Thursday, April 30, 2015

መንግስት በሰማያዊ ፖርቲ ላይ የከፈተውን የስም ማጥፋት ዘመቻ በአስቸኳይ ያቁም!!! – ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

ሰማያዊ ፓርቲ በየመን፣ ደቡብ አፍሪካና በሊቢያ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለውን በደል እየተከታተለ መንግስት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡ በእነዚህ ሀገራት ችግር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን በደል በማውገዝና መንግስትም መፍትሄ እንዲሰጥ መግለጫ ከማውጣት ባለፈ የደቡብ አፍሪካ መንግስት በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን በደል እንዲያስቆም አዲስ አበባ ለሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ደብዳቤ በመጻፍ ፓርቲያችን የቻለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተመሳሳይ መንግስት አይ ኤስ አይ ኤስ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን ዘግናኝ እርምጃ ለመቃወም የጠራውን ሰልፍም በመደገፍ ሰማያዊ ፓርቲ የመጀመሪያው ተቃዋሚ ፓርቲ ነው፡፡

ይሁንና የዜጎችን ስቃይ ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል የፈለገው ሕወሀት ኢህአዴግ ሰማያዊ ፓርቲ በወገኖቻችን ላይ ለሚደርሰው በደል መፍትሄ እንዲሰጥ መወትወቱ፣ የፖለቲካ ልዩነታችን ወደ ጎን አድርገን በሰልፉ ላይ መገኘታችን እንዳላስደሰተው ከሰልፉ ቀን ጀምሮ በፓርቲያችን ላይ የተከፈተው ዘመቻ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ መንግስት ሊቢያ ውስጥ በወገኖቻችን ላይ ለተፈፀመው ጭካኔ ምንም አይነት ትኩረት ባለመስጠቱ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ተቃውሞ በማሰማታቸው ያላሰበውን ሰልፍ ጠርቷል፡፡ በጠራው ሰልፍ ላይም መንግስት ለወገኖቻችን ያሳየው ንቀት ያበሳጫቸው ኢትዮጵያውያን ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡ በተቃውሞው ወቅት ከፍተኛ ድብደባ የፈፀመው ፖሊስ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኢህአዴግ አባላትን ጭምር ማሰሩ ይታወቃል፡፡ ይህ በሆነበት ወቅት ኢህአዴግ ለተነሳበት ቅሬታና ተቃውሞ ጣቱን ሰማያዊ ፓርቲ ላይ በመቀሰር ከፍተኛ ውንጀላና ዛቻ እያደረገ ይገኛል፡፡
ከሰልፉ ማብቃት ጀምሮም ጉዳዩን ገና ፖሊስ ሳይመረምረው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን ሰማያዊ ፓርቲ ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት እየጣረ ነው የሚል ውንጀላ አሰምቷል፡፡ ከዚህ ዕለት ጀምሮ የስርዓቱ አፍ በሆኑት ሚዲያዎች ሁሉ ቀን ከሌሊት ሰማያዊ ፓርቲ ሁከትና ብጥብጥ ሊያስነሳ ነው እያለ እያላዘነ ይገኛል፡፡ አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም ተብለው በተጠሩ ሰልፎችም ሁሉ ከአራጁ ቡድን ይልቅ ሰማያዊ ፓርቲ ለመቃወም እየተጠቀመባቸው ይገኛል፡፡
በሰልፉ ዕለት አባላቶቻችን ገና ሰልፉ ሳይጀመርና መስቀል አደባባይ ሳይደርሱ፣ ሁከትና ብጥብጥ ልታስነሱ ነው ተብለው የታሰሩ ሲሆን ሕወሀት ኢህአዲግ እንደሚለው በሰልፉ ላይ ያልነበሩት አባላቶቻችንም እንዲሁም ሰልፉ ካበቃ በኋላ እየታደኑ ተይዘው ታስረዋል፡፡ ይህን ያደረገው የራሱን አባላት ከቀበሌ ደብዳቤ እያስመጣ በፈታበት ወቅት ሲሆን በቦታው ያልነበሩትን አባላቶቻችንን በማሰር የፈጠራ ክስ በመክሰስ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም በፌደራል ፖሊስ አማካኝነት ተደጋጋሚ የስም ማጥፋት ዘመቻ በፓርቲያችን ላይ እያደረሰ ይገኛል፡፡
ትናንት ሚያዝያ 18/ 2007 ዓም ምሽት 2 ሰዓት ዜና ላይ የፌደራል ፖሊስ 7 የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን እና ከ20 በላይ አባላትን ማሰሩን በማስመልከት ፈፅሞ ከእውነት የራቀ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በእስር ላይ የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ቁጥር 6 ብቻ ሲሆን እነዚህ በእስር ላይ የሚገኙ የፓርቲው አባላት እንደማንኛውም ዜጋ ሀዘናቸውን ለመግለፅ ወደ መስቀል አደባባይ በማቅናት በነበሩበት ወቅት ሰልፉ የሚካሄድበት ቦታ እንኳን ሳይደርሱ በደህንነቶች አባላት ታፍነው የታሰሩ ናቸው፡፡ ሰልፉ ከመጀመሩ ከሰዓታት በፊት የታሰሩ የሰማያዊ አባላትን በሰልፉ ላይ ለተፈጠሩት ማንኛውም ድርጊቶች ተጠያቂ ማድረግም በእጅጉ መሰረተቢስ ነው፡፡
ይህ በህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት አማካኝነት እየቀረበ ያለው ክስ እና የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ህወሓት/ኢህአዴግ ለዜጎች ህይወት የማይጨነቅ እና በዜጎች ሞት የራሱን የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ እና ጠንካራ ተቃዋሚ የሆነውን ሰማያዊ ፓርቲን ለማጥቃት እየተጠቀመበት መሆኑን በተጨባጭ የሚያሳይ ነው፡፡ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያልተሰጠበትን ጉዳይ ተጠርጣሪ ከማለት ይልቅ ወንጀለኞች ናቸው በማለት በህገወጥ ስራ ላይ ተሰማርቶም ይገኛል፡፡
ይህ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በዋነኝነት ያነጣጠረው
1- ሰማያዊ ፓርቲን ከምርጫ ለማስወጣት እና ምርጫ 2007ን ያለምንም ተቀናቃኝ እና ስጋት ለማለፍ
2- ያለይሉኝታ እና ያለ ሀፍረት የፓርቲ እና የመንግስት ስልጣንን አቀላቅሎ የያዘው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጁ 662/2002ን በሚቃረን መልኩ ያሉትን የመገናኛ ብዙሀንን በሙሉ ተቀናቃኞቹን እና ተፎካካሪዎቹን ለማጥቂያነት እየተጠቀመባቸው መሆኑን ለማድበስበስ
3- ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ህወሓት/ኢህአዴግ እንዳደረገው ሁሉ አሁንም የሰማያዊ አመራሮችን እና አባላትን በማሰር ትግሉን ለማዳከም የተወጠነ ሴራ መሆኑን፡፡
4- በተለይም በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ ሚዲያዎች በሊቢያ እና በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ህይወት አደጋ ውስጥ እንዳለ እየተገለፀ በሚገኝበት ወቅት እና የኢትዮጵያ ህዝብም በአንድ ድምፅ መንግስት የዜጎችን ደህንነት እንዲያስጠብቅ እና በአይ ኤስ አይ ኤስ ላይ የአፀፋ እርምጃ እንዲወስድ እየወተወተ ባለበት ወቅት የህዝብን መሰረታዊ ጥያቄ ለማስረሳት እና ለማዘናጋት የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በኢትዮጵያውን ላይ የጭካኔ ድርጊት የፈፀመውን አይ ኤስ አይ ኤስን ወደጎን በመተው ሰማያዊ ፓርቲን የጥቃቱ ዋና አላማ አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡
ስለዚህ ሰማያዊ ፓርቲ መንግስት እና የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ከዚህ አኩይ ተግባራቸው የማይታቀቡ ከሆነ ፣የሰማያዊን ስም በሀሰት በማጠልሸት ስራ ላይ የተሰማሩ የመንግስት ተቋማትን እና ግለሰቦችን በህግ ፊት ለማቆም ዝግጅቱን ያጠናቀቀ መሆኑን እየገለፀ ሌሎች ተከታታይነት ያላቸውን እርምጃዎችም ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን እያስታወቀ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሰማያዊ ፓርቲ ለሚያደርጋቸው ህዝባዊ ጥሪዎች በንቃት ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ሚያዝያ 19/2007 ዓም
አዲስ አበባ988529_1584502611820936_8721941900200532873_n
11169883_1584502648487599_4615036497156649806_n

No comments:

Post a Comment