት በፊት ቢከሠት ኖሮ አዝን ነበር፡፡
በሁለተኛ ደረጃ፣ ‹የዓመት ዕረፍት(ሳባቲካል) አይሰጥሆም፤ ከእንግዲህ ማስተማርም አትችልም› ስባል ለራሴ በጥልቀት ተሰምቶኝ ያልኩት፣ ‹‹አሁን ገና ኢትዮጵያዊ ሆንኩ፤ ኢትዮጵያዊ ማለት መብቱ የሚረገጥ ማለት ነው›› የሚል ነበር፡፡ በዚኽ ሰባት ዓመት ቆይታዬ ከአሜሪካ ሳልፈታ ይዠው የመጣኹት የነፃነትና የመብት አቅዋም፣ ከአገራችን ፖሊቲካዊ ነባራዊ ዕቀባ በተፃራሪው እንደ ልቤ እንድተችና ያለገደብ እንድናገር አስችሎኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ሥርዓቱ ‹ይኼ አሜሪካ አይደለም፤ እንደ ጎረቤትህ ሳሆን እንደቤህ እደር› ተብዬለሁ፡፡ ይህን ስል ግን፣ እኔ በዕድሜዬ የምወልዳቸው ልጆች በሆነ ባልሆነ ክሥ ወኅኒ ቤት ተወርውረው ባሉበት ሁኔታ ከሥራ አባረሩኝ ብዬ የማለቅስ ሰው አይደለሁም፡፡ በእኒህ ብሩህ ተስፋ ባላቸው ወጣቶች ላይ ከደረሰው አንጻር ሲታይ መብቴ መረገጡ እውነት ቢሆንም፣ የአገራችን ተረት ‹‹እናቱ ውኃ ልትቀዳ የወረደች ልጅና እናቱ የሞተችበት ልጅ አንድ ጋር ቆመው ያለቅሳሉ›› እንደሚባለው ይመስልብኛል፡፡
በመጨረሻም በአንድ በኩል፣ በውጭ ለብዙ ዓመት ቆይቼ ስመጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የት ከረምክ ሳይለኝ ችሎታዬ በሚፈቅድልኝ ቦታ ሥራ ሰጠኝ፡፡ ለዚህ ትልቅ ምስጋና ነው የማቀርበው፡፡ ሆኖም በሌላ በኩል የውስጥ አስተዳደሩና የውጭ የፖሊቲካ ኃይሎች በመተባበር መክረው ከሕዝብ ባገኘሁት ቸርነት ላይ ወይነውብኛል!
ከዚህ በኋላስ ምን ዓይነት ሥራ ላይ ለማተኮር ያስባሉ?
ይህን ጥያቄ ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ባለበት አገር ብትጠይቀኝ ኖሮ፣ ጉዳዩ በራሴ የሚወሰን በሆኑ አሁኑኑ እመልስልህ ነበር፤ ነገር ግን እንደ ቤትህ እደር ተብዬአሁና የጥያቄው ምላሽ በእኔ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ እንዲያውም ጥያቄው በአንድ ወቅት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ አሉ የተባለውን ያስታውሰኛል፡፡ አንድ ሹም ጃንሆይ ፊት ቀርበው የንጉሡ ትችትና ተግሣጽ ሲገጥማቸው፣ ‹‹እንዲያውም ግርማዊ ሆይ፣ የሰጡኝ ሹመት ይቅርብኝ፤ የአባቴን ርስት እያረስኩ እኖራለኹ›› አላቸው፡፡ ጃንሆይም ወዲያው ‹‹እርሱንም እኛ ስንፈቅድ ነው…›› ብለው አሉ ይባላል፡፡ እኔም እንደ አቅሜ ለመሥራት ፍላጎት ቢኖረኝም በቀጣይ ምን መሥራት እንደምችልና እንደማልችል ብያኔው በመሠረቱ ከእኔ ውጭ ነው፡፡ በተቻለኝ መጠን ግን በአለችኝ ቀሪ ዕድሜ አገሬን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ በቅርቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚገኝበትን ተቋማዊ ሁኔታ በተመለከተ አንድ ጽሑፍ እንደማስነብብ ከወዲህ ለማሳወቅ እወዳሁ ፡፡

No comments:

Post a Comment