Saturday, April 11, 2015

የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት

የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 1 የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 2 የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ ሚያዚያ 2006 አዲስ አበባ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 3 ለመግቢያ ያህል ኢትዮጵያና ሶማሊያ ከሀምሌ 1969 እስከ መጋቢት 1970 ባለው ጊዜ በዘመናዊው የአፍሪቃ ታሪክ ከታዩት ታላላቅ ጦርነቶች መካከል አንዱን አካሂደዋል፡፡ የጦርነቱ መከሰት የኢትዮጵያንም ሆነ የአፍሪቃ ቀንድን ጂኦ-ፖለቲካ ከስረ መሰረቱ ቀይሮታል፡፡ ይሁንና በሁለቱም ወገን ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበት የዚያ ታላቅ ጦርነት ታሪክ በአግባቡ አልተመዘገበም፡፡
ጊዜ በሄደ ቁጥር በጦርነቱ ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸው የጦር መሪዎችና ተዋጊዎች ከምድራዊው ህይወት በመሰናበታቸው የጦርነቱ ውሎ በመረሳት ላይ ይገኛል፡፡ በቅርብ ዓመታት የታሪክ ማስታወሻዎቻቸውን የጻፉ የጦር ጄኔራሎችና የፖለቲካ መሪዎችም ደግሞ ለኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ተገቢውን ሽፋን አልሰጡትም፡፡ በመሆኑም እኔ ጸሐፊው (አፈንዲ ሙተቂ) ስለጦርነቱ የማውቀውን ታሪክ በትንሹም ቢሆን ለጓደኞቼ ማሳወቅ አለብኝ በማለት በፌስቡክ ግድግዳዬ ላይ የኢትዮ-ሶማሊያን ጦርነት የዳሰስኩበትን መጣጥፍ በዘጠኝ ክፍሎች ሳስነብብ ቆይቻለሁ፡፡ እነዚያ ጽሑፎች ናቸው እንግዲህ በዚህ አነስተኛ ድርሳን በአንድ ላይ የተሰበሰቡት፡፡ ይህ ድርሳን የጦርነቱን ታሪክ ሙሉ በሙሉ ይተርካል የሚል እምነት ፈጽሞ የለኝም፡፡ ነገር ግን ስለያኔው ታሪክ ለማወቅ ለሚፈልጉ አንባቢያን የዐይን መግለጫ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለጦርነቱ መጻፍ ለሚፈልጉትም እንደ አቅጣጫ ጠቋሚ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡ ***** በዚህ ድርሳን ውስጥ የምታነቧቸው ጽሑፎቹ የቀረቡት በፌስቡክ ላይ በተነበቡበት አኳኋን ነው፡፡ በጽሑፎቹ ውስጥ የመረጃ መፋለስ እንዳይኖርም ጥረት አድርጌአለሁ፡፡ ታሪኩን ስጽፍ እስከመጨረሻው ድረስ የገለልተኝነት መርህን ለመጠበቅ ብሞክርም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ለሀገሬ (ለኢትዮጵያ) ማድላቴን አልደብቃችሁም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በሚመለከት ግን ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ ሆኜ ነው የጻፍኩት (የደርግ፤ የኢህአፓ፣ የምዕራብ ሶማሌ፣ የህወሐትም ሆነ የኦነግ ደጋፊ አይደለሁም)፡፡ ጽሑፎቹን ለማዘጋጀት የጠቀሙኝ መረጃዎች በሶስት ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡ እነርሱም 1. ጦርነቱ በተካሄደበት የምስራቅ ኢትዮጵያ ክልል ባሉት ከተሞች ውስጥ ከሚኖሩ የጦርነቱ ተካፋዮች፣ የጦርነቱ ተጎጂዎች፣ ምርኮኞች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የታሪክ አዋቂዎች የተገኙ የቃል መረጃዎች 2. ጦርነቱን ከሚተርኩ መጻሕፍት፣ ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና ጥናታዊ ጽሑፎች የተገኙ መረጃዎች የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 4 3. ከልዩ ልዩ የኢንተርኔት ምንጮች የተገኙ መረጃዎች ናቸው፡፡ ከመጻሕፍትና መጽሔቶች የተገኙ መረጃዎች የተሟሉ አይደሉም፡፡ በብዙ መጻሕፍት ውስጥ የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት እንደ ንዑስ ምዕራፍ ሆኖ ነው የቀረበው፡፡ በዚህ ረገድ ከሁሉም ተሽሎ የሚገኘው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም የጻፉት “ትግላችን” የተሰኘ መጽሐፍ ነው፡፡ በጦርነቱ ዙሪያ ጥናት ለሚያደርጉ ተመራማሪዎች ይጠቅም ዘንድ የአስፈላጊ መጻሕፍትን ዝርዝር በድርሳኑ የመጨረሻ ገጽ ላይ አስፍሬአቸዋለሁ፡፡ ***** ይህ ድርሳን የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ለሆኑ ወገኖቻችን ነው የተዘጋጀው፡፡ ሁኔታዎች የሚያመቹ ከሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያነበውን አንድ መጽሐፍ በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ዙሪያ ለማዘጋጀት እሞክራለሁ፡፡ እስከዚያው ግን ወዳጆቻችን በዚህች አነስተኛ ሙከራችን እንዲያዘግሙ በአክብሮት እንጠይቃቸዋለን፡፡ በድርሳኑ ላይ ሃሳብና ትችት ለመሰንዘር የሚፈልግ ካለ ደግሞ ከታች ባሉት የኢ-ሜይል እና የፌስቡክ አድራሻዎች መጠቀም ይችላል፡፡ መልካም ንባብ!! አፈንዲ ሙተቂ ሚያዚያ 15/2006 አዲስ አበባ ኢ-ሜይል፡- afandimutaqi2012@gmail.com ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/afendi.muteki.7 የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 5 የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ክፍል አንድ ===የልጅነት ትዝታ=== ሚያዚያ ወር 1970፡፡ በአብዛኛው በሚሊሺያ ሀይል የተገነባው የኢትዮጵያ ሰራዊት እብሪተኛውን የሶማሊያ ወራሪ ያባረረበት የካራ ማራ የድል በዓል በብሄራዊ ደረጃ እንዲከበር ተወሰነ፡፡ በመሆኑም በምስራቅ ኢትዮጵያ ዋና ዋና ከተሞች በአማርኛ እንዲህ እየተባለ ተዘፈነ፡፡ “አባርሮ ገዳይ በረሃ ያለው ጠላቱን ዛሬ አመድ አረገው” ድሉ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ድል ነው፡፡ ክርስቲያንም ሆነ ሙስሊም፣ ኦሮሞም ሆነ አማራ ሀገርን ከወራሪ ለማዳን በተደረገው ጦርነት ደሙን አፍስሷል፤ አጥንቱን ከስክሷል፡፡ በመሆኑም በውጊያው ከፍተኛ ተሳትፎ የነበረው የምስራቁ የኦሮሞ ህዝብ እንዲህ ሲል ዘፍኗል፡፡ Jijjigaa gadi Ogaadeenis tiyya Irrattin du’a biyya haadha tiyyaa በቀላል አማርኛ ስንፈስረው እንደዚህ ሊሆን ይችላል፡ “ከጅጅጋ በታች ኦጋዴንም የኔ ናት እሞትላታለሁ ሀገሬ እናቴ ናት” እነኝህ መዝሙሮች ከነፍስ ካወቅኩ በኋላም ይዘመሩ ነበር፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታዬ የሙዚቃ ክፍለ ጊዜአችንን ከሚያደምቁልን ዋነኛ ሙዝሙሮቻችን መካከልም ነበሩ፡፡ ***** የሀብሮ አውራጃ የኢሰፓ ኮሚቴ ጽ/ቤት የሚገኘው የገለምሶ ከተማን ከሰሜናዊ አቅጣጫ ከሚያዋስነው የካምቦ ተራራ ጥግ ነው፡፡ ከዚህ ጽ/ቤት አጠገብ “ቱታ በሪሳ” የሚባል አነስተኛ ኳስ ሜዳ አለ፡፡ በልጅነታችን ለኳስ ጨዋታ ከምንሄድባቸው ስፍራዎች አንዱ ይህ “ቱታ በሪሳ” ነው፡፡ ታዲያ “ቱታ በሪሳ” ስንሄድ ሁል ጊዜ ኳስ አንጫወትም፡፡ አንዳንድ ቀን የኳስ ጨዋታውን የሚያስጥለን ሌላ አስገራሚ መጫወቻ ነበረን!! ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 6 ከሀብሮ አውራጃ የኢሰፓ ጽ/ቤት አጠገብ ከቆርቆሮ የተሰራ አንድ አውሮፕላን ነበረ፡፡ ይህ አውሮፕላን በመጠኑ ከአንድ መለስተኛ አውቶቡስ ጋር ይስተካከላል፡፡ ነገር ግን ጎማም ሆነ ክንፍ የለውም፡፡ ምንም ነገር ሳይደግፈው ከመሬት ላይ “ዧ” ብሎ ተዘርግቷል፡፡ እኛም “ዛሬ በሰማይ ላይ ስበርር ነው የዋልኩት” ማለቱ ስለሚያስደስተን የኢሰፓ ዘበኞች በማይደርሱበት በኩል እየሾለክን ወደ አጸደ ግቢው እንገባና ተአምር እንሰራለን፡፡ ይህም ከአውሮፕላኑ ሆድ ገብቶ መጨፈር ነው፡፡ ድሮ ድሮ “አውሮፕላኑ የጣሊያን ነው፤ የኢትዮጵያ ጀግኖች ናቸው መትተው የጣሉት” እንል ነበር፡፡ ትምህርት ቤት ከገባን በኋላ ግን እውነታውን ለማወቅ ቻልን፡፡ ለዚህም የረዱን የሙዚቃ አስተማሪያችን የነበሩት ጋሽ ደመቀ ነበሩ፡፡ ጋሽ ደመቀ አንድ መዝሙር ካስዘመሩን በኋላ የአውሮፕላኑን እውነተኛ ታሪክ እንዲህ ሲሉ አወጉን፡፡ “ከኢሰፓ ጽ/ቤት አጠገብ ያለው አውሮፕላን የእውነት ጢያራ ሳይሆን ሞዴል አውሮፕላን ነው፤ በ1970 በካራ ማራ የተገኘውን ድል ለመዘከር ከተዘጋጀው የጅጅጋ ፌስቲቫል በጨረታ የተገዛ ነው፤ የሀብሮ አውራጃ ከአስራ ሶስቱ የሀረርጌ አውራጃዎች የበለጠ ዋጋ ስላቀረበ ነው ጨረታውን ያሸነፈው” ሳይታሰበን አጨበጨብን! “አውራጃችን አንደኛ ወጣ” ከተባለ ማጨብጨብ የዘመኑ ወግ ስለነበረ ማጨብጨቡን ተላምደነዋል! ጭብጨባው ጋብ ሲል ጋሽ ደመቀ ያስጨበጡንን መዝሙር መዘመሩን ቀጠልንበት፡፡ የመዝሙሩ ግጥም የሚከተለው ነው፡፡ “የኢትዮጵያ ጀግና ጀግና ነው ሄደ በረሃ ሚሊሻው ፊቱ ደም መስሏል ተቆጥቷል ሶማሊያ ዛሬ ፈርዶባታል፡፡ የሶማሊያ ጦር እርቦት ሰማይ ሰማዩን በማየት ቃፊሩ መጥቶ በድንገት ዳቦ አስመስሎ ቦምብ ጣለላት ዳቦ ነው ብላ ስትሻማ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 7 ተቀጣጠለች እንደ ሻማ፡፡ ***** በምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ “ካራ ማራ” የሚል ስያሜ ያላቸው ሆቴሎችና ሻይ ቤቶች በብዛት ይገኛሉ፡፡ በኔዋ ገለምሶም “ካራ ማራ” ሆቴል አለ፡፡ ሆኖም “ካራ ማራ” አኩሪ ጀግንነት የተፈጸመበት የድል ሜዳ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስረዱን ጋሽ ደመቀ ነበሩ፡፡ በርግጥም ካራ ማራ የኢትዮጵያ ጦር ትልቁን ድል የተቀዳጀበት ወሳኝ የትግል ሜዳ ነው፡፡ ጦርነቱ የተካሄደው በጄኔራል ዚያድ በሬ የምትመራው ሶማሊያ ኢትዮጵያን በመውረሯ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጦር በካራማራ ተራራ ላይ ታላቁን ድል እስኪያገኝ ድረስ በብዙ ሂደቶች ውስጥ ማለፍ ነበረበት፡፡ እነሆ 36 ዓመታት ወደ ኋላ ተጉዘን ያንን ጦርነት እንዘክረዋለን፡፡ ===ቅድመ-ታሪክ=== የእንግሊዝ ሶማሊላንድ የምትባለው ግዛት በ1952 ነጻነቷን ተቀዳጀች፡፡ ከአራት ቀናት በኋላ ደግሞ የ“ኢጣሊያ ሶማሊያ” የምትባለው ምድር ነጻ ሆነች፡፡ በወቅቱ “የተበታተኑትን የሶማሊ ግዛቶች አንድ ላይ ሰብስቦ ታላቋ ሶማሊያን መፍጠር” የሚል እሳቤ ይንቀለቀል ሰለነበር የሁለቱ ግዛቶች ፖለቲከኞችም የጉዞ መስመራቸውን በዚህ ፈር ለመቀየስ ወሰኑ፡፡ በመሆኑም ሁለቱ የሶማሊ ግዛቶች ከስድስት ወር በኋላ በመቀላቀል “የሶማሊ ሪፐብሊክ”ን መሰረቱ፡፡ እነዚያ የሶማሊያ መሪዎች በያዙት መሬት ሳይብቃቁ “እያንዳንዱ የሶማሊ መሬት በአዲሲቷ ሶማሊያ ስር መግባት አለበት” የሚል አቋም እንደ መርህ ያዙ፡፡ በመሆኑም “ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ የያዙትን መሬቶቻችንን እንፈልጋለን” የሚል ሰበካ ጀመሩ፡፡ በዚያ ወቅት ጅቡቲና ኬኒያ ነጻነታቸውን አልተጎናጸፉም፡፡ ስለዚህ ሶማሊዎቹ ከቅኝ ገዥዎቹ ፈረንሳይና እንግሊዝ ጋር መጋጠም እንደማያዋጣቸው ስላወቁ ትኩረታቸውን በኢትዮጵያ ላይ አደረጉ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላም አነስተኛ የሰርጎ ገብ ሃይል በማደራጀት በምስራቅ ኢትዮጵያ ያለውን ቆላማውን የኦጋዴንን ክልል ለመውረር ሞከሩ፡፡ ነገር ግን በጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም የሚመራው ሶስተኛ ክፍለ ጦር በአስር ቀናት ውስጥ ሶማሊዎቹን አባረራቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ሶማሊዎቹ በኢትዮጵያ ላይ የፕሮፓጋንዳ ጦርነት አፋፋሙ፡፡ በ1955 የተመሰረተው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ሊገስጻቸው ቢሞክርም እነርሱ ግን ከአድራጎታቸው አልታቀብ አሉ፡፡ መሪያቸው የነበረው አደን አብደላ ዑስማን ዳሂር በአዲስ አበባ በተሰበሰበው የአፍሪቃ መንግሥታት ጉባኤ ላይ “ኢትዮጵያ መሬታችንን ወስዳለች” ሲል ከሰሰ፡፡ በአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ማቋቋሚያ ቻርተርም ላይ “የአፍሪቃ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ ሲወጡ ያላቸውን ድንበር ይዘው ይቆያሉ” የሚለውን አንቀጽ አልፈርምም አለ፡፡ በ1957 ደግሞ ሶማሊያ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 8 በይፋ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አወጀች፡፡ ይሁንና ጦርነቱ ረጅም ጊዜ ሳይቆይ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ሶማሊያ ከ1957 ሽንፈት በኋላ ይፋዊ ጦርነቱን ትታ በእጅ አዙር መዋጋቱን ነው የመረጠችው፡፡ ለዚህም ይረዷት ዘንድ “የኦጋዴን ሶማሊ አርነት ግንባር” እና “የምዕራብ ሶማሊ ነጻነት ግንባር” (ም.ሶ.ነ.ግ) የተባሉ ድርጅቶችን አቋቋመች (የኦጋዴን ሶማሊ አርነት ግንባር ከአሁኑ “የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር” ጋር አንድ አይደለም፡፡ አሁን ያለው “ኦብነግ” በ1975 ነው የተመሰረተው)፡፡ የነዚህ ድርጅቶች ዓላማ የኦጋዴንን ክልል ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ወደ ሶማሊያ መቀላቀል ነበር፡፡ ይሁንና ድርጅቶቹ ኦጋዴንን ሊገነጥሉት ይቅርና የሚረባ ውጊያ እንኳ ማድረግ አልቻሉም፡፡ በዚህም የተነሳ ከሁለቱ ድርጅቶች መካከል በደካማ አቋም ላይ የነበረው የኦጋዴን ሶማሊ አርነት ግንባር ብዙም ሳይራመድ ከስሟል፡፡ ም.ሶ.ነ.ግ ግን እየተንደፋደፈም ቢሆን ውጊያውን ቀጥሏል፡፡ ጄኔራል ሙሐመድ ዚያድ ባሬ ጥቅምት 1962 በመንፈቅለ መንግሥት ስልጣን ሲይዙ ደግሞ ሁሉም ነገር ከመሰረቱ ተቀየረ፡፡ “ሶማሊያ ከኢትዮጵያ የምትፈልገው ኦጋዴንን ብቻ አይደለም” ተባለ፡፡ “በኢትዮጵያ የተወሰደብን መሬት የሀረርጌ፣ ባሌ እና ሲዳሞ ክፍለ ሀገራትን የሚያጠቃልል ነው” የሚል አዋጅ ታወጀ፡፡ ይህ ሰፊ ግዛት በጥቅሉ “ሶማሊ ገልቤድ” (ምዕራብ ሶማሊያ) ተብሎ ተሰየመ፡፡ “በውስጡ የሚኖሩት ሶማሊ ያልሆኑ ህዝቦችም ከጊዜ ብዛት ቋንቋቸው ቢቀየርም ጥንተ ማንነታቸው ሶማሊ ነው” ተብሎ ተነገረ፡፡ በሶማሊያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ስደተኞችም አዲሱን መርህ እንዲያቀነቅኑ ተገደዱ፡፡ “እምቢ” ያሉት ደግሞ ወደ እስር ቤት ተወረወሩ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በባሌና በሲዳሞ ክፍለ ሀገራት የሚደረገውን ውጊያ የሚያስተባብር “የሶማሊ አቦ ነጻነት ግንባር” (ሶ.አ.ነ.ግ) የተባለ ድርጅት ተመሰረተ፡፡ በጥቅሉ የሶማሊያ መንግሥት “ከአዋሽ ወንዝ በታች ያለው መሬት በሙሉ የኔ ነው” የሚል አቋም ማራመድ ጀመረ፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ የሶማሊያ መንግሥት የሶሻሊዝም ተከታይ መሆኑን በይፋ በማወጁ ከሶቪየት ህብረት ጋር የወታደራዊ ተራድኦ ስምምነት ተፈራራመ፡፡ በስምምነቱ መሰረት ከሶቪየት ህብረት አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን በገፍ አገኘ፡፡ ለሰባት ዓመታት ያህልም ሰራዊቱን ሲያሰለጥንና ሲያደራጅ ሰነበተ፡፡ በውጤቱም የዚያድ ባሬዋ ሶማሊያ ከ70 የማያንሱ ዘመናዊ የውጊያ አውሮፕላኖችን የታጠቀ አየር ሀይል እና አራት ሜካናይዝድ ክፍለ ጦሮችን ያቀፈ ግዙፍ የጦር ሰራዊት ባለቤት ለመሆን ቻለች፡፡ እንግዲህ የሶማሊያ መንግሥት ይህንን ሁሉ ካደረገ በኋላ ነው በኢትዮጵያ ላይ ወረራ የፈጸመው፡፡ ***** ሚያዚያ 4/2006 ተጻፈ፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 9 የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ክፍል ሁለት === የድብቅ ወረራ=== የሶማሊያ መንግሥት ወረራውን በቀጥታ አልጀመረም፡፡ በቅድሚያ በድብቅ ያደራጃቸውን የምዕራብ ሶማሊ ነጻ አውጪ ግንባር/Western Somali Liberation Front (ም.ሶ.ነ.ግ- WSLF) እና የሶማሊ አቦ ነጻነት ግንባር/ Somali Abo Liberation Front (ሶ.አ.ነ.ግ- SALF) አሸማቂዎችን በማስቀደም ነው እድሉን የሞከረው፡፡ በዚህም መሰረት በመጋቢት ወር 1968 የም.ሶ.ነ.ግ ተዋጊዎች ከሀርጌሳ መስመር እየተነሱ በኦጋዴንና በደጋማው የሀረርጌ ክፍል ተሰማሩ፡፡ የሶ.አ.ነ.ግ ተዋጊዎች በበኩላቸው በባሌ ክፍለ ሀገር ወደ ውስጥ እየሰረጉ እስከ ጊኒር እና ጎሮ አውራጃዎች ድረስ ለመግባት ቻሉ፡፡ እነዚህ ሀይሎች ወደ ኢትዮጵያ በገቡበት ወቅት የደርግ መንግሥት ከኢህአፓ ጋር በገጠመው ትግል እየተናጠ ነበር፡፡ ጀብሃና ሻዕቢያም በሰሜኑ በኩል ወጥረው ይዘውታል፡፡ ኢዲዩ የተባለው ድርጅትም የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የጠረፍ ከተሞችን ይዞ ደርግን በማስጨነቅ ላይ ነበር፡፡ የም.ሶ.ነ.ግ እና የሶ.አ.ነ.ግ ሀይሎች እንደሚፈልጉት ድል ሊቀናቸው አልቻለም፡፡ ራቅ ባሉ ጫካዎችና ጥሻዎች ከመመሸግ በስተቀር ወደ ከተሞች እየተጠጉ የኢትዮጵያን ሰራዊት ማስጨነቅ አልቻሉም፡፡ በመሆኑም የሲቪል ልብስ የለበሱ የሶማሊያ ሰራዊት አባላት በም.ሶ.ነ.ግ ውስጥ በብዛት እንዲቀላቀሉ ተደረገ፡፡ ነገር ግን ይህኛውም ስትራቴጂ ውጤት ማስገኘት አልቻለም፡፡ ሁለቱ የም.ሶ.ነ.ግ እና የሶ.አ.ነ.ግ. ሀይሎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የትኛውንም ከተማ መቆጣጠር ተስኗቸው ነበር፡፡ በዚህ ተስፋ የቆረጡት የሶማሊያ የጦር አዝማቾችም ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ መደበኛ ሰራዊታቸውን እንዲያንቀሳቅሱ ይወተውቷቸው ጀመር፡፡ ፕሬዚዳንት ዚያድ ግን ለጦር አዝማቾቹ ውትወታ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት አልፈለጉም፡፡ ይህም የሆነው ከሶቪየት ህብረት አማካሪዎቻቸው የተሰጣቸውን ተግሳፅ በመፍራታቸው ነው፡፡ ሶቪየቶቹ “ኢትዮጵያን እየወረራችሁ ነው” የሚል ስሞታ ሲያቀርቡባቸው “እኛ አይደለንም፤ የኦጋዴን ሶማሊዎች ለነጻነታቸው የሚያደርጉት ትግል ነው” እያሉ ሲከላከሉ ቆዩ፡፡ በግንቦት ወር 1969 ደግሞ ያልተጠበቀ ክስተት ተፈጠረ፡፡ የጎዴ ከተማን እንዲያጠቃ የታዘዘ አንድ የም.ሶ.ነ.ግ ሻለቃ ከኢትዮጵያ ጦር በገጠመው የመከላከል እርምጃ ሙሉ በሙሉ ተደመሰሰ፡፡ 300 ያህል ተዋጊዎቹ በአንድ ቀን አለቁበት፡፡ በርካቶችም ቆሰሉ፡፡ የሽምቅ ተዋጊውን ቡድን እንዲመሩ የተመደቡ አስራ አራት የሶማሊያ የጦር መኮንኖችም ከሟቾቹ መሀል ነበሩ፡፡ ይህ ክፉ ዜና በሞቃዲሾ ሲሰማ በጦር ሀይሉ ውስጥ ከፍተኛ ቁጣ ተቀሰቀሰ፡፡ በፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ የሚመራው የሶማሊያ ከፍተኛ አብዮታዊ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር አስቸኳይ ጠራ፡፡ በስብሰባው መጨረሻ ላይ በተደረሰበት ስምምነት መሰረትም ለአንድ ወር የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 10 ያህል የድብቅ ወረራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተወሰነ፡፡ በዚህ ጊዜ ትኩረት የተደረገባቸው ከተሞች በኢትዮ-ሶማሊያ-ኬንያ ድንበር አቅራቢያ የምትገኘው የዶሎ ኦዶ ከተማ፣ በደቡባዊ ኦጋዴን የምትገኘው የባሬ ከተማ እና በደቡባዊ ባሌ ያለው የኤልከሬ ቆላማ ስፍራ ነው፡፡ በዚህ የድብቅ ውጊያ ወደ ኢትዮጵያ የዘመተው የሶማሊያ ሰራዊት መደበኛ ዩኒፎርም እንዲለብስ አልተደረገም፡፡ የዚህ ድብቅ ውጊያ ዓላማ የኢትዮጵያን ሰራዊት ማስበርገግና የውጊያ አቋሙን መፈተሽ ነበር፡፡ ====የይፋ ወረራ=== ሀምሌ 15/1969፡፡ በድብቅ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ አበቃ፡፡ ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ የታላቋ ሶማሊያ ምስረታ እውነት የሚሆንበት ጊዜ የመጣ መስሎ ታያቸው፡፡ በመሆኑም ለዘመናት ሲያደራጁት የነበረው ሰራዊት በሙሉ ሀይሉ ማጥቃት እንዲጀምር ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ለዓመታት ለወረራ ሲዘጋጅ የነበረው የሶማሊያ የጦር ሀይል በኢትዮጵያ መሬት ላይ ዘመተ፡፡ የሶማሊያ ጦር ወደ ኢትዮጵያ የገባው በሁለት መስመሮች ነው፡፡  የኦጋዴን መስመር፡ በዚህ መስመር ወደ ኢትዮጵያ የገባው የሶማሊያ ጦር በኦጋዴን የፌርፌር ከተማ ትይዩ ካለችው የበለድወይን ከተማ ነው የተነሳው፡፡ የመጨረሻ ግቡ ደግሞ መላውን የኦጋዴን ቆላማ አውራጃዎች መቆጣጠር ነው፡፡  የዶሎ ኦዶ መስመር፡ በዚህኛው መስመር የተሰለፈው ጦር የተነሳው ደግሞ ከሶማሊያዋ የባይዶዋ ከተማ ነው፡፡ ዶሎ ኦዶ ከምትባለው የድንበር ከተማ ከደረሰ በኋላም ለሁለት በመከፈል ወደ ባሌና ሲዳሞ ክፍለ ሀገራት እንዲዘምት ነው የታሰበው፡፡ በሁለት የተከፈለው ሰራዊት የመጨረሻው ግብ የባሌ ጎባ እና ነጌሌ ቦረና ከተሞችን መቆጣጠር ነው፡፡ ከባይዶዋ አካባቢ የተነሳው የሶማሊያ ጦር ይህ ነው የሚባል መከላከል አልገጠመውም፡፡ በመሆኑም በሲዳሞ ክፍለ ሀገር ወደ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ እየገሰገሰ ሄዶ ከነጌሌ ቦረና ከተማ 40 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ደረሰ፡፡ በባሌ ክፍለ ሀገር ደግሞ እስከ ደሎ መና (መስሎ) ከተማ ያለውን መሬት ለመያዝ ቻለ፡፡ ሶማሊዎች ውጊያው እንዲህ የቀለላቸው ብዛታቸው ስለረዳቸው አልነበረም፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያ በነዚህ መስመሮች ጠንከር ያለ ሰራዊት ስላልነበራት ነው፡፡ የነጌሌ እና የጎባ ከተሞች እንኳ በጠላት እጅ ከመውደቅ የተረፉት የኢትዮጵያ አየር ሀይል ለእግረኛ ተዋጊዎቹ ከፍተኛ የሽፋን እገዛ በማድረጉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሀይል የሶማሊያ ባለጋራውን በዐይነ ቁራኛ ሲጠብቅ የነበረው በኦጋዴን መስመር ነበር፡፡ በመሆኑም ከበለድወይን የተነሳው የሶማሊያ ሰራዊት የኦጋዴን አውራጃዎችን በቀላሉ ለመቆጣጠር አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያ ተዋጊዎች ኦጋዴንን ላለማስነጠቅ እስከ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 11 መጨረሻው ተሟሙተዋል፡፡ በተለይም በሐምሌ አጋማሽ (1969) ማብቂያ ላይ የቀብሪደሃር ከተማን ላለማስለቀቅ በተደረገው ትግል በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ተሰውተዋል፡፡ ===ሶስተኛው የወረራ ግንባር=== የኢትዮጵያ ሰራዊት ኦጋዴንን ላለማስነጠቅ በሚታገልበት ወቅት ሶማሊዎች በጦርነቱ ሂደት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያስከተለ እርምጃ ወሰዱ፡፡ ይህም የሶስተኛ የወረራ ግንባር መከፈት ነው፡፡ በዚህ የወረራ ግንባር የተሰማራው የሶማሊያ ሰራዊት የተነሳው ከሰሜን ሶማሊያዋ የሀርጌሳ ከተማ ነው፡፡ የመጨረሻ ግቡ ደግሞ የሀረርና የድሬ ዳዋ ከተሞችን ጨምሮ የደጋማውን የሀረርጌ ክፍል መቆጣጠር ነው፡፡ በሶስተኛው ግንባር የተሰማራው የሶማሊያ ጦር በብዛቱ በሌሎች ግንባሮች ከዘመተው ይበልጣል፡፡ በጣም ምርጥ የተባሉ የጦር መሳሪያዎችንም ታጥቋል፡፡ ሶማሊያ ካላት አራት ሜካናይዝድ ክፍለ ጦሮች መካከል ሁለቱ በዚህ ግንባር ተሰልፈዋል፡፡ የሶማሊያ አየር ሀይልም ሙሉ ሙሉ ትኩረቱን በዚህ ግንባር ላይ አድርጓል፡፡ የሶማሊያ የፕሮፓጋንዳ ሀይሎችም “ሀረር ተከበበች፣ ድሬ ዳዋ ተያዘች” እያሉ ማሸበር ጀምረዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት አመራሮች ሶማሊያ በሶስተኛው ግንባር ውጊያ ትከፍታለች ብለው አልጠበቁም ነበር፡፡ በመሆኑም ወረራውን ለማስቆም ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ከውሳኔ ላይ ለመድረስ ተቸገሩ፡፡ የሶማሊያ ጦር የመጨረሻ ጉዞ የት ሊሆን እንደሚችል ማወቅም ተሳናቸው፡፡ በመሆኑም ሊቀመንበር መንግሥቱና ሌሎች ጓዶቻቸው በጉዳዩ ዙሪያ ለመወሰን አስቸኳይ ስብሰባ ተቀመጡ (በስብሰባው ላይ የሶቪየት አማካሪዎችም ተገኝተው ነበር)፡፡ ስብሰባው በዝግ ከተደረገ በኋላ ኦጋዴንን በስልታዊ ማፈግፈግ መልቀቅና ድሬ ዳዋና ሀረርን ማዳን የሚለው ሃሳብ ተቀባይነት አገኘ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ጦር ከኦጋዴን ለቆ በጅጅጋና ጉርሱም አውራጃዎች ውስጥ እንዲሰፍር ተደረገ፡፡ ***** ሚያዚያ 5/2006 ተጻፈ፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 12 የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ክፍል ሶስት ===የኢትዮጵያ የአጸፋ ምላሽ==== በክፍል ሁለት እንደገለጽኩት የሶማሊያ ሀይሎች ኦጋዴንን በድብቅ በወረሩበት ጊዜ ኢትዮጵያ በውስጣዊ ፖለቲካ ተቀስፋ ተይዛ ነበር፡፡ ሀገሪቱን የሚመራው የደርግ መንግሥትም በኮሎኔል መንግሥቱ ቡድን እና በነሻምበል ዓለማየሁ ሀይሌ ቡድን ለሁለት ተከፍሎ ነበር፡፡ ሁለቱ ሀይሎች ለመጠፋፋት የሚፈላለጉ በመሆናቸው የሀገሪቱን ድንበር የማስጠበቁን ጉዳይ እምብዛም አላተኮሩበትም፡፡ በጥር 25/1969 ግን ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም በነሻምበል አለማየሁ ሀይሌ ቡድን ላይ የማያዳግም እርምጃ ወሰዱ፡፡ “አብዮቱ ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት ተሸጋግሯል” ተባለ፡፡ ይህም ቀይ ሽብርን ወለደ፡፡ በኢህአፓ ላይ የሚደረገው የመደምሰስ እርምጃ በይፋ ተጀመረ፡፡ አንድ ወር ሙሉ ሽብሩ በከተሞች ተጧጧፈ፡፡ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ለሶማሊያ ጉዳይ ሙሉ ትኩረት መስጠት የጀመረው በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ነው፡፡ በጊዜው በድንበር አካባቢ ያለው ግፊት እየተጠናከረ መምጣቱ ሪፖርት ስለተደረገ ነው የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን በይፋ ማንሳት የጀመረው፡፡ በመሆኑም ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማሪያም አቤቱታቸውን በድንገት ወደ አዲስ አበባ ለመጡት የኩባው ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ ሩዝ አሰሙ፡፡ ፕሬዚዳንት ካስትሮም ሊቀመንበር መንግሥቱንና ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬን የደቡብ የመን ዋና ከተማ በሆነችው አደን ላይ ሰበሰቧቸው፡፡ ሁለቱ መሪዎች በተናጠልና በጋራ ባደረጉት ውይይት ሊስማሙ አልቻሉም፡፡ የዚህም ምክንያት ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ያቀረቡት የመሬት ስጡን ጥያቄ በኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዘንድ ተቀባይነት በማጣቱ ነው፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ልዑካን “ሶማሊያ ውጊያ ጀምራለች” በማለት ላቀረቡት ክስ የሶማሊያው መሪ “ውጊያ አልጀመርንም፤ ውጊያ ማለት ምን እንደሆነ ወደፊት ታያላችሁ” የሚል ዛቻ አዘል ምላሽ መስጠታቸው የውይይቱን መንፈስ ረብሾት እንደነበረ ይነገራል፡፡ በኤደን የተደረገው ውይይት ያለ ውጤት ከተበተነ በኋላ ሊቀመንበር መንግሥቱ ለመጪው ውጊያ መዘጋጀት እንዳለባቸው ተገነዘቡ፡፡ በመሆኑም “ስጋ ሜዳ” በሚባለው ቦታ የሚገኘውና የቀድሞ የድኩማን ማቋቋሚያ ድርጅት ወላጅ አልባ ህጻናትንና ረዳት የሌላቸውን አረጋዊያን የሚንከባከብት ማዕከል ተወስዶ የጦር ማሰልጠኛ ካምፕ እንዲሆን ተወሰነ፡፡ ማሰልጠኛውም “ታጠቅ” በሚል ስያሜ ተጠራ፡፡ የጦርና የሲቪል ከፍተኛ ካድሬዎች ለስልጠና በደብረ ብርሃን የመምህራን ማሰልጠኛ እንዲከቱ ታዘዙ፡፡ ጡረታ ለወጡ ወታደሮች የሰርኩላር ጥሪ ተላለፈ፡፡ በየክፍለ ሀገሩ እጩ ሚሊሻዎች እንዲመለመሉ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 13 ይህ ሁሉ ከተደረገ በኋላ ሊቀመንበር መንግሥቱ ሚያዚያ 4/1969 በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገሩን እንዲያድን የሚያሳስበውን ታሪካዊውን የእናት ሀገር ጥሪ አደረጉ፡፡ ጥሪውን የሰማው የአዲስ አበባ ህዝብም ድጋፉን ሚያዚያ 6/1969 በአብዮት አደባባይ ባደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ገለጸላቸው፡፡ በክፍለ ሀገር ከተሞችም የድጋፍ ሰልፎች ተደረጉ፡፡ በቀበሌ ደረጃ በተዋቀሩ የእናት ሀገር ጥሪ አስተባባሪ ኮሚቴዎች አማካኝነትም ለሰራዊቱ ስንቅ የሚሆኑ ደረቅ የምግብ ዓይነቶችን (በሶ፣ ቆሎ፣ ዳቦ ቆሎ፣ ብስኩት ወዘተ..) ማዘጋጀት ተጀመረ፡፡ እንደ ኩባያ፤ ሳህን፤ ማንኪያ፤ ድስት ወዘተ.. የመሳሰሉ ቁሳቁሶችም የማብሰያና የመሰብሰቢያ እቃዎችም ከህዝቡ ተሰበሰቡ፡፡ ኢትዮጵያ የስልጠና ዝግጅቷን ካጧጧፈች በኋላ ሰኔ 19/1969 ለመጀመሪያ ጊዜ ታላቅ ወታደራዊ ሰልፍ አሳየች፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በመገናኛ ብዙሃን የሚደረገው የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ተፋፍሞ ቀጠለ፡፡ የወታደራዊ ሰልፉም ሆነ የፕሮፓጋንዳ ጦርነቱ ዓላማ በሶማሊያ ላይ የስነ- ልቦና ሽብር መፍጠር ነበር፡፡ ነገር ግን ሶማሊዎች ለኢትዮጵያ የስነ-ልቦና ጦርነት ተበግረው ወረራውን ከመፈጸም አልተቆጠቡም፡፡ የዚህም ምክንያቱ የኢትዮጵያ ሰራዊት የሰው ብዛት እንጂ ለውጊያ የሚረዱ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ያልታጠቀ መሆኑን የሚያውቁ መሆናቸው ነው፡፡ ==የኢትዮጵያ ሰራዊትን ለማስታጠቅ የገጠሙ ፈተናዎች== ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ሶማሊያ ወረራውን በጀመረችበት ወቅት በሁለቱ ሀገሮች የጦር ሰራዊቶች መካከል ከፍተኛ ልዩነት ነው የነበረው፡፡ ለምሳሌ የሶማሊያ የምድር ጦሩ አወቃቀር ይህንን ይመስል ነበር፡፡  እግረኛ ክፍለ ጦር =8 (ኢትዮጵያ አራት ክፍለ ጦር ነው የነበራት)  ኮማንዶ ብርጌድ= 4 (ኢትዮጵያ ምንም አልነበራትም)  ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር= 4 (ኢትዮጵያ ምንም አልነበራትም)  ታንከኛ ክፍለ ብርጌድ= 4 (ኢትዮጵያ አንድ ብቻ ነው የነበራት)  መድፈኛ ብርጌድ= 4 (ኢትዮጵያ አንድ ብቻ ነው የነበራት)  ቢኤም ሮኬት ሻለቃ= 7 (ኢትዮጵያ አንድ ብቻ ነው የነበራት)  የቀላል ሚሳየል አየር መቃወሚያ ሻለቃ= 5 (ኢትዮጵያ ምንም አልነበራትም) ሶማሊያ የታጠቀችው የከባድ መሳሪያ ዓይነትና ብዛትም የሚከተለው ነው፡፡  ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች 253 (ኢትዮጵያ 51 ነበራት)  ታንኮች = 608 (ኢትዮጵያ 132 ነበራት)  መድፎች = 260 (ኢትዮጵያ 48 ነበራት) የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 14  ቢ.ኤም ሮኬቶች = 125 (ኢትዮጵያ አንድ ብቻ ነበራት)  አየር መቃወሚያ ሚሳኤሎች = 75 (ኢትዮጵያ ምንም አልነበራትም)  ተዋጊ አውሮፕላኖች= 65 (ኢትዮጵያ 8 ብቻ ነው የነበራት) ኢትዮጵያ ያኔ የታጠቀችው አሜሪካ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት የሰራቻቸውን T-2 ታንኮችን ናቸው፡፡ የሰራዊቱ የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችም “ካርባይን” እና “ኤ.ም. ዋን” የሚባሉ አሮጌ ጠመንጃዎች ነበሩ፡፡ በመሆኑም የሶማሊያ ሰራዊት በመሳሪያ ብዛት ብቻ ሳይሆን በጥራትም ብልጫ ነበረው፡፡ ኢትዮጵያ ከሚያዚያ ወር መጨረሻ ጀምሮ የመሳሪያ ልመናውን ጉዳይ አጠናክራ ቀጠለች፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ በየመን ከተደረገው ውይይት በኋላ ለመሳሪያ ጥየቃ ወደ ሶቪየት ህብረት ተጓዙ፡፡ ሆኖም የክሬምሊን መንግሥት በቀላሉ ፊት አልሰጣቸውም፡፡ ይህም የሆነው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው ምክንያት ሶቪየት ህብረት ከሶሻሊስቷ ሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ተራድኦ ስምምነት የነበራት መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ሶቪየቶች በኢትዮጵያ በመካሄድ በነበረው ለውጥ ላይ ጥርጣሬ የነበራቸው መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም ሊቀመንበር መንግሥቱ ሶቪየትን ትተው ወደ ሌሎች የምስራቅ አውሮጳ ሀገሮች ተጓዙ፡፡ ይሁንና ከነዚህም ሀገራት መሳሪያ ለማግኘት የሶቪየትን ጥቅሻ ይፈልግ ስለነበር በለስ ሊቀናቸው አልቻለም፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ ከሶቪየት ወደ ቻይና ሲያመሩ ግን ያላሰቡት እድል ገጠማቸው፡፡ የቻይና መሪዎች ከሶቪየትም ሆነ ከሶማሊያ መሪዎች ጋር የማይጣጣሙ በመሆናቸው ለኢትዮጵያ የመሳሪያ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት አላመነቱም፡፡ በመሆኑም ታንኮችንና መድፎችን የማያካትት ለሁለት ክፍለ ጦር የሚበቃ ትጥቅ ለኢትዮጵያ ሰጡ፡፡ እንደ ቻይና ሁሉ ከሶቪየት መሪዎች ጋር የማይጣጣሙት የዩጎዝላቪያው መሪ ጆሲፍ ብሮዝ ቲቶም የኢትዮጵያ አርበኞች ከዩጉዝላቪያ ጓዶች ጋር የነበራቸውን የጋራ የትግል ወኔ በማስታወስ 70 አሜሪካ ሰራሽ ታንኮችንና እጅግ በርካታ ቀላል መሳሪያዎችን ከበቂ ጥይቶች ጋር አበረከቱ፡፡ በሌላ በኩል ሊቀመንበር መንግሥቱ ለአሜሪካ መሪዎችም የ“መሳሪያ ሽጡልን” ጥያቄ ማቅረባቸውን ይናገራሉ፡፡ ይህም የተደረገው በኢራንና በእስራኤል በኩል በተደረጉ ሚስጢራዊ ግንኙነቶች አማካኝነት ነው፡፡ አሜሪካኖቹ ለመሳሪያ ግዥ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከተቀበሉ በኋላ ጥቂት የመጓጓዣ አውሮፕላኖችን፣ ራዳሮችን፣ ጸረ ታንክ መሳሪያዎችንና 12 መድፎችን ሰጡ፡፡ ሆኖም ከአንድ ወር በኋላ ያለምንም ቅድመ ማስታወቂያ የመሳሪያ ሽያጩን አቆሙ፡፡ “አሜሪካኖቹ ለግዥው መቋረጥ የሰጡት ምክንያት ግልጽ አይደለም፤ ነገር ግን ሶሻሊዝምን በማወጃችን በዚህ ቂም ይዘው ነበር” ይላሉ-ሊቀመንበር መንግሥቱ፡፡ በአንዳንድ ፋይሎች ተጽፎ እንደሚታየው ከሆነ ደግሞ አሜሪካ “መሳሪያውን የከለከልኩት ሁለቱም ሀገራት መዋጋት የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 15 የለባቸውም የሚለውን የተባበሩት መንግሥታት ውሳኔን ተከትሎ” ነው ትላለች፡፡ ***** ሚያዚያ 6/2006 የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 16 የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ክፍል አራት === የዓለም አቀፍ ሀይሎች አሰላለፍ መቀየር=== ሶማሊያ የሶሻሊዝም ተከታይ መሆኗ የታወጀው ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ በመንግሥት ግልበጣ ስልጣን በያዙ በዓመቱ (እ.ኤ.አ. 1970) ነው፡፡ በዚህ አዋጅ መሰረት ነው ሀገሪቱ ከሶቪየት ህብረት ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ለማግኘት የበቃችው፡፡ በ1967 ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤን ከስልጣን ያወረደው የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በታህሳስ ወር 1967 ኢትዮጵያ የሳይንሳዊ ሶሻሊዝም ስርዓት ተከታይ ሀገር መሆኗን ቢያውጅም የሶቪየቶችን ሙሉ ይሁንታ ለማግኘት ቸግሮት ቆይቷል፡፡ ሶቪየቶች የኢትዮጵያ ወታደራዊ መሪዎችን እንደ ሀገር ወዳድ አብዮታዊያን እንጂ እንደ እውነተኛ ኮሚኒስቶች ለመቀበል ተቸግረው ነበር፡፡ በመሆኑም በክፍል ሶስት እንደተገለጸው የሶማሊያ ወረራ ባንዣበበት ወቅት ሀገራችን ከአሜሪካም ሆነ ከሶቪየት ህብረት (USSR) የጦር መሳሪያዎችን ለማግኘት አልቻለችም፡፡ ሚያዚያ ወር/ 1969፡፡ በዚህ ወር የኢትዮጵያ መሪዎች አንድ ያልታሰበ ፖለቲካዊ እርምጃ ወሰዱ፡፡ ይህም በኢትዮጵያ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊና ሲቪል ተቋማት እንዲዘጉ ማድረጋቸው ነው፡፡ በዚህ መሰረት በአስመራ የሚገኘው የቃኘው ወታደራዊ መረጃ ጣቢያ (ቃኘው ሰቴሽን)፣ በምጽዋ የነበረው የአሜሪካ የባህር ሀይል መደብ (በተለምዶ “ናምሩ” የሚባለው)፣ በአዲስ አበባ የነበረው የአሜሪካ ወታደራዊ አማካሪ ቡድን (ማግ-MAG)፣ የአሜሪካ የማስታወቂያ አገልግሎት (USIS) ተዘጉ፡፡ በማስከተልም በአሜሪካ የሰብዓዊ እርዳታ አገልግሎት ድርጅቶች ላይ ገደብ ተጣለ፡፡ የኢትዮጵያ መሪዎች አሜሪካዊ ተቋማትን ለመዝጋት የወሰኑት ሆን ተብሎ የሶቪየቶችን ቀልብ ለመግዛት በተወጠነ እቅድ አይደለም፡፡ ነገሩ የተከሰተው ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ኢትዮጵያ አስቀድማ የከፈለችበት የጦር መሳሪያ ሽያጭ እንዲታገድ በማድረጋቸው ነው፡፡ በጊዜው አሜሪካ የሶማሊያ ደጋፊ ባትሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ ሶሻሊዝም በመታወጁ ከሀገራችን ጋር የነበራትን ግንኙነት አለዝባ ነበር፡፡ የመሳሪያ ሽያጩንም ያገደችው በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ መተማመን በማጣቷ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሪዎች በአሜሪካ ተቋማት ላይ በወሰዱት እርምጃ የሶቪየት መሪዎች በኢትዮጵያ ላይ የነበራቸው እይታ በአንድ ጊዜ እንዲቀየር ነው ያደረጉት፡፡ በመሆኑም የሶቪየት ህብረት መሪዎች ያዝ ለቀቅ ሲያደርጉት የነበረውን የኢትዮ-ሶማሊያ አጀንዳ እንደራሳቸው ጉዳይ በመቁጠር ቅድሚያ ሰጡት፡፡ በግንቦት ወር 1969 ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ሞስኮን እንዲጎበኙ ተጋበዙ፡፡ በዚህ ፕሮግራም ከጓድ ሊዮኒድ ብሬዥኔቭ ጋር ከፍተኛ መግባባት ላይ ደረሱ፡፡ በመስከረም ወር በድብቅ በተያዘ ፕሮግራም አማካኝነት ሶቪየት ህብረት ኢትዮጵያ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 17 ላቀረበችው የወታደራዊ መሳሪያዎችና የቴክኒክ ድጋፍ ጥያቄዎች ሙሉ ምላሽ ሰጠች፡፡ ሶቪየቶች ይህንን ያደረጉት ከረጅም ዘመናት የአሜሪካ ተጽእኖ የተላቀቀችው ኢትዮጵያ እንደገና ተመልሳ የአሜሪካ አጋር እንዳትሆን በመሻታቸው ነው፡፡ አሜሪካ ለቃ በወጣችው የቀይ ባህር አምባ ላይም የራሳቸውን መረብ መዘርጋት ይፈልጉም ነበር፡፡ ሶቪየት ህብረት ይህንን ስታደርግ ከሶማሊያ መሪዎች ተቃውሞ እንደሚመጣባት አላጣችውም፡፡ ነገር ግን ሶማሊዎቹ በነበራቸው ከገደብ ያለፈ የመሬት ጥያቄ ተሰላችታ ስለነበር ለተቃውሞው ብዙም ግድ አልሰጠችውም፡፡ ለዚህም ነው በቅድሚያ ኢትዮጵያን ይዛ ሶማሊዎቹን “ ይህንን ነገር ብትተውት ይሻላችኋል” ማለቱን ነው የመረጠችው፡፡ ታዲያ የሶማሊያ መሪዎች የሶቪየትን እርምጃ እንደ ክህደት ነው የቆጠሩት፡፡ በመሆኑም በወረራው ማግስት (በህዳር ወር 1970) በሀገራቸው ውስጥ የነበሩትን ከሁለት ሺህ የማያንሱ የሶቪየት የሲቪልና ወታደራዊ አማካሪዎችን፣ የሚዲያ ሰዎችን፣ ቴክኖራቶችንና በነዳጅ ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ሰራተኞችን (ከነቤተሰቦቻቸው) አባረሩ፡፡ የሶማሊያና የሶቪየት ህብረት ግንኙነትም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተበጠሰ፡፡ ==== የኢትዮጵያ ጦር መደራጀትና መታጠቅ==== የሶቪየት ሀይሎች ከሶማሊያ መባረራቸው ለኢትዮጵያ ሰርግና ምላሽ ነው የሆነው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የጦር ሀይል ለመጀመሪያ ጊዜ ሶቪየት ሰራሽ T-34 ታንኮችን፣ መድፎችን ቢ.ኤም ሮኬቶችን የሚታጠቅበት ሁኔታ ተመቻችቶለታል፡፡ አሮጌ የነፍስ ወከፍ መሳሪያቹ በክላሽኒኮቭ (AK-47) እና ኤስ.ኤስ. እንደሚተኩም ቃል ተገብቶለታል፡፡ የግርኖቭ መትረየሶችና ላውንቸሮችም ከሶቪየት ህብረት እንደሚመጡ ተነግሯል፡፡ የአየር ሀይሉም የሚግ ጄቶችና ለወታደራዊ አቪየሽን የሚያገለግሉ አንቶኖቭ አውሮፕላኖችን ሊታጠቅ ተዘጋጅቷል፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ቃል የተገባላትን መሳሪያ በቶሎ ለማግኘት አልቻለችም፡፡ በመሆኑም ከሀምሌ 1969 እስከ ህዳር 1970 ድረስ ድሮ በነበሯትና ከቻይናና ከዩጎዝላቪያ ባገኘቻቸው መሳሪያዎች መከላከል ነበረባት (ኩባ 45, 000 የሚሆን “ቺቺ” የሚባለውን ባለ አገልግል ጠመንጃ ለኢትዮጵያ ብትሰጥም መሳሪያው ጥይት እየነከሰ ስለሚያስቸግር ለውጊያ መጠቀም አልተቻለም፤ ሊቀመንበር መንግሥቱ እንደሚሉት እነዚያ ጠመንጃዎች በመጋዘን ውስጥ ከቆዩ በኋላ እነ ጄኔራል ፋራህ አይዲድ በፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ላይ ሲያምጹ በእርዳታ ተሰጥቶአቸዋል)፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የሶቪየትና የሌሎች ሶሻሊስት ሀገራት መሳሪያዎች በፍጥነት ቢመጡላት እንኳ መሳሪያዎቹን ወዲያኑ በጥቅም ላይ ለማዋል የምትችልበት ሁኔታ አልነበረም፡ ፡ ምክንያቱ ደግሞ መሳሪያዎቹ ለኢትዮጵያ ሰራዊት አዲስ በመሆናቸው ስለ አጠቃቀማቸው ማወቁ ጊዜን የሚጠይቅ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም የኢትዮጵያ መደበኛ ሰራዊትና የአየር የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 18 ሀይል ከፍተኛ የውጊያ ስልጠና ያስፈልገው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መሪዎች ከላይ የተጠቀሱትን ሁኔታዎች ካጤኑ በኋላ ሁለት ውሳኔዎችን ወሰኑ፡፡ አንደኛው መደበኛ ሰራዊቱን ለማጠናከር የሚረዳ ተጨማሪ ሀይል በብዛት ተመልምሎ በስልጠና ላይ እንዲቆይ የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው በታጠቅ ካምፕ ሲሰለጥን የነበረው የሚሊሻ ሰራዊት በቶሎ ወደ ግንባር ተልኮ ወረራውን በመከላከል ላይ የነበረውን ሰራዊት እንዲያግዝ የሚል ነው፡ ፡ በተጨማሪም ሚሊሻውን የማሰልጠኑ ተግባር በየክፍለ ሀገሩ እንዲጀመር ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ መሪዎች የወሰዱት እርምጃ ከወታደራዊ ስልት አንጻር ሲታይ በጣም ትክክል ነው ተብሎ ተወድሷል፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የኢትዮጵያ መደበኛ ሰራዊት በብዙ እጥፍ የሚበልጠውን የሶማሊያ ሰራዊት ከሀገሩ ለማባረር የተጠናከረ ስልጠና ይፈልጋል፡፡ የውጊያ ስልጠናውን ካጠናቀቀ በኋላም ከሶቪየት ሰራሽ መሳሪያዎች ጋር እስኪተዋወቅ ድረስ በቂ ልምምድ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቂ ጊዜ ይሰጠው ዘንድ የግድ ይላል፡፡ በተለይ የከባድ መሳሪያ ተኳሾችንና የአውሮፕላን አብራሪዎችን በአጭር ጊዜ ለውጤት ማብቃት አይቻልም፡፡ ስለዚህ እነርሱ እስኪሰለጥኑ ድረስ የነርሱን ቦታ ሸፍኖ የሚዋጋ ሀይል መኖር ነበረበት፡፡ ይህንን ለማድረግ የተሻለው አማራጭም የሚሊሻ ሰራዊቱን በፍጥነት አሰልጥኖ ወደ ግንባር ማሰማራት ነው፡፡ ==== የመከላከል ውጊያ በምስራቅ ግንባር==== በክፍል ሁለት እንደተገለጸው ሶማሊያ አደገኛ ወረራ ያደረገችው በሀርጌሳ ግንባር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሰራዊትም በዚህ ግንባር ተጠቃልሎ በመግባት ከፍተኛ የመከላከል ውጊያ ሲያደርግ ነበር፡፡ በወቅቱ ለኢትዮጵያ መሪዎች ያስቸገረው የሶማሊያ ጦር የስምሪት አቅጣጫዎችንና የመጨረሻ ዒላማዎችን ማወቁ ነው፡፡ ቀደም ሲል በነበረው ግምት የሶማሊያ ሰራዊት ጅጅጋን ከያዘ በኋላ በማስከተል ወደ ሀረር ይመጣል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡ ነገር ግን የሶማሊያ ሰራዊት በነሀሴ አጋማሽ ላይ ጅጅጋንም ሆነ ሀረርን ሳይነካ ከጭናክሰን ከተማ ጀርባ ወደ ሰሜን ምዕራብ መጓዝ ጀመረ፡፡ የኢትዮ የኢትዮጵያ የጦር መሪዎች የሶማሊያ ሰራዊት በጉርሱም አውራጃ ውስጥ በማሳበር ወደ ሀረር ከተማ የሚያመራ ነበር የመሰላቸው፡፡ በመሆኑም በሀረር ዙሪያ የነበረውን ጥበቃ አጠናከሩ፡፡ የሶማሊ ሀይሎች በቀጥታ ወደ ድሬ ዳዋ እየገሰገሱ መሆናቸው ታወቀ፡፡ በዚህም ጊዜ በኢትዮጵያ መሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤ ተፈጠረ፡፡ “ለድሬ ዳዋ የሚረባ መከላከያ አልተደረገም” በሚል መወቃቀስ ተጀመረ፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማሪያም በነገሩ ዙሪያ ከጦር መሪዎቻቸው አስቸኳይ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ በከተማዋ የነበሩትን ሁለት ሚሊሻ ክፍለ ጦሮችና አንድ ነበልባል ብርጌድ ከከተማዋ ወጥተው የመከላከያ ምሽጋቸውን እንዲያበጁ ትዕዛዝ ተላለፈ፡፡ ከነዚህ ሀይሎች ጋር የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 19 ተደራቢ ሆኖ የሚዋጋ አንድ ሜካናይዝድ ብርጌድም በአፋጣኝ ተመደበ፡፡ ከዩጎዝላቪያ የተገኙት ሰባ ታንኮችም በዚህ ግንባር እንዲሰለፉ ተደረገ፡፡ አንድ ሚሊሻ ክፍለ ጦርና አንድ መደበኛ ብርጌድም ደግሞ የድሬ ዳዋን ከተማ እንዲጠብቁ ተደረገ፡፡ ደቡብ የመን ለኢትዮጵያ የሰጠችው ሰላሳ ሶስት ታንኮችም ከስፍራው ደረሱ፡፡ የኢትዮጵያ ሰራዊት የመከላከያ ጣቢያውን “ጀልዴሳ” በተባለ ስፍራ ላይ መሰረተ (ይህ ስፍራ ከድሬ ዳዋ በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ በ50 ኪሎ ሜትር ላይ ነው የሚገኘው)፡፡ ነሀሴ 5 ቀን 1969 ወደ ድሬ ዳዋ የሚያመራው የሶማሊያ ሰራዊት “ጀልዴሳ” ሲደርስ ያልጠበቀው ውጊያ ገጠመው፡፡ ሶስት ቀናት ሙሉ ቢዋጋም ጀልዴሳን ማለፍ አቃተው፡፡ በመሆኑም ተጨማሪ ጦር አስመጥቶ እንደገና ሌላ ጥቃት ከፈተ፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሀይሎችን አንበርክኮ ለማለፍ ሳይችል ቀረ፡፡ የሶማሊያ ሰራዊት በዚህ ተስፋ ሳይቆርጥ ለሶስተኛ ጊዜ ሀይለኛ የሜካናይዝ ውጊያ ከፈተ፡፡ ይሁን እንጂ የሶስተኛው ዙር ጥቃት ለሶማሊዎቹ ከበፊቱ የባሰ ውድቀትን ነው ያስከተለው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሰራዊት የውጊያ ስልቱን በመለወጡ ነው፡፡ ይህም ማለት ሰራዊቱ እንደ በፊቱ መከላከሉን ትቶ ወደ ማጥቃቱ እንዲገባ ነው የተደረገው፡፡ የኢትዮጵያ የጦር ኤክስፐርቶች ይህንን ለውጥ ያደረጉት የአካባቢው ሜዳማነት ለሜካናይዝድ ውጊያ የሚያመች መሆኑን በማጤናቸው ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በኮሎኔል ፋንታ በላይ የሚመራው የኢትዮጵያ አየር ሀይል ሙሉ ትኩረቱን በዚህ ግንባር ላይ እንዲያደርግ ታዝዞ ነበር፡፡ እነ ኮ/ል አሸናፊ ገብረጻዲቅ፣ ኮሎኔል ለገሠ ተፈራ እና ኮ/ል በዛብህ ጴጥሮስን የመሳሰሉ ተዋጊዎች የሶማሊያን ሰራዊት ከአየር ወደ ምድር ቀጥቅጠውታል፡፡ በመሆኑም የሶማሊያ ጦር ያልጠበቀው ሽንፈት ገጥሞታል፡፡ ለውጊያው ካሰለፋቸው ታንኮች መካከልም ብዙዎቹ ተቃጥለውበታል፡፡ በዚህም የተነሳ ሶማሊዎቹ በነሀሴ ወር መገባደጃ ላይ ድሬ ዳዋን የመያዝ እቅዳቸውን እርግፍ አድርገው በመተው ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ጅጅጋና ሀረር አዞሩት፡፡ ***** በመከረም 1970 የሶማሊያ ጦር ጅጅጋን ለመያዝ ውጊያ ከፈተ፡፡ በከተማዋ የቀረው የኢትዮጵያ ሀይል ባለው አቅም ሁሉ ከተማዋን ላለማስነጠቅ ተከላከለ፡፡ ይሁንና የሶማሊያ ጦር በሰው ሀይልም ሆነ በመሳሪያ ብዛት ስለሚበልጥ በያዘው መሳሪያ ስለሚበልጥ ሁለት ብርጌድ ብቻ ይዞ በሚዋጋው የኢትዮጵያ ጦር የሚመለስ አልሆነም፡፡ በተጨማሪም የሶማሊያ አየር ሀይል በውጊያው ላይ በከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ነበር፡፡ ስለዚህ ጳጉሜ 5/1969 የኢትዮጵያ ጦር በስልታዊ ማፈግፈግ ጅጅጋን እንዲለቅ ታዘዘ፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 20 በዚሁ መሰረት ጦሩ ከከተማዋ ወጥቶ በጅጅጋና በሀረር መሀል ካለችው አነስተኛዋ የቆሬ ከተማ አቅራቢያ (ከጅጅጋ በስተምዕራብ በኩል በ40 ኪሎ ሜትር ላይ) የመከላከያ ጣቢያውን መሰረተ፡፡ ከኦጋዴን ያፈገፈገው ጦርም በዚህ ግንባር ተሰልፎ የሶማሊያ ጦር ወደ ሀረር ከተማ እንዳይገፋ ገትሮ እንዲይዝ ተደረገ፡፡ ***** ሚያዚያ 6/2006 ተጻፈ፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 21 የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ክፍል አምስት ===ሀረርን የመከላከል ውጊያ=== የሶማሊያ ሰራዊት ከምስራቅና የደቡብ ኢትዮጵያ ከተሞች መካከል ከፍተኛ ትኩረት ያደረገው በሀረር ላይ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያት አለው፡፡ ሀረር ረጅምና ጥንታዊ ታሪክ ያላት ከተማ በመሆኗ የሶማሊያ መሪዎች የኛ ከተማ ናት ይሏት ነበር፡፡ በተለይም ሀረርን ከኢማም አህመድ ኢብራሂም አል-ጋዚ ታሪክ ጋር በማያያዝ ከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ ይነዙላት ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሀረር የዘመኑ ትልቁና ሐብታሙ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር የነበረው የሀረርጌ ዋና ከተማ ነበረች፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ ከነበሯት አራት ክፍለ ጦሮች መካከል በጣም ግዙፍ የሆነው የሶስተኛ ክፍለ ጦሮች ዋና የማዘዣ ጣቢያ የሚገኝባት ከተማ ነበረች፡፡ በአራተኛ ደረጃ ሀረር ብቸኛው የአትዮጵያ የጦር አካዳሚ የሚገኝባት ከተማ ነበረች፡፡ የሶማሊያ መሪዎች ይህንን ሁሉ በማመዛዘን ነው ሀረርን የትልቋ የድል ብስራት ማወጃ ማዕከል በማድረግ ያተኮሩባት፡፡ የሶማሊያ ጦር ሀረርን የመያዝ ጥረቱን የጀመረው በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ነው፡፡ ውጊያውንም የጀመረው ከሀረር በስተምስራቅ በ70 ኪሎ-ሜትር (ከጅጅጋ በስተምዕራብ በ40 ኪ.ሜ) ርቀት ላይ ባለው የቆሬ ግንባር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያኑ በዚህ ውጊያ ሲወጠሩ፣ የሶማሊያ ሰራዊት ከጭናክሰን ከተማ አቅራቢያ ተነስቶ በጉርሱም አውራጃ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት በመራመድ የኤጀርሳ ጎሮ ከተማን ያዘ፡፡ በዚህም ሳያበቃ ሀይሉን ለሶስት በመክፈል አንደኛውን ቡድን በትንሿ የፈላና ከተማ ከተማ አቅጣጫ ወደ ሀረር ላከው፡፡ ሁለተኛው ሀይል ከሀረር በስተሰሜን በመገስገስ የኮምቦልቻ ከተማን ከያዘ በኋላ ወደ ሀረር መግፋት ጀመረ፡፡ ሶስተኛው ሀይል ማንንም ባስደነቀ የጦር ሜዳ ጥበብ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ተጉዞ ከሀረር በስተምዕራብ ካለችው የአዴሌ ከተማ አጠገብ ደረሰ (የዚህኛው ግብረ-ሀይል ዓላማ የኢትዮጵያ ሰራዊት ከድሬ ዳዋ አቅጣጫ ድጋፍ እንዳይመጣለት መከላከልና ሀረርን ከጀርባ መክበብ ነው)፡፡ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሀረርን ላለማስነጠቅ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረግ ጀመረ፡፡ ለውጊያው ከተሰለፈው ሀይል በተጨማሪ በተጠባባቂነት የተያዙ የመደበኛና የሚሊሻ ሰራዊት አባላት በሙሉ ሀረርን ለመከላከል እንዲሰማሩ ታዘዙ፡፡ ነገሮች ሁሉ እንዲህ በከረሩበት ጊዜ ደግሞ የሶማሊያ ሰራዊት አንድ ግብረ ሀይል ሌላ ያልታሰበ የውጊያ ግንባር ከፈተ፡፡ ይኸውም ሀይል የመጣው ከሀረር ከተማ በስተደቡብና በደቡብ ምዕራብ በኩል ነበር፡፡ በዚህ በኩል ወደ ሀረር የደረሰው የሶማሊያ ሰራዊት ከሁለት አካባቢዎች ነበር የተነሳው፡፡ የአንደኛው መነሻ በባሌ ክፍለ ሀገር የምትገኘው የኤል-ከሬ ከተማ ናት፡፡ ከዚያች ከተማ የተነሳ አንድ የሶማሊያ ብርጌድ ሽቅብ ወደ ላይ እየተጓዘ የዋቢ ሸበሌን ወንዝ በማቋረጥ ከሀረር ከተማ በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ ከምትገኘው ትንሿ የ“ፊቅ” ከተማ ገባ፡፡ ሁለተኛው ሀይል ደግሞ በኦጋዴን ካለችው የደጋሀቡር የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 22 ከተማ ከተነሳ በኋላ ወደ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ እየገሰገሰ “ፊቅ” ከተማ ደረሰ፡፡ እነዚህ ሁለት ሀይሎች አንድ ላይ በመጣመር በቀድሞው የሀረር ዙሪያ አውራጃ ውስጥ ካለው የፈዲስ ወረዳ ከገቡ በኋላ ለሁለት ተከፈሉ፡፡ አንደኛው ሀይል የሰሜን ምስራቅ አቅጣጫን በመያዝ ሀረርን በደቡብ ምስራቅ የሚያዋስነውን የሀኪም ጋራ እንዲቆጣጠር ግዳጅ ተሰጠው፡፡ ሁለተኛው ሀይል ቀጥታ ወደ ሰሜን እየተጓዘ የሀረር ከተማ ምዕራባዊ ድንበር የሆነውን የአቦከር ተራራን እንዲይዝ ታዘዘ፡፡ የሶማሊያ ሀይሎች ፍጥነት በታየበት በዚህ ዘመቻቸው ሀረርን ሙሉ በሙሉ ለመክበብ ቻሉ፡፡ አልፎ ተርፎም በደቡብና በሰሜን በምዕራብ የመጡት ግብረ ሀይሎች መድፎቻቸውን የሀረር ከተማ ተጎራባች በሆኑት የአው ሀኪም እና የድሬ ጠያራ ቀበሌዎች ውስጥ በማስቀመጥ ከተማዋን መደብደብ ጀመሩ (ኮሎኔል መንግሥቱ በመጽሐፋቸው ገጽ 472 ላይ “የሶማሊያ ጦር ሀረርን ያዘ” ይላሉ፤ አንዳንድ ምንጮች ደግሞ “የሀረር ከተማ የተወሰኑ ክፍሎች በሶማሊያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ወድቀው ነበር” በማለት ጽፈዋል፤ ይሁንና በሀረር ከተማ ቆይታዬ ያነጋገርኳቸው የከተማዋ ነዋሪዎችና የያኔው የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት የሀረር ከተማ ከሁሉም አቅጣጫዎች ብትከበብም በሶማሊያ ሰራዊት እንዳልተያዘች አረጋግጠውልኛል፡፡ የሶማሊያ ሰራዊት ሀረርን ቢይዝ ኖሮ ከተማዋን ማስመለስም ሆነ ለቀጣዩ ጦርነት የኢትዮጵያን ሰራዊት መልሶ ማደራጀቱ በጣም አስቸጋሪ ይሆን ነበር)፡፡ የሶማሊያ ጦር ከሀረር ከተማ በአራት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ደርሷል፡፡ ታዲያ ከተማዋን ለመያዝ ያልቻለበት ምክንያት ምንድነው? ሶስት ምክንያቶች አሉት፡፡ አንደኛው ኢትዮጵያ በስልጠና ላይ የነበረውን የሚሊሻ ጦር በከፊል አስመርቃ በውጊያው እንዲሳተፍ ለማድረግ መቻሏ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የነበሩትን የጦር ሀይሎች በፍጥነት አጓጉዞ በመከላከሉ ውጊያ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ መቻሉ ይጠቀሳል፡፡ ይሁንና እነዚህ ሁለት ምክንያቶች እንደ ደጋፊ ተደርገው የሚወሰዱት እንጂ ዋናዎቹ ምክንያቶች አይደሉም፡፡ ሀረርን በሶማሊያ ወራሪ ሰራዊት ከመወሰድ የዳነችበት ዋነኛ ምክንያት የኢትዮጵያ አየር ሀይል ያደረገው ተጋድሎ ነው፡፡ ባለፉት ክፍሎች እንደገለጽኩት የኢትዮጵያ አየር ሀይል በወቅቱ ጥቂት የጦር አውሮፕላኖች ናቸው የነበሩት፡፡ ከሶቪየት የተገኙት አውሮፕላኖችም በዚያን ጊዜ ወደ ሀገር ቤት አልገቡም፡፡ ነገር ግን የአየር ሀይሉ አብራሪዎች በጣም የተዋጣላቸው በመሆናቸው ዒላማቸውን ሳይስቱ ይመቱ ነበር፡፡ በድሬ ዳዋ (ጀልዴሳ) ግንባር በርካታ ታንኮችን ከጥቅም ውጪ እንዳደረጉት ሁሉ በዚህም ግንባር የሶማሊያ መድፎችንና ሞርታሮችን በመደምሰስ ከዒላማቸው አሰናክለዋል፡፡ ታዋቂው የኢትዮጵያ አየር ሀይል አብራሪና የህብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሜዳይ ተሸላሚ ብርጋዴር ጄኔራል ለገሰ ተፈራ ብቃቱን ካሳየባቸው ግዳጆች አንዱ ያ ሀረርን ለመከላከል የተደረገው ውጊያ ነው፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 23 በነገራችን ላይ የሶማሊያ ሰራዊት ሀረርን ለመያዝ በተደረገው ዘመቻ መድፍና የቢ ኤም ሮኬቶችን እንጂ ታንክ መጠቀሙ አልተዘገበም፡፡ ይህም የአካባቢው ተራራማነት ለሜካናይዝድ ውጊያ የማያመች በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ === የሶቪየት፤ የኩባና የደቡብ የመን አጋርነት ለኢትዮጵያ=== ነሀሴ ወር 1970፡፡ ሶቪየት ህብረት ለመጨረሻ ጊዜ ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬን ወደ ሞስኮ ጠራቻቸው፡፡ በሀይል የያዙትን የኦጋዴንን ግዛት እንዲለቁ እና ጉዳዩን በሰላም እንዲጨርሱም መከረቻቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ዚያድ ግን በእምቢታቸው ጸኑ፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ መሪዎችን “ታገሱ! አትቸኩሉ” እያለች ስትመልስ የነበረው ታላቋ ሶቪየት የጦርነቱን አካሄድ የቀየረ ተግባራዊ እርምጃ ወሰደች፡፡ ቀደም ሲል በተስማማችው መሰረት በመስከረም 1970 ለኢትዮጵያ የ385 ሚሊዮን ዶላር መሳሪያ የሚሸጥበትን ሂደት ገቢራዊ ማድረግ ጀመረች፡፡ በመርከቦቿ ወደ ሶማሊያ ነዳጅ ማጓጓዙን አቋረጠች፡፡ ለሶማሊያ የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ሽያጭንም አቆመች፡፡ ሶማሊያ የሶቪየትን እርምጃ “ህገ-ወጥነት ነው” ስትል ኮነነችው፡፡ በማስከተልም በህዳር ወር 1970 በሀገሯ የነበሩትን የሶቪየት ወታደራዊ አማካሪዎችና ሲቪል ሰራተኞች አባረረች፡፡ ይህንንም ተከትሎትም ሶቪየት ህብረት ለመጀመሪያ ጊዜ ሶማሊያን “ወራሪ” በማለት አወገዘቻት፡፡ ወረራውን ለመቀልበስ ከኢትዮጵያ ጋር በሙሉ ፍላጎት እንደምትሰራም አስታወቀች፡፡ በዚህም መሰረት እንደ እርሷ ሁሉ የኢትዮ-ሶማሊያ ውዝግብን በሰላም ለመቋጨት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩትን ኩባና ደቡብ የመንን የሚያካትት ወታደራዊ “ህብረት” ተመሰረተ፡፡ የዚህ ህብረት ተግባር ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት የሶማሊያ ሰራዊትን ማባረር ነው፡፡ ሶስቱ ሀገራት በጦርነቱ የነበራቸው ተሳትፎ ሲጠቃለል የሚከተለውን ይመስላል፡፡ ሀ/. ሶቪየት ህብረት ሶቪየት ህብረት የምድር ጦር ሀይሏ ምክትል አዛዥ የነበሩትን ሜጀር ጄኔራል (በኋላ ፊልድ ማርሻል) ቫሰሊ ፔትሮቭን የዓለም አቀፉ ቡድን ሃላፊ አድርጋ መድባለች፡፡ የጄኔራሉ ሃላፊነት የኢትዮጵያን ሰራዊት ማማከርና በኢትዮጵያ መሪዎችና ሞስኮ በሚገኘው የሶቪየት ህብረት የጦር ሀይሎች ጠቅላይ መምሪያ መካከል እንደ አገናኝ ሆኖ ማገልገል ነው፡፡ ከጄኔራል ፔትሮቭ በተጨማሪ ሶቪየት ህብረት  በክፍለ ጦርና በብርጌድ ደረጃ የሚያገለግሉ የጦር አማካሪዎችን መድባለች፡፡  የከባድ መሳሪያና በረራ አሰልጣኞችን አስመጥታለች፡፡  የሶማሊያ የጦር ሀይል ክምችትና የስምሪት አቅጣጫዎችን የሚያሳዩ የጦር የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 24 መረጃዎችን (ስታቲስቲክስ፣ ካርታ ወዘተ) ለኢትዮጵያ ሰጥታለች፡፡  ለጦር ቁስለኞች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታና የቀዶ ጥገና ህክምና የሚሰጡ ሀኪሞችን መድባለች፡፡ ከዚህ ሌላ ሶቪየት ህብረት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አጋር ሆና ቆይታለች፡፡ ሆኖም ሶቪየቶች ድጋፍ ሰጪ ከመሆን ባሻገር ተዋጊ የጦር ሀይል አልመደቡም፡፡ ለ./. ኩባ በቆዳ ስፋቷ ትንሽ የሆነችው የኩባ ሶሻሊስት ሪፐብሊክ በጦርነቱ ሂደት በቀጥታ ከተሳተፉት ሁለት ሀገራት አንዷ ናት፡፡ በወቅቱ ኩባ ያስመጣችው የተዋጊ ብዛት ከ16, 000 እስከ 20, 000 ይገመታል፡፡ ከዚህ ሀይል መካከል ሁለቱ ሜካናይዝ ብርጌድ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የኩባ ጦር የሚመራው የሀሪቱ ም/የመከላከያ ሚኒስትር በነበሩት በጄኔራል አርናልዶ ኦቾዋ ሲሆን በዘመኑ በአንጎላ ተመድቦ የነበረውንም የኩባ የጦር ሀይል የሚያዙት እርሳቸው ናቸው፡፡ ኩባ ከወታደሮቿ በተጨማሪ የህክምና ሰራተኞችን ልካለች፡፡ ሐ/. ደቡብ የመን (የመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ) ደቡብ የመን ለጦርነቱ የመደበችው 2000 መድፈኞችን ነው፡፡ እነዚያ መድፈኛ የመኒዎች በቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆኑም አልሞ-ተኳሽ መሆናቸው በብዙዎች ዘንድ ተደንቆላቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት እንደለገጽትም ደቡብ የመን ለኢትዮጵያ 30 ታንኮችን ሰጥታለች፡፡ ***** ሶስቱ ሀገራት ለረጅም ጊዜ የሶማሊያ አጋር ነበሩ፡፡ ሶማሊያ የመሬት ጥያቄዋን ባነሳችበት ጊዜም ሀሳቧን እንድትቀይር ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ከዚህም አልፎ ፕሬዚዳንት ካስትሮ “ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያና ደቡብ የመን በኮንፌዴሬሽን ተያይዘው አንድ ታላቅ ህብረት መመስረት አለባቸው” የሚል ሃሳብ እስከ ማቀንቀን ደርሰዋል፡፡ የሶማሊያ ወረራ ገፍቶ ሲመጣ ግን ከኢትዮጵያ ጋር ተሰልፈዋል፡፡ ባለፈው ክፍል እንደገለጽኩት ሌሎች የሶሻሊስት ሀገራት በጦርነቱ ሂደት በቀጥታ ባይሳተፉም ለኢትዮጵያ የመሳሪያ ድጋፍ አበርክተዋል፡፡ ሶማሊያ በግልጽ የሶሻሊዝምን ካባ ወርውራ ወደ ምዕራቡ ዓለም መጓዝ የጀመረችው በዚያን ጊዜ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ቀደም ብሎም ቢሆን ከምዕራባዊያን ጋር ድብቅ ግንኙነቶችን ማድረግ እንደ ጀመረች አንዳንድ ምንጮች ያወሳሉ፡፡ ለምሳሌ ከአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ጋር ጥብቅ ቁርኝት ካለው አንድ ተቋም የተገኘ ጥናታዊ ጽሑፍ አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ ለሶማሊያ የጦር መሳሪያዎችን ለመሸጥ በድብቅ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 25 የተስማሙት ወረራው በተጀመረበት የሀምሌ ወር (1969) መሆኑን ይገልጻል፡፡ ከዐረብ ሊግ ሀገራት መካከል ግብጽና ሳዑዲ ዐረቢያ በድብቅ ሶማሊያን ይረዷት ነበር፡፡ ሊቢያና አልጄሪያ ግን የኢትዮጵያ ደጋፊ ነበሩ፡፡ ***** ሚያዚያ 8/2006 ተጻፈ፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 26 የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ክፍል ስድስት ===የኢትዮጵያ ህዝብ በሶማሊያ ወረራ ላይ የነበረው አቋም=== ሶማሊያ ኢትዮጵያን የወረረችበት ወቅት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጽማ በአድዋ ላይ ድል ከተመታችበት ዘመን በእጅጉ ይለያል፡፡ ኤርትራ በ1990 ባድመን ከወረረችበት ወቅትም በጣም ይለያል፡፡ በሁለቱ ወቅቶች ማዕከላዊውን መንግሥት ገትሮ ያስጨነቀ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በሀገሪቱ ውስጥ አልነበረም፡፡ በ1969-70 ግን አብዮታዊው የደርግ መንግሥት በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ነበር፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ከኢህአፓ ጋር በከረረ የከተማ ውጊያ ውስጥ ገብቷል፡፡ ቀይ ሽብርም የታወጀው በዚያን ጊዜ ነው፡፡ ጀብሃና ሻዕቢያ አስመራን በ10 ኪሎሜትር ራዲየስ ከበው ከዛሬ ነገ ከተማዋን እንይዛለን እያሉ በመጠባበቅ ላይ ነበሩ፡፡ “ኢዲዩ” የተባለው ድርጅት የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የጠረፍ ከተሞችን ይዟል፡፡ ህወሐት፣ ኦነግ፣ የአፋር ነጻ አውጪ ግንባር እና ሌሎችም ድርጅቶች በደርግ መንግሥት ላይ ብረት አንስተዋል፡፡ ደርግ ያንን ውጥረት ሁሉ ተቋቁሞ የሶማሊያን ወረራ መመለስ ነበረበት፡፡ እንደተመኘውም ሶማሊያን ለማባረር ችሏል፡፡ ታዲያ ደርግ ሶማሊያን ያባረረበትን ጉልበት ከየት አገኘ? በርካታ ምንጮች ይህንን ጉዳይ በትክክል አይጽፉትም፡፡ በተለይም ምዕራባዊያን ደርግን ስለሚጠሉት ብቻ “ኢትዮጵያ ያሸነፈችው ሶቪየትና ኩባ ስለተዋጉላት ነው” ይላሉ፡፡ የሚገርመው ግን ሶቪየት ህብረት ለኢትዮጵያ የመሳሪያና የስልጠና ድጋፍ ብትሰጥም ጦርነቱ እስኪያበቃ ድረስ ሶማሊያ በሰራዊት ብዛትና በመሳሪያ ጉልበት ከኢትዮጵያ የምትበልጥ መሆኑ ነው፡፡ ሶቪየት ህብረት ለረጅም ዓመታት የሶማሊያ አሰልጣኝና አስታጣቂ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ ከሶቪየት ህብረት የመረጃ ድጋፍ እንዳገኘችው ሁሉ ሶማሊያም ከሶቪየት ህብረት ሰፊ ድጋፍ ታገኝ ነበር፡፡ ታዲያ ሶቪየት ህብረት በህዳር ወር ውስጥ (1970) የኢትዮጵያን ጦር ማማከር ጀምራ ነው እንዴ ጦርነቱ በአራት ወር ውስጥ ብቻ ሊጠናቀቅ የቻለው? ዋናው ነጥብ ያለው እዚያ ላይ ነው! የኢትዮጵያ ህዝብ በጦርነቱ ሙሉ በሙሉ መንግሥትን በመደገፉ ነው ኢትዮጵያ ድል ለማድረግ የቻለችው፡፡ በአምስት ወር ውስጥ 80,000 መደበኛ ሰራዊትና እና 220,000 ሚሊሺያ ሰራዊት ለመመልመል የተቻለው ከግዳጅ ነጻ በሆነ ሂደት ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወታደር ዲሲፕሊን ጠባቂና የተመደበበትን ግዳጅ ለመወጣት ቁርጠኛ ሆኖ መገኘቱም ሌላ ነጥብ ነው፡፡ ህዝቡ በየቀበሌው የተመደበበትን ግዳጅ ሲወጣ የነበረ መሆኑም ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ ለምሳሌ የሰራዊቱ ቀለብ በአብዛኛው በህዝቡ ነበር የሚዘጋጀው፡፡ ታዲያ ብዙዎች የሚደነቁበት አንድ ነጥብ አለ፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገርንና መንግሥትን ለያይቶ የሚያይበት ሚዛን ነው፡፡ የደርግ መንግሥት ከየካቲት 1969-እስከ ህዳር የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 27 1970 ድረስ በቀይ ሽብር ልጆቹን ሲጨርስበት ነበር፡፡ ጦርነቱ እየተካሄደ እንኳ ቀይ ሽብር ሙሉ በሙሉ አላቆመም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆቹ በደርግ ታጣቂዎች የጥይት እራት ቢሆኑበትም በመንግሥቱ ላይ አላቄመም፡፡ በድንቁርናና በድህነት ሲማቅቅ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገርን ከጊዜያዊ መንግሥት ነጥሎ ማየትን ያውቅበታል፡፡ ለዚህም የያኔው የኢትዮጵያ ህዝብ የሶማሊያ ወረራን በልበሙሉነት ለመከላከል የቻለው፡፡ ህዝቡ እንደዚያ ባይሆን ኖሮ ሶማሊያ እንደ ምኞቷ በአዋሽ ብቻ ሳትገታ አዲስ አበባንም ጠቅልላ ትወስድ ነበር፡፡ ===የፖለቲካ ቡድኖች በወረራው ላይ የነበራቸው አቋም=== በዚያ ዘመን በኢትዮጵያ ምድር ከፍ ያለ ስም የነበራቸው የፖለቲካ ቡድኖች ሶስት ናቸው፡፡ አንደኛው ኢህአፓ (የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ) ነው፡፡ ሁለተኛው ከደርግ ጋር ያበረው መኢሶን (የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ) ነው፡፡ ሶስተኛው ኢዲዩ (የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት) ነው፡፡ ይህ ኢዲዩ (የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት) የተባለ ቡድን በጊዜው በጦርነቱ ላይ የወሰደው አቋም በግልጽ አይታወቅም፡፡ ቡድኑ የቀኝ ፖለቲካ አቀንቃኝ መሆኑ ሲጤን ግን ወረራውን ሳይቃወመው አይቀርም ሊያስብለን ይችላል፡፡ መኢሶን ከደርግ ጋር ይሰራ ስለነበር ወረራውን በመቃወም አቋም ወስዷል፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ በወቅቱ ቅድሚያ የሰጠው ወረራውን ለመቀልበስ ለሚደረገው ጥረት ሳይሆን የምንጊዜም ተቀናቃኙ የሆነውን ኢህአፓን በቀይ ሽብር ለመደምሰስ ለሚያደርገው ትግል ነው፡፡ መኢሶን በቀይ ሽብር አፈጻጸም ውስጥ የነበረው ሚና የደርግ መንግሥት ከነበረው ሚና በምንም አያንስም፡፡ እንዲያውም በመጋቢት 1969 (ከመጋቢት 13-መጋቢት 15/1969) በአዲስ አበባ ከተማ ለሶስት ቀናት የተካሄደውን የቤት ለቤት አሰሳ የመራው “መኢሶን” እንደነበረ በብዙ ምንጮች ተረጋግጧል (የኢህአፓው መሪ ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ እና የኢላአማ መሪ ማርቆስ ሀጎስን ጨምሮ በርካታ የኢህአፓ አባላት የተገደሉት ያኔ ነው፤ ኢህአፓም በአቅሙ ብዙዎችን ገድሏል)፡፡ ታዲያ የሚያስገርመው ከደርግ ጋር እንዲህ እጅና ጓንት ሆኖ ሲሰራ የነበረ ቡድን ማንም ባልጠበቀው መንገድ የሶማሊያ ወረራ በሚካሄድበት ወቅት (ነሃሴ 1969) ከደርጎች ጋር የነበረውን ህብረት አፍርሶ ወደ ህቡዕ ፓርቲነት ለመለወጥ ጥረት ማድረጉ ነው፡፡ መኢሶን እርምጃውን “የትግል ስልት ለውጥ ነው” ይለዋል፡፡ “ይህንንም ያደረግኩት ደርግ ከኢህአፓ ቀጥሎ እኔን ሊያጠፋኝ በሚስጢር ሲያደባ በማየቴ ነው” ይላል፡፡ ደርግ ግን ኩነቱን “ፍርጠጣ ነው” ይለዋል፡፡ የመኢሶንንም እርምጃ ከሶማሊያ ወረራ ጋር ያዛምደዋል፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማሪያም ከጋዜጠኛ ገነት አየለ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ “መኢሶን የስልጣን ጥመኛ ነው፤ ከኛ ጋር ቆይተው ስልጣን ለመቆናጠጥ አመቺ ጊዜ በመጠበቅ ላይ እያሉ ሶማሊያ ወረረችን፤ በመሆኑም ሶማሊዎቹ በጥቂት ቀናት ውስጥ አዲስ አበባ የሚገቡ ስለመሰላቸው ከዚህ ከደከመ መንግሥት ጋር ምን እንሰራለን በማለት ፈርጥጠዋል” ብለዋል፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 28 በጣም አወዛጋቢው ኢህአፓ የወሰደው አቋም ነው፡፡ የደርግ መንግሥት ባለስልጣኖች “ኢህአፓ እኛን በማውገዝ ከሶማሊያ ጋር በግልጽ ቆሟል” ይላሉ፡፡ ከዚህም አልፎ በቆሬ ግንባር በሰራዊታችን ውስጥ በሰገሰጋቸው ሰርጎ ገቦቹ አማካኝነት “ሳቦታጅ” በመስራት በረቀቀ ዘዴ ወግቶናል በማለትም ያከሳሉ፡፡ ለምሳሌ ኮሎኔል መንግሥቱ ሀይለማሪያም በቆሬ ግንባር የተሰማሩት የኢህአፓ ሰርጎ ገቦች “ድሬ ዳዋ በሶማሊያ ጦር ተይዟል፤ የቆሬ ምሽግም ከባቢሌ በኩል በመጣ ሀይል ተቆርጧል፤ የኢትዮጵያ ሰራዊት አልቆለታል፤ ጉድጓድ ውስጥ ተቀምጠን ጠላት እስኪመታን ድረስ መጠበቅ የለብንም፤ እጅ መስጠት ይሻለናል” እያሉ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ይነዙ ነበር” በማለት ጽፈዋል፡፡ በደርግ ወገን ሆነው የያኔውን ታሪክ ጻፉት አቶ ገስጥ ተጫኔም (በብዕር ስማቸው “ዘነበ ፈለቀ”) “ነበር” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዲህ ይሉናል፡፡ “የኢትዮጵያ ህዝብ የኤርትራ ተገንጣዮች አስቀድሞ ባወቀው ምክንያታቸው ከወራሪዋ ሶማሊያ ጋር በማበራቸው ባይገረምም ኢህአፓ የሶማሊያን ወረራ የመደገፏን ጉዳይ ግን እንደ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅትነቷ በጣም ያዘነበት ድርጊት ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ህዝብ መሀል ካወጧት የተሳሳቱ አቋሞቿ አንዱ ይህ ነበር” (ዘነበ ፈለቀ፣ “ነበር”፣ 1996፣ ገጽ 268) ለመሆኑ ኢህአፓ በያኔው መንግሥት ባለስልጣናት እንደተከሰሰው የሶማሊያ ወረራን በእርግጥ ደግፏል?…. ይህንን ጥያቄው መመለስ ይከብዳል፡፡ ኢህአፓ እስከ አሁን ድረስ “ደርጎች የፈጠሩት የስም ማጥፋት ነው እንጂ የሶማሊያ ወረራን የደገፍኩበት ወቅት የለም” በማለት ያስተባብላል፡፡ የተወሰኑ የቀድሞ የኢህአፓ አባላትና አንዳንድ የታሪክ ምሁራን ግን ኢህአፓ “ጦርነቱ የሁለት አድሃሪ መንግሥታት ጦርነት ነው፤ ጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ የሶማሊያ ህዝብ አድሃሪያንን ደግፎ በጦርነቱ መሳተፍ የለበትም” የሚል አቋም ወስዷል ይላሉ፡፡ ይህ ምን ማለት ነው?… ጦርነቱ በሁለት መንግሥታት ፉክክር የተወለደ ነው ማለት ነው?… አንድ ማንም የማያስተባብለው ሐቅ አለ፡፡ ጦርነቱ የተከሰተው ሶማሊያ ኦጋዴን በመውረሯ ነው፡፡ በመሆኑም በዘመኑ የነበረው ኢትዮጵያ መንግሥት ወረራውን ለመቀልበስ ያደረገው ትግል በማንኛውም መመዘኛ ሲታይ ፍትሐዊ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ደርግ ጨፍጫፊ ስለነበረ ብቻ ህዝቡ ከርሱ ጋር ሆኖ ሀገሩን ከወረራ እንዳይከላከል ጥሪ ማድረግ በምንም መልኩ አይሞገስም፡፡ ኢህአፓ ይህንን አድርጎ ከሆነ የታሪክ ተወቃሽ መሆኑ አይቀርለትም፡፡ ነገር ግን ይህንን አደረገ የተባለው ድርጅት በወቅቱ በደርግ መንግሥት የጭካኔ ብትር በከፍተኛ ሲመታ ነበር፡፡ በመሆኑም የኢህአፓ እርምጃ በደርግ የደረሰበትን ፍጅት ለመበቀል ተብሎ የተወሰደ የግብረ መልስ ምት ነው ሊባል ይችላል፡፡ ***** የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 29 በዚያ ዘመን አነስተኛ ሀይል የነበራቸው ህወሐትና ኦነግ በሶማሊያ ወረራ ላይ የወሰዱትን አቋም በማስረጃ አስረግጦ መተንተን አስቸጋሪ ነው፡፡ ይሁንና ድርጅቶቹ በጦርነቱ ወቅት ከሶማሊያ መንግሥት ጥቅሻ ያላገኙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የዚያድ ባሬ መንግሥት ሁለቱን ድርጅቶች ወደ ሞቃዲሾ የጠራው ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ነው፡፡ ጀብሃና ሻዕቢያ ደግሞ ወረራውን ደግፈዋል፡፡ ====የኢትዮጵያ የመልሶ ማጥቃት ቅድመ-ዝግጅት (ከህዳር 1970- የካቲት 1970)==== የሶማሊያ ሰራዊት ሀረርን ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት ከከፈሸበት በኋላ ይዞታውን ለማስፋት አልሞከረም፡፡ ሶቪየት ህብረት፣ ኩባ እና የመን ኢትዮጵያን በመደገፍ በጦርነቱ ውስጥ መግባታቸውን ሲረዳ በያዛቸው አካባቢዎች መከላከያውን ማጠናከሩን ነው የመረጠው፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ የመልሶ ማጥቃት ዝግጅቷን አጧጧፈች፡፡ ሶቪየት ህብረት በቃሏ መሰረት በታህሳስ ወር 1970 (ስድሳ ሰባት) የሚግ ተዋጊ ጄቶችን ለኢትዮጵያ ሰጠች፡፡ 600 ታንኮች፣ ከ200 በላይ ብረት ለበሶች፣ 150 ያህል መድፎች፣ 100 የቢ.ኤም ሮኬት ማስወንጨፊያዎች፣ ዙ-23 የአየር መቃወሚያዎች፣ ቀላልና ከባድ መትረየሶች፣ ቦምቦች፤ ሮኬቶች፣ ወዘተ… ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ዘመናዊ የሆኑ ሶቪየት ሰራሽ ዋዝ ጂፖች፣ ሽፍን ወታደራዊ መኪናዎች፣ “ኦራል”፣ “አይፋ” እና “ካማዝ” የሚባሉ ከባድ መኪናዎችም ለኢትዮጵያ ተሰጡ፡፡ የአውሮፕላንና የሂሊኮፕተር አብራሪዎች፣ ወታደራዊ መኮንኖችና የውጊያ አሰልጣኞች፣ የፈንጂ መሐንዲሶች፣ ወዘተ…. በአስቸኳይ ወደ ሶቪየት ህብረት እየተላኩ ተጨማሪ ስልጠና እንዲወስዱ ተደረገ፡፡ በሀገር ውስጥ ደግሞ ቀደም ብለው የተጀመሩት የፓራ-ኮማንዶ፣ የአየር ወለድ፣ የባህር ወለድ፣ የከባድ መሳሪያ ተኳሾች፣ የበታች አዛዦች፣ የመደበኛ ተዋጊዎች እና የሚሊሻ ወታደሮች ስልጠናዎች ተጠናክረው ቀጠሉ፡፡ የያኔውን ታሪክ በትክክል ለማወቅ እንዲቻለን የኢትዮጵያ መንግሥት ስልጠና ያካሄደባቸውን ማዕከላት ዝርዝር ማሳወቅ ያለብኝ ይመስለኛል፡፡ “ታጠቅ የጦር ሰፈር”፡- በሸዋ ክፍለ ሀገር ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ (20 ኪሜ ) የሚገኝ ሲሆን ኢትዮጵያ በታሪኳ የገነባችው ትልቁ የጦር ማሰልጠኛ ማዕከል ነው፡፡ በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ወቅት በታጠቅ ይሰለጥኑ የነበሩት ሚሊሻዎች ናቸው፡፡ ይህ ማዕከል በአንድ ጊዜ መቶ ሺህ ሰልጣኞችን ለመቀበል ይችላል፡፡ 1. “ኩሃ የጦር ሰፈር”፡- በትግራይ ክፍለ ሀገር የሚገኝ የጦር ማሰልጠኛ ነው፡፡ በዚህ ማዕከል የሰጠለኑት የመደበኛ ጦር አባላት ናቸው፡፡ 2. “አዘዞ ጦር ሰፈር”፡- በጎንደር ክፍለ ሀገር ነው የሚገኘው፡፡ በዚህኛውም ማዕከል የሰለጠኑት የመደበኛ ጦር አባላት ናቸው፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 30 3. “ለምለም ጦር ሰፈር” (ለምለም ግቢ)፡- በሸዋ ክፍለ ሀገር በደብረ ዘይት ከተማ የሚገኝ የጦር ማሰልጠኛ ነው፡፡ በዚህ ማዕከል የሰለጠኑት መደበኛ ተዋጊዎችና አየር ወለዶች ናቸው፡፡ 4. ዝዋይ ጦር ሰፈር፡- በሸዋ ክፍለ ሀገር ነው የሚገኘው፡፡ በዚህ ማዕከል የሰለጠኑት ፓራኮማንዶዎች ናቸው፡፡ 5. አዋሳ የጦር ሰፈር፡- በሲዳሞ ክፍለ ሀገር ከአዋሳ ሀይቅ ዳር ነው የሚገኘው፡፡ በዚህኛውም የጦር ሰፈር የሰለጠኑት የፓራኮማንዶ ተዋጊዎች ናቸው፡፡ 6. ለገዳዲ የጦር ማሰልጠኛ፡- ከአዲስ አበባ በሰሜን አቅጣጫ በ20 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በዚህኛውም ማዕከል የሰለጠኑት ፓራኮማንዶዎች ነበሩ፡፡ 7. አዋሽ አርባ የጦር ትምህርት ቤት፡- በሸዋ እና በሀረርጌ ድንበር አቅራቢያ (ከአዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ) ነው የሚገኘው፡፡ በዚህ ማዕከል የሰለጠኑት በአብዛኛው የታንክ፣ የመድፍና የሌሎች ከባድ መሳሪያ ተኳሾች ሲሆኑ አንድ የፓራኮማንዶ ብርጌድም በማዕከሉ ሰልጥኗል፡፡ የተዋጊ ወታደሮች፣ የመኮንኖችና የከባድ መሳሪያ ተኳሾች ስልጠና በተጧጧፈበት ወቅት የጦር መሳሪያዎቹ ወደ ኢትዮጵያ በመጓጓዝ ላይ ነበሩ፡፡ ታዲያ ከባድ መሳሪያዎቹ በታቀደላቸው ጊዜ ለመልሶ ማጥቃት ዘመቻው መዋላቸውን ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ መሪዎች የታንከኛና የመድፈኛ ተኳሾችን ስልጠና ከአዋሽ አርባ ወደ አሰብ ለማወዛር ተገደዋል፡፡ ይህም የተደረገው በጉዞ የሚባክነውን ጊዜ ለመቆጠብ እንዲቻል ተብሎ ነው (ታንኮቹን ከአሰብ ወደ ምስራቅ ግንባር በማጓጓዙ ሂደት የኩባ ጓዶች ተሳታፊ ነበሩ )፡፡ ***** ሚያዚያ 10/2006 ተጻፈ፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 31 የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ክፍል ሰባት ===የኢትዮጵያ የፕሮፓጋንዳና የዲፕሎማሲ ስራዎች=== ኢትዮጵያ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ለመክፈት ያቀደችው በየካቲት ወር ሁለተኛው አጋማሽ (1970) ነበር፡፡ ከዚያ በፊት በሁሉም የእርከን የሚሰሩ ተግባራትን ማከናወን ነበረባት፡፡ ከነዚህ ተግባራት መካከል አንዱ ቅስቀሳ እና ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ይህም በሶስት ዘርፎች የተከፈለ ነው፡፡ 1. በኢትዮጵያ ህዝብና ሰራዊት ላይ ያነጣጠረ ቅስቀሳ እና ፕሮፓጋንዳ፡ ዓላማው የኢትዮጵያ ህዝብ የመጨረሻው ድል እስኪገኝ ድረስ ለዘመቻው ደጀን ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ነው፡፡ የፕሮፓጋንዳ ስራው በዋናነት የሚካሄደው በመገናኛ ብዙሃንና በጋዜጦች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና የኢትዮጵያ ሬድዮ በፕሮፓጋንዳው ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው ሲሆን የአዲስ ዘመንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦችም ለጦርነቱ ሙሉ ሽፋን እንዲሰጡት ተደርገዋል፡፡ ከዚህ ሌላ ለሰራዊቱ አባላት የሚሰራጭ “ታጠቅ” የተሰኘ ጋዜጣ በወረራው ማግስት ተፈጥሯል፡፡ የኢትዮጵያ አርቲስቶችና ደራሲያን በቅስቀሳው ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ስለሀገር እና ስለ ዳር ድንበር የሚያወሱ ዘፈኖች፣ ድራማዎችና ጭውውቶች እየተዘጋጁ ለህዝቡና ለሰራዊቱ እንዲቀርቡ ተደርገዋል፡፡ በየቀበሌውም የቲያትርና የድራማ ቡድኖች ተቋቁመው ህዝቡን ይቀሰቀሱት ነበር፡፡ የመልሶ ማጥቃት ውጊያ ሲጀመር ደግሞ የኢትዮጵያ ሬድዮ የጦርነቱን ውሎ በቀጥታ ይዘግብ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ለቅስቀሳ ስራ በስፋት ያገለገለው ዋነኛ መፈክር “አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት” የሚለው ነው፡፡ 2. በሶማሊያ ህዝብና ሰራዊት ላይ ያነጣጠረ ፕሮፓጋንዳ ዓላማው የሶማሊያን ህዝብ ከዚያድ ባሬ አመራር መነጠልና በሶማሊያ ሰራዊት ላይ ስነ-ልቦናዊ ሽብር መፍጠር ነው፡፡ በዚህም መሰረት ሀረር እና አዲስ አበባ ያሉት የኢትዮጵያ ሬድዮ ቅርንጫፎች በሶማሊኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የዚያድ ባሬን መንግሥት ነውር እና ውስጣዊ ገመና የሚተረትሩ ተከታታይ ፕሮግራሞችን እንዲያስተላልፉ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ልዩ ሌላ በራሪ ጽሑፎች እየተዘጋጁ በአውሮፕላንና በተወንጫፊ ሮኬቶች አማካኝነት ለሶማሊያ ህዝብ እንዲበተኑ ተደርገዋል፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 32 3. በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠረ ፕሮፓጋንዳ ዓላማው የሶማሊያን መንግሥት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት ማዋረድና ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ድል ተጨማሪ ድጋፍ ማስገኘት ነው፡፡ በዚህ መሰረት ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ መረጃ የሚሰጥ ራሱን የቻለ ጽ/ቤት ተቋቁሟል፡፡ “የፕሬስ ሳምንት” በተባለ ፕሮግራም አማካኝነትም የውጪ ጋዜጠኞች ኢትዮጵያን እየገበኙ ጦርነቱ ያደረሰውን ጥፋት እንዲመለከቱ ተደርጓል፡፡ ***** በሌላ በኩል የዘመኑ የኢትዮጵያ መሪዎች በዓለም ዙሪያ ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራ ሰርተዋል፡፡ በውጤቱም የሶሻሊስቱ ካምፕ በየሶማሊያን ወረራ ሊያወግዝ በቅቷል፡፡ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትም የሶማሊያን ወረራ በማውገዝ ከኢትዮጵያ ጋር ቆሟል፡፡ የምዕራብ ሀገራት ግን ሶማሊያ ወራሪ መሆኗን እያወቁ እንኳ ሊያወግዟት አልፈቀዱም፡፡ ይህም የሆነው ሶቪየት ህብረት የኢትዮጵያ አጋር ሆና በመገኘቷ ነው፡፡ ===ኢትዮጵያ- ከመከላከል ወደ ማጥቃት=== የካቲት 1970፡፡ ኢትዮጵያ የማጥቃት ዘመቻዋን የምትከፍትበት ወሳኝ ወቅት መምጣቱን የሀገሪቱ መሪዎች ተናገሩ፡፡ በመሆኑም ስልጠናውን በብቃት ያጠናቀቀው ሰራዊት በሚከተለው ሁኔታ ተደራጀ፡፡ 1. በምስራቅ ግንባር  አራት ታንከኛ ብርጌድ  ሁለት መድፈኛ ብርጌድ  ሁለት የከባድ መሳሪያ (ቢ.ኤም) ተኳሽ ብርጌድ  ሁለት መደበኛ ክፍለ ጦር  አራት ህዝባዊ ሚሊሻ ክፍለ ጦር 2. በደቡብ ግንባር  ሁለት ህዝባዊ ሚሊሻ ክፍለ ጦር  አንድ መድፈኛ ሻለቃ 3. አየር ሀይል  የኢትዮጵያ አየር ሀይል በጠቅላላው ከታጠቃቸው 75 አውሮፕላኖች መካከል 40 የሚሆኑትን ለግዳጅ አሰልፏል፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 33 የኢትዮጵያ ጦር ካሰለፈው ሀይል በተጨማሪ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው አንድ ክፍለ ጦር የሚሆን የኩባ ሰራዊትና አንድ የደቡብ የመን መድፈኛ ብርጌድም በምስራቁ ግንባር ተሰልፈዋል፡ ፡ (የኢትዮጵያ ሰራዊት ለረጅም ጊዜ ሲከላከል የቆየው በሁለት መደበኛ ክፍለ ጦሮች፤ ሶስት ሚሊሻ ክፍለ ጦሮች፣ ሁለት ሜካናይዝድ ብርጌድና ሁለት ነበልባል ብርጌድ ብቻ ነው)፡፡ ***** የኢትዮጵያ ሰራዊት የማጥቃት ዘመቻውን በሚከተለው ሁኔታ ለመፈጸም ነበር ያቀደው፡፡ 1. ሶስት ፓራኮማንዶ ብርጌዶችን ከጅጅጋ በስተሰሜን ባሉት የጭናክሰን እና የማርዳፓስ ገዥ መሬቶች ላይ በጃንጥላ (ፓራሹት) በማውረድ ድንገተኛ ጥቃት መክፈት 2. ከአሰብ የተነሳ አንድ ታንከኛ ብርጌድና አንድ መድፈኛ ብርጌድ በጅቡቲ ድንበር ጥግ እየተጓዘ አውበሬ (ተፈሪ በር) በምትባለው ከተማ አቅጣጫ ወደ ጅጅጋ እንዲመጣና ጥቃት እንዲከፍት ማድረግ 3. በቆሬ ግንባር ያለው የኢትዮጵያ ጦር ወደ ምስራቅና ወደ ሰሜን እንዲነቃነቅ በማድረግ በጅጅጋና በጉርሱም አውራጃ ያለውን የሶማሊያ ሰራዊት እንዲከብብ ማድረግ 4. በተመሳሳይ መንገድ ከአሰብ የተነሳ ሁለት ታንከኛ ብርጌድና አንድ መድፈኛ ብርጌድ በድሬ ዳዋ በስተምስራቅ በኩል እየተጓዘ ጀልዴሳ በተባለው ቦታ የተከማቸውን የሶማሊያ ሰራዊት እንዲያጠቃ ማድረግ 5. የሶማሊያ ጦር ከላይ በተጠቀሰው መንገድ በተከፈበት ጥቃት ሲበረገግ በሀረር የሚገኝ አንድ ግብረ ሀይል ወደ ሰሜን ተጉዞ በኮምቦልቻና ኤጄርሰ ጎሮ የከተመውን የሶማሊያ ሰራዊት እንዲያጠቃ ማድረግ 6. በሀረር ያለ ሌላ ግብረ ሀይል ወደ ደቡብ ተነቃንቆ ሀኪም ጋራ እና አቦከር አቅራቢያ የከተመውን የሶማሊያ ሰራዊት ካጠቃ በኋላ እግር በእግር እየተከተለው በፈዲስ ወረዳ በኩል ወደ ፊቅ አቅጣጫ እንዲጓዝ፤ ብሎም ወደ ኦጋዴን እንዲገሰግስ ማድረግ 7. በባሌ እና ነጌሌ ቦረና የተመደቡት ሁለት ሚሊሻ ክፍለ ጦሮች ከአየር ሀይል ጋር በመሆን በደቡብ አቅጣጫ እንዲያጠቁ ማድረግ ኮሎኔል መንግሥቱ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ይህንን የውጊያ እቅድ ያወጣችው የሶቪየትና የኩባ አማካሪዎች ከመምጣታቸውና ኢትዮጵያ ከሶቪየት ያኘችውን የመሳሪያ ድጋፍ ከመረከቧ በፊት ነበር፡፡ በዚያ ዕቅድ መሰረት የታንክና የመድፍ ተኳሾች በአሰብ ላይ ስልጠናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ታንካቸውን ይዘው ወደ ጦርነቱ ቦታ እንዲሄዱ ነበር የተፈለገው፡፡ የውጊያው የመጨረሻ ፕላን ላይ ውይይት በሚደረግበት ወቅት የሶቪየት አማካሪዎች “ዕቅዱ ሶማሊያን ለመውረር የተዘጋጀ ይመስላል” በማለታቸው ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ውጥን ለመከለስ ተገዳለች፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 34 ሶቪየቶች ይህንን እንዲሉ ያደረጋቸው ኢትዮጵያ ካደራጀችው ሜካናይዝድ ጦር ውስጥ ሰማኒያ በመቶ የሚሆነው ለሰሜን ሶማሊያ ቅርብ በሆነችው የጅጅጋ መስመር እንዲሰለፍ በመደረጉ ይመስላል (ሀርጌሳ ከጅጅጋ በቅርብ ርቀት ላይ ያለች መሆኗን ልብ በሉ)፡፡ የሶቪየት ህብረት እና የኩባ አጋሮች ከሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ጋር ብዙ ከተወያዩ በኋላ የኢትዮጵያ ጦር በሚከተለው አኳኋን እንዲያጠቃ ተወሰነ፡፡ 1. የፓራኮማንዶ ጦር በአውሮፕላን ተጓጉዞ ከጅጅጋ ጀርባ ባለችው የ“ጭናክሰን” ቀበሌ ላይ እንዲከማችና ውጊያውን ከዚያ እንዲጀምር 2. በቆሬ ግንባር ያለው ጦር በሜካናይዝድ ተጠናክሮ ውጊያውን እንዲጀምር 3. የኩባ ሜካናይዝድ ጦር እና የየመን መድፈኛ ብርጌድ ከኢትዮጵያ ሜካናይዝድ ጦር ጋር በመቀናጀት በጀልዴሳ አካባቢ ያለውን የሶማሊያ ሰራዊት እንዲያጠቁ፣ ግዳጃቸውን ከጨረሱ በኋላም ወደ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ በማምራት በስፍራው ያሉ የኢትዮጵያ ከተሞችን ነጻ እንዲያወጡ 4. ከሀረር የተነሳው ጦር በኮምቦልቻ እና በፈዲስ አቅጣጫዎች ማጥቃት እንዲጀምር፣ ከዚያም ፊቅን ይዞ ወደ ኦጋዴን እንዲዘምት 5. በባሌና በነጌሌ ቦረና አቅጣጫዎች የተመደቡ ሚሊሻ ክፍለጦሮች በተመሳሳይ ቀን ማጥቃት እንዲጀምሩ 6. የኢትዮጵያ አየር ሀይል በሁሉም አቅጣጫዎች የተጠናከረ ድብደባ እንዲፈጽም፡፡ ***** የካቲት 23/1970፡፡ የኢትዮጵያ ጦር በጭናክሰን እና በቆሬ በኩል በጅጅጋ ላይ የተጠናከረ ጥቃት ከፈተ፡፡ የሶማሊያ ጦር ጥቃት ይመጣብኛል ብሎ ባልጠበቀው አቅጣጫ በመወጋቱ ተደናገጠ፡፡ ጅጅጋን ላለመልቀቅ መሟሟት ጀመረ፡፡ ሶማሊዎች በዚህ ውዥንብር ውስጥ እያሉ በጀልዴሳ ግንባር ሌላ ጥቃት ገጠማቸው፡፡ የኢትዮጵያ አየር ሀይልም እስከ ሶማሊያ ድንበር እየገባ የሶማሊያ ሰራዊትን የአቅርቦትና የእደላ መስመሮችን በመደብደብ ከጥቅም ውጪ አደረጋቸው፡፡ የሶማሊያ ሰራዊት ጅጅጋን ከለቀቀ ትልቅ የሞራል ውድቀት እንደሚገጥመው ያውቃል፡፡ በመሆኑም ከጅጅጋ በስተምዕራብ በኩል ባለው የካራ ማራ ተራራ ላይ ማዘዣውን በመስራት በከፍተኛ ደረጃ ተከላክሏል፡፡ ሆኖም በለስ አልቀናውም፡፡ ጥቃቱ በሁሉም ግንባር የተከፈተ በመሆኑ አጋዥ ሰራዊት ከየትም ማንቀሳቀስ አልቻለም፡፡ በመሆኑም የካቲት 26/1970 በካራ ማራ ተራራ ላይ ከባድ ሽንፈት ገጠመው፡፡ ጅጅጋን ለኢትዮጵያ ሰራዊት በመልቀቅ ወደ ሀርጌሳ መስመር አፈገፈገ፡፡ የኢትዮጵያ ሰራዊትም የካቲት 27/1970 ንጋት ላይ የጅጅጋ ከተማን ያዘ፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 35 የኢትዮ-ኩባ-የመን ጥምር ጦር በጀልዴሳ የተከማቸውን የሶማሊያ ሰራዊት ለሶስት ተከታታይ ቀናት ወጋ፡፡ ይህ ውጊያ ታንክ ከታንክ ጋር የተፋጨበት በመሆኑ በርካታ የጦር መሪዎች “የጦርነት ፊልም ይመስል ነበር” እያሉ አድናቆታቸውን ሰጥተውታል፡፡ የሶስቱ ሀገራት ጥምር ጦር ከሶስት ቀን በኋላ ግዳጁን በማጠናቀቅ በቆላው ምድር ላይ ገሰገሰ፡፡ የካቲት 30/1970 ግዳጁን በማጠናቀቅ ከኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር በስተደቡብ ያሉ ከተሞችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ፡፡ ከሀረር የተንቀሳቀሰው ጦር ደግሞ በሰሜን በኩል ግዳጁን በቀላሉ በመወጣት ኮምቦልቻን አልፎ እስከ ኤጀርሳ ጎሮ ድረስ ገስግሷል፡፡ ከሀረር በስተደቡብ የተነቃነቀው ግብረ ሀይል ግን ከሶማሊያ ሰራዊት ከፍተኛ የሆነ መከላከል ገጥሞታል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር የካቲት 29/1970 ፈዲስን የተቆጣጠረው ከባድ መስዋዕትነት ከከፈለ በኋላ ነው፡፡ በባሌ እና በነጌሌ ቦረና ግንባር የተሰለፈው ጦር ግን ጠንካራ መከላከል ሳያጋጥመው እስከ ጠረፍ ድረስ እየገሰገሰ የኢትዮጵያ ከተሞችን ሁሉ በቀላሉ ለመቆጣጠር ችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ባገኘው ድል ተብቃቅቶ አልቆመም፡፡ ከመጋቢት 1/1970 ጀምሮ ሁሉም ሀይሎች ወደ ኦጋዴን አቅጣጫ ዘምተዋል፡፡ ሆኖም የሶማሊያ ሰራዊት በከፍተኛ የሞራል ውድቀት ውስጥ ገብቶ ስለነበር ጠንካራ ጦርነት ይደረግበታል ተብሎ በታሰበው የኦጋዴን መሬት ላይ የሚረባ ውጊያ ለማድረግ አልተቻለውም፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ጦር መጋቢት 1/1970 ፊቅን፣ መጋቢት 3/1970 ደጋሃቡርን፣ መጋቢት 4/1970 ቆራሄን፣ ሰገግንና ቀብሪ ደሃርን፣ መጋቢት 5/1970 ወልወልንና ዋርዴርን፣ መጋቢት 7/1970 ጎዴን ያለ ምንም ውጊያ ተቆጣጥሯል፡፡ ***** ሚያዚያ 11/2006 ተጻፈ፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 36 የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ክፍል ስምንት ===የጦርነቱ ውጤት=== የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት በስምንት ወራት ውስጥ በኢትዮጵያ የበላይነት ተጠናቋል፡፡ የሶማሊያ መንግሥት ከመጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ ሰራዊቱን ከኢትዮጵያ ምድር አስወጥቷል፡፡ ሶማሊዎች ኦጋዴንን በ“ስልታዊ ማፈግፈግ” የለቀቁ መሆናቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ነገር ግን ከያኔው ዘመቻ ወዲህ ኦጋዴንን በከፍተኛ ሀይል ለመውረር አልሞከሩም፡፡ ከ1970-75 ባለው ጊዜ የም.ሶ.ነ.ግ (የምዕራብ ሶማሊ ነጻ አውጪ ግንባር) ከሶማሊያ ምድር እየተነሳ የደፈጣ ጥቃቶችን ለመፈጸም ቢሞክርም እንኳ የኢትዮጵያ ጦር በአነስተኛ ሀይል ያባርረው ነበር፡፡ በጦርነቱ የደረሰው ጉዳት በልዩ ልዩ ወገኖች በተለያየ መንገድ ተገልጿል፡፡ ለምሳሌ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም የጦርነቱን ጉዳት በሚከተለው ሁኔታ ጽፈውታል፡፡ ሰራዊት የሞተ የቆሰለ የተማረከ የሶማሊያ ሰራዊት 15,900 26,000 1,785 የኢትዮጵያ ሰራዊት 18,200 29,200 7 ዊኪፒዲያ የተሰኘው የኢንተርኔት ኢንሳይክሎፒዲያ ደግሞ ጉዳቱን እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል፡፡ ሰራዊት የሞተ የቆሰለ የተማረከ የሶማሊያ ሰራዊት 6,453 2,409 275 የኢትዮጵያ ሰራዊት 6,133 10,563 3,867 ከዊኪፒዲያ የተገኘው መረጃ አንድ ተቃርኖ አለው፡፡ ይኸውም “1/3ኛ የሚሆን “የሶማሊያ ሰራዊት ከጥቅም ውጪ ሆነ” እያለ በሶማሊዎች ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን አሳንሶ የሚያቀርብ መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም በጦርነቱ በሶማሊያ ሰራዊት ላይ የደረሰው ጉዳት በሁለቱ ምንጮች ከቀረበው የሚበልጥ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለመርዳት ከመጡት የውጪ ዜጎች መካከል 400 ኩባዊያን፤ 100 የመናዊያንና 33 የሶቪየት ህብረት ዜጎች ሞተዋል፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 37 ሁለቱ ሀገራት ለጦርነቱ ካሰለፏቸው ከባድ መሳሪያዎች መካከል ብዙዎችን አጥተዋል፡፡ በዚህ ረገድ በሶማሊያ ጦር ላይ የደረሰው ጉዳት ከበድ ይላል፡፡ ሶማሊያ ለጦርነቱ ካሰለፈቻቸው ታንኮች መካከል 200 የሚሆኑትን አጥታለች፡፡ ኢትዮጵያም 100 ታንክ ተደምስሶባታል፡፡ የኢትዮጵያ አየር ሀይል 15 ያህል አውሮፕላኖች ወድመውበታል፡፡ ሶማሊያ ግን 35 ጢያራዎችን አጥታለች፡፡ (የሚገርመው ነገር የኢትዮጵያ የአየር ሀይል ብዙ አውሮፕላኖችን የደመሰሰው በአየር በአየር ውጊያ ነው)፡፡ ጦርነቱ በሲቪሉ ህብረተሰብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ነው ያደረሰው፡፡ ለምሳሌ የሶማሊያ ጦር በፈጸመው ጥቃት “ቆሬ” የምትባለውን አነስተኛ ከተማ (ከሀረር በ70 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኝ) ሙሉ በሙሉ አውድሟል፡፡ የጅጅጋ ከተማን በሚለቅበት ጊዜም ከፍተኛ ፍጅትና ዘርፋ ፈጽሟል፡፡ የከተማዋ ህንጻዎች ሆን ተብለው ተደምስሰዋል፡፡ በሌላ በኩል የሶማሊያ አየር ሀይል በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ በኦጋዴን ክልል ባሉት የደጋሃቡር እና አዋሬ ከተሞች ላይ በፈጸመው ድብደባ በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን ገድሏል፡፡ በስምንቱ ወራት ውስጥ ከ10,000 ያላነሱ ኢትዮጵያዊያን በሶማሊያ ጦር ተግዘው ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ለአስራ አንድ ዓመታት ታስረዋል፡፡ የሶማሊያ ጦር በተለይም የሶማሊ ብሄረሰብ አባላት ባልሆኑት ላይ የሚያደርሰው ግፍ እጅግ የበረታ እንደነበረ ከልዩ ልዩ ምንጮ የተገኙ ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡ በሶማሊያ ጦር እጅ የወደቁ ምርኮኞችም ዓለም አቀፍ ድንጋጌን በጣሰ ሁኔታ ይሰቃዩ እንደነበረ ተረጋግጧል፡፡ የኢትዮጵያ ጦርም ኦጋዴንን መልሶ ከያዘ በኋላ የሶማሊያን ሰራዊት ደግፈዋል ባላቸው ላይ የግድያና የዘረፋ እርምጃ መውሰዱ ይነገራል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት የደረሰው በፊቅ፤ ጎዴ፣ ደጋሃቡርና ቀብሪ ደሃር አካባቢዎች ነው፡፡ አንዳንድ የጦር መሪዎች ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሶማሊዎችን ከሶማሊያ ጦር ባለመለየት ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ውርጅብኝ ሲያካሄዱባቸው ነበር ይባላል፡፡ በዚህም የተነሳ ከአንድ ሚሊዮን ያላነሱ ኢትዮጵያዊ ሶማሊዎች ሀገር ጥለው ተሰደዋል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ ድንበር ገብቶ ሲቪሎችን ምርኮኛ አላደረገም፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ እጅ የወደቁ የጦር ምርኮኞች ሰብዓዊ ክብራቸውን በማይነካ መልኩ ነው የተያዙት፡፡ የሶማሊያ ጦር ከኦጋዴን ሲወጣ በአካባቢው የተሰሩ የመሰረተ ልማት አውታሮችን አውድሟል፡፡ ይህ የውድመት እጣ ከደረሳቸው ግንባታዎች መካከል በዘመኑ ከአዲስ አበባው የቦሌ አየር ማረፊያ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ የነበረው የጎዴ አየር ማረፊያ እና ባሌና ሀረርጌን የሚያገናኘው ትልቁ የዋቢ ሸበሌ ድልድይ ይጠቀሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ጦር የመልሶ ማጥቃት ውጊያውን በከፍተኛ ፍጥነት ያገባደደ በመሆኑ አካሄዱ የሶማሊያ መሪዎችን በጣም አስፈርቶአቸው ነበር፡፡ በመሆኑም ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 38 “ኢትዮጵያ ሀገራችንን ልትወርር ስለሆነ እያንዳንዱ ዜጋ ለውጊያው ይሰለፍ” የሚል አዋጅ አስነግረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር የተባበሩት የሶቪየት አማካሪዎችም “ሶማሊያን ልትወርሩ ነው እንዴ?” እያሉ መጨቅጨቅ ጀምረው ነበር፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ጦር ኦጋዴንን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረ በኋላ በድንበሩ ላይ ቆሟል፡፡ === ጦርነቱ በሁለቱ ሀገራት ጂኦ-ፖለቲካ ላይ ያስከተለው ለውጥ=== የኢትዮ-ሶማሊያ ጦር በአካባቢው ጂኦ-ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ነው ያስከተለው፡፡ በጦርነቱ ያሸነፈችው ኢትዮጵያ የአካባቢው ልዕለ-ሀያልና ባለተጽእኖ ሀገር ሆና ወጥታለች፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ሀይልም በፊት ከፍተኛ እድገት በማሳየት ከአፍሪቃ ታላላቅ ሰራዊቶች አንዱ ሊሆን በቅቷል፡፡ በተጨማሪም በሶማሊያ ላይ በተገኘው ድል የተነቃቃው የኢትዮጵያ ሰራዊት “በምስራቅ የተገኘው ድል በሰሜንም ይደገማል” የሚል መፈክር በማንገብ ወደ ኤርትራ ከዘመተ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጀብሃና ሻዕቢያን ከደጋማው ምድር በማባረር ወደ ሳህል በረሃ (ናቅፋ) መልሶአቸዋል፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ድሮ የሶቪየት ህብረት ወዳጅ የነበረችው ሶማሊያ ከጦርነቱ በኋላ ጭልጥ ብላ ወደ ምዕራባዊያን ጉያ ገብታለች፡፡ ከሶቪየት ህብረት ጋር የማትጣጣመው ቻይናም ከጦርነቱ በኋላ ዋነኛዋ የሶማሊያ መሳሪያ አቅራቢ ሆና ብቅ ብላለች፡፡ በሌላ በኩል በጦርነቱ ሂደት ገለልተኛ ሆነው የቆዩት ጅቡቲና ሱዳን ከጦርነቱ በኋላ የሶማሊያ ደጋፊ ሆነዋል፡፡ ከትልቁ ጦርነት በኋላ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን ማስታጠቁን ቀጥላለች፡፡ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ለተነሱ ሀይሎች ሁሉ የዲፕሎማሲና የማቴሪያል ድጋፍ ታደርግም ነበር፡፡ በመሆኑም በዚያ ወቅት የነበሩት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ድርጅቶች (ጀብሃ፤ ሻዕቢያ፣ ኢህአፓ፣ ህወሐት፣ ኦነግ፣ ኦነእግ፣ ሲአን፣ ወዘተ..) አመራሮች በሶማሊያ ፓስፖርት ነበር የሚጠቀሙት፡፡ በተጨማሪም እያንዳንዱ ድርጅት በሞቃዲሾና በሀርጌሳ ጽ/ቤቶች ነበሩት፡፡ በሌላ በኩል በጦርነቱ ሽንፈትን የቀመሱት ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ የመሬት ይገባኛል ጥያቄአቸውን ለመከለስ ተገደዋል፡፡ ድሮ “እስከ አዋሽ ድረስ የኛ ነው” በማለት እንዳልሞገቱት ሁሉ ከጦርነቱ በኋላ አቋማቸውን በማለሳለስ “ኦጋዴን የኛ ነው” የሚል ፖሊሲ ማራመድ ጀምረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በትውልድ ሶማሊ ያልሆኑትን የኦሮሞና የሲዳማ ህዝቦችን ነጻ ያወጣል ተብሎ ለተቋቋመው “የሶማሊ አቦ ነጻነት ግንባር” (SALF) የሚሰጡትን ድጋፍ በማቋረጥ ለኦጋዴን ነጻነት ይታገላል የሚሉትን የምዕራብ ሶማሊ ነጻ አውጪ ግንባርን (WSLF) ብቻ መደገፍ ጀምረዋል፡፡ በውጤቱም ሶ.አ.ነ.ግ (SALF) የተባለው ድርጅት ከ1974 በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለማቆም ተገዷል፡፡ የሶማሊያ መንግሥት በጦርነቱ በመሸነፉ ውስጣዊ ቀውስና መፈካከስ አጋጥሞት ነበር፡፡ በጦርነቱ አካሄድ ላይ ልዩነት የነበራቸው ጄኔራል ፋራህ አይዲድ እና ኮሎኔል አብዱላሂ ዩሱፍ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 39 ከስልጣናቸው ተባረው ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል፡፡ እኒህ እውቅ የጦር መሪዎች ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ከሶማሊያ ጠፍተው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተቃውሞ ድርጅት ለማቋቋም በቅተዋል፡፡ የዚያድ ባሬን መንግሥት ለስድስት ዓመታት ከወጉት በኋላም በ1983 ከስልጣን አስወግደውታል፡፡ ***** ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማሪያም ሶማሊያን ማሸነፋቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ህዝብ የድሉን ብስራት በድምቀት እንዲያከብር አዋጅ አስነገሩ፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ ጦር ስትራቴጂካዊውን የካራማራ ተራራን የተቆጣጠረበት ውጊያ የድሉን ቁልፍ ያስጨበጠ በመሆኑ በብሄራዊ ደረጃ መዘከር እንዳለበት ተነገረ፡፡ በመሆኑም መላው ኢትዮጵያ ህዝብ የካራማራውን ድል በቅድሚያ በአውራጃ ደረጃ በተቋቋሙ ኮሚቴዎች አማካኝነት በየአካባቢው አከበረ፡፡ በማስከተልም ድሉ በጅጅጋ ከተማ በብሄራዊ ደረጃ በተዘጋጀው ታሪካዊ ክብረ-በዓል ተከበረ፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማሪያም ጦርነቱን በአጭር ጊዜ መፈጸማቸው ታላቅ ፖለቲካዊ ድል ነው ያስገኘላቸው፡፡ ከጦርነቱ በፊት እርሳቸውን ይጋፉ የነበሩ ባልደረቦቻቸው ከጦርነቱ በኋላ ድምጻቸውን ሙሉ በሙሉ አጥፍተዋል፡፡ ኢህአፓ የሚባለው ድርጅት ከድሉ በፊት ከጉያቸው ስር ሆኖ ሲያንጨንቃቸው እንዳልነበር ሁሉ ከድሉ በኋላ የት እንደገባ ሳይታወቅ ከአዲስ አበባ ከተማ ተሰውሯል፡፡ ሺህ ምንተሺህ የሚሆኑት የፖለቲካ ካድሬዎች “ቆራጡ መሪ” እያሉ የሊቀመንበሩ ስም በሀገሪቱ እንዲናኝ አድርገዋል፡፡ ሊቀመንበሩ ካዋቀሩት “አብዮታዊ ሰደድ” ጋር በደግም ሆነ በክፉ እየተጎሻሸሙ የፖለቲካ ስልጣን ለመቀራመት ያሰፈሰፉት “ወዝሊግ” እና “ማሌሪድ” የተሰኙ ድርጅቶችም ከድሉ በኋላ ቀስ እያሉ መክሰም ጀምረዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ዚያድ ባሬ ሁሉ ሊቀመንበር መንግሥቱም ከስልጣን ከመባረር አልዳኑም፡፡ እርሳቸው ከሊቢያው ሙአመር አል-ቀዛፊ (ጋዳፊ) ጋር ሆነው ዚያድን ለመፈንገል ሲታገሉ ካልጠበቁት አቅጣጫ በመጣ ሀይል ተወረሩ፡፡ ትልቁን የሶማሊያ ወራሪ ሰራዊት በኦጋዴን በረሃ የመከቱት ጀግና “ወንበዴ” እያሉ በሚንቁት አነስተኛ ሀይል ተበልጠው ከስልጣን ተወገዱ፡፡ ***** ኢትዮጵያና ሶማሊያ ከጦርነቱ በኋላም በጠላትነት መፈላለጋቸውን አላቆሙም፡፡ በ1972 የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ባደረገው ጥረት የተኩስ ማቆሚያ ስምምነት ቢፈራረሙም እስከ 1983 ድረስ በእጅ አዙር ሲዋጉ ነው የሰነበቱት፡፡ ሁለቱ መንግሥታት በጋራ የፈጸሙት መልካም ነገር ቢኖር በ1980-1981 የእስረኛ ልውውጥ ማድረጋቸው ብቻ ነው፡፡ ያ ታሪካዊ ጦርነት ሙሉ ፍጻሜውን ያገኘው በጥር/1983 የዚያድ ባሬ መንግሥት ከስልጣን በተወገደበት ጊዜ ነው የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 40 (ይህንን የምለው ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩ አይደለም፤ ጦርነቱ ሲለኮስ የነበረው የዚያድ ባሬ መንግሥት በዓለም አቀፍ መድረክ እውቅና የተሰጠውን የኢትዮጵያ ህጋዊ ድንበርን የማያከብር በመሆኑ ነው)፡፡ ***** ሚያዚያ 12/2006 ተጻፈ፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 41 የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ክፍል ዘጠኝ ====የጦርነቱ መሐንዲሶች ===== ይህ ታሪካዊውን የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት የምንቃኝበት የመጨረሻው ክፍል ነው፡፡ በዚህ ክፍል በኢትዮጵያ ወገን ሆነው ጦርነቱን ሲመሩ ከነበሩት አዋጊዎችና የጦር ሜዳ ጀግኖች መካከል ከአንዳንዶቹ ጋር እንተዋወቃለን፡፡ 1. ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ የኢትዮጵያ ጦር የበላይ አዛዥ ነበሩ፡፡ የጦርነቱን የዘመቻ እቅድ በመንደፍና ጦር በመምራት ሰራዊቱን ባያዋጉትም ለጦርነቱ የሚያስፈልገውን አመራር በመስጠት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በየሀገሩ እየዞሩ መሳሪያ በመለመንና የኢትዮጵያን ህዝብ በመቀስቀስ ረገድ የአንበሳ ድርሻ የነበራቸው፡፡ በተጨማሪም ሶስት መቶ ሺህ ሚሊሻ ጦር በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰለጠነበትን የታጠቅ ጦር ሰፈር የመሰረቱት እርሳቸው ናቸው፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ ተኩስ በሚደረግበት ትርዒት ውስጥ አልገቡም፡፡ ነገር ግን የሶማሊያ ጦር የሀረርን ከተማ ከቦ ሲያስጨንቃት በነበረበት ጊዜ በከተማዋ መሀል ላይ ባለው የሀረር የጦር አካዳሚ የጦር መሪዎቻቸውንና የሶቪየት ጓዶቻቸውን በመሰብሰብ ስለውጊያው ይነጋገሩ ነበር፡፡ ከዚህ እንደምንረዳው መንጌ ጭካኔ ቢኖርባቸውም ድፍረትም ነበራቸው፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ የኢትዮጵያ ጦር ጅጅጋን ከተቆጣጠረ በኋላ በማግስቱ ሊቀመንበር መንግሥቱ ከተማዋን መጎብኘታቸው ነው፡፡ 2. ፊልድ ማርሻል ቫሰሊ ፔትሮቭ፡ ሶቪየት ህብረት ከነበሯት እውቅ የውጊያ ስትራቴጂስቶች አንዱ ነው፡፡ የሶማሊያ ጦር ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ የሶቪየት ምድር ጦር ምክትል አዛዥ ነበር፡፡ በምዕራባዊያን የተጻፉ ሰነዶች ጄኔራል ፔትሮቭ ሶማሊያን ከኦጋዴን ያስወጣው ዘመቻ እቅድ ነዳፊ እና የሶስቱ ሀገራት ጥምር ጦር (ኢትዮጵያ፣ ኩባ እና ደቡብ የመን) ዋና አዛዥ ነበር ይላሉ፡፡ በደርግ በኩል ሆነው ታሪኩን የጻፉ ወገኖች ግን ማርሻል ፔትሮቭ አማካሪ ነው እንጂ የጥምር ጦሩ አዛዥ አልነበረም ነው የሚሉት፡፡ የማርሻል ፔትሮቭ (ኢትዮጵያ ሲመጣ ጄኔራል ነበር) ወታደራዊ ችሎታ ብዙ ተደንቆለታል፡፡ ነገር ግን ከኢትዮጵያ አዛዦች ጋር ተግባብቶ የመስራት ችሎታ አልነበረውም፡፡ በተለይም ከአየር ሀይሉ አዛዥ ከኮሎኔል ፋንታ በላይ ጋር በከፍተኛ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 42 ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ የውዝግቡ መነሻ የኢትዮጵያ የጦር አውሮፕላኖች ሶማሊያ ድንበር ውስጥ ገብተው ጥቃት መፈጸማቸው ነው፡፡ማርሻል ፔትሮቭ አውሮፕላኖቹ ሶማሊያ መግባታቸውን ይቃወማል፡፡ ኮሎኔል ፋንታ ደግሞ “መሬታችንን የያዘብንን ጠላት እስከ ሞቃዲሾ ድረስ ሄደን የመውጋት መብት አለን” ባይ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ማርሻል ፔትሮቭ ክሱን ለሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማሪያም አሰማ፡፡ መንጌም “ፋንታ ያደረገው ትክክል ነው” በማለት ፈረዱበት፡፡ በዚህም አኩርፎአፋቸው ነበር ይባላል፡፡ ማርሻል ፔትሮቭ ባለፈው የካቲት ወር ውስጥ በ97 ዓመቱ አርፏል፡፡ 3. ሌፍትናንት ጄኔራል አርላንዶ ኦቾዋ፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የኩባ ጦር አዛዥ ነው፡፡ ይህም ጄኔራል ግሩም የሆነ ወታደራዊ ችሎታ የነበረው ሲሆን ከኢትዮጵያ የጦር መኮንኖችም ጋር ተግባብቶ በመስራት ተደናቂነትን አትርፏል፡፡ እርሱ ያዘመተው ጦር ለፈጸመው ጀብዱ መታሰቢያ ይሆነው ዘንድ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ደረጃ ኒሻን ተሸልሟል፡፡ ጄኔራል ኦቾዋ ወደ አንጎላ የዘመተውንም የኩባ ጦር ይመራ ነበር፡፡ ነገር ግን በአንጎላ ምድር በለስ ሊቀናው አልቻለም፡፡ በደቡብ አንጎላ በተደረገ አንድ ውጊያ ብዙ የኩባ ወታደሮች ሲሞቱ “ለውድቀቱ ተጠያቂው አንተ ነህ” የሚል ወቀሳ ከፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ ቀርቦበታል፡፡ በዚሁ ጦስ ከስልጣኑ ወርዶ በቁም እስር ላይ እያለ “በአደንዛዥ እጽ እና በህገ-ወጥ የአልማዝ ንግድ ውስጥ እጁን ነክሯል” የሚል ክስ ቀረበበት፡፡ ክሱ በዝግ ችሎት ከታየ በኋላም የሞት ፍርድ ተፈረደበት፡፡ ሀምሌ 7/1981 በጥይት ተደብድቦ ተገደለ፡፡ 4. ብ/ጄኔራል ለገሠ ተፈራ (የህብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና)፡ የኢትዮጵያ አየር ሀይል ካፈራቸው ምርጥ አብራሪዎች አንዱ ነው፡፡ በአየር በአየር ውጊያ ስድስት የሶማሊያ ሚግ ጄቶችን በማጋየት ጀብዱ የፈጸመ ተዋጊም ነው፡፡ ሆኖም በመጨረሻው ዙር ባደረገው በረራ በሶማሊያ ድንበር ውስጥ ጥቃት አድርሶ ሲመለስ አውሮፕላኑ በመመታቱ ሊማረክ በቅቷል፡፡ ሶማሊዎቹ ጄኔራል ለገሠን ለአስራ አንድ ዓመታት ካሰሩት በኋላ በ1981 ለቀውታል፡፡ ጄኔራሉ በእስር ቤት ሳለ ከፍተኛ ስቃይ ስለደረሰበት ከእስር ተፈትቶ ወደ አዲስ አበባ በመጣበት ጊዜ ሰውነቱ አልቆ ከሞት የተነሳ አጽም ይመስል ነበር፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ ጄኔራል ለገሠን በልዩ ወታደራዊ ስነ-ስርዓት ከተቀበሉት በኋላ የሀገሪቱ የመጨረሻ ደረጃ ኒሻን የሆነውን “የህብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ” ሸልመውታል፡፡ ከጄኔራል ለገሰ ሌላ ይህንን ሜዳይ የተሸለሙት ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው (አንደኛው ሊቀመንበር መንግሥቱ ራሳቸው ሲሆኑ ሁለተኛው ብ/ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማሪያም ናቸው)፡፡ 5. ሌ/ኮ/ ፋንታ በላይ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 43 የኢትዮጵያ አየር ሀይል ዋና አዛዥ ሲሆን አየር ሀይሉ በሶማሊያ ባለጋራው ላይ የበላይነት እንዲቀዳጅ ያስቻለውን ወታደራዊ ስልት የነደፈ እውቅ መኮንን ነው፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ አየር ሀይል በሶማሊያ ድንበር ውስጥ እየገባ የሶማሊያ ሰራዊት የእደላና የስምሪት መስመሮችን እንዲደበድብ የሚለውን ሃሳብ ያመነጨው እርሱ ነው፡፡ በዚህም ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል፡፡ ሌ/ኮ/ ፋንታ በላይ በአየር ሀይል አዛዥነቱ እስከ 1979 አገልግሏል፡፡ በማዕረጉም እስከ ሜጀር ጄኔራል ደረጃ ደርሷል፡፡ በ1981 ተሞክሮ የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ዋነኛ ጠንሳሽ እርሱ እንደነበረም ይነገራል፡፡ መፈንቅለ መንግሥቱ ከከሸፈ ከሁለት ወር በኋላ ግን እስከ ዛሬ ድረስ እንቆቅልሽ በሆነ ሁኔታ ተገድሏል፡፡ ሌሎች የኢትዮጵያ የጦር አዛዦች 6. ኮሎኔል ተስፋዬ ገብረኪዳን፡ የኢትዮጵያ ታንከኛ ጦርን በማደራጀት ለውጊያው ያዘጋጀ መኮንን ነው፡፡ ኮሎኔል ተስፋዬ ከጊዜ በኋላ በሌፍትናንት ጄኔራል ማዕረግ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ሆኗል፡፡ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ሀገር ጥለው ከሄዱ በኋላም ለስድስት ቀናት የኢትዮጵያ መሪ ነበር፡፡ 7. ሌ/ኮ ሙላቱ ነጋሽ (በኋላ ሜጀር ጄኔራል)፡ ጄኔራል ሙላቱ በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ወቅት በአዲስ መልክ የተቋቋመው የምስራቅ እዝ ዋና አዛዥ ነበር፡፡ 8. ሌ/ኮ/ ተካልኝ ንጉሤ፡ በድሬ ዳዋ እና በጀልዴሳ ግንባር የተሰፈለውን የኢትዮጵያ ጦር የመራ መኮንን ነው፡፡ 9. ኮሎኔል ተስፋዬ ሀብተማሪያም (በኋላ ብ/ጄኔራል)፤ በጭናክሰን ግንባር አስደናቂ ጥቃት በመፈጸም ለታላቁ የካራማራ ድል መንገድ የከፈተው የኢትዮጵያ የፓራኮማንዶ ሀይል አዛዥ አዛዥ ነበረ፡፡ 10. ሌ/ኮ ደምሴ ቡልቶ (በኋላ ሜጀር ጄኔራል)፤ በደቡብ ግንባር የዘመተው የኢትዮጵያ ሰራዊት አዛዥ ነበር፡፡ ኮሎኔል ደምሴ በኢትዮጵያ ሰራዊት ውስጥ በነበረው ቆይታ እስከ ሜጀር ጄኔራል ማዕረግ ድረስ ለማደግ በቅቷል፡፡ በዚህ ማዕረግ የምስራቅና የሰሜን እዞች (አንደኛው አብዮታዊ ሰራዊትና ሁለተኛ አብዮታዊ ሰራዊት) ዋና አዛዥ ሆኖ ካገለገለ በኋላ ግንቦት 1981 በተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጦስ ተገድሏል፡፡ ***** ሚያዚያ 13/2006 ተጻፈ፡፡ የኢትየ-ሶማሊያ ጦርነት (1969-1970) ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ 44 ጠቃሚ የመረጃ ምንጮች 1. Evil Days, Thirty Years of War and Famine in Ethiopia: An Africa Watch Report, New York , September 1991 2. Gebru Tareke, “The Ethiopia-Somalia War of 1977 Revisited, Journal of African Historical Studies, pp-635-667 3. Gebru Tareke, The Ethiopian Revolution: War in the Horn of Africa, New Haven CT, Yale University Press, 2009 4. Kenneth G. Weiss, “The Soviet Involvement in the Ogaden War”, Center for Naval Analysis, Alexandria, Virginia, February 1980 5. Mesfin Wolde-Mariam: Somalia: A Problem Child of Africa, 1978 6. Tibebe Eshete, The Root Cause of Ogadeni Problem, Journal of North African Studies, Vol 13, Number 1, 1991 7. ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም፣ “ትግላችን”-የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ የትግል ታሪክ፡ ጸሐይ አሳታሚና አከፋፋይ ድርጅት፡ ሎስ አንጀለስ፡ 2004 8. ብ/ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ፡ የጦር ሜዳ ውሎዎች ከምስራቅ እስከ ሰሜን፡ አዲስ አበባ፣ 2000 9. ብ/ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማሪያም፣ የጦር ሜዳ ውሎ፣ አዲስ አበባ፣ 1996 10. ዘነበ ፈለቀ፣ “ነበር”፣ አዲስ አበባ፣ 1996 11. ገነት አየለ አንበሴ፣ የሌ/ኮ/ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ትዝታዎች፣ ሜጋ አሳታሚ ድርጅት፣ 1994

No comments:

Post a Comment