Monday, April 27, 2015

የታሰርኩ ለታ ‹‹ለሁለት አመት ያላየሁትን ጓደኛዬን ላገኘው ቀጠሮ ነበረኝ›› በፍቃዱ ኃይሉ

እኔ እና አጥኔክስ 10፡45 አካባቢ ከቀነኒሳ ሆቴል እየወጣን ነበር፣ ያን ቀን አብረን ነው የዋልነው፡፡ መንገድ ላይ እንዳለን ስልክ ተደውሎ ማሂ በፖሊሶች መያዟን ሰማን፡፡ ወዲያው የማሂን መያዝ በተመለከተ ቲዊት ላደርግ ስልኬን ስነካካ የማላውቃቸው ሰዎች ሁለታችንንም ከበቡን፤ ስልካችንና ላፕቶፓችንንም ነጠቁን፡፡ ምንም አይነት የተለየ እንቅስቃሴ አላደረግንም፡፡ ዙሪያ ገባየን ሳይ ሰው የተለመደ እንቅስቃሴውን ቀጥሏል፡፡
(ጋዜጠኛ በፈቃዱ ኃይሉ)
(ጋዜጠኛ በፈቃዱ ኃይሉ)

የሚገርመው ለሁለት አመታት ያህል አግኝቼው የማላውቀው ጓደኛዬ ጋር ቀጠሮ ስለነበረኝ ወደዚያ እየሄድኩ ነበር፡፡ ከጓደኛየ ጋር ብዙ ጊዜ ለመገናኘት ፈልገን አልመችህ ሲለን ረጅም ጊዜ ሳንገናኝ ቆየን፡፡ በዛ ዕለትም ሳላገኘው ወደእስር ተጋዝኩኝ፡፡ የነጠቁኝ ስልክ በተደጋጋሚ ሲደወል እና መልዕክት ሲገባ ይሰማኛል፡፡ የቀጠርኩት ጓደኛየ ይሆናል እያልኩ አስባለሁ፡፡


ሰዎቹ እኔን እና አጥኔክስን መኪና ውስጥ አስገብተው ወደ ቦሌ መድሃኒያለም ወሰዱን፡፡ ከዚያም ሌላ መኪና መጣችና አጥኔክስን ከእኔ ለይተው ወደሌላኛዋ መኪና ወሰዱት፡፡ አጥኔክስ ጋር ሲለያዩን አይዞን፣ አይዞን ተባብለን ተለያየን፡፡ ከዚያ እኔን የያዘችው መኪና ወደ እኔ ቤት ይዛኝ ከነፈች፡፡ የቤት ብርበራ ሊደረግ መሆኑ ገባኝ፡፡
ቤት ደርሰን የእኔን ክፍል እያንዳንዷን ነገር መፈተሽ ጀመሩ፡፡ አንደኛው በተለያየ ጊዜ የጻፍኳቸውን ጽሑፎች እያነበበ አየዋለሁ፡፡ ፍተሻው ቀጠለ፡፡ የሚፈትሹት ሰዎች ቀስ በቀስ እየወደዱኝ እንደሆነ ገባኝ፡፡ ማነጋገር ጀምረዋል፡፡ ቤቴ ውስጥ ያለኝ ብዙ ሀብት መጽሐፍ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ የቆዩ መጽሐፎችን ሳይቀር እያገላበጡ እያዩ የሚፈልጉትን ይይዛሉ፡፡ እኔ የጻፍኳቸውን ጽሑፎች እያገላበጡ ‹ለምን አታሳትማቸውም› ማለት ሁሉ የጀመሩ ነበሩ፡፡ የእውነት ሰዎቹ እየወደዱኝ ነበር (በሳቅ)፡፡ ፈታሾቹ ሳጥን ውስጥም መጽሐፍ፣ ካርቶን ውስጥም መጽሐፍ፣ ጠረጴዛ ላይም መጽሐፍ ሲያገኙ እየተገረሙ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ የእኔን ክፍል ፈትሸው ሲጨርሱ ዋናው ቤት ገቡ፡፡ እናቴም አባቴም ቤት ውስጥ ነበሩ፡፡ የዛን ሰሞን ሁኔታ ስላላማረኝ፣ ሊያስሩኝ እንደሚችሉና ቤቱም ሊፈተሽ እንደሚችል እነግራቸው ስለነበር ሳይዘጋጁ አልቀሩም፡፡ ቢሆንም ግን መደንገጣቸውና ፣ ማልቀሳቸው አልቀረም፡፡ ቤት ውስጥ ማየት የሚፈልጉትን እያዩ እያለ እራት እንድበላ አሳሰቡኝ፡፡ እራት ቀርቦልኝ እንዴት ይበላልኝ!
ፍተሻው አልቆ ከቤት ስወጣ ቤተሰቦቼን ለማረጋጋት ያህል ‹በጥርጣሬ ነው የያዙኝ፣ ሰኞ እወጣለሁ ይለቁኛል› አልኳቸው፡፡ ከዛም በመኪና ይዘውኝ ማዕከላዊ ወሰዱኝ፡፡ ማዕከላዊ እንደደረስኩ ሰውነቴ ድንዝዝ ሲል ይታወቀኛል፡፡ በቃ ራሴን የመጣል ስሜት ነበር የወረረኝ፡፡ ደሞ ድካሙ! ማዕከላዊ ተመዝግቤ ሌሎች እስረኞች ወዳሉበት ክፍል አስገቡኝ፡፡ በሩ ከኋላዬ ሲዘጋ ቀፈፈኝ፡፡ ወዲያው ውስጥ ያሉት እስረኞች ስለራሴ ጠየቁኝ፤ ነገርኳቸው፡፡ ሊያረጋጉኝ ሞከሩ፡፡

No comments:

Post a Comment