Monday, April 27, 2015

በአይሲስ የተጣሰው የቁርአን ቃል – “ሙስሊም ባልሆኑ ንፁሃን ሰዎች ላይ ግድያ የፈፀመ ሰው የጀነትን እጣን አያሸትም”

ኑርሁሴን እንድሪስ
በሁለቱ ታላላቅ እምነቶች ውስጥ (ክርስትና እና እስልምናን ማለቴ ነው) ለሰው ዘር በሙሉ የተላለፈ አንድ መለኮታዊ መልዕክት አለ፡፡ ይህ መልዕክት በሁለት ቅዱሳን መፃህፍት ውስጥ ቢገኝም መልዕክቱ ግን ተመሳሳይ ነው፡፡ የሰው ልጅን ነፍስ ማጥፋት የተወገዘ ተግባር መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እና ቁርአን ያወሳሉ፡፡ ይህን መልዕክት ለሰው ልጆች የላከው ደግሞ የሰማይና የምድር ፈጣሪ እንዲሁም የሰው ልጆችን ጨምሮ በሁለቱ መካከል ያሉትን በሙሉ ያስገኘው አምላክ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ምዕራፎቹ ውስጥ የሰው ልጅ ግድያን ይከለክላል፡፡ በማቲዎስ 5፡21፣ ምፅአት 20፡13፣ ሮሜ 13፡14፣ ዘፍጥረት 9፡5-6 … ወዘተ፤ በጣም ብዙ አንቀፆች ሰውን መግደል የማይፈቀድ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በማቲዎስ 5፡21 ውስጥ የሰፈረው ቃል እንዲህ ይላል፡-


(Photo File)
(Photo File)

“… አትግደል፤ የገደለ ሰው ይፈረድበታል …”
በቅዱስ ቁርአን ውስጥም የሰው ልጅን ነፍስ ማጥፋት ትልቅ ሀጢአት መሆኑ በብዙ አንቀፆች ውስጥ ፍሮአል፡፡ በአል-ሙምታሐና፡8፣ በአል-ኒሳ 89—91፣ በአል-በቀራ፡ 190፣ በአል-አንኢም፡151…
ውስጥ የመግደልን አስከፊነት ያነሳል፡፡ በአል-ማኢዳ፡32 ውስጥ የሰፈረው እንዲህ ይነበባል፡- “… አንድ ነፍስን የገደለ ሰው መላውን የሰው ዘር እንዳጠፋ ይቆጠራል፤ አንድ ነፍስን ያዳነ ሰው መላውን የሰው ዘር እንዳዳነ ይቆጠራል…”

በእስልምናም ሆነ በክርስትና እምነቶች ውስጥ የመግደልን አስከፊነት የሚገልፁ የአምላክ ቃላቶች ተቀምጠዋል፡፡ ምዕመናን ከዚህ ክፉ ተግባር እንዲቆጠቡም ሐያሉ አምላክ አዟል፡፡ ነገር ግን በእስልምናም ሆነ በክርስትና ሐይማኖት ተከታዮች በርካታ የግድያና የሽብር ተግባሮች መፈፀማቸውን ታሪክ ይነግረናል፡፡ እንደ ፖለቲካ ተመራማሪዎች ከሆነ፤ የሽብርተኝነት ዋና አላማ በመንግስት አልያም በሆነ አካል ላይ ተፅዕኖና ማስገደድን መፍጠር ነው፡፡ ሽብርተኝነት ከማንኛውም ሀይማኖት ጋር የሚገናኝ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ፍትህ ያጡ ግለሰቦች የሚከተሉት ተግባር ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ የፖለቲካ አላማን ያነገቡ ቡድኖች ፈፅሙት ነው፡፡ ሃይማኖቶች መግደል ክልክል መሆኑን የሚገልፁ ከሆነ ታዲያ ለምንድነው ሃይማኖተኞች የሚገድሉት? ግድያና ሽብር ማካሄድ የሚገናኘው ከሃይማኖት ጋር ነው ወይስ ከፖለቲካ? የተለያዩ እምነቶችን የሚያራምዱ የአለማችን ሰዎች በደርዘን የሚቆጠሩ ግድያና ሽብሮችን በንፁሐን ዜጎች ላይ ፈፅመዋል፡፡ ለምሳሌ በ2011 ዓ.ም የቀኝ ክንፍ ክርስቲያን አክራሪ የሆነው አንደርስ ብሪቬክ በኖርዌይ 77 ሰዎችን ገድሏል፡፡ ብሪቬክ ከፍተኛ የሆነ የእስልምና ሃይማኖት ጥላቻ እንደነበረው በወቅቱ ተገልጿል፡፡ በ2013 ዓ.ም የሶማሊያ ሙስሊሞች በዌስትጌት የገበያ ሞል ውስጥ ቦንብ አፈንድተው የ67 ሰዎችን ህይወት ቀጥፈዋል፡፡ በ1955 ዓ.ም በኦክላሐማ ከተማ ውስጥ የፈነዳው ቦንብ 166 ንፁሐንን ገድሏል፡፡ ድርጊቱን የፈፀሙት ደግሞ ቲሞቲ እና ቴሪ የተባሉ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ በ2002 ዓ.ም በባሊ ደሴት ላይ የፈነዳው ቦንብ የ202 ዜጎችን ነፍስ በልቷል፡፡ ድርጊቱን የፈፀሙት ጀማህ ኢስላሚያ የተባሉ የእስልምና ተከታዮች ናቸው፡፡ በ2004 ዓ.ም የሰሜን ምስራቅ ህንድ ክርስቲያኖች ድርጅት 44 ሰዎችን ገድሏል፡፡ በ2001 ዓ.ም የተጠለፈ አውሮፕላን በዓለም የንግድ ድርጅት ህንፃ ላይ ተጋጭቶ 3000 ንፁሐንን ገድሏል፡፡ ተግባሩን የፈፀሙት የአልቃኢዳ ሙስሊሞች ነበሩ፡፡
በ2015 በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የአል-ሻባብ ሙስሊሞች 148 ኬንያውያንን ገድለዋል፡፡
በ1972 ዓ.ም የካቶሊክ እምነት ተከታዮች የሆኑት የአይሪሽ ሪፐብሊካን አርሚ ቡድኖች በለንደን 47 ሰዎችን በቦንብ ፈጅተዋል፡፡ እነዚህን የመሰሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሽብርና ግድያዎችን በሁለቱም እምነቶች ውስጥ የሚገኙ ቡድኖችና ግለሰቦች ፈፅመዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ ሽብርና ግድያ ባለቤትነቱ የማንም ሃይማኖት አለመሆኑን ነው፡፡ የቀድሞ የግብፅ ሙፍቲ ሼክ አሊ ጎማኢ እንደተናገሩት፤ “ሽብርተኝነት ሃይማኖት የሚወልደው ጉዳይ አይደለም፡፡ ሽብርተኝነት የብልሹ አስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡ ሽብርተኝነት፣ የእብሪተኝነትና አጥፊነት መገለጫ ነው፡፡ ብልሹነት፣ እብሪተኝነትና አጥፊነት ከመለኮታዊ ልቦና ጋር የሚገናኙ አይደሉም፡፡” ራሱን የእስልምና መገለጫ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው አይሲስም የግብፁ ሙፍቲ በተናገሩት ውስጥ የሚፈረጅ መሆኑን ተግባራቱ ያሳያሉ፡፡ ባለፈው እሁድ በ28 ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ግድያ አላማው ግልፅ አይደለም፡፡ አይሲስ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ምን አይነት ቅያሜ ውስጥ ቢገባ ይሆን 28 ዜጎቿን የፈጀው? ለሚለው ጥያቄም መልስ የለውም። አይሲስ የገደላቸው
ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ ነው እንዳንል በማግስቱ 24 የኢራቅ ሙስሊሞችን ገድሏል፡፡ ለዚህም ነው የአይሲስ አላማና መገለጫ የግብፁ ሙፍቲ ከተናገሩት ጋር ይገናኛል ያልኩት፡፡ አይሲስ ሙስሊም ክርስቲያን ሳይል በሰው ዘር ላይ የዘመተ አረመኔ ቡድን መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
አይሲስ የሸሪአ ተከታይ ነው ከተባለ ለምንድነው ታዲያ በቁርአን ውስጥ የሚገኘውን አል-ማኢዳ፡32
የጣሰው? “አንድ ነፍስን ያጠፋ መላውን የሰው ዘር እንዳጠፋ ይቆጠራል፤ አንድ ነፍስን ያዳነ መላውን የሰው ዘር እንዳዳነ ይቆጠራል፡፡” የሚለው መለኮታዊ ቃል ለምንድነው በአይሲስ ያልተከበረው? የሰው ነፍስን አጥፍቶ ጀነትን መመኘት የዋህነት ይመስለኛል፡፡ በታላቁ መምህር በነብዩ ሙሀመድ የህይወት ፈለግ ውስጥ የዚህ አይነቱ ርዕዮት በፍፁም የተወገዘ ነው፡፡ በቡካሪ ሐዲስ ውስጥ ነብዩ ሙሀመድ የተናገሩት ይህን ይመስላል፡-
“ሙስሊም ባልሆኑ ንፁሐን ሰዎች ላይ ግድያ የፈፀመ ሰው የጀነትን እጣን አያሸትም” ንፁሐን ሰዎች ላይ ግድያ ፈፅመን ጀነት መግባት የምንመኝ ከሆነ ካሁኑ እርማችንን ማውጣት አለብን፤ ነብይ ሽታውን እንኳን እንደማናገኘው አርድተውናልና፡፡ በእስልምና ሐይማኖት ውስጥ ጥልቅ እውቀት ያለው አይሲስ ወይስ መልእክተኛው ሙሐመድ? አይሲስ የሚያራምደው እስልምና ከየት የመጣ ይሆን? ነብዩ ካስተማሩትና ካዘዙት የእስልምና እውቀት ውጭ ከየት ሊመጣ!

No comments:

Post a Comment