Sunday, March 20, 2016

እነ ሌንጮ በጎቹን ለተኩላዎች አሳልፈው መስጠት የለባቸውም | ናኦሚን በጋሻው

naomibegachaw@gmail.com
በኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር፣ ኦዴግ ዉስጥ ያሉ አመራሮች በጣም የተከበሩ በሳል አመራሮች ናቸው። ለአመታት በትግሉ ዉስጥ ያለፉ፣ በርግጥም ለኦሮሞው ማህበረሰብ የሚበጀዉን እና የሚጠቅመዉን የተረዱ። በኦሮሞዉና በሌላው ማህበረሰብ መካከል አለመተማመን እና መጠራጠር እንዳለ ፣ ይሄንንም ለመግዛት እና ለመበዝበዝ እንዲያመቸው ሆን ብሎ ያደረገው ሕወሃት እንደሆነ በሚገባ የሚያውቁ። የኦሮሞው ማህበረሰብ ከሌላው ጋር ያለውን ግንኙነትና ትስስር አጠናክሮ ለሁሉም እኩል የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት ይቻል ዘንድ ፍላጎት አላቸው። በፖለቲካ አመለካከታቸው ጥሩ መስመር ላይ ያሉ ነው የሚመስሉት።
ሆኖም እነ ኦቦ ሌንጮ ጽንፈኛ የሆኑትን እነ ጃዋር መሐመድና፣ ገረሱ ቱፋ ያሉ ወጣት አክራሪዎችን የፈሩ ይመስላል። እነ ጃዋር በሶሻል ሜዲያው እና በሚቆጣጠሩት የኦሮሞ ሜዲያ ኔትዎርክ ብዙ ስለሚጮኹ ብዙ እየተሰሙ የነኦቦ ሌንጮ ድምጽ እንዳይሰማ አድርገዉታል ። Outshine አድርገዋቸዋል።

እነ ጃዋር ሞሐመድ ለኢትዮጵያ በተለይም ደግሞ ለኦሮሞ ማህብረሰብ በጣም አደገኛ ናቸው። የነርሱ አይነት አስተሳሰብ ያላቸው ብዙ ተከታዮች አሏቸው። የኦሮሞ እንቅስቃሴ መሪ እንደሆኑ አድርገው ነው ራሳቸውን የሚያቀርቡት። የኦሮሞዎች እንቅስቃሴ መሪ ባይሆኑም ደግሞ በብዙዎች ዘንድ መሪ እንደሆኑ ተደርጎ የሚታይበት ሁኔታም አለ። እንዲሁ እንደቀላል ችላ ሊባሉ የሚችሉ አይደሉም። እነዚህን ሰዎች ማስቆምና ፖለቲካቸውን ማሸነፍ የግድ ያስፈልጋል። ኦሮሞ ወገኖቻችን ለመብት፣ ለመሬት ባለቤትነት፣ ለፍትህ በሚያደርጉት ትግል በአጋዚ ታጣዊዎች እንደ ቅጠል ሲረገፉ፣ በሺሆች የሚቆጠሩ ሲደበደቡና ሲታሰሩ፣ እነ ጃዋር ፣ ይህን ለመብት የተደረገ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ የሆነ፣ አኩሪ ሕዝባዊ እንቅስቃሴን ጥላሸት እየቀቡት፣ የእንቅስቃሴዉን መልክ ለማስቀየር የሚያደርጉትን እኩይ ተግባራት ገደብ እንዲይዙ ማድረጉ የግድ ነው። በተለይም እነ ኦቦ ሌንጮ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ደፍረውና ጡንቻቸዉን አፈርጥመው መሪነታቸውን በማሳየት የነጃዋርን አክራሪ፣ ጽንፈኛ፣ ከፋፋይ፣ ጸረ-ኦሮሞ እና ጸረ-ኢትዮጵያ አካሄድ በቃ ሊሉት ይገባል። ነጩን ነጭ፣ ጥቁሩን ጥቁር ማለት መጀመር አለባቸው።
ኦሮሞዉን ከሌላው ለመለየት፣ “ይሄ የኦሮሞ መሬት ነው ፣ ያ የአማራ መሬት ነው ፣ ሌላው በኦሮሚያ የሚኖረው ኦሮሞው ሲፈቅድ ነው፤ ሌላው በኦሮሚያ ዉስጥ እንደ ኬንያናዊ ነው … “ እያሉ የጥላቻ ፕሮፕጋንዳ የሚረጩ፣ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ፣ እንደነ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ አብዲሳ አጋ፣ አባ መገርሳ (አቡነ ጴጥሮስ) …ያሉ ጀግኖች ዋጋ የከፈሉበትን የኢትዮጵያ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ እያራከሱና ሲያድ ባሬ እንዳደረገው እንደ ጠላት ሰንደቅ እያዩ፣ ዘረኛና ከፋፋይ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ለመብትና ለፍትህ የሚደረገዉን የኦሮሞዎችን እንቅስቃሴ እንዲጠልፉት መፍቀድ የለባቸው። እነዚህ አክራሪ ኃይሎች በተባበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ክንድ ያለምንም ጥርጥር መሸነፍ አለባቸው። ይሽነፋሉምም። ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው ኦሮሞ ያልሆነው ኢትዮጵያዊ ፣ እንዲሁም ከአንድ ሶስተኛ የሚሆነው ከኦሮሞው ማህበረሰብ፣ አብዛኛው፣ የጥላቻንና የመከፋፈልን ፖለቲካ አይፈለግም። የኦፌኮ አመራር የነበሩት፣ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ፓርላማ ላይ ስለዚች ፈታና ላይ ስላለች አገራችን ሲናገሩ “ኢትዮጵያችን” ነበር የሚሉት። ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያዊነትን የማሳነስ ፖለቲክ ማንም ሊታገሰው የሚገባ ፖለቲካ አይደለም።
የኦሮሞ ማህበረሰብ መሰረታዊን መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች አሉት።
ኦሮሞዎች የሚያኮራ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ አላቸው። እነዚህ የኦሮሞ ቅርሶች የኢትዮጵያ ቅርሶችም ናቸው። ሊጠበቁ፣ ሊስፋፋ፣ ሊከበሩ ይገባል። አፋን ኦሮሞ የሚናገሩ ወገኖች ቁጥራቸው እንዲቀንስ ሳይሆን የበለጠ ቁጥራቸው እንዲጨመር፣ አፋን ኦሮሞ mainstream የአገሪቷ ቋንቋ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፣ ያስፈልጋልም። ብዙ ቋንቋ ማወቅ በረከት ነው። በዚህ ረገድ ሌላው አፋን ኦሮሞ የማይናገረው ማህበረሰብ በጭራሽ ችግር አይኖረዉም፣ ሊኖረውም አይገባም።
ችግር የሚኖረው አማርኛን የአፋን ኦሮሞ ጠላት አድርጎ የማየት ዘረኛ አመለካከት ነው። አማርኛ በመነገሩ አፋን ኦሮሞን ማሳነስ አድርጎ በማየት፣ አፋን ኦሮምኛ ብቻ ይነገር ማለት ጉዳት አለው። የተፈለገውን ዉጤት አያመጣም። አዳማን መመልከት ይቻላል። በሕዝቡ ላይ አፋን ኦሮሞ ብቻ እንዲሆን ለማድረግ ላለፊት 25 አመታት ተሞከረ ግን አልተሳከም። ሰዎች በተገደዱ ቁጥር በዉስጣቸው ጥላቻን ይቋጥራሉ። ነገር ግን እንደ ሃረር ባሉ አካባቢዎች እንደነበረው (በዚያ ብዙዎች አማርኛም፣ አፋን ኦሮሞም የሚናገሩ ናቸው። እየመረጡ ነው የሚናገሩት) ፣ አፋን ኦሮሞን በቀኝ እጅ፣ አማርኛን በግራ እጅ ይዞ መቀጠል ይቻላል። ካስፈለገም ሌላም ሶስተኛ ቋንቋንም። አንዱ የሌላው ተቃራኒ ተደርጎ መታየት የለበትም። በዚህ መልኩ፣ በፍቅርና በመግባባት ከተቻለ አፋን ኦሮሞ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ክልሎች ብዙ ህዝብ እንዲናገረው ማድረግ ፣ ቋንቋዉን ማሳደጉ ላይ መስራቱ ይበጃል። ዋናው ፍቅርና ሕዝቡ በልቡ ፍላጎት እንዲያድርበት ማድረጉ ነው። እንኳን አፋን ኦሮሞ አያቶቻችን የተናገሩትን ቋንቋ ቀርቶ፣ እንደ ጣሊያንኛ፣ አረብኛ ፣ ፈረንሳይኛ የመሳሰሉትን ቋንቋዎችን የምናወቅ ብዙ አይደለንም እንዴ ?
የኦሮሞ ማህበረሰብ ከሌላው ማህበረሰብ በተለየ ኢኮኖሚካሊ በጣም የተገፋ ነው። አሁን ባለው ስርዓት marginalized የሆነ ነው። በኢትዮጵያ ቢያንስ ከሰባ በመቶ በላይ የኢኮኖሚክ እንቅስቃሴ ያለው በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ነው። ከአዲስ አበባ ወጣ ካልን ደግሞ እንደ አዋሳ፣ድሬዳዋ ..ባሉ ቦታዎች ነው። የትላንቷ ትንሿ ቢሾፍቱ እንኳን፣ የወለጋ ክፍለ ሃገር ዋና ከተማ ከነበረችው ከነቀምቴ፣ የአርሲ ዋና ከተማ ከነበረችው ከአሰላ፣ የኢሊባቡር ዋና ከተማ ከነበረችው ከመቱ የትናየት ወደላይ ተመጥቃለች። ከአዲስ አበባ በፊት የተቆረቆረችዋን አምቦን ብንመለከት፣ አዲስ አበባ ዙሪያ ያለችው ቡራዪ በልጣታለች። ወሊሶን ብንመለከት፣ አዲስ አበባ ዙሪያ ያለችው ሰበታ በልጣታለች። በትግራይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአራት ከተሞች ያርፋል። በኦሮሚያ ግን ጂማ ብቻ ነው የሚያርፈው። መቀሌ ከጅቡቲ ሁለት ወደቦች ጋር በባቡር መስመር ልትገናኝ ነው፤ እነ ነቀመቴ ግን ተረስተዋል። በአጭሩ ሁሉም ነገር አዲስ አበባና አዲስ አበባ አካባቢ፣ መቀሌ፣ ባህር ዳርና አዋሳ ነው። ይሄ ትልቅ ኢፍትሃዊነትና የኢኮኖሚክ ግፍ ነው።
አብዛኛው የኦሮሚያ ወጣት ሆን ተብሎ አማርኛ እንዳይማር በመደረጉ የኢኮኖሚክ እንቅስቃሴ ባለባቸው ትላልቅ ከተሞች ሥራ የማግኘት እድሉ በጣም የመነመነ ነው። አንድ ጊዜ አንድ ጽሑፍ አነበብኩ። የአንድነት ፓርቲ ልሳን የነበረችው ፍኖት ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ። ጸሃፊው ወደ ወለጋ ከአዲስ አበባ ሲሄዱ ባስ ላይ አንዲት ወጣት ያገኛሉ። በአፋን ኦሮሞ ጨዋታ ይጀምራሉ። በነቀምቴ የከፍተኛ ትምህርት እንደጨረሰች ትነግራቸዋለች። ግን አዲስ አበባ ለአንድ አመት ሥራ ፈልጋ ስላላገኝች ወደ ነቀምቴ እየተመለሰች እንደሆነ ገለጸችላቸው። አማርኛ ባለማወቋ። ይች ወጣት ለመሻሻል፣ ለማደግ የድርሻዋን ተወጥታለች። ብዙ ደክምለች። ግን ስርዓቱ፣ ሲስተሙ አንቆ ወደታች ቀበራት።ተስፋዋ ጨለመ።
አንድ ጊዜ ደግሞ በኦሮሚያ ሚንቀሳቀስ በአንድ የግል ኩባንያ ነው። ሁለት ሰራተኞች ይቀጠራሉ። ብዙም አልቆየም ሥራ አስኪያጁ ቢሮ ይጥራሉ። “ለምንድን ነው ሪፖርት በጽሁፍ የማታቀርቡት ?” ይላቸዋል። ሰራተኞቹ አማርኛ ትንሽ ትንሽ ይናገራሉ። በቃል ሪፖርት ሊያቀርቡ ሞከሩ። በጽሁፍ አቅርቡልኝ አላቸው። ሰራተኞቹ በጣም ጨነቃቸው። “ሪፖርቱን በቁቤ ብንጽፈዉስ ?” አሉ። አማርኛ መጻፍና ማንበብ ስለማይችሉ። ለኦሮሚያ እና ለወረዳው መንግስት የሚላኩ ደብዳቤዎችን በቁቤ የምትጽፍ፣ በቁቤ የተጻፉትንም ወደ አማርኛ የምትተረጉም አንዲት ሰራተኛ አለች። ከዚያ ዉጭ በመስሪያ ቤቱ ዉስጥ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ነበር። ሰራተኞቹ ለጊዜው የቁቤ አስተርጓሚዋ ሪፖርታቸውን እየተረጎመች እንድታቀርብ ተደርጎ በስድስት ወራት ውስጥ አማርኛ መጻፍ የማይችሉ ከሆነ፣ ከሥራ እንደሚሰናበቱ ተነገራቸው። እነዚህ ሰራተኞች ይሄንን እድል ያገኙት አማርኛ ትንሽ መናገርም በመቻላቸው ነው። እንጂ መጀመሪያዉኑ አይቀጠሩም ነበር። እንግዲህ አስቡት ምን ያህል ለኦሮሞ ወጣት ሥራ የማግኘት እድል በጣም የጠበበ መሆኑን።
አፈ ጉባኤው አብዱላ ገመዳ ልጆቻቸዉን ያስተማሩት በአዲስ አበባ የግል ትምሀርት ቤት ነው። ቅዱስ ዮሴፍ። ሌሎች የኦህዴድ አመራሮችም ለልጆቻቸው ምርጥ ምርጡን ነው የሰጡት። ድሃ የኦሮሞ ወጣቶች ግን እንዳይሻሻሉ፣ ሥራ እንዳያገኙ፣ ቀና እንዳይሉ አጥር ታጥሮባቸው እንዲቀመጡ ተደርገዋል። ይሄ የኢኮኖሚክ ባርነት ነው።
ምን ችግር ነበረው የኦሮሞ ወጣት በሌሎችም ቦታዎች compete እንዲያደርግ የሚፈለገው ስልጠናና ትምህርት ቢሰጠው ? ምን ችግር ነበረው እነ አባዱላና የኦህዴድ ባለስልጣናት ለነርሱ ልጆች ያደረጉትን እሩቡን እንኳን ለድሃው የኦሮሞ ወጣት ቢያደርጉ ? አዎን በኦሮሞ ወጣቶች ላይ ትልቅ በደል ነው እየተፈጸመ ያለው። የዚህ በደል ዉጤት የሆነው፣ ተስፋ መቁረጥና ሥራ አጥነቱ ነው በአሁኑ ወቅት ላለፉት አራት ወራት ሲደረግ የነበረውን ተቃዉሞ ያነሳሳው። ለዚህም ተጠያቂው ሕወሃት ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ልሂቃን ራሳቸው ናቸው።
ኢኮኖሚክ ኢፍትሃዊነቱ እንዲሰተካከል ፣ ሁሉም እኩል እንዲሆን፣ የልማት እንቅስቃሴ በሁሉም ቦታ ያለ አድልዎ እንዲስፋፋ፣ ባጀት ሲመደብ በእኩልነት እንዲሆን ለማድረግ የሚደረግን ትግል ሌላው ማህበረሰብም የሚጋራው ትግል ነው።
በመሆኑም አሁን እነ ኦቦ ሌንጮ፣ መሪነትን በማሳየት ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻቸው ጋር መሰረታዊ በሆኑ ጥያቄዎች ዙሪያ የጋራ ማኒፌስቶ በማዘጋጀት ትግሉን ማቀናጀት አለባቸው። ሌላው ማህበረሰብ የኦሮሞዎችን እንቅስቃሴ እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርበዋል። ተገቢ ነው። ሌላው ለምን አይቀላቀልም ብሎ መጠየቅ ሳይሆን፣ ሌላው ያልተቀላቀለበትን ምክንያቶች በመመረምር፣ ሌላው እንዲቀላቀል ማድረግ የሚቻልበት ሥራ መስራት ይጠበቅባቸዋል።
እዚህ ላይ ለነሌንጮ ማስታወስ የምፈለገው፣ ሌላውም ማህብረሰብ በወያኔዎች እጅ ተገድሏል። በወያኔዎች ብቻ ሳይሆን በዘረኛ አክራሪዎች ኦሮሞዎችን የተፈናቀሉ፣ የተገደሉ ብዙ እንዳሉ መርሳት የለባቸውም። ሁላችንም እየደማን ነው። ሁላችንም እየሞትን ነው። ሁላችንም ግፍ እየተፈጸመብን ነው። የአንዱ ሕመም ከሌላው አይብስም። የአንዱ ደም ከሌላው አይረክስም። ሁላችንም የአገዝዙ ገፈት ቀማሾች ነን። ኦሮሞ፣ አማራ፣ ጉራጌ መባባላችንን ትተን፣ እርስ በርስ መወነጃጀሉ ቆሞ፣ የራሳችንን ሳንወጣ ከሌላው መጠበቅ አቁመን፣ ለሁሉም ዜጎች መሰረታዊ መብት መከበር በጋራና በቶሎ መቆም አለብን። ለዚህም እነ ኦቦ ሌንጮ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ። ፍላጎቱ እንዳላቸው አውቃለሁ። ጥያቄዎቹ ድፍረቱና ቁርጠንኘቱ ይኖራቸዋል ወይ ? ከነ ጃዋርና ገረሱ ቱፋ የሚወረወሩትን ቅስቶች መመከት ይችላሉ ወይ ? የሚሉት ናቸው።
እነ ጃዋር አንድነትን አይፈለጉም። የኦሮሞ ማህበረሰብ ከሌሎች ጋር መተባበር ከጀመረ ተሰሚነት እናጣለን ብለው ይፈራሉ። ጥባቸው ከኢፍትሃዊነት ጋር ሳይሆን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ነው። በመሆኑም ነዳጅ እየጨመሩ፣ ወያኔዎች ካደረጉት በማይተናነስ መልኩ፣ የኦሮሞ ብሄረተኝነትን ከመጠን በላይ እየለጠጡ፣ በአገራችን የስርዓት ለዉጥ እንዲመጣ ቁልፍ የሆነውን የኢትዮጵያዊያን መሰባሰብ እንዳይኖር እንቅፋት እየሆኑ ነው።
እነ ኦቦ ሌንጮ ይሄንን ማስቆም አለባቸው። በኦሮሞው ማሀብረሰብና በሌላው መካከል መቀራረቡ መጠናከር አለበት። ከሌሎች ጋር በመሆን አንድ አገር አቀፍ ትብብር በመፍጠር የጋራ ጥሪ ቢያቀርቡ፣ በርግጠኝነት የትግሉ መስመር ይቀየራል። ለኦሮሞ ወጣቶች የሚያስቡና የሚቆረቆሩ ከሆነ የኦሮሞ ወጣቶች እየከፈሉት ያለው መስዋእትነት ዉጤት በሚያመጣ መልኩ እንዲቃኝና ሌሎችንም ባሳተፈ መልኩ የበለጠ እንዲያድግ ማድረግ አለባቸው። በጎችን ለተኩላዎች አሳልፈው መስጠት የለባቸውም።

No comments:

Post a Comment