Wednesday, April 15, 2015

ህዝባዊ እምቢተኝነት ለነጻነት (የዲሲ የጋራ ግብረ ሃይል)

የዲሲ የጋራ ግብረ ሃይል
የኢትዮጵያ ህዝብ እሩብ ምእተ አመት በትከሻው ላይ የተሸከመው የባርነት ቀንበር እየተነቃነቀ ነው። እኛን ያስጨነቀን ደም ጠገቡ የወያኔ ስርዓት ወይስ ሃገራዊ ህላዌ ነው መንኮታኮት ያለበት? በኛ ልብ ውስጥ ከሚነደው የሃገር ፍቅር እሳት ብንነሳ መልሳችን የሚሆነው እየተነቃነቀ ያለው ስርዓቱ ነው ፤የሚንኮታኮተውም የስርዓቱ አራማጅ ህወሃት ነው የሚል መልስ እንሰጣለን። ይህ መልስ ግን ከቀቢጸ ተስፋ ወይም ከነጻነት ጥማት የመነጨ ምኞት ሳይሆን የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታን ተመርኩዘን በየአቅጣጫው ፈነዳሁ ፈነዳሁ የሚለውን ህዝባዊ አመጽ መነሻ በማድረግ ነው።

ባለፉት ፳፬ አመታት በተካሄዱ ፭ ሃገራዊ በሚባሉ ግን ወያኔያዊ በሆኑ ምርጫ ተብዬዎች የተከፈለውን መስዋዕትነት እንጂ የበቀለ የድል ፍሬ ሳናይ ዘመናት አስቆጠርን። ከተመክሮ እንዳየነው ምርጫ ዲሞክራሲን እንደማያመጣ ፤ ዲሞክራሲ እንጂ ፍትሐዊ ምርጫን የሚያመጣ ብለን ብንደመድም የተሳሳትን አይመስለንም፤ፍትሐዊ ምርጫ ይመጣ ዘንድ ወይም ድምጻችን አይሰረቅ በማለት በአካል፣በመንፈስ፣በቁስ፣በህይወት የተከፈሉትን መስዋዕትነት ብናደንቅም በምንም ተዓምር በወያኔ ከርሰ መቃብር ላይ ካልሆነ በስተቀር ፍትሐዊ ምርጫ ተካሄዶ ህዝብ ያሻውን የሚያወጣበት ሲሻው የሚያወርድበት ስርዓተ መንግስት ይቋቋማል ብለን በፍጹም የህወሃት ስርአት ግፍ እና በደል ከስሩ ካልተነቀለ በስተቀር አናምንም። ዛሬም ለ፭ኛ ግዜ ምርጫ እየተባለ በኢትዮጵያዊያን ላይ ለሚሰራውን ወንጀል አድማቂ በመሆን በተቃዋሚነት ያሉት ዋንኛውን ሚና የሚጫወቱ መሆናቸው መሰመር አለበት።
ያለፈውን ለጊዜው ብንዘለው እንኳን ዛሬ በወህኒ ቤት አስከፊ ሰቆቃ ውስጥ የሚገኙትን በርካታ የነጻነት ታጋዮችን ምርጫ ባልሆነ ምርጫ ውስጥ በመሳተፉ ስቃያቸውን አናባብስ፤ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት በኛ እምነት ከዚህ ካለቀለት ስርዓት ለመገላገል ከህዝባዊ እንቢተኝነት ሌላ አማራጭ አለ ብለን አናምንም ይህንንም የትግል ተመክሮ ለመቅሰም ብዙ ከህወሃት ጋር መጓዝ አያሻንም፤ ስለዚህ ተቃዋሚ ድርጅቶች ለውጥ ከማያስገኝ ምርጫ በተቻለ ፍጥነት እራሳችሁን በማግለል በህዝባዊ እንቢተኝነት የኢትዮጵያን ትንሳኤ ለማምጣት በሚደረገው ትግል በጋራ በመሆን ትግሉን እንድናጠናክር እናሳስባለን።
ከራሳችን ወገኖች የህዝባዊ እንቢተኝነትን መማር አለብን፤እየተካሄደ ባለው የነጻነት ትንቅንቅ ባሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እያደረጉ ያለው የእንቢተኝነት ትግል ለሃገራዊ የተቃዋሚ መሪዎችም ሆነ ለተቀረው የህብረተሰብ ክፍል ትምህርት ለጋሽነቱን አሌ ማለት አይቻልም እኛም ትግላቸውን ሳናደንቅ አናልፍም፤ ስለዚህ ምርጫችን የወያኔ ምርጫ ሳይሆን ህዝባዊ እንቢተኝነቱን አድርገን ግፍ የበዛበት ህዝብ ባንድ እንዲነሳ እውቀት እና ጉልበታችንን እዚያ ላይ ብናፈስ አይቀሬው ነጻነታችንን ያቀርበዋል። የሚደረገው ጸረ ህወሃት ትግል ይቀጥላል ለዚህም ተግባራዊነት የዋሽንግተን እና አካባቢው የጋራ ግብረሃይል መከፈል የሚገባውን ሁሉ ለመክፈል ዝግጁነታችንን እናረጋግጣለን።
ህብረት የድል ዋስትና ነው!!!
ከወያኔ ምርጫ ህዝባዊ ጡጫ!!!
ኢትዮጵያ በክብር እና በነጻነት ለዘላለም ትኑር!!!
የዲሲ የጋራ ግብረ ሃይል, dcjointtaskforce@gmail.com

No comments:

Post a Comment