Monday, April 27, 2015

ሕገ ወጥ ጎብኚ እንጅ ሕገ ወጥ ስደተኛ የለም!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ስደት ሕዝባችንን ከቀየው እያፈናቀለ በአራቱም መዓዝናተ ዓለም ማንከራተት ማንቀዋለል ማንገላታት ከጀመረ አራት ዐሥርት ዓመታት ሞላ፡፡ በደርግ ጊዜ ከተሰደዱት በዘመነ ወያኔ የተሰደዱት እኅት ወንድሞቻችን እናት አባቶቻችን እጅግ ይበዛሉ፡፡ ስደተኛ ወገኖቻችን በየተሰደዱበት ሀገር እንደሰው ታይተው የሰውነት ክብር የተነፈጋቸውና ብሔራዊ ክብራችን የወደቀው የተደፈረው የተዋረደው በዘመነ ወያኔ ነው፡፡ የሚገርመው ወያኔም ያው ቢሆንም ጨፍጫፊ የምንለው ደርግ “የዜጎች መዋረድ መደፈር የሀገር መዋረድ መደፈር ወይም ብሔራዊ ውርደት ነው” የሚል እንደ መንግሥት ከአንድ መንግሥት የሚጠበቅ ጠንካራ አቋም ስለነበረው ሌላው ቀርቶ ሊገላቸው የሚፈልጋቸው ተቃዋሚዎቹ አምልጠው በስደት ባሉባቸው የጎረቤት ሀገራት ችግርና እንግልት ሲገጥማቸው ለያሉበት ሀገር መንግሥት ከባድ ማስጠንቀቂያ በመስጠት መብቶቻቸው እንዲጠበቅ ያደርግ ነበር፡፡ በዘመነ ወያኔ ግን የሀገራችንና የዜጎች ክብርና ሞገስ እጅግ በሚያስደነግጥ እጅግ በሚያሳዝን እጅግ በሚያሳፍር ደረጃ በመውደቁ የሀገራችንና የዜጎቿ ክብርና ሞገስ የትም ቦታ በማንም ምናምንቴ ሁሉ የሚደፈር የሚረገጥ መጫወቻ መቀለጃ ለመሆን በቅቷል፡፡

video-migrant-boat-capsizes-near-italy-leaving-200-people-in-the-sea
ዜጎች በየተሰደዱበት ሀገራት ሀገርና መንግሥት እንደሌላቸው ኢሰብአዊ በደሎች ሲፈጸምባቸው ግዴታውን አውቆ አለሁ የሚላቸውና መብቶቻቸውን የሚያስከብርላቸው አንድም ዓይነት አካል አልባ ሆነዋል፡፡ በዘመነ ወያኔ ሀገራችንና ዜጎች እንዲህ ዓይነት ችግር ሊጋፈጡ ግድ ያለበት ምክንያት የወያኔ አገዛዝ የመንግሥት ቅርጽና አቋም ይዞ መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነቶችና ግዴታዎች ለመወጣት የሚያስችል ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ)፣ ሞራላዊ (ቅስማዊ)፣ ግብረገባዊ አቅም ብቃት ፍላጎትና ፈቃደኝነት አልባ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ሽባና ነውረኛ አገዛዝ ዜጎች በየተሰደዱበት ሀገራት ችግር በገጠማቸው ቁጥር ደርሶላቸው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ላለመወጣቱ የሚያቀርበው ምክንያትና ሽፋን “ሕገ ወጥ ስደተኞች ናቸው” የሚል ነው፡፡ ሕገ ወጥ ስደተኞች ስለሆኑም እነሱን ልረዳ የምችልበት ሕጋዊ አኪያሔድ የለኝም ይላል፡፡ ይህ ምክንያት በወያኔ አገዛዝ የተፈጠረ አስቀድሞ በነበረው ያልነበረ መሆኑን ልብ በሉ፡፡ ወያኔ ይሄንን የሚልበት የራሱ የሆነ ምክንያት አለው ወደ ኋላ ዕናየዋለን፡፡ ለነገሩ ወያኔ እንዲህ ይበል እንጅ ወገኖቻችን በየተሰደዱበት ሀገራት ኢሰብአዊ ግፍና በደል እየደረሰባቸው ካሉ ወገኖቻችን ከፊሎቹ በሚገባ ሕጋዊ የመኖሪያና የሥራ ፈቃዶች ያሏቸው ናቸው፡፡ ይሄም ቢሆን ግን ለሚያቀርቧቸው የእርዳታና የድረሱልኝ ጥሪ የአገዛዙ ኤምባሲ (የመንግሥት እንደራሴ) እና የቆንሲላ (የመንግሥት ጉዳይ አማካሪ) ጽ/ቤቶች አንድም ዓይነት የሚጠበቅባቸውን አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ አይደሉም፡፡ አገዛዙ እንዲህ ዓይነቱን ሴራ በዜጎች ላይ የሚፈጽምበት ምክንያት 1. አገዛዙ በሙሉ ትኩረቱ የሙሉ ጊዜ ሥራው አድርጎ የያዘው የሀገርና የዜጎችን ክብር በመሸጥ ጭምር ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም ጥቅሙን ማስጠበቅ ህልውናውን ማራዘም ስለሆነ፡፡ 2. ከቡድኑ ጥቅምና ቆሜላቸዋለሁ ከሚላቸው ወገኖቹ በስተቀር የሌሎችን ኢትዮጵያዊያን ወገኖችን ደኅንነት ጉዳይ ከመጤፍ የሚቆጥር ባለመሆኑ 3. አገዛዙ በሌሎች መንግሥታት ዘንድ እንደ አንድ መንግሥት የሚታፈር የሚከበር ባለመሆኑ ክብርና ሞገሥ አልባ በመሆኑ ናቸው፡፡ እነኝህን ደካማ የወያኔ አስተሳሰቦች ደግሞ ሁሉም በየትም ቦታ ስለሚታወቅ “ባለቤቱን ቃልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” እንደሚባለው ሁሉ የወያኔን ልብና አቅም ጠልቀው የሚያውቁት ባዕዳን በወገኖቻችን ነፍስ እንዳሻቸው ለመጫወት ለመቀለድ ድፍረቱን አገኙ፡፡

በእነዚህ ሰንካላና የደንቆሮ ምክንያቶቹ ግዴታውን የማይወጣው ወያኔ ግዴታውን ላለመወጣት “ሕገ ወጥ ስደተኛ” የሚለውን ቃል መሸሸጊያ አድርጎታል፡፡ ከወያኔም ውጪ ከሀገር ውጪ ያሉ ዜጎቹን ደኅንነትና መብት ላለማስጠበቅ ከኃላፊነቱ ለመሸሽ ይሄንን ቃል የሚጠቅስ ሞራሉ (ቅስሙ) የላሸቀ በመንግሥት ስም ያለ አካል አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ ለሌሎቹ መንግሥታት በየትም ሀገር ያለ ዜጋቸውን መብቶችና ደኅንነቶች ለማስጠበቅ ዜጋቸው ሆኖ ከመገኘቱ የበለጠ በቂ ምክንያት የላቸውም፡፡ እነዚህ ሀገራት ዜጎቻቸው ተሰደው በሚኖሩበት ሀገራት መብትና ደኅንነቶቻቸውን ማስጠበቅ አይደለም የመጨረሻ ከባድ የሚባል ወንጀል ሠርተውም በተገኙበት ወቅት እንኳን ቢሆን በተቻላቸው መጠን ሁሉ በወንጀሉ ከመጠየቅ ነጻ እንዲሆኑ እስከማድረግ ድረስ ከጎናቸው ይቆማሉ፡፡ ወያኔ ግን በተቃራኒ አቅጣጫ በመጓዝ የዜጎችን መብትና ደኅንነቶቻቸውን ላለማስጠበቅ ነው አንዴ ሕገ ወጥ ስደተኛ ሌላ ጊዜ ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ የላቸውም እያለ ዐሥር ምክንያት እየፈጠረ ኃላፊነቱን ላለመወጣት ጥረት የሚያደርገው፡፡
ይህችን “ሕገ ወጥ ስደተኛ” የምትል ቃል ወያኔ ብቻ አይደለም የሚጠቀምባት ምዕራባዊያን ሀገራት የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራትና ሌሎቹም ጭምር እንጅ፡፡ ልዩነቱ እነሱ ቃሉን የሚጠቀሙት ለዜጎቻቸው ሳይሆን ከተለያዩ ሀገራት ወደየሀገሮቻቸው ለሚገቡት ስደተኞች ሲሆን ወያኔ ደግሞ ቃሉን የሚጠቀመው ለወገኖቻችን መሆኑ ነው፡፡ እነሱ ለስደተኞች ይህንን ቃል የሚጠቀሙበት ምክንያትም የስደተኞቹን የስደተኝነት መብት ላለማክበር ሊያደርጉት የሚጠበቅባቸውን መስተንግዶ ላለመስጠት ላለማቅረብ ግዴታና ኃላፊነታቸውን ላለመወጣት ለመሸሽ ነው፡፡
ሲጀመር ሕገወጥ ስደተኛ ማለት ምን ማለት ነው? የቃሉ አጠቃቀምስ ትክክል ነው ወይ? ብለን ስንመረምር ፍጹም የተሳሳተ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስደተኛ ያሰደደው አንዳች አስገዳጅ ምክንያት ከሌለ በስተቀር አይሰደድም፡፡ ስደተኛ የሚሰደደው ያለበት አካባቢ ወይም ሀገር ለሕይዎቱ አደገኛ ሲሆንና ከተጋረጠበት አደጋ ሕይዎቱን ለማትረፍ ሲገደድ ነው፡፡ ስደተኛ የሚሰደደው የነፍስ ጭንቅ ሲይዘው ሲያጋጥመው ነው፡፡ ስደተኛ የሚሰደደው ጭላንጭል ተስፋ ሲያጣ ነው፡፡ ስደተኛ የሚሰደደው ምክንያቱ ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ)፣ ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊ የመሳሰሉት ሊሆን ይችላል በእነዚህ ምክንያቶች አሳዳጅ ሲኖርበትና ሲያሳድደው ነው፡፡
በእነኝህ አስገዳጅ ምክንያቶች ተገፍቶ ነፍሱን ለማዳን ለማቆየት እግሩ ወዳመራው የተሰደደን የሰው ልጅ ሁሉ ሁሉም የመንግሥታቱ ድርጅት አባል ሀገራት ሁሉ የመቀበል ተቀብሎም የማስተናገድ ግዴታ እንዳለባቸው የፈረሙት ስምምነት (convention) ይደነግጋል፡፡ ስደተኛ እነኝህን ያሰደዱትን ችግሮች ሁሉ ለመከላከል ሳይችል ቀርቶ ከአቅሙ በላይ ሆነውበት አፈናቅለው ያሰድዱታል እንጅ ወዶና ፈቅዶ በራሱ ላይ እንዲመጡበት እንዲፈጠሩበት እንዲከሰቱበት አድርጎ አይሰደድም፡፡ የሰው ልጅ ተረጋግቶ አስቦ አውጥቶና አውርዶ ወዶና ፈቅዶ ከሚኖርበት ሀገር ወደ ሌላ መሔድና ማየት የሚፈልገውና ወደዚያ ሀገርም ለመግባት ፈቃድ መጠየቅ ግድ የሚሆንበት ጎብኚ ሆኖ ያችን ሀገር ለመጎብኘት ሲያስብ ነው፡፡ የመጎብኘት ፍላጎት ሰላማዊና በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነው ከጀርባው የሚገፋው የሚያስገድደው ሰላማዊ ያልሆነ አንዳችም አስገዳጅ ክፉ ምክንያት የለም፡፡ ስለሆነም ገብቶ ለመጎብኘት ሊጎበኘው የፈለገውን ሀገር ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡ ፈቃድ ሳያገኝ ገብቶ ከተገኘ ይህ ሰው ሕገ ወጥ ነው የሀገሪቱ ምንግሥትም የሀገሪቱን ደኅንነት አደጋ ላይ ለመጣል እንደሚያሴር ሰላይ ሊቆጥረው ሊጠረጥረው ይችላል፡፡ ስደተኛ ግን እንዲህ አይደለም ድስት የሚገነፍለው ምን ሲሆን ነው? ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ስደተኛ የሚሰደደው በአስገዳጅና ጊዜ በማይሰጡ ምክንያቶች ነው፡፡ ተሰዳጁ የሚሰደድባቸው ሀገራት ይሄንን በአስገዳጅ ምክንያት የተሰደደን ሰው የመቀበል የማስተናገድ የሰብአዊና የሞራል (የቅስም) ግዴታ አለባቸው፡፡ ከሰብአዊነትና ከቅስም አንጻር ልናስተናግዳቸው የሚገቡ ነገሮች ሁሉ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ አይጠየቅባቸውም፡፡ አንዳች አውሬ ሊበላው እያሳደደው የነፍስ ጭንቅ ይዞት አድኑኝ እርዱኝ እያለ ሮጦ ዘሎ እሰው ቤት የገባ ሰው “በር አላንኳኳህም ሳይፈቀድልህ ግባ ሳትባል ነው የገባኸው ስለሆነም ሕገ ወጥ ነህ” ሊባል በፍጹም አይገባም ይህ ኢሰብአዊ ኢግብረገባዊ ኢቅስማዊ ፍረጃ አባባልና አስተሳሰብ ነው፡፡ ሰውየው ላንኳኳ ግባም እስክባል ልጠብቅ ካለ መበላቱ ነውና ማንኳኳትና ግባ እስኪባል መጠበቅ አይኖርበትም፡፡ ስለሆነም የጎብኚ እንጅ የስደተኛ ሕጋዊና ሕገወጥ የሚባል ነገር የለም፡፡ ቃሉ ራሱ ኢፍትሐዊና አጥቂ ቃል ነው፡፡ ቃሉ የተፈጠረውና እየተገለገሉበትም ያለው ኃላፊነታቸውንና ግዴታቸውን ላለመወጣት በሚጥሩ መንግሥታትና አካላት ነው፡፡
ከሀገራችን በተለያየ ምክንያት ዜጎች ቀያቸውን ለቀው ይሰደዳሉ ወገኖቻችን የሚሰደዱባቸው ሀገራት ወገኖቻችንን ላለማስተናገድ የሚጠቀሙበት አንድ ሌላ ቃል አለ “የኢኮኖሚ (የችጋር) ስደተኞች” የሚል፡፡ በዘመነ ወያኔ ከሀገራችን አንድም የኢኮኖሚ (የችጋር) ብቻ ተብሎ ሊጠራ የሚችል ስደተኛ የለም፡፡ ይሄንን ማንም ሰው ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ ምንም እንኳን ላይ ላዩን ሲያዩት ይምሰል እንጅ ዜጎች ከገጠር እስከ ከተማ እየተሰደዱ ያሉት በፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) በሆነ ምክንያት ነው፡፡ ገበሬው ወያኔ ካልሆንክ ወደድክም ጠላህም እኛን በግድ ካልደገፍክ ምርጥ ዘር ማዳበሪያና ሌሎችንም በዜግነቱ ሊያገኛቸው የሚገባውን ጥቅሞች አታገኝም በመባሉ ለችጋር ተዳርጎ በተፈጠረበት ድህነት ልጆቹ እየተሰደዱ ባለበት ሁኔታ፤ በከተማም ወያኔ ካልሆናቹህ በስተቀር ተብሎ ዜጎች በዜግነታቸው ብቻ ሊያገኝዋቸው የሚገቡትን ከሥራ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ዕድል ልታገኙ አትችሉም ተብሎ ደንቆሮው አገዛዝ ደንቆሮና አንባገነናዊ አቋም በመያዙ ዜጎች ለችግር በመዳረጋቸው ምክንያት ለመሰደድ በተገደዱበት ሁኔታ ወገኖቻችንን የኢኮኖሚ (የችጋር) ስደተኞች ብሎ ማለት እጅግ የተሳሳተ ፍረጃ ነው፡፡ ፍረጃው ምን ያህል ማስተዋል የጎደለውና ኢፍትሐዊ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ ምክንያቱ ባይገባኝም ሲጀመር ጀምሮ ዓለም እኛን በተመለከተ በምንም ነገር ላይ ትክክለኛ ፍርድን ሲፈርድ ታይቶ አይታወቅም፡፡ ዜጎች በኢፍትሐዊ ብየና እንደተፈረጁና እንደተንገላቱ አሉ ለወደፊቱም ይኖራሉ፡፡ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ብቻውን የኢኮኖሚ (የችጋር) ስደተኛ የለም፡፡ ምክንያቱም ያ ያሰደደው ችጋር የተፈጠረው በወያኔ ኢፍትሐዊና አንባገነናዊ አሥተዳደር ነውና፡፡ ይሄንን ስደተኛ ወገኖቻችንን የሚቀበሉ ሀገራትም ሆኑ የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኛ ተንከባካቢ ድርጅቶች አሳምረው ያውቁታል፡፡
እነኝህ ሀገራት ወገኖቻችን በግልጽ የፖለቲካ ስደተኞች መሆነናቸው እየታወቀም የፈረሙትን የመንግሥታቱ ድርጅትን ሕግ በመጻረር ወገኖቻችንን እያነቁ ለወያኔ አሳልፈው ሲሰጡ ለበርካታ ጊዜያት ተስተውለዋል፡፡ የመንን፣ ጅቡቲን፣ ሱዳንን፣ ኬንያን ዩጋንዳን ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከአውሮፓም ኖርዌይን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዓለም ለእኛ መቸም ፍትሐዊ ሆኖ አያውቅም ይሆናልም ብየ አልጠብቅም፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኛ ተንከባካቢ ድርጅቶች ወገኖቻችን ተሰደው በሚገኙባቸው ሀገራት የፖለቲካ ስደተኞች መሆናቸውን እያወቀም ወያኔና ሀገሮቹ በመመሳጠር ከሚያደርሱባቸው አፈና ሊታደጋቸው አልቻለም ሞክሮም አያውቅም፡፡ አደዳው ሲያጋጥምም የመንግሥታቱን ድርጅት ሕግ የሚጥስ የሚጻረር መሆኑን በመግለጽ አደጋውን ያደረሰባቸውን የዚያን ሀገር መንግሥትና የወያኔን አገዛዝ በመወንጀል አሥተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ሲያደርግ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ የፖለቲካ ስደተኛ ወገኖቻችን በእነዚህ ሀገራት ላሉ የመንግሥታቱ ድርጅት ስደተኛ ተንከባካቢ ድርጅቶች ማመልከቻቸውን ሲያቀርቡ ከሌሎች ሀገራት ፍጹም በተለየ መልኩ ብዙ እንግልት ይደርስባቸዋል፡፡ በድርጅቱ ያሉ ሠራተኞች የወያኔ ቅጥር ሠራተኞች ነው የሚመስሉት፡፡ ወገኖቻችን ከሌላው በተለየ መልኩ አግባብነት ፍጹም የሌለው መስተንግዶና እንግልት እንዲደርስባቸው ለምን እንደሚደረግ ፍጹም ግልጽ አይደለም፡፡ በእነዚህም ምክንያቶች ወገኖቻችን ችግር ገጥሟቸው ሲሰደዱ እንግልትና ተቀባይነት የማጣት ችግርን በመፍራት ኢትዮጵያዊነታቸውን ደብቀው ኤርትራዊ ወይም ሶማሊያዊ ነኝ በማለት በስደተኝነታቸው ሊያገኙ የሚገባቸውን ጥቅም ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በቀይ ባሕርና በሜዲትራኒያን ባሕር ስደተኞች የመስጠም አደጋ ደርሶባቸው ሲያልቁ ኤርትራዊያን ወይም ሶማሊያዊያን ተብለው ከሚገለጹት ማቾች ከ70% በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ናቸው፡፡ አውሮፓ ወይም መካከለኛው ምሥራቅ የገባ ዘመድ ወዳጅ ወይም የምታውቁት ሰው ካላቹህ ምናዊ ነኝ ብለህ ገባህ? ለምን? በሉና ጠይቁት ይነግራቹሀል፡፡
ምዕራባዊያን በእኛ ስደተኞች እጅግ እንደተማረሩ በየመድረኩ በምሬት ያወራሉ፡፡ ለዚህ ስደት የዳረገንንም ችግር ከእኛ በላይ ጠንቅቀው ያውቃሉ መፍትሔውንም ጭምር፡፡ ያላቸው ምርጫ ሁለት ነው ለመሰደዳችን መንስኤ ለሆነው አንባገነናዊ አገዛዝ ምንም ዓይነት ድጋፍና እርዳታ ባለማድረግ የራሳችንን ጉዳይ እኛው እንድንፈታው ለእኛው በመተው አንባገነን አገዛዞችን ተገላግለን በይነሕዝባዊ (ዲሞክራሲያዊ) አሥተዳደር እንድንመሠርት መንገዳችን ላይ ጋሬጣ ባለመሆን መተባበር ወይም በስደተኛ ጎርፍ ለመጥለቅለቅ መፍቀድ፡፡ ምዕራባዊያን ለወያኔ የብረት ምሰሶ ድጋፍ ባይሆኑ ኖሮ እውነቴን ነው የምላቹህ ይሄንን ስልም መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኘ ነው 23 ዓመታት አይደለም አንድ ዓመት እንኳን የመቆየት አቅም ባልነበረው ነበር፡፡ ነገር ግን ምዕራባዊያን ፍጹም አግባብነት ፍትሐዊነት ለሌለው ለከት አልባ ርሕራሔ ቢስ ለሆነው ጥቅማቸው ወያኔን እየደጋገፉ እዚህ አድርሰውታል፡፡ በአሁኑ ዘመን ምዕራባዊያን የሞግዚት አሥተዳዳሪዎቻችን ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ መንግሥት አልባ ከሆነችና ሉዓላዊነቷን ካጣች 23 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በሀገራችን ያለው አሥተዳደር የሞግዚት አሥተዳደር ነው፡፡
ሰሞኑን የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ምክትል ሚንስትር ያለችውን አልሰማቹህም? ሴትዮዋ የሀገሯ መንግሥት በየዓመቱ የሚያወጣውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሀገራት የሰብአዊ መብት አያያዝ የሚተነትንበትን መግለጫ በተጻረረ መልኩ የወያኔ አገዛዝ ዲሞክራሲያዊ መሆኑንና በዚህ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ማንም ብረት ማንሣት አይደለም ክፉ ነገር እንኳን ይናገርና ዋ! አይማረኝ ላልምረው” ማለቷን ሰምታቹሀል፡፡ አሜሪካን ስናውቃት ለሐሳብን በነጻ የመግለጽ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት ጠበቃ ነኝ በማለቷ እራሷን የዓለም ፖሊስ አድርጋ በመሾምም ይሄንንና ሌሎች ተጓዳኝ ዲሞክራሲያዊ (በይነ ሕዝባዊ) መብቶችን በዓለም ሀገራት ሁሉ አሰፍናለሁ ስትል ነበር የምናውቃት፡፡ ሴትዮዋ ባደረገችው ንግግር ግን “የተቃውሞ ሐሳባቹህንም እንኳን ቢሆን በአገዛዙ ላይ መግለጽ አትችሉም ጸባቹህ ከኔ ጋር ነው!” ስትል ዩ. ኤስ. አሜሪካ ቆሜለታለሁ የምትለው እሴት የውሸት መሆኑን አረጋገጠች፡፡ ለካ ያ ሁሉ በየዓመቱ ይወጣ የነበረ መግለጫ ሁኔታወችን ከዓለም ፖሊስነቷ ጋር ለማጣጣም ሲባል ለማስመሰል ይነገር የነበር ዲስኩር ኖሯል? አዎ! ያም በመሆኑ ነው በእርምጃ ሊደገፍ ያልቻለው፡፡ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ተብየው የሀገር ሉዓላዊነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ቢገባቸው ኖሮ ይህንን ድንበር ያለፈ የሀገርን ሉዓላዊነት ተዳፍሮ አለቅጥ በውስጥ ጉዳይ ላይ አራጊ ፈጣሪ ነኝ በሚል ስሜት ጣልቃ ተገብቶ የተነገረ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ምክትል ሚንስትር ንግግርን አጥብቀው በተቃወሙና እዛው ላይም እንዲታረም በጠየቁ ነበር፡፡ ሰውየው ግን ከዚህ ይልቅ ልባቸው ከበሮ እየደለቀ ነበር በደስታ የፈነጠዙት፡፡ የሞግዚት አሥተዳደር ቡችላ አሻንጉሊት ሉዓላዊነትን የት ያውቅና!፡፡ አሜሪካኖች “ሌላ ቀን መጥቶ ይሄ ቀን ያልፍና ያስተዛዝበናል ያ ቀን እንደገና” የሚለውን ተረት አያውቁትም ይሆን? አደራ እንዳትረሱብን በሉልኝ እባካቹህ ቅርብ የሆናቹህ ወገኖች፡፡
ትናንት ሚያዝያ 15 2007ዓ.ም. የአውሮፓ ሕብረት ሀገራት መሪዎች ከአፍሪካ የሚገቡ ስደተኞችን በተመለከተ ያደረጉትን አስቸኳይ ስብሰባ ውሳኔዎችን በማሳለፍ አጠናቀዋል፡፡ በውሳኔዎቻቸው ይሄንን ስደት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተደረገ የነበረውን ጥረት በሦስት እጥፍ በማሳደግ አዘዋዋሪዎችንና ደላሎችን ለመቆጣጠር፣ ጀልባዎችን ስደተኞችን ከመጫናቸው በፊት በሄሊኮፕተር በታገዘ ወታደራዊ ኃይል ለመደምሰስ የውሳኔ ሐሳቦችን በማሳለፍ ተስማምተው ተበትነዋል፡፡ የሠለጠነው ዓለም መሪዎች ሆይ! በቃ ይህችን ታክል ነው ማሰብ የምትችሉት? ውሳኔዎቻቹህ እጅግ አሳፋሪና ዘመኑን የማይመጥን ያለውንም ችግር ለመፍታት የማይበቃ ደካማ ውሳኔ ነው፡፡ በቃ ይሄው ነው መፍትሔው? ይሄ ላለው ችግር ዘላቂ መፍትሔን ያመጣል? በችግሩ መንስኤ ላይ ማተኮር አይሻልም? ይሄንን ለማሰብ ለምንድነው የማትፈልጉት? ለእኛ ከቀያችን እየተፈናቀልን መሰደድ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የእናንተ እጅ ስላለበትና የሞራል ብቃትና ወኔ ስላጣቹህ ነው? ስለዚህም ተገደን ከቀያችን ከሀገራችን ተፈናቅለን በገፍ ወደ ሀገሮቻቹህ በምንሰደድበት ጊዜ “ሕገ ወጥ ስደተኞች” እያላቹህ እኛን የማሸማቀቅ የሞራል (የቅስም) እና የፖለቲካ መብትና ብቃት የላቹህም፡፡ ስደተኛውን ከቀየው ከገዛ ሀገሩ እየተፈናቀለ ሳይወድ እንዲሰደድ በሚያደርገው ችግርና መፍትሔው ላይ አተኩራቹህ ሳትሠሩ ስደተኛ ይቁም፣ ደላላና አዘዋዋሪ ይጥፋ፣ ጀልባዎች ይደምሰሱ ብትሉ ወደ አውሮፓ የሚሻገሩ የኢትዮጵያን (ኤርትራን ጨምሮ) ስደተኞችን ይሄንን መስመር ጨርሶ እንዳያስቡ ለማድረግ ሰሞኑን በ30 ወንድሞቻችን መታረድና መረሸን ጀርባ የእናንተ እጅ ቢኖርበትምና በቀጣይም ተጨማሪ ሌላ ተመሳሳይ ግፍ ቢፈጸምም እንኳ ስደተኛ ይቆማል ብላቹህ ከቶውንም እንዳታስቡ፡፡
እባካቹህ! እናንት የምዕራባዊያን ምንግሥታት መሪዎች ሆይ! እባካቹህ? መንግሥቶቻቹህን በየግል ብልሹ ሰብእናዎቻቹህ መስመር እንዲጓዙ እንዲቃኙ አታድርጓቸው? መንግሥት የሚባለው ተቋም እኮ ልክ እንደ ሃይማኖት ተቋም ሁሉ ለሰብአዊነት፣ ለእውነት፣ ለፍትሕ፣ ለትክክለኛነት፣ ለእኩልነት፣ ለሞራል(ለቅስም) ድንጋጌዎች ከልብ የመገዛት ግዴታ ያለበት ተቋም እኮ ነው፡፡ ግፈኛ፣ ሸረኛ፣ ቁማርተኛ፣ ሐሰተኛ ሊሆን እኮ አይገባም! እንዲህ ዓይነት ደካማ የየግል ሰብእናቹህን ሳትጥሉና የመንግሥት ባለሥልጣን ሊይዘው የሚገባውን ምስጉን ሰብእና ሳትላበሱ ወደ መንግሥቶቻቹህ እየገባቹህ በምትሠሯቸው እኩይ ኢሰብአዊና ግፈኛ ተግባሮቻቹህ እኮ እኛ ተቸገርን፣ ተሰቃየን፣ ፍዳችንን በላን ኧረ እባካቹህ ስለፈጠራቹህ! ስለ ጉልበታቹህ አምላክ ብላቹህ እዘኑልን? ተውን? መንግሥቶቻቹህ ባላቸው ታማኝነት፣ ቅንነት፣ እውነተኛነት፣ ሀቀኝነት እንደ ሃይማት ተቋም ሁሉ የሚከበሩ፣ የሚታፈሩ፣ የሚፈሩ፣ የሚፈቀሩ መሆን እኮ ነበረባቸው! አለዛማ የወንበዴ ቡድን እንጅ ምኑን መንግሥት ሆናቹህት? በእውነት የሚያፍርና የሚሰማው ሰብእና ካላቹህ ልታፍሩ እኮ ይገባል፡፡ መንግሥቶቻቹህ በምስጉት ሰብእና የተገነባ ቢሆን ኖሮ እኮ ዓለም ፍጹም ሰላማዊ በሆነች ነበር፡፡ አንደኛው ሁለተኛው አሁን ደግሞ በምታደርጉት እኩይ ሴራ በየሀገሩ የተደረጉትና የሚደረጉትም ጦርነቶች እልቂቶች ባልተፈጠሩ ነበር፣ ሰው ከቀየው እየተፈናቀለ ባልተሰደደ ነበር፣ እናንተም በስደተኛ ባልተቸገራቹህ ነበር፡፡ “ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳል” ነውና የሚለው ቃሉ የዘራቹህትን ነው የምታጭዱት፡፡ የፈሰሰውና የሚፈሰው ደማችን እንዲሁ በከንቱ የሚቀር ይመስላቹሀል? በኃያሉ አምላክ ፊት ይፋረዳቹሀል! እናንተ ታርማቹህ ሰላም እንድንሆን ለማድረግ ባትፈቅዱም እረፍትና መዳን ለእኛ ከሌላ ስፍራ ይሆንልናል እናንተና የአባቶቻቹህ ቤት ግን ትጠፋላቹህ!!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለለም ትኑር!!!

No comments:

Post a Comment