Thursday, April 30, 2015

“ልጄ! እንካንተ እኔም ባልተወልድኩ”

…. ስሙን ሞት ይጥራውና እንኳን በአንደበቴ በህሊናዬ ሲንከላወስ እጅጉን የሚኰሰኩሰኝ ያ! መናጢ፤አናጢ፤ ግምበኛ፤አትክልተኛ ነኝ’ ባይ ‘መጤ’ ‘የቀን ሠራተኛ’ ለካስ ዋናው ሙያው ‘የጨለማ ሠራተኛ’ ኖሮ ወያኔዎች ኢትዮጵያን ወረው
መዲናንችንን ሲቆርጣጠሩ ይኸ ‘እንግዳ ሰው’ ከምንጊዜው እንደ እስስት ተቀያይሮ፤ የቀን ቱታውን አውልቆ፤ዪኒፎርሙን ጠርንቆ፤መትረየሱን ታጥቆ ሰፈራችንን ፊታውራሪ ሆኖ ሲያምሰን፤ ሲያተራምሰን ከረመ። አይ እኛ! ምንኛ ተላላዎች፤ሰው አማኞች፤ የዋሆችም ኖረናል።
ይባስ ብሎ ለሥራ ክብር ባላቸው የተከበሩ ጎረቤቶቻችንና የሰፈራችን አረጋዊያን፤ አባ ምንተስኖትና እማማ ገላኒ በትልቁ ግቢያቸው አስጠግተው እንዳቅሙ መጠነኛ ክፍል አከራይተው ቡናና፤ጠላ አብረው እየጠጡ፤ወሬ እየለጠጡ፤ዓመት ባል፤አውዳ ዓመት እንደ ዘመድ፤እንደ ሃገር ሰው የተገኘውን ሁሉ እኩል ተካፍለው፤ አክብረው ቢያኖሩት ‘ባለቀን’ ሆነና ለውለታቸው ምላሽ ግቢያቸውን በሙሉ ወርሶ እነርሱን ከከተማ ዳርቻ አልባሌ ቦታ ቀበሌ ቤት ጣላቸው።
በዘመኑ ሰዎች ቋንቋ አፍ መፍታቱን ሲያስረግጠን ከጆሯችን አልፎ በአናታችን የገደል ማሚቶ እስኪያስተጋባ ያምቧርቅብን ጀመር።
ምን ዓይነቱ የበላበትን ወጪት ሰባሪ!፤ ያጎረሰውን እጅ ነካሽ! ተብሎ በሃሜት ተብጠለጠለ፤ጉድም ተባለ፤ በዚህም አድራጐቱ የሰፈራችን ሕዝብ እርግማን፤ሃዘንና የሚሳለሟት የጨርቆስ አድባር (ቆሌ) ‘ምልጃ’ ተነባብሮ መቅስፍት ሆኖት አንድ ዓመት አይደፍንም ሲባል እርሱ ግን ጭራሹን እየፋፋ፤እየስፋ የዝቋላን ተራራ አክሎ፤አሥራ አሥር ዓመት አስቆጠረ። የሰፈራችን ሰው ግን በተገላቢጦሽ እርግማኑ እኛ ላይ ‘ያረፈ’ ይመስላል፤ ካመት ዓመት እየከሳን፤እየጠቆርን፤በሽታ እየሰረቅን፤ እየደቀቅን፤ ቀንና ሌሌት፤ከረምትና በጋ፤ሃያ አራት ዓመት ተፈራረቁብን።
ልጄ ፋኑዔል! የዚህን ግፈኛ ሰውና የዘመኑ ሰዎች በደል አንገብግቦህ ለተሰደድከው ስንቱን ልተርክልህ! ካፌ ይውጣ ብየ እንጂ ‘ለቀባሪው ማርዳት’ ነው። ይኸው ዛሬ ሰፈራችን ጭር ብላለች:: ስንቱን ኮረዳ፤ጎረምሳ አዋክበው፤በየሰበቡ እየገረፉ፤እያሰሩ፤እየገደሉም አገሩን እንዲጠላ፤አድርገው፤ባገሬ እንዲህ ከምዋረድ፤የሰው አገር አሞራ፤አፈር፤ምስጥም ይብላኝ ብሎ የተሰደደው ቁጥር ስፍር የለውም:: ብዙ ስደተኛች የውቅያኖስ ላይ አደጋ፤የዱር አውሬ ቀለብ መሆናቸውን፤ በበረሃው ሃሩር ዝለው በባድ አገር አሸዋ ላይ አፈር ሳይለብሱ መቀረታቸውን እንዳይሰማ የለም እንሰስማለን። የሰው አገር ሰዎችም ብዙ ጭካኔ የጣለባቸው፤ለነፍስ፤ለስጋ ክብር የሌላቸው ሰው እንደ ደሮ በቁሙ አስራ ሁለት እየበለቱ ኩላሊት፤ጉበት፤አንጀቱን ሁሉ ይሸቁጡበታል አሉ:: መርዶ በየቀኑ ይደርሰናል፤ሠፈራችን የሃዘን ድንኳን ሆና ከርማለች; አሁን ግን ማልቀስም፤ ድንኳን መትከልም አይትችሉም ተብለናል። መጪውን ማን ያውቃል! ያ ‘የእርነሱ ከይሴ’ የሞተ ጊዜ ሁለት ሳምንት አገር ሕዝብ ማቅ አልብሰው፤ሥራ አስፈትተው እምባ አምጣችሁ ታለቡ ተባልን። ልጄ አልዋሽህም አንድም ዘለላ ጠብ አላረኩም፤ ስንት እሚለቅስለት እያለ። ግና አሁንም የሚገለን፤የሚያስረን፤የሚያስድደን፤አልጠፋም። ቀን አግኝተን፤ቀን ሰጠናቸው ብዬም እፀፀታለሁ።
ይኸውልህ እድሜ ዘልዛላው እዚህ ዘመን ላይ አድርሶኛል። ያንተን ክፉ እንዳያሰማኝ፤ ሞቴን ብማጸንም አምላኬ እስካሁን አልሰማኝምና ከቆየሁ አይቀር ደግሞ ደጉን ያሰማኝ ዘንድ፤ ‘የማይቻለውን ሁሉ ችዬ’ እድሜየንና አበሳዬን እቆጥራለሁ።
ይኸ ሰብበኛ በጨለማ የነገሰ ‘የቀን ሰው’ ‘ወዲ ሃብቶም’’ እንደ ወፍጮ ቤት ላምባ ጢስ የሚተፋ ባለሸራ መኪናውን ካልጠፋ ቦታ ትንሿ ቤታችን መዳረሻ መዳፍ በማትሞላ ቅንጣት በረንዳችን፤ በእናትህ ስጦ ማስጫና፤ በአባትህ ጸሃይ መሞቂያ ላይ አራጦ ይበግርብናል:: ይባስ ብሎም ከመሸታ ቤት የቃረመውን መኪናውን ተገን አድርጐ ይሸናብን ጀመር፤ለዚህ ሰውና ለመሰሉ ሁሉ የንቀታቸው፤የብልግናቸው መጨርሻ የለውም። ክርፋቱ እያስመረረን በራችንን መክፈት እንሳቀቅ ነበር።
ታዲያ ይኸ ሁሉ ግፍ ላንድ ደካማ ጡረተኛ እጅግ ካቅም በላይ ነበር፤ቀበሌ ተመላልሸ እዚያም ያሉት አብዛኛዎቹ ‘ጠጉር ልውጥና’ ‘የዚሁ ሰውየ ቢጤዎች’ ናቸው ተስፋ መቁረጥን ተስፋ አድርጌ በሬን፤አፌንም ዘግቸ ከረምኩ።
አንተ ገና ላቅመ አዳም ያልበቃህ ወንዱ ልጄ የተበገረውን መኪና ተደግፎ ቆመክ፤ አለዚያም ጎማ አስተነፈስ ብሎ ‘ሆድ እቃውን አስተነፍሳለሁ’ እያለ ሲያሳድድህ ዋለ አደረም፤በመጨረሻም ክፉ ቂመኛ ሰው ነበርና ደመ ከልብ እንዳትሆን ብለን በዘመድ ጓደኛ ጉትጓቶ ወደ ሌላ ሰፈር ተሸሽገህ ባጀህ። እግዚአብሄር ወሽመጡን ይቁረጥለትና ሽንጡን ቀስሮ ጠዋትና ማታም የኛን በር መጸዳጃ አድርጎት አረፈ። ምን ይደረግ ልጄ! ቀን የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራልና!
ከብዙ ጊዜም በኋላ አቅም፤መላ፤ደራሽ፤ወገን፤ፍትህ፤መንግሥት ብናጣ የሚሻለው ስደት ነው ተብሎ አንዱ ልጄ ኃይዎትህን ታተርፍ ዘንድ ወደ ባዕድ አገር ተሰደድክ፤ እንደወጣህም ቀረህ፤ እኔም አልሸኘውህ፤ እስኪ ለቀነኞች ምድር ትስፋቸው። አቅጣጫህ ወደ ጸሃይ መውጫ ነው ስላሉኝ፤ ነጋ ጠባ ጀምበርን ልጄን አላየሽም ወይ ብየ እጠይቃታለሁ፡ አንጋጥጨ፤አይኔን በጭንቅ ጨፍግጌ፤ቅንድቤን ባራቱ ጣጦቸ ከልዬ:: ይሁንና ሳልፈልግ የምስማው የዚህኑ ምቀኛ የጥጋብ ዳናና ፤ግሳት፤ከበሮ፤ የመኪና ሩምታ ነው። አንተ ግና ድምጽህም፤ጠረንህም የትየለሌ ያህል ራቀብኝ።
እኔም ቤቴን ዘግቸ አምላኬን በቁጣና በጸሎት ግራ ሳላጋባው አልቀረሁም። አንዴ ሞቴን እንዲያቀርብልኝ፤ ሌላ ጊዜ እድሜየን እንዲያረዝምልኝ ሰማጸነውና ሳጣውረው። ሞቴን የምመኘው፤ መደፈሬን፤መዋረዴን፤ሃፍረቴን፤ለማሳጠር ሲሆን እድሜዬን እንዲያራዝምልኝ የምሻው ደግሞ የነዚህን ክፍ ሰዎችና ዘመን የመጨረሻ ፍጻሜ ለአድንድ ሰዓት አንድኳ ኖሬ፤መስክሬ ብሞት ነፍሴ ጽድቅን በምድር እንዳገኘች ስለምቆጥረው ነው።
አሁን ግን ሁሉ ነገር በዝቷል፤ከልክ አልፏል፤ ካምላክ አቅም በላይም ሳይሆን አልቀረም፤ የግፉ የመከራ ዳራቻ የለውምና ምንም ነገር መጠይቅ አቁሚያለሁ፤ደንዝዣለሁም ልበል? ሲያንገሸግሸኝ የምጠይቀው፤ ሰጣ-ገባ የምሞግተው እራሴን ነው፡ ሁነኛ የሚባል ሰው እንደ ልብ አይገኛም አልፎ አልፎ እግር የጣለውን ሁሉ ብማጸንም የልብ የሚያደርስ የለም።
የአክስትህ ልጅ ማንደፍሮ ከወዲያኛው ሰፈር ደብዳቤህን በጓደኞችህ ቤተሰቦች በኩል ደርሶ ሊያነብልኝ መጣ በአንድ አጋጣሚ ከመጣ ወዲህ ተመላልሶ ይጠይቀኛል፤ ሳላሳዝነው አልቀረሁም መሰል፡፤ ምርቃቴንም ወዶታል፤ ‘ሳልወድ የምሰራውን ሃጢያት ይቀንስልኝ ይሆናል’ ይለኛልም፤ ንስሃውን ግን ግልጦ ነግሮኝ አያውቅም።
ልጄ እንደበፊቱ ምርኩዜን ተደግፌ እስከ በር ብወጣ የመኪና ጎማ ስይሆን ሌላ ነገር ነበር ማስተንፈስ የምፈልገው! ግና ቁጭቴ እኔንው እንደ ቅንቀን እየበላ እንቅልፍ እየነሳ፤በችግር፤በሃሳብ እያከሳ የራሴን ገላ ይቀጣና ያኮስስ ጀመር። የቀኑ ስዎች ግን ድንች እንደ ተጫነበት ኩንታል እየሰፉ፤እየገዘፉ ናቸው።
የጐንቻው!
እኒህ የዘመኑ ጠብደሎች እንዲህ መሆኔንና፤መሆናችንን ገምተውን! እልክ እንኳ አይገባቸውም፡ጭራሽ ንቀታቸው እንደ ቁርጥማት፤ ሁለመናየን ይጠዘጥዘኝ፤ እንደ ራስ ምታት፤ ይፈነክተኝ ጀመር። አለዚያማ የጸሃይ መሞቂያየን፤ የስጦ ማስጫችንን ተነጥቄ በረንዳዬ መሽኛ ሆኖ፤ በአገሬ ባዳ ሆኘ፤ልጄን አሰድጄ ጉርምስናዬን፤ ጀብዱየን፤ ጀግንነቴን በህልሜም በእውኔም ወደ ኋላ አዝግሜ እመኛለሁ፤ ባንድ ጎኔ ደቃቃ አልጋዬ (ቃሬዛዬ) ላይ ተጋድሜ እያቃሰትኩ።
እናትህም የአንተ ናፍቆትና ትዝታ ህመምና ሰቀቀን ሆኖባት ብስጭት እንቅልፍ ነስቷት፤ አንድ ዓመት የአልጋ ቁራኛ ሆና ቆይታ ተገላገለች፤በቅርቡ የጻፍከው ድብዳቤ ደርሶ የአክስትህ ልጅ ‘ማንደፍሮ’ ተጠርቶ አነበበልኝ። ያንተንም ሃዘን፤ብስጭት፤ ሰማሁ፤እጅግ አዝኛለሁ አሁንም ግን በመንገድ ነህ አሉ ልጄ! ለመሆኑ ስደት ምን ያህል ይርቃል?
ልጄ ስንቱን አገር በርሃ ቋንጅተህ፤ውሃ ቀዝፈህ ከገራችን ሰማይ መራቅህን ሳስብ ለሃዘኔ ወሰን የለውም፡ እናትህ ከማለፏ በፊት ጥፋቱ የኛ ነው ብላ እራሷን ስትወቅስ ቆየች፤ ቤታችንን፤ ሰፈራችንን ለቀን ብንሄድ ኖሮ ስደት አይሄድም ነበር ብላ ነው።፡የእርሷ ነገር የእኒህ የቀነኞች ግዛት እስከ አገር ቂጥ መሆኑን ባይገባት እኰ ነው ። እኔም እስካሁን በጣር አለሁ:: ተስፍዬ አንተ ነህና የፈቀድቅበት፤ያቀድክበት ቦታ መድረስህን ሰምቸ እፎይ ብዬ ዳግም ሃሳብ ላላነሳ ላልጥል በደስታ ባሸለብኩ፤ ወደ ማይቀርበት መንገዴ። ግና ሳስበው ሦስት ዓመት ተመንፈቅ ማለት ለካ እንዲህ ረጀም እድሜ ነው፤ አንተን ያንቃቃሁበት እድሜ ከእኔም ሰባ ዘጠኝ ዓመት እንዲህ ረዝሞ ይሰማኛል። ታድያ አሁንም አረብ አገር እስር ቤት ነህ ይሉኛል:: እኛ የምንታሰርበት እስር ቤት ስፋቱን ሳስበው በቅዠት ዳር አገር ድረስ እስኪሰማ እቀባጥራለሁ፡ ጎረቤቱ አብዷል ሳይሉኝ አይቀሩም፤ ካበድኩ ቆይቻለሁ። በማበዴ አክስትህ ልጇ ‘ማንደፍሮ’ በሳምንት ሁለትና ሥስት ጊዜ አምስትና አስር ደቂቃዎች ብቅ ብሎ ይጠይቀኛል፡ ይኸም ብርቅ ሆኖብኝ ሰዓቱን ሲያሳልፍ ወይም አልፎ አልፎ ሲቀር ይከፋኛል።
ማንደፍሮ ድሮም ‘ግብቡ’ ነው አሁን ደግሞ ብሶበታል፤ እየቀርብኩት ስመጣ ከውጭ ወሬ እጠይቀዋለሁ፤ብዙ፤ብዙ ሚስጥር ነገርም አያካፈለኝ ሌላ ሰው አገኝ ይመስል አደራ ትንፍሽ እንዳትል ብሎ ሹክ ይለኛል። እርሱ በሹከታ ሲያወራ እኔን ሳል ይይዘኛል። እኔም የሆዴን አጫውተው ገባሁ።
አንድ አሳቻ ቀን ሞቅ ብሎት መጣና ወኔም የተላበሰ ይመስላል፤እንደ ድሮው በሹክሹክታ ሳይሆን አንደበቱን ፈካ ዘለግ አድርጐ እንዲያ የደላው የተደላደለው የመሰለኝ ሰውዬ የሆድ ብሶቱን ዘረገፈልኝ። የቀን ውሎው ግን አስመስሎ ለመኖር የሚያደርገው እንጂ ፍጹም ደስተኛ እንዳልሆነ አረዳኝ፤ጭራሽ በአንተም መሰደድ ቁጭት እንዳለው ገለጸልኝ። እኔም እንዴት ነው ይኸ ሰው ባለራዕዩ የሚሏቸው ‘አስገዝተው ያጠመቁት’ መስሎኝ ነበር ‘ያባይ ቦንድ’ አንድ ላምስት እያለ የቀበሌያችንን ቆሌ ሲያደነቁር ስሰማው ስለኖርኩ።
ታዲያ በዚያችው ምሽት ደፍሬ ሰማህ ማንደፈሮ እውነትም እንደ ስምህ በምግባርህም ድፍረቱን ይስጥህና ‘ጐማ ሳይሆን’ የዚያን ክፉ ሰው ፊኛ ና ትቢት አስተንፍስልኝ ለውለታህ ይህችን ቤቴን ላንተና ለልጄ እኩል የውርስ ኑዛዜ እጽፋለሁ አልኩት። እርሱም ሳያመነታ ተስማምቶ ፎክሮም ወጣ በቅጡ ደሃና እደር እንኳ ሳይለኝ። እኔ ደግሞ ፍትህ እርትህ ያየሁ ያህል ያንን ሌሊት የደስታ ሲቃ በሁለንተናዬ ሲያንዘፈዝፈኝ አደረ።
ያንን ሌሌት ደሜ በደም ስሬ በፍጥነት ሲራወጥ፤ ልቤ አለወትሮዋ እየተነሳች ስትፈጠረቅ፤ትንፋሼ አቀበት እንደምወጣ ሲያጥጠኝ አደረ። እንዳይነጋ የለም ነጋ፤ ማልጄ ማንደፍሮን ጠበቅሁት እርሱም በኩራት ጀብዱውን እስኪነግረኝ ቸኩሎ ከበር እየገፈተረኝ፤ እየደገፈኝም ወደ ጓዳ አመራን ዛሬ ግን ትናንታና ያዩሁበት ድፍረት የለም፤ እንደ ድሮው ያንሾካሹክ ጀመር፤ ቢሆንም አንዳች ገድል እንደሰራ ነው የሚተርክልኝ። ነገሩ ትንሽ ባዳ ቢሆንብኝም፤ የዘመኑ የውጊያ ስልት፤ እያለ ከታንክ እያስበለጠ፤ድምጽ አልባ ‘የጦር ቀጠና ላይ’፤ ጠጠር ጠብ ሳይል፤ አንዳች ድምጽ/ኮቴ ሳይሰማ፤ በኮምፒውተር ገብቸ ጉድ አድረጉት ነው እኰ የሚለኝ። የታተመ እጥፍጣፊ ወረቀት ከግልገል ሱሪው አውጥቶ እየዘረጋጋ እያመላከተም ሲተርክልኝ፤ ማይጨው፤ዶጋሌ፤አምባለጌ በመንፈሴ እየተሳሉ የጦር ውሎ ውጊያ በምናቤ እያስቃኘኝ ፍከራ ባይከጅለኝም አፌን ደም-ደም እያለው መንቀጥቀጥም ከጀለኝ፡ ይኸ መናጢ እርጅና አላሰናዝር ቢለኝ።
ታዲያ የነገሩን ጭብጥ ለመረዳት ህሊናዬና አቅሌ ነቅቶ ቢያዳምጥም በማንደፍሮ ታሪክ ውስጥ ‘አንዳች ኮሽ’ የሚል ነገር አልሰማ አለኝ፤ ቢሆንም መጨረሻውን ለማዬት እየጓጓሁ እህ! እለው ጀመር። እንዲህም እያለ ለኔ እንዲገባ ቃል እየመረጠ ተረተልኝ። በያዘው ወረቀት ላይ የዚያ ክፉ ሰው ምስል (ፎቶ) በቁም ተገማሽሯል፤ ሆድ እቃው ላይ ጦር (ቀስት) ተነጣጥሮበታል፡ በግርጌውና በዙሪያው በቀለም የተንቆጠቆጠ ጥፈሽ አጅቦታል። እያቃስትኩ የሰውየውን ምስል በአውራጣቴ ድፍጥጥ፤በሌባ ጣቴ አይኑን ጥንቁል እያደረግሁ፤በጋዜጣ ወጥቶ ነው?፤አድራጊው ታውቋል? እያልኩ መልሱን ሳልጠባበቅ ደጋግሜ ጠየቅሁት። መልሱ ግን ይበልጥ ግራ አጋባኝ። አይ አባባ ነገሩ እንደሚሉት አይደለምም አለኝ።
ትናንት ማታ ከዚህ እንደ ወጣሁ አንድ ስውር ‘ኢንተርኔት ቤት(ኮምፒውተር ከፍቸ መሰሎቸ ከሸፈቱበት ጫክ (ደን) ተቀላቅዬ ገጠገጥኩበት! ቢለኝም፤ ባሩድ፤ባሩድ አልሸት አለኝ። ቢሆንም እያከታተለ፤ ይኸው ይህ ታሪክና ፎቶ ግራፉ ዓለምን አዳርሶታል አለኝ። ዓይነቱ ስወዬ ግን ከነግሳንግስ መኪናው ከበሬና ከጎረቤታችን ፈቀቅ አላላም። አሁን በእውን ማርጀቴን አውቅሁት። ምን ይታዎቃል እንዳፉ ያርግልንና ማንደፍሮ የሚለው መጣጣፍ እንደ ደብተራ ድግምት ሰውን ከነጤንሳው አኑሮ ‘ፊኛውን፤አሞቱን፤ትቢቱን’ ያፍስ እንደሁ እስኪ መሽቶ እስኪነጋ እጠብቃለሁ።
ማንደፍሮ ግን እንዲህ አድርጐ ድል ያደረገውን መናጢ ሰው ጥላ እንኳ ፈርቶ ከቤት ሲወጣ እንዳይታይ እንደኔው ቤት ተዘግቶበት ሲንቆራጠጥ ውሎ ከ እኩለ ቀን በኋላ መኪናዋ ከሄደች ግማሽ ሰዓት ቆይቶ ተፈትልኮ ወጣ።
የነገረኝን ሁሉ መላልሸ ባስበው እንደ ጉም አልጨበጥህ አለኝ እንደገናም ሌላ ሃሳብ ማውጠንጠን ጀመርኩ፤ አለዚያማ ቀኑ እንዴት ውሎ ይመሻል፡ እንግዲህ ልጄ ያለህኝ፡የመጨረሻ ተስፋየ አንተ ብቻ ነህ።
እነሆ ማንደፍሮ ካየሁት ሦስት ቀን አለፈ በነገረኝ ጀብዱ፤ በነፈስ አጥፊነት ወይም ነፍስ ሊያጠፋ ህልም ካዬ ጋር ሻይ አብሮ በመጠጣት በሚለው የዘመኑ ‘ሽብርተኛ’ አዋጅ ‘እድሜ ልክ’ ተፈርዶበት ይሆን ብዬ ስጋት ገባኝ። መቸስ የቀኑ ሰወች ሰበብ ፍለጋ እንደ አህያና ጅቧ ሳታመካኝ ብላኝ አይነት የወንዙ ዳርቻ ገጠመኝ ዓይነት አይደለ።
ይባስ ብሎ ሰሞኑን በሰፈራችን አለውትሮው ለቅሶ በርክቷል፤ የብዙ የሰው ድምጽ ኡ ኡ ታ!፤ምሬት የተቀላቀለበት ጩኸት ከርቀት በያደባባዪ እሰማለሁ፤ ለኔ ግን ማንም መቶ የነገረኝ የለም፤ በመንፈሴም በህልሜም ፍራት፤ፍራት ይለኛል፤ አንዳች ድንጋጤ በውስጤ ይሰማኛል፤ እንዲያው በደህናህ ትሆን ልጄ? እንደዚህ በአይኔ ላይ ውል ብለህብኝ አታውቅም፤ ደግሞም ክፉ፤ክፉውን የጭንቀት ልቦናየ ሹክ እያለ ሆደ ባሻ አድርጐኛል፤ እምባየም ሳላስበው በጉንጮቸ ይወርዳል፤ ኧረ ለመሆኑ ያለፍክበት፤ያለህበት አገር፤ ሊቢያ፤የመን ደቡብ አፍሪቃ ከጦቢያ ስንት ጀምበር ይርቃል? እንዲህ ሄደህ፤ሄድህ፤ እስካሁንም አልደርስ ያልክ?! … ልጄ አሁንስ እንኳን አንተ፤ እኔም ባልተወለድኩ አልኩ! ___________ //___________
ዓረመኔው የወያኔ ኃርነት ትግራይ ቡድን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለው ጥላቻና የፈጸመው ግፍ፤ወንጀል ከአይሲስ አሸባሪ ቡድን አሥር እጅ ይበልጣል። አይሲስ ለዓለም አቀፍ የውንብድና ፕሮፓጋንዳው ሲል በእጁ የወደቁትን ‘ሰላሳ’ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችንን በአረመኔያዊ ጭካኔ ገድሏል። አረመኔው የወያኔ ‘መንግስታዊ አሸባሪ’ ደግሞ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ካገተበት ሃያ አራት ዓመት ጀምሮ፤ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን በግፉ ገድሏል፤አስሯል፤አሰድዷል ወደፊቱም ከዚህ በባሰ ይቀጥላል እድሜውን ባንድ ላይ ተነስተን ካላሳጠርነው በስተቀር።
ወገን! የጠላትህን፤የወያኔን ፍጹም አረመኒያዊ ልክ ጠንቅቀህ እወቅ! በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ኒዪክለር ቦምብ እስከ ማፈንዳት የማይመለስ ዓለም ያላወቀበት የአይሲስ የመጨረሻው ደረጃ ነው። አጋጣሚ ስታገኝ አትማረው! አንድ ሁን! ድል የሕዝብ ነው!!!
የጐንቻው! 22/04/15

No comments:

Post a Comment